የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ ዳግመኛ ተሻረ! የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ሕንፃ ግንባታ እንዳይመረመር ለሁለተኛ ጊዜ ተከላከለ! የከተማው ምእመን የደብሩን ጉዳይ በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት ለመፍታት አንድነቱን አጠናክሯል!

Bidding documentየፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በጓሮ በር ለሚገቡ ሙሰኞችና ጎጠኞች ሽፋን መስጠቱን ቀጥሎበታል፡፡ ልዩ ጽ/ቤቱ እንደቀድሞው ጊዜ ኹሉ ዛሬም በማይመለከተው ጉዳይ ጣልቃ እየገባ የቅ/ሲኖዶሱን ልዕልና የሚጋፋ የሕገ ቤተ ክርስቲያን ጥሰት እየፈጸመ ይገኛል፡፡

ሙሰኞችና ጎጠኞች የበላይነት ይዘው በተቆጣጠሩት ልዩ ጽ/ቤት የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ በመተላለፍ የሚፈጸመው ኢ-ፍትሐዊ ተግባር፣ የመንበረ ፓትርያርኩን ተቀባይነትና አገልጋዩና ምእመኑ በመልካም አስተዳደር መስፈን ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር መንሥኤ እየኾነ ይገኛል፡፡

ከላይ የምትመለከቱት፣ የድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የሕንፃውን ሒሳብና ግንባታ በአማካሪ ድርጅት ለማስመርመር የካቲት ፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በኢትዮጵያን ሄራልድ እና በአዲስ ዘመን ጋዜጦች ያወጣው የጨረታ ማስታወቂያ ነው፡፡ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ ከአማካሪ ድርጅቱ ጋራ በውል ከተያዘው ጊዜ ከስድስት ዓመት በላይ የዘገየና በሚልዮኖች የሚቆጠር የሕዝብ ገንዘብ የተዘረፈበት ነው፡፡ ይህንንም÷ በምእመናን ተሟጋች ቡድን፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎትና በቋሚ ሲኖዶሱ የተሠየመው ልኡክ በተለያየ ጊዜ ያካሔዱት ተደጋጋሚ ማጣራት በጉልሕ ያስረዳል፡፡

ቋሚ ሲኖዶሱ በእኒኽ ተደጋጋሚና ተደጋጋፊ ሪፖርቶች ላይ በመመርኮዝ የሕንፃ ግንባታው ጥራትና ሒሳብ በብቁና ገለልተኛ ባለሞያ እንዲመረመር መስከረም ፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ውሳኔ አስተላልፏል፤ ውሳኔውም ተፈጻሚ እንዲኾን የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለደብሩ አስተዳደር መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዚኽም መሠረት ምርምራ የሚያከናውነውን ድርጅት በውድድር ለመለየት የካቲት ፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ግልጽ ጨረታ ወጥቷል፡፡

Lique Tiguhan Birhane Mehari00

የፓትርያርኩን ልዩ ጽ/ቤት በጥቅመኝነት የተቆጣጠረው ብርሃኔ መሐሪ መዝባሪነቱ የሚጋለጥበትን የኦዲት ምርምራ ለማስተጓጎል እየተሟሟተ ነው

ይኹንና የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴውን ከሰበካ ጉባኤውና ከሀ/ስብከቱ ቁጥጥር ውጭ በማድረግና ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ ጋራ በመመሳጠር ምእመናን በገንዘብና በዐይነት ለግንባታው የሚያበረከቱትን አስተዋፅኦ ለግል ጥቅሙ ሲያካብት የቆየው ሊቀ መንበሩ ብርሃኔ መሐሪ፣ ምርመራው እስከ ግንባታው ፍጻሜ እንዲዘገይ የሚያዝ ደብዳቤ ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በማጻፍ ሒደቱን ለማስተጓጎል ሙከራ አድርጓል፡፡

የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ የሚፃረረውን የፓትርያርኩን ልዩ ጽ/ቤት ትእዛዝ ያልተቀበሉት የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የቅድመ ምርመራው ዝግጅት እንዲቀጥል መመሪያ በመስጠታቸው ግልጽ ጨረታ ወጥቶ የጨረታው ሰነዶች እየተሸጡ ባለበት ኹኔታ፣ መዝባሪው ብርሃኔ መሐሪ ለኹለተኛ ጊዜ ወደ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በመሔድና የተለመደውን ኔትወርኩን በመጠቀም ምርመራው እስከ ግንባታ ፍጻሜው ድረስ እንዲዘገይ አስቀድሞ የተላለፈው ትእዛዝ እንደጸና መኾኑን የሚያሳስብ ሌላ የትእዛዝ ደብዳቤ ዳግመኛ በማጻፍ በፋክስ ለድሬዳዋ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት እንዲደርስ አድርጓል፡፡

ከትላንት በስቲያ ምሽት ለሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት የደረሰው የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ደብዳቤ ምርመራው እንዲዘገይ ማዘዝ ብቻ ሳይኾን ሌላ አስደንጋጭም አሳዛኝም ይዘት አለው – ‹‹ፓትርያርኩ በሰጡት መመሪያ መሠረት›› በሚል በልዩ ጽ/ቤቱ የበላይ ሓላፊና በቀድሞው የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ፊርማ የወጣው ደብዳቤው፣ በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ላይ የኦዲት ምርመራ ግኝቶች የሚያረጋግጡትን ደንብና አሠራር የጣሰ ክፍያ በመካድ ‹የድንቢጧን ምስክርነት› ለመስጠት የደፈረ ኾኖ ተገኝቷል፡፡

ነሐሴ ፳፮ ቀን ፳፻፫ ዓ.ም. የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የኦዲት ምርመራ ቡድን ባቀረበው ባለ47 ገጽ ሪፖርት ግንባታውን ለማጠናቀቅ በውሉ ከተገለጸው 2‚984‚562.51 ሌላ 1‚864‚372.33 ተጨማሪ ገንዘብ ለኮንትራክተሩ ወጭ ኾኖ መከፈሉን ያረጋገጠውና በወቅቱ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊልጶስ የአፈጻጸም ማስተካከያና የቅርብ ክትትል እንዲደረግበት ለሀ/ስብከቱና ለሰበካ ጉባኤው መመሪያ የተሰጠበት የኦዲት ግኝት ልዩ ጽ/ቤቱ ‹‹ምንም ችግር የለበትም›› በሚል በደብዳቤው ከደመሰሳቸው ሐቆች ተጠቃሹ ነው፡፡???????????????????????????????

የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ በመፃረር ከመዝባሪው ብርሃኔ መሐሪ ጋራ መቆሙን ያረጋገጠበት ይኸው ደብዳቤ በሀ/ስብከቱ አድባራትና በድሬዳዋ አገልጋዮችና ምእመናን ዘንድ መሰማቱን በመንበረ ፓትርያርኩ ላይ ተከትሎ ከፍተኛ ምሬትና ቁጣ መቀስቀሱ ተነግሯል፡፡ ‹‹የሕዝብ ገንዘብ አታስመርምር የሚለኝ የለም፤ በአንድ ጉዳይ ላይ ተፃራሪ ውሳኔዎችን ለማስተናገድ አልችልም፤ ቋሚ ሲኖዶሱ እንደወሰነው አጥቢያው ሥራውን (የቅድመ ምርመራ ዝግጅቱን) እንዲቀጥል መመሪያ ሰጥቻለኹ፤›› ያሉት ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ልዩ ጽ/ቤቱ ዳግመኛ ያስተላለፈውን ትእዛዝ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፡፡

ባልተማረው ትምህርትና በሌለው ሥልጣን ራሱን በመሾም የሚታወቀው መዝባሪው ብርሃኔ መሐሪ፣ ብቃት ያለውና ገለልተኛ የኾነ አማካሪ ድርጅት በግልጽ አሠራር ተለይቶ ምርመራው እንዲካሔድ ለደብሩ አስተዳደር መመሪያ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ በፍ/ቤት ውሳኔ ከቀረበባቸው ውንጀላ ነጻ በኾኑ ግለሰቦች ጉዳይ ሳይቀር ሊቀ ጳጳሱን በፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት እየከሠሠ ከሓላፊነት ለማሥነሳት፣ በደብሩ አስተዳዳሪ ላይ ደግሞ አካላዊ ጥቃት ለማድረስ እየዛተ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ውዝግቡን በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት በተጀመረው መንገድ ለመቋጨት የቆረጠው አገልጋዩና ምእመኑ በተለያዩ ጊዜያት የተካሔዱ የኦዲት ምርመራዎችንና የማጣራት ሪፖርቶችን የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት አላግባብ ከጻፋቸው ደብዳቤዎች ጋራ በመያዝ ወደ ከተማው አስተዳደርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ቅርንጫፍ ቢሮዎች ለማምራት መዘጋጀቱ ከስፍራው እየተገለጸ ይገኛል፡፡

Advertisements

One thought on “የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ ዳግመኛ ተሻረ! የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ሕንፃ ግንባታ እንዳይመረመር ለሁለተኛ ጊዜ ተከላከለ! የከተማው ምእመን የደብሩን ጉዳይ በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት ለመፍታት አንድነቱን አጠናክሯል!

  1. Anonymous March 24, 2016 at 11:41 am Reply

    ውድ የኦርቶዶክ ተዋህዶ ብርቅዬ ልጆች ናችሁና የእናታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ልጅ መድኃኔኣለም ክርስቶስ ብርታቱን ያድላችሁ ለፈተናው እንዳትንበረከኩ ብርታቱን ለማህበረ ቅዱሳን ልጆች ውድቀትን ለአማሳኞች ይስጥልን ብርት ሲቀጠቀጥ ይጠነክራል የተዋህዶ ልጆችም እንደብረት ነን ሳጥናኤል አትፎክር መውደቅህ አይቀርምና ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: