ማኅበረ ቅዱሳን የደረሰበት ፈታኝ ወቅት

FACT magazine Megabit 3rd cover(ፋክት፤ ቅጽ ፪ ቁጥር ፴፱፤ መጋቢት ፳፻፮ ዓ.ም.)
ተመስገን ደሳለኝ

 • በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም አዝማችነት በማኅበሩ ላይ የደቦ ዘመቻ ከተከፈተ ሰነባብቷል፡፡ በጥናት ስም በተከታታይ የሚወጡና በየመድረኩ የሚቀርቡ ወረቀቶች ማኅበሩን የኦርቶዶክስ አክራሪ ከማለት አሻግረው ‹‹የግንቦት ሰባት መንፈሳዊ ክንፍ/የግንቦት ሰባት ከበሮ መቺ/›› ሲሉ ይወነጅሉታል፡፡
 • የማኅበሩ አመራሮች እንዲኽ ዓይነቱን ውንጀላ በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ከአቶ በረኸት ስምዖን እስከ ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም፣ ከአዲስ አበባ የጸጥታ ሓላፊዎች እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ አቶ ፀጋይ በርሀ ድረስ ያሉ ባለሥልጣናትን በቢሯቸው ተገኝተው ውንጀላው ተቀባይነት ያለው ማስረጃ የማይቀርብበት የሐሰት እንደኾነ ቢያስረዱም መፍትሔ እንዳላገኙ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
 • በግልባጩ በመንግሥት ተቋማት ያሉ የፋክት መጽሔት መረጃ አቀባዮች፣ በግንቦት ወር ከሚካሔደው የሲኖዶሱ መደበኛ ዓመታዊ ጉባኤ በፊት፣ ከኻያ የሚበልጡ የማኅበሩ አመራሮችን ከሽብርተኝነት ጋራ በማያያዝ ለመክሰስና ማኅበሩንም እንደተለመደው በዶኩመንተሪ ፊልም ለመወንጀል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
 • በዚኽ አስቸጋሪ ወቅት ደግሞ መነሣት የሚኖርበት አስቸጋሪ ጥያቄ፣ እንዴት ይህን ማኅበር ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ይቻላል? የሚለው ሲኾን ምላሾቹም ኹለት ናቸው፡፡ ‹‹ችግሮች ኹሉ የየራሳቸው በጎ ገጾች አሏቸው›› እንዲሉ፣ ማኅበሩ የደረሰበትን ይህን ፈታኝ ጊዜ ተከትለው የሚመጡ ኹለት ወቅቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ በቀጣዩ ወር የሚታሰበው የስቅለት ቀን ነው፡፡ ኹለተኛና በእጅጉ የተሻለ ነው ብዬ የማስበው ጊዜ ደግሞ ቀጣዩ የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ነው፡፡
 • የሃይማኖቱ ተከታዮች በሙሉ በየቤተ ክርስቲያኑ የሚውሉበት የስቅለት በዓል የትኞቹም የሕገ መንግሥቱ ሐሳቦች አልያም የሞራል ዕሴቶች የማይገዛው ሥርዓት እጁን ከማኅበሩና ከቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይ እንዲያነሣ ለመጠየቅ ብሎም ሕያውነታቸውን የመሠረቱበትን ሃይማኖት ለማስከበር የተመቸ ቀን ስለመኾኑ ማስታወስ አባላቱን አሳንሶ መገመት እንዳይኾን ተስፋ አደርጋለኹ፡፡

‹‹ማሕበረ ወያኔ››

በኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሚመራው መንግሥት ከናቅፋ እስከ ጉና ተራራ ያሉ ምሽጎቻቸውን ከሰማይ በጦር አውሮፕላን፣ ከምድር እሳት በሚያዘንቡ ቢ.ኤሞችና መድፎች ሳያቋርጥ ቢደበድብም በሀገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ ከቀን ወደ ቀን ግዛታቸውን እያሰፉ የተጠናከሩት ‹‹ወንበዴዎች›› ራስ ምራት ኾነውበታል፡፡ የኤርትራ ‹‹ነጻ አውጭ›› ቤዝ-ዓምባው በተወሰነ መልኩም ቢኾን ለጥቃት የመጋለጥ ዕድሉ አናሳ በኾነው የሳህል በርሓ በመኾኑ አብዛኛው የአመራር አባል መሸሸጊያ አድርጎታል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ አካባቢ የሚንቀሳቀሱት የወያኔ መሪዎች ምሽጋቸው እንደ ሳህል ምቹ ባለመኾኑ፣ በርካታ ክፉ ቀናትን ካሳለፉባቸው ቦታዎች መካከል በተራራማ አካባቢዎች በሚገኙ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ገዳማት ውስጥ መደበቅ እንደኾነና በየስፍራው መዘዋወር ሲፈልጉም ራሳቸውን ከሚሰውሩባቸው ዘዴዎች ውስጥ በቀሳውስቱና መነኰሳቱ አልባሳት መጠቀም አንዱ እንደነበር በትግሉ ዙሪያ የተዘጋጁ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ በተለይም ታጋይ መለስ ዜናዊና ኣባይ ፀሃዬን ጨምሮ የአመራር አባላቱ የገዳማቱ ቤተኛ ነበሩ፡፡

በርግጥ እኒኽ የወያኔ መሪዎች በእንዲህ ዓይነቱ ከመርፌ ዓይን በእጅጉ በጠበበ ዕድል ‹ሕይወታችን ከሞት ተርፎ ኰሎኔል መንግሥቱን በጓሮ በር ወደ ዝምባቡዌ ሸኝተን በትረ መንግሥቱን ለመጨበጥና ለኻያ ምናምን ዓመታት ኢትዮጵያን ታኽል ታላቅ አገር አንቀጥቅጠን ለመግዛት እንበቃለን› የሚል ጠንካራ እምነትና የርግጠኝነት ስሜት በወቅቱ ነበራቸው ብሎ ማሰብ ለእነርሱም ቢኾን አዳጋች ይመስለኛል፤ የኾነው ግን ይኸው ነበር፡፡

‹‹ማሕበረ ቅዱሳን››

መለስ ዜናዊና ጓዶቹ በለስ ቀንቷቸው ባልጠበቁት ፍጥነት የመንግሥት ‹‹ጠንካራ ይዞታ›› የሚባሉ ከተሞችን እየተቆጣጠሩ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ግሥጋሴ ሲያፋጥኑ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ደግሞ በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሰብሳቢነት፣ በደኅንነት ሠራተኞችና በኢሠፓ ካድሬዎች ገፋፊነት ትምህርታቸውን አቋርጠው ለወታደራዊ ሥልጠና ደቡብ ኢትዮጵያ ወደሚገኘው ብላቴ የጦር ማሠልጠኛ ከተቱ፤ ዩኒቨርስቲውም ተዘጋ፡፡

ከመላው ዘማቾች የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የኾኑ ሠልጣኞች በየድንኳኑ እየተሰበሰቡ ፈጣሪ ከመዓቱ ይታደጋቸው ዘንድ በጸሎት መማፀን የሕይወታቸው አካል አደረጉት፡፡ ከቀናት በኋላ በአንዱ ዕለት አንድም ለመታሰቢያና ለበረከት፣ ኹለትም ስብስቡ ሳይበተን ወደፊት እንዲቀጥል በሚል እሳቤ ‹‹ማኅበረ ሚካኤል›› ብለው የሰየሙትን የጽዋ ማኅበር መሠረቱ፡፡…ይኹንና ከመካከላቸው አንዳቸውም እንኳ በ1977 ዓ.ም. በፓዌ መተከል ዞን የተደረገውን የመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም እንዲያመቻቹ በዘመቱ ተማሪዎች ከተመሠረተውና ቅዱሳን ከሚዘከሩባቸው ሌሎች የጽዋ ማኅበራት ጋር በመዋሐድ የዛሬውን ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› እንደሚፈጥሩ መገመት የሚችሉበት የነቢይነት ጸጋ አልነበራቸውም፤ የኾነው ግን እንዲያ ነበር፡፡

ሃይማኖትን ጠቅልሎ የመያዝ ዕቅድ

በትጥቅ ትግሉ ወቅት የህወሓት አመራር ገዳማትን ለመሸሸጊያነት ብቻ ሳይኾን ለሥልጣን እርካብ መወጣጫነትም ጭምር ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ከድርጅቱ መሥራቾች አንዱ አረጋዊ በርሄ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ በሚል ርእስ ሠርቶት ኋላ ወደ መጽሐፍ በቀየረው “The Origin of TPLF” የጥናት ጽሑፉ ላይ÷ ‹‹የቤተ ክርስቲያኗ ሥልጣን (በትግራይ የነበረውን) ለማድቀቅ ሲባል በስብሃት ነጋ የሚመራ የስለያ ቡድን ተቋቋመ፡፡ ይህ ቡድንም ደብረ ዳሞን ጨምሮ በትግራይ ውስጥ ባሉ ገዳማት አባላቱን መነኰሳት በማስመሰል፣ የገዳማቱን እንቅስቃሴ በህወሓት ፍላጎት ሥር የማስገዛት ሥራ ሠርቷል›› ሲል በገጽ 317 ላይ ገልጧል፡፡ ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ሃይማኖትን ጠቅልሎ ለመያዝ የተነሣበትን ገፊ ምክንያትም እንዲኽ በማለት አብራርቷል፡-

‹‹ቤተ ክርስቲያኗ ተከታዮቿን፣ ለነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲገዙ ከማስተማር በዘለለ የብሔራዊ ንቃት(ማንነት) ማስተማርያም ነበረች፡፡ …ለህወሓት እንቅስቃሴ ዕንቅፋት እንደነበረች ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያኒቱን በህወሓት ዓላማ ሥር ለማሳደር ፍላጎት ነበር፤ በዚህ የተነሣም የእርስዋን ተጽዕኖ ለማግለል ጥልቅ ርምጃ ወስደዋል፡፡›› /ገጽ 315 – 316/

ዶ/ር አረጋዊ ‹‹ጥልቅ ርምጃዎች›› ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል አንደኛው ‹‹ለአጥቢያ ቀሳውስቱ ኮንፈረንስ በማዘጋጀት፣ በትግራይ ውስጥ ያሉትን አብያተ ክርስቲያን ለብቻ ነጥሎ ህወሓት በሚያራምደው የትግራይ ብሔርተኝነት ሥር ማካተት›› እንደነበረ በዚኹ መጽሐፍ ጠቅሷል፡፡ ይኹንና አስገምጋሚ መብረቅ የወረደብን ያኽል የምንደነግጠው፣ ዶክተሩ ከዚኹ ጋራ አያይዞ ‹‹የተጨቆነው የትግራይ ብሔርተኝነት የተነሣሣውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ተጽዕኖ ለመገዳደር ነው›› በማለት መመስከሩን ስናነብ ነው፡፡ የአረጋዊ መረጃ የሰሚ-ሰሚ ወይም በቢኾን ሐሳብ የተቃኘ አይደለም፤ ይልቁንም ራሱን በመሪነትና ሐሳብ በማዋጣት ከተሳተፈበት ከድርጅቱ የፖሊቲካ ፕሮግራም የተቀዳ እንጂ፡፡

የኾነው ኾኖ ህወሓት ከ1970-72 ዓ.ም. ድረስ ባሠለጠናቸው ካድሬ ካህናት አማካይነት ‹‹ነጻ በወጡ›› መሬቶች ላይ ራሱን የቻለ የቤተ ክህነት አስተዳደር (ከማእከላዊ ሲኖዶስ የተገነጠለ) መመሥረቱ ይታወሳል፡፡ ድርጅቱ ለእኒኽ አብያተ ክርስቲያን መተዳደርያ ደንብ ከመቅረፅ አልፎ ዓላማውንም እንደ ዓሥርቱ ትእዛዛት በፍጹም ልባቸው የተቀበሉ ‹‹መንፈሳዊ ክንፍ›› አድርጓቸው እንደነበረ አረጋዊ በርሄ ተንትኖ አስረድቷል፡፡

እንዲኽ ዓይነቱ ሰርጎ ገብነት በእስልምና ላይም መተግበሩ አይዘነጋም፡፡ በተለይም የእምነቱ ተከታዮች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ወላጆቻቸው ሙስሊም የኾኑ ታጋዮችን እየመረጠና ከክርስቲያን ቤተሰብ የወጡ ካድሬዎችንም ሐሰተኛ የሙስሊም ስም እየሰጠ ‹የትግሉ ዓላማ እስልምናን ማስፋፋት› እንደኾነ በመግለጽ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ይሠራ ነበር፡፡ በዚኽ ስልቱ በተወሰነ ደረጃም ቢኾን የአንዳንድ ዓረብ አገሮችን ቀልብ ማግኘት ችሏል፡፡ ይህ ደግሞ ከዓረቦቹ በገፍ ርዳታ ያጎረፈለት ሲኾን ወደ መሃል አገር የሚያደርገውን ጉዞም አፋጥኖለታል፡፡

ከመንግሥት ለውጥ በኋላም ሁለቱንም እምነቶች የተቆጣጠረው በታጋይና ምልምል ‹ካህናት› እና ‹ሼኾች› ለመኾኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ዛሬም በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት አስተዳደራዊ መዋቅር የበላይ በኾነው በጠቅላይ ቤተ ክህነት ውስጥ ከሚገኙ ዐሥራ ስምንት መምሪያዎች ውስጥ ዐሥራ ስድስት ያኽሉ በህወሓት ሰዎች የመያዛቸው ኩነት ስልቱ በተሳካ ኹኔታ መተግበሩን ያስረግጣል፡፡

በተለይ ዋነኛው ሰው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቅ/ሲኖዶሱን በሚመለከት ጉዳይ ላይ ጭምር ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ‹‹የመንግሥት ባለሥልጣናትን ላማክር›› ሲሉ በተደጋጋሚ መደመጣቸው፣ ትችትና ተቃውሞ በተሰነዘረባቸው ቁጥር ‹‹መንግሥት ያግዘኛል ብዬ ነው እዚኽ መንበር ላይ የተቀመጥኹት፤ ባያግዘኝ ሥልጣኑን አልቀበልም ነበር›› በማለት በግላጭ ሲመልሱ መስተዋላቸው ለሥርዓቱ ተጽዕኖና ጣልቃ ገብነት እንደማሳያ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ከዚኽ ቀደም ለሦስት ወራት የቋሚ ሲኖዶሱ አባል ኾነው የሠሩ አንድ ጳጳስም ‹‹ኹልጊዜ ቋሚ ሲኖዶሱ ሲሰበሰብ እርሳቸው ‹መንግሥት እንዲኽ አለ›፤ ‹መንግሥት ሳይፈቅድ›… የሚል ንግግር ይጠቀማሉ›› በማለት ለፋክት አስተያየት ሰጥተዋል(በነገራችን ላይ ፓትርያርኩ ነገር የመዘንጋት፣ ለውሳኔ የመቸገር፣ ዕንቅልፍ የማብዛትና መሰል ችግሮች ሥራቸውን እያስተጓጎሉባቸው እንደኾነ ይነገራል፤ ራሳቸውም ‹‹ሲጨንቀኝ እተኛለኹ፤ ስተኛ ደግሞ እረሳዋለኹ›› በማለት ችግሩን አምነው ተቀብለዋል፡፡)

በእስልምና እምነት ውስጥም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ከቀድሞው መጅሊስ የባሰ እንደኾነ በርካታ ሙስሊም ምእመናን የሚያውቁት እውነታ ነው፡፡ ይህ መጅሊስ የሚዘወረው እንደተለመደው በምክትል ፕሬዝዳንቶች ሲኾን፣ ይህች ዓይነቱ ጫዎታ ደግሞ ህወሓት ጥርሱን የነቀለበት ስለመኾኑ ነጋሪ አያሻም፡፡ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሼኽ ከድር ለ17 ዓመታት የትግራይ ክልል መጅሊስና የሸሪአ ፍ/ቤቱን ደርበው በመያዝ ምእመናኑን ቀጥቅጠው ሲገዙ ከመቆየታቸውም በላይ ታጋይ እንደነበሩ በኩራት ለመናገር እንደሚደፍሩ የቅርብ ሰዎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ በአናቱም ከታጋይ የመረጃ ምንጭ ባይረጋገጥም የመጅሊሱ ፕሬዝዳንት ሼኽ ኪያር መሐመድ ከእኚኹ ታጋይ ምክትላቸው ጋራ በአንዳንድ ጉዳዮች መስማማት ባለመቻላቸውና ‹‹መንግሥት የሚያዘውን ኹሉ ለመሥራት ለምን እንገደዳለን?›› የሚል ተቃውሞ እስከ ማሰማት በመድረሳቸው በቅርቡ ከሓላፊነታቸው ሊነሡ እንደሚችሉ ተወርቷል፡፡

ኢሕአዴግ እና ‹‹መንፈሳዊ ገበያው››

ግንባሩ የእምነት ተቋማትን በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ጠርንፎ መያዝን እንደ ዋነኛ ዓላማ አድርጎ የመንቀሳቀሱ መግፍኤ ከሦስት ጉዳዮች አንጻር በአዲስ መሥመር ለመተንተን እገደዳለኹ፡-
የመጀመሪያው÷ ቤተ ክህነት በነገሥታቱ ዘመን የነበራትን ፖሊቲካዊ ተሰሚነት (ምንም እንኳ ራሱ ኢሕአዴግም በአፋዊነት ከማውገዝ ቸል ባይልም) ለቅቡልነት መጠቀሚያ የማድረግ ፍላጎቱ ነው፡፡ በገቢር እንደታየውም በኃይል በተቆጣጠራቸውም ኾነ ካድሬዎቹ ሊደርሱባቸው በማይችሉ የገጠር ቀበሌዎች ተቀባይነት ለማግኘት ማኅበራዊ ተቀባይነት ባላቸው ሼኾች፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት ሲቀሰቅስ በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ እንዲኹም የእስልምና እምነት በታሪክ ያሳለፈውን አገዛዛዊ ጭቆናን ይኹን የደርጉን ኹሉንም ሃይማኖት ማግለልን በማጎን ለፕሮፓጋንዳ ተጠቅሞበታል (በወቅቱ የድርጅቱ አመራር አባል የነበሩት አቶ ገብሩ ኣስራት እንደ ሼኾች በመልበስና በመጠምጠም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ብዙኃኑ ታጋዮች አይዘነጉትም) በዚኽ ዘመንም በአብያተ እምነቶች ካድሬ ጳጳሳትንና ካድሬ ሼኾችን አሰርጎ የማስገባቱ ምሥጢር ይኸው ነው፡፡

እንደ ኹለተኛ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው÷ የታገለለትን ዘውግ ተኰር ፖሊቲካ ያለአንዳች ተግዳሮት ማሳለጥን ታሳቢ ማድረጉ ይመስለኛል፤ ምክንያቱም የኹሉም ሃይማኖቶች ‹‹የሰው ልጆች ኹሉ የአንድ አምላክ ፍጡሮች ናቸው›› በሚል አስተምህሮ የሚመሩ ከመኾናቸው አኳያ፣ ማንነታቸውን በዘውግ ከፋፍሎ ማስተዳደርን ቀላል አያደርገውምና ነው፡፡ ስለዚኽም መፍትሔው አክራሪ ብሔርተኛ ‹መንፈሳውያን› በየእምነቱ ተቋማቱ እንዲፈለፈሉና ከፍተኛውን የሥልጣን ዕርከን መቆጣጠር እንዲችሉ በማብቃት ላይ የተመሠረተ ብቻ መኾኑን የህወሓት መሪዎች ያውቃሉ፡፡

ይህ ‹ዕውቀታቸውም› ይመስለኛል ሀገራዊ ስሜት የሌላቸው፣ በችሎታ ማነስና በሥነ ምግባር ጉድለት የሚታወቁ፣ እንዲሁም በእምነት አቋማቸው በተከታዮች ዘንድ ተኣማኒና ቅቡል ያልኾኑ ሰዎች ቦታውን እንዲይዙ እስከ ማድረግ ያደረሳቸው፡፡ የራሳቸው የስለላ መዋቅርም ጥቅምት 2 ቀን 1995 ዓ.ም. ‹‹ለዋናው መሥሪያ ቤት፣ አዲስ አበባ፤ ከ-ል.ዮ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን ይመለከታል›› በሚል ርእስ ለደኅንነቱ ዋና መሥ/ቤት በላከው ጥናታዊ ዘገባ ላይ እውነታውን እንዲኽ ሲል ገልጾታል፡-

‹‹ለፓትርያርኩ ወዳጅነት አላቸው የሚባሉ ሊቃነ ጳጳሳት ከሦስትና አራት ብዙም ያልበለጡ ናቸው፡፡ ፓትርያርኩ ምንም ዓይነት ተቀባይነትና ከበሬታ ያጡ በመኾናቸው ህልውናቸውን የአንዳንድ መሪዎችን ስም በመጥራትና እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም ላይ የተንጠለጠለ ኾኗል፡፡››

ከዚኽ ሪፖርት በኋላም እንኳ በቀጣዩ ሢመት ለማስተካከል አለመሞከሩ መከራከሪያውን አምነን እንድንቀበል ያስገደድናል፡፡

አገዛዙ መንፈሳዊ ተቋማትን ጠቅልሎ ለመያዝ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ በሦስተኛነት ሊጠቀስ የሚችለው ምክንያት፣ ምንም እንኳ ተሳክቷል ሊባል ባይቻልም፣ በሥነ ምግባር መታነፅ፣ በአገር አንድነት ማመን፣ ለሕዝብ ጥቅም በወገንነትና በሓላፊነት ስሜት መቆም፣ የትኛውንም ሕገ ወጥነት ለምን ብሎ መጠየቅና መሰል መንፈሳዊ አስተምህሮዎችን መርሑ አድርጎ የሚነሣ ትውልድ እንዳይፈጠር መከላከልን ታሳቢ አድርጎ እየሠራ ያለውን ሤራ ነው ብዬ አስባለኹ፡፡ ምክንያቱም የሥርዓቱ ሰዎች በዚኽ መልኩ የሚቀረፅ ትውልድን ዛሬ ባነበሩት የጭቆና ቀንበር ለተራዘሙ ዓመታት መግዛት ከባድ እንደኾነ ለመረዳት አይሳናቸውምና ነው፡፡

ከዚኽ ጋራ አንሥተን ማለፍ ያለብን ጭብጥ መቃብር ከሚቆፈርለት የኢትዮጵዊ ብሔርተኝነት ጋራ የሚያያዝ ነው፡፡ የሃይማኖቱና የማእከላዊ መንግሥቱ የቅድመ – አብዮቱ ጋብቻ (በምንም ዓይነት መከራከርያ ልንሟገትለት ባንችልም) ቤተ ክርስቲያኒቱ ለኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነቱ ብያኔ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጓን አያስክደንም፡፡ ይህም ‹የሃይማኖቱን ተቋም የብሔርተኝነቱ ወካይ ኾኖ እንዲታሰብ ይገፋዋል› ብሎ ለሚያምነው ህወሓት፣ ሃይማኖቱ ተቋማዊ ነጻነት እንዳይኖረው የሚቻለውን ኹሉ ሲያደርግ፣ ሃይማኖቱን በማዳከም የብሔርተኝነት መንፈሱንም ማላላት ይቻላል ከሚል መነሾ ነው ብሎ መደምደም ተምኔታዊ አያስብልም፡፡

ገደል አፋፍ የቆመው ማኅበረ ቅዱሳን…

ሥርዓቱ የሃይማኖት ተቋማቱንና መንፈሳዊ መሪዎቹን ለመቆጣጠር ገፊ ምክንያቶች ኾነውታል ብዬ ከላይ ለማብራራት የሞከርኋቸውን ሦስት ምክንያቶች ሙሉ ለሙሉ መተግበርን አስቸጋሪ ያደረጉበት፣ በቀጥታ በምእመናኑ የተመሠረቱ ማኅበራት መኾናቸውን መገመት ይቻላል፡፡ ለማስረጃም ያኽል ከኦርቶዶክስ ክርስትና – ማኅበረ ቅዱሳን፣ ከእስልምና ያለፉትን ኹለት ዓመታት የእምነቱ ተከታዮች ወካይ ኾኖ የተመረጠው ኮሚቴ አባላት መንግሥትንም ኾነ መጅሊሱን በመገዳደር ያደረጉትን አበርክቶ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ይኹንና የሙስሊሙን ተወካዮች በገፍ ሰብስቦ እስር ቤት ካጎረ በኋላ፣ ከሲኖዶሱም ኾነ መሰል ማኅበራት ጠንካራ እንደኾነ የሚነገርለትን ማኅበረ ቅዱሳንን ዋነኛ ዒላማ አድርጎ ለመደፍጠጥ የቆረጠ ይመስላል፡፡ የማኅበሩ አባላት በዓለማዊ/ዘመናዊ ዕውቀት የተራቀቁ፣ በሀገራዊ አንድነት ፈጽሞ የማይደራደሩ፣ በጥቅመኝነት የማይደለሉ…የመኾናቸው ጉዳይ አገዛዙ ከኃይል አማራጭ የቀለለ መፍትሔ የለም ብሎ እንዲያምን አድርጎታል ብዬ አስባለኹ፡፡

በርግጥ በአቶ መለስ ይዘጋጅ እንደነበር ከኅልፈቱ በኋላ በይፋ በተነገረለት የኢሕአዴግ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት – አዲስ ራዕይ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አብዛኛውን ጊዜ ‹‹የከሰሩ ፖሊቲከኞች፣ ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት፤ አንድ ሃይማኖት አንድ ሀገር እና ሙስሊም ማኅበረሰብ ቀደም ሲል ሲደርስበት የነበረውን በደል በማራገብና በመቀስቀስ፣ ከዚኽም አልፎ ተገቢነት የሌላቸው አዳዲስ ጥያቄዎች በማቅረብ ለማነሣሣትና ለማተረማመስ ሲሠሩ ማየት የተለመደ ኾኗል›› በማለት ከሚያቀርበው የሾላ በድፍን ፍረጃ ዘልሎ መንፈሳውን ማኅበራትን በስም ጠቅሶ ያወገዘባቸው አጋጣሚዎች ብዙም አልነበሩም፡፡

ዛሬ ዛሬ ግን ማንኛውንም ሃይማኖታዊ የመብት ጥያቄን ‹‹ወሃቢያም ይኹን ማኅበረ ቅዱሳን…›› በማለት ማውገዙ የተለመደ ኾኗል፡፡ ከውግዘትም ተሻግሮ ጥያቄዎቻቸውን በሕጋዊ መንገድ ወደ ዐደባባይ ያወጡትን የሙስሊሙን ተወካዮች ሰብስቦ አስሯል፤ በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ሰላማዊ ተቃውሞዎችንም በማስታከክ በበርካታ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ግድያና ሥቅየትን ጨምሮ ብዙ ግፍ በመፈጸም ጉዳዩን በጠመንጃ ብቻ የሚፈታ አድርጎ ካወሳሰበው ሰነባብቷል፡፡

‹‹ቀጣዩ የኢሕአዴግ ዒላማ ማኅበረ ቅዱሳን ይኾን?›› በሚል ከስድስት ወራት በፊት በዚኹ መጽሔት ላይ ለማተት እንደሞከርኁት ኹሉ፣ ከላይ በተዘረዘሩ የፖሊቲካ አጀንዳዎችና በሚቀጥለው ዓመት የሚካሔደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ በለመደው የማጭበርበር መንገድ አሸንፎ ያለኮሽታ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ዓለማዊ ይኹን መንፈሳዊ ነጻ ተቋማት እንዳይኖሩ በይፋ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ድርጊቶችን እየፈጸመ ያለው የእነ ኣባይ – በረከት መንግሥት፣ በአኹኑ ወቅት ሙሉ ትኩረቱን በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ማድረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህን አፈና ለማሳካትም ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በፍጹም ልባቸው ከመተባበር ለአፍታም እንደማያመነቱ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያኽል አንዱን በአዲስ መሥመር ላቅርብ፡-

ከወራት በፊት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አስተዳደርን ወደ ዘመናዊነት ለማሻገር ሲኖዶሱ ጥናት ተደርጎ እንዲቀርብለት ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡ እናም ጥናቱ ተጠናቆ አገልጋዩና ምእመኑ እንዲወያይበት ሲኖዶሱ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ከኹሉም አድባራትና ገዳማት የተውጣጡ 2700 ሰዎች የተሳተፉበትና በድምሩ 14 ቀናት የፈጀ ውይይት ይጠራል፡፡ በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ አማካይነት በተመራውና ጥናቱን በሠራው የባለሞያ ቡድን ፈጻሚነት የተከናወነው ውይይት ሲካሔድ በነበረባቸው በመጨረሻዎቹ ሳምንታት በአንዱ ቀን ‹ከአንዳንድ የአድባራት አስተዳዳሪዎች ብርቱ ተቃውሞ አጋጥሟል› መባሉን ተከትሎ በሊቀ ጳጳሱና በፓትርያርኩ መካከል የሚከተለው ውዝግብ መካሔዱን ሰምቻለኹ፡-
‹‹ጥናቱን የሚሠሩት ባለሞያዎች ናቸው ብለውኝ አልነበረም ወይ?››
‹‹አዎ! ታዲያስ ባለሞያዎች ናቸው የሠሩት››
‹‹አይደለም! የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ናቸው፤ እርስዎ አታለውኛል!››
‹‹የጥናት ኮሚቴው አባላት በቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸውና በየአጥቢያው ባላቸው ተሳትፎ ተጠርተው የመጡ ሞያቸውን ዓሥራት ያደረጉ ናቸው፡፡››
‹‹በፍጹም ጥናቱ የማኅበረ ቅዱሳን ነው!››
‹‹ቅዱስ አባታችን ቢኾንስ፣ ከጠቀመን ችግሩ ምንድን ነው?››
‹‹በቃ! ውይይቱ ከመንግሥት ይቋረጥ ተብሏል፡፡››
‹‹ለምን ይቋረጣል?››
‹‹የጥናቱ ተቃዋሚዎች ረብሻ ያስነሣሉና የጸጥታ ስጋት አለ››
‹‹ለምንድን ነው ረብሻ የሚያስነሡት? ከፈለጉ መጥተው መሳተፍ ይችላሉ፤ እኛ እየተወያየን አይደለም እንዴ! ተቃውሞ ያለው መጥቶ ሐሳቡን ይግለጽ እንጂ ማቋረጥ እንዴት መፍትሔ ይኾናል? ደግሞስ ሲኖዶሱ አይደለም ሰነዱ ወደ ታች ወርዶ ይተችበት ብሎ የወሰነው?››
‹‹የለም! ይቁም ተብሏል፤ ይቁም!››
‹‹እንግዲያስ የከለከለው አካል ራሱ መጥቶ ይንገረን፡፡››

ምልልሱ ከተጠናቀቀ ከሰዓታት በኋላ አንድ ባለሥልጣን ቢሮ ድረስ መጥቶ፣ ትእዛዙን ያስተላለፈውን አካል ገልጾ ውይይቱ እንዲቋረጥ አሳሰባቸው፤ እርሳቸውም ‹‹እናቋርጣለን፤ ነገር ግን ‹እናንተ የጸጥታ ስጋት አለ› ብላችኹ በደብዳቤ ሓላፊነቱን ውሰዱ፡፡ እኛም ለካህናቱ ለምእመናኑ ኹኔታውን ዘርዝረን እንገልጻለን›› የሚል ምላሽ ሰጥተው ይሸኙታል፡፡ ከዚህ በኋላ እንግዲህ ‹ውይይቱ ይቋረጥ› የሚለው ማስፈራሪያ ለጊዜው ግልጽ ባልኾነ ምክንያት ሊነሣ የቻለው፡፡ ኩነቱ ግን ፓትርያርኩ ማኅበሩን በጥርጣሬ ማየታቸውንና በአገዛዙ ለሚወሰድበት ማንኛውም ርምጃ ተባባሪ መኾናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡

ሌላው መንግሥትና ፓትርያርኩ፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ በሰምና ወርቅነት እየሠሩ መኾናቸውን የሚያመላክተው የዛሬ ሳምንት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የማኅበሩ ተቃዋሚዎች ያደረጉትን ውይይትና ያወጡትን የአቋም መግለጫ ስናስተውል ነው፡፡

ለመጽሔቱ ዝግጅት ክፍል የደረሰው በድምፅ የተቀረፀ የውይይቱ ሙሉ ክፍል እንደሚያስረዳው፣ ተሰብሳቢዎቹ ማኅበሩን በተመለከተ ያወጡት የአቋም መግለጫ÷ የማኅበሩና የዋነኛ መሥራቾችና አባላት የባንክ አካውንት፣ ቀላልና ከባድ ተሸከርካሪዎች ጨምሮ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች፣ ት/ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት፣ የአክስዮን ተቋማት፣ የንዋያተ ቅድሳት ማምረቻዎችና ማከፋፈያዎች፣ ከቀረጥ ነጻ የገቡና በመግባት ላይ ያሉ ዕቃዎች በሚመለከታቸው የመንግሥት መሥ/ቤቶች እንዲታገዱ በቅ/ሲኖዶስ አማካይነት ደብዳቤ እንዲጻፍ፤ ከምእመናን በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ የሚቀበለው ዓሥራት እየፈረጠመበት ስለኾነ እንዳይቀበል ይከልከል፤ የግቢ ጉባኤያት(የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) እርሱ በሚቀርፀው ትምህርት እንዳይወሰዱብን በደንብ መሥራት፤ ተጠሪነቱ ከዋና ሥራ አስኪያጅነቱ ሥር ወጥቶ በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ውስጥ አንድ ንኡስ ክፍል ይኹን የሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ከዚኽ ሤራ ጀርባ ፓትርያርኩና ተቃዋሚዎቹ አግዞናል የሚሉት መንግሥት በትብብር መቆማቸውን የሚያሳየው በተቀረፀው ድምፅ ላይ፣ የተቃዋሚዎቹ አስተባባሪ መሰብሰቢያ አዳራሹን ለመጠቀም የቻሉት በአቡኑ መልካም ፈቃድ እንደኾነ ከመግለጽ በዘለለ ‹‹ቅዱስ አባታችን በዚኽ ተቃውሞ ምክንያት ከሥራ የሚባረር የለም፤ አይዟችኹ አትፍሩ ብለውናል›› በማለት ሲናገሩ መደመጣቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹ከዚኽ ግቢ አቅም ኖሮት የሚያስወጣን የለም እንጂ ካስወጡን መንግሥታችን ቸር ስለኾነ ከእርሱ ቦታ ተቀብለን የራሳችንን ቤተ ክርስቲያን እናቋቁማለን›› እና ርስ-በርስ ለመረዳዳት ‹‹የአዲስ አበባ አገልጋዮች ማኅበር እንመሠርታለን›› እስከ ማለት መድረሳቸው ከአገዛዙ ጋራ ያላቸውን የጠበቀ ቁርኝት ያመላክታል፡፡ በነገራችን ላይ በስብሰባው እንዲሳተፉ ከተቀሰቀሱት 169 አድባራትና ገዳማት እንዲኹም ከዐሥር ሺሕ በላይ ሠራተኞቻቸው መካከል የተገኙት የስምንት ያኽል አድባራት አስተዳዳሪዎችና 150 ያኽል ተሳታፊዎች ብቻ እንደነበሩ ከምንጮች አረጋግጫለኹ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም አዝማችነት በማኅበሩ ላይ የደቦ ዘመቻ ከተከፈተ ሰነባብቷል፡፡ በጥናት ስም በተከታታይ የሚወጡና በየመድረኩ የሚቀርቡ ወረቀቶች ማኅበሩን የኦርቶዶክስ አክራሪ ከማለት አሻግረው ‹የግንቦት ሰባት መንፈሳዊ ክንፍ/የግንቦት ሰባት ከበሮ መቺ/›› ሲሉ ይወነጅሉታል፡፡ በጥቅሉ የእኒኽ ጥናት ተብዬዎች መደምደሚያ ‹‹ማኅበሩ ከጽንፈኛ የፖሊቲካ ኃይሎች ጋራ ትስስር የፈጠሩና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ዝንባሌ ያላቸው ትምክህተኞች ምሽግ ነው፤ አመራሩና የኅትመት ውጤቶቹ የፖሊቲካ አዝማሚያ ይታይባቸዋል፤ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር/አስተዳደር ጣልቃ ይገባል፤ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው ይሠራል፤ በውጭ ጽንፈኛ የፖሊቲካ ኃይሎች ይዘወራል›› የሚሉ ናቸው፡፡

የማኅበሩ አመራሮች እንዲኽ ዓይነቱን ውንጀላ በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ከአቶ በረኸት ስምዖን እስከ ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም፣ ከአዲስ አበባ የጸጥታ ሓላፊዎች እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ አቶ ፀጋይ በርሀ ድረስ ያሉ ባለሥልጣናትን በቢሮአቸው ተገኝተው ውንጀላው ተቀባይነት ያለው ማስረጃ የማይቀርብበት የሐሰት እንደኾነ ቢያስረዱም መፍትሔ እንዳላገኙ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በግልባጩ በመንግሥት ተቋማት ያሉ የፋክት መጽሔት መረጃ አቀባዮች፣ በግንቦት ወር ከሚካሔደው የሲኖዶሱ መደበኛ ዓመታዊ ጉባኤ በፊት፣ ከኻያ የሚበልጡ የማኅበሩ አመራሮችን ከሽብርተኝነት ጋራ በማያያዝ ለመክሰስና ማኅበሩንም እንደተለመደው በዶኩመንተሪ ፊልም ለመወንጀል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በአቡነ ገብርኤል ሰብሳቢነት የሚመራው የሃይማኖት ተቋማት ምክር ቤት ከእነዶ/ር ሺፈራው ጋር ስብሰባውን ባካሔደበት አንድ ሰሞን ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ ዶ/ር ሺፈራው አቡኑን ቃል በቃል እንደነገራቸው የተሰማው ነገር ይህን መረጃ የሚያጠናክር ነው፡-
‹‹በማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ ያሉና ማኅበሩን ለተቃውሞ ፖሊቲካ እንቅስቃሴ የሚጠቀሙ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አሉ፤››
‹‹ምንድን ነው ማስረጃኽ?››
‹‹ዝርዝራቸው አለኝ፤ በሀገር ውስጥ ካሉ ጋዜጠኞች በተጨማሪ በስደት የሚገኙና በሽብር ተግባር የተሠማሩም አሉበት፤››
‹‹እኛ እስከምናውቀው ማኅበሩ ከእንዲኽ ዓይነት ተግባር የራቀ ነው፤ ማስረጃ አለ ካልኽ ደግሞ አቅርብና እንየው፤ ከዚኽ ውጭ እንዲኽ ዓይነቱን ክሥ አንቀበልም፡፡››

በአናቱም የግንባሩ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት የማኅበሩን ስም ሳይጠቅስ በደፈናው የወነጀለበትንና ለምን ብለው የሚጠይቁ ጳጳሳትን በሚከተለው አገላለጽ ማሸማቀቁን ስናስታውስ የማኅበሩ ዕጣ ፈንታ በመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ መቆሙን ያስረግጥልናል፡-
‹‹በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትርምስና ብጠብጥ ለመፍጠር፣ በኦርቶዶክሶችና ሌሎች ሃይማኖቶች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሞክሩት የደርግና የተለያዩ ትምክህት ኃይሎች ቅሪቶች ናቸው፡፡ እኒኽ የትምክኽት ኃይሎችና አንዳንድ የእምነቱ አባቶች በጋራ ሃይማኖትን በፖሊቲካ ዓላማ ዙሪያ ብቻ መጠቀሚያ አድርገው እየሠሩ ለመኾናቸው ከ97 ምርጫ በኋላ አንዳንድ በአሜሪካ የሚገኙ ጳጳሳት ቅንጅት በጠራው ሰልፍ ላይ የሃይማኖት አባትነት ካባቸውን እንደለበሱ ከመሰለፍ አልፈው አስተባባሪ ኹነው መታየታቸው በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡›› /አዲስ ራዕይ፤ ሐምሌ – ነሐሴ 2005 ዓ.ም.)

የኾነው ኾኖ ከፍረጃውና ከእስራቱ በተጨማሪ ማኅበሩን ለማዳከም በዋናነት በአገዛዙ የተነደፉት ዕቅዶች ማኅበሩ መሠረቱን ከጣለበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት አባላት ከማለያየት፣ ንብረቶቹን ከመውረስ ጋራ የሚያያዙ ናቸው፡፡ (ከላይ የተመለከተው የተቃዋሚዎች የአቋም መግለጫም ለማኅበሩ የደም ሥር ለኾኑት እኒኽ ኹለት ጉዳዮች ትኩረት የሰጠ መኾኑን ልብ ይሏል)

ስቅለትን ለተቃውሞ

ኢሕአዴግ ወደ መንግሥታዊ ሥልጣን በመጣ ሦስተኛ ዓመት ላይ ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግቦችና ቀጣይ ርምጃዎች›› በሚል ርእስ ለካድሬዎች በበተነው ድርሳን (በአቶ መለስ እንደተዘጋጀ ይገመታል)፣ ይህን አኹን የተነጋገርንበትን ሃይማኖታዊ ተቋማትን ለሚያቅዳቸው ሥልጣንን የማራዘሚያ አማራጮች ስለመጠቀም ካወሳ በኋላ ተቋማቱን ለሥርዓቱ ፖሊሲዎች እንዲታመኑ ማድረጉ ዋነኛ እንደኾነ ያሠምርበታል፡፡ ይህ የማይቻል ከኾነ ደግሞ፣ እስከ ከፍተኞቹ መንፈሳውያን መምህራን ድረስ ዘልቆ በመግባት ሃይማኖቶቹን መምራት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግብ መኾን እንዳለበት ያው ሰነድ በግልጽ ቋንቋ ይናገራል፡፡ እንግዲኽ ከመጅሊሱ እስከ ማኅበረ ቅዱሳን ያየነው መንግሥታዊ አፈና የዚኽን ኻያ ዓመት የሞላው የተጻፈ ሐሳብ መተግበርን ነው፡፡

ግና፤ ከዚኽ ቀደም በተጻፈ ነውረኛ ሐሳብ ትግበራ ፊት ከኹለት ዐሥርት በላይ ህልውናውን ለማቆየት የተጋው ማኅበረ ቅዱሳን፣ ከላይ በሚገባ በጠቀስኋቸው አሳማኝ መረጃዎችና ተጨባጭ ኹነቶች በተከታታይ መከሠት መጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ ተመልክተናል፡፡ በዚኽ አስቸጋሪ ወቅት ደግሞ መነሣት የሚኖርበት አስቸጋሪ ጥያቄ፣ እንዴት ይህን ማኅበር ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ይቻላል? የሚለው ሲኾን ምላሾቹም ኹለት ናቸው፡፡

‹‹ችግሮች ኹሉ የየራሳቸው በጎ ገጾች አሏቸው›› እንዲሉ፣ ማኅበሩ የደረሰበት ይህ ፈታኝ ጊዜን ተከትለው የሚመጡ ኹለት ወቅቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ በቀጣዩ ወር የሚታሰበው የስቅለት ቀን ነው፡፡ ኹለተኛና በእጅጉ የተሻለ ነው ብዬ የማስበው ጊዜ ደግሞ ቀጣዩን የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ለማስገደጃነት መጠቀም ነው፡፡

በተለይም የሃይማኖቱ ተከታዮች በሙሉ በየቤተ ክርስቲያኑ የሚውሉበት የስቅለት በዓል አገዛዙ እጁን ከማኅበሩና ከቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይ እንዲያነሣ ለመጠየቅ የተመቸ ቀን ስለመኾኑ ማስታወስ አባላቱን አሳንሶ መገመት እንዳይኾን ተስፋ አደርጋለኹ፡፡ ከዚኽ የቀረው ጉዳይ ‹‹ሃይማኖታችኹን ተከላከሉ›› ብለው ላስተማሩት ቅዱሳት መጻሕፍትና ለሰማያዊው መንግሥት መታመን ብቻ እንደሚኾን እንረዳለን፡፡
************************************************************
ማስታወሻ፡- ጽሑፉ በመጽሔቱ የቀረበበት ርእስ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን የመጨረሻዎቹ ቀናት›› የሚል ነው፡፡ ይኸው የጽሑፉ ዐቢይ ርእስና ጽሑፉ ማኅበረ ቅዱሳን ለደረሰበት ፈታኝ ወቅት በመፍትሔነት የጠቆማቸው ነጥቦች ከጡመራ መድረኩ አንጻር ከመጠነኛ ማስተካከያ ጋራ ተጣጥመው እንዲቀርቡ መደረጋቸውን እንገልጻለን፡፡

Advertisements

34 thoughts on “ማኅበረ ቅዱሳን የደረሰበት ፈታኝ ወቅት

 1. Teshale Mezgebu March 30, 2014 at 2:21 pm Reply

  where is secularism???

  • Teshale March 30, 2014 at 2:28 pm Reply

   The aim of destructing MK is due to the following very reasons.
   1/ The gov’t does not want the church to have better futurity, while MK is working in-revers of this fact.
   2/ MK members have national unity than ethnic diversity.How this gov’t likes this.
   3/ This gov’t never like the collaboration of educated people.
   4/ Mainly, the destruction of the church is the long plan of the existing government.
   Therefore, who are working with the government to practice this evil aim:
   1/ The government it self.
   2/ The government Authorities who are working for their religion. Because the protestant has long plan to control the church in the near future.
   3/ The fake priest who are working for the government in the church. Like Nibure Ed Elyas etc
   4/ The fake priests who are working for protestants in the church.
   5/ The most corrupted the church’s employees.

   All these are working together secretly for their common aim.But it seems no one stands for MK. This is an indication that God is working with them. These artificially powered politicians they think they have all power to do what ever they want, but GOD is more than them.

 2. Anonymous March 30, 2014 at 4:22 pm Reply

  ‹‹ቤተ ክርስቲያኗ ተከታዮቿን፣ ለነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲገዙ ከማስተማር በዘለለ የብሔራዊ ንቃት(ማንነት) ማስተማርያም ነበረች፡፡ …ለህወሓት እንቅስቃሴ ዕንቅፋት እንደነበረች ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያኒቱን በህወሓት ዓላማ ሥር ለማሳደር ፍላጎት ነበር፤ በዚህ የተነሣም የእርስዋን ተጽዕኖ ለማግለል ጥልቅ ርምጃ ወስደዋል፡፡›› /ገጽ 315 – 316/

  “KE EGZIHABIHER GAR YEMITALU YIDEKALU”

  REFLECTION OF GLOBALIZATION- DESTROYING GENERATION:- OBJECTIVE OF EPDR

 3. yetayali ewunetu March 30, 2014 at 4:24 pm Reply

  it is clear that the current government do not like to see power full Orthodox church, Dr. Shiferaw T/mariam is the one selected to fulfill this evil mission. our fathers fear political leaders than Lord. If you are from Christ no can can eliminate you . please try to investigate your error. there are many options to continue your goal here or outside. downfall to devil !

 4. dawit March 30, 2014 at 4:25 pm Reply

  ማኅበረ ቅዱሳን የሚፈርሰው በራሱ ተግባር ነው፤ ኢሕአዴግ ላለፉት 22 ዓመታት መቼ ነካው?

  ይህ ህንጻ የማነው? የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን? የመንበረ ፓትርያርክ? የኢንቨስተር? የነጋዴ? የአስመጪና ላኪ?

  የሀገሬ ሰው «ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል» ይላል። ይህ አባባል ለሰሞነኛው የማኅበረ ቅዱሳን የጅቡ በላኝ ጩኸት ይስማማል። ኢህአዴግ ሊያጠፋኝ ነው ሲል በየግል ጋዜጣው ማስወራቱ 22 ዓመታት ኢህአዴግ በሚመራት ሀገር ውስጥ ያልነበረ ይመስላል። ሲነግድ፤ ሲያስነግድ፤ ሲሸጥ ሲለውጥ፤ከግብርና ታክስ ተከልሎ በሚሊዮኖች ብር ህንጻ ሲገነባ በሀገሪቱ ኢህአዴግ ያላየው ወይም የማያውቀው ይመስላል። ኢህአዴግ ማኅበረ ቅዱሳንን በአስማት ይሁን በምትሃት እስከዛሬ ሳያየው ቆይቶ አሁን ለማየት ዓይኑን ሲከፍት ማኅበረ ቅዱሳንን አገኘውና ሊበላው ስለሆነ ማኅበረ ቅዱሳን ኢህአዴግ ሊያጠፋኝ ለምን ፈለገ ሲል ለመጠየቅ የተገደደ ይመስላል። በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለው ተግባሬ ከማኅበረ ካህናቱ ጋር አጋጨኝ፤ በማያገባኝ አስተዳደር ውስጥ እጄን ሳስገባ ተገኘሁ እንዳይል ከመሬት ተነስቶ ኢህአዴግ ሊውጠኝ ነው ወደሚል ቅስቀሳ መግባቱን ከመምረጡ በስተቀር በምድር ላይ ያለው እውነታ ግን የምርጫ ዘጠና ሰባት ውጤትና ተከትሎ የመጣው ፖለቲካዊ ቀውስ ስንቱን ፓርቲና የተቃዋሚ መሪዎች እየደፈጠጠ ሲያልፍ ማኅበረ ቅዱሳን ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ ታዛ ተጠልሎ አልፏል። ኢህአዴግ ቢያጠፋው ኖሮ ያኔ ባጠፋው ነበር።
  ከዚህ በፊት ማኅበሩ እንደጥራጊ አውጥቶ የጣለው ዳንኤል ክብረት ይህን ኢህአዴግ ሊበላኝ ነው የሚለውን የማኅበረ ቅዱሳንን ዘፈን እንዲህ ሲል በደጀሰላም ብሎግ ላይ አውጥቶ ነበር።
  «እኔ እንደምገምተው የማኅበሩ አባላት መንግሥትን እንዲፈሩ እና እንዲጠሉ የሚፈልጉ አካላት በአመራሩ ውስጥ ሳይኖሩ አይ ቀርም፡፡ ምንጊዜም አንዳች ከባድ ነገር ሲነሣ መንግሥት እንዲህ ብሎናል፣ በዚህ ስብሰባው እንዲህ ብሏል፣ ሊዘጋን ነው፣ ሊያስረን ነው፣ ሊጨርሰን ነው ከማለት ያለፈ አንድም ቀን በጎ ነገር ስለ መንግሥት የማያነሡ አካላት አሉ»
  ስለዚህ ከዚህ አባባል ተነስተን ልንል የምንችለው ነገር ይህ መንግሥት ሊበላን ነው የሚለው ዜማ እንደስልት የተያዘና መንግሥት በአባላቱ ዘንድ እንዲጠላ የተዘየደ መሆኑ ነው። ከዚያም ባሻገር መሰሪ ስራውን ለመደበቅ ራሱን ጻድቅ አድርጎ በሌሎች ሰዎች ዘንድ ለመሳል የታቀደ ጥበብ ሲሆን ጻድቁ ማኅበረ ቅዱሳንን ኢህአዴግ ሊያጠፋው ስለሆነ ኦርቶዶክሳውያን የሆናችሁ ሁሉ የዚህን መንግሥት መሠሪነት ተመልከቱ ብሎ ክፉ ስዕል ለመስጠት የተፈለገ ብልጠት ነው።
  እውነቱ ግን ማኅበረ ቅዱሳን ነጋዴ ድርጅት መሆኑ ማንም ያውቃል። የግል ይሁን የአክሲዮን ማኅበር መሆኑ ያልታወቀና የራሱን ሀብት የፈጠረ ተቋም ስለመሆኑም ስራው ምስክር ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ከንግድ ተቋማቱና ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮቹ ባሻገር የራሱ የሆኑ አባላት ያሉትና የአባልነት መዋጮ የሚሰበስብ ድርጅት ነው። ከዋናው ማዕከል ጀምሮ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቁመት የራሱ የሆነ መዋቅርና ራሱን የቻለ አደረጃጀት ያለው ነገር ግን አደረጃጀቱ በየትኛው የሀገሪቱ የአደረጃጀት ፈቃድ ላይ እንደቆመ ያልታወቀ መሆኑም እርግጥ ነው። ይህንን የራሱ ተቋማዊ ኅልውና ያለውን ማኅበር በሀብቱ፤ በንግድ ተቋማቱ፤ በመዋቅራዊ አካላቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመቆጣጠርና የማዘዝ ምንም ሥልጣን የላትም። በአንጻሩም ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስር ተሸፋፍኖ እንደመጠለሉ መጠን ቤተ ክርስቲያኒቱ በማኅበሩ ላይ የመቆጣጠርና የማዘዝ ሥልጣን እንዳላት ግምት ያለው በመሆኑ መንግሥት ይህን ድርጅት ነክቶት አያውቅም። ስለዚህ ይህንን ማኅበር ቤተ ክርስቲያኒቱም፤ መንግሥትም ሳይመለከቱት ከሁለት ወገን ቁጥጥር ነጻ ሆኖ 22 ዓመት ዘልቋል።
  «ለሁሉም ጊዜ አለው» እንዲሉ ሆኖ ማኅበሩን ማነህ? ምንድነህ? የት ነህ? ምን አለህ? ምን አገባህ? የሚሉ ካህናትና የአመራር አካላት ተባብረው በመነሳት መጠየቅ ሲጀምሩ ጥቂት ሟሳኞችና አሟሳኞች ወደሚል ሃሳብ ለመውረድ ተገዷል። በምንም ደረጃ ያሉ ሰዎች ማኅበረ ቅዱሳንን መክሰስ መቻላቸው የማኅበሩን ማንነት ማሳያው ተግባሩ እንጂ ክሱ አይደለም። እየተከሰሰ ያለው ማኅበር በተግባሩ ያልታወቀ ማኅበር ባለመሆኑ በሟሳኞችና አሟሳኞች የቃላት ጫወታ እየፈጸመ የቆየውን ሸፍጥ ሸፍኖ ማስቀረት አይቻልም።
  ማኅበረ ቅዱሳን በተግባር በሌለው ሥልጣንና መብት መናፍቃን ናቸው ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን በራሱ ጥቁር መዝገብ አስፍሮ አስደብድቧል፤ ሰልሏል፤ ስም አጥፍቷል፤ አስፈራርቷል፤ እንዲሰደዱ አድርጓል። ማኅበረ ቅዱሳን በቤተክርስቲያኒቱ ስም መጽሔትና መጻሕፍትን፤ ካሴትና ቪዲዮ፤ አልባሳትና ንዋየ ቅድሳትን ከታክስና ከቀረጥ ነጻ ሆኖ ነግዷል። የማኅበረ ቅዱሳን አቋም የሚቃወሙ ሁሉ ጠላቶቹ ናቸው። የሚደግፉት ደግሞ ጳጳሳቱ ሳይቀሩ ወንጀል ቢኖርባቸው እንኳን የቤተ ክርስቲያኒቱ ታማኝ አገልጋይ ተደርገው ዜና ይሰራላቸዋል፤ ሙገሳ ይሰጣቸዋል። አባ እስጢፋኖስን ማንሳት ይቻላል። ጠላቶቼ ከሚላቸውና ስማቸውን ሌሊትና ቀን ሲያጠፋቸው ከቆዩት ጳጳሳት ውስጥ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ደግሞ የጥላቻ የአፍ መፍቻው ናቸው። ሌሎቹም ፈርተው አንገታቸውን ደፍተውለታል። የተገዳደረውን አንገት ያስደፋል፤ አለያም ቀና ካለ አንገቱን ይሰብራል። ሌላው ቀርቶ ሲያመሰግናቸው የነበሩትን አዲሱን ፓትርያርክ ጠላቶቼ የሚላቸውን ሰዎች ሲቀጣ በቆየበት መልኩ በስም ማጥፋት ቅጣት ናዳውን እያወረደባቸው ይገኛል። ለራሱ ኅልውና ብቻ የሚጨነቅ፤ ካልመሰለው ደግሞ ሲያወድሳቸው ለነበሩት ሳይቀር ግድ የሌለው ማኅበር ስለመሆኑ ከድርጊቱ ተነስቶ መናገር ይቻላል። ወትሮውንም ሸፋጭ ነጋዴ ገንዘቡን እንጂ ወዳጅና እውነት በእሱ ዘንድ ዋጋ የሌላቸው ስለሆኑ የሚያስበው ጊዜያዊ ትርፉን ብቻ ነው። በዚህ ዙሪያ ማኅበሩ አሸንቅጥሮ የጣለውና ለተቀበለው የእጅ መንሻ በውጪ እንዳለ የሚለፈልፈው ዳንኤል ክብረት ማኅበሩ ስለግለሰቦችና ስለቤተ ክርስቲያኒቱ ደንታ ቢስ እንደሆነ ያጋለጠው እንዲህ ሲል ነበር።
  «ዲያቆን በጋሻው ማስተማር የጀመረው መቼ ነው? ማኅበሩ በነዲያቆን በጋሻው ላይ ሃሳብ ዛሬ መሠንዘር ለምን ጀመረ? በጋሻው ለቤተ ክርስቲያን አደጋ ነው ብሎ ስላሰበ አይደለም፡፡ በጋሻው ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ ስለ ተናገረ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ምንም ያልተናገረው ማኅበር ስሙ ሲነሣ ቤተ ክርስቲያን ተነካች ብሎ ተነሣ፡፡ ማኅበሩ አቡነ ጳውሎስን በተመለከተ የተለየ አቋም መያዝ የጀመረው መቼ ነው? «እርሳቸው ማኅበሩን ሊያፈርሱ ነው» ብሎ መሥጋት ከጀመረ በኋላ፡፡ አባ ሠረቀንም ቢሆ ንኮ ዛሬ ዛሬ በእምነት ችግር ይከሳቸዋል እንጂ፣ ከእርሳቸው ጋር ያለው ዋናው ችግሩ ማኅበሩ መነካቱ ነው፡፡ አባ ሠረቀ ማኅበረ ቅዱሳንን ሳይነኩ የፈለጉትን ቢሆኑ ኖሮ አይናገራቸውም ነበር፡፡ ባለፈው ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ ላይ ችግር ሲፈጠር፣ ዝምታን መርጦ የነበረው አመራር የመንግሥት አካላት ከቤተ ክህነቱ ባለሥልጣናት ጋር ሆነው ስለ ማኅበሩ ሲያወያዩት ግን አገር ይያዝልኝ አለ፡፡ የአዋሳ ምእመናንን ችግር በዝምታ ያለፈው አመራር አባ ሠረቀ አንዳች ነገር ተናገሩ ብሎ ድምፁን አሰምቶ ተናገረ፡፡ እነዚህ እና መሰል ሁኔታዎች አመራሩ የሚቆረቁረው ማኅበሩ ሲነካ እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱ ስትነካ አለመሆኑን ያመለክታሉ» ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን ከራሱ በላይ ማንንም እንደማይወድ እርግጥ ነው።
  ማኅበረ ቅዱሳን በፖለቲካው ዙሪያ ከምርጫ 97 በፊትም ሆነ በኋላ ስላለው ሁኔታ መንግሥት በቂ መረጃ እንዳለው ይሰማል። በዚህ ዙሪያ መንግሥት ያለውን መረጃ እስኪያወጣ ድረስ የምንለው ነገር የለም። ነገር ግን ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲያምሳት መቆየቱን፤ እጁን እያስገባ ሲኖዶሱን ሳይቀር እንደሚጠመዝዝ እናውቃለን። ማኅበሩ ደፋርና የልብ ልብ የተሰማው አንዳንድ የሲኖዶስ አባላት ተጠግቶ የጉባዔ ሃሳብ በራሱ መንገድ እስከመጠምዘዝ የመድረሱን አቅም እየለካ በመሄዱ ነው። ዛሬ ላይ ያ ነገር የለም። ፓትርያርክ ማትያስ ለዚህ የማኅበሩ ሃሳብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ገና አንድ ዓመት ሳይሞላቸው ከኢህአዴግ ጋር ተመሳጥረው ሊያጠፉኝ ነው እያለ ስም ወደማጥፋት ወርዷል። በተቃራኒው ደግሞ ማንም እንደማያጠፋው በሚገልጽ ጀብደኝነቱ ፓትርያርክ ጳውሎስም እንደዚሁ ሊያጠፉኝ ሞክረው እንደማያዋጣቸው አውቀው አጃቸውን ከእኔ ላይ ለማንሳት ተገደዋል በማለት ለፓትርያርክ ማትያስ የማስጠንቀቂያ ማስታወቂያ እየሰራ ይገኛል። እጅዎን ከእኔ ላይ የማንሳትን ጉዳይ ችላ ሳይሉ ከቀድሞው ፓትርያርክ ትምህርት ውሰዱ በማለት ማሳሰቢያ እየሰጠ መሆኑ ነው። የሚፈራው ከተገኘ ጥሩ ጀብደኝነት ነው፤ ነገር ግን ባለቀ ጊዜ ማላዘን ዋጋ የለውም። ማኅበረ ቅዱሳን ቤተክርስቲያኒቱ ስንት ችግር ባለባት ሰዓት ራሱ ችግር ፈጣሪ ሆኖ ካለቦታው የተገኘ ማኅበር ስለሆነ ተገቢ ቦታውን መያዝ ካለበት ሰዓቱ አሁን ነው። ማኅበረ ካህናቱና የቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር አባላት ጠንክሮ መታገል የሚገባችሁ ወቅት ቢኖር ዛሬ ነው። ማኅበሩ ቁጭ ብሎ አዋጭ የሆነውን መንገድ መቅረጽ ካለበት ቶሎ ብሎ ይህንኑ እንዲፈጽም ምክር እንለግሰዋለን። የአክሲዮን ማኅበር፤ የሃይማኖት ተቋም፤ በጎ አድራጊ ድርጅት ወይም የተሻለ ነው ብሎ የደረሰበትን ውሳኔ ወደተግባር መቀየር ካለበት ቀኑ ሳይመሽ በብርሃኑ ይሆን ዘንድ ልናሳስበው እንወዳለን። ሲሆን ዘንድሮ፤ ካልሆነም በቀጣዩ ዓመት፤ ቢረዝም፤ ቢረዝም አንድ ቀን ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጉያ እንደመዥገር የተጣበቀበት ቀን እንደሚያበቃ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ምክንያቱም ማኅበሩና ተግባሩ፤ ካህናቱና አስተዳደሩ መቼም ቢሆን አሁን ባለው መንገድ አብረው መጓዝ አይችሉምና ነው። ከዚህ ሁሉ ፓትርያርኩም፤ ካህናቱም፤ አመራሮችም፤ መንግሥትም ይህንን ማኅበር ቦታ የማስያዙን ጉዳይ ችላ ሊሉት አይገባም። ማኅበረ ቅዱሳን ሳይኖር ቤተ ክርስቲያን ነበረች፤ ማኅበረ ቅዱሳን ሳይኖርም ትኖራለች!!! «ማኅበረ ቅዱሳን ከሌለ ቤተ ክርስቲያን ትጠፋለች» የሚለው ራሱ ማኅበረ ቅዱሳን ብቻ ነው።

  • Anonymous March 30, 2014 at 6:30 pm Reply

   mr dawit, I think your position is clear – you are one of the small-mined tplf cadres; how on earth you blindly accuse ማኅበረ ቅዱሳን without a single evidence? …. shame on you!!

  • aynalem March 30, 2014 at 7:14 pm Reply

   MK is people who can’t be destroyed. Answer for our patriarch”the Egyptian orthodox church is now leading by physicien (His Holiness Aboune Theodros was studying pharamcy),bete Kristian be chemistry ena be physics atemeram lalut

  • Anonymous March 30, 2014 at 8:59 pm Reply

   ዳዊት አንተ ውሻ ነህ ውሻ በበላበት ይጮኃል አይን አውጣ መናፍቅ ወያኔ

  • ሊቀ ነቢያት March 31, 2014 at 8:08 am Reply

   ጥላቻህ እጅግ የገነነ ነው ከአንተ ጩኸት ይልቅ የዘረዘርካቸው ነገሮች እውነት ቢሆን እንኳን ማቅ ሥራ ሠርቶ ስለሆነ የአንተ ጩኸት መውደቂያ የለዉም

  • በአማን ነጸረ March 31, 2014 at 10:10 am Reply

   ልጅ DAWIT እግዚአብሄር እጅህን ይባርከው!!ቋ… ሲል ልቤ ውስጥ ተሰማኝ!!ጽሁፍህን ትንፋሼን ውጬ ነው የዘለቅሁት!!የልቤን ተናገርክ!!አስተያየት ሰጭው ሁሉ 2ሺህ ዘመን የኖረችውን ቤ/ክ ህልውና በማኅበረቅዱሳን መኖርና አለመኖር ሊለካ ሲሯሯጥ አይቼ ለካ በማኅበር ተሁኖ የሚሰራ ኃጢአትና ወንጀል ጽድቅ ነው ወደ ማለት ወርጄ ነበር!!ለካ ዘመን መዋጀት ማለት አባቶችንና ኮሌጆችን ለሁለት ከፍሎ በማራከስና በማወደስ ነው እንደማለት እየቃጣኝ ነበር!!አንተ ብቅ ስትል ተጽናናሁ!!
   እኔም የራሴን ጅራፍ ይዤ እመለሳለሁ!!ቤ/ክ በስመ ነጻ ሚዲያዎች እና በጥቂት ልበቀሊላን ማእከላዊነቱዋ ተፈቶ ዝርው ስትሆን ማየት አንፈልግም!!ማኅበረቅዱሳንን ወደ ቦታው!!ቦታው እዛ ታች መምሪያ ስር ነው!!ይሄን ሁሉ የገነነበትን በጎ ስራ የሰራውም በመምሪያው ስር እያለ ነው!!ምንድን ነው አሁን ደርሶ አገር ይያዝልኝ?? የሽግግሩ ጊዜ እሱ እንዳሰበው ስላልሆነ እኮ ነው!!ምሁራን… ምሁራን…እያላችሁ ራሳችሁን ትሸጣላችሁ!!ለመሆኑ የትኛው ምሁራን ስብስብ ነው ሀገሪቷን ችግር የቀረፈው??የእኛን ምሁራን እኮ ምናውቃቸው ቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር ሲያመጡ፣በ97 እሳት አትጫጫሩ ሲሉን ነው!!እናንተም ከዛ አንጎቨር የነቃችሁ አትመስሉም!!ሀገሪቱ የምሁራን ስብስብ አይበርክትልሽ ተብላ ተረግማለች መሰለኝ!!

  • Anonymous March 31, 2014 at 1:22 pm Reply

   ante orthodox calhonek ayagebahim. bethone gen yehin atelem neber

  • Anonymous March 31, 2014 at 2:43 pm Reply

   Mr. Dawit, you know why you write this comment. And we are also aware of that. don’t be foolish as such!!

  • mastewal March 31, 2014 at 3:07 pm Reply

   Never look the comment by this person easily, it’s looks something serious,, it seems the end to Christianity in Ethiopia, this people never fail to destroy what they go for. Mechem yegehanem dejoch ayechluwatim new enji.

  • Anonymous March 31, 2014 at 5:08 pm Reply

   egziabher ke egnagar bayihon telat minigna benaken
   gin hulum begizew alfoal chernetu sitebiken
   yemitwagaw ye egziabherin lijoch mehonun bitawuk tiru neber ”
   ” abetu yemiserutin ayawukumina yikir belachew” enilalen
   mk yemitekelilewum yemibetinewum zelealemawi amilak enji seyitan aydelem.
   ante seyitan zewor bel kefite!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!1

  • Besemayat March 31, 2014 at 8:50 pm Reply

   be achiru ye WEYANE degafi na ashikabach negn atlim min yih hulu asikebatereh!!! Egzihabher amlak Libonahin yabiralih!!!

 5. 2119 March 30, 2014 at 6:09 pm Reply

  1. ‹‹የአፍራሽ ግብረ ኃይሉን ጡንቻ ለመመከት ሁሉም በያለበት ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል ፤ …..››
  2. ‹‹ይህ የአንድ ማኅበር ጉዳይ ሳይሆን አንዲት ቤተ ክርስቲያንን የማፈራረስ ስም አጠራሯን የማጥፋት ሴራ ነው…..››
  3. ምንም ጥርጥር የለውም “አቡነ” ማቲያስ ከ”አቡነ” ጳውሎስ ይብሳሉ !!!!!
  4. አብዛኛው ሕዝበ-ክርስቲያን ይህን መረጃ እንዲያገኝ ሁላችንም እንረባረብ!!!!
  5. ከሁሉም በላይ ሁላችንም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በፅናት የምንቆምበት ወሳኝ ወቅት ቢኖር ይህ ነው!!!!

 6. Joney March 30, 2014 at 6:47 pm Reply

  Am sorry betame .

 7. dagmawi March 30, 2014 at 11:29 pm Reply

  The TIGRAY LED regime identified THREE MAIN ENEMIES
  1 Orthodox church
  2 Amhara
  3 Amharic Language
  so it is expected from this vicious, evil and selfish TPLF people to unleash their attack against MAHBER KIDUSAN who is serving as a basis for ORTHODOX CHURCH by teaching young Ethiopians about social values, and their religion
  WOYANES are against anything Ethiopian they don’t want the youth to learn about their religion, and their history that is why they are continuously attacking MAHEBER KIDUSAN since its inception and they will dismantle it soon HOW SOMEONE WITH A NORMAL MIND ACCUSE MAHBERE KIDUSAN be akaririnte kkkkkkkk TIME will come and these evil PEOPLE WILL pay the price

 8. Anonymous March 31, 2014 at 5:21 am Reply

  ay dawi yeleyelh tehadiso, merzama menafikina………

 9. Anonymous March 31, 2014 at 6:37 am Reply

  1. ‹‹የአፍራሽ ግብረ ኃይሉን ጡንቻ ለመመከት ሁሉም በያለበት ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል ፤ …..››
  2. ‹‹ይህ የአንድ ማኅበር ጉዳይ ሳይሆን አንዲት ቤተ ክርስቲያንን የማፈራረስ ስም አጠራሯን የማጥፋት ሴራ ነው…..››
  3. ምንም ጥርጥር የለውም “አቡነ” ማቲያስ ከ”አቡነ” ጳውሎስ ይብሳሉ !!!!!
  4. አብዛኛው ሕዝበ-ክርስቲያን ይህን መረጃ እንዲያገኝ ሁላችንም እንረባረብ!!!!
  5. ከሁሉም በላይ ሁላችንም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በፅናት የምንቆምበት ወሳኝ ወቅት ቢኖር ይህ ነው!!!!

 10. Anonymous March 31, 2014 at 6:39 am Reply

  Mr Dawit Ke nate ga kalewu yelek egna ga yalewu ashenafi newu..chewatawu kamarachihu mekaberachihun azegaju….

 11. Anonymous March 31, 2014 at 6:50 am Reply

  የሚገርመው አላማቸው አለማዊ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እንኳን እንደዚህ ስለ ቤተክርስቲናችን መረጃ ሲኖራቸው እኛ በቤቱ የምንኖር ዝም ብለን የምንመላለስ ክርስቲኖች ልብ አለማለታችን በጣም ነው የሚገርመው…… አስኪ በየቤተክርስቲኑ በተለይም በትልልቆቹ የተሰማሩትን መነኩሴ መሳይ አስተዳዳሪዎችን ተመልከቱ ለካ ገንዘቡን በይፋ እየዘረፉ ፎቅ ስሰሩ፣ መኪና ሲገዙ እንዴው አንድ መነኩሴ እንዲህ ሲሆን እንኳን ሰው እግዚአብሔር ምን ይለናል ብለው የማይፈሩ ለምንድን ነው ብየ አስብ ነበር ለካ የነሱ አላማ ከመዝረፉ ባሻገር የቤተክርስቲናችንን ተቀባይነት ከህዘቡ ለማራቅ ነው…. ለዚህም እኮ ነው በየሰፉ፣ በዘር የሚከፋፍሉን…. ክርስቲያኖ ሌሎች በአለም ያሉት እህት አቢያተ ክርስያናት አሁን እንዲህ ከሥራት ውጭ የሆኑት ልክ እንደዚህ አይት ሥራ ተሰርቶባቸው ነው ስለዚህ ልንነቃ ይገባናል….. በተለይም አብዛኛው ሰው መረጃ ላይደርሰው ስለሚችል እያነበብን ፕሪንት እያደረግን ለሁሉም ክርስቲያን ማሳወቅ አለብን…… ማኅበረ ቅዱሳን እኮ በልቦናችን ያለ እጂ ህንፃ ላይ የተቀመጠ አይደለም በየአመቱ በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ በየዓመቱ የቤተክርስቲንን ትምርት የተማርን ችግሯን የተረዳን በሚሊዮኖች የምንቆጠር በሀገር ቤት ብቻ ሳይሆን በአለም የተሰማሩ በሥራቸው አንቱ የሚባሉ ናሳን ጭምር የሚመሩ ትልዶችን ያቀፈ እኮ ነው……

 12. Anonymous March 31, 2014 at 7:30 am Reply

  ከኛ ጋራ ያለው ከሁሉም ይበልጣል

 13. Mesfin Dubale March 31, 2014 at 7:33 am Reply

  አሁን ያለን አማራጭ አንድ ብቻ ነዉ በያለንበት ነቅተን መዘጋጀት- በልዑል እግዚአብሂር ቸርነት በእመቢታችን ምልጃ በቅዱሳን ጥበቃና ፀሎት ታሪክ ይቀየራል፡፡

 14. Anonymous March 31, 2014 at 9:12 am Reply

  No problem. If they destroy the current Mahibere Kidusan, surely we will establish 1000 Mahibere kidusans. Thanks God!

 15. Anonymous March 31, 2014 at 2:22 pm Reply

  ሰዎች ! ተመስገንም ሆነ አንዳንዶች የሳቱት ነገር መንግስት ማህበረ ቅዱሳን በእርግጥም የአክራሪዎች ጎራ ነው ብሎ አይደለም ዒላማ ያደረገው ፡፡ ትልቁ ምክንያት balance ማድረጊያ ነው ፡፡ መንግስት ባልተጠና መልኩ ሙስሊሞችን የአክራሪዎች ምሽግ ናችሁ ብሏቸዋል ፡፡ እርምጃም ወስዷል ፡፡ (በግሌ እርምጃው ሙሉ ለሙሉ ስህተት ነበር የሚል እምነት የለኝም ፡፡ ስክነት ፣ ማስተዋልና መለየት ግን ይጎድለዋል )ይህ ደግሞ የሚታይ ኪሳራ አምጥቶበታል ፡፡ በእርምጃው ምክንያት ብዙዎች ሙስሊሞች በክርስቲያን መንግስት እንደተጠቁ ተሰምቷቸዋል ፡፡ ለቅስቀሳና ድጋፍም ተጠቅመውበታል ፡፡
  ስለዚህ መንግስት ራሱን ነፃ ለማውጣት ከክርስቲያኑ ወገን ‹‹ አክራሪ ፈልጎ ማግኘት ›› ነበረበት ፡፡ ቀዩ ካርድ ማህበረ ቅዱሳን ላይ ወደቀ ፡፡ እነሆ አቶ መለስ የነቀነቁትን ጦር አቶ ሀይለማርያም ለመወርወር ተዘጋጅተዋል ፡፡
  አለበለዚያማ – ሀይማኖተን ማጥበቅ ፣ ለሥርዓቱ መገዛትና መቆም ፍቺው ‹‹ አክራሪነት ››ቢሆን ሠልፈኞቹም ብዙ በሆኑ ነበር ፡፡ ለማንኛውም መንግስት ከኪሣራ ወደ ኪሣራ በደመነፍስ መሮጡን ቀጥሏል ፡፡ እኛም ከዳር ቆመን እያየነው ነው ፡፡

 16. Anonymous April 1, 2014 at 7:21 am Reply

  No No No, what ever is the challenge, we never think to disturb The Good Friday to oppose the Government. We believe, if the Gov is doing as written on webs, God him self will fight. MK Ye amets mahiber aydelem.

 17. Anonymous April 1, 2014 at 10:09 am Reply

  ጥቅም ሰጪ ግን የማይታወቅ ክፋት ያዘሉ ተቋማት በታሪክም ተከስተዋልና አሁንም ይከሰታል ብሎ እንዲህ ማሰብ ይገባናል፡፡ ስለ ማህበረ ቅዱሳንም ማንነት እንዲሁ በጥንቃቄ ማጤን ከኦርቶዶክሳዊያን ሁሉ ይጠበቃል፡፡ በተለይ በተለይ በአስተምሮ ላይ ማህበሩ ከመመስረቱ በፊት ከተጻፉ መጽሐፍት ጋር በማነጻጸር ተረት ተረትን ይቃወማል ወይስ አይቃወምም ማለት እና መወሰን ይገባል እንጂ በደፈናዉ መናገር ለምክኒያት አልባ ስህተት ይዳርጋል ብዬ አስባለዉ፡፡ ምክኒያቱ በመንግስት ከሚፈራዉ አሸባሪነት ይልቅ ምእመናን የሚያስት አሳቾች በእምነት ዉስጥ ትልቁን የአደገኝነት ሥፍራ ይይዛሉና፡፡ ስለ ማህበረ ቅዱሳን ለማዉራት የተዘጉ አድባራትን ማስከፈት ካህናትን የመቅጠር ስራን መስራቱን አይቶ ማህበሩ ኦርቶዶክሳዊ ነዉ ማለት ስህተት ነዉ ስል ያለ ማቅማማት ነዉ፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ድምጽ ሰምቶ በገፍ ወደ ቤተክርስትያን የገባዉን ወጣት በክርስቶስ ወንጌል ፍሬ እንዳያፈራ አናቂ እሾክ ሆኖ በተረት ተረት ትምህርቱ አጋልጧልና፡፡ ማህበረ ቅዱሳን መንግስት በሚለዉ አሸባሪነት ለማለት ይከብድ ሆናል ነገር ግን ምእመናንን በተረት ተረት ትምህርት ህይወት(የክርስቶስ ትምህርት) ከሆነች የክርስትና መንገድ ፈቀቅ እንዲሉ አድርጓል ስል በሙሉ እምነት ነዉ፡፡

  • Anonymous April 2, 2014 at 6:29 am Reply

   አቤት ባለ መረጃ፤ ድንቄም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን ተከትሎ ከክርስቶስ የተለየው ትውልድ የትኛው ይሆን ወዳጄ፤
   የተዘጉ አብያተ ክርክስቲያናትን ስላስከፈተ ብቻ አናድንቀው ማለት ምንኛ ፌዝ ነው እናንተ፤ ከክርስቶስ ወንጌል አለመለየት ማለት ጌታ ጌታ ብለው ከሚጮሁባቸው አዳራሾች መለየት ማለት ከሆነ ትክክለ፤ ከጌታ ወንጌል አለመለየት ማለት ከሱስ፣ ከስርቆት፣ ከሙሰኝነት፣ ከቤ/ክ ጡት ነካሽነት፣ ከኃጢያት ርቆ በንስሐና በሥጋ ወደሙ ተወስኖ መኖር ከሆነ ትክክል፤ ከጌታ ወንጌል አለመለየት ማለት በዓለምና በምድራዊ እውቀት ብቻ ታጥሮ ሊጠፋ የሚችልን ትውልድ አቅፎ የተዘጋች ቤ/ክንም ከፍቶ፣ የተፈቱ ጉባዔ ቤቶችን አሰባስቦ፣ አብነት መምህራንና ተማሪዎችን ከስደት መልሶ በተቀደሰው የክርስቶስ ቤ/ክ ማኖር ከሆነ ትክክል ነው፡፡
   ማኅበረ ቅዱሳንና ሰንበት ት/ቤቶች፤ ሌሎችም እውነተኛ ማኅበራት ከዚህ ውጭ ምን ሰሩ ወዳጄ፤
   የእናንተ ዓላማ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት እንዳይከፈቱ፤ ወጣቱ ሕይወቱን በየአዳራሹ እንዲያጣ፤ ንጽህት ቅድስት ተዋሕዶ ቤ/ክ እንድትጠፋ ስለሆነ ግን ማኅበረ ቅዱሳንን ዝም ብለን አንደግፍ አስባለህ፡፡ ለማለዘብም ሞከርክ፡፡ ተወው ማኅበረ ቅዱሳን የእናንተ ድጋፍና ልዝብ ግን መርዘኛ አንደበትን አይፈልግም፡፡ ይልቅ ግልጽ አቋማችሁን አውጡና እንተያይ፡፡

  • hiruy April 2, 2014 at 9:44 am Reply

   ይድረስ ኦርቶዶክሳዊ ትውፊቶችን ሁሉ ተረት ለማለት ለምትፋጠኑ!!
   1. በመ/ቅዱስ ቅዱሳንን አማልዱን ማለትና ለቅዱሳን የአክብሮት ስግደት መስገድ ኃጢኣት ነው የሚል ጥቅስ ካለ አምጡልን!!ቃሉን ካላመጣችሁ ግን እናንተንም የተረት አባት አድርገን እንድናያችሁ እንገደዳለን!!በእናንንተ አነጋገር ከተመራን እነ ኤልሻዳይና እነ ኢማኑኤል ቲቪዎች የሚደሰኩሩዋቸው ዲስኩሮችም ተረት ናቸው ማለት ነው!!በተለይ ትንቢታዊ ኮንፈረንስ በሚባለው ዳንኪራችሁ የሚወራው ተረትና የነፓስተር ጆሹዋ የፈውስ ተረት ሆዴን እስኪያመኝ ያስቀኛል!!ጥንቆላ ከረባት ለብሳ በጉዋሮ በር ትምጣ!! ያሰኘኛል!!ለስንት የጠብቅናችሁ ሰዎች የወያላ ጎረምሳ ፓስተሮችና የናይጀሪያ ጠንቁዋይ ፓስተር ተብየዎች መጫወቻ ሆናችሁ አረፋችሁት እላለሁ!!
   2. በተለይ ኢ/ዊ ፓስተሮች፤ግዴለም ወደ ኦርቶዶክስነትም አትመለሱ!!ግን እባካችሁ ለእርዳታ ስትሉ ኢንተርናሽናል የሚል ታፔላ እየለጠፋችሁ ሀገሪቱን የውጭ ሚሺነሪዎች መናህሪያ አታድርጉዋት!!ቢያንስ የቸርቹ ቁልፍ በእናንተ እጅ ይሁን!!ሰዎቹ(የውጭ ፓስተሮች) ለብር ነው ቅርንጫፍ የሚከፍቱት!!ለዕምነት ከሆነማ ቸርች እንደሱቅ በደረቴ በተንሰራፋባት አዲስአበባ ብቻ በዚህ መጠን ቅርንጫፍ ከማብዛት ወጣ ብለው ወደ ገጠር ይከፍቱ ነበር!!እናንተም መኮረጁን ስለማታውቁበት ኩረጃችሁ “አሜን” የሚለውን የብዙ ብሄረሰቦች ቃል “ኤሜን” በሚለው ፈረንጅኛ ቃል ከነመሀረቡ መሆኑ በጣም ያስቀይማል!!ራሳችሁን ሁኑ!!
   3. ዘመናዮቹ አማንያን፡ ቀልባችሁን ገዝታችሁ ወደ ራሳችሁ እስክትመለሱ በታይትና በሚኒ እየዘለሉ ቅጥ በሌለው መልኩ አረፋ እየደፈቁ ለጌታ አምልኮ ነው ማለቱን ቀጥሉበት!!የእናንተ እግዜር እንደኤልዛቤል ውቃቢ ጠሪዎች ካልጮሁ እና አቡዋራው እስኪጨስ ካልተንፈራፈሩ አይሰማም አሉ!!አይዙዋችሁ!!በዚሁ ከቀጠለ ገና የመዝሙር ምሽት ቤት ይከፈታል!! እረ በአዳር ፕሮግራም ጌታን እናስመልካለን ብለው ተነስተው የመዝሙር ፓርቲ ለወጣቶች የሚሉትን አስመላኪ ተብየ ዲጄዎቻችሁን አስታግሱልን!!እኛስ ለእናንተ በተረትነት የሚታየውን ስለክርስቶስ መስክረው አክሊለ-ክብር የተቀበሉ ቅዱሳንን ገድል በጸጥታ የበረታው ቁሞ የደከመው ተቀምጦ እየሰማን ነበር!!
   4. አትሸወዱ!!ኦርቶዶክስነት ወደው ፈቅደው በፍቅር የሚይዙት ሃይማኖት እንጅ በግድ ታስረው የሚያዙበት ዕምነት ስላልሆነ በነጻነት እምነታችሁን ቀይራችሁዋል!!ግን አሁንም ኢትዮጵያዊ ናችሁ!!ታዲያ ኢ/ዊ የሆነውን ባህል ሁሉ ኦርቶዶክስን ስለሚያስታውስ እያላችሁ ስታጣጣሉትና በምእራባዊ ባህል ስትወረሩ ሳይ ወይ አለማስተዋል እላለሁ!!በዚህ ዙሪያ ገና ወደፊት የምለው ይኖረኛል!!በዚያው በምናውቀው ብሎግ እንገናኝ!!
   እስከዚያው ልብ ይስጣችሁ!!

 18. Anonymous April 2, 2014 at 6:13 am Reply

  አቤት ባለ መረጃ፤ ድንቄም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን ተከትሎ ከክርስቶስ የተለየው ትውልድ የትኛው ይሆን ወዳጄ፤
  የተዘጉ አብያተ ክርክስቲያናትን ስላስከፈተ ብቻ አናድንቀው ማለት ምንኛ ፌዝ ነው እናንተ፤ ከክርስቶስ ወንጌል አለመለየት ማለት ጌታ ጌታ ብለው ከሚጮሁባቸው አዳራሾች መለየት ማለት ከሆነ ትክክለ፤ ከጌታ ወንጌል አለመለየት ማለት ከሱስ፣ ከስርቆት፣ ከሙሰኝነት፣ ከቤ/ክ ጡት ነካሽነት፣ ከኃጢያት ርቆ በንስሐና በሥጋ ወደሙ ተወስኖ መኖር ከሆነ ትክክል፤ ከጌታ ወንጌል አለመለየት ማለት በዓለምና በምድራዊ እውቀት ብቻ ታጥሮ ሊጠፋ የሚችልን ትውልድ አቅፎ የተዘጋች ቤ/ክንም ከፍቶ፣ የተፈቱ ጉባዔ ቤቶችን አሰባስቦ፣ አብነት መምህራንና ተማሪዎችን ከስደት መልሶ በተቀደሰው የክርስቶስ ቤ/ክ ማኖር ከሆነ ትክክል ነው፡፡
  ማኅበረ ቅዱሳንና ሰንበት ት/ቤቶች፤ ሌሎችም እውነተኛ ማኅበራት ከዚህ ውጭ ምን ሰሩ ወዳጄ፤
  የእናንተ ዓላማ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት እንዳይከፈቱ፤ ወጣቱ ሕይወቱን በየአዳራሹ እንዲያጣ፤ ንጽህት ቅድስት ተዋሕዶ ቤ/ክ እንድትጠፋ ስለሆነ ግን ማኅበረ ቅዱሳንን ዝም ብለን አንደግፍ አስባለህ፡፡ ለማለዘብም ሞከርክ፡፡ ተወው ማኅበረ ቅዱሳን የእናንተ ድጋፍና ልዝብ ግን መርዘኛ አንደበትን አይፈልግም፡፡ ይልቅ ግልጽ አቋማችሁን አውጡና እንተያይ፡፡

 19. Anonymous April 2, 2014 at 1:02 pm Reply

  ፋክት መጽሔት መረጃ (መረጃቸው ትክክለኛ መሆኑን በሂደት እያየን) መሰጠታቸውን ብቻ ቢቀጥሉ ጥሩ ነው፡፡
  ዕለተ ዓርብን የስቅለት ዕለት ወይንም ምርጫ ዕለት ለዓመጽ ተነሱ የሚለው ጥሪው ግን ፍጹም ፍጹም አልቀበለውም፡፡ ብዙዎችም አንቀበለውም፡፡
  ማኅበረ ቅዱሳንን የማያውቅ ወይንም የራሱ ዓላማ ያለው ሰው በስሜት የጻፈው ይመስላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የዓመጽ ማኅበር አይደለም፡፡ ሕግና ደንብ ያለው፤ ምንም ችግርና ፈተና ቢመጣ በሕግ በሥርዓት በቤ/ክንም በሀገርም ህጋዊ መንገዶችና መንገዶች ብቻ የሚታገል ነው፡፡ አባላቱም እንዲህ የተቃኙ መሆናቸውን እኔ ለዓይን ጥቅሻ ሳልጠራጠር እናገራለሁ፡፡ በግለሰብ ደረጃ አንዳንድ ግላዊ እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊኖራቸው ቢችል እንኳ ስሜታቸውን እንዳሳዩ ይታረማሉ፡፡ እነርሱም ይሰማሉ፡፡ ይህን እሴት የሰጠን የቅዱሳን አምላክ ይመስገን፡፡
  ይልቁንም በማኅበሩ ስምና ሽፋን አንዳች የዓመጽ ነገር እንዳይኖር ነቅተን እንጠብቃለን፡፡ የሰንበት ት/ቤት አባላትም በመሆናችን በየትኛውም ደረጃ ዓመጽን እንከላከላለን፡፡ ከየትኛውም ጻድቅ አባትና እናት አልተማርነውምና!!!! ስለዚህ ቤ/ክ ውስጥ ያውም በዕለተ ስቅለት ዓመጽ መጥራት ወንጀል ብቻ ሳይሆን ኃጢያትም ነው፡፡
  ምናልባት ፈሪ ትሉኝ ይሆናል፡፡ አዎ! ከቀደሙት አበው ያልወረስነውን መስራት ያስፈራል፡፡፡
  ኃይለ ሥላሴ

 20. Biniam Tesfaye April 9, 2014 at 6:39 pm Reply

  DAWIT AND BEAMAN; both of you are a very big dog,robber,thief,the enemiy of EOTC.see;you,people who seem you and this gov’t will be destroyed after a few days.Remember,we are ethiopian!!!!!!

 21. rahel2002 September 25, 2015 at 6:53 pm Reply

  በቶሮንቶ ቅድሥት ማርያም ቤተከርስቲያን የተነሳው የሃይማኖት ውዝገብና መንስኤው
  እነዚሁ የእመ ቤታችን እና የቅዱሳን ፍቅር የአንገበገባቸው የቶሮንቶ ምአመናን በአንድነት ጉባኤው ላይ በቀሲስ ዶ/ር መብራቱ ኪሮስ የተስጠውን የስህተት ትምህርት እርምት እንዲደርግበት በመጠየቃቸውና ትምሀርቱ ምንም ስህተት የለውም ተብሎ ከካቲድራሉ አስተዳዳሪ ጉዳዩን ለማስተባበል በመሞከሩ ክፍተ አልመግባባት አስነስቶአል ::አስትዳዳሪው l ሊቀ ካህናት ምሳለ እንግዳ ለብዙ ዘመናት የደክሙበት ቤተከርስቲያን የመናፍቃንና የተሃድሶ መ ታጎሪያ እንዲሆን ይፈልጋሉ ብሎ ማመን ቢክብድም ” ኪዳነ ምሕረትን ድጅ ጠናሁ” ማለት ስህተት ነው የተባልበትን ትምሀርት ክግርማ ሞገሳቸው ከእመ ቤታችን መንበር ፊት ቆመው ትምሀርቱ ስህተት የለውም ማለታቸው ለምን ይሆን?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: