ለፓትርያርኩ እንደራሴ እንደሚመደብ የሚገልጽ የሕግ ረቂቅ ለውይይት ቀረበ

 • ‹‹የፓትርያርኩን ሥልጣን ይገድባል›› በሚል ተተችቷል
 • ‹‹አመራራቸውን በብቃት እንዲያከናውኑ የሚያግዝ ነው›› /የሕግ ረቂቁ/
 • ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሚያስተላልፉት በብሔራዊ ቋንቋ ብቻ ይኾናል

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፫ ቁጥር ፯፻፵፰፤ ግንቦት ፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)

His Holiness Abune Mathias with thier Graces the Archbishopsየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ ፓትርያርኩ የተጣለባቸውን አባታዊ ሓላፊነትና መንፈሳዊ አመራር በሚጠበቀው ብቃትና ደረጃ ለማከናወን እንዲችሉ የሚያግዝ እንደራሴ እንደሚመደብ በሚገልጽና የፓትርያርኩን ሓላፊነትና ተጠያቂነት በጉልሕ የሚያሳዩ አንቀጾችን ባካተተ የሕገ ቤተ ክርስቲያን ረቂቅ ላይ እየተወያየ እንደኾነ ተገለጸ፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ በ1991 ዓ.ም. ያወጣችውንና ስትገለገልበት የቆየችውን ሕግ ከሌሎች ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ጋራ በማጣጣም፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕድገትና ልማት እንዲሁም ከነባራዊ ኹኔታዎች ጋራ በማገናዘብ ያሻሽላል የተባለው የሕግ ረቂቅ ለውይይት የቀረበው ቅዱስ ሲኖዶሱ የትንሣኤ በዓል በዋለ በኻያ አምስተኛው ቀን በሚያደርገውና ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በመካሔድ ላይ በሚገኘው ኹለተኛ ዓመታዊ መደበኛ የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ነው፡፡

patriarch Ab Mathiasከምልዓተ ጉባኤው ኻያ ሦስት የመነጋገርያ አጀንዳዎች መካከል በግንባር ቀደምነት የቀረበውና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጎች፣ ደንቦችና ልማዳዊ አሠራሮች ኹሉ ይገዛል የተባለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቁ÷ ርእሰ አበውና ለካህናቷና ለምእመናንዋ ኹሉ መንፈሳዊ አባት በመኾን በማናቸውም ጉዳዮች ቤተ ክርስቲያኒቱን የመወከል ሥልጣን እንዳላቸው በሕጉ ለተገለጸው ለፓትርያርኩ እንደራሴ እንደሚሾም በአንቀጽ 24 ላይ ማስፈሩ ተመልክቷል፡፡

ለፓትርያርኩ እንደራሴ የመመደብ አስፈላጊነት፣ ‹‹ቅዱስ ፓትርያርኩ ከቤተ ክርስቲያን የተጣለበትን ሓላፊነትና መንፈሳዊ አመራር በሚጠበቀው ብቃትና ደረጃ ለማከናወን እንዲችል የሚያግዝ›› መኾኑን በሕግ ማሻሻያ ረቂቁ ተገልጧል፡፡ እንደራሴው የሚመደበው የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ብቻ በሚሳተፉበት ምርጫ ሲኾን ለምርጫው ሦስት ዕጩዎች በፓትርያርኩ እና ወይም በቅ/ሲኖዶሱ አባላት ጥቆማ ተለይተው እንደሚመረጡ፣ የሚመረጠውም አንድ አባት በቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔ በእንደራሴነት እንደሚመደብ ተጠቅሷል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖት፣ ቀኖናና ትውፊት የመጠበቅና የማስጠበቅ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያለአድልዎ የማስተዳደር ሓላፊነት ላለባቸው ለፓትርያርኩ በእንደራሴነት የሚመረጠው ሊቀ ጳጳስ በአባትነት የሚመራው ሀገረ ስብከት ወይም በማእከል የሚገኝ የሥራ ሓላፊነት ያለው ቢኾንም በሕጉ የተመለከተውን መመዘኛ ማሟላት እንደሚገባው ተገልጧል፤ መመዘኛው ከ50 – 60 ዓመት የዕድሜ ገደብ የሚያስቀምጥ ሲኾን የአስተዳደር ችሎታና የመንፈሳዊ አመራር ልምድን፣ መንፈሳዊና ዘመናዊ ዕውቀት አጣምሮ መያዝን እንደሚጠይቅ ተዘርዝሯል፡፡

አንቀጹ ‹‹ግለሰባዊ የሥልጣን ፈላጊነት ስሜት የሚገንበት፣ የፓትርያርኩን ሥልጣን የሚጋፋና መካሠስን የሚያበረታታ ነው›› በሚል የሕግ ማሻሻያ ረቂቁን የተቃወሙ የቤተ ክህነት ሓላፊዎች፣ ምደባው አስፈላጊ ኾኖ ከተገኘም እንደራሴው በፓትርያርኩ ጥቆማ ብቻ መመረጥ እንዳለበት የቃሉ ትርጉም እንደሚያስገደድ በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡

የአህጉረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎች በአንጻሩ፥ የእንደራሴው ምደባ፣ ፓትርያርኩ በርእሰ ጉባኤነት የሚመሩትን የቅዱስ ሲኖዶሱን አካላትና የሥራ ክፍሎች በማቀናጀት በአዲስ መልክ ለማቋቋም በሌሎች አንቀጾች ከቀረቡት የረቂቁ ሐሳቦች ጋራ ተዳምሮ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና ብልሹ አሠራር እንዲታረም የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት በማድረግ ላይ ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አመራር መጠናከር የራሱ አስተዋፅኦ ያለው በመኾኑ እንደሚደግፉት መግለጻቸው ተነግሯል፡፡

ከሥልጣን አኳያም እንደራሴው ቅዱስ ፓትርያርኩን በዕለት ተዕለት ሥራውና በመንፈሳዊ አገልግሎቱ ከማገዝ ውጭ ‹‹ለቅዱስ ፓትርያርኩ ከተሰጡት ተግባራት ውስጥ የሚጋራው የተለየ ሓላፊነት አይኖረውም፤›› በሚል በረቂቁ የሰፈረውን አንቀጽ በመጥቀስ ፓትርያርኩን የመደገፍ እንጂ የመጋፋት ሚና እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

ተጠያቂነትን በተመለከተም ፓትርያርኩን ጨምሮ ኹሉንም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት፡-

 • ቤተ ክርስቲያኒቱን በበላይነት ለሚመራውና ለሚጠብቀው እንዲኹም ቤተ ክርስቲያኒቱን በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ላለው ቅዱስ ሲኖዶስ ተጠሪ በማድረግ፣
 • በሕይወት ባሉበት ጊዜ ኹሉ ቋሚ ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረትና ሌላም የገንዘብ ማስገኛ ምንጭ እንዳይኖራቸው፣ በስጦታም ኾነ በውርስ የሚያገኙት ሀብት በሞት በሚለዩበት ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ንብረት እንደሚኾንና በስጦታም ኾነ በውርስ ለሦስተኛ ወገን እንደማይተላለፍ በማረጋገጥ
 • እያንዳንዳቸው በተሾሙበት ቀን የፈጸሙትን የመሐላ ቃል አፍርሰው ሃይማኖትን ቢያፋልሱ፣ ቀኖና ጥሰው ቤተ ክርስቲያኒቱን ቢያስነቅፉ፣ በአስተዳደር በደልና በአመራር ጉድለት የካህናቱንና የምእመናኑን አመኔታና ተቀባይነት ቢያጡ በማስረጃ ተደግፎ በሚቀርብ ክሥና ቅሬታ የሚጠየቁበት፣ ለመታረም ፈቃደኛ ካልኾኑም ከሓላፊነታቸው የሚገለሉበት ሥርዓት በረቂቁ በመካተቱ፣ በፓትርያርኩ አልያም በወቅታዊ እይታ ላይ ብቻ የታጠረ ረቂቅ እንዳልኾነ ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡

ጉዳዩ በዋናነት የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ አመራር በማጠናከር ልዕልናዋንና ክብሯን፣ አንድነቷንና ሥርዓቷን ከማስጠበቅ አንጻር ሊታይ ይገባል የሚሉት የሥራ ሓላፊዎቹ፡- ምልዓተ ጉባኤው የሕግ ማሻሻያ ረቂቁን በጥልቀት በማዳበር ከፍተኛው መንፈሳዊ፣ ሕግ አውጭና አስተዳደራዊ አካል የኾነው የቅዱስ ሲኖዶሱ ሉዓላዊ ሥልጣን በማንም የማይገሠስበት፣ ቤተ ክርስቲያኗ ዛሬም እንደቀድሞው ልዕልናዋና ክብሯ፣ አንድነቷና ሥርዓቷ የሚጠበቅበት፣ ሃይማኖታዊና ልማታዊ ሥራን በመሥራት የመሪነት ሚናዋን የምታጠናክርበት መሣርያ አድርጎ እንደሚያጸድቀው እንጠብቃለን ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ ፓትርያርኩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታላላቅ በዓላት ላይ እንዳስፈላጊነቱ እየተገኘ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሚሰጠው እንዲሁም በብዙኃን መገናኛ መንፈሳዊ መልእክት የሚያስተላልፈው በአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ብቻ እንደሚኾን በሕግ ማሻሻያ ረቂቁ ላይ መስፈሩ ተጠቅሷል፡፡

Advertisements

7 thoughts on “ለፓትርያርኩ እንደራሴ እንደሚመደብ የሚገልጽ የሕግ ረቂቅ ለውይይት ቀረበ

 1. Anonymous May 17, 2014 at 5:10 pm Reply

  …ቤተ ክርስቲያኗ ዛሬም እንደቀድሞው ልዕልናዋና ክብሯ፣ አንድነቷና ሥርዓቷ የሚጠበቅበት፣ ሃይማኖታዊና ልማታዊ ሥራን በመሥራት የመሪነት ሚናዋን የምታጠናክርበት መሣርያ አድርጎ እንደሚያጸድቀው እንጠብቃለን ብለዋል፡፡

 2. Anonymous May 17, 2014 at 8:18 pm Reply

  በእውነቱ ለቅዱስ ፓትርያርኩ እንደራሴ ሊሾም መታሰቡ ተቀባይነት ያለው ጉዳይ ነው
  ለእንደራሴነትም በመጀመሪያ ደረጃ ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ብጹዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሊሆኑ ይገባል፡፡

 3. beka May 18, 2014 at 4:18 am Reply

  “ምዕዳንና ቡራኬ የሚሰጠው እንዲሁም በብዙኃን መገናኛ መንፈሳዊ መልእክት የሚያስተላልፈው በአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ብቻ እንደሚኾን በሕግ ማሻሻያ ረቂቁ ላይ መስፈሩ ተጠቅሷል”
  እባካችሁ አሁንም ስለብሄራዊ ቋንቋ ታወራላችሁ? ኢትዮጵያ ውስጥ የስራ ቋንቋ እንጂ ብሄራዊ ቋንቋ የለም። አማርኛና ግዕዝ ላይ ሙጭጭ ብላችሁ ክርስትና እንዳይፋፋ ምክንያት አትሁኑ። ለኣማራ ብሄር በቀር ገጠር ለሚኖር ሌላው ኢትዮጵያዊ በማይሰማበት ቋንቋ መዕዳ ሌላም ሌላም ብትሉት እንዴት ሊረዳችሁ ነው። ምንም እንኳን የእምንቱ ተከታይ ብሆንም በዚህ ጉዳይ በጣም ነው ማዝነው። ኢትዮጵያን በኣግባቡ የተረዳችሁ አልመሰለኝም። ለሌላውን ቋንቋ ቀደም ባሉ ጊዜያት ትኩረት ብትሰጡትና ሀይማኖታዊ ትምህርት ቢሰጥበት ኢትዮጵያ ውስጥ የኦርቶዶክስ ተከታይ መቶ ፐርሰንት ባደረሳችሁት። ህዝቡ ለአህዛብ እምነት መስዋትነት መሆን የእናንተም አስተዋጽዎ እንዳለበት እወቁት። እባካችሁ መቼም የዲያብሎስን አሰራር ለእናንተ አይነገርም። በስንት ነገር እየተተራመስን እያወቃችሁት ይህቺን ሀይማኖት ከቋንቋ ጋራ ባታያይዝዋት። እባካችሁ እባካችሁ ይህንን ወሬ ከሚዲያ አውጡት። እስቲ ለራሳችሁ አስቡት ለእናንተ በማትሰሙት ቋንቋ ሀይማኖት ባስትምራችሁ, ምዕዳ, ጸሎት ቢደረግላችሁ? ይሄ ህግ በፍጹም መጽደቅ የለበትም። አስቡበት። የእግዚአብሄር ሰላም ይሁንላችሁ !!!!

 4. Berhanu Yemaneberhan May 18, 2014 at 11:52 am Reply

  Thanks!

 5. tewhado May 20, 2014 at 4:37 am Reply

  ይህ ነገር የረጅም ጊዜ ቤተክርስቲያንን የመቆጣጠሪያ እቅድ ይሆን ብዬ አሰብኩና ሆዴን ባር ባር አለው። ከዚህ ቀደም የትኛው ሕግ በተግባር ሲተረጎም አየን? ታዲያ ይህ ጥሩ የሚመስል እቅድ የመንግስት የረጅም ጊዜ እቅድ ከኋላው እንደሌለ በምን እርግጠኞች እንሆናለን?

  እንደው ማኅበረ ቅዱሳን ሰራው ቢሉኝ ኖሮ ለቤተ ክርስቲያን ታስቦ የተሰራ ነው እል ነበር። ደግሞም ተቃውሞ ይበዛበት ነበር።

  አሁን ግን ሁኔታው አስፈራኝ።

  ብቻ አባቶቻችንን የመከፋፈል፣ የፓትርያርኩን ቦታ የማዳከም ሥራ እንዳይሆን።

  እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን ይጠብቅልን።

 6. Anonymous May 21, 2014 at 2:22 pm Reply

  ተዋሕዶ የልቤን አውጥተህ ስለጻፍክልኝ አመሰግናለሁ። ይህንን እና ለፓትርያሪኩ እንደራሴ የመሾሙን ነገር ሳስበው በምስጢር የተቀነባበረ ነገር ያለ ነው የሚመስለኝ። በኔ አስተያየት ሁለቱም አስፈላጊ አደሉም። ምናልባት ቅዱስ ሲኖዶስ በቋሚ ኮሚቴዎች እና በመማክርት ጉባኤ ቢደራጅ መጠነኛ የሆነ ጥቅም ሊኖረው ይችላል፤ ነገር ግን ስንት አንገብጋቢ ጉዳይ እያለ በነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ ትኩረት መሰጠቱን ሳስበው ለሴራ የተቀነባበረ ይመስለኛል። ለመሆኑ ፓትርያሪኩ ምኑን ሰርተውት ነው ሥራው የበዛባቸው። ዋናው ሥራ መሰራት የነበረበት እኮ ባንድ ሰው ብቻ ሳይሆን በቤተ ክህነቱ መዋቅር ነው። ስለዚህ ቤተ ክህነቱን ማጽዳት ሲያስፈልግ፥ የሌለ ችግር አለ ብሎ መፍትሄ ለመፈለግ መጣር ድካም ብቻ ነው ትርፉ። እስቲ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እንደዚህ ዓይነት የእደራሴ ባህል ካላቸው ብትገልጹልን መልካም ነው። እኔ ግን ምንም መልካምነቱ አይታየኝም። በቢልዮን የሚቆጠሩ ምእመን ያላት የካቶሊክ ቤ/ን እንደራሴ ፓትርያሪክ ከሌላት ለኛ የሚያስፈልግበት ሁኔታ አይታየኝም። This is just my suspicion and I may be wrong.

 7. Anonymous May 21, 2014 at 3:20 pm Reply

  ቅዱስ ሲኖዶሱ በቋሚ ኮሚቴዎች እና በመማክርት ጉባኤ ሊደራጅ ነው ለፓትርያርኩ እንደራሴ እንደሚመደብ የሚገልጽ የሕግ ረቂቅ ለውይይት ቀረበ ስለዚህ ወደፊት ፓትርያርኩ ቋሚ ኮሚቴዎችን ሲመሩ፣ እንደራሴው ደግሞ የመማክርት ጉባኤውን ይመራሉ። አለመስማማት ቢፈጠር የአገሪቱን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል መንግስት ።።። እርምጃ ይወስዳል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: