ፓትርያርኩ ለአማካሪነት ባስጠጓቸው አካላት ማንነት ተተቹ

 • የአመራርና የውሳኔ ሰጭነት አቅማቸው አጠያያቂ ኾኗል

(ፋክት፤ ቅጽ ፪ ቁጥር ፴፮ የካቲት ፳፻፮ ዓ.ም.)

his grace abune elsae

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ
የሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ከዓመት በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፮ው ፓትርያርክ ኾነው የተመረጡበት አንደኛ ዓመት በዓለ ሢመት፣ የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. የተከበረላቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ከሚታወቀው አስተዳደራዊ መዋቅር ውጭ ለአማካሪነት አቅርበዋቸዋል በተባሉ አካላትና ግለሰቦች ማንነት ሳቢያ በአንድ የቅዱስ ሲኖዶሱ አባል ትችት ተሰነዘረባቸው፡፡

የፓትርያርኩ የመጀመሪያ ዓመት በዓለ ሢመት በተከበረበት ዕለት ማምሻውን፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በተዘጋጀ የራት መርሐ ግብር ላይ ትምህርት እንዲሰጡ የተጋበዙት የሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ‹‹እርስዎ ከማን ጋር ወርደው ነው እየተማከሩ ያሉት?›› ሲሉ ፓትርያርኩን መጠየቃቸውና የምክር ቃል መለገሣቸው ታውቋል፡፡

በኤጲስ ቆጶስነት ሹመት ዘመነኛቸውና ቀራቢ ወንድማቸው መኾናቸውን ያወሱት አቡነ ኤልሳዕ፣ አቡነ ማትያስ ከረዥም ጊዜ የውጭው ዓለም ቆይታና አገልግሎት በኋላ ለፕትርክና ክብር መብቃታቸው በይበልጥ እርሳቸውን ደስ እንደሚያሰኛቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹አንድ ፓትርያርክ ከማን ጋር ነው ምክሩ?›› በማለት ወንድማዊ ነው ያሉትን ምክራቸውን የቀጠሉት ሊቀ ጳጳሱ፣ አቡነ ማትያስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመምራት የተቀበሉትን ታላቅ ሓላፊነት ከቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊና ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋራ በቅርበት እየተመካከሩ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው፣ ከዚያም ሲያልፍ ከቋሚ ሲኖዶስና አስፈላጊ ከኾነም የቅ/ሲኖዶሱን ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት መምክር እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡

‹‹ምክርዎት ከሌላ ጋር ከኾነ በጣም አስቸጋሪ ይኾናል›› ሲሉ ያሳሰቡት አቡነ ኤልሳዕ፣ ፓትርያርኩ መዋቅሩንና ደረጃቸውን ጠብቀው ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ ከመምከራቸውም ባሻገር በአመራራቸውና ውሳኔያቸው ላይ ተጽዕኖ እያሳረፈ ነው የሚባለውን የጎሰኝነት ከበባም የሚያመለክት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የፓትርያርኩ በዓለ ሢመት የተከበረበት ዕለት የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መታሰቢያ መኾኑን ያዘከሩት አቡነ ኤልሳዕ፣ ኢትዮጵያዊው ሐዋርያ ከውጭ ከመጡት ሌላው ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጋር በመላው ሀገሪቱ እየተዘዋወሩ ሲያገልግሉት ‹‹ከየት መጣኽ አልተባባሉም፤ ዘር ጎጥ አልተጠያየቁም፤ ቅዱስነትዎም ከሥራ ጓደኞችዎ ጋራ ከየት መጣኽ ሳንባባል በአንድነት እየተመካከርን ነው ማገልገል ያለብን፤ ከዚያ ወርደን መገኘት የለብንም፤›› በማለት ምክር አዘል ትምህርታቸውን አጠቃለዋል፡፡

የሊቀ ጳጳሱ ምክር አዘል ትምህርት ወቅታዊና ተገቢ መኾኑን ለፋክት የተናገሩ የበዓለ ሢመቱ ተሳታፊዎች፣ ፓትርያርኩ በአማካሪነት አቅርበዋቸዋል የሚባሉትን ግለሰቦች በስም በመጥቀስ÷ ቅዱስነታቸው በንግግር ከሚታወቁበት መልካም አስተዳደርን የማስፈን፣ ለሙስናና ብክነት የተጋለጡ ብልሹ አሠራሮችን በወሳኝ መልኩ የመቅረፍና የማድረቅ ጥረት ጋር የሚጣጣም ማንነት ጨርሶ እንደሌላቸው ያስረዳሉ፡፡ [ግለሰቦቹ በሓላፊነት በሠሩባቸው ቦታዎች የዘርና የመንደር ቡድን በማቋቋም በአቀባይና ተቀባይ (ኔትወርኪንግ) ባደራጇቸው ደላሎች የሙስና ገበያን በማጧጧፍ ቅጥር፣ ዕድገትና ፍትሕ ፈላጊውን አገልጋይና ሠራተኛ በከፍተኛ ደረጃ በማተራመስ፣ ሊቃውንቱን እየገፉ ከፍተኛ በደል በማድረስ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብቶችና ንብረቶች ለግል ጥቅም በማካበት የሚታወቁ ናቸው፡፡]

‹‹ሙሰኞችንና ጎሰኞችን ሰብስቦ ሙስናንና ጎሰኝነትን እታገላለኹ ማለት እንዴት ይቻላል?›› የሚሉት አስተያየት ሰጭዎቹ፣ ፓትርያርኩ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ አካል የኾነውን የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሥልጣን እስከ መጋፋት መድረሳቸውን በመጥቀስ ይህም ከግለሰቦቹ የኡለታዊ ምክር ተጽዕኖ ጋር የተያያዘ ሊኾን እንደሚችል ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል፡፡

ፓትርያርኩ ችግር መኖሩን እንጂ የችግሩ ፈጣሪዎች ተንኮል ምን እንደኾነ በትክክል ለመረዳትና ለማስረዳት ሲቸገሩ እንደሚስተዋል አስተያየት ሰጭዎቹ ይናገራሉ፡፡ ከወራት በፊት የእርምትና የማስተካከያ ርምጃ ለመውሰድ ‹‹እጅግ አስቸኳይ›› በሚል አቡነ ማትያስ ሲጠቀሙባቸው የቆዩ አነሣሽ ቃላት አኹን አኹን እየተዘነጉ የለውጥ እንቅስቃሴውን ለመምራትና ለማጠናከር የሚጣጣሩ ጳጳሳትና ባለሞያዎች በአማካሪነት ከተጠጉት ግለሰቦች ጋራ በተሳሰሩ የለውጡ ተቃዋሚዎች በፓትርያርኩ ፊት በግልጽ የሚዘለፉበት ኹኔታ መኖሩ ተጠቁሟል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ የተቋማዊ ለውጥ ጥረቶች የፓትርያርኩን የላቀ የአመራር ክህሎትና የውሳኔ ሰጭነት አቅም የሚጠይቁ እንደኾኑ የጠቁሙት ምንጮቹ፣ ከጽናትና አረዳድ አኳያ ይታይባቸዋል በሚባለው በተፈላጊው አቋም ያለመርጋትና የአቅም ውስንነት፣ ሊቃነ ጳጳሳቱና የመንግሥትም አካላት ጭምር ጥያቄ ማንሣት መጀመራቸው አያይዘው ገልጸዋል፡፡ የሊቀ ጳጳሱ አቡነ ኤልሳዕም ያልተጠበቀ ግልጽ ምክር ከዚህ ጥርጣሬ ሊመነጭ እንደሚችልና በቀጣይም የቅ/ሲኖዶሱ መነጋገርያ ሳይኾን እንደማይቀር በአስተያየት ሰጭዎቹ ተመልክቷል፡፡

Advertisements

7 thoughts on “ፓትርያርኩ ለአማካሪነት ባስጠጓቸው አካላት ማንነት ተተቹ

 1. Anonymous March 9, 2014 at 3:19 pm Reply

  Peter@dire.com ያልታደለ ምዕመን፣ ያልታደለ ትውልድ፣ ያልታደለች ሀገር….
  ፓትርያርኩ የቤተ ክርስቲያኒቷን አስተዳደር የማሻሻል አቋሜ ‹‹አልተበረዘም፤ አልተከለሰም›› ማለታቸው እኮ እራሳቸውን ለማሰተዋወቅ ያህል ያለፈ የተግባር ሥራ እንዳልሆነ አሁን አሁን እውነት እየሆነ እየመጣ ይገኛል፡፡ ባይሆንማ ኖር ለምን ገና ከሞሾማቸው የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ጥሰው ለሙሰኞች ቤተክርስቲያኒቷን አሳልፈው ሰጡ? የድሬደዋው ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ ህንጻ ስራ በሙሰኞች ተዘርፏልና ቅዱስ ሲኖዶስ ሂሳቡ ይጣራ፣ ይመርመር ብሎ የወሰነው ውሳኔ እኮ በሳምንቱ ነው ያለ ቅድመ ሁኔታ በራሳቸው ስልጣን በአንድ ገጽ ደብዳቤ ሽረው ምርመራውን እንዲቋረጥ የወሰኑት፣ ሌላው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚታየውን ብልሹ አሰራር እና ሙስና እንዲጠፋ የሚሟገቱትን ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን ከሙሰኞች፣ ከተሃድሶዎች ጋር አብረው ሲወቅሱ፣ ከማገዝ ይልቅ ስራቸውን ሲያደናቅፉ በግልጥ ታይቷል፣ እየታየም ነው፡፡
  ጎሰኝነትንስ እዋጋለሁ የሚሉትም እኮ ገና ከጅምራቸው በአዲስ አበባ አድባራት የጎሳ ‹‹መሳዮቻቸውን›› ያለ ስልጣናቸው እየሰገሰጉ ነው…. ብዙ መዘርዘር ይቻላል…፡፡
  ግን ለእኚህ አባት እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን እንዲባርክላቸው፣ መንጋውን በአግባቡ እንዲጠብቁት በጽኑ እንመኛለን፡፡ ይህን ኃላፊነታችን ግን በአግባቡ ከብፁአን አባቶች ጋር በህብረት በአንድ ቃል … የማይወጡት ከሆነ እምነታችንን፣ ቤተክርስቲያናችንን፣… ከተሀድሶ መናፍቃን፣ ከሙሰኞች፣ ከአረማውያን ‹‹ካድሬዎች›› …. የመጠበቅ የሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ምዕመን የውዴታ ግደታችን ነው፡፡
  ላቆብ ብዬ ሌላ አንዱን ሃሳቤን እንድገልጥ ውስጤን አስገደደኝ፤ እኚህ አባታ 45 ሚሊኖን ተከታይ ምዕመናንን የመምራት፣ የማስተዳደር… አቅማቸውስ ምን ያህል ነው? ብዙዎች እኮ ገና ከጅምሩ በስራቸው በጣም ግራ እየተጋቡ ከአጠገባቸው መሸሽ ጀምረዋል፣ በአንድ ‹‹የካድሬ›› የስልክ መልዕክት በርግጎ ይህንን ሁሉ ውርጅብኚ በመረጣቸው ምዕመን ላይ ማውረድስ ምን ይሉታል፣ የመረጣቸው እኮ ኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ምዕመኑ እንጂ የፌዴሬሽኑ አቶ ‹‹…›› አይደለም ግን እኚህ አባት ይህንን እንኳን መገንዘብ፣ ማገናዘብ አልቻሉም፤ በአጠቃላይ ይህችን ቀጥተኛ፣ ቅድስት፣ ጥንታዊ፣… ቤተክርስቲያን የማስተዳደር ብቃታቸው ፍጹም አጠራጣሪ፣ አስፈሪ ነው፡፡ ያልታደለ ምዕመን፣ ያልታደለ ትውልድ፣ ያልታደለች ሀገር….

 2. kasa March 10, 2014 at 6:51 am Reply

  [ግለሰቦቹ በሓላፊነት በሠሩባቸው ቦታዎች የዘርና የመንደር ቡድን በማቋቋም በአቀባይና ተቀባይ (ኔትወርኪንግ) ባደራጇቸው ደላሎች የሙስና ገበያን በማጧጧፍ ቅጥር፣ ዕድገትና ፍትሕ ፈላጊውን አገልጋይና ሠራተኛ በከፍተኛ ደረጃ በማተራመስ፣ ሊቃውንቱን እየገፉ ከፍተኛ በደል በማድረስ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብቶችና ንብረቶች ለግል ጥቅም በማካበት የሚታወቁ ናቸው፡፡]
  ‹‹ሙሰኞችንና ጎሰኞችን ሰብስቦ ሙስናንና ጎሰኝነትን እታገላለኹ ማለት እንዴት ይቻላል?››

 3. Anonymous March 11, 2014 at 5:49 am Reply

  ከእናንተ ማኅበር ከማኅበረ ቅዱሳን የበለጠ ሙሰኛ እና ዘረኛ ከቶ በቤተክርስቲያኒቱ አለ ወይ? እናንተ ስትጠፉ ሙስናና ዘረኝነትም አብሮ ይጠፋል።

  • Anonymous March 12, 2014 at 10:04 am Reply

   I know who are you?

   • Anonymous March 17, 2014 at 11:13 am

    we also know who u r??no more blind support 4 mk, we shall see it critically in light of the interest of our Holy EOTC. mk and EOTC r not synonyms.

 4. Anonymous March 13, 2014 at 2:40 pm Reply

  [ግለሰቦቹ በሓላፊነት በሠሩባቸው ቦታዎች የዘርና የመንደር ቡድን በማቋቋም በአቀባይና ተቀባይ (ኔትወርኪንግ) ባደራጇቸው ደላሎች የሙስና ገበያን በማጧጧፍ ቅጥር፣ ዕድገትና ፍትሕ ፈላጊውን አገልጋይና ሠራተኛ በከፍተኛ ደረጃ በማተራመስ፣ ሊቃውንቱን እየገፉ ከፍተኛ በደል በማድረስ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብቶችና ንብረቶች ለግል ጥቅም በማካበት የሚታወቁ ናቸው፡፡]
  ‹‹ሙሰኞችንና ጎሰኞችን ሰብስቦ ሙስናንና ጎሰኝነትን እታገላለኹ ማለት እንዴት ይቻላል?››

 5. Anonymous March 26, 2014 at 11:12 am Reply

  የአብርሃም አምላክ የይስሃቅ አምላክ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሄር ይቅር ይበለን፤ ቤተክርስቲያናችንና ሃገራችንን ይጠብቅልን!!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: