ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በእንተ ትንሣኤኹ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት00
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

 • በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
 • ከሀገር ውጭ በተለያየ አህጉር የምትኖሩ፣
 • የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችኹ፣
 • በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችኹ፣
 • እንዲኹም የሕግ ታራሚዎች ኾናችኁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፤

እርሱ ሕያው ኾኖ ሕያዋን መኾናችንን በትንሣኤው ላበሠረን ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ እንኳን በሰላም አደረሳችኹ!!

‹‹ወርኢናሃ ለሕይወት፤ ወተዐውቀት ለነ፤
‹‹ሕይወትን አየናት፣ አወቅናትም›› (፩ኛዮሐ.፩÷፪)

የሕይወት መገኛና ምንጭ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፤ ከእግዚአብሔር የተገኘው ሕይወት የሰው ልጅ የዕውቀት ብርሃን ነው፤ አምላካዊ ሕይወት ካለው ሰው የሚፈልቅ ብርሃናዊ ዕውቀት ጽልመታዊውን ዓለም በብሩህነቱ ያሸንፋል እንጂ በጽልመታዊው ዓለም አይሸነፍም፡፡ (፩ኛዮሐ.፩÷፬ – ፭)፡፡

የሰው ልጅ ሕያው አምላክ በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ፍጡር በመኾኑ ሕያውና ክቡር፣ ዘላለማዊና ብርሃናዊ፣ የማሰብ፣ የማመዛዘን፣ የመምረጥና የመወሰን ነጻነት ያለውና ከሌሎች ፍጥረታት ኹሉ የላቀ አእምሮ ያለው ልዑል ፍጡር ነው፡፡
ሰው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ነጻነትና አእምሮ መሠረት ነጻነቱን ተጠቅሞ የመረጠውን የማድረግ ነጻነት ያለው ፍጡር ቢኾንም በነጻ ዕውቀቱና ምርጫው ለሚፈጽመው ኹሉ እርሱ ራሱ ሓላፊነቱን ይወስዳል፡፡

ይህም ማለት በምርጫው መሠረት የሚሠራው ሥራ ኹሉ በእውነተኛው ዳኛ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ኾኖ ከተገኘ ምስጋናን፣ መልካም ኾኖ ካልተገኘ ግን ተጠያቂነትንና ፍርድን ያስከትልበታል ማለት ነው፡፡

ከዚኽ አንጻር የመጀመሪያው ሰው የኾነው አዳም ማድረግ ያለበትና ማድረግ የሌለበት ተለይቶ ከእግዚአብሔር ቢነገረውም የተነገረውን ሕግ ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ የራሱን ነጻ ምርጫ ተጠቅሞ ‹‹አትብላ›› የተባለውን በላ፡፡ በመኾኑም ይህ ድርጊት በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ ታላቅ ስሕተትና ድፍረት ነበረና ተጠያቂነትን አስከተለ፤ በመጨረሻም ሕይወትን የሚያሳጣ የሞት ፍርድንና ቅጣትን በራሱና በልጆቹ ላይ አመጣ፡፡

ፍርዱ ሥራ ላይ ከዋለበት ቀን ጀምሮ ሰው ሕይወቱን ዐጣ ማለትም ከእግዚአብሔር አንድነት ተለየ፤ ሞትና ሲኦልም ሰውን ከእግዚአብሔር ለይተውና የራሳቸው ተገዥ አድርገው እስከ ስቅለተ ክርስቶስ ድረስ በቁጥጥራቸው ሥር አዋሉት፡፡ ኾኖም እግዚአብሔር በባሕርዩ መሐሪና ፈራጅ እንደመኾኑ ለፈራጅነቱና ለመሐሪነቱ የሚስማማ መንገድ አመቻችቶ መሐሪነቱንና ፈራጅነቱን በፈጸመበት በክርስቶስ ሞት ቤዛነት የሰው ልጅን ታረቀው፤ ያጣውንም ሕይወት መለሰለት፤ በምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን አማካይነትም እንደገና ሕይወቱን እንዲያገኝ አደረገ፡፡ (ዮሐ. ፮÷፶፮ – ፶፰፤ ማር. ፲፮÷፲፮)

ይህን አስመልክቶ ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር÷ ‹‹በመጀመሪያው ሰው (አዳም) ሞት መጣ፤ በኹለተኛው ሰው (ክርስቶስ) ግን ትንሣኤ ሙታን ኾነ፤ ኹሉም በአዳም እንደሚሞቱ እንደዚኹ ኹሉም በክርስቶስ ሕያዋን ይኾናሉ፤›› ብሏል፡፡ (፩ኛቆሮ ፲፭÷፳፩-፳፪፤ ሮሜ ፭-፲፪-፲፱)

ትንሣኤ ዘክርስቶስከዚህ የምንረዳው ዓቢይ ቁም ነገር በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት ያጣናት ሕይወት፣ በክርስቶስ መታዘዝ ያገኘናት መኾናችንን ነው፤ ጌታችንም ‹‹ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይኾናል፤ ሕያው የኾነም፣ የሚያምንብኝም ኹሉ ለዘላለም አይሞትም፤ እኔም በመጨረሻዪቱ ቀን አስነሣዋለኹ፤›› ብሎ ትንሣኤና ሕይወት መኾኑን እንደነገረን የሰው ልጅን ለዘላለማዊ ሕይወት እንደገና አበቃው፡፡ (ዮሐ.፮÷፶፬፤ ፲፩÷፳፭-፳፮)

የዚኽንም እውነታ በትንሣኤው አበሠረን፤ የእርሱ ትንሣኤ የትንሣኤያችን ዋዜማ ነውና የቀደመችው ሕይወት እንደተመለሰችልን በትንሣኤው ዐየናት፤ አወቅናትም፡፡ (ኤፌ. ፬÷፭-፯)

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት

የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ልጅ የዘላለማዊ ሕይወት ማረጋገጫ ነው፡፡ ለበርካታ ዘመናት በተስፋ ይጠበቅ የነበረው የክርስቶስ ነገረ አድኅኖ እና ነገረ ትንሣኤ በጊዜው ጊዜ እውን እንደኾነ ኹሉ፣ እንደዚያው በተስፋና በእምነት እየተጠባበቅነው ያለ የሰው ልጅ ሕይወታዊ ትንሣኤ ጊዜው ሲደርስ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት እውን ይኾናል፡፡ (፩ኛቆሮ ፲፭÷፳-፳፫፤ ፩ኛተሰ ፬÷፲፫-፲፰)

ይኹን እንጂ ዛሬም ሕይወትን በሚሰጥ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ያለን ስለኾን የሕይወትን ጣዕም አሁንም ማጣጣም እንችላለን፡፡ ሕይወት ጣዕም የሚኖረው በፍቅር ሲታጀብ ነው፡፡ ፍጹም ፍቅር የዘላለማዊ ሕይወት ኃይል ነው፡፡ ፍቅር ፍጹም የሚኾነው ሦስቱን አቅጣጫዎች ማእከል አድርጎ ሲገኝ ነው፡፡

ይኸውም ወደ ላይ እግዚአብሔርን በፍጹም ፍቅር መከተል ስንችል፣ ወደ ጎን በአርኣያ እግዚአብሔር የተፈጠረውን የሰው ልጅ በአጠቃላይ መውደድ ስንችል፣ ወደ ታች ደግሞ የምንኖርባትን ምድርና በውስጧ ያሉ ፍጥረታትን ስንከባከብ ነው፡፡ ይህን ካደረግን ፍጹም ፍቅር ከእኛ አለ ማለት እንችላለን፤ እግዚአብሔር ይህን ዓይነት ፍቅር እንዲኖረን በሃይማኖት አስተምሮናል፡፡

በመኾኑም እኛ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ለመግለጽ በመዋዕለ ጾሙ በጸሎት፣ በምጽዋትና በስግደት ስንገልጽ እንደቆየን ኹሉ፣ በፋሲካው በዓላችን እግዚአብሔር የሰጠንን በረከት ከተቸገሩ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ጋራ በመካፈል ለወገኖቻችን ያለንን ፍቅር ልንገልጽ ይገባናል፡፡

በዚኽ ዕለት በዓሉን ስናከብር የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ ጧሪ የሌላቸው አረጋውያን፣ አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናት፣ በልዩ ልዩ ምክንያት የአካልና የአእምሮ ጉዳት ደርሶባቸው የበይ ተመልካች የኾኑ ወገኖች ሁሉ ከእኛ ጋራ በማዕዳችን ተሳታፊ ኾነው በዓሉን በደስታና በምስጋና እንዲያከብሩ ማድረግ ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት፤

የትንሣኤ መሠረታዊ ትርጉም ከሞት በኋላ በሕይወት መኖርና መመላለስ ነው፡፡ ስለኾነም የትንሣኤን በዓል ስናከብር ባለፉት ዘመናት በድህነትና ኋላ ቀርነት ከሞት አፋፍ ደርሳ የነበረችውን ሀገራችን በልማትና በዕድገት ትንሣኤዋን ለማረጋገጥ ቃል በመግባት በዓሉን ማክበር ሀገራዊ ብቻ ሳይኾን ሃይማኖታዊ ግዴታ መኾኑን መገንዘብ አለብን፡፡

ምክንያቱም ጠንክረን በመሥራት ምድራችንን እንድናለማና እንድንከባከብ ከኹሉ በፊት ያዘዘ እግዚአብሔር ነውና፤ በተለይም የልማታችን የጀርባ አጥንት ኾኖ እንደሚያገለግል ታላቅ ተስፋ የተጣለበት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተያዘው ፍጥነት ሥራው ተሠርቶና ተጠናቆ የዕድገታችን ተሸካሚ ምሶሶ ኾኖ ማየት እንድንችል ኹሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡

የሀገራችን የልማትና የዕድገት መርሐ ግብሮች ዘርፈ ብዙ እንደመኾናቸው መጠን ገበሬው በየአካባቢው እያከናወነው የሚገኝ አፈርን የመገደብና አካባቢን በአረንጓዴ ልማት የማስዋብ ሥራ ያለመቋረጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ ቤተ ክርስቲያችን በግባር ቀደም ተሰልፋ እንደምትሠራ በዚኽ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ ያሉም ኾኑ ወደፊት ሊሠሩ በዕቅድ የተያዙ የሀገራችን የልማትና የዕድገት ሥራዎች በሕዝቡ የተባበረ ድጋፍ ሲከናወኑ የሀገራችን ብልጽግና እውን እንደሚኾን የኹላችንም እምነት ነው፡፡ ስለኾነም ለዚህ ስኬት የኢትዮጵያውን ሁሉ ጽናት፣ አንድነት፣ ስምምነትና ፍቅር፣ ሰላምና ተቻችሎ መኖር የማይተካ ሚና እንዳላቸው ለአፍታ እንኳ መዘንጋት የለብንም፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት፤

ልማታችን በተፈጥሮ ሀብት ክብካቤ ብቻ ሳይኾን የተቀደሰውና የተከበረው ባህላችንና ሰብኣዊ ሥነ ምግባራችንን ጠብቆ በማስጠበቅ ጭምርም መኾን ይገባዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ሀገረ እግዚአብሔር እንደኾነች በተደጋጋሚ የተነገረላት ያለምክንያት አልነበረም፤ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን በማናቸውም ጊዜ ከነውረ ኃጢአትና ከርኵሰት ኹሉ ርቀው፣ ሕገ ተፈጥሮንና ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀው፣ እግዚአሔር የሚለውን ብቻ አዳምጠውና አክብረው የሚኖሩ ቅዱሳን በመኾናቸው እንጂ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ሊፈጸም ቀርቶ ሊወራ የማይገባውን ሰዶምንና ገሞራን በእሳት ያጋየ ግብረ ኃጢአት በኢትዮጵያ ምድር መሰማቱ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያውያን የሰጠውን የቅድስና ክብር የሚያሳጣ ከመኾኑም ሌላ በሀገራችን ላይ ልማትና ዕድገት ሳይኾን መቅሰፍትና ውድቀት እንዳያስከትልብን ኹሉም ኢትዮጵያዊ ይህን የሰዶም ግብረ ኃጢአት በጽናት መመከት አለበት፡፡

ተፈጥሮን ለማልማት እየተረባረብን እንደኾነ ኹሉ ከዚህ ባልተናነሰ ኹኔታ የሰዶም ግብረ ኃጢአትን በመከላከል በቅዱስ ባህልና ሥነ ምግባር እጅግ የበለጸገና የለማ ትውልድ ማፍራት የልማታችን አካል ማድረግ አለብን፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህን ግብረ ኃጢአት እስከ መጨረሻው ድረስ አምርራ የምትዋጋው መኾኑን በዚህ አጋጣሚ ለመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፡፡ ስለኾነም ሕዝባችን ለሰላምና ለአንድነት፣ ለእኩልነትና ለልማት፣ ለቅዱስ ባህልና ሥነ ምግባር ቅድሚያ ሰጥቶ በኹሉም አቅጣጫ ልማቱን እንዲያፋጥን፣ ሃይማኖቱንም እንዲጠብቅ መልክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የትንሣኤ በዓል ያድርግልን!!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ፤ ይቀድስ፤ አሜን!!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም

Advertisements

3 thoughts on “ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በእንተ ትንሣኤኹ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ

 1. Kebede April 20, 2014 at 10:26 pm Reply

  ”እንዲኹም የሕግ ታራሚዎች ኾናችኁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፤” በመንግሥታቸው እሥር ቤቶች የሚማቅቁት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ጥፋተኞች ስለሆኑ ነው የታሰሩት የሚለውን አባ ማትያስም ይስማማሉ ማለት ነው ? እነእስክንድር ነጋ ፥ እነ አንዱዓለም አራጌ ፥ እነርእዮት ዓለሙን የመሳሰሉት በሺህ የሚቆጠሩት የህሊና እሥረኞች የማንን ህይዎት አጥፍተው ነው ወይም ደግሞ የማንን ንብረት ዘርፈው ነው በመንግሥታቸው እሥር ቤት እየማቀቁ የሚገኙት? አዬ አባ ምን አለ ”ወለእለ በመዋቅሕት ጽኑዓን ዘምስሌሆሙ ትሄሉ=በጽኑ እስራት ካሉትም ጋራ አብረሀቸው የምትኖር አምላክ” የሚለውን የኪዳኑን ቃል አጽንዖት ሠጥተው በግፍ የተሰሩት እንዲፈቱ መንግሥትዎን መጠየቅ አቃተዎት ? ከሠጡት ቃለ ቡራኬ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የመንግሥትዎን ፕሮፓጋንዳ የሚያንጸባርቅ ሁኖ ነው ያገኘሁት። ለማንኛውም እንኳን አደረሰዎት።

 2. Sewmehon April 21, 2014 at 8:55 am Reply

  በየሆስፒታሉና በየጠበል ቦታ ያላችሁ… ቢባል……

 3. ግእዝ በመሥመር-ላይ April 21, 2014 at 7:16 pm Reply

  ሐራዎች፦ እስከ ማእዜኑ???

  የማታምኑበትን–ይልቁንም የምትቃወሙትን–ነገር እስከ መቼ ስታራግቡ ትኖራላችኍ? ደግሞስ በቀይ ቀለምና በመሥመር የምንታለል ይመስላችዃል እንዴ? የልማታዊው ጳጳስ ዐይነተኛ መልእክት ቍልጭ ብሎ ተቀምጧል’ኮ። ሰብሰብ አድርጎ ባጭሩ ማስቀመጥ ቢያስፈልግ፤ እንዲኽ ነው የሚለው፦

  – ሕይወት የለም።

  “የትንሣኤ መሠረታዊ ትርጕም… ምድራችንን እንድናለማና እንድንከባከብ… በተለይም የልማታችን የጀርባ አጥንት… ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተያዘው ፍጥነት ሥራው ተሠርቶና ተጠናቆ የዕድገታችን ተሸካሚ ምሶሶ ኾኖ ማየት እንድንችል ኹሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡”

  -በሰማይ አምላክ የለም።

  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ማፍረስ አንዱ እና ዋና ዐላማው የኾነውን የዐላዊውን መንግሥት “መርሐ ግብሮች… ያለመቋረጥ ተጠናክ[ረው] እንዲቀጥ[ሉ] በማድረግ ረገድ ቤተ ክርስቲያችን በግባር ቀደም ተሰልፋ እንደምትሠራ በዚኽ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡”

  -እሊኽን መመሪያዎች ስንፈጽም እና ስናስፈጽም ምእመናን ነቄ እንዳይሉ ያስፈልጋል።

  ለዚኽም መሸፈኛ የውሸት ቃላት እንደረድራለን፦ “…የኢትዮጵያውን ሁሉ ጽናት፣ አንድነት፣ ስምምነትና ፍቅር፣ ሰላምና ተቻችሎ መኖር የማይተካ ሚና እንዳላቸው ለአፍታ እንኳ መዘንጋት የለብንም፡፡”

  -ሙግት ለለመደውም ጕልበቱን በከንቱ የሚጨርስበት አጀንዳ መፍጠር አይቸግረንም፦

  “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህን ግብረ ኃጢአት [የሰዶም ግብረ ኃጢአትን] እስከ መጨረሻው ድረስ አምርራ የምትዋጋው መኾኑን በዚህ አጋጣሚ ለመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፡፡”

  -የመልእክቱ ፍሬ ነገር ይኸው ነው። ገብቶናል።

  ይቺን ለእኛ ጥሬን ለጌኛ!

  ሐራዎች ግን ይኽን እና ይኽን የመሰለውን ዅሉ በምን ሒሳብ እንደምታራግቡት አልተረዳንም!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: