በብሩህ ተስፋና በሰላም የታጀበ በዓለ ሢመት – የጎሰኝነትና የሙስና አሜከላን መንቀል እንጀምር!

Zena Betekirstian Logo

 • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ዓላማ ከምኞትና ከተስፋ አልፎ ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ ሊቃውንት፣ ካህናትና ምእመናን ተባብረው ለተግባራዊነቱ መሰለፍ ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ከኹሉ በላይ ግን የብፁዓን አባቶች ሓላፊነት የገዘፈ ኾኖ ሲገኝ ነው፡፡
 • የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መዳከም የሚጎዳው እኛ አገልጋዮቿንና ምእመኖቿን ብቻ አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያን መድከም የኢትዮጵያ መዳከም ጭምር ነው፤ የሀገራችን የህልውና መሠረት የተጣለው በዚኽች ቤተ ክርስቲያን ላይ ነውና፡፡

(ዜና ቤተ ክርስቲያን፤ ፷፪ ዓመት ቁጥር ፷፫፤ የካቲት ፳፻፮ ዓ.ም.)

Enthronment of His Holiness Abune Mathias

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ይህችን ታላቅ፣ ብሔራዊት፣ ጥንታዊትና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን ለመምራት በእግዚአብሔር ፈቃድ ተመርጠው በፓትርያርክነት መንበር ከተቀመጡ እነኾ አንድ ዓመት ኾነ፡፡

ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በፊት የነበሩ አምስት ቅዱሳን አባቶች እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የኾነ ሀብተ ጸጋና መለያ ጠባይ ነበራቸው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስም የራሳቸው የኾነ መለያና መገለጫ ኹነቶች ይዘው ነው የመጡት፡፡

ቅዱስነታቸው በዚኽ ታላቅ መንበር ከቆዩበት ጊዜ አንጻር ስለ እርሳቸው ብዙ ለማለት ጊዜው ገና ቢመስልም ከሕይወት ታሪካቸው፣ ከረዥም ጊዜ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎታቸው፣ ከኹሉም በላይ ካለፈው አንድ ዓመት እንቅስቃሴያቸው በመነሣት ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን የሰላም፣ የፍቅርና የፍትሕ ሰው መኾናቸውን በርግጠኝነት መመስከር ይቻላል፡፡

የሌላውን ኹሉ ትተን ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ግቢ እየነፈሰ ያለው ሰላማዊ አየር፣ የተረጋጋ የሥራ መንገሥና ግርግር አልባ እንቅስቃሴ ላስተዋለ የቅዱስነታቸው ሕይወት በሰላምና በፍቅር የታጀበ መኾኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ እንዲያውም ያለፈው አንድ ዓመት የቅዱስነታቸው የፕትርክና ዘመን መለስ ብለን ለማስተዋል ስንሞክር በትንቢተ ኢሳይያስ፡-

‹‹ለድኾች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፣ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ ለተማረኩትም ነጻነትን፣ ለታሰሩትም መፈታትን፣ ለዕውራንም ማየትን እናገር ዘንድ ልኮኛል፡፡ የተወደደችውን የእግዚአብሔርንም ዓመት የተመረጠች ብዬ እጠራት ዘንድ፣ አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ፣ የሚያለቅሱትንም ኹሉ አጽናና ዘንድ፣ በዐመፅም ፈንታ አክሊልን፣ በልቅሶም ፈንታ የደስታ ዘይትን፣ በሐዘንም መንፈስ ፈንታ የምስጋና መጎናጸፊያ እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል፡፡›› (ት.ኢሳ.፷፩÷ ፩ – ፫)

ተብሎ የተጠቀሰውን ኃይለ ቃል ከቅዱስነታቸው ሢመት ጋራ የተሳሰረ ምሥጢር ያለው ኾኖ ይገኛል፡፡

የትምህርት፣ የሥነ ጥበብና የተግባረ እድ ማእከል፣ የመልካም አስተዳደር ሥርዐት በር ከፋች፣ ለተቸገሩ መማጠኛ ከተማ ኾና ለዘመናት የኖረችው ለሀገራችን የበረከት ምንጭ ጋሻና ጥላ ኾና የቆየችው ቤተ ክርስቲያናችን ያለፈ ክብርዋንና ስምዋን በሚያጎድፉ እንደ ሙስና፣ ዘረኝነትና አድልዎ በመሳሰሉ ጎጂ ገጽታዎች እየታመሰች ባለችበት የፈተና ወቅት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለዚኽ ታላቅ በዓለ ሢመት መብቃት ለቤተ ክርስቲያናችን ብሥራት ይዞ የመጣ የተስፋና የሰላም ምልክት ነው የምንለውም ለዚኹ ነው፡፡

በተግባር እያየነውና እያስተዋልነው እንዳለውም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባለፈው አንድ ዓመት ትልቅ ትኩረት ከሰጧቸው የሥራ ዘርፎች መካከል የሙስናንና የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶች ከቤተ ክርስቲያናችን በሚወገዱበት ዙሪያ ያነጣጠሩ ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ባስተላለፏቸው ቃለ ምዕዳኖቻቸውም በእነዚኽ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው አባታዊ መልእክቶቻቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ለአብነት ያህል ሰኔ ፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ብፁዕ አቡነ ማትያስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ኾነው መመረጣቸውን ምክንያት በማድረግ በስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተደረገው የትውውቅ መርሐ ግብር ቅዱስነታቸው፡-

‹‹የዚኽች ቤተ ክርስቲያን ልጆችና አገልጋዮች የኾን ኹላችን ከቤተ ክርስቲያን ባሕርይ የማይስማሙትን እንደ ሙስና፣ ዘረኝነትና አድልዎ የመሳሰሉ መንፈሳዊ መንገዳችንን የሚያበላሹብን አሠራሮችን በማስወገድ እውነተኝነት፣ ሐቀኝነት፣ ሓላፊነትና ተጠያቂነት የሕግ የበላይነት የሰፈነበት አሠራር ልንከተል ይገባል፤ መለያዎቻችንና ገንዘባችን እነዚኽ ናቸውና፡፡ አለበለዚያ እኛ አልጫ ከኾን ምእመናን በምን ይጣፍጣሉ? ማንስ ቀናውንና የእግዚአብሔር መንገድ ያሳያቸው?››

በማለት ያስተላለፉትን አባታዊ መመሪያ ማስታወስ ይቻላል፡፡

በቅርቡም በ፴፪ው በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ባስተላለፉት ቃለ በረከት፡-

‹‹ለመልካም አስተዳደር መስፈን ምዕራፍ ከፋች በኾነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ ልናደርገው የሚገባንን ምግባረ ሠናይ ኹሉ በመፈጸምና በማስፈጸም ለቤተ ክርስቲያን ያለንን ደጀንነት በተግባር መግለጽ ይጠበቅብናል፡፡››

በማለት መሪ ቃል ቅዱስነታቸው በቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ የሚታዩ ጉድለቶችን ለማስወገድ ቁርጠኛ አቋም መያዛቸውን የሚያመለክት ነው፡፡

ይህ የተቀደሰ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ዓላማ ከምኞትና ከተስፋ አልፎ ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናትና ምእመናን ተባብረው ለተግባራዊነቱ መሰለፍ ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ከኹሉ በላይ ግን የብፁዓን አባቶች ሓላፊነት የገዘፈ ኾኖ ሲገኝ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንዳዘዘውና ቀደምት አባቶች እንዳቆዩት ሥርዐት የካህናት ርስታቸውና ሀብታቸው እግዚአብሔር ብቻ ነው (ዘዳግ.፲፰÷፪)፡፡

ሐዋርያት ፈተና በበዛበት የጭንቅ ሰዓት ወንጌልን ለዓለም ያዳረሱት በሕዝቡ ዘንድ መወደድን፣ መታመንና መታፈርን ያገኙት አንድ ቤተሰብ ኾነው በቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ማኅበር በመጸለያቸውና ገንዘባቸውን የአንድነታቸው ማጠናከሪያ፣ የሃይማኖት ማስፋፊያ በማድረጋቸው ነው፡፡

አኹንም አልፎ አልፎ ድክመት የሚታይባቸው ካህናት ያለፈ ስሕተታቸውን በማረም በሙስና ያደፈውን የቤተ ክርስቲያናችን ስም ለማንጻት፣ በዘርና በወንዝ ልጅነት የደበዘዘ የብርሃን ጸዳልዋን መልሶ ለማብራት በተጀመረው እንቅስቃሴ በፊታወራሪነት ሊሰለፉ ይገባል፡፡ አለበለዚያማ ቅዱስነታቸው እንዳሉት እኛ አልጫ ኾነን ምእመናንን ማጣፈጥ አይቻለንምና፡፡ ኹላችን ልንገነዘበው የሚገባን ሌላው ቁም ነገር አለ፡፡ ይኸውም መጽሐፍ፡-

‹‹ያልደከማችኹበትን እንድታጭዱ ላክኋችኹ፣

ሌሎች ደከሙ፣ እናንተም በድካማቸው ገባችኹ›› (ዮሐ. ፬÷፴፰)

እንዳለ እኛ እየተመገብነው ያለነው ቀደምት አበው ዘርተው፣ አጭደው ጎተራ ሙሉ አስቀምጠውልን የሔዱትን ነው፡፡

አኹን አኹን በቤተ ክርስቲያናችን ችግሮች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት አባቶቻችን በተዉልን ስንቅ ላይ የራሳችን መጨመር ሳንችል በመቅረታችን ስንቁ አልቆ የወንጌል ሞሰቡና ሌማቱ ቃለ እግዚአብሔር መጠማት በመጀመሩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መዳከም የሚጎዳው እኛ አገልጋዮቿንና ምእመኖቿን ብቻ አይደለም፡፡ የዚኽች ቤተ ክርስቲያን መድከም የኢትዮጵያ መዳከም ጭምር ነው፤ የሀገራችን የህልውና መሠረት የተጣለው በዚኽች ቤተ ክርስቲያን ላይ ነውና፡፡

ስለዚኽ ኹላችንም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚደረገው እንቅስቃሴ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ በሰላም ተባብረን በውስጣችን ማቆጥቆጥ የጀመረው የጎሰኝነትና የሙስና አሜከላን መንቀል እንጀምር፡፡ የቅዱስ ፓትርያርኩ ብሩህ ራዕይ የሚሳካውም ይኼኔ ነው፡፡

Advertisements

2 thoughts on “በብሩህ ተስፋና በሰላም የታጀበ በዓለ ሢመት – የጎሰኝነትና የሙስና አሜከላን መንቀል እንጀምር!

 1. በአማን ነጸረ March 4, 2014 at 9:01 am Reply

  1. ይበል!!እንዲህ ነው ጽሁፍ!!እሰይ ዜና ቤተክርስቲያን!!ሰውን ሳይሆን ኃጢአትን ዘልፎ መናገር አስተምሩልንማ!!ያውም በቅዱሳት መጻህፍት ንባብና ትርጉዋሜ በማጀብ!!ባጭር ገጽ መባል የሚገባውን ሁሉ ብላችሁዋል!!ተስፋችንን ሳትገድሉ ያለውን ድክመት አሳይታችሁናል!!መቀረፍ ያለበትን እንከን ያለደረቅ ውንጀላ ነግራችሁናል!!አበሳውን እንደሌሎች እኛና እነሱ እያላችሁ ሳይሆን እኛ በሚል ስሜት ተጋርታችሁናል!!ደስ አለኝ!!በተግሳጽና በውንጀላ ዘገባ መሀል ያለውን ልዩነት ስላሳያችሁን!!ለዚህስ አይደል እውነተኛ የቤ/ክ ድምጽ የምላችሁ!!
  2. እናንተ ዕንቁዎች…በተለይ የቅኔው መዝገብ መ/ምስጢር ወልደሩፋኤል ፈታሂ ያኑርዎት ከማለት በቀር ምንም አልልም!!ምን ያህል እንደምወድዎትና እንደማከብርዎት ልቤን ገልጨ ባሳይ ደስ ባለኝ!!ለዛው፣ምስጢሩ፣ቅንነቱ፣ለሊቃውንት መቆርቆሩ፣ለህገ ቤ/ክ ልእልና ባፍም በመጣፍም መሙዋገቱ ተሰጥቶዎታል!!ብቻ እጸልያለሁ… አለቃ ዘነብ ኢትዮጵያዊ እንደሚሉት ….እግዚአብሄር እስቲሻር ሚካኤል እስኪሞት እንዲያኖርዎት!!
  3. ምናለ ታዲያ ዜና ቤተክርስቲያን እንዲህ ወቅት እየጠበቀች ብቻ የምታንጸባርቅ ሳትሆን በየጊዜው ያለውን የቤ/ክ እንቅስቃሴ በስማበለው በየኢንተርኔቱ ከምንሰማ ተጠናክራ ወቅታዊ መረጃ በመስጠት የቤ/ክ ድምጽ ብትሆን!!እባካችሁ ቢያንስ ይቺ ጋዜጣ ዌብሳይት ይኑራት!!እንደው ፓትርያርኩም ሆነ ጠ/ቤ/ክህነቱ በደንብ የተደራጀ የህዝብ ግንኙነት ቢኖራቸው መልካም ነው!!
  4. እውነት ለመናገር እንደቤተክህነት ሚዲያ ላይ ምንም እየተሰራ አይደለም!! አስቡበት!!አጀንዳቸው በልዩ ልዩ የቡድን ፍላጎት የተተበተበ ሚዲያዎች የልባችንን እያደረሱት አይደለም!!የሚሰብኩት ወንጌልን ሳይሆን ረሳቸውን እየሆነ ስለመጣ ብዙ ቅር እያለን ነው!!አባቶች እባካችሁ አስቡበት!!እንደተቁዋም ጠንካራ ሚዲያ ይኑረን!!ያለው ኦፊሻል የቤተክርስቲያኑዋ ዌብሳይትም እንደገና በደንብ ሆኖ ተሸሽሎ መሰራትና ቶሎ ቶሎ አፕዴት እንዲደረግ በቂ የሰው ሀይል መድቡለት!!
  5. አንዳንዶች ራሳቸውን በሚዲያቸው ሲሸጡ ቆይተው ዛሬ እኛ ከሌለን አለቀላችሁ እያሉ እያስቀየሙን ነው!!አንድም ልሳን ኖሩዋቸው ለብዙ ሰው መድረሳቸው ባመጣው መታበይ!!በሌላም በኩል እናንተ ከማህሌትና ከቅኔ ዘረፋው በተጉዋዳኝ ራሳችሁን ለህዝቡ ስላላሳያችሁ!!ብታሳዩም በራሳችሁ መድረክ ሳይሆን የሌሎች አዳማቂ በመሆን ስለሆነ!!እንደባለቤት ሳይሆን እንደእንግዳ!!ስለዚህ የራሳችሁ መድረክ ይመቻችና ወደ አደባባዩ ውጡ!!ስንት ሊቃውንት ያሉዋት ቤ/ክ በየአመትበአሉ በየዶክመንተሪው በሚዲያ እሱዋን ወክለው የሚናገሩት እነ ዲያቆን እከሌ ብቻ መሆናቸው ምዕመኑን ሊቃውንት እንደሌሉት አስመስሎ የተሳሳተ መልእክት እያስተላለፈ ነው!!
  6. ስለዚህ ውጡ በአደባባይ!!እናንተ ተናገሩ እኛ እንሰማለን!!ያኔ በምዕመን ስም ካህኑን ለማሸማቀቅ የሚሞክሩ ብልጣብልጦችም ልብ ይገዛሉ!!እውነተኛው የካህናትና ምዕመናን ለዘመናት የዘለቀ በሰበካ ጉባኤ፣በማህበር፣በሰንበቴ፣በልማት ኮሚቴ፣በሰንበት ትምህርት ቤት….የተገመደ የአንድነትና የፍቅር ገመድ እንዳልተበጠሰ እና በቤ/ክ ማንም ባይተዋር እንደሌለ ሁሉም ይረዳል!! ብቻ ተናገሩ!!አሁን ድልድይ የለንም!!ድልድዩ አውደምህረቱ ነው!!ካህኑን ከምእመን ያገናኛል ያልነው ድልድይ ወዲህ ለካህናት፣ወዲያ ለምእመናን የሚያወራው ተላያይቶአል!!እሱ ራሱን ጠገነም አልጠገነም አሁን ወደ መድረክ የመውጫችሁ ጊዜ ነው!!በፍጥነት….ወደ ምእመኑ ድረሱ!!
  መኃትዊሀ ለቤ/ክ የተባላችሁ ሊቃውንት ስለእናንተ ስናገር ልቤ ይሞቃል!!ያቆያችሁ!!

 2. Habtie March 6, 2014 at 12:47 pm Reply

  Hey beaman nestere please don’t blame others. see yourself!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: