አክራሪነትና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር – የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአክራሪነት ትርጉም የተሳሳተ ነው! የፈራጁን ማንነትም መጠራጠር ይኖርብናል!

(አዲስ ጉዳይ፤ ቅጽ ፰ ቁጥር ፪፻፲፪፤ ሚያዝያ ፳፻፮ ዓ.ም.)

Addis Guday Logoዲያቆን ዳንኤል ክብረት

 • እስከ አሁን በታተሙ ቅዱሳት መጻሕፍትም ኾነ ለጥምቀት በታተሙ ካኔቴራዎች ላይ በኤፌሶን ፬÷፬ ላይ ያለው ጥቅስ ከነመገኛው ተጠቅሶ ከመታተሙ በቀር አንድ ሀገር የሚል የለውም፡፡ ከእውነታ አንጻር ይህን ጥቅስ መጥቀስ በራሱ ስሕተት ነው፤ የሌለን ነገር እንዳለ አድርጎ ማቅረብ ነውና፡፡ ‹‹ጥቁር ድመትን በጨለማ ውስጥ መፈለግ አስቸጋሪ ነው፤ በተለይ ደግሞ ድመቷ ከሌለች›› እንደሚባለው፡፡
 • ከሃይማኖትና ከጥምቀት ጋራ በአንድ ላይ አንድ ሀገር የሚል የክርስትና ትምህርትሊኖር የማይችለው ከክርስትና ዶግማ ጋራ የማይሔድ በመኾኑ ነው፡፡ ይህን ጥቅስ እስከ አሁን ፖሊቲከኞች እንጂ ሃይማኖተኞች ሲጠቅሱት አልታየም፡፡ ይህ እምነት ደግሞ የኹሉም የክርስትና አማኞች እምነት ነው፡፡ እንዴት ተነጥሎ የአንድ ማኅበር አባላትን ሊያስፈርጅ እንደቻለ የሚያውቁት ፈራጆቹ ብቻ ናቸው፡፡
 • እነዚህን ሦስት ነገሮች አንድ ላይ በማምጣት ‹‹አንድ ሀገር›› የሚለው ሐሳብ አምታች እንዲኾን ተደረገ እንጂ ‹‹አንድ ሀገር›› የሚለው ሐሳብ በራሱ በሕግ ወንጀል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕግ ሁለት ዜግነትን አይፈቅድም፡፡
 • ‹‹ለአንድ ሀገር አንድ ሃይማኖት›› ቢል ሌሎችን የማስወገድ ሐሳብ አለው ሊባል ይችላል፡፡ ‹‹አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሀገር፣ አንድ ጥምቀት›› ማለት ግን የሰውዬውን አንድ እምነትን መቀበሉን፣ አንድ ጥምቀት መጠመቁን፣ የአንዲት ሀገር ዜጋ መኾኑን ከማመልከት ውጭ ነውሩም፣ ኃጢአቱም ወንጀሉም ምኑ ላይ ነው? እስኪ አንቀጽ ይጥቀሱልን፤ ወይስ ትክክል የሚኾነው ስንት ሀገር ነው?
 • በቅዱስ ጳውሎስ የኤፌሶን መልእክት ላይ ያለው ቃል ‹‹አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት›› የሚል ነው፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊም ይኹኑ ከዚህ በፊትም ይህን የሚያቀነቅኑ ኃይሎች ግን ‹‹አንድ ጌታ›› የሚለውን አውጥተው ‹‹አንድ ሀገር›› የሚል ጨምረውበታል፡፡ ለምን? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ ይህ ነገር የዚህን መፈክር ምንጭ እንድንጠረጥር ያደርገናል፡፡ እዚህች ሀገር ውስጥ ‹‹ጌታ›› የሚለው ወጥቶ በሌላ እንዲተካ የተደረገው እነማንን ላለመቀላቀል እንደኾነም መገመት ይቻላል፡፡
 • ‹አንድነት› የክርስትና ዋናው መለያ ነው፡፡ ለዚኽም ነው አንድ ሃይማኖትና አንዲት ጥምቀት የሚለው እምነት ትክክለኛ የሚኾነው፡፡ በ፫፻፹፩ ዓ.ም. በቁስጥንጥንያ የተሰባሰቡ ፻፶ አባቶችም ‹‹ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለስርየተ ኃጢአት፤ ኃጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን›› በማለት በማለት የደነገጉትም ለዚህ ነው፡፡ ይህን ማለት አክራሪነት ከኾነ ፍረጃው ሠለስቱ ምእትንና ፻፶ው ሊቃውንትንም ይጨምራል ማለት ነው፡፡ ታድያ ማን ተረፈ? ደግሞስ አንዲት ጥምቀት ብሎ ማመን አክራሪነት ከኾነ ትክክለኛ የሚኾነው ስንት ጥምቀት መቀበል ነው? ስንት ጥምቀት መቀበል እንዳለብን የሚደነግግልን ማነው? የፌዴራል ጉዳዮችስ የጥምቀትን ቁጥር ወደ መበየን እንዴት ገባ? ‹‹ፍቅርን እዚኽ ውስጥ ምን ዶለው?›› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፡፡
 • ‹‹አንድ›› ማለት የሌላ አለመኖርን ሳይኾን ‹‹የሌላው ትክክል አለመኾንን›› የሚገልጥ ነው፡፡ አንድ አምላክ ብቻ አለ ሲባል ‹‹አማልክት›› ተብለው የሚጠሩ ሌሎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ይህን መጽሐፍ ቅዱስም ‹የአሕዛብ አማልክት›› በማለት ጠርቶ የሀልዎት/ህላዌ ዕውቅና ሰጥቷቸዋል፤ ነገር ግን ትክክል አይደሉም ማለቱ ነው፡፡
 • የእኔ ትክክል ነው ማለት ሌሎች መኖር የለባቸውም፤ መጥፋትም አለባቸው ማለት አይደለም፡፡ ይህ የዕውቀትና የእምነት ክርክር ነው፡፡ እንኳን በሥላሴ አርኣያ የተፈጠሩ ሰዎችን ቀርቶ ሰይጣንንም እንኳን እንዲጠፋ መመኘት ክርስቲያናዊ አይደለም፡፡ ሰይጣንን መቃወም ሰይጣንን ማጥፋት አይደለም፤ መከራከርና መገዳደር እንጂ፡፡፡
 • ‹‹አንዲት ሃይማኖት›› እና ‹‹አንዲት ጥምቀት›› የሚለው የአኹኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በሚቀበሉትና በሚያነቡት መጽሐፍ ቅዱስም ውስጥ ይገኛልና የሚኒስቴር መሥ/ቤቱ የአክራሪነት መመዘኛ ይኼ ከኾነ ነገሩ ተያይዞ የት እንደሚደርስ ማየቱ የተሻለ ይኾናል፡፡፡

 

 

Dn. Daniel Kibretባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሚያዝያ ፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. የወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ የሰጡትን መግለጫ አንብቤ ነበር፡፡ ከመግለጫቸው ውስጥ እጅግ የገረመኝና ይህን ጽሑፍ እንድጽፍ ያደረገኝም አክራሪነትን በተመለከተ የሰጡት ትርጓሜ ነው፡፡

መንግሥት ማኅበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት እንዳልፈረጀ ከገለጡ በኋላ፣ ‹‹ይህ ሲባል ግን እንደ ማንኛውም ተቋም የተቀደሰውን ዓላማ የሚያራክሱ፣ ማኅበሩን ወዳልኾነ አቅጣጫ የሚወስዱ ግለሰቦች አይኖሩም ማለት እንዳልኾነ ጠቅሰዋል። በተለይም ‹‹አንድ ሃይማኖት! አንድ ሀገር! አንድ ጥምቀት!›› እያሉ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ። እንደዚህ ዓይነቶቹ ግለሰቦች በአክራሪነት ሊፈረጁ ይችላሉ›› በማለት አክራሪ የሚባሉ አባላትን አቋም ገልጠውታል፡፡

እንደ እርሳቸው፣ በእርሳቸውም በኩል እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከኾነ ‹‹አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሀገር፣ አንድ ጥምቀት›› ብሎ ማመን ‹‹አክራሪ›› የሚያሰኝ ነው፡፡ እስኪ ይህን የሚኒስቴሩን መግለጫ ከእውነታ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት እና ከእምነት አቋም አንጻር እንመልከተው፡፡

‹‹አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሀገር፣ አንድ ጥምቀት›› የሚል ጥቅስም መፈክርም እስከ አሁን ታይቶ አይታወቅም፡፡ በኤፌሶን መልእክት ፬÷፬ ‹‹አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት›› የሚል ቃል ነው የሰፈረው፡፡

እስከ አሁን በታተሙ ቅዱሳት መጻሕፍትም ኾነ ለጥምቀት በታተሙ ካኔቴራዎችም ላይ ይኼው በኤፌሶን ፬÷፬ ላይ ያለው ጥቅስ ከነመገኛው ተጠቅሶ ከመታተሙ በቀር አንድ ሀገር የሚል የለውም፡፡ ከእውነታ አንጻር ይህን ጥቅስ መጥቀስ በራሱ ስሕተት ነው፤ የሌለን ነገር እንዳለ አድርጎ ማቅረብ ነውና፡፡ ‹‹ጥቁር ድመትን በጨለማ ውስጥ መፈለግ አስቸጋሪ ነው፤ በተለይ ደግሞ ድመቷ ከሌለች›› እንደሚባለው፡፡

ይህ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አባባል ከሌላው እውነት ጋራም ይጋጫል፡፡ ክርስትና ሁለት ሀገሮች እንዳሉን የሚነግረን ሃይማኖት ነው፡፡ በዚህ በምድር በሥጋ የምንኖርባትና በላይ በሰማይ ለዘለዓለም የምንኖርባት፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ፣ ‹‹እኛስ ሀገራችን በሰማይ ነው››(ፊልጵ.፫÷፳) በማለት የተናገረው፡፡ ሃይማኖትና ጥምቀት ግን በዚህ በምድርም በላይ በሰማይም የማይደገሙ፣ መንትያም የሌላቸው በመኾናቸው ሁለትነት አይስማማቸውም፡፡

ከዚህም በላይ ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የላከው መልእክት ክርስቲያኖች በአንድ ጊዜ በሁለት ዜግነት ውስጥ እንደሚኖሩ መግለጡን ሊቃውንት ተርጉመውታል፡፡ ‹‹በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን፣ በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን›› (ኤፌ.፩÷፩)፡፡ እነዚህ የኤፌሶን ክርስቲያኖች እንደ ሰውነታቸው ኤፌሶን በምትባል ሀገር፣ እንደ ክርስቲያንነታቸውም ክርስቶስ በሚባል ወሰንና ዘመን በሌለው ሀገር ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ሊቃውንት መንግሥተ ሰማያት ማለት ራሱ ክርስቶስ ነው፤ እርሱን ወርሰን በእርሱ እንኖራለንና፡፡

ስለዚህም ከሃይማኖትና ከጥምቀት ጋራ በአንድ ላይ አንድ ሀገር የሚል የክርስትና ትምህርት ሊኖር የማይችለው ከክርስትና ዶግማ ጋራ የማይሔድ በመኾኑ ነው፡፡ ይህን ጥቅስ እስከ አሁን ፖሊቲከኞች እንጂ ሃይማኖተኞች ሲጠቅሱት አልታየም፡፡ ይህ እምነት ደግሞ የኹሉም የክርስትና አማኞች እምነት ነው፡፡ እንዴት ተነጥሎ የአንድ ማኅበር አባላትን ሊያስፈርጅ እንደቻለ የሚያውቁት ፈራጆቹ ብቻ ናቸው፡፡ ምናልባትም ፈራጆቹም ይህን ማመናቸው የማይቀር ይመስለኛል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን ሦስት ነገሮች አንድ ላይ በማምጣት ‹‹አንድ ሀገር›› የሚለው ሐሳብ አምታች እንዲኾን ተደረገ እንጂ ‹‹አንድ ሀገር›› የሚለው ሐሳብ በራሱ በሕግ ወንጀል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕግ ሁለት ዜግነትን አይፈቅድም፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ሌላ ዜግነት ሲያገኝ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ወዲያው ያጣልና፡፡ (የዜግነት ዐዋጅ ቁጥር 378/96፣ ዐንቀጽ 19 – 20/1)፡፡ ይህ ማለት ሊኖርኽ የምትችለው ሀገር አንዲት ናት ማለት ነው፡፡ የመንግሥት ሚዲያዎችም ዜግነታቸውን የለወጡትን ኢትዮጵያውያን ‹‹ትውልደ ኢትዮጵያውያን›› ይሏቸዋል እንጂ ‹‹ኢትዮጵያውያን›› አይሏቸውም፡፡ ይህም ማለት የሀገራችን ሕግ አንድ ኢትዮጵያዊ አንድ ሀገር (እርሷም ኢትዮጵያ) ብቻ ሊኖረው እንደሚችል ይደነግጋል ማለት ነው፡፡

ከዚህም በላይ አንድ ኢትዮጵያዊ ‹‹እኔ የምትኖረኝ አንዲት ሀገር ብቻ ናት›› ቢል ችግሩ ምኑ ላይ ነው፤ ደግሞም ብዙዎቻችን እንደዚያ ነን፡፡ ትምረርም፣ ትረርም ያለችን አንዲት ሀገር ናት፤ ትመችም፣ ትቆርቁርም ያለችን አንዲት ሀገር ብቻ ናት፡፡ ስለዚህም ምን የቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርት ባይኾን አንድ ኢትዮጵያዊ ተነሥቶ ‹እኔ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሀገር፣ አንድ ጥምቀት ብቻ እቀበላለኹ›› ቢል በሕግስ፣ በሞራልስ፣ በልማድስ ምንድን ነው የሚያስጠይቀው፡፡

‹‹ለአንድ ሀገር አንድ ሃይማኖት›› ቢል ሌሎችን የማስወገድ ሐሳብ አለው ሊባል ይችላል፡፡ ‹‹አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሀገር፣ አንድ ጥምቀት›› ማለት ግን የሰውዬውን አንድ እምነትን መቀበሉን፣ አንድ ጥምቀት መጠመቁን፣ የአንዲት ሀገር ዜጋ መኾኑን ከማመልከት ውጭ ነውሩም፣ ኃጢአቱም ወንጀሉም ምኑ ላይ ነው፡፡ እስኪ አንቀጽ ይጥቀሱልን፤ ወይስ ትክክል የሚኾነው ስንት ሀገር ነው?

ይህን ሐሳብ ከቅዱሳት መጻሕፍት አንጻር ስንመረምረው አስገራሚ ነገር እናገኛለን፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ የኤፌሶን መልእክት ላይ ያለው ቃል ‹‹አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት›› የሚል ነው፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊም ይኹኑ ከዚህ በፊትም ይህን የሚያቀነቅኑ ኃይሎች ግን ‹‹አንድ ጌታ›› የሚለውን አውጥተው ‹‹አንድ ሀገር›› የሚል ጨምረውበታል፡፡ ለምን? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ ይህ ነገር የዚህን መፈክር ምንጭ እንድንጠረጥር ያደርገናል፡፡ እዚህች ሀገር ውስጥ ‹‹ጌታ›› የሚለው ወጥቶ በሌላ እንዲተካ የተደረገው እነማንን ላለመቀላቀል እንደኾነም መገመት ይቻላል፡፡

‹‹አንድ›› የሚለውን ሐሳብ ከክርስትና አስተምህሮ አንጻር ስንመለከተው አክራሪ ሳይኾን ዐዋቂ የሚያሰኝ ኾኖም እናገኘዋለን፡፡ ‹‹አንድ›› የሚለው ሐሳብ በሦስቱም ታላላቅ የዓለም እምነቶች መሠረታዊ የእምነት ቁጥር ነው፡፡ ቁጥሮች በቅዱሳት መጻሕፍት አኃዛዊ/የብዛት ዋጋ (numerical value) ሳይኾን መንፈሳዊ ዋጋ ነው ያላቸው፡፡ ሦስት የምስጢረ ሥላሴ፣ አምስት የእምነት አዕማድ፣ ሰባት የፍጹምነት፣ ዐሥር የምሉዕነት፣ መቶ የእግዚአብሔር መንጋ፣ ሺሕ መጠንና ልክ የሌለው ዘመን እያለ ይቀጥላል፡፡

የኦሪት (ይሁዲነት) እምነት መሠረቱ በ‹‹አንድ አምላክ› ማመን ነው፡፡ በእስልምናም ከመሠረታውያኑ አምስቱ የእምነቱ አዕማድ አንዱ ‹‹በአንድ አምላክ(አላህ) ብቻ ማመን›› ነው፡፡ በክርስትናም ቢኾን በአንድ አምላክ ማመን መሠረታዊ እምነት ነው፡፡ አምላክ አንድ ነው ካልን ደግሞ ሃይማኖትም አንድ ነው ማለታችን ነው፡፡

ከላይ ካነሣናቸው ታላላቅ እምነቶች አንዱም እንኳን ሃይማኖት ሁለት ነው ወይም ሦስት ነው የሚል ፈጽሞ የለም፡፡ በዚህም መሠረት ‹አንድ ሃይማኖት›› ማለት አክራሪነት ከኾነ በዓለም ላይ አክራሪ ያልኾኑት የቡድሃ፣ የኮንፊሺየስ ወይም የሌሎች የሩቅ ምሥራቅ እምነቶች ተከታዮች አለያም ደግሞ እምነት አልባ ሰዎች ብቻ ናቸው ማለት ነው፡፡ ይህ ከኾነ ደግሞ ከዓለም ሕዝብ ከሁለት ሦስተኛው በላይ አክራሪ ነው ያሰኛል፡፡

በክርስትና ትምህርት ‹‹አንድ›› የሚለው ቃል ከቁጥር ዋጋ በላይ አለው፡፡ የእምነት ቁጥር ነው፤ ሊደገሙ፣ ሊሠለሱ የማይችሉ ነገሮች መገለጫም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ውስጥ ቢያንስ ዘጠኙ ‹አንዶች› የታወቁ የእምነት መሠረቶች ናቸው፡፡

 1. አምላክ አንድ ነው፡- ክርስትና ብዙ አማልክትን አይቀበልም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም አማልክት የሚላቸው ኹለት ነገሮችን ነው፡፡ አንድም የአሕዛብን ጣዖታት (የአሕዛብ አማልክት እንዲል)፣ ያለበለዚያም ቅዱሳንን (እግዚአብሔር በአማልክት ማኅበር ቆመ) እንዲል፡፡
 2. ሥጋዌ አንድ ነው፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ አዳምን ለማዳን ሰው ሆኗል፡፡ ዳግም አይወለድም፣ ሰውም አይሆንም፡፡
 3. ሃይማኖት አንድ ነው፡- ሃይማኖት ወደ እግዚአብሔር የመጓዣ መንገድ፣ ፍኖተ እግዚአብሔር፣ ወይም እግዚአብሔር ዓለምን ፍለጋ ያደረገው ጉዞ በመኾኑ ምንታዌ የለውም፡፡ ወደ አንድ እግዚአብሔር የሚወስደው ትክክለኛው መንገድ አንድ ነው፡፡ ይህንንም ቅዱስ መጽሐፍ ‹የእግዚአብሔር መንገድ› ይለዋል (ኤር. ፭÷፬)
 4. ጥምቀት አንዲት ናት፡- ጥምቀት የሞት ምሳሌ ነው፤ መጠመቅም ከክርስቶስ ጋር መሞት ነው(ሮሜ ፮÷፫)፤ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ብቻ ሞቷልና እኛም አንድ ጊዜ ብቻ እንጠመቃለን፤ ሞትም አንድ ጊዜ ብቻ ነውና ጥምቀትም አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ጥምቀት እንደ ቁርባንና ንስሐ አይደገምም፡፡
 5. ክህነት አንድ ጊዜ ነው፡- ክህነት እያደገ ይሄዳል እንጂ አንድ ሰው በአንድ መዓርግ ሁለት ጊዜ አይካንም፤ ክህነቱን ቢያፈርስም ምእመን ሆኖ ይኖራል እንጂ እንደገና አይካንም፡፡
 6. ፍጥረት አንድ ጊዜ ነው፡- እግዚአብሔር ፍጥረትን አንድ ጊዜ ነው የፈጠረው፤ ደግሞ የፈጠረው ፍጥረት የለም፡፡ በቀዳሚት ሰንበት ፍጥረት ሲፈጸምም ከዚያ በኋላ እንደገና አይፈጠርም፡፡ ይባዛልለ፤ ይዋለዳል፤ ያረጃል፤ ይሞታል እንጂ ፍጥረት እንደገና አይፈጠርም፡፡
 7. የመጨረሻው ፍርድ አንድ ጊዜ ነው፡- የዓለም መጨረሻ አንድ ጊዜ በመጨረሻው ቀን ፍርድ የሚዘጋ ነው፡፡ ሁለት ሦስት ጊዜ የሚሰጥ የዓለም የፍርድ ቀን የለም፡፡
 8. ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፡- በኒቂያ በ፫፻፳፭ ዓ.ም. የተሰባሰቡት ፫፻፲፰ ሊቃውንተ እንደ መሰከሩት ‹ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት›፡፡ ሁለትነትና ሦስትነት የለባትም፡፡
 9. ተክሊል አንድ ጊዜ ነው፡- ተክሊል የሰማያዊ አክሊል ምሳሌ ነው፡፡ ሰማያዊ አክሊል አንድ ጊዜ የሚሰጥ፣ ተሰጥቶም የሚኖር ነው፡፡ የእርሱ ምሳሌ የሆነው ተክሊልም አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጥ፣ ተሰጥቶም የሚኖር ነው፤ አይደገምም፡፡

መሠረታዊ የኾኑትን ዘጠኙን አነሣን እንጂ ‹አንድነት› የክርስትና ዋናው መለያ ነው፡፡ ለዚኽም ነው አንድ ሃይማኖትና አንዲት ጥምቀት የሚለው እምነት ትክክለኛ የሚኾነው፡፡ በ፫፻፹፩ ዓ.ም. በቁስጥንጥንያ የተሰባሰቡ ፻፶ አባቶችም ‹‹ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለስርየተ ኃጢአት፤ ኃጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን›› በማለት በማለት የደነገጉትም ለዚህ ነው፡፡ ይህን ማለት አክራሪነት ከኾነ ፍረጃው ሠለስቱ ምእትንና ፻፶ው ሊቃውንትንም ይጨምራል ማለት ነው፡፡ ታድያ ማን ተረፈ? ደግሞስ አንዲት ጥምቀት ብሎ ማመን አክራሪነት ከኾነ ትክክለኛ የሚኾነው ስንት ጥምቀት መቀበል ነው? ስንት ጥምቀት መቀበል እንዳለብን የሚደነግግልንስ ማነው? የፌዴራል ጉዳዮችስ የጥምቀትን ቁጥር ወደ መበየን እንዴት ገባ? ‹‹ፍቅርን እዚኽ ውስጥ ምን ዶለው?›› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፡፡

እነዚህን ሃይማኖታዊ ድንጋጌዎች በተነገሩበትና በተጻፉበት ዐውድ ውስጥ መረዳትን ይጠይቃል፡፡ ‹‹አንድ›› ማለት የሌላ አለመኖርን ሳይኾን ‹‹የሌላው ትክክል አለመኾንን›› የሚገልጥ ነው፡፡ አንድ አምላክ ብቻ አለ ሲባል ‹‹አማልክት›› ተብለው የሚጠሩ ሌሎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ይህን መጽሐፍ ቅዱስም ‹የአሕዛብ አማልክት›› በማለት ጠርቶ የሀልዎት/ህላዌ ዕውቅና ሰጥቷቸዋል፤ ነገር ግን ትክክል አይደሉም ማለቱ ነው፡፡ አንድ ሰው በስሕተት ዳግም ሊያጠምቅ አይችልም እያለ አይደለም፡፡ ጥምቀቱ የተደገመ ከሆነ ስሕተት ነው እያለ ነው፡፡ ‹‹አንድ ሃይማኖት›› ሲልም ርቱዕ የኾነችው እምነት አንዲት ናት፤ ሌሎቹ የተሳሳቱ ናቸው እያለ ነው፡፡

ይህ አስተሳሰብ የእምነት አቋም ነው፡፡ በተለይም ሦስቱ የዓለማችን ታታላቅ እምነቶች ‹‹ርቱዕ፣ ትክክለኛና፣ ድኅነት የሚገኝበት ሃይማኖት›› የሚሉትን ይበይናሉ፤ በብያኔያቸውም የእነርሱ እምነት መኾኑን ይገልጣሉ፡፡ በእምነት አቋም ውስጥ ‹‹ብዙ ትክክለኛ እምነት›› ሊኖር አይችልም፡፡ በሀገር ውስጥ ግን ብዙ እምነቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እምነት ብዙ እምነቶችን ሊያስተናግድ አይችልም፡፡ ብዙ እምነቶችን ሊያስተናግድ የሚችለው ሕገ መንግሥት ነው፡፡

ደግሞም ያኛው ስሕተት ነው እኔ ትክክል ነኝ ማለት አክራሪነት አይደለም፡፡ እምነት ነው፡፡ እንኳን አንድ እምነት አንድ የፖለቲካ ፓርቲ እንኳን ትክክለኛው የሰላም፣ የዴሞክራሲና የዕድገት መሥመር የእኔ መሥመር ነው፣ የሌላው ስሕተት ነው ብሎ አይደለም እንዴ እየተፎካከረ ያለው፡፡ ይህ በአክራሪነት ካስፈረጀ፣ እንኳን ፖሊቲከኛው በፖለቲካ የለኹበትም የሚለውም አይተርፍ፡፡ እርሱ ራሱ ‹‹ፖለቲከኛ አለመኾን ነው ትክክለኛው›› እያለ ነውና፡፡

የእኔ ትክክል ነው ማለት ሌሎች መኖር የለባቸውም፤ መጥፋትም አለባቸው ማለት አይደለም፡፡ ይህ የዕውቀትና የእምነት ክርክር ነው፡፡ እንኳን በሥላሴ አርኣያ የተፈጠሩ ሰዎችን ቀርቶ ሰይጣንንም እንኳን እንዲጠፋ መመኘት ክርስቲያናዊ አይደለም፡፡ ሰይጣንን መቃወም ሰይጣንን ማጥፋት አይደለም፤ መከራከርና መገዳደር እንጂ፡፡

ማጠቃለያ
ከላይ ባነሣናቸው ነጥቦች ብቻ እንኳን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሰጠው የአክራሪነት ትርጉም የተሳሳተ መኾኑን ማየት ይቻላል፡፡ ‹‹አንዲት ሃይማኖት›› እና ‹‹አንዲት ጥምቀት›› የሚለው የአኹኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በሚቀበሉትና በሚያነቡት መጽሐፍ ቅዱስም ውስጥ ይገኛልና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአክራሪነት መመዘኛ ይኼ ከኾነ ነገሩ ተያይዞ የት እንደሚደርስ ማየቱ የተሻለ ይኾናል፡፡

Advertisements

15 thoughts on “አክራሪነትና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር – የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአክራሪነት ትርጉም የተሳሳተ ነው! የፈራጁን ማንነትም መጠራጠር ይኖርብናል!

 1. Agew April 19, 2014 at 12:55 pm Reply

  One of the most sensible articles composed by Daniel. I believe you are born to write!!! I wish I could hear what these people respond to this article. But I know they have no answer. It is just they don’t want to see MK. They hate us. A such simple!!

  TesfaMeskle from Arat Kilo.

 2. oyared April 19, 2014 at 12:59 pm Reply

  የእኔ ትክክል ነው ማለት ሌሎች መኖር የለባቸውም፤ መጥፋትም አለባቸው ማለት አይደለም፡፡ እንኳን በሥላሴ አርኣያ የተፈጠሩ ሰዎችን ቀርቶ ሰይጣንንም እንኳን እንዲጠፋ መመኘት ክርስቲያናዊ አይደለም፡፡ ሰይጣንን መቃወም ሰይጣንን ማጥፋት አይደለም፡፡

 3. Anonymous April 19, 2014 at 2:06 pm Reply

  10q d/n this is what is expected from you God b with you.

 4. ም.ክ.ረ. April 19, 2014 at 3:03 pm Reply

  ዲ/ን ዳንኤል፡- እግዚአብሔር ይስጥልን። ይህ የሁላችንም ሃሳብና እምነት ነው። በአንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት ለምናምን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን። እንደ እኔ ግምት እነዚህ ሰዎች/ከሳሾቹ/ ይህ እውነታ በፍፁም ጠፍቷቸው አይመስለኝም፤ ዓላማው ነጥሎ መምታት ነውና…. ነቅተናልም።

 5. Anonymous April 19, 2014 at 4:42 pm Reply

  Aye Daniel kibiret, Ante eko neh andu mereja tsehafi ” SIWIR AMERAR ALE TETENKEKU BILEH YAWEJIHEW LE’ALEM”. technically, you seems “SMART”. All senior members of MK are aware of what you are doing know with anti-MK group.

  ATFIRIM ahun yihinin sititsif be’egziabher.

  • Mamo April 24, 2014 at 7:15 pm Reply

   Amelekaketih betam yetebebe new…Wondim….Arikeh lemayet mokir….Tebab!!!!

 6. Kebede April 19, 2014 at 7:38 pm Reply

  በጣም ጥሩ መልስ ነው ተቀናቃኙ ሃይል የሚቀበለው ከሆነ። ችግሩ ግን መንግሥታችሁ በሀሳብ ሳይሆን ሀሳብን ማሸነፍ የሚፈልገው ባለው መንግሥታዊ በሆኑ የማፈኛና የመጨቆኛ መሳሪያዎቹ ነው። ማሸነፍም ሆነ መሸነፍ በሀሳብ ብቻማ ቢሆን ኑሮ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሠለጠኑት ሀገሮች ቁጥር ውስጥ ትገባ ነበር። አሸናፊው ጠመንጃ መሆኑ ነው እንጅ ችግሩ። ”ሰይጣንንም እንኳን እንዲጠፋ መመኘት ክርስቲያናዊ አይደለም፡፡ ሰይጣንን መቃወም ሰይጣንን ማጥፋት አይደለም፡፡” የሚለው ነገር ግን አልገባኝም። ሠይጣን እኮ አምላኩን በመፈታተኑ ከማኅበረ መላእክት ተለይቶ ጠፍቷል። ከሠይጣን መጥፋት የበለጠ ጥፋት አለ እንዴ ? ወይስ መጥፋትን ከህልውና አንፃር አይተውት ነው ? ከክርስትና አስተምህሮ አንፃር ግን ሠይጣን ከመላእክት ተለይቶ ጠፍቷል። ጥንተ ጠላታችን ሠይጣን ሠይጣናዊ ህልውናው ጨርሶ እንዲጠፋም ክርስቲያኖች መጸለይ አለብን። ለማንኛውም ንበል ኩልነ ‘ ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን ! በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን ! አሰሮ ለሠይጣን ! አግዓዞ ለአዳም ! እምይእዜሰ ኮነ ፍስሥሐ ወሰላም !! ዓሜን ።

 7. Sewmehon April 21, 2014 at 8:01 am Reply

  የፌዴራል ጉዳዮች መሰረታዊ ችግር የጥናታዊ ጽሁፍ መስፈርት ያላJሉ፤ በአሉባልታ የታጨቁ፤ ገለልተኛ ያልሆኑ የደህንነት አካላትን (በቤተክርስትያኗ ላይ መሰረታዊ ተቃርኖ ባላቸው ፖለቲከኞች የሚዘወሩ) እንዲሁም የማኅበሩ የኃይማኖት ማለትም የኦርቶዶክስ ተከላካይነት አላነቃንቅ ያላቸው የውስጥ ና የውጭ አካላትን በተለይም የሙሰኞችና «የተኃድሶ» አራማጆች ጥምረትን በመረጃ ምንጭነት የሚጠቅሱ «ጥናታዊ ጽሁፍ »ተብለው በየመድረኩ የሚቀርቡ አሳፋሪ ይዘት ያላቸው እንደ መነሻ ጠቀሙ ነው!

 8. Anonymous April 22, 2014 at 11:22 am Reply

  Great! but we have to unite than ever before!!!!!

 9. Anonymous April 25, 2014 at 8:40 am Reply

  ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ ረጅም እድሜ ከጤና ጋር ያድልልን፡፡
  ጆሮ ያለው ይስማ፡፡

 10. Yosey April 25, 2014 at 8:44 am Reply

  ጆሮ ያለው ይስማ!!! ቃለ ሕይወት ያሰማልን

 11. Anonymous April 28, 2015 at 12:55 pm Reply

  ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ ረጅም እድሜ ከጤና ጋር ያድልልን

 12. weleteselase August 4, 2015 at 4:54 pm Reply

  ዲያቆን ዳንኤል ክብረት መልእክትህ ለእኔ ገብቶኛል በእውነት ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ ስለዳዊት ብሎ የህዝቄልን እድሜ የጨመረ አምላክ ስለአቡነተክለሀይማኖት ብሎ የአንተንም እድሜ እንዲጨምርልህ የዘወትር ፀሎቴ ነው፡፡ ሙሉጌጥ/ወለተስላሴ ነኝ/

 13. denekew shumet August 6, 2015 at 2:24 pm Reply

  my brother be hard keep it up

 14. Anonymous August 29, 2017 at 6:56 am Reply

  ልክነው

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: