የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የሕንፃ ግንባታ ጥራትና ሒሳብ ምርመራ እንዲዘገይ የሰጠውን ትእዛዝ የተቃወመው የድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ከሓላፊነቱ ለቀቀ: የሥራ ዘመኑ ሳይጠናቀቅ የለቀቀ ኹለተኛው ሰበካ ጉባኤ ነው!

  • የቁጥጥር አገልግሎቱ የሕዝብ ገንዘብና ንብረት ይመርመር በሚል ልዩ ጽ/ቤቱን እያሳሰበ ነው
  • ልዩ ጽ/ቤቱ ከተልዕኮውና ዓላማው ውጭ የሚንቀሳቀስ አማሳኝ መዋቅር ኾኗል
  • የፓትርያርኩን አንደኛ ዓመት በዓለ ሢመት ለማክበር በሳምንት ርቀት ላይ እንገኛለን

???????????????????????????????ሥራው ሙሉ በሙሉ የቆመውንና በሚልዮን የሚቆጠር የምእመናን ንብረትና ገንዘብ የተመዘበረበትን የድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ ጥራትና ሒሳብ ምርመራ በማዘግየትና በመከላከል አማሳኞችን ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በተደጋጋሚ ባስተላለፈው ትእዛዝ ያዘኑ የደብሩ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት ከሓላፊነታቸው የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸው ተሰማ፡፡

በኹለተኛ የአገልግሎት ዘመኑ ላይ የሚገኘው የደብሩ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት ትላንት፣ የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ረፋድ ላይ ለድሬዳዋ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ባስገቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ÷ በግለሰብ ተጽዕኖና ቁጥጥር ሥር ያለችን ቤተ ክርስቲያን ለማስተዳደር እንደሚቸገሩ በመግለጽ ከትላንትናው ዕለት ጀምሮ ከሓላፊነታቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን የካህናትም የምእመናም ኾና ሳለ ‹‹ፓትርያርኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለግለሰብ አሳልፈው ሰጥተዋታል፤›› በማለት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበሩንና የሕገ ወጥ ጥቅም ተካፋዮቹን መዝባሪነት ለመሸፋፈንና ከተጠያቂነት ለመታደግ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በተደጋጋሚ የሚያስተላልፈውን ተገቢነት የሌለው ትእዛዝ አባላቱ በጽኑ ተቃውመዋል፡፡

ከሒሳቡ ገቢና ወጭ በተጨማሪ ከዲዛየኑ ውጭ እንደተሠራና የግንባታው ጥራትም መፈተሽ እንዳለበት በባለሞያዎች አስተያየት እየተሰጠ መኾኑን የሚገልጹት ምእመናኑ፣ የኦዲት ምርመራው ይዘግይ ቢባል እንኳን የሕንፃ ሥራው ሳይመረመር ከተቋራጩ ተረክቦ ታቦቱን ማስገባት ስለማይቻል፣ በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት ደረጃ ባለውና በገለልተኛ አማካሪ መሐንዲስ ለማስመረመር ግልጽ ጨረታ ካወጡ በኋላ እያደረጉ የሚገኙት የቅድመ ምርመራ ዝግጅት ቀጥሎ ምርመራው መተግበር እንዳለበት በአጽንዖት ገልጸዋል፡፡

የሳባ ደ/ኃ/ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪውን ጨምሮ ካሉት ዘጠኝ አባላት መካከል በትላንትናው ዕለት መልቀቂያቸውን ለሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት በተናጠል ያስገቡት አራት ምእመናን ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ አራቱ የደብሩ አገልጋይ ካህናት ሲኾኑ ነጻ አገልግሎት እንደሚያበረክቱት ምእመናን መልቀቂያ ባያስገቡም ከምእመናኑ ጋራ የአቋም አንድነት እንዳላቸው ተገልጧል፡፡

በውል ከተያዘው ጊዜ ውጭ ለስድስት ዓመታት ከዘገየውና ከስምንት ሚልዮን ብር በላይ ለምዝበራ ከተጋለጠበት ከዚኹ የሕንፃ ሥራ ጋራ በተያያዘ ከአኹኑ በፊት የነበረውና ሕገ ወጥ አሠራርን የተቃወመው ሰበካ ጉባኤ፣ ከቃለ ዐዋዲው ውጭ ተጠሪነታቸውን ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ባደረጉት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ብርሃኔ መሐሪ ግፊትና በቀድሞው ሊቀ ጳጳስ ውሳኔ የሥራ ዘመኑን ሳይጨርስ ታግዶ ከአገልግሎት ውጭ የኾነ ሲኾን ከተመሳሳይ ውዝግብ ጋራ በተገናኘ የሥራ ዘመኑን ሳይጨርስ ከሓላፊነት የለቀቀው የአኹኑ ሰበካ ጉባኤ ሁለተኛው ነው፡፡

የተሟጋች ቡድን ወገን ከኾኑና ቀደም ሲል ከሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው በተቃውሞ ለቀው በወጡ ምእመናን ጥያቄና በቀድሞው የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ፈቃድ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት መምሪያ ኦዲት ቡድን ነሐሴ ፳፮ ቀን ፳፻፫ ዓ.ም. ለወቅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ባቀረበው ሪፖርት÷ ከደንብና መመሪያ ውጭ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለተቋራጩ መከፈሉ ተረጋግጦ አፈጻጸሙ በሀ/ስብከቱና በሰበካ ጉባኤው ሕጋዊ ማስተካከያ እንዲደረግበት መመሪያ ተላልፎ ነበር፡፡

የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ባለፈው ዐርብ ምሽት ለሀ/ስብከቱ በጻፈውና በብፁዕ አቡነ ገሪማ ፊርማ በወጣው ደብዳቤ ግን፣ በዚኽ የኦዲት ሪፖርት ከተገለጹ ግኝቶች በተፃራሪ ‹‹ምንም ችግር እንደሌለ የቤተ ክህነቱ ልኡካን ማረጋገጣውቸውን›› እና ‹‹የሕንፃው ግንባታ ምርመራ ሳያስፈልገው እንዲቀጥልና ታቦቱ እንዲገባ ሒሳቡም ታቦቱ ከገባ በኋላ እንደሚመረመር›› የሚገልጽ ነው ተብሏል፡፡ ዘግይቶ እንደተሰማውም የግንባታ ጥራቱና የወጭና ገቢ ሒሳቡ በምርመራ እስኪታወቅ ድረስ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ላይ የጣለው የገቢ ማሰባሰብ እገዳም የብርሃኔ መሐሪ የጥቅም ተካፋይ እንደኾነ በሚነገረው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ ሓላፊ ደብዳቤ እንዲሻር ተደርጓል፡፡

የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በማይመለከተው ጉዳይ የሰጠው የምርመራ ማዘግየትና መከላከል ትእዛዝ አግባብ እንዳልኾነና ተመዝብሯል የተባለ የሕዝብ ገንዘብ ቋሚ ሲኖዶሱ መስከረም ፱ ቀን ፳፻፮ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት መመርመር እንዳለበት የገለጸው የሀ/ስብከቱ አስተዳደር ኹኔታው ከአቅሙ በላይ እንደኾነ በአዲስ አበባ ለሚገኙት የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ማስታወቁ ተነግሯል፡፡

ሊቀ መንበሩ አቶ ብርሃኔ መሐሪ ከሦስት ተቀጣሪ ሠራተኞቻቸው ጋራ ብቻ በቀሩበት በዚኽ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ የሚፈጸመው ሕጉንና ደንቡን የጣሰ አሠራር፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት ኦዲት ቡድን ከሦስት ዓመት በፊት ባቀረበው ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ በተሰጠው የብፁዕ ዋ/ሥ/አስኪያጁ መመሪያ ሳይስተካከል አኹንም ቀጥሎ በአነስተኛ ስሌት ከብር ስምንት ሚልዮን ግምት ያለው የሕዝብ ገንዘብና ንብረት መመዝበሩን የምእመናን ተሟጋች ቡድን በ፳፻፬ ዓ.ም.፣ የቋሚ ሲኖዶስ ልኡክ በ፳፻፭ ዓ.ም. ባደረጓቸው ክትትሎች መረጋገጡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን ዕድገትና ቅድስና የሚመኙ፣ በተግባርም ለመደገፍና በነጻ ለማገልገል የሚፋጠኑ፣ የተለያዩ ሞያዎች ያሏቸው ምእመናን ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ጀምሮ ወሳኝ መዋቅሮችን በተቆጣጠሩ አማሳኞችና ጎጠኞች የጥቅም ሰንሰለት ተማረው ከአገልግሎት ውጭ መኾናቸው እስከ መቼ???

His Holiness Abune Mathias briefing the pressብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ግንቦት ፳፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሁለተኛው ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ያሰሙትን አስቸኳይ የእርምት ርምጃ ጥሪ መሠረት አድርጎ በቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተቋቋመው የፀረ ሙስናና መልካም አስተዳደር ዐቢይ ኮሚቴ ለጥቅምቱ ፳፻፮ ዓ.ም. ምልዓተ ጉባኤ ባቀረበው የመሪ ዕቅድ ማህቀፍ ከቤተ ክርስቲያናችን ዕሴቶችና መርሖዎች አንጻር የሙስና ትርጉም፣ ሃይማኖታዊ አስተዳደራዊና ሞያዊ ሥልጣንንና ሓላፊነትን አላግባብ በመገልገል የግል ጥቅምን በማካበት ብቻ ሳይኾን ምእመናን በመከፋፈልና በማጋጨት፣ ፍትሕን በማሳጣትና በማዘግየት ተነሣሽነታቸውን መጉዳት፣ ከአገልግሎት ማራቅንና ከሃይማኖታቸው እንዲወጡ መንሥኤ መኾንን ያጠቃልላል፡፡

ቃል የገቡበትንና በሓላፊነት የተረከቡትን ወይም የተሾሙበትን አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ ሥልጣን እና የሞያ ሓላፊነት በመፃረር ንብረትንና ገንዘብን ማባከን ወይም ለግል ጥቅም ማዋል ወይም ለቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ መሳካት ውጤት ያመጣሉ ተብለው ለአገልግሎት የተነሣሱና የተሰለፉ አገልጋዮችና ሠራተኞች ውጤታማ እንዳይኾኑ ግልጽ በኾኑ የተለያዩ መንገዶች ማሰናከል፣ ዕውቀታቸውን ማባከን ኹሉ ሙስና ነው፡፡

ሙስናን በመግታት የቤተ ክርስቲያናችንን መሠረታዊ ተልእኮ ለማስፈጸም የግለሰቦችን ወይም የቡድንን ወይም የአንድን ተቋም አሠራር፣ ጠባይና አስተምህሮ ያጤነ ግንዛቤ መወሰድ እንደሚገባው የሚያሳስበው ገለጻው÷ የተለያዩ የለውጥ አማራጮችን ለመተግበር በታሳቢነት ሊያዙ ይገባል ካላቸው የምእመኑ ክርስቲያናዊና ተጨባጭ ኹኔታዎች መካከል የሚከተለው ሐተታ ይገኝበታል፡-

  • ሙስና የሰለቸው፣ ፍትሕ የተጠማ፣ በሃይማኖቱ  ስም ያሉ ምግባረ ብልሹ አገልጋዮች ያስመረሩት ሕዝብ ነው፡፡ በመኾኑም ፍትሕና ርትዕ በአስቸኳይ ተግባራዊ ኾነው ማየት ይፈልጋል፡፡ ይህን ኹኔታ የሚያሰፍኑ ተግባራዊ ርምጃዎችን ሁሉ ከልቡ ይደግፋል፤ ይሳተፋልም፡፡ ተሳትፎው አሉታዊ እንዳይኾንና በሌሎች ኢ-ክርስቲያናዊ አጀንዳ ባላቸው ኃይሎች እንዳይጠለፍ ጥበቃ፣ መረጃና፣ ሰፋ ያለ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
  • መንፈሳዊና እግዚአብሔርን የሚፈራ ሕዝብ ነው፡፡ በመኾኑም ከላይ የተከበሩና ከሐሜት ነጻ በኾኑ አባቶች የሚነገረውን በተግባር ተፈጽሞ እስከተመለከተ ድረስ ያለማወላወል ገንዘቡን፣ ጊዜውነና ዕውቀቱን ለመስጠት የተዘጋጀ ሕዝብ ነው፡፡ በመኾኑም በለውጡ የሚነገሩ ዜናዎችና የታወጁ የለውጥ አቅጣጫዎች ኹሉ እየተፈጸሙ የሚታዩ መኾን ይገባቸዋል፤ የማይደረግ መነገር የለበትም፤ እምነት ያጎላልና፡፡

የስድስተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን አንደኛ ዓመት በዓለ ሢመት ለማክበር በሳምንት ርቀት ላይ እንገኛለን፡ ከቤተ ክርስቲያናችን ክብርና ቅድስና ጋራ የማይጣጣመውን የቤተ ክህነቱን አስተዳደራዊ ብልሽት በሥር ነቀል የማስተካከያ ርምጃዎች ማረም ፓትርያርኩ ከበዓለ ሢመታቸው ቀን ጀምሮ ቀዳሚ ትኩረት የሰጡት አጀንዳ ነው፡፡

አማሳኝነትና ጎጠኝነት መገለጫው ያደረገ ቢሮክራሲን መስተካከል በአጭር ጊዜ ለማምጣት አዳጋች ቢኾንም የቤተ ክህነቱን የተቋማዊ ለውጥ መሠረት ማስቀመጥና አቅጣጫውን መቀየስ እጅግ አስፈላጊ፣ እጅግ አስቸኳይ መኾኑን ቅዱስነታቸው በመግለጫዎቻቸው አሳስበዋል፡፡ በቆሙባቸው መድረኮች ኹሉ ሓላፊነት፣ ሐቀኝነትና ተጠያቂነት የተሞላበት መልካም አስተዳደር ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እስከ መንበረ ፓትርያርክ እንዲሰፍን ደጋግመው ተናግረዋል፤ እንዲያውም ‹‹መልካም አስተዳደር ከሌለ ኹሉም ነገር ከንቱ እንደኾነ እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡

ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ እንደተነሣው ኹሉ ለመልካም አስተዳደር መስፈን ምዕራፍ ከፋች በኾነችው በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ ልናደርግ የሚገባንን ምግባረ ሠናይ ኹሉ በመፈጸምና በማስፈጸም በያለንበት ደጀንነታችንን ለማረጋገጥ መነሣሣት እንደሚጠበቅብን አባታዊ ትምህርት፣ መመሪያና ቃለ በረከት ሰጥተውናል፡፡

ከቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ ተልዕኮ ጋራ የሚጣጣም ሥር ነቀል የለውጥ ርምጃ በቆራጥነት ተግባራዊ ለማድረግ ታስቦ በፓትርያርኩ ፊታውራሪነትና በቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ በተቋቋሙት የፀረ ሙስና፣ የአስተዳደር መሻሻል እና የገንዘብ አያያዝ ሥርዐት ማሻሻያ ዐበይት ኮሚቴዎች ተደራጅቷል፡፡ ዛሬ ከአንድ ዓመት በኋላ የት ነን? ከቃለ ነቢብ(rhetoric) ውጭ ምን የተግባር ርምጃ አስመዘገብን? ምን ውጤት አገኘን?

 

Advertisements

One thought on “የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የሕንፃ ግንባታ ጥራትና ሒሳብ ምርመራ እንዲዘገይ የሰጠውን ትእዛዝ የተቃወመው የድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ከሓላፊነቱ ለቀቀ: የሥራ ዘመኑ ሳይጠናቀቅ የለቀቀ ኹለተኛው ሰበካ ጉባኤ ነው!

  1. Anonymous February 24, 2014 at 7:22 am Reply

    The construction of the church is about to be completed. The picture posted here may be taken before three or four years. We all agree that it is the biggest church in Eastern Ethiopia. The community understood how the construction delayed, mainly because of the higher cost of construction materials. We are confused how the issue of auditing is becoming burning issue while the church will be inaugurated after two months. Let us fear God who can see the covered and the uncovered. I appreciate the tolerance of the church construction committee unlike the “sebeka Gubaye” members who left their position because they felt to realize their rigid idea.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: