በመናፍቅነት የተከሰሱት የቪዝባደን ቅ/ጊዮርጊስ ደብር አስተዳዳሪ «ቄስ» ገዳሙ ደምሳሽ ጉዳይ ዛሬ በቋሚ ሲኖዶሱ ይታያል

 • በአ/አ የሚገኙት ተከሳሹ ከፓትርያርኩ ጋራ በቅዳሴ እየተሳተፉ በመታየት ለማምታት እየሞከሩ ነው
 • የግለሰቡን ኑፋቄ አስመልክቶ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በተደጋጋሚ የተላኩ ማስረጃዎች ‹እንደጠፉ› ሲገለጽ መቆየቱ ተከሳሹ ከዓላማ ተባባሪዎቹ ጋራ የጥቅም መረብ ለመዘርጋቱ ማሳያ ኾኗል
 • በእልቅና ካባ ፓስተር መቅደስ ገባ?!

በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር አስተዳዳሪ የኾኑትና በመናፍቅነት አቤቱታ የቀረበባቸው የ«ቄስ» ገዳሙ ደምሳሽ ጉዳይ ከበርካታ ዓመታት ያላሰለሰ የአካባቢው ምእመናን ተደጋጋሚ ጥያቄ በኋላ ዛሬ ረቡዕ በቋሚ ሲኖዶሱ እንደሚታይ ተገለጸ፤ ተከሳሹም ከዚኹ ጉዳይ ጋራ በተያያዘ አዲስ አበባ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ ሰሞኑን መታየታቸው ተጠቁሟል።

አቤቱታው የቀረበባቸው የደብሩ አስተዳዳሪ ለረጅም ዓመታት በፕሮቴስታንት እምነት ውስጥ በፓስተርነት ሲያገለግሉ እንደቆዩ የተገለጸ ሲኾን፥ በጀርመን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሓላፊ በኾኑት ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ፳፻፭ ባለጉዳዩ ይቅርታ መጠየቃቸውና ወደ ቀደመች ሃይማኖታቸው መመለሳቸው በዐውደ ምሕረት በግላጭ ተነግሮ በወቅቱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የነበሩትን የብፁዕ አቡነ ዮሴፍን ዕውቅና ሳያገኝ ዛሬ ባሉበት ሓላፊነት ክህነታቸው ተመልሶላቸው እንዲቀመጡ ተደርጓል።

«ቄስ» ገዳሙ ደምሳሽ በፕሮቴስታንት ቤተ እምነት ውስጥ በይፋ በፓስተርነት ሲያገልግሉ በነበሩባቸው ጊዜያት  ሁለት መጻሕፍትን ያሳተሙ ሲኾን ሌሎች ሁለት ተጨማሪ መጻሕፍትን «ተመልሰዋል» ከተባሉ በኋላ መጻፋቸው ታውቋል። መጻሕፍቱ ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውጭ የኾኑ የኑፋቄ ትምህርቶችን የያዙ ቢኾኑም ከልካይ ሳይኖራቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሚያስተዳድሩት አጥቢያና በአንዳንድ አድባራት ውስጥ በሽያጭ ሲያሰራጩ ቆይተዋል።

‹‹ያላግባብ ክህነታቸው ተመልሶላቸዋል፥ የኑፋቄ ትምህርታቸውንም በቃል ከሚያስተምሩት ባሻገር ስሕተት በተሞላቸው የራሳቸው መጻሕፍትና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እምነት ውጤት በኾነውና  በቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በተወገዘው በጮራ መጽሔት በኩል ምእመናንን እየበከሉ ነው፤›› በማለት ከአካባቢው ሊቀ ካህናት አንሥቶ መላው ሕዝበ ክርስቲያኑ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በተደጋጋሚ በርካታ ደብዳቤዎችንና የምእመናን የአቤቱታ ፊርማዎችን አሰባስበው ሲልኩ ቆይተዋል። ይኹንና አቤቱታቸው ምላሽ ሳያገኝ ከሦስት ዓመታት በላይ ዘልቋል፤ ይህም ተከሣሹ በአስተዳዳሪነት ባሉበት ደብር ጥቂት የማይባሉ ምእመናንን ወደ ፕሮቴስታንት እምነት ለማስኮብለል ኹኔታውን የተመቸ እንዳደረገላቸው ተጠቅሷል።

His_Grace_Abune_Mussie

ብፁዕ አቡነ ሙሴ
የደቡብ ደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

በአሁኑ ወቅት መቀመጫቸውን በጀርመን ሀገር ያደረጉት የደቡብ፣ ደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ፥ የምእመናኑን አቤቱታ ለሚመለከታቸው አካላት በተቀናጀ መልኩ ለማቅረብ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሰው የምእመናን አንድነት በኩል የቀረበላቸውን የጽሑፍ ፣ የምስል እና የድምፅ መረጃዎች በመያዝ ለፓትርያርኩ ጽ/ቤት ጥያቄውን በደብዳቤ በማሳወቅ አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ብፁዕ አቡነ ሙሴ የምእመናኑን አቤቱታ በቀጥታ ለፓትርያርኩ ጽ/ቤት በደብዳቤ ከማቅረባቸው በፊት የምእመናን አንድነቱ በተደጋጋሚ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሲልካቸው የነበሩ ደብዳቤዎች የውኃ ሽታ እየኾኑ ምላሽ ሳያገኙ ቀርተዋል። በአውሮፓ የማኅበረ ቅዱሳን ማእከልም ይህንኑ ጉዳይ የሚመለከት ደብዳቤ ከማስረጃ ጋራ አያይዞ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት መላኩ ተገልጧል።

ይኹንና ጉዳዩ ከምን እንደደረሰ በተደረገ ክትትል ደብዳቤው ከቤተ ክህነቱ እንደጠፋ ቢገለጽም ጠፋ የተባለው ደብዳቤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ባለው አፍራሽ ተልእኮው በሚታወቅ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎግ ላይ ወጥቶ ሊታይ ችሏል። የዋሃን ምእመናንን ለማሰናከልና የክሕደት እንክርዳድን ለመዝራት ዘወትር የሚታትረው ይኽው ብሎግ ደብዳቤውን ከማውጣቱም ባሻገር ከቪዝባደኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ አለቃ ጋራ ያለውን የዓላማ አጋርነት ይህንኑ ደብዳቤ ይዞ በወጣው ዘገባ ርእስ «የወንድሞች ከሳሽ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ማሳደዱን ቀጥሏል» በማለት በግላጭ አሳይቷል።

ቀናዒ አገልጋዮችና ምእመናን የግለሰቡን ኑፋቄ ለመከላከል ካደረጓቸው ጥረቶች መካከል ‹‹መጻሕፍትን መርምሩ፤ በእልቅና ካባ ፓስተር መቅደስ ገባ›› በሚል ርእስ በኅዳር ወር ፳፻፬ ዓ.ም. መ/ር ኅሩይ ኤርሚያስ ተከሳሹ ያለከልካይ በመጽሐፍ ላሰራጩት ኑፋቄ ምላሽ የሰጡበት መጽሐፍ ተጠቃሽ ነው፡፡

ለዓመታት የጀርመን ምእመናን ልቅሶና ጩኸት ሲሰማበት የነበረው የመናፍቁን «ቄስ» ጉዳይ የክርስቶስን መንጋ ከነጣቂ ተኩላዎች በበትረ መስቀላቸው እንዲጠብቋት እግዚአብሔር የሾማቸው ብፁዓን አባቶች በቅዱስነታቸው መሪነት ይኽን ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት እንደሚሰጡት የመላው ምእመናን ጸሎት እና ምኞት ነው።

«አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።» (ግብ. ሐዋ.፳ ÷፳፰)

……………………………………………………………………………………..

ተያያዥ ዘገባዎችን ይከታተሉ

‹‹በእልቅና ካባ ፓስተር መቅደስ ገባ?›› መጽሐፍ ታተመ        

(ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ፤ መጋቢት 19 ቀን 2004 ዓ.ም.)

ስንሻው ወንድሙ

Mmr Hiruy Ermias' Bookከዓመታት በፊት ፓስተር እንደነበሩ በሚነገርላቸው ግለሰብ ተዘጋጅተው በጀርመን ሀገር ለታተሙት የቅሰጣ መጻሕፍት ምላሽ የሰጠ መጽሐፍ መታተሙ ታወቀ፡፡ ገዳሙ ደምሳሽ በተባሉትና በአሁኑ ወቅት በጀርመን ቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በተሾሙ ግለሰብ ተዘጋጅተው ለታተሙት ሦስት መጻሕፍት ምላሽ የሰጡት መምህር ኅሩይ ኤርምያስ የተባሉ  በዚያው በጀርመን የሚኖሩ ሊቅ ሲኾኑ፤ የመጽሐፋቸው ርእስ «መጻሕፍትን መርምሩ በእልቅና ካባ ፓስተር መቅደስ ገባ ?» የሚል እንደኾነ ከቦታው የደረሰን ሪፖርት ያስረዳል፡፡

መጽሐፉ 219 ገጾች ያሉት ሲኾን አዘጋጁ በመጽሐፉ መግቢያ እንደገለጹት መልስ የሰጡባቸው መጻሕፍት “የመናፍቃን ሰፊ የቅሰጣ ማስፈጸሚያ ወጥመዶች አካል፤ በውጭ ሳይኾን በውስጥ ተጠምደው ምእመናንን በገዛ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው አደባባይ የሚያጠምዱ ናቸው ” ብለዋል፡፡ አክለውም መልስ የሰጡባቸው  መጻሕፍት «ቤተ ክርስቲያንን ይሳደባሉ፣ ይተቻሉ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያንቋሽሻሉ» ካሉ በኋላ የእሳቸው መልስ የኑፋቄ መጻሕፍቱን ደራሲ ተደራሽ ያደረገ ቢመስልም ዋና «ዓላማው መላው ምእመናን ሃይማኖታቸውን እንዲጠብቁና የተሳሳተ ትምህርት ሰርጎ እንዳይገባ ማንቃትና ማዘጋጀት ነው» ብለዋል፡፡

በመጻሕፍቱ ይዘትና በአዘጋጁ ወቅታዊ አስተምሕሮ በመደናገር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መፍትሔ እንድትሰጣቸው ከአካባቢው አስተዳደር ጀምሮ እስከ ሊቃውንት ጉባኤና ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ አቤት ሲሉ የቆዩት ምእመናን በመምህር ኅሩይ መጽሐፍ መጽናናታቸውንና መደሰታቸውን ከቦታው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

መልስ የተሰጠባቸውን መጻሕፍት አዘጋጅ አስመልክቶ ከአካባቢው ምእመናን በደረሰን አቤቱታ መሠረት፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ምእራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከትን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስንና በቤተ ክርስቲያኗ የሀገረ ጀርመን ሊቀ ካህናት የኾኑትን ሊቀ ካህናት ዶክተር መርዐዊ ተበጀን በማነጋገር ሰፋ ያለ ዘገባ በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በኅዳር ወር፣ ቅጽ 19፣ ቁጥር 236 እትማችን ሰፋ ያለ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡

*                                       *                                    *

በጀርመን አገር በሚገኙ አብያተ ከርስቲያናት በሚፈጸሙ ሃይማኖታዊ ሕጸጾች እና በደሎች ላይ ተገቢው የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ የምእመናን አንድነት ጠየቀ

(ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ 19ኛ ዓመት ቁ.236፤  ኅዳር 2004 ዓ.ም.)

በጀርመን አገር በኑፋቄ ትምህርታቸው የሚታወቁትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ አስተዳዳሪ የሆኑት የ«ቀሲስ» ገዳሙ ደምሳሽ እና ከአንድ መቶ ሥልሳ ሺሕ ዩሮ በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ ለግል ጥቅም ባዋሉ ግለሰብ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ መእመናን ጠየቁ፡፡

በጀርመን አገር የሚገኘው የምእመናን ኅብረት ይህንኑ በማስመልከት ሰሞኑን ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ለጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊ እና ለሌሎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ባሰራጨው ደብዳቤ ከቤተ ከርስቲያኒቱ ሥርዐትና ደንብ ውጪ የተፈጸመው በደል ተጣርቶ አፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡

ኅብረቱ ባሰራጨው ደብዳቤ እንዳመለከተው የቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በማገልገል ላይ ያሉት «ቀሲስ» ገዳሙ ከአሁን ቀደም በመናፍቃን የእምነት ድርጅት ውስጥ በሰባኪነት አገልግሎታቸው በተጨማሪ፤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውጪ ሦስት የኑፋቄ መጻሕፍትን አዘጋጅተው አሰራጭተዋል፡፡ በቅርቡም አራተኛ መጽሐፍ አዘጋጅተው ያሳተሙ ሲሆን ሌሎች ኑፋቄ አዘል ሦስት መጻሕፍት በማዘጋጀት ላይ እንዳሉ ጠቁሟል፡፡

መጻሕፍቱ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማ ውጪ የሆኑ መልእክት የሚያስተላልፉ መሆናቸውን የጠቀሰው ይህ ደብዳቤ ከዚህ ውጪ የተለያዩ የኑፋቄ ትምህርቶችን በማስተማር እና በካሴት በማሳተም ምእመናንን እያሳቱ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ በግልጽ የታወቁ አምስት የቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ያገለግሉ እና ከእርሳቸው እግር ሥር የማይጠፉ የነበሩ ምእምናን እና የሰበካ ጉባኤው አባላት ወደ ሌላ እምነት ተቋም ሔደው እንዲጠመቁ ማድጋቸውን ጠቅሰው፤ ከአሁን ቀደም ለፃፏቸው መጻሕፍት እና የኑፋቄ ትምህርቶችን ሳያስተካክሉ እና እርማት ሳይሰጡ እንዲሁም የፀፀት ምላሽ ሳይሰጡ በ1997 ዓ.ም የአስተርዩ ማርያም በዓል ዕለት በጀርመን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊ በሆኑት ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርአዊ ተበጀ አማካኝነት «ቀሲስ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተመልሰዋል» የሚል ማደናገሪያ መልእክት መተላለፉ እንዳሳዘነው ኅብረቱ በጻፈው ማመልከቻ ጠቅሷል፡፡

እኚሁ ግለሰብ ቀደም ሲል በኅቡዕ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ያለምንም ፍራቻ በግላጭ ስለሚዘሩት ኑፋቄ ጀርመን ሀገር ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በመጠቆም አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም አስተዳደሩ ለጥያቄው መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ነገሩን ወደ ጎን በመተው እና በማለባበስ ላይ መሆኑን ደብዳቤው ጠቅሷል፡፡ ግለሰቡ በተለያዩ አድባራት እየተገፉ ትምህርት እንዲያስተምሩ ከዚህም አልፎ ለሚያደርጉት ተፃራሪ ድርጊት አስተዳደሩ ድጋፍ እየሰጡ እንደሚገኝ በቅሬታ ደብዳቤው ገልጧል፡፡

ይህ ድርጊት በርካታ ምእመናንን ያሳዘነ እና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲርቅ ምክንያት እየሆነ ስለሆነ የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት መፍትሔ እንዲሰጡ የምእመናን ኅብረቱ በአፅንኦት አሳስቧል፡፡ ኅብረቱ ባቀረበው አቤቱታ በሙኒክ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከመቶ ሠላሳ ሺሕ ዩሮ በላይ ገንዘብ አጥፍተው በሊቀ ጳጳሱ የታገዱት ካህን ጉዳይ ተጣርቶ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢውን የእርምት እርምጃ እንደትወስድ ጠይቀዋል፡፡

«በሃይማኖታችን እና በመላው ምእመናን ላይ የተቃጣውን ከባድ የእምነት ፈተና ለመቋቋም እንድንችል ጉዳዩን በጥልቀት መርምራችሁ ተገቢውን ውሳኔ በአፋጣኝ እንድትሰጡበት በልዑል እግዚአብሔር ስም እንማፀናለን» ሲል የምእመናን ኅብረቱ ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ባሠራጨው የአቤቱታ ደብዳቤ አመልክቷል፡፡

ጉዳዩ የሚመለከታቸው በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊ ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርአዊ ተበጀ በአቤቱታው ላይ ተጠይቀው  በሰጡት ምላሽ፤ «ቀሲሰ» ገዳሙ ከአሁን ቀደም የሌላ እምነት ተከታይ ቢሆኑም ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመመለሳቸው በክህነታቸው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

«ቅዱስ ቤተ ክርስትያን ወደ እርሷ የመጡትን ትቀበላለች፣ አታገልም፡፡ የቀሲስ ገዳሙም ጉዳይ ይኸው ነው፡፡ ሊቃነ ጳጳሳትም አቡነ ዮሴፍ እና አቡነ እንጦንስ በፈቀዱት መሠረት አገልግሎቱን እንዲሰጡ እየተደረገ ነው፡፡» ያሉት ሓላፊው፤ አሳተሙት ስለተባለው የኑፋቄ መጻሕፍት እና ትምህርት በሊቃውንት ጉባኤ ተመርምሮ ውሳኔ እንዲሰጥበት ሒደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ሚያዝያ ጊዮርጊስ የንግስ ዕለት የሰሜን አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ «ቀሲስ» ገዳሙ በዓውደ ምሕረት ላይ ባስተማሩትን ትምህርት በመደሰት «መጋቢ ሐዲስ» የሚል ሹመት መስጠታቸውንም ሓላፊው ተናግረዋል፡፡

ሓላፊው እንዳሉት የቀሲስ ገዳሙን በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በአገልግሎት እንዲቀጥሉ የሚቃወሙ በርካታ ምእመናን እንዳሉ ሁሉ የሚደግፏቸውም የዛን ያህል የበዙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለያየ አቅጣጫ የሚመጣውን ቅሬታ አጣርቶ ውሳኔ ለመስጠት በሚደረገው ሒደት የቤተ ክርስቲያኒቱ ትክክለኛ አካሔድ በመከተል ውሳኔውን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እና የምእመናን ኅብረቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት በየጠየቀው በሙኒክ ቅዱስ ቤተ ጊዮርጊስ ቤተ ከርስቲያን ገንዘብ ምዝበራ ጉዳይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ «ይህ ጉዳይ በሀገሪቱ ፍ/ቤት በሕግ የተያዘ በመሆኑ ምንም የምለው ነገር የለኝም፤ በተፈፀመው ወንጀል ግን አዝኛለሁ» ብለዋል፡፡ ድርጊቱ እንዴት እና መቼ እንደተፈፀመ እንዲሁም ማን እንደፈፀመው ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ ውሳኔ ሲያገኝ በይፋ እንደሚገለጽም አስረድተዋል፡፡

«በጥምቀት አንድ ነን» በሚል ከአሁን ቀደም ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር ስለፈረሙት ጉዳይ ማስተካከያ ስለመሰጠቱ እና ስለአለመሰጠቱ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ጉዳዩ የቆየ በመሆኑ መነሳት እንደሌለበት ቿቅሰው፣ ሆኖም ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክለው መፈራረማቸው ዛሬም ስሕተት ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

«በመፈራረማችን ያጣነውም ያገኘነውም ነገር የለም፡፡ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት መሥራች ከመሆናችን አንፃር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር እንጂ ከዛ ውጪ የተደረገ ስምምነት አይደለም» ያሉት ሓላፊው፤ «በዚህ በኩል ከማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አካል ‘ትክክል አላደረክም’ ያለኝ የለም» ብለዋል፡፡

«በመፈራረሜ የፈፀምኩት ስሕተት ባለመኖሩ አልፀፀትም ይቅርታም አልጠይቅም፣  የምፀፀተው ስፈራረም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ፈቃድ ባለመጠየቄ ነው፤ እንዲህ ሰዎችን የሚያሳዝን መሆኑን አላወኩም፡፡ ፈቃድ ብጠይቅ ትልቅ ቁም ነገር ነበረው» ሲሉ ሓላፊው ተናግረዋል፡፡

የመገናኛ አውታሮች በሰፉበት፣ ዘመኑን ዋጁ በሚባልበት በዚህ ወቅት ከዓለም ተገልለን ብቻችንን ከመሆን እንዲህ ያለ ኅብረት መፍጠር ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸውም ሓላፊው አስረድተዋል፡፡ በምእመናኑ ኅብረት ጥያቄ እና በሊቀ ካህናት ዶ/ር መርአዊ ተበጀ ምላሽ ላይ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ጥያቄ የቀረበላቸው የሰሜን ምእራብ አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ በጀርመን የሚነሱ የምእመናን ጥያቄዎችን ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ከቀሲስ ገዳሙ ጉዳይ የጠራ መረጃ ስላልተገኘ እስካሁን በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት እርምጃ ለመውሰድ ያስቸገረ መሆኑን ጠቅሰው ጉዳዮቹ ተጣርተው በቅርቡ ውሳኔ እንደሚሰጥባቸው ተናግረዋል፡፡

የተፃፉት የኑፋቄ መጻሕፍት ላይ ወደ ፮ የሚሆኑ ነጥቦችን አውጥተው ማብራሪያ እንዲሰጡ በጠየቋቸው ጊዜ «ቀሲሱ» ‘አማርኛ ችግር ስላለብኝ ነው’ ማለታቸውን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው መጻሕፍቶቹ በሊቃውንት ጉባኤ እና በቅዱስ ሲኖዶስ በተቋቋመው የሃይማኖት ጉዳይ አጣሪ ኮሚቴ ተመርምረው ስሕተት እንዳለባቸው ከታመነ ቤተ ክርስቲያኒቱ እርምጃ እንደምትወስድ ተናግረዋል፡፡ ወደ ጀርመን ተመልሰው ከሌሎች ካህናት ጋር ስለ ጉዳዩ በመወያየት ተጨማሪ የማጣራት ሥራ እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡

የኑፋቄ ትምህርት ለሚያስተምሩ ግለሰብ እንዴት መጋቢ ሐዲስ የሚል ማዕረግ ሰጡ) የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፤ «ቀደም ሲል በሌላ እምነት እስከ ፓስትርነት ደረጃ የደረሰ ማዕረግ እንደነበረው ባለማወቄ እና በትምህርቱም ምእመናንን ጥሩ እውቀት ማስጨበጡን በመገንዘብ ይህንኑ ማዕረግ በቃል ሰጥቼዋለሁ፡፡ በጽሑፍ ያረጋገጥኩበት እና እውቅና የሰጠሁበት ሁኔታ ግን የለም» ብለዋል፡፡

ያ ማዕረግ የቤተ ክርስቲያኒቱ እውቅና እንደሌለው፣ ባለማወቅ በቃል የተፈፀመ ስሕተት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ የተፃፈው መጽሐፍ እንግሊዝ ሀገር ለሚገኙ ሊቃውንት ሰጥተው ስሕተቱ እየተነቀሰ እንዲወጣ እየተደረገ መሆኑን ብፁዕነታቸው ጠቅሰው፤ ከአሁን ቀደም ‘አቡነ ዮሴፍ ፈቅደው አገልግሎት እንዲሰጥ አደረጉ’ የተባለውን እና ማን አለቃ አድርጎ እንደሾማቸው በማጣራት ወደ ጀርመን ተመልሰው ከካህናቱ ጋር የመወያየት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ብፁዕነታቸው በሙኒክ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ስለተፈፀመው ምዝበራ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ከ19 ዓመት በላይ በዛው ቤተ ክርስቲያን በሓላፊነት ሲያገለግሉ በነበሩ ቄስ መስፍን ድርጊቱ መፈፀሙን ጠቅሰው፤ ጉዳዩ በሀገሪቱ ፍ/ቤት ለመከሰስ በአቃቢ ሕግ እየተመረመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሰበካ ጉባኤ እና ምእመናን ባደረጉት የኦዲት ምርመራ በሰነድ ብቻ 166 ሺሕ ዩሮ መጉደሉን እንዳረጋገጡ ጠቅሰው፤ ከሰነድ ውጪ ያለ ደረሰኝ ከምእመናን የገባ በርካታ ገንዘብም ይጎድላል የሚል እምነት መኖሩን አስረድተዋል፡፡ የገንዘብ አሰባሰብና አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ችግር መኖሩን ብፁዕነታቸው ቿቅሰው፤ ይህን ማስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ግለሰቡ ለፈፀሙት ተግባር ቤተ ክርስቲያኒቱ የራሱን ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ ለመውሰድ እንድትችል አህጉረ ስብከቱ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር በጥምቀት አንድ ስለመሆኗ ስለተፈረመው ሰነድ ጉዳይ በሰጡት ቃል ፍርርሙ እርሳቸው ወደዛ ሀገር ከመሔዳቸው 2 ዓመት ቀድሞ የተፈፀመ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፍርርሙ ለአንድ ግለሰብ ለጥቅም ሲባል የተፈፀመ እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱ እውቅና የሰጠችው አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ከፊርማ ያለፈ በተግባር የተፈፀመ ምንም ዓይነት ነገር እንደሌለ ያመለከቱት ብፁዕነታቸው፤ ጉዳዩን ከምእምናን በደረሳቸው ጥቆማ መሠረት ለቅዱስነታቸው ጭምር ማሳወቃቸውን አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ የምእመናን ኅብረትም ሆነ ሌሎች የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወዳጆች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ተቀብሎና መርምሮ ተገቢውን እርማት ለመስጠት ጥረቱ እንደሚቀጥል ብፁዕነታቸው ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ የደቡብ፣ ደቡብ ምእራብ እና ደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ሐምሌ 2 ቀን 2003 ዓ.ም «ለሚመለከተው ሁሉ» በሚል በጻፉት ደብዳቤ «ቀሲስ ገዳሙ ደምሳሽ በመባል የሚጠሩት ግለሰብ በፍራንክፈርት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ክብረ በዓል ላይ ታቦተ ሕጉ በቆመበትና ማኅበረ ምእመናን በተሰበሰቡበት ከስሕተቴ ተመልሻለሁ ሀገር ቤት ሔጄ ንስሐ ገብቻለሁ በማለት ለሕዝቡ በአስታወቁበት ወቅት ከስሕተት መመለስዋና ንስሐ መግባትዎ መልካም ነው ሆኖም ግን ቤተ ክርስቲያን መጠቀም የሚችሉት እንደማንኛውም ማኅበረ ምእመናን ነው ከማለት በስተቀር በቤተ ክርስቲያን ክህነት አገልግሎት ተመድበው እንዲሠሩ በቃልም ሆነ በጽሐፍ ያስተላለፍኩት ምንም ዓይት ትዕዛዝ የሌለ መሆኑን እገልጻለኹ፤» ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

*                                     *                                    *

የደቡብ የደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ አህጉረ ስብከት ዓመታዊ ጉባኤውን አካሔደ

(ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል ድረ ገጽ፤ ጳጉሜን 02 ቀን 2005 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የደቡብ፣ የደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀ/ስብከት ከነሐሴ 24 – 25፣ 2005 ዓ.ም በጀርመን ሀገር በሚገኘው የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ እንጦንስ ገዳም ዓመታዊ ጉባኤውን አካሄደ፡፡ በዕለቱም ብፁዕ አቡነ ሙሴ የአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ ጉባኤያት እና የመንፈሳውያት ማኅበራት ተወካዮች በተሳታፊነት ተገኝተዋል፡፡ ጉባኤው በብፁዕነታቸው ቡራኬ በጸሎት ከተከፈተ በኋላ ከቀረቡ አጀንዳዎች መካከል ሀገረ ስብከቱን ማዋቀር፣ የመንበረ ጵጵስና ጽ/ቤት መቀመጫ መወሰን እና በሀገረ ስብከቱ ሥር ባሉ አጥቢያ አብያተክርስቲያናት ወቅታዊ ችግሮች ተወያይቶ መወሰን የሚሉ ሦስት አጀንዳዎችን መርጦ በማጽደቅ ውይይቱን ጀምሯል፡፡Participants

የደቡብ፣ ደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ አህጉረ ስብከት በሥሩ የሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሥራቸውንና አገልግሎታቸውን በአንድነትና በመተባበር እንዲሠሩ የሚያስተሳስራቸው መዋቅር ባለመዘርጋቱና ሀ/ስብከቱ መንበረ ጵጵስና ስላልነበረው የሚጠበቅበትን መንፈሳዊ አገልግሎት ለመፈጸምና ለማስፈጸም ሳይችል መቆየቱን በመጥቀስ ሀ/ስብከቱ ሥራውን በተገቢ ሁኔታ መሥራት እንዲችል ሁሉን ያማከለ መዋቅር መዘርጋትና ሥራውንም በየክፍሉ የሚያስፈጽሙ ክፍሎችን ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ ለጉባኤው ገልጸዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ጉባኤው  በመዋቅሩ መቋቋም ላይ የጋራ ስምምነት በመያዝ መንበረ ጵጵስናው በጀርመን ሀገር እንዲሆን ወስኗል፡፡ የሀገረ ስብከቱን ሥራ እንደሚጠበቀው ማከናወን ይቻል ዘንድ ሁሉም አጥቢያዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ በመስማማት ዓመታዊ የበጀት ወጪ በማስላት በአጥቢያዎች ላይ የገንዘብ ምደባ ተደርጓል፡፡ የሀገረ ስብከቱን ሥራዎች በአግባቡ ለማከናወን እንዲያግዝም በብፁዕነታቸው የሚመራ ስድስት አባላት ያሉት ሥራ አስፈጻሚ በጉባኤው ተመርጧል፡፡ የሥራ አሥፈጻሚው የአገልግሎት ዘመንም ሁለት ዓመት እንዲሆን ተወስኗል፡፡

በሦስተኛ አጀንዳንት ተይዞ የነበረው በአህጉረ ስብከቱ ሥር ባሉ አጥቢያ አብያተክርስቲያናት ዙሪያ የሚታዩ ወቅታዊ ችግሮችን በተመለከተ ሦስት ጉዳዮችን አንስቶ ተወያይቷል፡፡ እነዚህም “ገለልተኛ” ብለው ራሳቸውን ስለሚጠሩ አጥቢያዎች፣ ስለ ቀድሞው የሙኒክ ቅ/ገብርኤል ቤ/አስተዳዳሪ እና በሃይማኖት ሕጸጽ ምክንያት በምእመናን ክስ ቀርቦባቸው ውሳኔ እየተጠባበቁ ስላሉት የቪዝባደን ቅ/ጊዮርጊስ አስተዳዳሪ ቄስ ገዳሙ ደምሳሽ ሲሆን ብፁዕ ሊቀጳጳሱ በካህናት ጉባኤ ጉዳዩን በማጣራት ውሳኔ እንዲሰጡበት ጉባኤው ተስማምቷል፡፡ በተለይም በትምህርታቸው ምክንያት በምእመናን ክስ ስለቀረበባቸው ካህን ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር አፋጣኝ ውሳኔ እንዲያገኝ ጉባኤው በአጽንኦት አሳስቧል፡፡ በመጨረሻም ብፁዕ ሊቀጳጳሱ ለጉባዔው መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉትን ሁሉ በማመስገን ጉባኤው በጸሎት ተጠናቋል፡፡

Advertisements

10 thoughts on “በመናፍቅነት የተከሰሱት የቪዝባደን ቅ/ጊዮርጊስ ደብር አስተዳዳሪ «ቄስ» ገዳሙ ደምሳሽ ጉዳይ ዛሬ በቋሚ ሲኖዶሱ ይታያል

 1. በአማን ነጸረ March 19, 2014 at 7:54 am Reply

  1. የኑፋቄ ክስ እንዲህ ሥርዐቱን ጠብቆ ሲመጣ ደስ ይላል!!በዚህ ረገድ የአውሮፓ ማእከል የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እና መላው ምዕመናን ከብፁዕ አቡነ ሙሴ ጋር ሆነው ችግሩን በህዝባዊ ውግዘት ሳይሆን በትክክለኛው የቤ/ክ ሥርዓት እልባት ለመስጠት ያደረጉትን ተጋድሎ አደንቃለሁ!!
  2. በእልቅና ካባ ፓስተር መቅደስ ገባ? የሚለውን የቅኔ መምህር፣የትርጉዋሜ መጻህፍት አዋቂ እንዲሁም የአመቱን የቅዱሳንን ታሪክ ባጭሩ አጣፍጠው በ2 ቅጽ ያሳተሙልንን ውድ የቤ/ክ ልጅ የመ/ር ህሩይን መጽሐፍ በወፍ በረር የማየት አጋጣሚ አግኝቼ ስለነበር የተጠርጣሪው መናፍቅ ጉዳይ እልባት አለማግኘቱ ለእኔም ብዥታ ፈጥሮብኝ ነበር!!
  3. እርግጥ የተጠርጣሪውን መጽሐፍ በህሩይ ተጠቅሶ ከማንበብ ውጭ ዋናውን ቅጅ የማግኘት አጋጣሚ ስላላገኘሁ መጽሐፋቸውን ሳላነብ ስለእሳቸው መናፍቅነት ከሲኖዶስ ቀድሜ ለመደምደም አልተቻኮልኩም – መጠርጠሬ ባይቀርም!!
  4. እንግዲህ አባቶች የእኔንም ሆነ የመሰሎቼን ብዥታ በሚያጠራ መልኩ የቀረበውን ማስረጃ መርምረው ለቤ/ክ ይበጃል የሚሉትን ውሳኔ እንደሚወስኑ ተስፋ አደርጋለሁ!!በፍጥነት ውሳኔ ላይ ካልደረሱም እስከዚያው ለጊዜው የግለሰቡን ስልጣነ-ክህነት ይዘው(አግደው) ቢያቆዩ ተገቢ ይመስለኛል!!ለማንኛውም ሃይማኖታዊ በሆኑ ጉዳዮች ሁሉ ቅ/ሲኖዶስ ለሚያሳልፋቸው ውሳኔያቸው ተገዥ መሆን ግድ ነው!!ብፁዕ አቡነ ገሪማ እንዳሉት በቤ/ክ የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ ይግባኝ የሌለው ፍርድ ነውና!!
  ወነአምን በአሀቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላእለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት!!

 2. Bin March 19, 2014 at 8:51 am Reply

  yeminorew be german ager new. kenehatiyatem bihon wode bete kirstiyan eyehedku egelegelalhu. tadiya beteley be bealat qenat be andu atbiya be german ager kalut abyate krstiyanat be andu sinisebaseb hulgize alqishe new yemimelesew. enem bicha aydelehum leloch wondimochina ehitochim betemesasay huneta alqisew yimelesalu. lezih mikniyatu degmo enih yetebalu menafiq sew be abatoch mekakel ende abat eyetegegnu ye nufaqe timihirtachewun sizeru silemayina sile misema new. be ewunet be zih ager yemininor sewoch siqay wust new yalenew. abatoch lidersulin yigebal. ewunet hono be sinodos ketaye,, wusanewun eninafiqalen. ke baed ager nuro gar mekera kebedebin eko. ere ye abat yaleh…ere chuhetachinin simun..

 3. Mestawot Tarekegne/Wisbaden-Germany March 19, 2014 at 2:21 pm Reply

  we are very glad to see here the coverage of the issue. and we are very eager to hear the decision. till then we wish to our religion and motherland all the best!!!

 4. Anonymous March 19, 2014 at 7:11 pm Reply

  . የኑፋቄ ክስ እንዲህ ሥርዐቱን ጠብቆ ሲመጣ ደስ ይላል!!በዚህ ረገድ የአውሮፓ ማእከል የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እና መላው ምዕመናን ከብፁዕ አቡነ ሙሴ ጋር ሆነው ችግሩን በህዝባዊ ውግዘት ሳይሆን በትክክለኛው የቤ/ክ ሥርዓት እልባት ለመስጠት ያደረጉትን ተጋድሎ አደንቃለሁ!!

 5. Kebede March 19, 2014 at 7:31 pm Reply

  ”መናፍቅ” ያስባላቸውን የነገረ መለኮት ትምህርት ከዚህ ላይ ቢገለጽልን ጥሩ ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የእምነትዋ መመሪያ አድርጋ ከምትቀበላቸው ሐዲሳት፤ ብሉያትና ሊቃውንት የሚቃረን ትምህርት የሚያስተምር ሁሉ ኣዎ መናፍቅ ሊባል ይችላል። አዋልድ መጻሕፍትን እንደ ዶግማ መጻሕት አልቀበልም ማለት ግን መናፍቅ አያስብልም።

 6. Anonymous March 21, 2014 at 6:23 pm Reply

  ወንድማችን አቶ ከበደ የግደለሽነት ጥያቄ በማቅረብህ ብዙ አልተገረምኩም የ3 መጻህፍት ስህተቶች እዚህ ቢቀርቡልኝ ብለህ መጠየቅህ ግን ግራ ያጋባል፤ ግን እውነት ይሄ ነው ስህተቱ ተብሎ ቢነገርህ የምትደነግጥ ሰው ነህ? ከሆንክ እኮ ከላይ ዜናው ላይ ስህተቶቹ ምን እንደሆኑ ፍንትው አድርጎ በማሳየት የሰውየውን ማንነት ያጋለጠ መጻፍ ታትሞ ነበር የሚል ዜና ነበረልህ ለምን ገዝተህ ወይ ተውስህ አላነበብክም ? አዋልድን አልቀበልም ማለት መናፍቅ አያስብልም ያለከው ሌላው አሳብህ ደግሞ አስቂኝ ነው ፤ አዋልድ የሚባሉት አንተ ሊቃውንት ያላካቸውን መጻህፍት የጻፉ ቅዱሳን የጻፋቸው የስርአት የጸሎትና የትምህርት መጻህፍት አይደሉ እንዴ? ዝም ብለህ በደፈናው ለኦርቶዶክስ ሃይማኖት ሳይሆን ለገዳሙ ደምሳሽ ጥብቅና ቆሜአለሁ አትልም?

 7. Kebede March 22, 2014 at 5:58 pm Reply

  ወንድም ስም የለህ፥ ሊቃውንት ተብለው የምንቀበላቸው መጻሕፍት በኃይማኖት አበውና በመጽሐፈ ቅዳሴ ውስጥ የሚገኙት በነቅዱስ አትናቴዎስ ፥ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስና ዘእንዚናዙ ፥ ቅዱስ ቄርሎስ ፥ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ፥ ቅዱስ ባስልዮስ፥ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፥ ቅዱስ ኤፍሬም ዘሶርያ ወዘተ የመሳሰሉት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊቃንት ያስተማሩትን ትምሕርት ነው። ከነዚህ ሊቃውንት በኋላ በየዘመኑ በነገሥታቱና በደባትሩ የተጻፉት ገድላት፥ ድርሳናትና የጸሎት መጻሕፍት በነገረ መለኮት ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች በአስረጅነት አይቀርቡም ፤ ቀርበውም አያውቁም። እነዚህን ”አልቀበልም ” የሚል ሰው ”መናፍቅ ” ሊባል አይገባውም። ሌላው ቢቀር በሀገራችን በኢትዮጵያ ግንቦት 21 ቀን 1870 ዓ.ም የተደረገውን የቦሩ ሥላሴን ጉባኤ ታሪክ ማንበቡ በቂ ነው። አዎ የተባለው ግለሰብ የጻፈውን መጽሐፍ አላነበብኩም። ለዚያም ነበር ያነበቡት መሠረታዊ ጭብጡን እንዲጠቁሙኝ የጠየኩት። መጠየቅ ድግሞ ኃጢአት አይደለም። ‘የጠየቀ አወቀ፥ ያልጠቀ ደነቆረ’ እንደሚሉት ኣበው።

 8. Anonymous March 25, 2014 at 2:25 pm Reply

  betam tiru sira

 9. Anonymous November 8, 2014 at 10:14 pm Reply

  እኔ የምለዉ እኛ የተለየ ከቋም ያላቸዉ አካህናትን የሚወገዝበት እንደ መናፍቅ የሚቆጠርብት ዓለም የማህበረ ………ን አቋም ያላራገበ ሁሉ ለምንድን ነዉ መናፍቅ የሚባለዉ

 10. Anonymous May 12, 2016 at 9:43 am Reply

  ከሁለት አመት ሙሉ አላስረክም ሲል ቆይቶ ገዳሙ ደምሳሽ ንስሐ አልገባም ስጋውናደሙ መታሰቢያ ነው በማለቱ ወደነበረበት አዳራሽ ተመለሰ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: