የብፁዕ አቡነ ቶማስ የሕይወት ታሪክ እና ዜና ዕረፍት

(የምዕራብ ጐጃም ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት – ፍኖተ ሰላም)

His Grace the late Abune Thomas, Archbishop of West Gojjamየብፁዕነታቸው ልደትና ዕድገት

ብፁዕ አቡነ ቶማስ በቀድሞው አጠራር በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በቆላ ደጋ ዳሞት አወራጃ በደጋ ዳሞት ወረዳ በመንበረ ስብሐት ዝቋላ ፬ቱ እንስሳ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ ከአባታቸው ብላታ ተገኘ ይልማ ገብረ ሕይወት ከእናታቸው ከወ/ሮ ውድነሽ ቸሬ መጋቢት 14 ቀን 1935 ዓ.ም ተወለዱ፡፡

‹‹ዘእንበለ እፍጥርከ አእመርኩከ ወዘእንበለ ትንፃ እምከርሰ እምከ ቀደስኩከ ወረሰይኩከ መምህረ ለአሕዛብ.›› ተብሎ ለነቢዩ ኤርምያስ እንደተነገረለት (ኤር. 1÷4)፣ ብፁዕ አባታችን በብፅአትና በፈቃደ አምላክ የተገኙ ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ በመኾናቸው በወላጆቻቸው ቤት ‹‹ወልህቀ በብህቅ እንዘ ይትኤዘዝ ለአዝማዲሁ ወለይእቲ እሙ›› (ሉቃስ 2÷51) እንደተባለው፣ ለወላጆቻቸው በመታዘዝና በማገልገል ካደጉ በኋላ ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በተወለዱ በሰባት ዓመታቸው በደጋ ዳሞት ወረዳ ጉድባ ቅድስት ማርያም ከሚገኙት ከታላቁ ሊቅ መምህር አንዱዓለም አስረስ ከመልክአ ፊደል ጀምሮ ጸዋትወ ዜማ ተምረዋል፡፡

በመቀጠልም ከቀደሙት ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሊቀ ጳጳስ ዘጎጃም በ1948 ዓ.ም ማዕርገ ዲቁና ተቀብለዋል፡፡ በተሰጠው የመመዘኛ ፈተና ችሎታቸውንና ብቃታቸውን ከተመለከቱ በኋላ የትምህርት ቤት መጠሪያ መዘምር፣ ወላጆቻቸው ባለኽ ተገኝ ብለው ያወጡላቸውን ስም ለውጠው በመንፈስ ቅዱስ የብፁዕነታቸውን የወደፊት አባትነት የተረዱት ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ከዛሬ ጃምሮ ስምኽ ፀሐይ ነው ብለው ሰይመዋቸዋል፤ በኋላም በመምህራቸው ፈቃድ ከመምህር ገብረ ሥላሴ፣ ከመምህር ለይኩንና ከተለያዩ መምህራን ቅኔ ተምረዋል፡፡

በዕውቀትና በዕድሜ እየበሰሉ በሔዱ ጊዜ ቅኔውን የበለጠ ለማዳበር የቅኔው ማዕበል ወደሚፈስባት ታላቋ ገዳም ደብረ ምዕራፍ ዋሸራ ማርያም ሔደው ከታላቁ ሊቅ ከመምህር ማዕበል ፈንቴ ቅኔውን ከነአገባቡ ግሱን ከነእርባ ቅምሩ ተምረው በመምህርነት ተመርቀዋል፤ በኋላም ወደ ጸዋትወ ዜማ ት/ቤት ተመልሰው በደጋ ዳሞት ወረዳ ከሚገኙት ከታወቁት ሊቅ መሪጌታ ካሳ መንገሻ ከጾመ ድጓ እስከ ድጓ አጠናቀዋል፡፡ በመቀጠልም የአቋቋም ትምህርታቸውን በዚያው በደጋ ዳሞት ከሚገኙት ከመምህር ዋሴ አስረስ፣ ዝማሬ መዋስዕት ከመምህር ወልዴ ማንአምኖኽ ተምረው ተመርቀዋል፡፡

የብፁዕነታቸው ጉዞ ለተምህሮ መጻሕፍት ከጎጃም ወደ ሸዋ

ብፁዕነታቸው ከትምህርት ወደ ትምህርት ለመሸጋገር በነበራቸው ጽኑ ፍላጐት ትርጓሜ መጻሕፍትን ለመማር ከጐጃም ወደ ሸዋ ተሻግረው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከሚገኙት አድባራት በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ተቀምጠው ከሊቀ ሊቃውንት ሞገስ መጻሕፍተ ሊቃውንትን ጀምረውና ጐን ለጐን ዘመናዊ ትምህርት አጠናቅቀው እያሉ በኋላ ግን ምኞታቸው ገዳማዊ ሕይወት ስለነበረ አዲስ አበባን ለቀው ለብሕትውና ምቹ ወደ ኾነው ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገብተዋል፡፡

በገዳሙ ውስጥ ሳሉ ቀደም ሲል የጀመሩትን የብሉያትንና የአቡሻህርን ትርጓሜ ደግሞ ከመምህር ገብረ ሕይወት ገብረ አምላክ ተምረውና ከነምልክቱ አጠናቅቀው አስመስክረዋል፤ በኋላም የብፁዕነታቸውን መንፈሳዊና ገዳማዊ ሕይወት በዓይነ ኅሊና ከተረዱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በ1959 ዓ.ም ማዕረገ ምንኩሰና፣ ቅስናና ቁምስና ተቀብለዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ከደቀ መዝሙርነት ወደ መምህርነት

‹‹መጠኑ ለረድእ እምከመ ኮነ ከመ ሊቁ፤ የደቀ መዝሙር መጠኑ እንደ መምህሩ መኾን ነው›› እንደተባለው ለብፁዕነታቸውም ይህ በረከት ደርሷቸው የመጻሕፍት ሊቃውንትን ትርጓሜ ያስተማሯቸውን መ/ር ቢረሳው ደስታን ተክተው እንዲያስተምሩ በሊቃውንቱ የተመረጡት ብፁዕ አቡነ ቶማስ ነበሩ፡፡

የዚያን ጊዜው መምህር መዘምር የዛሬው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቶማስ፣ ከመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ፊት ቀርበውና ተፈትነው ችሎታቸውንና ብቃታቸውን ከምንም በላይ የተረዱላቸው ቅዱስ ፓትርያርኩ ይደልዎ ብለው በ1961 ዓ.ም በታላቁ ገዳም በደብረ ሊባኖስ በመምህራቸው ወንበር ተቀምጠው እንዲያስተምሩ ሹመዋቸዋል፡፡

በመምህሩ ወንበር ተመርጦ የሚሾም ደቀ መዝሙር ከደቀ መዛሙርቱ የተለየ ዕውቀትና ስጦታ ያለው መኾኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው እንደገና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተመርጠው ወደ ሌላ አገልግሎት እስከገቡበት ጊዜ ድረስ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ወንበር ዘርግተው ጉባኤ አስፍተው መጻሕፍተ ሐዲሳትንና መጻሕፍተ ሊቃውንትን እያስተማሩ መምህርነትን ከብሕትውና ታላቅነትን ከትሕትና ጋር አስተባብረው ይዘው ለ11 ዓመታት ቆይተዋል፤ ለብዙ መምህራንም የዕወቀት (የቀለም) አባት ኹነዋል፤ በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፍርተዋል፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ጥሪ ከጉባኤ መካከል

‹‹እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ ወየሐውር እምኃይል ውስተ ኃይል፤ የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣል፤ ከኃይልም ወደ ኃይል ይሔዳል›› ተብሎ እንደተጻፈ፣ በርናባስንና ጳውሎስን ለልዩ አገልግሎት የጠራ መንፈስ ቅዱስ ብፁዕነታቸውንም ለልዩ መንፈሳዊ አገልግሎት ስለመረጣቸው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በነበሩት በ1972 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ተጠሩ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ባሠሩት በመካነ ሕያዋን ጎፋ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ለአንድ ዓመት፣ በደብረ ነጐድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ለአምስት ዓመት፣ በደብረ ሣህል የካ ቅዱስ ሚካኤል ለሁለት ዓመት አድባራቱን በማስተዳደር፣ በማገልገልና ምእመናኑን በወንጌል በማነፅ የተጣለባቸውን ሓላፊነት ከመወጣት ጋር ልዩ ልዩ ዓበይት ተግባራትን አከናውነዋል፡፡

ለመጥቀስም ያህል በደብረ ነጐድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ ደብረ ጐለጐታ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን አሠርተዋል፤ እንዲሁም በየካ ደብረ ሣህልና በአካባቢው አድባራት የሚገኙ ወጣቶችን በማሰባሰብ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥልጠና በመስጠት ወጣቱ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ እንዲሰለፍ አድርገዋል፡፡ ምእመናኑን እስከ ቤተሰቦቻቸው መዝግቦና ቆጥሮ ለመያዝ የሚያስችል ቅጽ አዘጋጅተው በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሥራ ላይ እንዲውል አድርገዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ያዘጋጁትም ቅጽ በየደረጃው ባለው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር እስከ ዛሬ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ብፁዕነታቸው ከ1972 እስከ 1979 ዓ.ም ለስምንት ዓመታት ያህል ከላይ በተጠቀሱት ታላላቅ አድባራት በርካታ የልማት ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡

የብፁዕ አቡነ ቶማስ ለኤጲስ ቆጶስነት መመረጥ

በመንፈስ ቅዱስ ጥሪ የብፁዕነታቸው የመንፈሳዊ አስተዳደር ብቃትና የቅድስና ሕይወት ታይቶ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እጅ ተሹመውና አቡነ ቶማስ ተብለው ከ1979 ዓ.ም አስከ 1980 ዓ.ም የድሬዳዋና የምዕራብ ሐረርጌ አህጉረ ስብከት ጳጳስ ኾነዋል፡፡ ትንቢት ይቀድሞ ለነገር እንደሚባለውም የቀደሙት ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የዲቁና ማዕርግ በሰጧቸው ወቅት ያወጡላቸው ፀሐይ የሚለው መጠሪያ ስም ትክክለኛ ትርጓሜውን አግኝቷል፤ ቶማስ ማለት ፀሐይ ማለት ነውና፡፡ በዚያን ጊዜም ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ከነበራቸው መንፈሳዊ የደስታ ስሜት በመነሣት በትር ሙሴና አይከናቸውን ለብፁዕነታቸው ሸልመዋቸዋል፡፡

ከሢመተ ኤጲስ ቆጶስነት በኋላ፡-

 • ከ1980 እስከ ግንቦት 30/1980 ዓ.ም. ለ6 ወራት አሰብ ሀገረ ስብከት
 • ከሰኔ ወር 1980 እስከ 1983 ዓ.ም. ወለጋ እና አሶሳ አህጉረ ስብከት
 • ከ1983 እስከ 1984 ዓ.ም. እንደገና ተመልሰው ምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት
 • ከ1984 እስከ 1987 ዓ.ም. ደቡብ ኦሞ/ጂንካ/ ሀገረ ስብከት
 • ከ1988 እስከ 1991 ዓ.ም. ሰሜን ሽዋ- ስላሌ ሀገረ ስብከት
 • ከ1991 እስከ 1993 ዓ.ም. ሰሜን ኦሞ/አርባ ምንጭ/ ሀገረ ስብከት
 • ከ1993 እስከ 2001 የአዊና የመተከል አህጉረ ስብከትን በሊቀ ጳጳስነት አገልግለዋል፡፡

በአጠቃላይ ብፁዕነታቸው የአሠራርና የአስተዳደር ችግር በተከሠተባቸው፣ ስብከተ ወንጌል ባልተስፋፋባቸው አህጉረ ስብከት ችግር ፈቺ ናቸውና ‹‹ሥራውን ያስተካክላሉ›› በሚል ቅዱስ ሲኖዶስ ሲመድባቸው ምደባውን እየተቀበሉ ሓላፊነታቸውን ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሊቃውንት ጉባኤ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጂ ዲን፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሃይማኖተ አበው መምህርና የቦርዱ ሰብሳቢ ኹነው በማገልገል ቅዱስ ሲኖዶስ የጣለባቸውን መንፈሳዊ ሓላፊነት በብቃት ተወጥተዋል፡፡

ከ2001 – 2005 ዓ.ም ደግሞ የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያምና የመንበረ መንግሥት ግቢ ቅዱስ ገብርኤል ገዳማት የበላይ ጠባቂ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ኾነው አገልግለዋል፡፡

በጠቅላላው ብፁዕነታቸው ተዘዋውረው በሠሩባቸው አህጉረ ስብከት ኹሉ መንበረ ጵጵስና እና ልዩ ልዩ የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶችን በማሠራት፣ ልማቶችን በማስፋፋት፣ አድባራትንና ገዳማትን በማሳነጽ ለተተኪው ትውልድ የታሪክ አሻራ አስቀምጠው አልፈዋል፤ እንደ ምሳሌም የሰሜን ኦሞ፣ የሰሜን ሽዋ – ሰላሴ፣ የአዊ እና የመተከል አህጉረ ስብከት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ብፁዕነታቸው ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት

ወንጌልን በቃልና በኑሮ መስበክ ትክክለኛው የሐዋርያነት መግለጫ ነው፡፡ ይህን መንፈሳዊ ጸጋ ከፈጣሪ የተቀበሉት ብፁዕ አብነ ቶማስ በሔዱባቸው አህጉረ ስብከት ኹሉ ተቀዳሚ ተግባራቸው የሚያደርጉት ስብከት ወንጌልን ነው፡፡ አዲስ ሰባክያንን መቅጠር፣ ሰባኪ ባልደረሰባቸውና መኪና በማይገባቸው የገጠር አድባራትና ገዳማት ሳይቀር እየተዘዋወሩ ወንጌልን ለትውልድ ማድረስ የብፁዕነታቸው መለዮ ነው፡፡

ከመካከለኛው ኢትዮጵያ እስከ ጠረፋማው የአገራችን ክፍል ከዚያም አልፎ እስከ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የብፁዕነታቸው ዜና ስብከት ያልተሰማበት ቦታ የለም፡፡ ከዚህም የተነሣ ወደ ወለጋ እና አሶሳ አህጉረ ስብከት ተመድበው በሔዱበት ጊዜ 5000 ሐዲስ አማንያንን አጥምቀዋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተ ክርስቲያን እምነት ርቀው የነበሩ ወገኖችን አስተምረው ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው መልሰዋል፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት በነበሩበት ዘመንም የጠፉትን የመፈለግ ኖላዊ ተግባራቸውን በማስቀጠል 10,000 ሰዎችን አጥምቀው ሀብተ ውልድና ስመ ክርስትና አሰጥተዋል፡፡ በጠቅላላው ከ15,000 በላይ የሚኾኑ ምእመናንን ወደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት መልሰዋል፡፡

የክርስቶስን አሰረ ፍኖት በመከተል ተዘዋውረው ባገለገሉባቸው አህጉረ ስብከት ኹሉ ኃጥዕ ጻድቅ አማኒና መናፍቅ ሳይለዩ በማኅበራዊ ኑሮ ምእመናንን አግዘዋል፡፡ በተለያዩ ማረሚያ ቤቶችና ሆስፒታሎች እየተገኙ አባታዊ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ በመስጠት ምእመናንን ሲያጽናኑ ቆይተዋል፡፡ በተለይ በወለጋና አሶሳ አህጉረ ስብከት በነበሩበት ወቅት ችግር ውስጥ የነበሩ 650 አርሶ አደሮችን ከመንግሥት የሰፈራ ቦታ አስፈቅደው በወለጋ ክፍለ ሀገር በማስፈር ሰዎች የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩና የሀብት አቅም እንዲፈጥሩ አድርገዋል፡፡

በዚህም አቅም አንዳንዶቹ በአዲስ አበባ ከተማ ቤት ሠርተው ሀብት አካብተው ይገኛሉ፡፡ ብፁዕነታቸው በጨለማ ለሔደው ሕዝብ በወንጌል ብርሃን እንዲኖር የሕይወት መሠረት ኾነውታል፡፡ በድካምና በሕመም ያልከሰመው ቃላቸው እስከ ዛሬም ለምእመናን መድኃኒት ነበርና፡፡

ብፁዕነታቸው በአብነት ት/ቤቶች መስፋፋት

ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚተጉ አባቶቻችን አስቀድመው የሚሠሩት አብነት ት/ቤቶችን ነው፡ ብፁዕነታቸውም በተሰየሙባቸው አህጉረ ስብከት በተለይም በሰሜን ኦሞ እና በወለጋ አህጉረ ስብከት በሊቀ ጵጵስና በሚያስተዳድሩበት ወቅት ከግብረ ጵጵስናው ጐን ቤተ ጉባኤ በመክፈት ደቀ መዛሙርትን አሰባስበው ከራሳቸው የወር ደመወዝ ገንዘብ፣ ቀለብና ልዩ ልዩ ቁሳቁስ በማሟላት ትምህርተ ሃይማኖትና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ለበርካታ ደቀ መዛሙርት አስተምረው ለአገልግሎት አሰማርተዋል፡፡

የደግ ሥራ ደጋፊና አስፈጻሚ እርሱ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ስለኾነ የብፁዕነታቸውን ቅን ሐሳብ ሁሉ እያስፈጸመ እነዚህን ታላላቅ የአብያተ ክርስቲያናት ተቋማት ከሠሩና ከአስተዳደሩ በኋላ ዛሬ በዚኽ ወቅት ለረጅም ጊዜ ሲያስቡለትና ሲቆረቆሩለት የነበረው የምዕራብ ጐጃም ሀ/ስብከት ከባሕር ዳር ከተማ ሲወጣና ማዕከሉን ፍኖተ ሰላም ሲያደርግ ባላቸው የሥራ ልምድ አካባቢውን በማልማት በበጐ ፈቃዳቸው ‹‹ሠናይ ለብእሲ ለእመ ኮነ መቅበርቱ ውስተ ርስቱ›› በሚል መሪ ቃል ያቀረቡትን ቅዱስ ሲኖዶስ ተቀብሎ ለዚህ አንጋፋ ሀገረ ስብከት በሊቀ ጳጳስነት መድቧቸዋል፡፡

በብፁዕነታቸው ከኅዳር 9 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምረው አዲሱን ሀገረ ስብከት በማቋቋምና ልዩ ልዩ የሀገረ ስብከት ሠራተኞችን በመመደብ እየሠሩና እያሠሩ ይገኙ ነበር፤ መደበኛ ሥራቸውንም በበቂ ኹኔታ ለማስኬድ ሀገረ ስብከቱ አዲስ በመኾኑ የተነሳ በርካታ መሰናክሎችና የቢሮም ኾነ የንብረት ችግሮች አጋጥሟቸዋል፡፡

ይኹንና ያላቸውን የረዥም ጊዜ የሥራ ልምድና ተሞክሮ በመጠቀም ችግሮችን ተቋቁመው በ2004 እና በ2005 ዓ.ም. የበጀት ዓመቶች የሠሯቸው የሐዋርያዊ ጉዞ፣ የስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የልማት፣ የሰበካ ጉባኤ ዕድገትና የልዩ ልዩ ተግባራት የሥራ አፈጻጸም በ31ኛውና በ32ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ከጠቅላላ አህጉረ ስብከቶች ጋር ተመዝኖ በሁለቱም ተከታታይ ዓመታት 2ኛ ደረጃ በማግኘት ልዩ ልዩ ሽልማቶችን ሀገረ ስብከቱ እንዲሸለም አድርገዋል፡፡ በዚህም የብፁዕነታቸው የልማት ራዕይና በሳል አመራር ስኬታማ ኾኗል፡፡

ከዚህም ሌላ በሀገረ ስብከቱም ውስጥ በሚገኙ ታላላቅ አድባራት የአብነት መምህራንን በመቅጠር እንዲያስተምሩ አድርገዋል፡፡ በሀገረ ስብከት ደረጃም አንድ የድጓ መምህርና አንድ የአራቱ ጉባኤያት መምህር በመቅጠር ከ14ቱ ወረዳዎች የተውጣጡ ደቀ መዛሙርት ወርኃዊ ክፍያ እየተከፈላቸው መደበኛ ትምህርታቸውን እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ ብፁነታቸውም ከቤተ ጉባኤው መካከል እየተገኙ ለመምህራንና ለደቀ መዛሙርት የሚያደርጉት ልዩ ልዩ አባታዊ ድጋፍና ትምህርት ከፍተኛ ከመኾኑም በላይ ሕይወታቸው ከቤተ ክርስቲያን ዕድገትና ከጉባኤ ሊቃውንት ጋር እንዲኖር የሚመኙት ብፅዕ አቡነ ቶማስ የ፬ቱ ጉባኤያት ትምህርት ቤቱን መርቀው በከፈቱበት ወቅት፣ ‹‹በዚህ ቦታ ፬ቱ ጉባያት ሲነገሩ ካየኹ ዛሬም ልሙት ይበቃኛል›› በማለት ከእንባ ጋር በተቀላቀለ ቃለ ማኅዘኒ ያሰሙት አባታዊ ንግግር ሁልጊዜም በሊቃውንቱና በደቀ መዛሙርት ልቡና ሲታወሱ እንዲኖሩ የሚያደርጋቸው ሕያው ቃል ነው፡፡

በጣዕመ ስብከታቸውም ኾነ በሊቅነታቸው እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ንዋይ ኅሩይ›› ለመባል የበቁትና የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና የነገረ መለኮት አመስጥሮ ሞያቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በሌሎችም የተመሰከረላቸው ብፁዕ አቡነ ቶማስ፣ ምዕራብ ጐጃም ሀገረ ስብከትን ለማስተዳደር ተመድበው የቆዩበት ጊዜ አጭር ቢኾንም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ኾነ ለምእመናን የሚበጁ ልማቶች እንዲስፋፋ አድርገዋል፡፡ ከዚህም መካከል፡-

 1. ለምእመናንና ለካህናት መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡ ከ26 በላይ አዲስ አብያተ ክርስቲያን እንዲሠሩ አድርገዋል፡፡
 2. በ14ቱም ወረዳዎች ተከታታይ የኾነ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግና ሰፊ የስብከት ወንጌል ጉባኤ በመፍቀድ ትምህርተ ወንጌል እንዲሰጥ፣
 3. የቤተ ክርስቲያን ልማትና አገልግሎት እንዲጠናከር አድርገዋል፡፡
 4. ከመንግሥት ቦታ በማስፈቀድ ደረጃውን የጠበቀ መንበረ ጵጵስና አሠርተዋል፡፡
 5. ታላላቅ አድባራትንና ገዳማትን ተዘዋውረው በመጐብኘት ገዳማቱ ቅርሳቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ አባታዊ ትምህርትና መመሪያ ከመስጠታቸውም በላይ በዕድሜ ብዛት ያረጁ ገዳማትን ባለሀብቶችን በማስተማርና የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ በዘመናዊ ሕንፃ አሠርተዋል፡፡

በአጠቃላይ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ዕለት ዕለት የሚከብደኝ የአብያተ ክርስቲያን ጉዳይ ነው›› የሚሉት ብፁዕነታቸው፣ የነበረባቸው ሕመምና ድካም ሐሳባቸውን ሁሉ ሳይቀለብሰው ለወደፊት በሀገረ ስብከት ደረጃ ሊሠሯቸው ያቀዱአቸውን የልማት ራዕዮች በርካታ ነበሩ፡፡ እነርሱም፡-

 • ከከተማ አስተዳደሩ ጀምሮ በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ካስፈቀዱት ቦታ ላይ
  የሀገረ ስብከቱን ቢሮ መሥራት፣
 • በሁሉም አብያተ ክርስቲያን በነገረ መለኮት፣ በትርጓሜ መጻሕፍት የበሰሉ ሰባክያን መመደብ፣
 • የቤተ ክርስቲያንን ልማትና የአብነት ት/ቤቶችን የበለጠ ማጠናከር፣
 • በሀገረ ስብከት የካህናት ማሠልጠኛ መንፈሳዊ ኮሌጅ ማቋቁም፣

የመሳሰሉትን በጐ ራዕዮቻቸውን ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ እንዳሉ ባደረባቸው ሕመም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ሆስፒታሎች ሲረዱ ከቆዩ በኋላ በተወለዱበት ወርኃ መጋቢት 2006 ዓ.ም 16 ለ17 ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ላይ በ71 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም በሞት ዐርፈዋል፡፡ብፁዕ አቡነ ቶማስየምዕራብ ጎጃም(ፍኖተ ሰላም) ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ሥርዓተ ቀብር

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ሓላፊዎች፣ የክልል 3 እና የምዕራብ ጐጃም ዞን የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ መላው የምዕራብ ጐጃም ሀገረ ስብከት የገዳማት እና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንትና ካህናት እንዲኹም በርካታ ሕዝበ ክርስቲያን በተገኙበት መጋቢት 18 ቀን 2006 ዓ.ም በፈለገ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡

ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም ለሀገረ ስብከትና ወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሠራተኞች በጠቅላላ በብፁዕነታቸው ሐዘንና ሥርዐተ ቀብር ላይ ለተገኛችኹ ሐዘንተኞች እግዚአብሔር መጽናናትን እንዲሰጥልን እንመኛለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የምዕራብ ጐጃም ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት
ፍኖተ ሰላም

Advertisements

2 thoughts on “የብፁዕ አቡነ ቶማስ የሕይወት ታሪክ እና ዜና ዕረፍት

 1. gishabay2003 March 29, 2014 at 11:28 am Reply

  e/r melikam abat endeeriso yale yisten amen!

 2. Anonymous November 16, 2014 at 8:40 am Reply

  yersiobereket begna bememenanuyeder amen amen

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: