ማኅበረ ቅዱሳንን የማፍረስ አደገኛው ተልእኮ

FACT Miyaziya cover on MK

 • በመኾኑም ታጋዮቹ የመንግሥትነት ሥልጣንን ሲቆናጠጡ ቤተ ክርስቲያንን የማጥቃት የቀደመ ሕልማቸውን አሐዱ አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ቀደም ይዛ የነበረውን መሬት መንጠቅ፣ በግፍ የተነጠቀቻቸውን ቤቶችና ሕንፃዎች አሟልቶ አለመመለስ፣ ቤተ ክርስቲያኗ በማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተለይም የማስታረቅና ግጭቶችን በሰላም የመፍታት ተልእኮዋን በመንጠቅ አዲስ ለተመሠረቱት ፖሊቲካዊ ማኅበራት መስጠት፤ ከዚኽም ባሻገር ከትጥቅ ትግል አንሥቶ በስለላና በሌሎች ተግባራት ህወሓትን ሲያገለግሉ የነበሩ ‹‹ታጋይ መነኮሳት››ን፣ ቀሳውስትንና ጥቁር ራሶችን በቤተ ክርስቲያኗ ቁልፍ ቦታዎች መሾም ከብዙ በጥቂቱ ሊጠቀሱ የሚችሉ ርምጃዎች ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ በየገዳማቱ የሚሹለከለኩ ሰላዮች፣ በየገዳማቱና አድባራቱ የሚሾሙ ካድሬዎች፣ የድርጅቶችና መመሪያዎች ቦታዎችን ከሕጋዊና ፍትሐዊ አሠራር ውጭ ለዓመታት በሓላፊነት የተቆጣጠሩና በስብከተ ወንጌል ስም የሚቀመጡ ግለሰቦች ተደማምረው ቤተ ክርስቲያኗ የፖሊቲካ አውድማ እንድትኾን ተደርጓል፡፡
 • ‹‹Open Doors፡ Serving Persecuted Christians World Wide›› የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት በተለያየ መንገድ ሰበሰብኋቸው ያላቸውን መረጃዎች በመጠቀም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማፈራረስ የነበራቸውን አቋም በሚመለከት እንዲህ ብሏል፡- ‹‹መለስ ዜናዊ የማኅበረ ቅዱሳንን እንቅስቃሴን የሚደግፉ አልነበሩም፡፡ የመለስ ሞት እምነቱን በተሐድሶ[ፕሮቴስታንታዊ ኑፋቄ] መንገድ መምራት ለሚሹ ወገኖች ትልቅ ኪሳራ አስከትሏል፡፡ መለስ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማንኮታኮት ያቀዱበት ፖሊቲካዊ ግብ፤ በቤተ ክርስቲያኗ ለመሸጉት የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆች ትልቅ ዕድል ነበር፡፡ ተተኪው ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አክራሪውን ማኅበረ ቅዱሳን የማፈራረስ አቅም ያላቸው አለመኾኑ ለተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆች ትልቅ ኪሳራ አስከትሏል፡፡››
 • ኢሕአዴግ መንግሥታዊ ሥልጣን በያዘ ማግስት ተግባራዊ ካደረጋቸው ኹነቶች መካከል የኢትዮጵያን ታሪክ ዳግም የመፃፍ ጅማሬ ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ ኢሕአዴጋዊ የታሪክ ትርክት ተምሮ እንዲያድግ ተገድዷል፡፡ በመኾኑም ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን ታሪክ የመቶ ዓመት አድርጎ ከመጻፍ በተጓዳኝ፣ የቀደሙ ነገሥታት የአንድን ብሔር የበላይነት ለማረጋገጥ የታተሩ አድርጎ ይከሣቸዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ማኅበረ ቅዱሳን ከመቶ ሺሕ በላይ የሚኾኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን በሚያስመርቅበት የግቢ ጉባኤ ትምህርት የኢትዮጵያና የቤተ ክርስቲያኗ ታሪክ የመቶ ሳይኾን ሦስት ሺሕ ዓመታት የዘለቀ እንደኾነ ያስተምራል፡፡ ኢሕአዴግ ለዓመታት የለፋበት አዲሱ የታሪክ ትርክት በወጣቶችና በምሁራን ዘንድ ተቀባይ እንዳይኾን ካደረጉት ተቋማት መካከል ማኅበረ ቅዱሳን ዋነኛው መኾኑ ጥርስ ውስጥ እንዲገባ አድርጐታል፡፡
 • ሌላው የጥላቻ ምንጭ፣ በግራ ዘመምና በቀኝ ዘመም ፖሊቲካ አስተምህሮ መካከል ያለው የልዩነት ግድግዳ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ለዘመናት ተጠብቆ የቆየውን ኢትዮጵያዊ ማንነት፣ ባህል፣ ትውፊት፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች እንዳልነበሩ የማድረግ፤ አገርን አፍርሶ የመገንባት የግራ ዘመም ፖለቲካ የሚያራምድ ፓርቲ ሲኾን፤ ከዚህ በተለየ ወጣቶች የቀደመ ማንነታቸውን፣ አስተሳሰብና ባህል ጠብቀው እንዲያቆዩ ቤተ ክርስቲያኗ (በማኅበረ ቅዱሳን አማካይነት) እያደረገች ያለችው አስተዋፅኦ በገዢዎቹ ዘንድ የሚወደድ አልኾነም፡፡ ይህን አቋሙን የሚያሳየውን አንቀጽ፣ ለዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ሥልጠና በተዘጋጀ ሰነድ ላይ በግልጽ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል፡- ‹‹አብዛኞቹ የሃይማኖት ትምህርቶች በባህልና ልምድ የሚሠሩ፣ ዓለም ከደረሰበት ዘመናዊ ሥርዓት ጋራ ተሳስረው ለሕዝቡ የማይቀርቡና ሃይማኖትኽ እንዳይነካብህ ተጠንቅቀኽ ጠብቅ የሚል ብቻ የሚያስተጋቡ ናቸው፡፡›› (ገጽ ፳፱) ከዚህ ጀርባ የማኅበረ ቅዱሳን እገዛ ከፍተኛ መኾኑ ለሥርዓቱ የሚመች አልኾነም፡፡
 • ከዚህ ቀደም ያሻቸውን ሲያደርጉ ለነበሩ ‹‹ካድሬ ካህናት›› አካሔዱ የሚመቻቸው ባለመኾኑ፤ እንደተለመደው ‹‹መንግሥታቸው›› እንዲታደጋቸው ይሻሉ፡፡ የቀድሞው ፓትርያርክ ‹‹ልጄ/አቶ መለስ እያለ ምንም አልኾንም›› ይሉት እንደነበረው ኹሉ፤ ተከታዮቻቸው መንግሥት የማኅበረ ቅዱሳንንና የጠንካራ አባላቱን አካሔድ እንዲገታላቸው ይሻሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ምርጫ በደረሰ ቁጥር የማኅበሩ አባላት ሕዝቡን ያሳምፃሉ፤ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በውስጣቸው ይዘዋል የሚሉት ክሦችና፤ ተምሯል የሚባለው የሚበዛው ኦርቶዶክሳዊ የአገሬው ልሂቅ መሰብሰቢያው እዚያ መኾኑ እንዲሁ ለሚደነብረው ኢሕአዴግ ተጨማሪ ራስ ምታት ኾኗል፡፡

(ፋክት፤ ቅጽ ፪ ቁጥር ፵፪፤ ሚያዝያ ፳፻፮ ዓ.ም.)

ሙሉነህ አያሌው

Muluneh Ayalew of FACTባሳለፍነው ሳምንት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተወካይ ባለሥልጣንና የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን በአክራሪነት ተፈርጇል ወይስ አልተፈረጀም?›› የሚለውን ውዥንብር ለመመለስ በሚሞክር መጠይቅ በአንድ የአገር ቤት ጋዜጣ ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ‹‹በየትኛውም መድረክ ላይ ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ ነው ተብሎ የተነሣበት ኹኔታ የለም›› ያሉ ሲኾን፤ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ በበኩላቸው ‹‹ማኅበሩን በይፋ (ሰረዝ ከኔ) በአክራሪነት የፈረጀው አካል የለም›› ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

የሁለቱ ተቋማት ተወካዮች የሰነዘሯቸው አስተያየቶች፣ ማኅበሩ ከመንግሥት በኩል ነፃና ገለልተኛ እንዲኾን የተፈቀደለት እንዳልኾነ ፍንጭ የሚሰጡ ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ተቋም አክራሪ ተብሎ የሚፈረጅ ሳይኾን፤ ከውስጥ ኾነው ማኅበሩን የሚዘውሩ ግለሰቦች የሚያራምዷቸው አመለካከቶች የ‹አክራሪነት› ጠባይ ያላቸው መኾኑን መንግሥት ያምናል፡፡ ይህ አመለካከት ኹለት መልክ ያለው ነው፡፡ መንግሥት ቤተ ክርስቲያኒቱን የማፍረሱን የዘመናት ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ እንዳይመች ያደረጉትን የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ነቅሶ በማውጣት በአክራሪነት መፈረጅ አንዱ ሲኾን፤ በዚህ መንገድ ማኅበሩን ከጠንካራ አመራሮቹ በመነጠል ለማደንበሽ የሚያስችል ተልእኮ ያለው ነው፡፡ ኹለተኛው አንድምታ÷ የማኅበሩን መጠሪያ ምእመኑን ለማሳት እንዳለ ጠብቆ እንዲቀጥል በማድረግ፤ ለመንግሥት ፖሊሲና ስትራተጂ የሚመቹ፣ ሃይማኖተኝነቱን ሽፋን ያደረጉ ፖሊቲከኞችን በመሰግሰግ የቤተ ክርስቲያኗን ድምፅ ማፈን ነው፡፡ መንግሥት አኹን የፈለገውና እያደረገ ያለውም ይህንኑ ነው፡፡

ማኅበሩን በይፋ አክራሪ ነው ያለ ማንም ባይኖርም የአክራሪነት ዝንባሌ ያላቸው ግለሰቦች በውስጡ መኖራቸውን መካድ የሚቻል እንዳልኾነ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል፡፡ ያለመግባባቱ መነሻም እንዲህ ዓይነት አገላለጽ መኾኑን መካድ አይቻልም፡፡ ይህን ሐሳብ ትንሽ አፍታተን ለማየት እንሞክር፡፡ ቀዳሚው ማኅበሩን የመሠረቱትን ግለሰቦች ይመለከታል፡፡

የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ ርእይና ዓላማ የተቀረፀው በነዚህ ‹‹አክራሪ›› የሚል ታፔላ በተለጠፈላቸው አመራሮች መኾኑን የማኅበሩ ምንጮች ይጠቅሳሉ፡፡ የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ የረቀቀው እነዚህ ግለሰቦች ባፈለቋቸው ተቋማዊ የአስተዳደር መርሖች ኾኖ ሳለ ድርጅቱን ከአመራሩ ነጥሎ ለማየት መሞከር ጤናማ አይደለም፡፡

መንግሥት እንደሚለው ግለሰቦቹ በርግጥም የአክራሪነት ዝንባሌና ድርጊት የሚታይባቸው ከኾኑ ድርጅቱ የሕገ ወጥ አባላት መሸሸጊያ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ መንገድ አንድን ተቋም በተጨባጭ ለመወንጀል ቀላሉ መንገድ ማስረጃዎችን ይዞ ለፍርድ ማቅረብ ነው፡፡ ጥያቄው ግን ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ ማስረጃዎች መንግሥት አለው? ‹‹ሕግና ፍትሕ›› ባለበት አገር ወንጀለኛ (በተለይ ደግሞ የእምነት አክራሪነትና ጽንፈኝነት) ዓይቶ እንዳላየ የሚያልፍ ‹‹ልበ ሰፊ›› መንግሥት ከወዴት ተገኘ? የሚል ይኾናል፡፡

ይህን ጉዳይ በሚመለከት (ምንም እንኳ ጉዳዩ ከረር ያለ ኾኖ ሳለ ነገሩን አለሳልሰው ያለፉት) አስተያየታቸውን የሰጡት የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ፤ ኢሕአዴግ በተለያዩ አጋጣሚዎች ማኅበሩን እንደ ማኅበር ሳይቀር አክራሪ እንዳለው ቢያውቁም፤ ‹‹መንግሥት ማኅበሩ አክራሪ ነው›› የሚል አስተያየት አልሰጠም ለማለት ሞክረዋል፡፡ ዋና ጸሐፊው ‹‹መንግሥት ማኅበሩን በይፋ አክራሪ ነው አላለም›› በምትለው ንግግራቸው ውስጥ ‹‹በይፋ›› የምትለው ቃል ሰፊ ትርጉም ተሸክማ እናገኛታለን፡፡ መንግሥት አንድን ተቋም ‹‹አክራሪ ወይም አሸባሪ ነው›› ብሎ ለማስፈረጅ ‹‹በይፋ›› መናገር አለበት የሚል የፖሊቲካ ትርጉም አለው፡፡ ተቋማትን አክራሪ አድርጎ ለመፈረጅ ለስሙም ቢኾን የፓርላማን ይኹንታ ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡ ዋና ጸሐፊው ሊሉ የፈለጉትም ይህንኑ ሊኾን ይችላል፡፡ መንግሥት ማኅበሩን በፓርላማ አቅርቦ አክራሪ ነው ብሎ በይፋ አለማስፈረጁ፤ ከዚህ ቀደም በተለያዩ መድረኮች ማኅበሩ አክራሪ ነው ብሎ የተናገረውን ቃል የሚያሽር አይደለም፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቷን እና ሥርዓቷን ማፍረስ

ህ.ወ.ሓ.ት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከጥንት ጀምሮ የማፍረስ ዕቅድ የነበረው ለመኾኑ ከድርጅቱ መሥራቾች አንዱ ከነበረው ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በላይ ምስክር ማቅረብ የሚያሻ አይደለም፡፡ የቀድሞው የህወሓት መሥራች ታጋይ ለዶክትሬት ድግሪ ማሟያው “A Political History Of TPLF; Revolt, Ideology And Mobilization In Ethiopia” በሚል ርእስ በሰየሙት ጥናታዊ ጽሑፋቸው ይህን እውነት በደንብ ይገልጹታል፡፡ በተለይ ጥናታዊ ጽሑፉ ከገጽ 300 ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኗን ክፉኛ የማብጠልጠል አመለካከት እንደነበር ያመለክተናል፡፡ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ከቀድሞዎቹ መንግሥታት ጋራ በነበራት ቁርኝት ከገዢው መደብ ጋራ የተሰናሰለ የጥቅም እና የጨቋኝነት ግንኙነት ነበራት›› በሚል የሚጀምረው ማብጠልጠል በሌላ መልኩ ከዚህ ቀደም የነበሩ መንግሥታት ሕዝቡን የጨቆኑትን ያህል ቤተ ክርስቲያንም የራሷን ድርሻ እንደምትወስድ ይገልጻል፡፡

በመኾኑም ታጋዮቹ የመንግሥትነት ሥልጣንን ሲቆናጠጡ ቤተ ክርስቲያንን የማጥቃት የቀደመ ሕልማቸውን አሐዱ አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ቀደም ይዛ የነበረውን መሬት መንጠቅ፣ በግፍ የተነጠቀቻቸውን ቤቶችና ሕንፃዎች አሟልቶ አለመመለስ፣ ቤተ ክርስቲያኗ በማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተለይም የማስታረቅና ግጭቶችን በሰላም የመፍታት ተልእኮዋን በመንጠቅ አዲስ ለተመሠረቱት ፖሊቲካዊ ማኅበራት መስጠት፤ ከዚኽም ባሻገር ከትጥቅ ትግል አንሥቶ በስለላና በሌሎች ተግባራት ህወሓትን ሲያገለግሉ የነበሩ ‹‹ታጋይ መነኮሳት››ን፣ ቀሳውስትንና ጥቁር ራሶችን በቤተ ክርስቲያኗ ቁልፍ ቦታዎች መሾም ከብዙ በጥቂቱ ሊጠቀሱ የሚችሉ ርምጃዎች ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ በየገዳማቱ የሚሹለከለኩ ሰላዮች፣ በየገዳማቱና አድባራቱ የሚሾሙ ካድሬዎች፣ የድርጅቶችና መመሪያዎች ቦታዎችን ከሕጋዊና ፍትሐዊ አሠራር ውጭ ለዓመታት በሓላፊነት የተቆጣጠሩና በስብከተ ወንጌል ስም የሚቀመጡ ግለሰቦች ተደማምረው ቤተ ክርስቲያኗ የፖሊቲካ አውድማ እንድትኾን ተደርጓል፡፡

እነዚህንና መሰል ዕቅዶች ተግባራዊ የተደረጉት፣ የቤተ ክርስቲያንን መንበር መጨበጥ ከተቻለ በኋላ ነው፡፡ ለዚህም የብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ከመንበሩ መነሣትና ድርጅቱን ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ከውጭ አገር ገንዘብ በመሰብሰብ ሲያግዙ የቆዩትን የቀድሞውን ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ በመተካት ተጀመረ፡፡ መንበሩ አስተማማኝ መኾኑን ካረጋገጡ በኋላ የተካሔደው፣ መድረኮችን በመጠቀም እንደተለመደው የ‹‹አማራንና የቤተ ክርስቲያንን›› አገዛዝ አጣምሮ በመተረክ የጥላቻ ፖሊቲካ በሌሎቹ ዘንድ መንዛት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗን የአንድ ብሔር መገለጫ በማድረግ አገራዊ ትስስሯ/ማስተሳሰርያነቷ እንዲላላና እንዲበጠስ ማስቻል ሌላኛው ተልእኮ ነበር፡፡ እነዚህ ተረኮች መሠረት የሌላቸውና ኾን ተብለው የተቀነባበሩ ለመኾናቸው የቀድሞው የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ ምስክር ናቸው፡፡

ሚኒስትሩ ‹‹ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ አንድነት በኢትዮጵያ›› የሚል ጥራዝን እንደ መነሻ በመውሰድ በፕላዝማ ባደረጉት ገለጻ (በተለይ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል መድረኮች) ‹‹ሲገዛኽ የኖረው የሰሜን ኦርቶዶክሳዊ ነፍጠኛ ነው፤ ቤተ ክርስቲያኗም የእነርሱ ብቻ ናት…›› የሚል ንግግር በማሰማት እሳት ለመጫር ሞክረው ነበር፡፡ በወቅቱ የተናገሩትን ንግግር መሠረት በማድረግ ከ‹ሐመር› መጽሔት (ኅዳር/ታኅሣሥ ፲፱፻፺፰ ዓ.ም.) ጋራ ያደረጉት ቃለ ምልልስ ጉዳዩን ጠብ ከመጫር ውጭ የሚያምኑበት አለመኾኑን የሚያመላክት ነበር፡፡

ሐመር፡- ‹‹የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የነፍጠኛው የአማራና የጉራጌ ሃይማኖት ብቻ ነው›› ብለው መናገርዎ…
አቶ ተፈራ፡- የአማራና የጉራጌ የሚባለውን ደግሞ ከተመቻችኹ በሌላ ጊዜ እንወያያለን፤ የሚቀላችኹ መጽሐፍ አለ፤ መጽሐፉን ሔዳችኹ ማንበብ ነው፡፡
ሐመር፡- ይህን የመጨረሻ ጥያቄአችን ቢያደርጉልን ክቡር ሚኒስትር
አቶ ተፈራ፡- የለም፣ የለም በጣም አመሰግናለሁ፣ ፕሮግራም ስላለኝ ነው አንተ ጥያቄ እየጠየቅኽ መልስ ሳይኾን የምትፈልገው ለማሳመን ነው የምትሞክረው…
(በቃለ መጠይቁ መግቢያ ላይ ‹‹የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋዜጠኞች ይፈልጉኻል›› ስባል ደስ ስላለኝ ነው ያገኘኋችኹ›› ያሉት የቀድሞ ሚኒስትር ጥያቄዎቹ ሲጠጥሩባቸው የመረጡት በዚኽ መንገድ ማቆምን ነበር፡፡)

እነዚህን አፍራሽ መንግሥታዊ ተልእኮ በመመከት ረገድ ማኅበረ ቅዱሳን የተጫወተው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በመኾኑም መንግሥት ማኅበሩን አስቀድሞ ካላከሸፈ በስተቀር የረዥም ጊዜ ሕልሙ ሊሳካ የሚችል አይመስልም፡፡ ይህን ሐሳብ ወደ ኋላ እመለስበታለኹ፡፡ በርግጥ ማኅበረ ቅዱሳን በመንግሥት ዓይን አክራሪ ነው ወይስ አይደለም? አክራሪ ተብሏል ወይስ አልተባለም? የሚለውን አስቀድመን እንይ፡፡

አክራሪው ማነው?

አንድን የእምነት ተቋም አክራሪ ነው ወይስ አይደለም? ብሎ ለመፈረጅ ሦስት መሠረታዊ የሕግ ጥሰቶች ሊኖሩ እንደሚገባ መንግሥት ይደነግጋል፡፡ የአክራሪነት (የጽንፈኛነት) አመለካከትም የሚከተሉትን የሕግ መሠረቶች ካለማክበር የሚመነጩ እንደኾኑ ሕገ መንግሥቱ ላይ ተቀምጧል፡፡

እነዚህ ‹‹የዜጐችን የሃይማኖትና የእምነት ነፃነት በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስ (አንቀጽ ፳፯)፤ የሃይማኖት እኩልነትን በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስ (አንቀጽ ፳፭) እና መንግሥታዊ ሃይማኖት ወይም ሃይማኖታዊ መንግሥት በአገራችን ለመመሥረት መንቀሳቀስ (አንቀጽ ፲፩)›› የሚሉት አንቀጾች ተቋምን በአክራሪነት ለማስፈረጅ በቂ እንደኾኑ ትርጓሜ ተሰጥቷቸዋል፡፡ አንድን የእምነት ተቋም አልያም የእምነት ድርጅት አክራሪ ብሎ ለመፈረጅ እኒህን ሦስት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች የመጣስ ኹኔታዎች መሟላት እንዳለባቸው መንግሥት ይጠቁማል፡፡ መንግሥት እነዚህን መስፈርቶች ከግምት ውስጥ አስገብቶ ይኹን አይኹን ባይታወቅም ማኅበረ ቅዱሳንን በግልጽ አክራሪ ያለበትን ማስረጃ ማሳየት ይቻላል፡፡

ማሳያ – ፩

mahibere kidusan‹‹የሃይማኖት አክራሪነትና የፀረ – አክራሪነት ትግላችን›› በሚል ርዕስ በ፳፻፬ ዓ.ም. ለኢሕአዴግ አመራር አባላት ሥልጠና የቀረበ ጥራዝ፤ ከኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች መካከል መንግሥት አክራሪ ብሎ የፈረጃቸው አካላት መኖራቸውን ያትታል፡፡ ‹‹በኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ማዕቀፍ የአክራሪነትና የጽንፈኝነት አመለካከትና ተግባር እየተንጸባረቀ የሚገኘው በማኅበረ ቅዱሳን አደረጃጀት ነው›› (አጽንዖት የኔ) በማለት ፍረጃውን የሚጀምረው ይህ ጥራዝ በምክንያትነት ያቀረባቸው ኹለት ነጥቦች እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡ መንግሥት የማኅበሩ ልሳን የኾኑት ‹‹ስምዐ ጸድቅ›› ጋዜጣና ‹‹ሐመር›› መጽሔት፣ ሕዝብንና መንግሥትን የሚያጋጩ አፍራሽ መልእክቶች በማስተላለፍ ሕዝብ መንግሥትን በጥርጣሬ እንዲያይ አድርገውታል ይላል፡፡ መንግሥት ይህን ፍረጃ ያጠናክራሉ ያላቸውን ኹለት ማሳያዎች አቅርቧል፡፡ ማኅበሩ ‹‹መንግሥት አክራሪዎችን በማሥታገስ እንጂ በመዋጋት አልሠራም፡፡ በመቻቻል ስም ታሪክ መጥፋት ወይም መጥቆር የለበትም›› የሚሉ ማኅበሩ ያነሣቸውን ነጥቦች ማሳያ አድርጎ አቅርቧል፡፡ እነዚህ ኹለት ነጥቦችም ማኅበሩ በመንግሥት ዓይን አክራሪ ተብሎ ለመፈረጅ የተገኙ ማስረጃዎች ኾነው ቀርበዋል፡፡

‹‹መንግሥት አክራሪዎችን በማሥታገስ እንጂ በመዋጋት አልሠራም›› የሚለው የማኅበሩ አቋም መልሶ ማኅበሩን እንዴት አክራሪ ሊያስብለው እንደሚችል ግልጽ አይደለም፡፡ መንግሥት ይህን የማኅበሩን መልእክት አልቀበልም ማለቱ ሲተረጐም ያለው አንደምታ አንድ ብቻ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪነትን ‹‹ከመታገሥ›› ይልቅ ‹‹መዋጋት›› ተገቢ ነው የሚል አቋም ሲይዝ፤ መንግሥት በበኩሉ አክራሪነትን ‹‹መዋጋት›› ሳይኾን ‹‹መታገሥ›› ይገባል የሚል የተቃረነ እምነት ያለው መኾኑን ከማሳየት የዘለለ ትርጉም አይሰጥም፡፡

የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ ‹‹ማኅበሩ በማንኛውም የፖሊቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት አይኖረውም›› የሚለውን አቋም፣ መንግሥት ጠምዝዞ ‹‹ቤተ ክርስቲያንና ገዳማትን ለፖሊቲካ ጥቅም ማዋል፤ ከተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶች ጋራ በመተሳሰር ፀረ መንግሥት ቅስቀሳና አድማ የማስተባበር ሥራ ይሠራል›› በሚል ማኅበሩን በሰነዶቹ ይከሥሳል፡፡ መንግሥት ማኅበሩን ለመፈረጅ የሚያበቃ ማስረጃ ያለው ባይኾንም ተቋሙን እያብጠለጠለ ያለበት ክሥ ዝርዝር ሲጠቃለል አራት መሠረታዊ አዕማድ አሉት፡፡ ማኅበሩ ‹‹በዋነኝነት ወጣቶች ላይ አተኩሮ ይሠራል፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችንና መምህራንን ይመለምላል፤ የተቃዋሚ ፖሊቲካ ድርጅቶች አባላትን በውስጡ ይዟል፤ ያለፉት ሥርዓቶች ባለሥልጣናትንና ደጋፊዎችን በውስጡ ይዟል›› የሚሉት መኾናቸውን እንገነዘባለን፡፡

ማሳያ – ፪

‹‹አክራሪነት/ጽንፈኝነት ዝንባሌዎችና መፍትሔዎቻቸው›› በሚል ርእስ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር በኾኑት በዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም ነሐሴ/፳፻፭ ዓ.ም በቀረበ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ፤ ማኅበሩ አክራሪ ተብሎ ለመፈረጁ ሌላ ማሳያ ይኾናል፡፡ ኃምሳ ገጾች ባለው በዚህ ጥራዝ ውስጥ፣ የአክራሪነትና ጽንፈኛነት እንቅስቃሴ በዋናነት የሚታየው በተለያዩ ማኅበራት አደረጃጀት ውስጥ ራሳቸውን ደብቀው የሚሠሩ ግለሰቦችና ቡድኖች መኾናቸውን ኢሕአዴግ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ጉዳዩ ‹‹እንዲህ የሚሉ አሉ›› የሚል አሉባልታ መነሻ ያደረገ ከመኾን የዘለለ ማስረጃ የሚያስቀርብ አይደለም፡፡ ለዚኽም ኹለት ዐረፍተ ነገሮችን ከጥራዙ እንጥቀስ፤ ‹‹አንዳንድ መግለጫዎችን ስንመለከት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት የሃይማኖታችንን ክብር፣ ሞገስና ታሪክ ቀንሷል በሚል የሚያስተጋቡ አሉ፡፡›› (ገጽ ፳፯)

‹‹የሃይማኖቶች እኩልነትና መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለው መርሕ ( አክራሪ ተብለው ከሚያስፈርጁ ድንጋጌዎች መካከል መጠቀሱን ሳንዘነጋ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ክብርና ሞገስ፣ ታሪክና ጥቅም የነፈገ አድርገው የሚያስተጋቡ ግለሰቦችና ቡድኖች አሉ፡፡›› (ገጽ ፴)

መንግሥት ለእነዚህ ችግሮች ምክንያት ነው ካላቸው ነጥቦች መካከል የሃይማኖት ዕውቀት ክፍተትን የሚሞላ የተማረ የሰው ኃይል እየተሟጠጠ በመሔዱ እንደኾነ ያትታል፡፡ ይህ ክፍተት የእምነት ተቋማት ከሌላ አገር ለሚመጡ ሰባክያንና አስተሳሰባቸው ተጋላጭ እንዲኾኑ እንዳደረጋቸውና የአክራሪነት መንፈስም በቀላሉ ፈር ሊይዝ እንደቻለ ይገልጻል፡፡

ማሳያ – ፫

ሌላው የአክራሪነት ማሳያ ማኅበሩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በግቢ ጉባኤ የሚያስተምርበት መንገድ አክራሪ ለመባል ያበቃው እንደኾነ የሚያትት ነው፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች በማኅበሩ ሥር ታቅፈው መንፈሳዊ አገልግሎት ማግኘታቸው ለአክራሪነት መነሻ ምክንያት ተደርጎ ለመጠቀሱ ሌላ ጥራዝ እንጥቀስ፡፡

‹‹የብዝኃነት አያያዝ፣ የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ዝንባሌዎችና መፍትሔዎች›› በሚል ርእስ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በ፳፻፮ ዓ.ም ለዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ሥልጠና ባዘጋጀው ሰነድ ይህን አመለካከት ሲኮንነው ይስተዋላል፡- ‹‹ዩኒቨርስቲዎችን የሃይማኖት መምህራን መመልመያና ማስታጠቂያ መድረክ አድርጐ የመጠቀም ዝንባሌ ውሎ ሲያድር ዩኒቨርስቲዎች ከተቋቋሙባቸው ዓላማ እያወጡ ብቁ ዜጋን የማፍራት አገራዊ ግብ የሚያሰናክል ሂደት ነው፤›› (ገጽ ፲፯) በማለት ማኅበሩ ዩኒቨርስቲዎች የተቋቋሙለትን የጥናትና ምርምር ዓላማ ግቡን እንዳይመታ በማድረግ፤ የትምህርት ጥራትን በእጅጉ የሚጎዳ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደኾነ ይከሣል፡፡

ጉዳዩ ይበልጥ ግራ የሚያጋባውና በርግጥም ማኅበሩ ያደረገውን እንቅስቃሴ አፍራሽ ነው የሚለውን የኢሕአዴግ ክሥ እንዳናምን የሚያደርገን፤ መፍትሔ ብሎ ያስቀመጠውን ሐሳብ በመተቸት፣ ከተነሣበት ሐሳብ ጋራ ፈጽሞ የተቃረነ ለመኾኑ እዚያው ጥራዝ ላይ መመልከታችን ነው፡፡ ኢሕአዴግ ለችግሩ መፍትሔ ብሎ ያስቀመጠው ‹‹ሃይማኖታዊ የወጣት፣ የሴቶች፣ የምሁራን አደረጃጀቶች ተፈጥረው ራሳቸውንና ሌላውን ተከታይ በተደራጀ ኹኔታ የተሟላ ሃይማኖታዊ ዕውቀት እንዲኖራቸው፣ ከአሉባልታዎች እንዲጠበቅና የአክራሪነት አመለካከትና ተግባር የሚታገል አቅም ኾኖ እንዲደራጅ መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ ተጠሪነታቸው በየራሳቸው የሃይማኖት ተቋም በማድረግ ሕገ መንግሥታዊ፣ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲኾኑ መደገፍ ይቻላል፡፡›› (ገጽ ፳፱) ካድሬ ካህናትን ማፍራት ማለት እንግዲህ እንዲህ ነው፡፡

ማኅበሩን ማፍረስ ለምን አስፈለገ?

‹‹Open Doors፡ Serving Persecuted Christians World Wide›› የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት በተለያየ መንገድ ሰበሰብኋቸው ያላቸውን መረጃዎች በመጠቀም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማፈራረስ የነበራቸውን አቋም በሚመለከት እንዲህ ብሏል፡- ‹‹መለስ ዜናዊ የማኅበረ ቅዱሳንን እንቅስቃሴን የሚደግፉ አልነበሩም፡፡ የመለስ ሞት እምነቱን በተሐድሶ[ፕሮቴስታንታዊ ኑፋቄ] መንገድ መምራት ለሚሹ ወገኖች ትልቅ ኪሳራ አስከትሏል፡፡ መለስ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማንኮታኮት ያቀዱበት ፖሊቲካዊ ግብ፤ በቤተ ክርስቲያኗ ለመሸጉት የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆች ትልቅ ዕድል ነበር፡፡ ተተኪው ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አክራሪውን ማኅበረ ቅዱሳን የማፈራረስ አቅም ያላቸው አለመኾኑ ለተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆች ትልቅ ኪሳራ አስከትሏል፡፡››

ኢሕአዴግ ማኅበረ ቅዱሳን ህልውናውን የተነጠቀ ባዶ ቀፎ እንዲኾን የሚፈልግበት በርካታ ምክንያት ያለው ቢኾንም እዚኽ ላይ ማቅረብ የሚቻለው የተወሰኑትን ብቻ ይኾናል፡፡ በመኾኑም ‹‹ወጣቶችን ያደራጃል›› የሚለው የኢሕአዴግ ክሥ ውስጡ ሲፈተሽ፣ ማኅበሩ ከኢሕአዴግ ርእዮተ ዓለም በተቃራኒ የሚቆሙ ወጣቶች ልብ እያሸፈተ ይገኛል የሚል አንድምታ አለው፡፡ አንድምታዎቹ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሚታገለው ኢሕአዴግና የአገሪቷን ህልውና ለመታደግ የበኩሉን በሚታትረው ማኅበር መካከል የሚዋልሉ ናቸው፡፡

ኢሕአዴግ መንግሥታዊ ሥልጣን በያዘ ማግስት ተግባራዊ ካደረጋቸው ኹነቶች መካከል የኢትዮጵያን ታሪክ ዳግም የመፃፍ ጅማሬ ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ ኢሕአዴጋዊ የታሪክ ትርክት ተምሮ እንዲያድግ ተገድዷል፡፡ በመኾኑም ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን ታሪክ የመቶ ዓመት አድርጎ ከመጻፍ በተጓዳኝ፣ የቀደሙ ነገሥታት የአንድን ብሔር የበላይነት ለማረጋገጥ የታተሩ አድርጎ ይከሣቸዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ማኅበረ ቅዱሳን ከመቶ ሺሕ በላይ የሚኾኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን በሚያስመርቅበት የግቢ ጉባኤ ትምህርት የኢትዮጵያና የቤተ ክርስቲያኗ ታሪክ የመቶ ሳይኾን ሦስት ሺሕ ዓመታት የዘለቀ እንደኾነ ያስተምራል፡፡ ኢሕአዴግ ለዓመታት የለፋበት አዲሱ የታሪክ ትርክት በወጣቶችና በምሁራን ዘንድ ተቀባይ እንዳይኾን ካደረጉት ተቋማት መካከል ማኅበረ ቅዱሳን ዋነኛው መኾኑ ጥርስ ውስጥ እንዲገባ አድርጐታል፡፡

ሌላው የጥላቻ ምንጭ፣ በግራ ዘመምና በቀኝ ዘመም ፖሊቲካ አስተምህሮ መካከል ያለው የልዩነት ግድግዳ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ለዘመናት ተጠብቆ የቆየውን ኢትዮጵያዊ ማንነት፣ ባህል፣ ትውፊት፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች እንዳልነበሩ የማድረግ፤ አገርን አፍርሶ የመገንባት የግራ ዘመም ፖለቲካ የሚያራምድ ፓርቲ ሲኾን፤ ከዚህ በተለየ ወጣቶች የቀደመ ማንነታቸውን፣ አስተሳሰብና ባህል ጠብቀው እንዲያቆዩ ቤተ ክርስቲያኗ (በማኅበረ ቅዱሳን አማካይነት) እያደረገች ያለችው አስተዋፅኦ በገዢዎቹ ዘንድ የሚወደድ አልኾነም፡፡ ይህን አቋሙን የሚያሳየውን አንቀጽ፣ ለዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ሥልጠና በተዘጋጀ ሰነድ ላይ በግልጽ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል፡- ‹‹አብዛኞቹ የሃይማኖት ትምህርቶች በባህልና ልምድ የሚሠሩ፣ ዓለም ከደረሰበት ዘመናዊ ሥርዓት ጋራ ተሳስረው ለሕዝቡ የማይቀርቡና ሃይማኖትኽ እንዳይነካብህ ተጠንቅቀኽ ጠብቅ የሚል ብቻ የሚያስተጋቡ ናቸው፡፡›› (ገጽ ፳፱) ከዚህ ጀርባ የማኅበረ ቅዱሳን እገዛ ከፍተኛ መኾኑ ለሥርዓቱ የሚመች አልኾነም፡፡

ተኛው ነጥብ፥ የውስጥና የውጭ ካድሬዎች የፈጠሩት ኅብረት ነው፡፡ ከትጥቅ ትግል አንሥቶ ህወሓትን ሲያገለግሉ ከቆዩ መነኰሳት፣ ቀሳውስትና ጥቁር ራሶች መካከል ጥቂት የማይባሉት ፓርቲው ሥልጣን ከያዘ በኋላም በድርጅቶችና መምሪያዎች፣ በየአህጉረ ስብከቱ፣ በየአድባራቱና ገዳማቱ በመሰግሰግ የግል ጥቅማቸውን እያሳደዱ ይገኛሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስትዘረፍ የሚዘርፉ፤ በደል ሲፈጸም ከጀርባ ኾነው የሚያበረታቱና ፍጹም ሃይማኖታዊ ምግባር የሌላቸውን ግለሰቦች ለማስቆም ብሎም ጠንካራ መዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር ለመዘርጋት ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታደርገውን ጥረት የማኅበሩ አባላት በሚደረግላቸው ጥሪና በሚሰጣቸው ግዳጅ መሠረት በተለያየ መንገድ እያገዙ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ያሻቸውን ሲያደርጉ ለነበሩ ‹‹ካድሬ ካህናት›› አካሔዱ የሚመቻቸው ባለመኾኑ፤ እንደተለመደው ‹‹መንግሥታቸው›› እንዲታደጋቸው ይሻሉ፡፡ የቀድሞው ፓትርያርክ ‹‹ልጄ/አቶ መለስ እያለ ምንም አልኾንም›› ይሉት እንደነበረው ኹሉ፤ ተከታዮቻቸው መንግሥት የማኅበረ ቅዱሳንንና የጠንካራ አባላቱን አካሔድ እንዲገታላቸው ይሻሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ምርጫ በደረሰ ቁጥር የማኅበሩ አባላት ሕዝቡን ያሳምፃሉ፤ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በውስጣቸው ይዘዋል የሚሉት ክሦችና፤ ተምሯል የሚባለው የሚበዛው ኦርቶዶክሳዊ የአገሬው ልሂቅ መሰብሰቢያው እዚያ መኾኑ እንዲሁ ለሚደነብረው ኢሕአዴግ ተጨማሪ ራስ ምታት ኾኗል፡፡ ምርጫ 97ን ኢሕአዴግ የገመገመበት ሰነድ ይህን እውነት እንደሚያስረዳ ተዘግቧል፡፡

ኢሕአዴግ እንዳሰበው ማኅበሩ ላይ ጣቱን መቀሰሩ በቀላሉ የማይወጣው አሳር ውስጥ ሊከተው የሚችል ለመኾኑ ከሰሞኑ ግምገማ የተገነዘበ ይመስላል፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ትኩሳት በመጫርና በማብረድ የማይመለስ ማዕበል ተነሥቶ ሥልጣኑን የሚጠራርግ ሕዝባዊ አብዮት ሊነሣ እንደሚችል ሳያውቅ የቀረ አይመስልም፡፡

Advertisements

10 thoughts on “ማኅበረ ቅዱሳንን የማፍረስ አደገኛው ተልእኮ

 1. Kebede April 19, 2014 at 9:01 pm Reply

  “እነዚህንና መሰል ዕቅዶች ተግባራዊ የተደረጉት፣ የቤተ ክርስቲያንን መንበር መጨበጥ ከተቻለ በኋላ ነው፡፡ ለዚህም የብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ከመንበሩ መነሣትና ድርጅቱን ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ከውጭ አገር ገንዘብ በመሰብሰብ ሲያግዙ የቆዩትን የቀድሞውን ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ በመተካት ተጀመረ፡፡ መንበሩ አስተማማኝ መኾኑን ካረጋገጡ በኋላ የተካሔደው፣ መድረኮችን በመጠቀም እንደተለመደው የ‹‹አማራንና የቤተ ክርስቲያንን›› አገዛዝ አጣምሮ በመተረክ የጥላቻ ፖሊቲካ በሌሎቹ ዘንድ መንዛት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗን የአንድ ብሔር መገለጫ በማድረግ አገራዊ ትስስሯ/ማስተሳሰርያነቷ እንዲላላና እንዲበጠስ ማስቻል ሌላኛው ተልእኮ ነበር፡፡ እነዚህ ተረኮች መሠረት የሌላቸውና ኾን ተብለው የተቀነባበሩ ለመኾናቸው የቀድሞው የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ ምስክር ናቸው፡፡” እንከን የለሺ ጽሑፍ ነው። ሐቁን የሚያሳይ ማጉያ መነፀር ነው !

 2. Birhan Bihil April 20, 2014 at 2:42 am Reply

  ጎልያድም ኃይል የእግዚአብሔር መሆኑን ዘንግቶ እንዲሁ በአደባባይ…. የእግዚአብሔር ወዳጅን ሊያጠፋ/ሊጥል ዝቶ ነበር…. ግን እራሱ ተዘረረ እንጂ…. እነዚህ ደግሞ የት አካባቢ የት ሰፈር ያለውን ማኀበረ ቅዱሳን ነው የሚያፈርሱት…. አወዳደቄን/አሟሟቴን አሳምርልኝ ቢሉ ይሻላቸዋልIIIII

 3. Anonymous April 21, 2014 at 7:06 am Reply

  በእግዚአብሂር እንጂ በእብሪት በሰራዊት ብዛት መደገፍ ለየትኛዉም አገር መንግስት እንዳልበጀ /እንደማይበጅ/ ከመፅሀፍ ቅዱስ መማርተገቢ ነዉ!

 4. oyared April 21, 2014 at 8:27 am Reply

  ኢህአዴግ ዝም ብሎ ባይደነብር ይሻለው ነበር፡ ፓትርያርኩንም በተላላኪዎቹ በኩል የያዛቸው ይመስላል እርሳቸውም ማኀበሩን ለማዳከም እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ይሰማል ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ብታሳውቁን

 5. Getu April 21, 2014 at 9:15 am Reply

  የፌዴራል ጉዳዮች መሰረታዊ ችግር የጥናታዊ ጽሁፍ መስፈርት ያላJሉ፤ በአሉባልታ የታጨቁ፤ ገለልተኛ ያልሆኑ የደህንነት አካላትን (በቤተክርስትያኗ ላይ መሰረታዊ ተቃርኖ ባላቸው ፖለቲከኞች የሚዘወሩ) እንዲሁም የማኅበሩ የኃይማኖት ማለትም የኦርቶዶክስ ተከላካይነት አላነቃንቅ ያላቸው የውስጥ ና የውጭ አካላትን በተለይም የሙሰኞችና «የተኃድሶ» አራማጆች ጥምረትን በመረጃ ምንጭነት የሚጠቅሱ «ጥናታዊ ጽሁፍ »ተብለው በየመድረኩ የሚቀርቡ አሳፋሪ ይዘት ያላቸው ሰነዶችን እንደ መነሻ መጠቀሙ ነው!

 6. በአማን ነጸረ April 21, 2014 at 10:19 am Reply

  ፖለቲከኞችን ለምን እንደስጋት እንደምታዩአቸው አይገባኝም!!የማኅበረቅዱሳን ትልቁ ስጋት ኢህአዴግም፣ቤ/ክህነትም፣ቤተመንግስትም፣አይደለም፡፡የማኅበሩ ስጋት፡
  (1) አመራሩ፡
  የአመራረሩ ውስጡን ከመፈተሸ ይልቅ ችግሮች ሁሉ ከውጭ እንደሚመነጩ እና ይህም መልካም ስራን በማይወዱ የቤተክህነቱና የቤተመንግስቱ ኢህአዴጋውያን የመጣ እያስመሰለ አለባብሶ ማረስ ማብዛቱ ነው፡፡ይሄ ችግር ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ስለሆነ በአንድ ጊዜ የሚወገድ አይመስለኝም፡፡ጠላት በማብዛት ሳይሆን ውስጥን በመፈተሸ ብዙ ወዳጆችን የሚስብ ሩቅ አሳቢ አመራር እስኪመጣ ድረስ ይቆያል፡፡እስከዚያው የማኅበሩ ጦስ ለሲኖዶሱም ተርፎ ፈተናው ከጋዜጣ ወደምንወዳት ቤ/ክ እንዳይተላለፍ አምላከ ቤ/ክ ይርዳን፡፡
  (2) የተወሰኑ ተራ አባላት፡
  ሌላው ስጋት ጥቂት የማይባሉ አባላቱ በየአቅጣጫው የሚቀርብላቸውን የማኅበሩን በጽድቁ መፈተን የሚተርኩ ዕቡይ ዜናዎች ያለምንም ማጣራት እንደትምህርተ ሃይማኖት እንደወረዱ ተቀብለው አሜን…አሜን ማለታቸው ነው፡፡አመራሩም ሆነ አባላቱ የቅኝት ለውጥ ማድረግ አልፈለጉም፡፡እዛው አቡነ ጳውሎስ ዘመን ላይ እንደተቀረቀሩ ናቸው፡፡አልወጡም፡፡የቤተክርስቲያንን በጎ ገጽታዎች ከማንጸባረቅ ይልቅ ዛሬም ክፉ ክፉውን ብቻ በመንቀስ እንደ ደሃ አደግ(ዕጓለማውታ) ማላዘኑን መርጠዋል፡፡የቅኝት ችግር ነው፡፡ወጣቶች በአጉል የአውሮፓ ኳስ ተሰልበው ልባቸው ወደ ውጭ እንዳይኮበልል ይይዝልናል ያልነው ማኅበር ልጆቻችንን ዳግም የግብጽ የመንፈስ ቅኝ ተገዥ አድርጎ አውጥቷቸዋል፡፡ስለዚህ በግብጽ የሆነው ሁሉ በኢ/ያ ካልሆነ የሚል ፈሊጥ አምጥተው ሲቃዡ ይውላሉ፡፡ማኅበራቸውን አጠፋህ ያለ ሁሉ መናፍቅ እና ካድሬ ይመስላቸዋል፡፡ይሄ አመለካከት በራሱ በኦርቶዶክሳዊም ሆነ በፖለቲካዊ ሚዛን አክራሪ ባያሰኝ ጭፍን ሊያስብል እንደሚችል አልተገነዘቡም፡፡እናም ማኅበሩ ወደቀ ሲል ተሰበረ እያሉ ማኅበሩን በኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት ቦታ አግብተውት 18ቱን መምሪያዎችና 3 ኮሚሽኖችን ያቀፈውን ጠቅላይ ቤተክህነት ለአንድ ለአቅመ-መምሪያ ያልደረሰ ማኅበር ሰውተው ሲራቀቁ ይውላሉ፡፡ከሲኖዶስ ቀድመው ያወግዛሉ፣ከፍርድ ቤት ቀድመው ይወነጅላሉ፡፡እንደ እውነቱ ደግሞ ብዙዎቹ አባላት እንዲህ ለማለት የሚያስችል ያን ያህል የጠለቀ ሃይማኖታዊ እውቀት ያላቸው አይደሉም፡፡እርግጥ ኦርቶዶክሳዊ ቀናኢነታቸውን እመሰክራለሁ፡፡ሆኖም ማስተዋል ያልታከለበት ቀናኢነት ስንዴውን ከእንክርዳዱ ጋር ለመንቀል እንደሚዳረግ አልተረዱም፡፡ያ ደግሞ አደጋ ነው፡፡የሆታ ቡድን መሆን ነው፡፡
  (3) አደረጃጀቱና ተጠሪነቱ፡
  ቤተክህነት ማኅበረቅዱሳንን የሚያውቀውም ሆነ የሚቆጣጠረው ማኅበሩ ባስመረለት ልክ ነው፡፡ያ መስመር ከታለፈ በማዕከሉ የተጠራቀሙ አሸማቃቂ የጽርፈት ሰይፎችና ፍረጃዎች በቤተክህነቱ ላይ እንደተቋምና ግለሰብ ይመዘዛሉ፡፡ስለሆነም አሁን ባለው ሁኔታ በሚዲያና በነባር አባላቱ ተጽእኖ ፈጣሪነት በወሬ ካልሆነ በቀር በተግባር በቤተክህነት ስር ያለ ተቋም ከመምሰል ወደ ቤተክህነት ተገዳዳሪነት ተለውጧል፡፡ተጠሪነቱም አንድ ጊዜ ለሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሌላ ጊዜ ለብጹዕ ስ/አስኪያጁ እየዋለለ መስመር አልያዘም፡፡የቤተክህነቱ ደፍሮ ማኅበሩ የቤ/ክንን ደረሰኞች እንዲጠቀምና ፐርሰንትም እንዲከፍል ግፊት አለማድረግም ሌላው ክፍተት ነው፡፡ክፍተቱ በዋነኝነት ማኅበሩ ካሰመረው ባለፉት ላይ ሁሉ በጭፍን ይተኩሳል የሚል ፍርሃት የወለደው ነው፡፡ይሄ ፍርሃት በመንግስት በኩል ቤተክህነቱ ማኅበሩን እየተቆጣጠረ ስላልሆነ አደብ እናስገዛው የሚል አዝማሚያ እያመጣ ሲሆን ከቤተክህነት ወገንም የመንግስትን አዝማሚያ ለመቃወም የጎላ ጥረት አለመካሄዱ ማኅበሩ በቤተክህነት በኩል እንደ ልጅ ሳይሆን እንደክፉ አሳጢታ ጎረቤት እየታየ መሄዱን ያመለክታል፡፡ያም ሆኖ አሁንም ቤተመንግስቱ ከቤተክህነቱ ጥቅሻ ካላገኘ በቀር ማኅበረቅዱሳን ላይ እጁን ያነሳል ብየ አላምንም፡፡ስለሆነም መፍትሄው ቀላል ነው፡፡ቤተክህነቱንም ሆነ የቤተክህነት ሰራተኞችን ልዩ ልዩ ስም እያወጡ ከማበሻቀጥ በህግ ስር አድሮ ለቤተክርስቲያን ጥቅም በትክክል በማኅበሩ ዐለማ፣ራዕይና ተልእኮ ስር ያሉትን መርሆዎች ለማስፈጸም መጣር፡፡ካድሬ፣ሙስና፣ዘረኝነትና ተሃድሶ የሚሉ ቃላትን የማኅበሩን ተገቢነት የሌለው እብሪታዊ አካሄድ በሚቃወሙ ሁሉ በጭፍን እየመዘዙ አጉል መከላከያና የመጫወቻ ካርዶች እያደረጉ ፍለጠው ቁረጠው ከማለት ታዥነትን የሚያመላክቱ ትሩፋቶች ላይ ማተኮር፡፡በተለይ እነዚህን ካርዶች ያለቦታቸው ራስን ለመከላከል ብቻ በየአጋጣሚው መምዘዝ ቤ/ክንን፣ምዕመናንን፣ማኅበሩን፣መንግስትን፣ወዘተ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ማኅበሩ ከሌሎች የቤ/ክ አካላት ጋር ያለው ግንኙነት በአብዛኛው በመተማመን ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ይሄ ችግር የሚፈታው አደረጃጀቱንም ሆነ ተጠሪነቱን ያለፈውን 22 አመት ተሞክሮ ገምግሞ በማኅበሩ መመሪያ ላይ ክለሳ በማካሄድ ለአባላት ጭምር የስነምግባር መመሪያ በማዘጋጀት ነው ብየ አምናለሁ፡፡

 7. በአማን ነጸረ April 21, 2014 at 10:21 am Reply

  (4) የሚዲያዎችና የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ማኅበሩን ለዐላማ ለማሰለፍ መቋመጥ፡
  አዝናለሁ፡፡ሀገሬ መፍትሄ ከሚጠቁሙ ይልቅ ብሶትን የሚያባብሱ ሚዲያዎችና ፖለቲከኞች ይበዙባታል፡፡ይሄ ርግማን ሳይሆን አይቀርም፡፡ለዛ ነው ንጉሣዊ አስተዳደር ስለፈጠረው ብሶት ሲያወሩ በአንድ ቃል ተስማምተው ስለመፍትሄው ግን 17 አመት የተዋጉ 17 ታጣቂ ድርጅቶች የኖሩን፡፡ለዛ ነው ስለዚህአዴግ አስከፊነት እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲያወጁ የነበሩ ምሁራን በ5 አመት ውስጥ ለ5 የተሸነሸኑት፡፡ለዛ ነው በየ6 ወሩ እየሞቱ የሚነሱ ከሀቅ ይልቅ የድርሰት መልክ የያዘ ዜና የሚያስነብቡ ሚዲያዎች መድረኩን የያዙት፡፡ይሄ መረገም ነው፡፡እነኚህ ፖለቲከኞች የሚናገሩትንና የእነሱኑ እስትንፋስ ለማስቀጠል ደፋቀና የሚሉ ምውታን ጋዜጦችን ተቀብሎ ራስን ለእነሱ ምርኩዝ ከማድረግም አልፎ በአንድ ሃይማኖት ጥላ ስር ለመንፈሳዊ ዐላማ ስለተቋቋመ ማኅበር ነጋ ጠባ ሲለፍፉ ተቀብሎ ማስተጋባት ነውር ነው፡፡እነሱ ለእለቱ እባብ ነው ለሚሉት መንግስት መቀጥቀጫ ሊያደርጉት እንጅ የማኅበርም ሆነ የሃይማኖት ፍቅር አቃጥሎአቸው አይደለም፡፡ማኅበሩ የተፈለገው ለሰልፍ ነው፡፡ሰልፍና ሰለፊ ደግሞ ብዙ እያምታቱ ያሉ ቃላት ናቸው፡፡እነዚህ ቃላት እስኪጠሩ አደብ መግዛት አይከፋም፡፡
  (5) የማኅበሩን ልሳናት ለማኅበሩ ብቻ መርህ፡
  የማኅበሩ ልሳናት አገልግሎታቸው ለጠቅላላዋ ቤ/ክ ሳይሆን ስለማኅበሩ ብቻ ሆኗል፡፡በተለይ ያለፈው ወር ሐመር መጽሄት ስለመዋቅራዊ ጥናት እዘግባለሁ ብሎ ጀምሮ ማኅበሩን ከጉልላቱ በላይ እያወጣ የካበበት ሐተታ አስገርሞኝ ነበር፡፡ያሁኑ ግን ሚዲያ ለቤተክርስቲያን ያለውን አስፈላጊነት ጠለቅ አድርጎ የዳሰሰ በመሆኑ ማመስገን ይኖርብኛል፡፡የባለፈው ምን አስገረመህ ካላችሁ የአዲስአበባ የአብነት መምህራን ከዲግሪ እኩል ይከፈላችኋል ሲባሉ አለማመናቸውን አጥኚው አስታውሶ ፈገግ አለ የሚለው አስቆኛል፡፡ምክንያቱም በአዲስ አበባ የዲግሪ ደሞዝ ከታክስ በፊት 1499ብር ሲሆን የአንድ የአዲስ አበባ የአብነት መምህር ደሞዝ በአማካይ ታክስ የለሌበት 2600 ብር አካባቢ ነው፡፡ለዚህ ነበር ይቺ ጥናት ከመሳቢያ ነው የወጣችው ያልነው፡፡ለዚህ ነበር በመምህር ደንደስ ማህበር ተወደስ ያልነው፡፡ማኅበሩ ራሱ በነበረበት ጊዜ ስለሄዱብን 10 ሚሊዮን አማንያን ሲጽፍ ከኃላፊነቱ ሽሽት እጁን ወደ ቤተክህነት መጠቆሙና በተወገዙ መናፍቃን ጉዳይ ሌሎች የቤ/ክ አባላት አስተዋጽኦ እንዳላደረጉ አድርጎ ራሱን በብቸኝነት የተዋሕዶ አርበኛ ማድረጉም አስገርሞኛል፡፡ዘገባው የእነ መልአከ መንክራት ሀይሌ አብርሃን እና የአቡነ እስጢፋኖስን እርቅ ከልብ አይደለም ሲል በይፋ መኮነኑም ይቺ መጽሄት ልብና ኩላሊትም ትመረምራለች ማለት ነው አሰኝቶኛል፡፡በቅርቡ ማኅበሩ ስብሰባ አድርጎ ያወጣውን መግለጫም አንብቤዋለሁ፡፡አሁንም ማኅበሩ ፈተናዎች ከውጭ እና ከቤተክህነት ሰዎች ብቻ እንደሚመጡበት ለማሳመን መሞከሩን አልወደድኩለትም፡፡ስለሚዲያ አጠቃቀም የተናገሩት ጥሩ ሆኖ ሳለ ከራሳችንም ውስጣዊ ችግር አለ ብሎ ላለማመን ይዳዳዋል፡፡እሱ ነው የችግሩ ስር፡፡ሁሌም የምንፈተነው ደግ ስለምንሰራ ብቻ ነው ብሎ ማመንና ይሄንኑ በየልሳናቱ ማራገብ ስህተት ነው፡፡ምንአልባት እንዲህ አይነት ፈተናዎች በትክክል ከመናፍቃንና የእነሱን ድምጽ ከሚያጮሁት ተሃድሶ ነን ባይ ብሎጎች ሲመጣ አብረን ተሰልፈን እንመክተዋለን፡፡ነገር ግን በሁሉም ነገር እንደእኛ ያላሰበ ሁሉ ተሃድሶ፣ዘረኛ፣ጎቦኛ ነው ብላችሁ በአንድ ቅርጫት ውስጥ ለመጨመር አጉል ስታስፈራሩ አንሰማችሁም፡፡በእሱ አንስማማም፡፡እኛም የሥላሴ ልጅነት ለሰጠችንና እንደየአቅማችን አስተምራ ለወግ ለማዕረግ ላበቃችን፣ስንሞት ጸሎተፍትሃት አድርሳ በክብር ስለምታሳርፍን ቤ/ክ የመናገር መብት አለን፡፡ገና ለገና ሃሳባችሁ ከማኅበራችን አልገጠመም እየተባልን የሚደርስብንን ስልጣን አልባ የማኅበራዊ ሚዲያ ውግዘት ለመቀበል ጫንቃ አለን፡፡ቆይ በአዲስ መስመር እንዲል አቤ ቶኪቻው እኛም በአዲስ መስመር….
  (6) አትሳሳቱ!!ጥይት አታብክኑ!!እንደ ኦርቶዶክሳዊ ስለማኅበሩ ስጽፍም ሆነ ስናገር ጥፋቱን ተመኝቼ አይደለም፡፡መስመሩን ሲስት ሃይ ሊባል ይገባል ብየ ስለማምን ነው፡፡በአጭር እንዳይቀጭ ስለምሰጋ ነው፡፡ ማኅበሩ የመላእክት ስብስብ አይደለም ከማለት ውጭ ስለማኅበሩ ውስጣዊ ድክመት በኦርቶዶክሳዊ ወገኖች እንዳይጻፍ የማሸማቀቅ ዘመቻ አለ ብየ አምናለሁ፡፡ለዚህ ደግሞ በማኅበሩ ላይ በተሃድሶ ብሎጎች የሚቀርቡ ጭፍንና በሬ ወለደ ክሶችን ከእኛ ማኅበሩ ቤ/ክንን በማጉላት ፈንታ እየሸፈናት ነው፣በማቀፍ ፈንታ እያፈናት ነው ለሚል አስተዳደር ተኮር ጥያቄ በማምታት ለመድፈቅ እየተሞከረ ነው፡፡

 8. H.mariam April 22, 2014 at 7:27 am Reply

  Betam des yemil tsuf new
  gin yihin website lamayawku wandimoch ena ehetoch be fabebook yemiyagegnubet menged bimechachi
  share madreg binchil
  Egziabher Hagerachin ethiopia Tewahido Haymanotachin Mahibdrachin Mahibere Kidusanin yitebikilin
  “Ethiopia hagerachinin darwan Esat mehalwan genet adergo yitebikilin”

 9. Anonymous April 22, 2014 at 2:07 pm Reply

  mengest gen tena ata ende ebede hone ya hulu amakari meneden new yemisrew yehagrachenene berr eyebelu…. betarfu yeshaal

 10. Anonymous June 9, 2014 at 4:20 am Reply

  በጣም ያሳዝናል ምንም አይነት ነገር መናገር አልችልም እግዚአብሔር ስራውን ይስራ መንግስትስ አላማው ስለሆነ ነው የሚገርመኝ ፓትሪያሪኩ ናቸው ትሻልን ሰድጀ ትብስን አመጣሁ ይበሉ በጣም ያሳዝናል ምንም አይነት ነገር መናገር አልችልም እግዚአብሔር ስራውን ይስራ መንግስትስ አላማው ስለሆነ ነው የሚገርመኝ ፓትሪያሪኩ ናቸው ትሻልን ሰድጀ ትብስን አመጣሁ ይበሉ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: