አባትም አባት ልጅም ልጅ እንዲኾን፣ ተክለ ሃይማኖት ሆይ ጸልይልን

His Holiness Abune Mathias with their Graces the archbishops winding up the Synod meetingመላዋ ኢትዮጵያ እንደ አንድ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከት ትቆጠር የነበረችበት የ1600 ዓመታት የሞግዚትነት ታሪክ ከብዙ ተጋድሎና እልክ አስጨራሽ ጥረት በኋላ አክትሞ የመንበረ ፕትርክናውን ነጻነት መቀዳጀቷ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የተበሠረበት ዘመን ነው – በዓለ ሢመተ ፓትርያርክ፡፡

ብሔራዊ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ ከመቋቋሙ በፊት ለዛሬው ጠቅላይ ቤተ ክህነት መሠረት የጣለውና በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመን ከየክፍለ ሀገሩ የአብነት ት/ቤቶች በተውጣጡ 72 ሊቃውንት መስከረም ፰ ቀን ፲፱፻፲፰ ዓ.ም. በታላቁ ቤተ መንግሥት ቅጽር የተሰበሰበው የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ጉባኤ (መንፈሳዊ ጉባኤ ዘመንግሥተ ኢትዮጵያ) ቤተ ክርስቲያናችን ለተቀዳጀችው የመንበረ ፕትርክና ነጻነት የጎላ አስተዋፅኦ ያደረገ ነው፡፡

የኮፕት ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ የሚሾመው ሊቀ ጳጳሳት÷ ‹‹ለዘለዓለም የግብጽ ሰው ብቻ እንጂ ኢትዮጵያዊ መኾን የለበትም›› የሚለው አቋሟ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለ1600 ዓመት በፈቃድዋ ትሠራበት በነበረው ልማድ ላይ ተመሥርቶ የቆየና አኹን ደግሞ በፈቃድዋ ታሻሽለው ዘንድ የሚገባት እንደኾነ መንፈሳዊ ጉባኤው አስታውቋል፡፡ የቀድሞው ልማድ የሕዝቡን ባህልና ቋንቋ የማያውቁና በሕዝቡ ቋንቋ የማይሰብኩ፣ በቤተ ክርስቲያናችንና በአገራችን ላይ አደጋ በደረሰ ጊዜ ጥለው የሚሸሹ ግብፃውያን ጳጳሳት የታዩበት በመኾኑ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ብርቱ ጉዳት አድርሶባታል፡፡

የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያዊ ሊቀ ጳጳሳት በኢትዮጵያ እንዳይሾም የምታነሣው ሌላው ቃል ‹‹ወሰብአ ኢትዮጵያሰ ኢይሢሙ ሊቀ እማዕምራኒሆሙ – የኢትዮጵያ ሰዎች ከሊቃውንቶቻቸው መካከል ኤጲስ ቆጶሳት አይሹሙ›› የሚለውን በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፬ ቁጥር ፶ የሰፈረ አንቀጽ ነው፡፡

መንፈሳዊ ጉባኤው እንደተቸው፣ ይህ አንቀጽ ኢትዮጵያውያን ጳጳስ ከእስክንድርያ ለማስመጣት በእጅ መንሻ የሚሰጡትን ጥቅም ላለማጣት ሲባል የተፈጠረ እንጂ የኮፕት ቤተ ክርስቲያን እንደምትለው ከቅዱሳን አበው ከሠለስቱ ምእት በጉባኤ ኒቂያ ተጽፎ የተወሰነ አይደለም፤ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ፍትሕ መንፈሳዊ የሌለና በሥርዋጽ የገባ፣ በክርስትና እምነት የዘርና የወገን ልዩነት የሚያደርግ ነው፡፡

ብፁዕ አቡነ ገሪማ አንቀጹን በተቹበት ጽሑፋቸው÷ በ፲፭ው መ.ክ.ዘ ከዓረብኛ ወደ ግእዝ ከተተረጎሙት ቅዱሳት መጻሕፍት አንዱ በኾነው ፍትሐ ነገሥት በሥርዋጽ የገባው፣ ሰሜን አፍሪቃና መካከለኛው ምሥራቅ በ፯ው መቶ ዓመት በሰለሙ ዓረቦች በተወረረ ጊዜ የእስክንድርያው ኮፕት ቅዱስ ሲኖዶስ በዓረቦቹ ተጽዕኖ ከእስክንድርያ ወደ ካይሮ ተዛውሮ በካይሮ አሮጌ ከተማ መዓልቃ በተባለው ቦታ በተደረገው ስብሰባ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡

ብሔራዊና ሃይማኖታዊ ስሜት የነበረው በ፲፩ው መ.ክ.ዘ የነገሠው ቅዱስ ሐርቤ ወስመ ጥምቀቱ ገብረ ማርያም የኢትዮጵያን ስፋት፣ የሕዝበ ክርስቲያኑን ብዛት በማየት መላ ኢትዮጵያን ዞረው፣ ተዘዋውረው በሕዝቡ ቋንቋ የሚያስተምሩ፣ የሚባርኩ፣ የሚቀድሱ፣ የሚክኑ ዐሥር ኢትዮጵያውያን ቆሞሳት የኤጲስ ቆጶስነት ሥልጣነ ክህነት በመስጠት እንዲሾምለት በምስር – ካይሮ የመካነ መዓልቃውን ቅ/ሲኖዶስ ጠይቆ ነበር፡፡

ይኹንና ከላይ የተጠቀሰውን የፍትሐ ነገሥት ሥርዋጽ በመጥቀስ የመካነ መዓልቃው ሲኖዶስ እምቢተኛ ኾነ፡፡ እንዲያውም ሚያዝያ ፲ ቀን በሚነበበው የስንክሳር መጽሐፋችን ‹‹ወበዛቲ ዕለት›› በሚለው ‹‹ኢትዮጵያውያን የማይገባቸውን ኤጲስ ቆጶስነት ስለተመኙ እግዚአብሔር ተቆጥቶ በሀገራቸው ላይ ሦስት ዓመት ሙሉ ጠል ለመከር፣ ዝናም ለዘር ከልክሏቸው በድርቅ ቀጣቸው›› በማለት ግብፃዊው ዳግማዊ ፓትርያርክ ገብርኤል በታሪክ መዝግቦት ይገኛል፡፡ እኛም ይህን እንደ መልካም ነገር አድርገን ሚያዝያ ፲ ቀን ወበዛቲ ብለን በመነሣት እናነበዋለን፡፡ ይህን ወበዛቲ ዕለት የሚለውንና ሌላውንም ‹‹ወሰብአ ኢትዮጵያሰ ኢይሢሙ ሊቀ እማዕምራኒሆሙ›› የሚለውን ቅዱስ ሲኖዶስ አስቦበት ከዛሬው ዕለት ጀምሮ ከመጽሐፈ ስንክሳሩ እና ከፍትሐ ነገሥቱ ቢያወጣው ያማረ፣ የሠመረ ታሪክ በኾነ ነበር፡፡

ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በአንደኛው መቶ ዓመት በሐዋርያት ዘመን በ፴፬ ዓ.ም. በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አማካይነት ነው (ግብ.ሐዋ.፰÷፳፮-፵)፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ታውቆ በኤጲስ ቆጶስ ተባርኮና ተቀድሶ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም የተጀመረውም በ፬ው መቶ ዓመት በቅዱስ ፍሬምናጦስ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ነው፡፡ በሶርያ የተወለደ ግሪክ በኾነው አባ ፍሬምናጦስ ኤጲስ ቆጶስነትን ከእስክንድርያ ማምጣትም የክርስትናውን ታሪክ ከግብጽ አለማምጣት መኾኑ ለኹላችንም ግልጽ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ጉባኤ ሊቃውንት ለእስክንድርያው የቅዱስ ማርቆስ መንበር በሰብሳቢው ዕጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አማካይነት ሰኔ ፳፩ ቀን ፲፱፻፴፮ ዓ.ም. ባስተላለፈው የውሳኔ ማስታወቂያው÷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳትንና ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም ሥልጣን ያለው ኢትዮጵያዊ ሊቀ ጳጳሳት ከኢትዮጵያውያን መንፈሳውያን አባቶች መካከል በእስክንድርያው ፓፓና በመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ ተባርኮና ተቀብቶ እንዲሾምላት ያነሣችው የመንፈሳዊ መብት ጥያቄ የቅዱስ ማርቆስን አባትነት አያስቀርባትም፡፡

ፋሽስት ኢጣልያ ከኢትዮጵያ ተጠራርጎ ከወጣ ከ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ወዲህ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ጉባኤና በካይሮ ቅዱስ ሲኖዶስ መካከል በተፈጠረው ቅራኔ በየጊዜው ውይይት ለማድረግ የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት መልእክተኞች ወደ ካይሮ በመመላለስ ከስምምነት ላይ በመድረሳቸው በ፲፱፻፵ ዓ.ም. አምስት ኢትዮጵያውያን ቆሞሳት ኤጲስ ቆጶሳት ኾነው በካይሮ ተሾሙ፤ ቀደም ሲል የተጀመረው ውይይትም ቀጥሎ በ፲፱፻፵፫ ዓ.ም. የሊቀ ኤጲስ ቆጲስነቱ ማዕርግ ተገኘ፡፡

his grace the late abune gorgorios the second

ይህ መንበር ቅዱስ በመኾኑ ያለፈውን የሚናገር የወደፊቱን ትንቢት የሚገልጽ ያዘኑትን የሚያረጋጋ የተቸገሩትን የሚረዳ፣ መንፈሳውያን አገልጋዮችን የሚመግብ ከፍተኛ መንበር ነው፡፡ ይህ መንበር የሃይማኖት ብቻ ሳይኾን ለክብርና ለታሪክ ልዩ ልዩ የሃይማኖት ተከታዮች ያከብሩታል፤ ለታሪክ ልዕልና ይከበራል፡፡ ይህ መንበር በቀላል የተገኘ አይደለም፤ በሥጋዊ አካልም ቢኾን ስለ መንበሩ ሲባል በከፍተኛ ደረጃ አድክሟል፡፡ እንግዲኽ ይህን መንበር ለአገራችን እንደ ታላቅ በረከት ነውና የምንመለከተው፡፡(የቀድሞው የሸዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ ለ፫ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፲ኛው በዓለ ሢመት በጽሑፍ ካሰፈሩት መልእክት)

ከዚኽ በኋላ ከኢትዮጵያ ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት ተውጣጥቶ የተሠየመው ልኡክ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻውን የፓትርያርክነት ማዕርግ ለማምጣት ውይይቱን ስላላቋረጠና መልካም ውጤትም ስላስገኘ በ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ኾነው በግብጻዊው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ፮ በካይሮ ተሾሙ፡፡

በዚህ ሹመት ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙትና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ መብቷንና ታላቅ ክብሯን እንድትቀዳጅ ለ31 ዓመታት የተካሔደውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የመሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ባሰሙት ንግግር÷ ‹‹የኢትዮጵያ ታላቅነትና የሥልጣኔ ዕድገት ከሃይማኖት ትልቅነቷ ጋራ የተባበረ እንዲኾን ያስፈልጋል፡፡ ድካማችንን ባርኮ ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ለኢትዮጵያ የተገኘበትን ይህን ታላቅ ቀን ለማየት ላበቃን ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ በሐዋርያው በቅዱስ ማርቆስ ልጆች መካከል ዛሬ የተገኘው መልካም መግባባትና መከባበር ሁለቱ ቤተ ክርስቲያኖቻችን በመደጋገፍ የሚፈጽሙትን መንፈሳዊ አገልግሎት ለብዙ ፍሬ የሚያበቃው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ለዚኽ ማዕርግ በቅተው ከባድ አደራ ያለበትን የፓትርያርክነት ተግባርዎን ሲጀምሩ ሥራዎን ለማከናወን እግዚአብሔር ይርዳዎ›› ብለው ነበር፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስም በዚያ ሢመታቸው ወቅት ካሰሙት ታሪካዊ ንግግር መካከል፡- ‹‹ያንድ ነጻ መንግሥትና ያንድ ነጻ ሕዝብ እናት መሠረታዊነቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ረገድ ራሷን ችላ የምትተዳደርበት እንድትኾን ግርማዊነትዎ ያደረጉት ድካም ከታሪክ በላይ ነው፤ በመንበረ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ሳድሳዊ የተፈጸመው ይህ የፓትርያርክነት ሥነ በዓል ለመጭው ትውልድ መታሰቢያ ይኾን ዘንድ በቤተ ክርስያናችን ከፍተኛ የታሪክ ምዕራፍ የያዘ ይኾናል፤ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ በረከትና ረድኤት የኢትዮጵያን ሕዝብ ይባርክ ይቀድስ፤ ኢትዮጵያ በነጻነት ትኑር፡፡›› የሚል ይገኝበታል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በመንበረ ተክለ ሃይማኖት የመጨረሻውን የክህነት ማዕርግ መብቷን (የኤጲስ ቆጶስነት፣ የሊቀ ኤጲስ ቆጶስነትና የፓትርያርክነት ጸጋን) ለማረጋገጥ በእነንጉሥ ሐርቤ ሃይማኖታዊና ብሔራዊ ስሜት ተቆስቁሶ በእነ ዐፄ ዮሐንስ ንጉሠ ጽዮን ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ የተቀጣጠለውና በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ የፈጸመችው ተጋድሎ እንዲኹ ያለራእይ አልነበረም – በራስዋ ቋንቋና በራስዋ ልጆች ምእመናኗን በማስተማር የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በከፍተኛ ደረጃ ለማስፋፋት፤ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅሟን በማጎልበት ለሕዝብዋ በቂ አገልግሎት ለማበርከት ነበር፡፡

Abune Gerima Sept_21_2006በብፁዕ አቡነ ገሪማ አገላለጽ÷ ከ1600 የዘመናት ደጅ ጥናት በኋላ ፈቃደ እግዚአብሔር ኾኖ ጊዜው ሲደርስ በጊዜው ጊዜ የኢትዮጵያውያን ምኞት ተፈጽሞ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያውያን ኤጲስ ቆጶሳት ሊቃነ ኤጲስ ቆጶሳትና ፓትርያርኮች መባረክ መቀደስ ሥልጣነ ክህነት መቀበል ችለዋል፡፡

እግዚአብሔርን የሚያምን፣ ሀገሩን ወገኑን የሚወድ፣ እውነትን የሚከተል በማንኛውም ጊዜ የመንፈስ ደስታ ይሰማዋል፤ ይህንም ያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው፡፡

ለቀደምት አበው ምስጋና ይድረሳቸውና፣ ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፕትርክና ራስዋን ከቻለችበት ከ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 54 ዓመታት ስታከብረው በቆየችው የመንበረ ተክለ ሃይማኖት የነጻነት በዓል በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ከኀምሳ በላይ በኾኑ አህጉረ ስብከት ተስፋፍታለች፤ በሌላ አገላለጽ ከብሔራዊነት ወደ ዓለም አቀፋዊነት ተሸጋግራለች፡፡

የመንበረ ተክለ ሃይማኖት ወራሽ የኾነው ብሔራዊ ቅዱስ ሲኖዶስ አምስት ፓትርያርኮች አንብሮተ እድ በተሾሙ 109 ሊቃነ ኤጲስ ቆጶሳት (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ 17፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ 9፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት 28፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ 6፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ 49)  ከ50 ሚልዮን በላይ ምእመናን አባታዊ አመራር የሚያገኙበትና ለሐዋርያዊ ሥራዋ የሚያገለግሉ የጠነከሩ መሠረቶችን በዓለም ዙሪያ መሥርታለች፡፡

በብፁዕ አቡነ ገሪማ የበዓለ ሢመት ጽሑፍ እንደተመለከተው፣ ይህ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፊትና ኋላ የኾነ፤ የሚኾን ብዙ የተነገረ፤ የሚነገር የታሪክ ገጽታ ያለው በመኾኑ ዕለታዊ፣ ወርኃዊ፣ ዓመታዊ ብቻ አድርገን መተው የለብንም፡፡ ዛሬ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ አንደኛ ዓመት በዓለ ሢመት የምናከብረው፣ ቅዱሳን ፓትርያርኮች በየዘመነ ክህነታቸው ያስመዘገቧቸውን የሥራ ውጤቶችንም በማዘከር ነው፡፡

ዛሬ በዓለ ሢመት ሲከበር፣ ያን ኹሉ የአባቶቻችንን ተጋድሎ በማስታወስ ሐዋርያዊ ተልእኳችንን ከዳር ለማድረስ የሐዋርያዊ መሠረቶቻችንን ዕንቅፋት በማስወገድ አንድነታቸውን የመጠበቅና አቅማቸውን የማጎልበት ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በአንደኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸው አከባበር ላይ እንደተናገሩት፣ ‹‹በዓለ ሢመት የአንድ ግለሰብ በዓል ሳይኾን የቤተ ክርስቲያኒቱ ክብርና ልዕልና ለመጠበቅ የሚፈጸም ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ በዓል ነው፤ ፓትርያርኩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ወኪል እንጂ ባለቤት አይደለም፤ ለዚኽም ነው ይህ ክብረ በዓል የሚደረግለት፡፡››

የቅዱሳን ፓትርያርኮች በዓለ ሢመት መከበር ያለበት በሓላፊነት ስሜት ለተሻለ ሥራ በመነሣሣት መኾኑን ያስገነዘቡት ቅዱስነታቸው፣ ዓላማውም ይኸው ነውና የቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ክብር በምን ላይ አለ? በፊትስ እንዴት ነበረ? አኹንስ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በተሳካ ኹኔታ ለማከናወን ምን መደረግ አለበት በሚል አስተውሎት በዓሉ ሊከበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ክርስትናችን የሚያወግዘውን የዘርና የወገን ልዩነት ተዋግተን፣ ሕገ ወጥ ጥቅምን አስቀርተን ያስከበርነውን መንበረ ፕትርክናችን ዛሬም በሌላ ገጽ ከከበበው ጎሰኝነትና ሙሰኝነት ነጻ አውጥተንና ነጻነቱን ፍጹም አድርገን ክብሩንና ልዕልናውን ወደ ላቀ ደረጃ ልናደርሰው ይገባል፡፡ የመንበረ ተክለ ሃይማኖት ወራሽ የኾነውና ከፍተኛውን የክህነት ማዕርግ የተቀዳጀው ብሔራዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ፓትርያርክና ሊቃነ ጳጳሳት አባትነታቸው፣ የእኛም ልጅነታችን ሊረጋገጥ የሚችለው በቤተ ክርስቲያናችን የተቋማዊ ለውጥ ጥረቷ ፊት የተጋረጠው ይኽ ፈተና በእኛው የተጠናከረ መተባበር ሲወገድ ብቻ ነው፡፡

Megabe Mistir Wolde Rufael Fetahiእኒኽንና የመሳሰሉትን የነጻነቱን በዓል ቁም ነገሮች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና ተግዳሮቶች የሚጠቁሙ ቅኔዎች በበዓለ ሢመቱ አከባበር ቀን የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ከኾኑት መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ ቀርበው ተሰምተዋል፡፡ ‹‹ያልተቀኙትን ቅኔ መተርጎም ያላሳደጉትን ውሻ ጆሮ እንደመቆንጠጥ ነው›› ይባላልና ባለቅኔው ባቀረቡበት አኳኋን በጡመራ መድረኩ ተስተናግደዋል፡፡ የማበረታቻ ውዳሴውን ያኽል ዕለቱንና ወቅቱን የተመለከተ ታሪክ፣ ትምህርት፣ ማሳሰቢያና ምክርም ተካቶበታልና በጎ በጎውን እንረዳበት፡፡ ‹‹አባትም አባት ልጅም ልጅ እንዲኾን፣ ተክለ ሃይማኖት ሆይ ጸልይልን›› ይላል የመጀመሪያው ጉባኤ ቃና…

ቅኔያት

ከመጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ

ጉባኤ ቃና

አበዊነ አበ ወውሉድነ ውሉደ

ከመ ይኩኑነ ጸሊ ተክለ ሃይማኖት ፈድፋደ

ጉባኤ ቃና

ተክለ ሃይማኖት ዕቀቦ በጸሎትከ ዘዘልፍ

ለርእሰ አበው ማትያስ እስመ ፈተናሁ ግዙፍ

ጉባኤ ቃና

ጳውሎስ ንቃሕ እምንዋምከ ይእዜ

በበዓለ ማትያስ ለከ አኮኑ ይደልዎከ ኑዛዜ

ጉባኤ ቃና

ለበዓለ ቅዱስ ማትያስ ግዝፈ ሥጋ አልቦቱ

እም ዓመት ዓመተ እስመ ጸዋሚ ውእቱ

 

ኩልክሙ

ለርእሰ አበው ማትያስ እመንገለ ጽሕሙ

ናስተማስሎ በአሮን ዘእንበለ ከንቱ ውዳሴ

ወእመንገለ ዓይን ይመስል ሱስንዮስሃ ነጋሤ

አምጣነ ወአሉ ወኃደሩ

እንዘይፈጥሩ ኪያሁ ሥላሴ

ወተፈጥረ ለሕዳሴ

ከማሁ ለኖኅ ድኅረ ተፈጥረ ድምሳሴ

 

ለዓለም

ትካትሂ በደብረ ሲና በከመ አርአዮ ለሙሴ

እንዘ ያስተፃምር ነበልባለ ምስለ ሐመልማል አምላከ አውሴ

ኢይፈቅድ ይፍልጥ እምነ ብእሲ ብእሴ

ለማትያስ ሕሊናሁ እመ የአብዩ ለቅዳሴ

እምአጽባዕት አጽባዕት ወእምናሴ ምናሴ

ለማትያስ ሕሊናሁ እመ የአብዩ ለቅዳሴ

 

፪ኛ ኩልክሙ

ኦ ማትያስ አግአዜ ኩሉ

አግአዚተ ትኩን ለዓመትከ ስድዳ

ለወልደሩፋኤል ምስሌሁ ወምስለ ካልአን ውሉዳ

ወበዓመትከ ጽጌሬዳ

ሙስና ተሰደ እም ቤተ ክህነት ቤርሙዳ

 

ለዓለም

ዕቀባሂ ለብኩርናከ ፍጥረተ ዓለም ዘንዕዳ

ወአስምዕ ተጽእኖታ ለበዓለ ቤት ወለእንግዳ

ውሉደ ቤታ ለአጋር እስመ ዖድዋ በዐውዳ

ወቦ በአመክሮ እምሉዓላሌሃ ከመያውርዳ

ላእከ ቤተ ቦንኬ ሥሉጥ በውስተ ስፉሕ ማሕፈዳ

ወቦ በአመክሮ እምሉዓሌሃ ከመያውርዳ

 

መወድስ

አበ ብዙኃን ማትያስ ናስተበቁአከ

እም ዝንቱ ዓመት ወሚመ እምይእዜ

በበሕቅ ትግበር ለውሉድከ ኑዛዜ

ወከመትጸጉ ለጊዜከ ጊዜ

እስመ እግዚእነ በበሕቅ

ዘኩሎ ፈጸመ ወአሰሰለ ትካዜ

ወሚመ በእራሁ እንዘይከውን አኃዜ

ዓለማተ ለፍጥረቱ ዘኮነ ተአዛዜ

ወእንበለ ዕረፍት የሐውጽ ነገደ ጉራጌ ወዶርዜ

አሕጸረ ጊዜያተ ጳውሎስ ዘሳንሆዜ

 

ኩልክሙ

አበዊነ ቁሙ በእግረ ዋህድና

ጸላኢ ኢይርከብ በውስትነ ቤተ

ወኢይባዕ ውስጠ እንዘ ይተሉ ፍልጠተ

ወቤቴል አሐቲ ኢትኩን ዝርወተ

አኃዝ ማኅበራተ*

መዋግደ ብዙኅ ጸጋከ ወአስተናድፍ ሥርዓተ

ማትያስ ኖላዊነ በዘረሰይከ ክሡተ

ለቤቴል ሙስናሃ ዘኮነ ኅቡአተ

እንዘ ያውእዙ ደመ ወይሰብሩ አዕፅምተ

ዘአወፈዩከ አበዊከ ጥንታዊተ ሃይማኖተ

ወአባግኢከ ትዕቀብ እስመረከብከ እብሬተ

ዘአወፈዩከ አበዊከ ጥንታዊተ ሃይማኖተ

Advertisements

2 thoughts on “አባትም አባት ልጅም ልጅ እንዲኾን፣ ተክለ ሃይማኖት ሆይ ጸልይልን

 1. በአማን ነጸረ March 11, 2014 at 2:51 pm Reply

  ሐራ እግዚአብሄር ይስጥልኝ!!
  በጽሁፍ በሚያቀርቡዋቸው የተከሸኑ ጽሁፎችና ስብከቶች የሚመስጡኝንና በኢኦተቤክ የውጭ ግንኙነት ዙሪያ ብዙ ጥልቅ መጣጥፎችን ቢያወጡም ሳይዘመርላቸው ከመንጦላእቱ ጀርባ ሆነው የደከሙትን አባት ብፁዕ አቡነ ገሪማ ንግግር ጠቀስ ስላደረጋችሁልን፣በሀሴት ተሞላሁ!!
  ከግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሥ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ስለ ቤ/ክ ጥቅም ያለአንዳች ፍርሃት ፊትለፊት በብዕራቸውና በውብ ቅኔዎቻቸው ሲጋደሉ ለኖሩት ሊቁ መጋቤ ምስጢር ቅኔዎች ማሳያነት ብሎጉዋን በመፍቀዳችሁ፣ደስ አለኝ!!አይ ሊቁ!!አያልቅባቸው!!የሲመቱ ዕለት እለተ – ተ/ሃይማኖት ጋር ማለትም በ24 መዋሉን አስተውለው ምስጢሩን እያዋሀዱ እንደጾም ብፌ ይደረድሩታል!!አይ ስጦታ!!ሁላችሁንም ያኑራችሁማ!!
  እንዲህ በአደባባይ ስለአባቶቻችን ነውር ሳይሆን ስለክብራቸው፣ስለግብራቸው፣ስለ መልካም ንግግሮቻቸውና ምዕዳኖቻቸው ሳነብ ደስ ይለኛል!! እጉዋለማውታ፣ደሀአደግ የመሆን ስሜት አይሰማኝም – ምርጥ ምርጥ አባቶችና ሊቃውንት እንዳሉን አውቃለሁዋ!!
  አምላከ ተ/ሃይማኖት ያረፉትን በዓጸደገነት ያኑርልን፣ያሉትን አፋቅሮ ለመንጋው እውነተኛ እረኛ በመሆን ሐዋርያዊ ተልእኮአቸውን እንዲወጡ እግዚአብሄር መንፈስቅዱስ ያበርታልን!!እኛንም አባቶቹን አሳዝኖ ወደመቃብር የሚያወርድ ትውልድ ከመሆን ይሰውረን!!
  ሐራዎች እንዲህ ሠናይ ዜና ማቅረብንም አስለምዱን እስኪ!!ለቤ/ክ ቀናኢ መሆናች ሳያንስ ቅኝታችሁን ተስፋ በሚያስቆርጡ ዜናዎች ላይ ብቻ ማድረጋችሁ ሁሌ ቅር ይለኛል!!ማዘወትር ቢያቅታችሁ አንዳንዴ እንኩዋ ደግ ዜናዎችን ጣል አድርጉ!!ወቀሳ ብቻ መናገር አያንጽም!!ተአማኒነትም ያሳጣል!!
  ለዚች ዘገባችሁ ግን ደግሜ ላመስግን!!

 2. Anonymous March 12, 2014 at 7:13 am Reply

  ለቅኔዉ
  ይበል ብለናል

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: