የገንዘብና የሰው ሀብት አስተዳደር ጥያቄ ለቤተ ክርስቲያን

(ሐመር፤ ፳፩ ቁጥር ፲፤ የካቲት ፳፻፮)

ዳዊት አብርሃም

የካቲት ፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተቋማዊ ለውጥ አመራር የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ተጠናቅቆ ርክክብ ተካሒዷል፡፡ የጥናቱን አጠቃላይ ሒደትና ወደፊት ሊገጥመው የሚችለውን ተግዳሮት ከትንታኔ ጋራ ይዘን ቀርበናል፡

*                        *                       *

Hamer Magazine on change mgt

የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የሠለጠነ ሊኾን ይገባዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን የተንሰራፋው ሙስናና ብልሹ አሠራር እንዲሁም የሥነ ምግባር ውድቀት ወደ ከፋ የንቅዘት ደረጃ ደርሷልና ሊገታ ይገባዋል የሚሉ ጥሪዎች መሰማት ከጀመሩ ዓመታት ነጎዱ፡፡ የብልሽቱ ስፋትና ጥልቀት፣ የሙስናው ውስብስብነትና የመሪዎች ቸልተኝነት እንዲሁም የታወቀውን ችግር ለመፍታት ከመሪዎች የሚጠበቀው ቁርጠኝነት ዝቅተኛ መኾን የተረዳ እየኾነ ሲመጣ ምእመናን ጥሪያቸው ምላሽ ሊያገኝ የሚችልበት ዕድል ዝግ ኾኖ ስለታያቸው ተስፋቸውን ቆረጡ፤ መምህራኑም ‹‹ነባህነ ነባህነ ከመኢዘነባህነ ኮነ፤ አለቀስን አለቀስን ነገር ግን እንዳላለቀስን ኾን›› የሚለው የነቢዩ ሙሾ የዕለት ዜማቸው ኾነ፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት ግን ይህን የተቆረጠ ተስፋ የሚቀጥል ጭላንጭል ብልጭ በማለቱ ሐሳቦች ሁሉ ወደ አንድ ቦታ አትኩረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦት ወር ፳፻፭ ዓ.ም ባደረገው ዓመታዊ የርክበ ካህናት ጉባኤው የቤተ ክርስቲያን የአሠራርና የአደረጃጀት ለውጥ ጥናት ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንዲጀመር መመሪያ ሰጠ፡፡ ተልዕኮውን የተቀበለው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም በፍጥነት የባለሞያ ቡድን አቋቁሞ ወደ ተግባር ገባ፡፡

A.A Diosces Head Office

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት

በሀገረ ስብከቱ የተቋቋመው የባለሞያ ቡድን አባላት በዚህ ዓይነቱ ሥራ የዓመታት ልምድ ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ቤተ ክርስቲያንን በአገልግሎት ቀረብ ብለው ለማወቅ ዕድሉ የነበራቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ከዘመናዊው ትምህርት በተጨማሪ በአብነቱ መስክ እስከ ቅኔ የዘለቀ ትምህርት የሰነቁ እንዲም በስልጣነ ክህነቱም እስከ ቅስና የደረሱ ይገኙበታል፡፡ የታዘዙትን በጸጋ ተቀብለው ወደ ተግባር የሚወስዳቸውን የድርጊት መርሐ ግብርና የጊዜ ሰሌዳ በጊዜ ቀልሰው ሙሉ ትኵረታቸውን በመስጠት የተረባረቡት፤ በጥቂት ወራትም የሥራ ፍሬያቸውን ለቅዱስ ሲኖዶስ ለማቅረብ የቻሉት ይኸው ከቤተ ክርስቲያን ጋር በጥልቅ የተሳሰረ ሕይወታቸው ስለረዳቸው ይመስላል፡፡

የጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ የሆነው ታደሰ አሰፋ እርሱና የሥራ ባልደረቦቹ የሥራ ፍሬያቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ያቀረቡበትን ኹኔታ ሲያስታውስ ፈገግ ይላል፡፡ ‹‹ጥናቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ በቀርበ ጊዜ በጣም የተደሰቱት ብጹዓን አበው ለሰነዱ በጣም ሳሱለት፡፡ ሳይተገበር እንዳይቀር መጨነቅ የጀመሩትም ወዲያውኑ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ውይይት መክፈት የለውጡ ተቃዋሚ በሆኑ ሰዎች አተካራ ጊዜ እንዲባክን መፍቀድ ስለሆነ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረግ ጠይቀው ነበር›› ይላል፡፡ ‹‹እኛ ግን ሥራችን በአባቶች ፊት ሞገስ ስላገኘልን ብንደሰትም በሁሉም ባለ ድርሻ አካላት እንዲተችና እንዲዳብር ስለፈለግን ውይይቱ እንዲፈቀድ መጠየቅ ነበረብን፡፡ “ተቃውሞ ቢኖርም ከሚታፈን በጊዜ ወጥቶ ቢስተናገድ ይሻላል” ብለን ስላስረዳን ውይይቱ ተፈቅዶ መድረኮች ተመቻቹ፡፡››

የእንምከርበት መድረክ

A.A.D Parish churches discussion on change mgt.ሰነዱ ከመተግበሩ በፊት ረቂቁ ወደ ታች ወርዶ ለውይይት መቅረብ የለበትም የሚለው የአንዳንድ አባቶች ሐሳብ ከሥራ አመራር ሳይንሳዊ መርሆ አንጻር ካየነው ትክክል ነው፡፡ ማንኛውም አስተዳደራዊ የመዋቅር ማሻሻያ የሚመለከተው በታችኛው መዋቅር ሠራተኞች ሳይሆን የተቋሙን የበላይ አመራር ስለሆነ ሊተች የሚገባው በአንድ መንገድ ብቻ ነው – በመሪዎች ጉባኤ፡፡ ታደሰ አሰፋ ስለዚህ ጉዳይ ሲያስረዳ ‹‹ከበርካታ ድርጅቶች ጋር ባለኝ አብሮ የመሥራት ልምድ እንደማውቀው የመዋቅር ማሻሻያ ጥናት ለበታች ሠራተኞች ቀርቦ እንዲተች አይደረግም፡፡ የተለመደው አሠራር የጥናቱን ረቂቅ ለተቋሙ የበላይ መሪዎች ብቻ አቅርቦ በመሪዎች አስተያየት እንዲሰጥበት ማድረግ ነው፡፡ ሆኖም ዐዲሱ መዋቅር ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ ተበድለናል የሚሉ ሠራተኞች ካሉ ቅሬታቸውን እንዲያቀርቡ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ የትም ቦታ ላለ ተቋም የሚያገለግል የታወቀ አሠራር ነው፡፡››

አሠራሩ እንዲህ ከሆነ ታዲያ ለምን በዚሁ መንገድ አልተኬደም? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች አሉ፡፡ እንደነዚህ ሰዎች ከሆነ የሰነዱ ረቂቅ ለውይይት መቅረቡ ምንም ጥቅም የለውም፡፡ እንዲያውም ጊዜንና ገንዘብን የሚያባክን ከመሆኑም ሌላ ሙያዊውን ሥራ ሙያቸው ባልሆኑ ሰዎች እንዲገመገምና ተገቢነት የሌላቸው ሐሳቦች በሥራው ላይ ጫና እንዲፈጥሩ መፍቀድ ነው፡፡ ምክንያቱም ሙያዊው አማራጭ በግብታዊነት ከሚሰነዘሩ ሐሳቦች ጋር የመታረቅ ግዴታ ውስጥ ከገባ ሥራው የተሠራው ላጠቃላይ ተቋሙ ሆኖ ሳለ ወደ ግለሰባዊነት ደረጃ ሊወርድ፤ ብሎም ወደ ነባሩ የንቅዘት አዘቅት ሊገባ ይችላል፡፡ ስለዚህ ረቂቁ በታወቀውና ተቀባይነት ባለው አሠራር መሠረት በሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ታይቶ ቢስተካከልና የሠራተኞች ቅሬታ ጊዜውን ጠብቆ በቅሬታ ሰሚ በኩል እየተስተናገደ የሥርዓቱ ውሱንነት እየተሟላ ቢሄድ የተሻለ ነው ባይ ናቸው፡፡

ሆኖም ታደሰ ውይይቱን አልጠላውም፡፡ የጥናት ቡድኑ አባላት ከተለመደው አሠራር ወጣ ብለው ውይይቱ እንዲኖር የፈለጉበትን ምክንያት ሲያስረዳ ‹‹ለውጥ ሁሌም ቢሆን ተቃውሞ ይገጥመዋልና ጥናቱ በፍጥነት ተግባራዊ ሆኖ ከሚያስደነግጥ ወዲያውም የማናውቀው ነገር መጣብን አሰኝቶ ብዙ የተለፋበት ሰነድ ወደ ኋላ ከሚመለስ ከወዲሁ ቢተች አስፈላጊውንም ተግዳሮት በጊዜ ቢያልፍ የተሻለ እንደሚሆን የባለሙያ ቡድኑ አባላት ተስማምተንበታል፡፡ ለመስማማት ያበቃንም የቤተ ክርስቲያኒቱ ኹኔታ ከሌሎች ተቅዋማት ለየት ይላል የሚል መነሻ ምክንያታችን ነው፡፡ በኛ ቤተ ክርስቲያን ኹኔታ ውይይት ሳይካሄድ አንዳች ዓይነት ለውጥ ለመጫን መሞከር ይበልጥ አደገኛ ነው›› ይላል፡፡

ዜናውን በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ሲከታተሉ የነበሩ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ያሳዘነው ግን ሰነዱን እንቃወማለን የሚል አቋም ይዘው የመጡ ወገኖች ሐሳባቸውን በጨዋነት ከማስረዳት ይልቅ በአደባባይ በቅዱስ ፓትርያርኩ ፊት ጸያፍ የስድብ ቃላት መወርወራቸው ነው፡፡ ስድቡ ደግሞ ያነጣጠረው ሰነዱን ባዘጋጁትና ተሳዳቢዎቹ ከሰነዱ ጀርባ አለ ብለው ከሚያምኑት ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ነው፡፡ እንዲያውም ስብሰባው ሰነዱን ለመቃወም ሳይሆን ማኅበረ ቅዱሳንን ለማብጠልጠል የታለመ ይመስል ነበር፡፡

his grace abune estifanos

ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ ተናጋሪዎች ብጹዓን ሊቃነ ጰጳሳትን ሲዘልፉ በእውነቱ እነዚህ ሰዎች የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ናቸው? አሰኝቷል፡፡ በተለይ የስድቡ ዋነኛ ኢላማ የነበሩት የአዲስ አባባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተናጋሪዎች አንደበት ‹‹እዚያው ጅማቸው ይሂዱልን›› ተብለዋል፡፡ ብጹዕነታቸው በጅማ ሀገረ ስብከት ክርስቲያኖች ላይ በደረሰ ግፍ ብዙዎች ምእመናንና ካህናት ሰማዕትነት ሲቀበሉና አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ በነበረበት በዚያ የፈተና ጊዜ በነደደው እሳት መሀል ተገኝተው ሕዝቡን አጽናንተው አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹና ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲተገበሩ ያደረጉ በዚህም ተግባራቸው የቤተ ክርስቲያንን ቁስል የጠገኑ አገልጋይ ናቸው፡፡

ተሳዳቢዎቹ ግን ይህ አልታያቸውም፡፡ እንዲያውም ‹‹ደጆችሽ አይዘጉ ምንትስ ቅብጥርስ›› እያሉ ለቤተ ክርስቲያን የቆሙ የአገልግሎት ማኅበራትን አንኳስሰዋል፡፡ ‹‹እነዚህ ሰዎች በርግጥ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከሆኑ መልካሙ አገልግሎት ባይታያቸውና ሠራተኞችን ማድነቅ ባይሆንላቸው እንኳ ጅማ የሀገሪቷ አካልና የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድ ሀገረ ስብከት እንጂ የግዞት ስፍራ እንዳልሆነች እንዴት ዘነጉት?›› የሚለው የታዛቢዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ ከቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ፍጹም ባልጠበቁት በዚህ ጸያፍ ንግግር አዝነዋል፡፡ ‹‹ማንም ሰው የተሰማውንና የመሰለውን መናገር መብቱ ነው፡፡ ሆኖም መሳደብና የሰውን መብት በሚጋፋ መልኩ መናገር ተቀባይነት የለውም፡፡›› ሲሉም ገስጸዋል፡፡ ስድቡና ሌላው ባደባባይ የተሰማው ንግግር ያስቆጣው ቅዱስነታቸውን ብቻ አይደለም፡፡ ተቃውሞውን ተከትሎ ሌሎች ብዙዎች ካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮች ቅዱስ ፓትርያርኩ ፊት ቀርበው ለቤተ ክርስቲያን እድገትና መሻሻል የሚበጅ ነገር ሳይተገበር እንዳይቀር ተማጽነዋል፡፡ እግረ መንገዳቸውንም ቤተ ክርስተያኒቱ ያለባትን የአሠራርና የአስተዳደር ድክመት እንደ ምቹ አጋጣሚ ተጠቅመው ብዝበዛ ላይ የተሰማሩ ወገኖች በሚፈጥሩት ጫና ጅምር ሥራው እንዳይጨናገፍ ደጋግመው ከመጠየቅ ጋር በነርሱ በኩል የሚፈለገውን አገልግሎት ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን እየገለጹ ቃል ኪዳን ገብተዋል፡፡

ይህ ደግሞ አንድ ነገር መጠቆም ችሏል፡፡ በነባሩ የአሠራር ሥርዓት እንደ ልባቸው ይሆኑ የነበሩት ሰዎች ጥቂት እንደሆኑና ጩኸታቸው የብዙዎች መስሎ ቢያስጨንቅም ብዙኀኑ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥቅም ተብሎ የሚመጣውን ለውጥ የሚደግፍ መሆኑን ነው፡፡ በርግጥም ወይዘሮ ቅድስት የተባሉ የምእመናን ተወካይ በቅዱስ ፓትርያርኩና በብጹዓን አበው ፊት ቀርበው እንደገለጹት አሁን እየተሠራ ያለው ጥናት ‹‹የዘመናት የምእመናን ለቅሶ ምላሽ ነው፡፡››

የማኅበረ ቅዱሳን ነገር

ተቃውሞው በዋናነት ያነጣጠረው  ከሰነዱ ጀርባ ተደብቋል የሚል ቅድመ ግምት በተጣለበት ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ነበር፡፡ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ተስፋዬ ቢሆነኝ ስለጉዳዩ ተጠይቆ በተደጋጋሚ እንዳስረዳው ግን ማኅበሩ በጥናቱ ውስጥ እጁ የለበትም፡፡ ‹‹ምን አልባት የማኅበሩ አባላት የሆኑ ግለሰቦች በቡድኑ ውስጥ ቢገኙ ያጋጣሚ ጉዳይ እንጂ ማኅበሩ ስለወከላቸው አይደለም፤ ደግሞም የማኅበሩ አባላት በግላቸው ለቤተ ክርስተያን የሚሰጡት አገልግሎት የግል መብታቸው ስለሆነ ማኅበሩ የሚያዝበትና የሚቆጣጠረው አይደለም›› ብሏል፡፡

ታደሰ ‹‹እኔ የማኅበረ ቅዱሳን አባል ነኝ፡፡ የቡድኑ አባል የሆንኩት ግን ከማኅበሩ ጋር በተያያዘ ሳይሆን በምኖርበት አጥቢያ ባለኝ አገልግሎት እንዲሁም በሙያዬ ምክንያት ብቻ ነው፡፡ የሌሎቹም ምርጫ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡›› ካለ በኋላ ‹‹የሚያስገርመኝ ነገር ግን እኔ በግሌ በሠራሁት ሥራ አጥቢያዬ ወይም በመደበኛነት ተቀጥሬ የምሠራበት ድርጅት ስሙ ሳይነሳ በተደጋጋሚ የሚዘለፈው በአባልነት የማገለግልበት ማኅበር ብቻ መሆኑ ነው፡፡›› ብዙዎች እንደሚገልጹት ደግሞ ተቃዋሚዎቹ ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ማነጣጠራቸው ከዚህ ቀደም ማኅበሩ አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን በመቃወም ያበረከተውን ገንቢ አስተዋጽኦ ዛሬም ሙሰኞችን ለማንጠፍ በተዘጋጀው ሥርዓት አማካይነት እንዳይደግመው ቀድሞ ለማጠርና ለማሸማቀቅ ስለሆነ  በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ገለልተኛ እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸው ወገኖች የገለልተኝነት ሚናቸውን በረሱበት በዚህ ሰዓት የማኅበሩ ዝምታ በዝቷል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የተቋቋመው ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ስለሆነ በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ገለልተኛ አቋም የመያዝ መብት እንደሌለው የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ተስፋዬ ቢሆነኝ ይገልጻል፡ በአንጻሩም ‹‹የተሠራው የተቋማዊ መዋቅርና የአሠራር ሥርዓት ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ መደገፍ ግዴታው ነውና ማኅበረ ቅዱሳን ለሥርዓቱ ሙሉ ተግባራዊነት የበኩሉን ለማድረግ ዝግጁ ነው፡፡››

ለመኾኑ ነባሩ ሥርዓት ምን ችግር ኖሮበት ነው ለውጥ ያስፈለገው?

ጥናት ቡድኑ ሥራውን የጀመረው ነባሩን ሥርዓት በመፈተሽ ነው፡፡ ከቃለ ዓዋዲው በተጨማሪ በ፲፱፻፺፩ ዓ.ም እና በ፳፻፩ዓ.ም የወጡ ሕጎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በወቅቱ ፓትርያርክ (በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ) የወጣ ነው፡፡ እነዚህ ሕጎችና አጠቃላይ መዋቅሩ ሲፈተሽ ከዋና ዋና መለኪያዎች አንጻር የሚከተሉት ችግሮች ተገኝተውበታል፡፡

የመዋቅር የአደረጃጀትና የአሠራር ችግሮች፡-  በነባሩ አሠራር በቀላሉ ይተች የነበረው አንድ ነገር ታች ያሉ የመዋቅር አካላት ሊፈቱት የሚገባቸውን ትናንሽ ችግሮች ካለምንም ምክንያት እያዘለሉ ወደ ሊቀ ጳጳሱ አልፎም ወደ ፓትርያርኩ ማስተለለፋቸው ነው፡፡ ይህ ኹኔታ ባንድ በኩል ጊዜን ሲያባክን በሌላ በኩል ደግሞ ችግሮቹ ሳይፈቱ እንዲቀሩ ያደርጋል፡፡ እንዲያውም ያወሳስባቸዋል፡፡

የነባሩ ሥርዓት ሌላ ችግር ምእመናንን ማግለሉ ነው፡፡ ምእመናን በሥራው ውስጥ የባለቤትነት ስሜት ስለሌላቸው በየአጥቢያው ከፍ ያለ የሥነ ምግባር ዝቅጠት ሲታይና ዝርፊያ በግላጭ ሲካሔድ ከሀሜት ያለፈ ምንም ሳይጋፈጡ አይተው እንዳላዩ የሚሆኑ በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ባይተዋርነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ አማሳኞችም ከልካይ ቀረቶ ተመልካች አልነበረባቸውም፡፡

የውስጥ ችግሮች በሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት መፈታት እያቃታቸው ወደ ዓለማዊ ፍርድ ቤቶች መወሰዳቸው ሌላው የአሠራርና የአደረጃጀቱ ድክመት መገለጫ ነው፡፡ ይህ ኹኔታ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ መሆኑ በጥናቱ ታይቷል፡፡ ብዙዎችን ሲያስገርም የኖረው ሌላ ችግር ደግሞ በሙስናና በሌሎች የሥነ ምግባር ችግሮች ብዙ ቀውስ ያመጡ የገዳማትና የአድባራት አለቆችና ሠራተኞች የእርምት እርምጃ ሳይወሰድባቸው እንዲያውም እድገት አግኝተው ወደ ሌላ ቦታ መዛወራቸው ነው፡፡

የሰው ሀብት አስተዳደር ችግር፡- ገና ከጅምሩ ሠራተኛ ሲቀጠር የቅጥሩ አስፈላጊነት ተረጋግጦ የተለመደው የትምህርትና የልምድ ሁኔታ ከሚፈለገው የሥራ ዓይነት ጋር ተገናዝቦ አይደለም፡፡ አንድ ኃላፊ በማንኛውም ጊዜ የፈለገውን ሰው በፈለገው የደሞዝ መጠን ይቀጥራል፡፡ ትውውቅ፣ ዝምድናና ደጅ ጥናት ለመቀጠር በቂ መስፈርት የሆኑ እስኪመስል ድረስ በየጊዜው ሠራተኞች በዚህ ዓይነት መንገድ ይቀጠራሉ፡፡ እኩል ደረጃ ይዘው ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ አገልጋዮች የተለያየ ደሞዝ ይከፈላቸዋል፡፡ አጥቢያዎች ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይ ሠራተኖችን እንዲቀበሉ ሀገረ ስብከቱ አንዳንዴም መንበረ ፓትርያርኩ እያስገደደ ሠራተኞችን ይልክባቸዋል፤ በራሱ በአጥቢያው አስተዳደርም በግብታዊነት የሚቀጠሩ ሠራተኞች በርካቶች ናቸው ፡፡

በዚህ መልኩ የሚቀጠሩ አገልጋዮች የሥራ መዘርዝር የሌላቸው ሲሆን የተቀጠሩበትን የሥራ መስክ ለመሥራት የሚያስችል አነስተኛውን ክህሎት እስከማጣት ሲደርሱ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ በሌላ ቋንቋ ሳይሆን በአማርኛ ፊደላት አንድ መስመር መጻፍ የማይችሉ ዋና ጸሐፊዎችና ቁልቁል መደመር የማይችሉ ሒሳብ ሹሞች አሉ፡፡ በአንጻሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ተገቢውን ቦታ አያገኙም፤ ይገፋሉ፡፡ ከዚህ በተረፈ የአገልጋዮችን መብትና ጥቅም የሚያስጠብቅ ምንም ተጨማሪ ነገር የሌለ ሲሆን እንደ ጡረታ ያሉ የኑሮ ዋስትናዎች ጨርሶ የማይታሰቡ ሆነዋል፡፡

የሒሳብ አሠራርና የቁጥጥር ችግር፡-  የአድባራትና ገዳማት ዋና የገቢ ምንጭ የሆነው ሙዳየ ምጽዋት  ወጥነቱን በጠበቀ መልኩ ካለመሠራቱ በላይ ሲከፈትም ሆነ ገቢው ሲቆጠር የሚመለከታቸው አካላት ስለማይገኙ ለምዝበራ ተጋልጧል፡፡ አልፎ ተርፎም ያልተፈቀደ ሙዳየ ምጽዋት በድብቅ በማስገባት፣ ሐሰተኛ ደረሰኝ በማሳተምና በመሳሰለው ወንጀል ለመፈጸም ዕድሉ ክፍት ሆኗል፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ ለገጠር አብያተ ክርስቲያናት ዕርዳታ ለማሰባሰብና  የሙዚየም ግንባታን ለመደገፍ ተብሎ የሚሰበሰበው ገንዘብ ግልጽነትና ተጠያቂነት ለጎደለው የገንዘብ አያያዝ እንደ አብነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡

ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን ለሚሰጡት ስጦታ ደረሰኝ የመቀበል ልምድ ስለሌላቸው ይህን ክፍተት ለግል መጠቀሚያ ያደረጉ ወገኖች እንዲበራከቱ አግዟል፡፡ ደረሰኝ ሲጠየቁም በራሪውን ይሰጡና በቀሪው ላይ ያነሰ የገንዘብ መጠን ይመዘግባሉ፡፡ የውጪ ምንዛሪ በስጦታነት ሲመጣም በአብዛኛው የሚዘረፍ ሲሆን የሚመነዘረውም ብዙውን ጊዜ አግባብነት በሌለው ኹኔታ ነው፡፡

የሒሳብ አሠራሩ ዘመናዊ ካለመሆኑም በላይ ጊዜውን የጠበቀ ሪፖርት ለሚመለከታቸው አካላት አይቀርብም፡፡ የቁጥጥር ሥርዓቱ ሙያዊ በሆነ መልኩ አልተዘረጋም፡፡ ባለሙያ ያልሆኑ ሰዎች በኦዲተርነትና በሒሳብ ሹምነት መቀመጣቸው ጠንካራ ቁጥጥር እንዳይኖር በር የከፈተ ሲሆን  የቁጥጥር ሠራተኞች ኦዲት ቢያደርጉ እንኳ የገንዘብ ኦዲት ብቻ እንጂ የሥራ አፈጻጸም ኦዲት ከቶውንም የሚያስቡት አይደለም፡፡

ኦዲትና ኢንስፔክሽን እንደ ማሳያ

እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ የጥናት ቡድኑ ሰባት የመፍትሔ ሐሳቦችን የጠቆመ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የመጀመሪያ ተብሎ የተቀመጠው ዘመናዊና ሁሉን አቀፍ የሰለጠነ ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ በርካቶች ስለ ቤተ ክርስቲያን ችግር ሲነሳ መዋቅሩና የአሠራር ሥርዓቱ ድክመት ኖሮበት ሳይሆን በትክክል ስላልተሠራበት ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ ይህ አመለካከት እውነታነት ባያጣም ሙሉ በሙሉ ግን ትክክል እንዳልሆነ ባለሙያዎችን ያስማማል፡፡ በነባሩ ሥርዓት ውስጥ የነበሩ አንዳንድ መዋቅራዊ ኹኔታዎች  ሠራተኞች ወደ ጥፋት እንዲወድቁ የሚያስገድዱ ክፍተቶች እንዳሉባቸው ጥናቱ አሳይቷል፡፡

ለዚህ እንደምሳሌ የሚጠቅሰው በነባሩ መዋቅር ውስጥ የቁጥጥር አገልግሎት ተጠሪነቱ ለሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እንዲሆን መደረጉ ነው፡፡ የቁጥጥር ተግባር የሚመለከተው ሥራ አስኪያጁንም ጨምሮ እንደመሆኑ በሥራ አስኪያጁና በኦዲተሩ መካከል ከአስተዳደራዊ የጎንዮሽ ግንኙነት በዘለለ ቀጥተኛ የተጠሪነት ግንኙነት መኖር እንደሌለበት የሥራ አመራር ሳይንስ መርሆ ያስገድዳል፡፡ የቁጥጥር ሠራተኛ ለሥራ አስኪያጁ ተጠሪ ሆነ ማለት የሥራ ዋስትናው በሥራ አስኪያጁ የሚወሰን ሆነ ማለት ነው፡፡ ከሥራ ሊያባርረኝ ይችላል ብሎ እየሰጋ እንዴት ሊቆጣጠረው ይችላል? እንዲያውም ወንጀሉ እንዳይጋለጥ ተባብሮ መሥራቱ የማይቀር ይሆናል፡፡

በሚሻሻለው ሥርዓት ላይ ይህ ክፍተት አይኖርም፡፡ ኦዲትና አንስፔክሽን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ስለተደረገ ሥራ አስኪያጁን ብቻ ሳይሆን ለሊቀ ጳጳሱም የቁጥጥር ድጋፍ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ የኦዲተሩ ስልጣን ገደቡን እንዳይጥስ ሊቃነ ጳጳሳቱ በበኩላቸው በቅዱስ ሲኖዶስ አባልነታቸው ይቆጣጠሩታል፡፡ በዚህ መልክ የቁጥጥር ሥርዓቱ ትክክለኛ ሚዛኑን የጠበቀ ሆኖ ሲገነባ በሥራ አመራር ስልት ‹‹ቼክ ኤንድ ባላንስ›› የሚባለው መርሆ ቦታውን ያገኛል፡፡

የቁጥጥር ሥርዓቱ ከላይ ጀምሮ በዚህ መልክ ወደታች ይወርድና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሲደርስ የተለየ መልክ እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ይኸውም ከላይ ባሉት የመዋቅር አካላት በግለሰብ ባለሙያ የሚዋቀረው ክፍል አጥቢያ ላይ ግን በቡድን መልክ የሚዋቀር ይሆናል፡፡ በቡድኑ ውስጥ ከምእመናንና ከሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ተወካዮች የሚካተቱ ሲሆን የሚመረጡበት መስፈርትም ሙያ፣ መንፈሳዊ ሕይወትና አገልግሎት ይሆናል፡፡

ሂደቱን በሽርፍራፊ ገጠመኞች

ካሽ ሬጂስተር፡- በደረሰኞች በኩል እየተፈጠረ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የተጠቆመው አሠራር የዘመኑ ቴክኖሎጂ የወለደው የገንዘብ መመዝገቢያ ማሽን (ካሽ ሬጂስተር) ሲሆን እያንዳንዱ ማሽን ከሀገረ ስብከቱ ጋር ካለ ማዕከላዊ የመረጃ ቋት ጋር የተሳሰረ በመሆን ለቁጥጥር ሥርዓቱ መዳበር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

ወጥ ሙዳየ ምጽዋት፡- ሙዳየ ምጽዋት ወጥነት ባለው መልኩ ከአንድ ማዕከል ተሠርቶ ስለሚሰራጭ ለየት ያለ ሙዳየ ምጽዋት በድብቅ የመግባቱ ነገር ተረት ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ዐዲሱ ሙዳየ ምጽዋት አቆላለፉና አስተሸሸጉ አንድ ዓይነት ደረጃ ይኖረዋል፡፡ ቁልፎቹ አንድ ቦታ የሚቀመጡ ሲሆን የቁልፍ ማስቀመጫው በበኩሉ በኮምቢኔሽን (ኮድ) እና በሁለት ቁልፎች በሚዘጋ ሳጥን ይሆናል፡፡ የቁልፍ ማስቀመጫው ሳጥን ሁለት ቁልፎች በሁለት የተለያዩ ሰዎች እንዲያዝ ይደረጋል፡፡ እዚህ ላይ ፈገግ የሚያደርግ ነገር ተፈጥሮ ነበር፡፡ ሰነዱ ለውይይት በቀረበበት ሰዓት አንደኛው ቁልፍ በደብር አለቆች እጅ ይያዛል ብሎ አቅራቢው ሲናገር ሁለት ተቃራኒ ጥያቄዎች ቀረቡ፡፡ አንደኛው ከአለቆች ወገን የቀረበው ሲሆን ‹‹እንዴት ብንናቅ ነው እኛ አለቆች ቁልፍ ያዥ የምንሆነው?›› ሲል ሌላኛው ወገን ደግሞ ‹‹በያጥቢያው የተንሰራፋውን ሙስና የሚመሩት እነማን ሆኑና ነው አሁን ደግሞ ለቁልፍ ያዢነት የሚታጩት?›› የሚል ነው፡፡

ጸሐፌ ትዕዛዛት፡- ሌላ ፈገግታ ያጫረው ክርክር የደብር ጸሐፊዎችን የተመለከተው ሐሳብ ነው፡፡ በሚሻሻለው ሥርዓት ውስጥ የደብር ጸሐፊነት ቦታ መገደፉ ቅር ያሰኛቸው ሰዎች ቅሬታቸውን የገለጹት ‹‹ምነው መንግሥት እንኳ ጸሐፌ ትዕዛዛት አለው አይደል እንዴ?›› በሚል ነው፡፡ የአድባራት ዋና ጸሐፊነት በድንገት የተጀመረ መዋቅር ሆኖ ሳለ የስልጣን ወሰኑ ግን ከሚገባው በላይ ስላበጠ ማሻሻያው ካጠቃላይ መዋቅሩና ሊኖረው ከሚገባው የሥራ ድርሻ አኳያ እንዲሰምር አድርጎ ቀንብቦታል፡፡ የጸሐፌ ትዕዛዛት ሥልጣን ጥንት በዘመነ ፊውዳሊዝም ያበቃለት መሆኑን ያልሰሙት ወንድሞች ያነሱት ክርክር ለአጥኚው ቡድኑ አባላት ክፋት ብቻ ሳይሆን የግንዛቤ እጥረትም ተቃውሞና ሙግት እንደሚያመጣ እንዲያስቡ ያደረጋቸውና በዚህም ፈገግ እያሉ በትዕግስት እንዲያስረዱ የረዳቸው ይመስላል፡፡

እነ አቶና ወይዘሪት፡- ሌላው በስፋት ሲደመጥ የነበረው ትችት የጥናት ቡድኑን ማንነት የተመለከተ ነው፡፡ አንዳንዶች ‹‹ሰዎቹን አናውቃቸውም›› ያሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ‹‹የዓለማዊ ትምህርት እንጂ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት የማያውቁ ሰዎች ናቸው›› ብለዋል፡፡ እንዲያውም ‹‹አቶና ወይዘሪት የሚባሉ ሰዎች ያጠኑት ጥናት እንዴት ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ ይሆናል?›› ሲሉ የተሰሙ አስተያየት ሰጪዎች ነበሩ፡፡ አስተያየቱ ግን ባንድ ጎኑ ስሜትን የሚያንጸባርቅ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ፍጹም ስህተት መሆኑ ለማረጋገጥ አይከብድም፡፡ ስሜታዊነቱ አናውቃቸውም የሚለው ነው፡፡ ሁሉም የቡድኑ አባላት በአገልግሎታቸው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የቆዩ እንደመሆናቸው በአገልጋዮች ዘንድ የታወቁ ናቸው፡፡ ጥያቄው ቅን ከሆነም የትና በምን ሲያገለግሉ እንደቆዩ ጠይቆ ማወቅ ይቻላል፡፡

ስህተቱ ደግሞ ዕውቀታቸውን አስመልክቶ የቀረበው ነው፡፡ የባለሙያ ቡድኑ አባላት በዓለማዊ ትምህርት ለሥራው የሚመጥን ትምህርታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ መንፈሳዊውንም ሄደውበታል፡፡ ከቡድኑ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት ቀሲስ ሰሎሞን አለነ ‹‹ለዚህ ዓይነት ንግግር ምላሽ አያስፈልግም፤ ደግሞም አስተያየቱ በትክክል የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ከተማሩት ወገን እንዳልመጣ የምናውቀው ነው›› ይላሉ፡፡

የትችቱ ሌላው ጸያፍ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምእመናን ሊኖራቸው የሚገባውን ድርሻ መናቁ ነው፡፡ አንድ አስተያየት ሰጪ እንዳሉት ‹‹ምእመን የሚሰጠውን ሰጥቶ ዘወር ይበል እንጂ ስለ ቤተ ክርስቲያን ደሞ ምን አገባው? እየተባለ እንደ ዘበት የምንሰማው ንግግር ለአደባባይ የቀረበበት አጋጣሚ ነው›› ይላሉ፡፡ ጨምረውም አንዳንድ አገልጋዮች ‹‹ምእመናን የቤተ ክርስቲያን አባላት እንጂ አካላት አይደሉም›› የሚል ንቀት አዘል አመለካከት እንዳላቸውና ከምእመናኑም ብዙዎች ባለማወቅ ይህን አግላይ አስተያየት አሜን ብለው መቀበላቸውን ይናገራሉ፡፡ በአንድ ደብር ግን አርአያ የሚሆኑ ምእመናን ይህ ዓይነቱ ንቀት አዘል አስተያየት ሲገጥማቸው ‹‹አይደለም በአስተዳደር ውስጥ በሥርዓተ ቅዳሴው እንኳ ይበል ሕዝብ ተብሎ መእመኑ የሚሳተፍበት ሥርዓት ተሠርቶ የለም እንዴ?›› ብለው እንደሞገቱ አብነት ይጠቅሳሉ፡፡

ዲግሪና ጉባኤ ቤት፡- በአንድ የአብነት ጉባኤ ቤት ያስመሠከረ አገልጋይ ደረጃው ከመጀመሪያ ዲግሪ ጋር እኩያ ሆኖ ይታሰብለታል፡፡ የሚለው የዐዲሱ ሥርዓት አንድ አንጓ በተሰማ ጊዜ ትምህርታቸው ተንቆባቸው የነበሩ አገልጋዮች ማመን ተስኗቸው ከሰነዱ ላይ አስነብቡን ሲሉ አንዳንዶች ግን እንዴት የአብነት ትምህርት በዩኒቨረስቲ ዲግሪ ይገመታል? ሲሉ ተቃውሞ እንዳቀረቡ የጥናት ቡድኑ አባላት በፈገግታ የሚያስታውሱት ሌላ ገጠመኝ ነው፡፡ ‹‹በርግጥ እነኚህ ሰዎች አማራጭ መመዘኛ ቢያቀርቡልን ደስ ብሎን በተቀበልነው፡፡ ሆኖም አይደለም የአብነት ትምህርት ተምረው የተመረቁት ይቅርና እራሳቸው አስተምረው የሚመርቁት መምህራኑ ከዚያ ሁሉ እውቀታቸው ጋር የት ተጥለው እንዳሉ የማያውቁ ሆነው ነው?›› ይላል ታደሰ በከፍተኛ ቁጭት፡፡ አሁንም ቢሆን ብዙ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ተገፍተው ምንም ዓይነት ትምህርት ያልተማሩት በዘመድ አዝማድ ሲቀጠሩ ስናይ በርግጥ በነባሩ ሥርዓት የአብነት ትምህርት ያንድ ዲግሪን ያህል ቦታ እንዳልተሰጠው ግልጽ ይሆንልናል፡፡

የበለጠውን ችግር የፈጠረው ተቃውሞ ግን ለመማር ፍላጎት ያጡ ሰዎች የሚያነሱት ነው፡፡ ‹‹ብዙዎቹ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ወጣቶች ናቸው፡፡ መማር ለሚፈልግ ደግሞ አገሪቱ ውስጥ የትምህርት ዕድል በቂ ነው፡፡ ተማሩ ተብለው ቢታዘዙ በሁለትና ሦስት ዓመት ውስጥ ዲፕሎማቸውን ይዘው ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ በሚሻሻለው መዋቅር ውስጥ የተሻለ ቦታ አያጡም፡፡ ሆኖም ጉዳዩ የረብሻ መንስዔ እንዲሆን የፈለጉ ሰዎች ‹አልተማራችሁም ብለው ከሥራ ሊያባርሩን ነው፡፡› በሚል ብዙ ካህናትን አሳስተው ከጎናቸው ለማሰለፍ ሞክረዋል፡፡ አንዳንዶችም እውነት መስሏቸው ተደናግረው ባልገባቸው ጉዳይ ጭፍን ተቃዋሚ ሆነዋል፡፡ … በዐዲሱ መዋቅር ከሥራ ገበታው የሚነሳ ሰው አይኖርም፤ ሁሉም ተደልድሎ ሲያበቃ ትርፍ ሰዎች ቢገኙ ትርፍነታቸው ታውቆ እዚያው የነበሩበት ቦታ ላይ ሆነው ይጠብቃሉ እንጂ ከቦታቸው አይነሱም›› ይላል ታደሰ፡፡

ይህ ደግሞ ሌላ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ‹‹የማይመጥኑ ሰዎችን ዐዲሱ ሥርዓት ተሸክሞ የሚቀጥል ከሆነ ተሻሻለ መባሉ ምኑ ላይ ነው?›› የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ታደሰ ሲመልስ ‹‹አብያተ ክርስቲያናት እስካሁን ባለው አያያዝ እንኳ ተቀማጭ ገንዘባቸው ብዙ ነው፡፡ እንዲያውም ባደረግነው ጥናት ባንዳንድ አጥቢያዎች በዐሥር ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ብሮች በባንክ ተቀማጭ እንደሆኑ ለማወቅ ችለናል፡፡ ቁጠባ ከብክነት ጋር ሲነጻጸር መልካም ተግባር ነው፡፡ ከልማት አንጻር ካየነው ግን ገንዘቡ ላልተወሰነ ጊዜ በባንክ ተቀምጦ መቀጠሉ ተመራጭ አይሆንም፡፡ አሁን የተሻለ አሠራር ሲኖር ደግሞ ገቢው ከዚህ በላይ ስለሚጨምር አብያተ ክርስቲያናት ገንዘባቸውን ከባንክ እያንቀሳቀሱ ለሥራ እንዲያበቁት ዐዲሱ ሥርዓት ያዘጋጀው አማራጭ አለ፡፡

ይኸውም ገንዘቡ ባንክ መቀመጡ ቀርቶ በተጠኑ የልማት መስኮች ላይ እንዲውል የሚያደርግ አማራጭ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እንኳን ትርፍ ሠራተኛ ሊኖሩ ቀርቶ የሠራተኛ እጥረት ስለሚፈጠር ዐዲስ ሠራተኞች በብዛት ይፈለጋሉ፡፡ ገንዘቡ በአግባቡ ከተያዘ ቤተ ክርስቲያን በሚፈለግባቸው ቦታዎች ላይ በጥናትና በሕጋዊ አግባብ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ይተከላል፡፡ እስከዛሬ ሲሠራ እንደነበረው በካህናትና ጥቂት ምእመናን ያልተቀናጀ ጥረት ቦታ እየተያዘ በግብታዊነት መታነጹ ቀርቶ አንድ ቤተ ክርስቲያን ለምን ያህል ክርስቲያኖች እንደሚያስፈልግ እየተጠና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ይሠራል፡፡ በዚህ ጊዜ ተጨማሪ አገልጋዮች ያስፈልጋሉ፡፡ ሠራተኛ መቀነስ የማያስፈልገው በዚህ ምክንያት ነው፡፡››

የጥናት ሰነዱ እንደሚጠቁመው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ሥራ ፈት ገንዘብ መዋል የሚችልበት ብዙ አማራጮች አሉ፡፡ ስለዚህም ከላይ ታደሰ ከገለጸው የልማት ፈንድ በተጨማሪ የበጎ አድራጎት ፈንድ፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት መርጃ ፈንድ፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማጠናከሪያ ፈንድ፣ እንዲሁም የአብነት ትምህርት ቤቶች ማጠናከረያ ፈንድ እንዲቋቋም ይደረጋል፡፡ በዚህም ለምዝበራ ብቻ ሳይሆን ለሥራ ፈትነት የሚጋለጥ ገንዘብ አይኖርም፡፡ በተጨማሪም ዋስትና የለሽ ሆኖ የኖረው የአገልጋዮች የኑሮ ኹኔታ በዚሁ መቀጠል ስለሌለበት የጡረታና የክምና ዋስትናን የሚፈጥር አሠራር እንዲኖር ተጠቁሟል፡፡

ካህናት እና ለውጥ

መምህር ይቅር ባይ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ በመጣ ጊዜ ሁሉ ተቃዋሚዎቹ ካህናት ናቸው፡፡ ነገር ግን ካህን የሚቃወመው እስኪገባው ድርስ ነው፡፡ ከገባው ዋና ደጋፊ የሚሆነው ራሱ ነው›› ይላሉ፡፡ በርግጥ ይህን የአስተዳደር ለውጥ የተቃወሙ ካህናት ብዙ አይደሉም፡፡ ጥቂቶቹም ቢሆኑ ግን በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ተቃውሞ ለውይይት በቀረበው ሰነድ ላይ አላቀረቡም፡፡ ለውጡ ተግባራዊ መሆን የለበትም ብለው የሚያምኑ ሰዎች ካህናቱን በመሰብሰብ ለአድማ የመቀስቀስ ሥራ ግን ሠርተዋል፡፡ የመቀስቀሻ ስልታቸው ደግሞ ‹‹እናንተ ዘመናዊ ትምህርት ስለሌላቸሁ የተማሩ ሰዎችን አስገብተው እናንተ  ልትወገዱ ነው፡፡›› እንዲሁም ‹‹ወደ ገጠርና ጠረፋማ ስፍራ ልትገፉ ነው›› የሚሉ ናቸው፡፡ አንድ መምህር ስለዚሁ ነገር አስተያየት ሲሰጡ ‹‹ብዙ አገልጋዮች ለአገልግሎት ወደ ክልል ከተሞች ስንወጣ ወደ ገጠር ለመውረድ አይፈልጉም፤ በዚህም የተነሳ ኑልን ተብለው ሲለመኑ ‹ቦታው ገጠር ነው?› የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ በጣም የሚገርመው ግን አብዛኞቹ ገጠርን የሚጠሉ አገልጋዮች ከገጠር የመጡ ናቸው፡፡›› ይላሉ በሐዘን በተዋጠ ድምፀት፡፡

ታደሰ ግን ‹‹በዚህ ለውጥ ትግበራ ምክንያት ከሥራ ገበታው የሚነሳ ወይም የሚዛወር ሰው አይኖርም›› ይላል፡፡ ‹‹ወደ ገጠር ለስብከተ ወንጌል የሚላኩ ሰዎች አበላቸውና ሌሎች አስፈላጊ ጥቅሞቻቸው ተጠብቆላቸው እንዲያገለግሉ የሚያደርግ ሥርዓት ግን ይኖራል፡፡ ይህ ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን ዋነኛ ሥራ ከግብ የሚያደርስ ሲሆን በዛውም አገልጋዩ እንዳይጎዳ የሚጠብቅ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ግን በአገልጋዮች ፈቃደኝነት ላይ ተመሠርቶ እንጂ በግዳጅ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ያለ ፍላጎቱ አስተምር የተባለ ሰው ትክክለኛውን ትምህርት ያስተምራል ተብሎ አይታሰብም፡፡›› በዚህ መልክ የተቀረጸው ረቂቅ ጥናት ሥርዓቱ ስብከተ ወንጌልን ማዕከል ያደረገ ሊሆን ይገባዋል በሚል ሰነዱ ያስቀመጠውን የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያስታውስ ነው፡፡

ስብከተ ወንጌልንና የቤተ መቅደስን አገልግሎት ማዕከል ያደረገ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ የሚሆነው እነዚህ ተግባራት ከቤተ ክርስቲያን ማዕከላዊ ዓላማ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ዋነኛ ሥራዎች ስለሆኑ ነው፡፡ በነባሩ የአሠራር ሥርዓት ግን ዋነኛው ሥራ ችላ ተብሎ ደጋፊው ሥራ ግን አብጦ ቆይቷል፡፡ ዐዲሱ ሥርዓት ተግባራዊ ሲሆን ዋናው ሥራ የዋናነት ቦታውን ይይዛል፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ በቤተ መቅደስና በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ላይ ላሉ አገልጋዮች የተሻለ ደሞዝና ጥቅማ ጥቅም ይከበርላቸዋል፡፡ እስከ አሁን ግን ቤተ መቅደስ ማገልገል ዝቅ ተደርጎ እየታሰበ ቅዳሴ ከሚቀድሰው ካህን ይልቅ የመዝገብ ቤት ሠራተኛው የተሻለ ሲከፈለው ቆይቷል፡፡ ተገልብጦ የቆየው ሥርዓት ሲስተካከል የብዙዎቹ ካህናት ሕይወት ይሻሻላል፡፡ ይህ የገባቸው ካህናት የለውጡ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ከምዝበራ ድኖ ለአገልግሎት ሲውል የአገልግሎቱ አካል የሆኑት ካህናትም ስለሚጠቀሙ የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ለቤተ ክርስቲያን ይሆናል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ ኋላ እንዳያርስ

የመዋቅር ጥናት ቡድኑ የጥናቱን የመጀመሪያ ረቂቅ ባጠናቀቀበት ሰሞን አንድ አባት ደስታ ፈንቅሏቸው ‹‹እናንተ ይህን የሠራችሁ ስማችሁ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በወርቅ ቀለም ተጽፏል›› ሲሉ ተናገሩ፡፡ በቦታው ከነበሩት የጥናት ቡድኑ አባላት መካከል አንደኛው ‹‹ብጹዕ አባታችን እንደ ቃልዎ ይሁንልን፤ ሆኖም ይህ ጥናት በወረቀት ከቀረ ዋጋ አይኖረውም፡፡ የሁላችንም ስም በወርቅ ቀለም የሚጻፈው ጥናቱ ሲተገበር ነው›› አለ፡፡ የዚህን ወንድም ስጋት ብዙዎች ይጋሩታል፡፡

His Holiness Patriartch Abune Mathiasከዚህ ቀደም የታጠፉ የሲኖዶስ ውሳኔዎችን እያስታወሱ እንዲሁም የአማሳኞችን ጩኸት አከል ዛቻ በመስማት ይህ ነገር በከንቱ ይቀር ይሆን? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ የምእመናን ተወካዮች ቅዱስ ፓትርያርኩ ፊት ቀርበው ይህን ስጋታቸውን በእንባቸው በገለጹበት ዕለት ቅዱስነታቸው ‹‹አስቀድሜ ሙስና፣ ብልሹ አሠራርና የመሳሰሉት ከቤተ ክርስቲያን ሊወገዱ ይገባል ብዬ የጮህኩት እኔ ነኝ፤ አሁን ታዲያ መልሼ ይህ ነገር ሳይተገበር ይቅር ብል ጩኸቴን የምቀማው እኔው ራሴ ነኝ›› ሲሉ የምእመናንን ልብ የሚያረጋጋ ንግግር ሰጥተዋል፡፡

ይህ ሥራ የተሠራው የግንቦት ፳፻፭ ዓ.ም ርክበ ካህናት ላይ የተሰበሰበው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በወሰነው ውሳኔና በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ነው፡፡ የባለሙያ ቡድኑ አባላት ስመ ክርስትና ስለሥራው መቃናት አባቶች በጸሎት እንዲያሳስቡ ከሚጠይቅ ጦማር ጋር  ለታላላቅ ገዳማትና አድባራት ተልኮ ጸሎት ተደርጎበታል፡፡ ለሥራው የተቋቋመው የባለሙያ ቡድን የሰጠው አገልግሎት በገንዘብ ቢሰላ በጣም በትንሹ ሁለት ሚልዮን ብር እንደሚያወጣ ይነገራል፡፡ ስለዚህ የዚህ ሥራ መክሸፍ የሚያስከትለው ኪሳራ ቁሳዊም መንፈሳዊም ነው፡፡ ከዚህም በላይ ነባሩ ሥርዓት በብዙ መልኩ ሲታይ መቀጠል የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ስለዚህ ተሻሽሎ ሊተካ ግድ ሆኗል፡፡

ለብዙዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ምዝበራና የሥነ ምግባር ዝቅጠት ወይንም ሙስና የሚመስላቸው የግለሰቦች አላግባብ መበልጸግ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ንቅዘት ግለሰቦችን አበልጽጎ፤ ከተቋሙ ደግሞ ጥቂት ገንዘብ አጉድሎ የሚመለስ አይደለም፡፡ ተቋሙን ጨርሶ እስከማውደም የሚደርስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ተቋም እንደመሆኗ ንቅዘቱ በዚህ ከቀጠለ መጥፋቷ አይቀርም፡፡ እንዲያውም ቤተ ክርስቲያንን ከሌሎች ምድራውያን ተቋማት ልዩ የሚያደርጋት የንጽሕና አገልግሎቷ ስለሆነ ሙስናን በውስጧ አቅፋ መኖር አትችልም፡፡ የክፋት አሠራር ጸንቶ መልካም የሆነውን ነገር እስከመጨረሻው አሸንፎ እንደማይኖር በሃይማኖት የታወቀና የታመነ ቢሆንም በተለይ ክፋት በሰለጠነበት በዚህ ዘመን ንቅዘትና ሥርዓት አልባነት ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊያደርሱ የሚችሉት ጉዳት ቀላል እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡

ለዚህም ብዙ ምልክቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ ከዐሥር ሚልዮን በላይ ክርስቲያኖች ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ወጥተው ጠፍተዋል፡፡ ሥልጣነ ክህነትና ምንኩስና እንደምናምንቴ ተቆጥሯል፡፡ ሊቃውንት ሥራ በሞላባት ቤተ ክርስቲያን እየኖሩ ሥራ አጥ ሆነዋል፡፡ ጥንታውያን አድባራት ተዘግተዋል፡፡ ምእመናን ለረሀብና ለህመም ተጋልጠው የሚረዳቸው ቀርቶ የሚያጽናናቸው አጥተዋል፡፡ ሃይማኖታቸውን ለውጠው ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሚሰደዱ ወጣቶች ሕይወታቸውን ከማጣታቸው በፊት ሰብአዊ ክብራቸውን ሲያጡ ቤተ ክርስቲያን አልደረሰችላቸውም፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ቤተ ክርስቲያን ሰውና ገንዘብ አጥታ እንዳልሆነ መስካሪው ብዙ ነው፡፡ ችግሩ ከማስተዳደሩ ላይ ነው፡፡ የማስተዳደሩን ሥራ ለመሥራት ደግሞ የሰለጠነ ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡

የመጨረሻው መጀመሪያ

the team with his grace abune estifanosየካቲት ፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ልዩ ቀን ነበረች፡፡ በሀገረ ስብከቱ አስተባባሪነት የተቋቋመው የባለሙያ ቡድን ሲያጠና የቆየውን የተቋማዊ ለውጥ አመራር የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነድ ለሀገረ ስብከቱ በይፋ አስረክቧል፡፡ ዐሥራ ሦስት አባላት ያሉት የባለሙያ ቡድን ከአንድ ሺሕ በላይ አጠቃላይ ገጾች ያሏቸውን ዐሥራ ሁለት ሰነዶች በሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ተገኝቶ በአስተባባሪው ታደሰ አሰፋ በኩል ሲያስረከብ ሀገረ ስብከቱም ከልዩ ምስጋና ጋር በሊቀ ጳጳሱ አማካይነት በይፋ ተረክቦ ሰነዱን የራሱ አድርጎታል፡፡ ሰነዱ በሊቀ ጳጳሱ አማካይነት ለቋሚ ሲኖዶስ የሚቀረብ ሲሆን የሚጠበቀው ነገር በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ነው፡፡ ከዚያ በፊት ደግሞ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ለምእመናንና ለካህናት ይሰጥበታል ተብሎ ይታሰባል፡፡

የጥናት ቡድኑ አባላት ይህን ሥራ የሚቃወሙ ሰዎች የፈጠሩት ከባድ ተግዳሮት እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም ለማሸማቀቅና ለማስበርገግ የታለሙ ድምጾች እንዳልጠፉ አይሸሽጉም፡፡ ነገር ግን ስድቡንና ሌላውን ጩኸት  ለቤተ ክርስቲያን ሲባል እንደ ሙሉ ደስታ መቀበል እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ ደግሞም ‹‹የቤተ ክህነቱን ጸባይ ለሚያውቅ ሰው አስፈሪ የሚመስለው ጩኸት የሚያስፈራው አይሆንም›› ይላሉ አንዱ ባለሙያ፤ ከዚህ ቀደም በሙያቸው ለማገልገል ገብተው በድንጋጤ የወጡ እርሳቸው የሚያውቁዋቸውን ምእመናንን በትዝታ እያስታወሱ፡፡ የቡድኑ አስተባባሪ ታደሰ አሰፋ ቀለል አድርጎ የሚገልጸው ተግዳሮት በርግጥም ቀላል መሆኑ የታወቀው ለተቃውሞ መጣን ብለው በጸያፍ ቃላት ሲናገሩ ከነበሩት መካከልም ነገሩ እንደማያዋጣ የገባቸው ሰዎች ከጥቂት ቀናት በኋላ ይቅርታ እንደጠየቁ ሲታወቅ ነው፡፡ በርሱ አገላለጽ ‹‹ይቅርታ መጠየቅ ታላቅነት ቢሆንም ከልብ የመነጨ መሆኑን ለማስመስከር ደግሞ በተግባር መግለጥ ያስፈልጋል፡፡››

ሁሉም የባለሙያ ቡድኑ አባላት ተግዳሮቱ ቀላል ቢሆንም  የጥናቱ ረቂቅ ተግባራዊ ሆኖ የቤተ ክርስቲያንን እድገት ለማየት እንድንችል ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እስከ መእመናን ድረስ እያንዳንዱ ክፍል ሳይዘናጋ በየበኩሉ ሊራዳ እንደሚገባው ያስታውሳሉ፡፡ በተለይ ቅዱስ ሲኖዶስ ከመጀመሪያው አቅጣጫ ሰጥቶ ያስጀመውን ሥራ ለማስተግበር ከመቻሉ በፊት በጎን የሚካሄዱ ሕገ ወጥ ጫናዎች እንዳያሰናክሉበት ነቅቶ ሊጠብቅ ይገባዋል፡፡ የቡድኑ መሪ ታደሰ በፈገግታና በረጋ መንፈስ ቀለል አድርጎ የሚገልጸው ይህ ጉዳይ እርሱና የሥራ ቡድኑ አባላት ብዙ የለፉበት ምእመናንና ካህናቱም ተስፋቸውን የጣሉበት ሥራ እንደሆነ በሁሉም ልብ ዕውቅ ነው፡፡

የሥርዓት ቤት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብቷን የሚያስተዳድርላት ታማኝ መጋቢ በማጣትና በሥርዓት አልበኝነት ትጠፋ ይሆን? በሚል ስጋት ተውጠው የነበሩት ሁሉ ‹‹ኢታርእየነ እግዚኦ ሙስናሃ ለቤተ ክርስተያን›› ከሚል ጸሎት ጋር  የወረቀት ሥራውን አጠናቆ ተግባራዊነቱን የሚጠባበቀውን የለውጥ ሂደት ትንፋሻቸውን ውጠው ይከታተሉታል፡፡ ይህም በታላቅ ኃላፊነት ለተያዙት አገልጋዮች ብቻችሁን አይደላቸሁም የሚል የብርታት ድምፅ ነው፡፡ የጸሎታቸውም ትርጓሜ ‹‹አቤቱ የቤተ ክርስቲያንን ጥፋቷን አታሳየን›› የሚል ነው፡፡

Advertisements

22 thoughts on “የገንዘብና የሰው ሀብት አስተዳደር ጥያቄ ለቤተ ክርስቲያን

 1. Anonymous March 1, 2014 at 3:22 pm Reply

  ይሄን ጉድ ሰምታችሁዋል!!!!!!!!!!
  አሸናፊ መኮንን ግብረ ሰዶማዊ መሆኑን ታውቃላችሁ?
  በርካታ እሱን ሲከተሉ የነበሩ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ሁሉ የሚያወሩት ግብረ ሰዶማዊ መሆኑን ነው። በዛ ላይ ውሸታም ሀሰተኛ ነቢይ እና ገንዘብ አፍቃሪ ነው። እድሜውን ሙሉ ሙዳይ ሙጽዋት አቅፎ የሚኖር ሰው ነው። ሰው መስሎን እሱ ጋር ስንመላለስ ሁሌ የሚገርመን ለሙዳይ ሙጽዋት ያለው ፍቅር ነው ከቢሮው ለአፍታም አይለያትም። ከሱ በቀር ማንም አይቆጥራትም። የእግዚአብሔርን ገንዘብ እየበዘበዘ ለግል ጥቅሙ የሚያውል ጀግና ነው። በአንድ አመት ውስጥ ብቻ ሌላ ምንም ተጨማሪ ገቢ ሳይኖረው ራቫ 4 መኪና ገዝቷል ሱቅ ከፍቷል። ይቅርታ የሚል መጽሀፍ ለስሙ ጽፏል ነገር ግን በምድር ላይ እሱን የሚወዳደር ቂመኛ የለም።
  አታግቡ የሁል ጊዜ ምክሩ ነው። ምነው ቢሉ ለሱ እንዲመቸው ነዋ።
  በእግዚአብሔር ስራ ውስጥ የስጋ ጥቅሙን የሚያሳድድ ሸፍጠኛ ግለሰብ አያስፈልግም።
  በዛ ላይ ያለበት የእውቀት ችግር በግልጽ የሚታይ ነው። ሊቅ መስሎን ለተጠጋነው የመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች የህጻን ትምህርት አስተማረን። ከዛ ቢያንስ የሚናገረው ትንሽ እውቀት እንዲኖረው በተለያየ መንገድ ኮሎጅ ገብቶ እንዲማር ለማድረግ ሞከርን መቸ ሰምቶ እራሱን ሊቀ ሊቃውንት አድርጎ ያስቀመጠ ጀግና ነው።
  አሁን ደግሞ እንደ ጳጳስ ያደርገዋል አሉ።
  በእውነት ብትቀርቡ እና ሕይወቱን ብትመረምሩ እንዲህ ያለ ግለሰብ እንዴት የኛን አገልግሎት ተቀላቀለ? ትላላችሁ። አሳዛኝአሳፋሪ እና አቅሙን የማያውቅ ግለሰብ ነው። እኔ እማዝነው ለበርካታ የዋህና ጨዋ ተከታዮቹ ነው።
  የተሃድሶ ነገር ያሳዝናል

  • weg March 2, 2014 at 3:57 am Reply

   Please don’t run to disclose others’ sin.

  • Anonymous March 2, 2014 at 1:31 pm Reply

   “ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ፤ ጸያፍ ነገር ነውና።” ኦሪት ዘሌዋውያን 18፥22

  • Anonymous March 2, 2014 at 1:34 pm Reply

   ዝም ብሎ ኮሜንት ከመለጠፍ ጉዳዩን አጣርቶ በዘገባ መልክ ማውጣት አይሻልም። እውነት ከሆነም ልጁ ንስሀ ይግባ ውሸት ከሆነም ከውሸት ጋር ከመተባበር ተጠበቁ።

 2. Ambachew March 1, 2014 at 4:29 pm Reply

  እባካችሁ ሌሎች ተጨማሪ መረጃዎችንም ጻፉልን፡፡

 3. Anonymous March 2, 2014 at 12:20 pm Reply

  for my fathers will is that every one who looksto the son and belives in him shall have eternal life,and Iwill raise him up at the last jon6;40 Ashenafi never did such kinds of evil work belive or not never never

 4. teshomemk March 3, 2014 at 7:45 am Reply

  I wonder that 8 of 10 team members are mk members.why you deny that mk is not at the back? I was one of the laities who summoned by mk at the new building hall to support the change. If mk done like this why it denied its backing. What most wonder is , mk’s denial letter distributed to bishops. “Albelashimin min ametaw” allu. I personally support the change, but not mk’ approach.

  • Anonymous March 3, 2014 at 3:25 pm Reply

   Dear Teshome, can you send your full comment and objection through the e – mail adress of Hammer magazine?

 5. Anonymous March 3, 2014 at 7:49 am Reply

  እዚህ ቦታ ላይ ልንወያይ የሚገባው የቤተ ክርስቲያንን የአስተዳደርና የፋይናንስ ሥርዓት ለውጥ አስመለክቶ ነው፡፡ ጉዳዩ ልዩ ትኩረት የሚሻ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለባሕረይዋ በማይስማማት መለኩ በሙስና እንድታድፍ እየተገደደች ነው፡፡ ምእመናን እየጠፉ ነው፡፡ አብያተ ክርስቲያናት እየተዘጉ ነው፡፡ አደጋውን እንገንዘብ፡፡

 6. Anonymous March 3, 2014 at 7:50 am Reply

  ለብዙዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ምዝበራና የሥነ ምግባር ዝቅጠት ወይንም ሙስና የሚመስላቸው የግለሰቦች አላግባብ መበልጸግ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ንቅዘት ግለሰቦችን አበልጽጎ፤ ከተቋሙ ደግሞ ጥቂት ገንዘብ አጉድሎ የሚመለስ አይደለም፡፡ ተቋሙን ጨርሶ እስከማውደም የሚደርስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ተቋም እንደመሆኗ ንቅዘቱ በዚህ ከቀጠለ መጥፋቷ አይቀርም፡፡ እንዲያውም ቤተ ክርስቲያንን ከሌሎች ምድራውያን ተቋማት ልዩ የሚያደርጋት የንጽሕና አገልግሎቷ ስለሆነ ሙስናን በውስጧ አቅፋ መኖር አትችልም፡፡ የክፋት አሠራር ጸንቶ መልካም የሆነውን ነገር እስከመጨረሻው አሸንፎ እንደማይኖር በሃይማኖት የታወቀና የታመነ ቢሆንም በተለይ ክፋት በሰለጠነበት በዚህ ዘመን ንቅዘትና ሥርዓት አልባነት ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊያደርሱ የሚችሉት ጉዳት ቀላል እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡

 7. Anonymous March 3, 2014 at 7:51 am Reply

  ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ ከዐሥር ሚልዮን በላይ ክርስቲያኖች ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ወጥተው ጠፍተዋል፡፡ ሥልጣነ ክህነትና ምንኩስና እንደምናምንቴ ተቆጥሯል፡፡ ሊቃውንት ሥራ በሞላባት ቤተ ክርስቲያን እየኖሩ ሥራ አጥ ሆነዋል፡፡ ጥንታውያን አድባራት ተዘግተዋል፡፡ ምእመናን ለረሀብና ለህመም ተጋልጠው የሚረዳቸው ቀርቶ የሚያጽናናቸው አጥተዋል፡፡ ሃይማኖታቸውን ለውጠው ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሚሰደዱ ወጣቶች ሕይወታቸውን ከማጣታቸው በፊት ሰብአዊ ክብራቸውን ሲያጡ ቤተ ክርስቲያን አልደረሰችላቸውም፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ቤተ ክርስቲያን ሰውና ገንዘብ አጥታ እንዳልሆነ መስካሪው ብዙ ነው፡፡ ችግሩ ከማስተዳደሩ ላይ ነው፡፡ የማስተዳደሩን ሥራ ለመሥራት ደግሞ የሰለጠነ ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡

 8. Anonymous March 3, 2014 at 9:30 am Reply

  ይህ ጽኁፍ በየብሎጉና በየጋዜጣው ሲራገብ የከረመውን የአንድ ወገን አስተያየት ከማንጸባረቅ በቀር ምንም አዲስ ነገር የለውም.ማኅበረቅዱሳን እንዲህ ወርዶ የተለጣጠፈ ጽሁፍ በወርቃማዋ ልሳኑ በሐመር በማስነበቡ አዝናለሁ.
  አጻጻፋችሁ በጥናቱ እንደሌላችሁበት ሳይሆን ከመኖርም በላይ ሙሉ ረቂቁ ከእናንተ እንደወጣና ለጊዜው በሊቃውንቱ ይታይ መባሉም እንዳንገበገባችሁ በደንብ ያስታውቃል.ነጠላ የደበቀውን ትምክህትና መመጻደቅ እድሜ ለሚዲያው ቆየን ከታዘብነው.
  አማኙ የጠፋው ከጥናት ጉድለት ሆነም አልሆነም በዚህ 20 አመት 10 ሚሊዮን ምእመን ሲጠፋብን እኮ እናንተም ነበራችሁ.ማንን ነው ነጥላችሁ የምትወቅሱት ??ብቻ የዘንድሮ ሁኔታችሁ ያሳዝናል.በአደባባይ መመጻደቅን ሙያ አረጋችሁት. በዚህ ግብራችሁ ከብዙ ካህናት ልብ እየወጣችሁ ነው – በተለይ ከላይኞቹ. አሁን የሞዴል 30 መውሰጃችሁ ጊዜ ቀርቦላችሁዋልና እስኪ እናንተው እንዴት በቤ/ክ ደረሰኝ ገንዘብ እንደሚሰበሰብ ታሳዩናላችሁ.ፐርሰንት በመክፈል ከህግ በታች ለማደር መዘጋጀታችሁን ለማረጋገጥም እንናፍቃለን
  እንግዲህ ለቅድስቱዋ ተዋህዶ እረኛውን ከመንጋው የሚያስማማ፣ተጠራጣሪዎችን ገፍቶ ሳይሆን አጽናንቶ የሚመልስ መልአከ ምህረት ወሳህል ይላክልን ከማለት በቀር ምንም አንልም.

  • Anonymous March 4, 2014 at 7:24 am Reply

   በአንድ በኩል ዐዲስ ነገር የለውም ብለህ ወዲያው ደግሞ አጻጻፋችሁ ረቂቁ ከእናንተ እንደወጣ ያስታውቃል፡፡ ማለትህ የተጋጨ ሐሳብ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ መልካም ሐሳብ ሊያበሳጭህ አይገባም፡፡ ለውጥ እነሚያስፈልግ አምኖ ከመቀበል ውጪ ሌላ ምንም ምርጫ የለም፡፡ ይልቅስ አንተም የሚጠቅም ሐሳብ ካለህ አበርክት፡፡

   • Anonymous March 4, 2014 at 11:13 am

    አዲስ ነገር የለውም ማለቴ የሐመርን ወሬ ከየብሎጉ ስናነበው ስለከረምን፣ረቂቁ ከእናንተ እንደወጣ ያስታውቃል ማለቴ የማታ ማታ ራሳቸው ስላመኑና የሚያወሩትም ለሌላ ለማንም አካል ከሲኖዶስ በቀር የሌለው ረቂቅ በእነሱ እጅ ብቻ ስላለ ነው.አለቀ. ማጋጨት ካልፈለክ በቀር ምኑም አይጋጭ.
    በነገርህ ላይ ይሄን ማህበር በደግ እንዳላይ የሚያደርገኝ እኛን የሚቃወም ሁሉ ርኩስ ነው የሚል ጭፍንና ግብዝ አስተያየታችሁ ስለሚያስጠላኝ ነው. አዝናለሁ. ከልቤ እየወጣችሁ ነው. ሃይማኖቴን ግን ከእናንተ ሳይሆን ከቤተክርስቲያን ስላገኘሁዋት ስለግብዞች ብየ አልተዋትም.የዚህን ያህልም ደካማ አይደለሁም.
    እውነት ለመናገር ሰው ጥናቱን ሳያይ ማኅበረቅዱሳን አለበት በሚል ብቻ ያን ያህል ዘመቻ ተካሄደ ካላችሁ ማኅበሩ ራሱን መመርመር ነበር እንጅ ጉዳዩ ካለቀ በሁዋላ ማኅበሩ ከተደበቀበት መጋረጃውን ገልጦ መውጣት አልነበረበትም. ቀረርቶውን ተውት. ለመድነው እኮ. ሌባም፣መናፍቅም፣ዘረኛም፣ሰነፍም ያልሆነ ብዙ በአካሄዳችሁ የማይደሰት ሰው ስላለ ራሳችሁን መርምሩ. የክተት አዋጁን ተውት.መመጻደቁም ይቅር. አባቶችን ከምዕመናን ማቀራረቡንስ ትታችሁታል.ለማቃቃር መሞከራችሁም በቀረልን.እረ በፈጠራችሁ በከተማ ዙሪያ ሚዲያውን አጃቢ አድርገን ተንቀሳቀስን ብላችሁ አትደንፉብን.ስከኑ፣ስከኑ፣ስከኑ.

  • Anonymous March 4, 2014 at 7:29 am Reply

   ፖሊስን የሚፈራ ማን ነዉ ሌባ አይደለምን
   አለቃ የሚያስደነብረዉ ማንን ነዉ ሰነፉን ሰራተኛ ነዉኮ
   ጽዳት የሚያስደነግጠዉ ና ድራሹን የሚያጠፋዉስ ማንን ነዉ ዝንብን አይደለምን
   ማኅበረ ቅዱሳንን የሚጠላ ማን ነዉ; መናፍቅና ቤተመቅደስ ዘራፊዉ

 9. Anonymous March 4, 2014 at 7:25 am Reply

  በአንድ በኩል ዐዲስ ነገር የለውም ብለህ ወዲያው ደግሞ አጻጻፋችሁ ረቂቁ ከእናንተ እንደወጣ ያስታውቃል፡፡ ማለትህ የተጋጨ ሐሳብ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ መልካም ሐሳብ ሊያበሳጭህ አይገባም፡፡ ለውጥ እነሚያስፈልግ አምኖ ከመቀበል ውጪ ሌላ ምንም ምርጫ የለም፡፡ ይልቅስ አንተም የሚጠቅም ሐሳብ ካለህ አበርክት፡፡

 10. Anonymous March 4, 2014 at 7:54 am Reply

  ሰው እንዴት መልካም ነገርን የቃወማል ብዬ ለውጡን በሚቃወሙ ሰዎች ልገረም እጀምርና መልሶ ደግሞ ሰው ሁልጊዜም መልካሙን ብቻ እንደማይመርጥ ትዝ ሲለኝ ወደ አውነታው እመጣለሁ፡፡በእርግጥ ይህን የለውጥ አሠራር የሚቃወሙ እነማን ኛቸው ? አንዳንዶቹ እምነት የለሾች ሌሎቹ በፍቅረ ንዋይ የነደዱ፣ሌሎቹም በፍቅረ ሢመት የተቃጠሉ አንዳንዶቹ ያልተማሩ ጨዋዎች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ የማይታደሰውን የቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነትና አስተምህሮ ይታደስ የሚሉ ነገር ግን አውነተኛ ተሐድሶ የሚያሻውን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር እና የፋይናንስ አሠራር እንደበሰበሰ ይቀጥል የሚሉ የፕሮቴስታንት ተላላኪዎች ተሐዶሶዎች ናቸው፡፡
  አሮጌው መንገድ (ሙሰኝነትና ኋላቀር አሠራር) በዘመናት ተፈትኖ ያረጀና ያፈጀ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱን ያዋረደ አሠራር በመሆኑ ሊታዘንለት እና ጊዜ ሊሰጥለት የሚገባ አይደለም፡፡ለምን ቢሉ ከበቂ በላይ ጊዜ አግኝቶ የታየና በውጤቱም ንቅዘትና መበስበስ ብቻ ስለሆነ፡፡ስለዚህ አባቶች በጀመራችሁት የለውጥ አርምጃ በፍጥነት ወደ ፊት፡፡ጊዜ በፈጀ ቁጥር ጥረቱ ለመቀልበሱ ምልክት መሆኑ ታውቆ በፍጥነት ወደ ፊት፡፡ለብልህ አይነግሩ ለአንበሳ አይመትሩ ነውና አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጉዳዩን በተለያዩ የተሻሉ ማዕዘኖች እንደሚመለከቱት ተስፋችን ነው፡፡
  ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ አፋራም ሊሆን አይገባውም፡፡ይህ ከተሳካ እኮ የድካማችሁን ፍሬ ልትመለከቱ ነው ማለት ነው፡፡ዛሬ ዛሬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንድታፍርና እንድትሸማቀቅ ልዩ ልዩ ስልታዊ እንቅስቃሴዎች እየተመለከትን ነው፡፡ስለዚህ ማኅበሩ የአፍረት ዓይነ ርግቡን ጥሎ ወደ አደባባዩ ይምጣ፡፡በእርግጥ ይህ ጽሑፋችሁ አንድ ጅምር ነው ጸሐፊውን እግዚአብሔር ይባርከው፡፡
  ቤተ ክርስቲያን ወደ ቀደመ ግርማዋና መታፈሯ ትመለስ ከተባለ ምናምነቴ አስተሳሰብ እና አሠራርን በቁርጥ በቃ ልንለው ይጋባል፡፡አሁን እኮ ቤተ ክርስቲያን ወደ መገፋት እየሄደች ነው ታዲያ ምንድነው የሚጠበቀው፡፡
  ምእመናን ምን ይሆን የምትጠብቁት ? ይህ ሁሉ ምዝበራ እኮ የሚፈጸመው በገዛ ገንዘባችሁና በድካማችሁ ላብ ነው፡፡ይህ ሁሉ ትዕቢት እና ትዝርኅት እኮ የሚታየው በእናንተ ላይ ነው፡፡የለውጡ ቁጥር አንድ ለመሆን ተነሡ፡፡ከተመልካችነት ወደ ተሳታፊነት እንዲሉ የተሳትፎችሁ ጊዜ አሁን ነው፡፡ለምትወዷት ቤተ ክርስቲያን ሆ ብላችሁ ተነሡ፡፡
  ሰው እንዴት መልካም ነገርን የቃወማል ብዬ ለውጡን በሚቃወሙ ሰዎች ልገረም እጀምርና መልሶ ደግሞ ሰው ሁልጊዜም መልካሙን ብቻ እንደማይመርጥ ትዝ ሲለኝ ወደ አውነታው እመጣለሁ፡፡በእርግጥ ይህን የለውጥ አሠራር የሚቃወሙ እነማን ኛቸው ? አንዳንዶቹ እምነት የለሾች ሌሎቹ በፍቅረ ንዋይ የነደዱ፣ሌሎቹም በፍቅረ ሢመት የተቃጠሉ አንዳንዶቹ ያልተማሩ ጨዋዎች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ የማይታደሰውን የቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነትና አስተምህሮ ይታደስ የሚሉ ነገር ግን አውነተኛ ተሐድሶ የሚያሻውን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር እና የፋይናንስ አሠራር እንደበሰበሰ ይቀጥል የሚሉ የፕሮቴስታንት ተላላኪዎች ተሐዶሶዎች ናቸው፡፡
  አሮጌው መንገድ (ሙሰኝነትና ኋላቀር አሠራር) በዘመናት ተፈትኖ ያረጀና ያፈጀ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱን ያዋረደ አሠራር በመሆኑ ሊታዘንለት እና ጊዜ ሊሰጥለት የሚገባ አይደለም፡፡ለምን ቢሉ ከበቂ በላይ ጊዜ አግኝቶ የታየና በውጤቱም ንቅዘትና መበስበስ ብቻ ስለሆነ፡፡ስለዚህ አባቶች በጀመራችሁት የለውጥ አርምጃ በፍጥነት ወደ ፊት፡፡ጊዜ በፈጀ ቁጥር ጥረቱ ለመቀልበሱ ምልክት መሆኑ ታውቆ በፍጥነት ወደ ፊት፡፡ለብልህ አይነግሩ ለአንበሳ አይመትሩ ነውና አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጉዳዩን በተለያዩ የተሻሉ ማዕዘኖች እንደሚመለከቱት ተስፋችን ነው፡፡
  ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ አፋራም ሊሆን አይገባውም፡፡ይህ ከተሳካ እኮ የድካማችሁን ፍሬ ልትመለከቱ ነው ማለት ነው፡፡ዛሬ ዛሬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንድታፍርና እንድትሸማቀቅ ልዩ ልዩ ስልታዊ እንቅስቃሴዎች እየተመለከትን ነው፡፡ስለዚህ ማኅበሩ የአፍረት ዓይነ ርግቡን ጥሎ ወደ አደባባዩ ይምጣ፡፡በእርግጥ ይህ ጽሑፋችሁ አንድ ጅምር ነው ጸሐፊውን እግዚአብሔር ይባርከው፡፡
  ቤተ ክርስቲያን ወደ ቀደመ ግርማዋና መታፈሯ ትመለስ ከተባለ ምናምነቴ አስተሳሰብ እና አሠራርን በቁርጥ በቃ ልንለው ይጋባል፡፡አሁን እኮ ቤተ ክርስቲያን ወደ መገፋት እየሄደች ነው ታዲያ ምንድነው የሚጠበቀው፡፡
  ምእመናን ምን ይሆን የምትጠብቁት ? ይህ ሁሉ ምዝበራ እኮ የሚፈጸመው በገዛ ገንዘባችሁና በድካማችሁ ላብ ነው፡፡ይህ ሁሉ ትዕቢት እና ትዝርኅት እኮ የሚታየው በእናንተ ላይ ነው፡፡የለውጡ ቁጥር አንድ ለመሆን ተነሡ፡፡ከተመልካችነት ወደ ተሳታፊነት እንዲሉ የተሳትፎችሁ ጊዜ አሁን ነው፡፡ለምትወዷት ቤተ ክርስቲያን ሆ ብላችሁ ተነሡ፡፡

  • Anonymous March 4, 2014 at 11:45 am Reply

   በስሜት አትፈርጅ እባክህ
   መጀመሪያ አዞ እንባውን ትተህ የማኅበርህን አካሄድ አርም
   ለስድቡ ትደርስበታለህ
   እንደ አባ ህርያቆስ የልዑልን መኖሪያ ለማየት እስከመድረስ ድረስ ማሰብህን ከደሰኮርክ በሁዋላ ንግባእኬ ኀበ ጥንተ ነገር ስትል መደምደሚያህ ሰዎችን መፈረጅ ከሚሆን አለማሰብህ ይሻልህ ነበር.

   • Anonymous March 4, 2014 at 3:22 pm

    እስኪ ለቤተ ክርስቲያን ይበጃል የምትለውን አንድ ሐሳብ ሰንዝር፡፡ ወይስ ተቃውሞ ብቻ ነው ያለህ? ተቃውሞም ከሆነ ከስሜት በጸዳ መልኩ ከጽሑፉ ውስጥ ስህተት ነው የምትለውን ቢያንስ አንድ ነገር አመልክት፡፡ በጭፍን መቃወም ዋጋ የለውም፡፡

   • Anonymous March 5, 2014 at 7:14 am

    ጽሁፉ አዲስ ነገር ስለሌለውና በየብሎጉ፣በየጋዜጣው ወጥቶ ብዙ ስለተባለበት ምንም መጨመር አያስፈልግም. በበቂ ሁኔታ ቀድሞ ተተችቱዋል.
    ለምሳሌ ያህል ጥቀስ ካልከኝ ፡ መናፍቃንን ብቻውን ተዋግቶ ያሸነፈው ማኅበረቅዱሳን እንደሆነ ሐመር ትለፍፋለች. ግን ብቻውን አልነበረም. በሺህ ሚቆጠሩ የማኅበሩ አባል ያልሆኑ ሰባክያነ ወንጌሎች፣የቤ/ክህነት ስብከተ ወንጌል መምሪያ፣የየአጥቢያው ካህናት የውጊያው አካል ነበሩ. አሁንም ናቸው. ሆኖም አፍ ያለው ማኅበር ሁሉንም ዋጋ ጠቅልሎ ወሰደና በመናፍቃን ስለተነጠቁት መንጋዎቻችን ሲናገር ደግሞ ልክ የቤ/ክ አካል እንዳልነበረ አድርጎ የለሁበትም ይልናል. ይሄን ድርጊት በስሙ ስንጠራው መመጻደቅ እንለዋለን. ድክመቱንም ጥንካሬውንም ላለመጋራት የሚደረገው ጥረት ተነጥሎ ለመታየት የመፈለግ አጉል መንገድ ከሚባል ውጭ ስም የለውም.
    ቢያንስ መናፍቃኑ ምድር ጠበበን ብለው እነቦንኬን አስጠርተው ወከባ በፈጠሩበት ወቅት ስማቸውን ዘወትር የምትዘለዝሉት ታላቁ አባት አቡነ ጳውሎስ በሰጡት ቀጥተኛ ትእዛዝ ዘመቻ-ፊልጶስ በሚል በየአጥቢያው የወሰድናቸውን መሰረታዊ ኮርሶች አንረሳቸውም. ስለሆነም ማንም መናፍቃንን ብቻየን ተዋጋሁ እያለ ቢፎክር አንሰማውም. ለነገሩ በአንድ መንኩሴ ሀይል በሺ የሚቆጠር ከአረማዊነት የተለመሰ ምእመንን ልክ በማኅበሩ ስብከት እንደተመለሰ አድርጎ ከመለፈፍ ውጭ ይዞታችሁ በሆነው የከተማው አካባቢ አንድም መናፍቅ አስተምራችሁ ስትመልሱ አይተን አናውቅም. እንደውም ከእናንተ በተሸለ መልኩ የየአጥቢያው ካህናትና ሰባክያን ብዙዎችን ወደ ደገኛይቱ ሃይማኖት መልሰው ሲየስጠምቁ አይተናል. ችግሩ እነሱ የሐመር ባለቤት አይደሉም. ስለዚህ አይወራላቸውም.
    ስለለውጥ ጥናቱም ቢሆን ማኅበረቅዱሳን ከመጣ ወዲህ የተጀመረ አይደለም. ድሮም እንቅስቃሴው አለ. የማኅበረቅዱሳንን የሚለየው ወሬው ቀድሞ በየጋዜጣው በመዘራቱ ነው. ውይ ወሬ አለባችሁ. በቅርቡ እንኩዋን የአሁኑ የአንበሳ አውቶቡስ ስ/አስኪያጅ አቶ በድሉ የሚመሩት ጥናት ነበር- ለፍጻሜ ባይበቃም.
    በምንም መመዘኛ ጥናቱ ዳግም ይታይልን ማለት ሌብነትና መናፍቅነት ነው ተብሎ መደምደም የለበትም. ነውር ነው. ፍረጃ ነው. የሐመር ጽሁፍ ይሄን ግዙፍ ስህተት ፈጽሙዋል. ጥናቱ ምንያህል ከቃለዓዋዶው ጋር ይጣጣማል የሚለውንም ሳይመልስ በጎን አልፎታል. ለነገሩ ማኅበሩ ያለበት ሁሉ ቡሩክ ነው ብሎ የሚያስብና ያላየውን ጥናት ሳይቀር ካልተተገበረ ብሎ የሚጮህ ብዙ ቲፎዞ ስላላቸው ያን ያህል መጨነቅ የለባቸውም.
    ሐመር በምዕመኑ ስም ለማስፈራራት ከመነሳት ውጭ በተቃዋሚው ወገን ያለው መከራከሪያ ምን እንደሆነ አጣርታ ለመጻፍ ደንታ የላትም. ምክንያቱም ሌላው ወገን ልሳን ስለሌለው የትም አይደርስም. ስለሆነም ያሻችሁን ስም ትለጥፉበታላችሁ. ደግነቱ ብዙዎቹ ለእናንተ ቦታ መስጠት ከተው ቆይተዋል. ስራ ይበዛባቸዋል. ብዙ አገልግሎታቸውን የሚፈልግ ቅን ምእመን አለ. በሰበካ ጉባኤ፣በህንጻ ኮሚቴ፣በሰንበቴ የታቀፉ የምእመናን ድምጾችን መስማት ይሻላቸዋል.

 11. Anonymous March 4, 2014 at 9:15 am Reply

  I think this is fasting time but why you disiminate false statment like satan .

 12. Anonymous March 5, 2014 at 11:47 am Reply

  ከጥናት ቡድኑ አባላት ውስጥ 6ቱ አቶ፣አንድ ወ/ሮ፣2 ቀሲስ፣4 ዲ/ን. Total=13.የሐመር ሊቃውንት እነኚህ ናቸው. ወይ ሊቅነት. ዲቁና እና ቅስናም ሊቅነት ሆነው ብቅ አሉ. ማዕረጋቱን እናከብራቸዋለን. ግን እውነት እንነጋገር ከተባለ ሊቅ የሚያሰኙ አይደሉም.
  እስከ ቅኔ የተማሩ መባሉም ገርሞኛል. በአይቴ ሀሊፈኪ ድጉዋ ተምህርኪ አሉ አበው. እስከ ማለት ምንድነው. ጉባኤ ቃና ነው ዘአምላኪየ. ወይ ቅኔ የተቀኙ ብትሉ መልካም. ዝምብሎ እስከ የለም. ቅኔ ላይ ለመድረስ የግእዝ ንባብ ማወቅ በቂ ነው፣ ንባብ ማወቅ ደግሞ ሊቅ አያሰኝም. ስለሊቃውንት ተሳትፎ ቀ/ሰሎሞን ሲጠየቅ በብልጠት ማለፉን አድንቄያለሁ. ምንስ ቢሆን በጉባኤ ቤት አልፎ የለ.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: