የመንፈሳዊ ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት የአገልግሎት ፈቃድ ታገደ

 • ‹‹ዕውቅናችን ሕጋዊ ነው፤ ቅሬታችን በአግባቡ አልተስተናገደም፡፡›› /የኅብረቱ አመራሮች/
 • በየሀገረ ስብከቱ ለተበራከቱት ማኅበራት መመሪያ እንዲዘጋጅላቸው ተጠይቋል

(ኢትዮ-ምኅዳር፤ ቅፅ ፪ ቁጥር ፸፪፤ ረቡዕ፣ ሰኔ ፲፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)

YeTimket Lijoch BeSera Lay

ዉሉደ ጥምቀት በሥራ ላይ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የተደራጀው ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት›› የአገልግሎት ፈቃድ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ መታገዱ ተገለጸ፡፡ የእግድ ውሳኔው ለኹሉም ማኅበራት በማዕከል ተዘጋጅቶ የጸደቀ ቋሚ ደንብ አለመኖሩን መነሻ በማድረግ የተላለፈ መኾኑ ተጠቅሷል፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ፊርማ ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ባለፈው ግንቦት ወር የተላለፈው የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ፣ ‹‹ለመንፈሳውያን ማኅበራት በወጥነት የሚያገለግል ደንብ እስኪወጣ ድረስ›› ለማኅበራት ኅብረቱ በጥር ወር 2006 ዓ.ም. የተሰጠው የአገልግሎት ዕውቅና የታገደ መኾኑን አስታውቋል፡፡

በመላ ሀገሪቱ ራሳቸውን አደራጅተው የሚንቀሳቀሱ የመንፈሳዊ ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ከ86‚000 በላይ መድረሳቸውን በሪፖርቱ የሚጠቅሰው የመንበረ ፓትርያርኩ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ፣ የማኅበራቱ እንቅሰቃሴ ‹‹ወሰን የለሽ›› ነው፤ ዓላማቸውም ‹‹ወጣቱን በማደራጀት ሳይሆን በመከፋፈል የራሳቸውን ፍላጎት ማሟላት ነው፤›› በማለት ሲከሳቸው ቆይቷል፡፡ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያኒቱ የሚደራጁበት ሕጋዊና ዕውቅና ያለው የአገልግሎት መዋቅር የሰንበት ት/ቤት እንደኾነ የተገለጸ ሲኾን በእግዱ ደብዳቤ ላይም ይኸው መመልከቱ ተገልጧል፡፡

ከ200‚000 በላይ ወጣቶችንና ጎልማሶችን ያቀፉት የ85 አጥቢያዊ ማኅበራት ኅብረቱ አመራሮች በበኩላቸው፣ ዕውቅና በተሰጣቸው በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ የተላለፈባቸውን እግድ አግባብነት ለመጠየቅ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም ‹‹አትሳለሙ፤ አታስቀድሱ፤ አትቁረቡ ያላችኹ የለም፤ የእናንተ ድርሻ ይኸው ነው፤›› ከሚል ምላሽ በቀር በምንጠብቀው አባታዊና መንፈሳዊ መንገድ አልተስተናገድንም፤ ‹‹ብታነጥፉ ባታነጥፉ ለእኔ ጉዳዬ አይደለም፤ እንኳን 200‚000 ለምን አንድ ሚልዮን አትኾኑም!›› የሚል ኃይለ ቃል መስማታቸው ያልጠበቁትና በእጅጉ ያሳዘናቸው መኾኑን ተናግረዋል፡፡

YeTimket Lijoch

ዉሉደ ጥምቀት በአገልግሎት ላይ

የዕውቅናቸው መሠረት፣ በፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለቅዱስነታቸው ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በሐምሌ ወር 2005 ዓ.ም. የተሰጠው መመሪያ መኾኑን አመራሮቹ አውስተዋል፤ በመመሪያው መሠረት በጥር ወር 2006 ዓ.ም. በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በተጻፈ ደብዳቤ የአገልግሎት ፈቃድ ማግኘታቸውን በመግለጽ ‹‹ድንገተኛና ቀርበን ያልተጠየቅንበት ነው›› ባሉት የእግድ ውሳኔ ላይ ፓትርያርኩን አግኝተው ለማነጋገር ቢሞክሩም ‹‹ለመግባት አልቻልንም›› ብለዋል፡፡

ዕውቅናውና የፈቃድ አሰጣጡ በሌሎች አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ለመንፈሳውያን ማኅበራት አገልግሎት ዕውቅና ከሚሰጡበት ሥርዓት ያልተለየና በዚኹ መንገድ ዕውቅና ያላቸው ሌሎች የጉዞና የበጎ አድራጎት ማኅበራት በአገልግሎት ላይ በሚገኙበት ኹኔታ በማኅበራት ኅብረቱ ላይ የእግድ ውሳኔው የተላለፈበት መነሻ ግር አሰኝቶናል ብለዋል – አመራሮቹ፡፡

ተጠሪነቱ ለአ/አበባ ሀ/ስብከት የኾነው የወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረቱ የሚመራበት ባለ17 አንቀጽ መተዳደርያ ደንብ÷ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች ከቀድሞው ፓትርያርክ በተላለፈ መመሪያ መሠረት ጥናታዊ ቅድመ ዝግጅት ያደረጉበትና በስብከተ ወንጌል፣ በበጎ አድራጎትና በልማት ተግባራት ላይ የሚያተኩር እንደኾነ ያስረዱት አመራሮቹ፣ በማደራጃ መምሪያው አንዳንድ ሓላፊዎች የተዘረዘሩት ችግሮች በኅብረቱ የታቀፉትን ማኅበራት እንደማይገልጻቸው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የኅብረቱ ምሥረታ መነሻም በ2000 ዓ.ም. በተከበረው የጥምቀት በዓል÷ ባንዴራ በማውጣት፣ ቄጤማ በመጎዝጎዝና ምንጣፍ በማንጠፍ ሥነ በዓሉን በማድመቅ ‹‹ለእናት ቤተ ክርስቲያን በተሰጠን ጸጋ መጠን የጀመርነው አገልግሎት የክሕደትና ኑፋቄ ወረርሽኝን የሚያስፋፉ መሰል ማኅበራትን በማጋለጥና በመከላከል በተሻለ መልኩ እንዲጠናከር›› በማሰብ የተቋቋመ መኾኑን አስረድተዋል፡፡

በጥቅምት ወር 2002 ዓ.ም. የተመሠረተው የማኅበራት ኅብረቱ፡-

 • ኹሉም አባል ማኅበራት በየአጥቢያቸው በአባቶች ካህናት የበላይ ጠባቂነት ክብካቤና ክትትል እንዲደረግላቸው
 • የኅብረቱ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የንኡሳን ክፍሎች ሓላፊዎችና አባል ማኅበራት ማንኛውንም የፖሊቲካ አጀንዳ ከማስፈጸም፣ ከማይታወቁ ማኅበራት ጋራ ኅቡእ ግንኙነት ከማድረግና ከብልሹ ምግባራት መጠበቃቸውንና መከልከላቸውን የማረጋገጥ፣፤
 • የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት በመፃረር በሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን የሚካሔዱ አጥቢያዊ መርሐ ግብሮችንና ፈቃድ የሌላቸው አካላት በርዳታ ስም ግላዊ ጥቅም የሚያካብቱባቸውን ሕገ ወጥ ልመናዎችን በአባል ማኅበራቱ አማካይነት በጥብቅ የመቆጣጠር
 • በየአጥቢያው ስብከተ ወንጌልን የማጠናከርና ለመንጋ ቅሰጣ በተጋለጡ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎቱን የማስፋፋት፣
 • ወጣቶችና ጎልማሶች ከሱስ የራቁ፣ በምግባር የተለወጡና በአቅም ራሳቸውን የቻሉ በማድረግ የአገልግሎት ተሳትፏቸውን የማጠናከር፣
 • አጥቢያዎች በወጣቱ ሞያና ጉልበት ችግሮቻቸው እንዲቀረፍ የማገዝ፣ በየወኅኒውና በየጠበል ሥፍራው የወደቁ ሕሙማንን፣ አሳዳጊ አልባ ሕፃናትንና ጧሪ አልባ አረጋውያንን የመርዳትና የወንጌል አገልግሎት የመስጠት፣
 • ወደ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት መንፈሳዊ ጉዞዎችን በተቀናጀ አኳኋን የማካሔድ፣
 • ማኅበራት በያሉበት አድባራትና ገዳማት መንፈሳዊ በዓላት ባማረና በደመቀ ኹኔታ እንዲከበሩ የማድረግ ዝርዝር ዓላማዎች እንዳሉት ከመተዳደርያ ደንቡ ለመረዳት ተችሏል፡፡
SSD Gen Assembly deliberating

ሦስተኛው ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ በመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት አዳራሽ

በተያያዘ ዜና፣ ግንቦት 30 እና ሰኔ አንድ ቀን ለሦስተኛ ጊዜ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ የመምሪያው የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት የተካሔደው ሀገር አቀፉ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ባለ15 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡

ጠቅላላ ጉባኤው በመግለጫው፣ በየሀገረ ስብከቱ የመንፈሳውን ማኅበራት መበራከት ለሰንበት ት/ቤቶች ጫናና ዕንቅፋት መፍጠሩን ገልጾ በሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት ትኩረት ተሰጥቶ መመሪያ እንዲዘጋጅላቸው፣ ከአጥቢያ አስተዳዳሪዎችና ሰበካ ጉባኤያት ጋራ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ለፖሊስና ለጸጥታ አካላት በሚቀርብ የክሥና አቤቱታ ጋጋታ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያኒቱ በራሷ የሚፈታበት አቅምና አሠራር እንዲኖር ጠይቋል፤ ልዩነትን በማስወገድና የተደራጀ አንድነትን በመጎናጸፍ ከአባቶች ጋራ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገትና ልዕልና እንደሚሠራ ጠቅላላ ጉባኤው በመግለጫው አስፍሯል፡፡

SSA Gen Assembly 2006በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ቃለ ዐዋዲ እና በ1986 ዓ.ም. ሕገ ደንብ የተጠቀሰው የሰንበት ት/ቤቶች አባላት የዕድሜ ገደብ እንዲነሣም በመግለጫው ተጠይቋል፡፡ ቃለ ዐዋዲውና ሕገ ደንቡ እንደሚደነግገው፣ ዕድሜያቸው ከ4-30 የኾኑት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕፃናትና ወጣቶች በአጥቢያቸው የሚደራጁትና የሚያገልግሉት በሰንበት ት/ቤቶች ነው፡፡ ‹‹መዋቅሩ ከነስሙ ት/ቤት ነው፤ ገደቡም አባላቱ በዕውቀትና ልምድ የሚበስሉበትንና የተሻለ አገልግሎት የሚያበረክቱበትን የዕድሜ ክልል አያካትትም፤›› በሚል የቀረበው የማሻሻያ ጥያቄ ለአራተኛ ጊዜ በመጠናት ላይ በሚገኘው ቃለ ዐዋዲ ተቀባይነት ካገኘ ሰንበት ት/ቤቶች ከ30 ዓመት በላይ ያሉ ጎልማሶችን በመደበኛ ኹኔታ ለማቀፍ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል፣ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ሰንበት ት/ቤቶች በግንቦት ወር 2004 ዓ.ም. በሃይማኖት ኑፋቄ ስለተጠረጠሩ ግለሰቦች ያቀረቡት የጥናት ሰነድ በቅ/ሲኖዶስ በኩል እንዲታይ ጠቅላላ ጉባኤው በመግለጫው ጠይቋል፤ በቀጣይም ከአዲስ አበባ ውጭ በየሀገረ ስብከቱ ቤተ ክርስቲያንን ከመናፍቃን ቅሰጣ ለመጠበቅና ማንነታቸውን ለማጋለጥ የሚያስችል ጥናት ለማድረግ የጉባኤው ተሳታፊ ሰንበት ት/ቤቶች ቃል መግባታቸውን ከመግለጫው ለመረዳት ተችሏል፡፡

Advertisements

3 thoughts on “የመንፈሳዊ ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት የአገልግሎት ፈቃድ ታገደ

 1. Getnet Mesfin June 17, 2014 at 12:43 pm Reply

  Keep up!

 2. Anonymous June 18, 2014 at 11:29 pm Reply

  I think it is better to leave Sunday schools for the age below 30 years old, may be a little higher. It may bring unintended consequences, like sextual harasment and the like. Look at the accusasions being labeled on the Vatican. Yeqotun awered bila yebibituan talechi. In general I’m not a fan of top down approach.

 3. Anonymous June 21, 2014 at 3:35 pm Reply

  Is there any plan to visit S. Sudan refugees in Ethiopia? This is something the church needs to orginize real quick. No preaching or teaching. Just feed and let them drink the hungry and thristy, kiss their chucks, wash their legs, sit, talk, laught and cry with them. Then, when their suffering subsides, they will remember the blessings they received in Jesus name. They really need an honest help, not politically motivated one. They suffered way too long.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: