የሰንበት ት/ቤቶች ሀገር አቀፍ አንድነት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ነገ ይጀመራል

 • ጠቅላላ ጉባኤው በየዓመቱ የሚካሔድበት በዓለ ጰራቅሊጦስ ‹‹የሰንበት ት/ቤቶች ቀን›› ነው
 • ሰንበት ት/ቤቶች ከአማሳኞች ጋራ የገቡበት ግጭትና አፈታቱ የጠቅላላ ጉባኤው ትኩረት ነው
 • ጥያቄያቸው በአግባቡና በወቅቱ ባለመፈታቱ ወጣቶች በየቦታው እየተንገላቱና እየታሰሩ ነው
 • ከ፳ ሚልዮን በላይ ጠቅላላ ወጣቶች በሰንበት ት/ቤቶች የታቀፉት ከ፬ ሚልዮን አይበልጡም
 • 60 ሺሕ ወጣቶች በ102 ማኅበራት የተደራጁበት የአ/አ ወጣቶች ማኅበራት ኅብረት ፈቃድ ታገደ

(ምንጭ፡- አፍሮ ታይምስ፤ ቅጽ ፩ ቁጥር ፳፤ ዓርብና ቅዳሜ፣ ግንቦት ፳፱ – ፴፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)

sunday_school

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ፣ ሦስተኛውን ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ከግንቦት ፴ – ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. እንደሚያካሒድ ተገለጸ፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ በየዓመቱ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ሰንበት የሚካሔደው ጠቅላላ ጉባኤው በመላ ሀገሪቱ የሚገኙት ሰንበት ት/ቤቶች፡-

 • የአገልግሎት ሥርዓታቸውን በወጥነት ለመምራት የሚያስችል መሪ ዕቅድ እንዲያወጡበትና ትግበራውን በአህጉረ ስብከት የአፈጻጸም ሪፖርቶች እንዲከታተሉበት፣
 • በዚኽም በጋራ ችግሮቻቸው ዙሪያ የተሞክሮና ልምድ ልውውጥ በማድረግ እርስ በርሳቸው መልካም ግንኙነትን እንዲያዳብሩበትና እንዲማማሩበት፣
 • በአጠቃላይ ሰንበት ት/ቤቶችን ከላይ እስከ ታች በማደራጀት በማደራጃ መምሪያው ተደራሽ የኾነ ሀገር አቀፍ አገልግሎት እንዲኖር በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ኹለገብ ተሳትፎ እንዲያሳድጉበት፣

ታስቦ ከ፳፻፬ ዓ.ም. ጀምሮ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ በወረዳ/ክፍላተ ከተሞች አብያተ ክህነት ጽ/ቤቶች እና በአህጉረ ስብከት ደረጃ በተቋቋሙ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መሠረትነት የተቋቋመ መኾኑ ተገልጧል፡፡

ለኹሉም ሰንበት ት/ቤቶች በሚበጁ የአገልግሎት ስልቶች፣ መሪ ዕቅዶች፣ መንፈሳዊና ሀገራዊ ፋይዳ በተላበሱ የልማት ሐሳቦችና ወጥ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ በማተኮር የሚያገለግለው ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ለኹለት ቀናት የሚመክርበትን የጠቅላላ ጉባኤ መርሐ ግብሩን የሚያከናውነው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ እንደኾነ ተጠቅሷል፡፡

በየዓመቱ በዓለ ጰራቅሊጦስ የሚውልበትን ሰንበት ‹‹የሰንበት ት/ቤቶች ቀን›› በማለት ሠይሞ በሚካሔደው ጠቅላላ ጉባኤ፣ የአዲስ አበባ 160 አድባራትና ገዳማት ሰንበት ት/ቤቶችን ሊቃነ መናብርትን ጨምሮ ከ36 አህጉረ ስብከት ከእያንዳንዳቸው አምስት አምስት ልኡካን (የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ የሰንበት ት/ቤት ክፍሎች ሓላፊዎች፣ ሦስት የየአህጉረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮች) በአጠቃላይ 500 ያህል ተሰብሳቢዎች በተወካይነት እንደሚሳተፉበት ታውቋል፡፡

ሀገር አቀፉ ጠቅላላ ጉባኤ በሥራ ላይ በሚውልባቸው ቀናት÷ ከማደራጃ መምሪያው እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ለአዳጊ ሕፃናትና ለወጣቶች ወጥና ኹለገብ አገልግሎት ለመስጠትና የሰንበት ት/ቤቶችን ትስስር በማጠናከር ዘመኑን ለመቅደም ያስችላል በተባለውና ጥቅምት ፲፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ በጸደቀው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ባለ39 አናቅጽ የውስጥ መመሪያ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት እንደሚያካሒድ ተጠቁሟል፡፡

በመምሪያው የአምስት ዓመት ስትራተጅያዊ ዕቅድ መሠረት የሕፃናት ትምህርት መማሪያና መዝሙር አገልግሎት በወጥነት ለማስፈጸም የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ያዘጋጀውና በሞዴልነት የተወሰደው ሰነድም ለውይይት ይቀርባል ተብሏል፡፡

በየአህጉረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች ያጋጠማቸውን ችግር በተመለከተ ጉባኤው የቡድን ውይይት የሚያደርግ ሲኾን ከዚኹ ጋራ በተያያዘ በተለይ በሰንበት ት/ቤቶችና በአማሳኝ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች መንሥኤና አፈታታቸው የጉባኤው ቀዳሚ ትኩረት እንደሚኾን ይጠበቃል፡፡

abune-qelemntos2

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊና የከምባታ ሐዲያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ያቀረበው የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያስረዳው፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ዕጦት የሰንበት ት/ቤቶች ዋነኛ ችግር ነው፡፡

ሪፖርቱ እንደሚያትተው፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በየቦታው እየተንገላቱና እየታሰሩ ናቸው፤ የሰንበት ት/ቤት የሥራ አመራር አባላት መብታቸው በሕግ አግባብ ሲጠይቁ ከአጥቢያ እስከ ሀገረ ስብከት ድረስ ያሉ ሓላፊዎች ችግራቸውን ተረድተው በአግባቡና በወቅቱ አይፈቱላቸውም፤ እንዲያውም በሙስና እና ብልሹ አሠራር የተዘፈቁ የደብር አለቆችና ጸሐፊዎች የላይ ፈሪ የታች ፈሪ እያሉ ‹‹የጽዋ ማኅበራትን በተጓዳኝ እያደራጁባቸው ነው፡፡››

የችግሮቹ መፍትሔ ግልጽ የወጣቶች ርእይና ስትራተጂ በማስቀመጥ የሰንበት ት/ቤቶችን አንድነት አደረጃጀት ከሀገር አቀፍ እስከ አጥቢያ ማጠናከር መኾኑን የሚያስቀምጠው ሪፖርቱ÷ አደረጃጀቱን ለመምራት የሚያስችል የውስጥ መመሪያ በቅ/ሲኖዶስ መጽደቁን፣ የ፳፻፮ እና የ፳፻፯ ዓ.ም. ዝርዝር የድርጊት መርሐ ግብር ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ በማውረድ እንዲሠራበት መደረጉን፣ የኹሉም የሰንበት ት/ቤቶች አደረጃጀቶች እንቅስቃሴ በማእከል ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገበት መኾኑንም ዘርዝሯል፡፡

ሪፖርቱ አክሎም፣ ለማደራጃ መምሪያው የሚፈቀደው የበጀት መጠን መምሪያው በዓመታዊ ዕቅድ ደግፎ ከሚያቀርበው የበጀት ጥያቄ ጋራ አለመመጣጠኑ፣ መመሪያው በሀገር አቀፍ ደረጃ ያወጣውን የሥልጠናና ግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር ለማጠፍ እንዳስገደደው፣ የሥርዓተ ትምህርትና የመዝሙር መጻሕፍትን በወቅቱ ለማሳተምም እንዳዳገተው አስታውቋል፡፡

ሌሎች የመምሪያው ምንጮች በበኩላቸው፣ የበጀት እጥረት ለተጠቀሱት ችግሮች በመንሥኤነት መጠቀሳቸውን ቢቀበሉትም ከዐሥርት ዓመታት በላይ በማደራጃ መምሪያው በሓላፊነት የቆዩት ዋና ሓላፊ መ/ር ዕንቊ ባሕርይ ተከሥተ የአመራር ብቃት እንዲሁም ክፉኛ የተጠናወታቸው የአግላይነትና ጠቅላይነት አባዜ ተያይዞ ሊታይ እንደሚገባው ያሳስባሉ፡፡

EOTC SSGAssembly

የሰንበት ት/ቤቶች ሀገር አቀፍ አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ (ፎቶ ፳፻፬ ዓ.ም.)

ምንጮቹ እንደሚገልጹት፣ ዋና ሓላፊው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶችን በማደራጀትና በማስተባበር ለመምራት ያላቸው ብቃት የዘመኑ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች የደረሱበትን ንቃትና የአገልግሎት ዝግጁነት የሚመጥን አይደለም፤ በጽኑ አቋማቸውና ክሂላቸው የሚታወቁ የሰንበት ት/ቤት አባላትን ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ናችኹ›› በሚል እየፈረጁ ለማሸማቀቅና ለመከፋፈል ይሞክራሉ፤ ‹‹የማኅበሩ አባላትምኮ ወንድሞቻችን ናቸው፤›› የሚል ምላሽ ከሰጧቸውም ውሰጥ በጠቅላላ ጉባኤ እንዳይሳተፉ እስከማገድና እስከማዋከብ ደርሰዋል፡፡

ከነገ ጀምሮ በሚካሔደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንኳ አህጉረ ስብከት የሚያቀርቧቸውን ሪፖርቶች ኹሉ እኔ ካላቀረብኹ በሚል ከአዘጋጅ ኮሚቴው ጋራ ግጭት ውስጥ የገቡት ዋና ሓላፊው፣ ለመምሪያውና ለሰንበት ት/ቤቶች መራራቅ መንሥኤ መኾናቸውን ምንጮቹ በምሬት ይናገራሉ፤ ሰንበት ት/ቤቶችና የአንድነት አመራሮች ከዋና ሓላፊው መ/ር ዕንቊ ባሕርይ ጋራ ስምምነት በማጣታቸው ከመምሪያው የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ጋራ እጅና ጓንት ኾነው በመሥራት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

በአኹኑ ወቅት ከመምሪያው ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ ጋራ የተጠናከረ መልካም ግንኙነት እንዳለ የሚያስረዱት ምንጮቹ÷ መምሪያው ከፍተኛ የበጀት እጥረት እንዳለበት በተገለጸበት ኹኔታ ለጉባኤ ዝግጅት የተጠቀመበት የሰንበት ት/ቤቶች የገንዘብ አስተዋፅኦ ሒሳብ ሪፖርት በዋና ሓላፊው አለመቅረቡን፣ ፹፩ዱ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰንበት ት/ቤቶች ለማሰራጨት ታቅዶ የተሰበሰበው ገንዘብ ስርጭቱ ሳይከናወን በመቅረቱ የደረሰበት እንደማይታወቅ በመጥቀስ በዋና ሓላፊው ላይ ሌላም ብርቱ ጥያቄ እንዳላቸው አልሸሸጉም፡፡

ዘንድሮ የማደራጃ መምሪያው ለኹለት ቀናት ለሚያካሒደው ጠቅላላ ጉባኤ የሚያስፈልገው 106 ሺሕ ብር ወጪ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት 160 ሰንበት ት/ቤቶች እያንዳንዳቸው በተጣለባቸው ድርሻ መጠን ባደረጉት አስተዋፅኦ መሸፈኑና እንዲሁም በማኅበረ ቅዱሳን የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉ ታውቋል፡፡

በአኹኑ ወቅት ከጠቅላላው የሀገሪቱ ሕዝብ ከኃምሳ ሚልዮን በላይ መድረሱ በተነገረው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ምእመን ውስጥ ኻያ ሚልዮን ያህሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ 37‚332 አብያተ ክርስቲያናት እንዳሉ የማደራጃ መመሪያው የመጋቢት ወር የዕቅድ ክንውን ሪፖርት የሚጠቅስ ሲኾን ሰንበት ት/ቤቶች የተቋቋሙባቸው አጥቢያዎች ብዛት 8610 ብቻ መኾናቸውን ያመለክታል፡፡ በሰንበት ት/ቤቶቹ የታቀፉት ወጣቶች ቁጥር በሪፖርቱ ኹለት ሚልዮን(2‚710‚253) እንደኾኑ ቢጠቀስም ሌሎች መረጃዎች እስከ ከአራት ሚልዮን ሊደርሱ እንደሚችሉ ነው የሚገልጹት፡፡

***

በኹሉም አብያተ ክርስቲያናት ሰንበት ት/ቤቶች እንዲቋቋሙ የተቋቋትም እንዲጠናከሩ በ፲፱፻፸ ዓ.ም. በተሻሻለው ቃለ ዐዋዲ ከታዘዘበት ወዲህና ከታሪክም አኳያ ከስድሳ ዓመታት ያላነሰ የሰንበት ት/ቤቶች አገልግሎት ልምድ አለን በሚባልበት ኹኔታ በማደራጃ መምሪያው የተጠቀሱት የሰንበት ት/ቤቶች አኃዝና የታቀፉባቸው ወጣቶች ቁጥር ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብን ሪፖርቱ በግልጽ ያስጠነቅቃል፡፡ በአኹኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በማዕበል እንደተከበበች መርከብ መኾኗን የሚያስገነዝበው ሪፖርቱ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ማዕበሉን ማለፍ የምትችለው ዘመኑን መቅደም በሚችሉ ልጆቿ መኾኑን›› ያስገነዝባል፡፡

በርግጥም ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው ዘመኑን የሚዋጅ ተተኪ ትውልድ ያስፈልጋታል፤ ሊቀ ትጉኃን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኜ በአንድ ወቅት እንደተናገረው፣ ‹‹ወጣት የሌላት ቤተ ክርስቲያን ከሥሩ እንደተቆረጠች ዛፍ ናት፡፡›› ወጣቶች ተተኪነት፣ ተጨባጭና ቀጣይነት ያለው እንዲኾን ከማስቻላቸውም ባሻገር የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲፋጠንና የቤተ ክርስቲያን አንድነትና ማንነቷ ተጠብቆ እንዲቆይ ያደርጋሉ፤ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያንን ጥቃት በመከላከልና ሞያቸውን ለቤተ ክርስቲያናቸው የማበርከት ድርሻም አላቸው፡፡

ይኹንና÷ የመንፈሳዊነት እጥረት፣ የኢኮኖሚ ችግርና ከሥራ አጥነት ጋራ ተያይዞ ለሱስ ተጋላጭ መኾን፣ ጊዜን በአላስፈላጊ ነገሮች ማሳለፍ፣ በሃይማኖት መቀሰጥና ስደት፣ የሉላዊነት አስተሳሰቦችንና ለውጦችን ለማስተናገድ የሚደረገው ዝግጅት አናሳነት የወጣቱ መሰናክሎችና ተግዳሮቶች እንደኾኑ በሀገር አቀፍ አንድነት ጉባኤው ላይ የቀረቡ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

መፍትሔውም ከቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ ከልማት ሥራዎችና ከምእመናን እንደሚመነጭ ያስቀምጣል፡፡ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ረገድ የሰንበት ት/ቤት አሠራር በሥርዓተ ማኅበር፣ በሥርዓተ ትምህርትና በሥርዓተ ተልእኮ ዘመኑን እንዲዋጅ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ የልማት ሥራዎችን በማሳደግ ወጣቱ ለራሱና ለቤተ ክርስቲያኑ ምርታማ እንዲኾን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በየዘመኑ ለሚነሡት የተሳሳቱ ትምህርቶችና አስተሳሰቦች በቂ ምላሽ መስጠት የሚችሉ መንፈሳዊ ኮሌጆችንና ሊቃውንትን ማጠናከር ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ ምእመናን ልጆቻቸውን ወደ ሰንበት ት/ቤት መላክ እንዲማሩና ሰንበት ት/ቤቶች እንዲጠናከሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይገባል፡፡

***

በተያያዘ ዜና፣ ከ60 ሺሕ በላይ የአዲስ አበባ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች በ102 ማኅበራት በመታቀፍ በአንድነት የተደራጁበት የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበራት ኅብረት የአገልግሎት ፈቃድ በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔና ውሳኔውን መሠረት አድርጎ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በተጻፈ ደብዳቤ መታገዱ ተገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በኩል በየካቲት ወር የአገልግሎት ደንብ ጸድቆለትና ዕውቅና ተሰጥቶት መንቀሳቀስ የጀመረው የኅብረቱ ፈቃድ የታገደው፣ ‹‹ለማኅበራት ደንብ አልተዘጋጀም፤ ለማኅበራት ኹሉ ወጥ ደንብ ባልተዘጋጀበትና ባልጸደቀበት ኹኔታ የተሰጠ ነው፤›› በሚል እንደኾነ ተዘግቧል፡፡

መንፈሳውያን ማኅበራት በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸውና በጉልበታቸው ለቤተ ክርስቲያን የሚያበረክቱት ትውፊታዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚታመንበትና አስፈላጊነቱ የማያጠያይቅ ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሦስተኛ ዙር የሚደረገውን ጠቅላላ ጉባኤ በአፍሪቃ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ አህጉር ባሉን አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች የአንድነት ጉባኤያትን መሥርቶ ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ እየታሰበ፣ በአንድ ወቅት በኾነው መንገድ የተሰበሰበውና በጎ አስተዋፅኦው የተረጋገጠው አካል ሳይበተን ከሰንበት ት/ቤቶች ጋራ የጀመረውን መልካም ግንኙነት አጠናክሮ በተገቢው አሠራርና ቁጥጥር በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር የሚጠበቅበት ሥርዓት ቢበጅለት የተሻለ ይኾናል፡፡

ይህ ሊኾን የሚችልበት መንገድ እንዳለ ቢታወቅም ‹‹በቁጥር ይህን ያህል ደርሰዋል፤ ከአጥቢያ እስከ ላዕላይ መዋቅር፣ ከወጣቱ እስከ መድረኩ ያለውን አገልግሎት ለመቆጣጠር እየሠሩ ናቸው፤›› የሚለው ክሥና ‹‹የፖሊቲካ መድረክና የፖሊቲካ ዓላማዎች ማስፈጸሚያ ሊኾኑ ይችላሉ፤›› በሚል የሚቀርብባቸው ውጫዊ ስጋት በኅብረቱ ላይ ለተላለፈው እግድ በምክንያት ተጠቅሷል፡፡

Advertisements

5 thoughts on “የሰንበት ት/ቤቶች ሀገር አቀፍ አንድነት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ነገ ይጀመራል

 1. gishabay2003 June 6, 2014 at 11:10 am Reply

  i am proud to our young ,orthodox tewahehido associations i am always
  on the side of you to involve and support! God bless our association
  amen!

 2. M.E June 6, 2014 at 3:03 pm Reply

  ወጣቱ ይህንን የታድሶዎች ሴራ ይበጣጥሳል!!!!

 3. Anonymous June 6, 2014 at 7:27 pm Reply

  The dream of our beloved Father (Aba) Serekebrhan is really come true. may God Bless you our father .And we love you all members of the Sunday School and may the Holy Spirit gives you all the gift of wisdom and understanding. this is time to stand all together in order to protect our Church. so lets be united all of us to bring the new generation unto light. do not fight each other about any association but we have to fight against the enemies of our church.

 4. weg June 7, 2014 at 1:52 pm Reply

  MK new yeemiaderajachew teblo endayletefbet bicha. Bechem yezendro gud malekia yelew.

 5. zeradawit June 7, 2014 at 8:14 pm Reply

  sereke means ye chikunu RESSA new andim senbet temari yemiwedew yelem. enkuan mewded kuakkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkk

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: