ቅ/ሲኖዶሱ የሀገረ ስብከቱን የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነድ ተረከበ

 • የአብዛኞቹ የአብነት መምህራን የጤና ችግር ከዐይን እክል ጋራ የተያያዘ ነው
 • ‹‹የተለያዩ የጤና ምርመራዎች ከተደረገላቸው 170 መምህራን ከ70 በላይ የሚኾኑት የካታራክት እና ትራኮማ ተጠቂ ናቸው፤ ዋነኛ መንሥኤው ኬሚካል ተቀላቅሎበት የሚመረት የጧፍ ጢስ ነው፤ ክብካቤና ክትትል ካልተደረገላቸው ለዐይነ ስውርነት ያደርሳቸዋል፡፡›› /የማኅበረ ቅዱሳን ሞያ አገልግሎት የሕክምና ቡድን/

(ሰንደቅ፤ የካቲት ፲፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)

sendek logoየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተሠራውን የመዋቅር የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት ሰነድ ከሀገረ ስብከቱ ጋራ መረካከቡ ተገለጸ፡፡

ባለፈው ሳምንት ዐርብ ፓትርያርኩ በርእሰ መንበርነት በሚመሩት የቋሚ ሲኖዶሱ ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የመዋቅር የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት ሰነዱን ለቅዱስ ሲኖዶሱ ያስረከቡት በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የጅማ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ናቸው፡፡ ጥናቱ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመራ በቂ ሕግ ነው ተብሎ በቅ/ሲኖዶሱ ሲታመንበት ጸድቆ እንደሚተገብር ሊቀ ጳጳሱ አስታውቀዋል፡፡

የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናቱ፣ በአራት ተከፍሎ የነበረው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ወደ አንድ እንዲመጣ በቅ/ሲኖዶስ ከተወሰነ በኋላ ለሦስት ወራት የሽግግር ጊዜ የተሠራውን የአደረጃጀትና ተቋማዊ መዋቅር የሙከራ ትግበራ ተከትሎ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መመሪያና ቡራኬ በተቋቋመና 13 የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሞያ አባላት ባሉት አጥኚ ቡድን የተዘጋጀ መኾኑ ተመልክቷል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደር በኹሉም ዘርፍ በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለባቸውና በቋሚ ሲኖዶሱ ላይ ርክክብ የተካሔደባቸው የመዋቅር የአደረጃጀት የአሠራር ጥናት ሰነዶች ብዛት ዐሥራ ሦስት ሲኾን ከአንድ ሺሕ ገጽ ያላነሰ ጠቅላላ ብዛት ያላቸው እንደኾኑ ከቋሚ ሲኖዶሱ ርክክብ አንድ ቀን አስቀድሞ በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት በተካሔደ መርሐ ግብር ላይ ተገልጧል፡፡

His Grace Abune Estifanos with the 12 documentsየጥናት ሰነዶቹም የአደረጃጀትና የመዋቅር ጥናትና መመሪያ፣ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ደረጃ መስፈርት ጥናትና መመሪያ፣ የአገልግሎት መደቦች የሥራ ዝርዝር ሰነድ፣ የተፈላጊ ችሎታ መመሪያና የሰው ኃይል ትመና ሰነድ፣ የደመወዝ ስኬል ጥናት ሰነድ፣ የአገልጋዮች ማስተዳደርያ፣ የፋይናንስ፣ የልማት ሥራዎች፣ የግዥ፣ ሽያጭና ንብረት አስተዳደር፣ የዕቅድ ዝግጅት፣ ሪፖርትና ግምገማ፣ የኦዲትና ኢንስፔክሽን ፖሊሲዎችና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያዎች እንዲኹም የሥልጠና ማእከልና የአረጋውያንና የሕፃናት መርጃ ማእከል ፕሮጀክት ጥናት ሰነድ እንደኾኑ ተዝርዝሯል፡፡

የጥቅምት ቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ለጥናቱ በሰጠው ይኹንታና በሰጠው አቅጣጫ መሠረት የጥናት ሰነዱ ለርክክብ ከመቅረቡ አስቀድሞ÷ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያና ድርጅት ሓላፊዎችን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ሓላፊዎች፣ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች፣ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ የሀገረ ስብከቱ ማኅበረ ካህናት፣ ማኅበረ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እንደተወያዩበት ተገልጦአል፡፡

በውይይት የተነሡት ሐሳቦች በአግባቡ ተመዝግበውና ተገምግመው በእያንዳንዱ የመዋቅርና የአሠራር መመሪያ ውስጥ እንዲካተቱ መደረጉን የባለሞያ ቡድኑ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ አሰፋ ያስረዱ ሲኾን ለ14 ቀናት በጥናቱ ላይ በተካሔደው ውይይት 96 በመቶ ተቀባይነት እንዳገኘ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ጥናቱን እንድናደርግ የተሰጠን ዕድል ታሪካዊ ነው፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ ችግር ፈቺ እንደኾነ ለሚያምኑበት የጥናት ሰነድ ዝግጅት መሳካት አስተዋፅኦ አድርገዋል ያሏቸውን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የሀገረ ስብከቱን ሓላፊዎችና አገልጋዮች እንዲኹም የለውጥ እንቅስቃሴውን ያስጀመሩትንና ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በኹሉ ነገር አልተለዩም ያሏቸውን ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን አመስግነዋል፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ  እንደወሰነውም በካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች አስተያየት ዳብሮ የቀረበው የጥናት ሰነዱ በቋሚ ሲኖዶሱ ጸድቆ ወደ ተግባር ይገባ ዘንድ አደራ ብለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ በትውፊታዊውና ጥንታዊው የቤተ ክርስቲያኒቱ የትምህርት ማእከላት በኾኑት አብያተ ጉባኤያት ወንበር ተክለው የሚያስተምሩ የአብነት መምህራን ዋነኛ የጤና ችግር ከዐይን እክል ጋር የተያያዘ መኾኑን ሰንደቅ የደረሰው መረጃ ጠቁሟል፡፡

An Accomplished Scholars of the Ethiopain Orthodox Tewahido Church Traditional Schools

አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል የውስጥና የውጭ ተባባሪዎቻቸውን አሰልፈው በፓትርያርኩ ደብዳቤ ያሳገዱት የሦስተኛው ዙር ሀገር አቀፍ የአብነት መምህራን ጉባኤ ተሳታፊ የምስክር ሊቃውንት በማኅበረ ቅዱሳን የዋናው ማእከል ጽ/ቤት በራፍ

ማኅበረ ቅዱሳን ለሦስተኛ ጊዜ ባዘጋጀውና በፓትርያርኩ ደብዳቤ እንደታገደ በተገለጸው የአብነት መምህራን ሀገር አቀፍ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ከኹሉም አህጉረ ስብከት ተውጣጥተው ወደ አዲስ አበባ ከመጡት 202 የምስክር መምህራን መካከል ለ170ዎቹ ተሳታፊዎች የጤና ምርመራ መደረጉን መረጃው ያመለክታል፡፡

W.ro Alemtsehay Meseret, Deputy Board Chair of Kidusat Mekanat Limat ena Mahiberawi Agelgilot

ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት 

የማኅበረ ቅዱሳን ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ

የንዋያተ ቅድሳት ምርት ከቤተ ክርስቲያናችን የገቢ ማስገኛ ዘዴዎች በአማራጭነት ሊካተት ይችላል፡፡ ንዋያተ ቅድሳት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቅዳሴና በልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች የምትጠቀምባቸውን ግብአቶች ያጠቃልላል፡፡ እነዚህ ግብዓቶች ቤተ ክርስቲያን ካላት መንፈሳዊ አገልግሎት÷ ቅዳሴ፣ ክርስትና፣ ተክሊልና ፍትሐት ስፋት እንዲኹም የምእመናኑና የአብያተ ክርስቲያኑ ብዛት ከግምት ስናስገባው ከፍተኛ ምርትንና ሽያጭን ይጠይቃል፡፡

ምርቱና ሽያጩ ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የገቢ ምንጭ ለመፍጠር ብቻ ሳይኾን የአመራረቱን ትውፊትና ሥርዐት ለመጠበቅ፣ ከከተማ ውጭ ያሉትን ገዳማትና አድባራት የንዋያተ ቅድሳት እጥረት ለመቀነስ በከፍተኛ ኹኔታ ያግዛል፡፡

ለዚኽ ገለጻ ተብሎ በተሰበሰበው መረጃ መሠረት፣ በአኹኑ ሰዓት ንዋያተ ቅድሳት በገበያ ላይ ለሽያጭ የሚቀርቡት 95% ከቤተ ክርስቲያን ጋራ ምንም ግንኙነት በሌላቸው ለትርፍ በተቋቋሙ ወይም በሚሠሩ የግል አቅራቢዎች ወይም አምራቾች ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል፡- 95 በመቶ የጧፍ ምርት በአብዛኛው ከመርካቶ የግል አቅራቢዎች የሚቀርብ ነው፡፡

ምእመናን በአነስተኛ ግምት በዓመት ወደ 93 ሚልዮን ብር ለጧፍ ግዥ ያወጣሉ፡፡ ከ93 ሚልዮን ብር ሽያጭ 20 ሚልዮን ብር ትርፍ ይገኛል ተብሎ ሊሰላ ይችላል፡፡ ይህ ትውፊቱን ጠብቆ በቤተ ክርስቲያን ካህናት ተመርቶ ቢኾን ኖሮ የካህናቱም ገቢ በዚኹ መጠን ያድግ ነበር፡፡

የጧፍ ምርት፡- የሰው ኃይል፣ የፈትል ክር፣ ሰም ወይም ዋክስ በአካባቢ በሚሠራ ቴክኖሎጂ በመጠነኛ ዋጋ የሚዘጋጅ ነገር ግን ኹሌም ገበያ ያለው ምርት ነው፡፡ የተለየም ሞያ የማይጠይቅ ሥራ ነው፡፡ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ካህናት፣ የካህናት ሚስቶች በቀላሉ ሥልጠና ቢሰጣቸው ኑሯቸውን ሊያሻሽሉ ይችላሉ፡፡

ጧፍ በቤተ ክርስቲያን ካለመመረቱ የተነሣ በአኹኑ ሰዓት አምራቾች የሚጠቀሙበት የሰም ዋጋ ውድ ከመኾኑ ጋራ ተያይዞ ትውፊቱን ለመጠበቅ የሚያስችል ምክንያት ስለሌላቸው በአብዛኛው ሻማና ሞራ እንዲኹም ልዩ ልዩ ኬሚካሎች በመጠቀም ጣፉን በማምረት ላይ ናቸው፡፡ ይህም ከጧፉ ጢስ ጋራ በተያያዘ ካህናትን ለጤና ችግር እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት የጧፍ ማምረቻ ማሽን ፈብርኮ በየዓመቱም 250‚000 ጧፍ ከሰም ያመርታል፡፡ ምርቱን ለማምረት ለሚፈልጉ አብያተ ክርስቲያናት የማሽን ሥራና ሥልጠና ይሰጣል፡፡

/የምጣኔ ሀብትና የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ባለሞያዋ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ በ፴፪ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ‹‹በቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ አነስተኛ የገቢ ማስገኛ ዘዴዎችን ተግባራዊ ስለማድረግ›› በሚል ርእስ ካቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ የተወሰደ/

 

ማኅበሩ በሀገር አቀፉ ጉባኤ ዝግጅት መልካም አጋጣሚ በጽ/ቤቱ ባቋቋመው ጊዜያዊ ክሊኒክ ለተስተጓጎለው ጉባኤ ተሳታፊዎች የዐይን፣ የውስጥ ደዌ፣ የነርቭ፣ የአጥንትና ሌሎችም የበሽታ ዐይነቶች ላይ በተሟሉ የሕክምና መሣርያዎችና በየዘርፉ ስፔሻሊስቶች ባካሔደው ቅድመ ምርመራና ክትትል ከ70 በላይ የአብነት መምህራን ካታራክት እና ትራኮማ ችግር እንዳለባቸው ተረጋግጧል፡፡

ምርመራውን ያካሔዱት የማኅበሩ የሞያ አገልግሎት ዋና ክፍል የሕክምና ቡድን አባላት÷ የአብነት መምህራኑ በየአብያተ ጉባኤያቸው ለብርሃን ምንጭነት የሚጠቀሙባቸው ከንጹሕ ሰም ያልተሠሩና ቀለም ተቀላቅሎባቸው የሚመረቱ ጧፎች ጢስ፣ ባነሰ አልያም በድንግዝግዝ ብርሃን ማንበባቸው፣ የግል ንጽሕና አጠባበቅና ዕድሜ ከዐይን ጋራ ተያይዞ በስፋት ለታየው እክል በመንሥኤነት ዘርዝረዋል፡፡

ክብካቤና ክትትል ካልተደረገ ለዐይነ ስውርነት ለሚዳርገው ይኸው የዐይን እክል ከተለየላቸው ከ70 በላይ መምህራን ለ50ዎቹ የንባብና የፀሐይ መነጽሮች ታድሏቸዋል፤ ከዐሥር ሺሕ ብር በላይ ግምት ያላቸው መድኃኒቶችም ተበርክቶላቸዋል፤ መነጽር ላልደረሳቸውም የስፖንሰርሽፕ ድጋፍ ተጠይቋል፡፡

መምህራኑና ተማሪዎቻቸው ከሚጠቀሙባቸው ያልታከመ የወንዝና የምንጭ ውኃ ጋራ የተያያዙ ውኃ ወለድ የሆድ ሕመሞች፣ የቆዳ በሽታዎች በዚኹ አጋጣሚ በተደረገ የጤና ምርመራ ታውቀው ጊዜያዊ መድኃኒት መሰጠቱ ተነግሯል፡፡

ምርመራውን ከምኒልክ ሆስፒታልና ሌሎች የግል የሕክምና ማእከላት ጋራ በመተባበር ማከናወኑን የገለጸው የሕክምና ቡድኑ፣ መምህራኑ እንደሚገኙባቸው አብያተ ጉባኤያት ርቀትና ቅርበት በተለይ ለዐይናቸው ጤንነት የሚያደርገውን ክትትል እንደሚቀጥልበት ገልጧል፤ በመጪው ወርኃ ጾምም በየአህጉረ ስብከቱ በግል ጤና አጠባበቅና በመከላከል ላይ ያተኮረ የሃይጅን/የጤና አጠባበቅ ሥልጠና ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም አመልክቷል፡፡

Advertisements

2 thoughts on “ቅ/ሲኖዶሱ የሀገረ ስብከቱን የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነድ ተረከበ

 1. kk February 21, 2014 at 12:12 pm Reply

  bravo MK, you are doing great!!!

 2. Ras Berhanu August 21, 2017 at 3:57 pm Reply

  ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ በወ/ሮ ዓለምፀሐይ መሠረት የማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ሓላፊ ለ32ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች በጥናት መልክ ቀርቦ ለ33ኛው ጉባኤ በተዘጋጀው ዐዋጅ ነጋሪ መጽሔት 7ኛ ዓመት ቁጥር 10 ጥቅምት 2007 የተወሰደ ነው፡፡

  የገቢ ማስገኛ ዘዴ ማለት፡- ዓላማው ትርፍን ሊያስገኝ የሚችል የሥራ ዘርፍ ማለት ነው፡፡

  የገቢ ማስገኛ ዘዴ ማለት ማንኛውም ሥራ ሆኖ ነገር ግን ዓላማው ትርፍ ማግኘትና ሰዎች በገንዘባቸው ሊገዙት፣ ሊቀይሩት የሚችሉት ምርት አገልግሎት በማቅረብ ትርፍ የምናገኝበት ሥራ ነው፡፡

  አነስተኛ የገቢ ማስገኛ ዘዴ ትርፍ ሊያስገኝ የሚችሉ የሥራ ዘርፎችን በሚከተታተል ሁኔታ መቋቋም መቻል ነው፡፡

  በተለይ አንስተኛ የገቢ ማስገኛ ማቋቋም የሚከተሉት ጠቀሜታዎች አሉት፡-
  በመጠነኛ በትንሽ ኢንቨስትመንት ወይም ወጭ ሥራ መፍጠር
  የአካባቢን ማኅበረሰብ በሥራ ማሳተፍ መቻሉ
  በአካባቢ በሚገኝ ሀብትና ቴክኖሎጂ በቀላሉ ወደ ምርት መቀየር መቻሉ
  በዝቅተኛ ወጭ ሥልጠና መስጠት መቻሉ
  አነስተኛ የገቢ ማስገኛ ዘዴዎችን ተግባራዊ ማድረግ ለዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ እድገት ዘላቂነት ያለው ዋነኛ ድርሻ እያበረከተ መጥቷል፡፡ ለምሳሌም ዛሬ በአውሮፓ ኅብረት ሀገሮች 25 ሚሊዮን የሚሆኑ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ይገኛሉ፡፡ ለ75 ሚሊዮን ዜጎችም የሥራ እድል ፈጥረዋል፡፡ ከፍተኛ እድገት በማስመዝገብ ላይ ባለችው ሲንጋፖር አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የሀገሪቱን ምርት 47 በመቶ ይይዛሉ፡፡ 62 በመቶ የሥራ እድል ፈጥረዋል፡፡ የሕዝብ ብዛት ባላቸው በቻይናና በሕንድም ያለው ተሞክሮ ተመሳሳይነት አለው፡፡ በአገራችን የኢኮኖሚ እድገትም ዜጎችን በአነስተኛ ጥቃቅን እንዲሳተፉ በርካታ ማበረታቻም እየተደረገ ይገኛል፡፡

  አነስተኛ የገቢ ማስገኛ ዘዴዎችን ለዜጎች ሥራ በመፍጠር በቂ ገቢ እንዲያገኙና ከድህነት እንዲወጡ ከማድረጉም ባሻገር ሰዎች ለመንፈሳዊና ማኅበራዊ ቀውስ እንዳይጋለጡ ከ10 ዓመታት ወዲህ ዋነኛ መፍትሔ እየሆነ መጥቷል፡፡ የዳበረ ማኅበራዊ ዋስትና በመኖሩ ምክንያት ሥራ የሌላቸው ዜጎችን ወይም ሥራን በፍቃድ በመተው በመንግሥት የገንዘብ ድጎማ የሚተዳደሩ ዜጎች ላይ ለልዩ ልዩ ማኅበራዊ ቀውሶች እየተጋለጡ በመምጣታቸው አውሮፓ ሀገር ዜጎች ያለሥራ የሚያገኙትን ማኅበራዊ ዋስትና ጊዜ እንዲያጥር በሥራ እንዲጠመዱ የሚያስችል አዳዲስ ፖሊሲዎች እንዲቀረጹ ሆኗል፡፡ ከዚህም መካከል ዜጎች በሥራ እንዲጠመዱ በአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲሳተፉ ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችን ማድረግ ነው፡፡ ዛሬ በአውሮፓ አገሮች ኢኮኖሚ 60 እስከ 70 የሚሆነው ገቢያቸው በአነስተኛና በመካከለኛ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲመሠረት ሆኗል፡፡

  አብያተ ክርስቲያናት በገቢ ማስገኛ ዘዴዎች እንዱሳተፉ መሆናቸው ድህነትን ከመቀነስ ባሻገር በተለይ በገቢ ራሳቸውን ችለው ለአማንያን ምቹ ሁኔታ ፈጥረው ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ያስችላል፡፡
  አብያተ ክርስቲያናት ወደ ገቢ ማስገኛ ልማት ሥራዎች ከመግባታቸው በፊት በቅድሚያ ምን የሀብት ዓይነት እንዳላቸው እና እንደሌላቸው መለየት እጅግ አስፈላጊ ነው ይህም ምን መሥራት እንዳለባቸው ያቀዱትን ሥራ ለመሥራት፣ ምን እንደሚጎድል ለማወቅ ያስችላቸዋል፡፡

  የገቢ ማስገኛ ዘዴ ሐሳብን ስለማፍለቅና ስለ መምረጥ
  ሀብትን ለመጠቀም የሚያስችሉ በአካባቢያችን ያሉ በጎ አጋጣሚዎች ወይም እድሎችን ለመለየት ምን ጊዜም ቢሆን አካባቢን መቃኘትና ያለንን ሀብት በአግባቡ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ በአካባቢያችን ያለውን ሀብት መሠረት በማድረግ አማራጭ የገቢ ማስገኛ ዘዴዎችን መንደፍ እንችላለን፡፡

  የንግድ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች ከአካባቢያችን በመምረጥ እንዲሁም በሙያ የሚያግዙትን ሰዎች በመያዝ በእያንዳንዱ በቀረበው ሐሳብ ላይ ውይይት ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ጊዜ መውሰድና ማጥናት ያስፈልጋል፡፡
  የሚከተሉት ነጥቦች የቀረበውን ሐሳብ ለማመዛዘን ያግዙናል፡፡
  ምን፡- ለሽያጭ ያዘጋጀነው /የምናመርተው የምንሰጠው አገልግሎት
  ለማን፡- የምርታችን ተጠቃሚ ማን ነው? የትኛውን የግዥ ፍላጎት ነው የምናሟላው
  እንዴት፡- እንዴት እናመርታለን? ምርታችንንስ ውጤት በምን መልኩ ለተጠቃሚያችን እናቀርባለን?
  የገቢ ማስገኛ ዘዴ ወይም ዕቅድ
  የገቢ ማስገኛ ዘዴ ወይም ዕቅድ ገቢ እንዲያስገኝልን ያሰብነው የሥራ ዓይነት ተግባራዊ ከማድረጋችን በፊት ለሥራው በቂ ሀብት መኖሩንና በቂ ገቢ ማስገኘት መቻሉን ማረጋገጥ ያስፈልገናል፡፡ ገቢ እንዲያስገኝልን ያሰብነውን የሥራ ዓይነት ተግባራዊ ከማድረጋችን በፊት ለሥራው በቂ ሀብት መኖሩን በቂ ገቢ ማስገኘት መቻሉን የምናይበት ወይም የምናረጋግጥበት እቅድ ወይም ሰነድ ነው፡፡

  የገቢ ማስገኛ ዘዴ ዕቅድ የሚከተሉትን ዝርዝር ጉዳዮች ይይዛል፡፡
  የሥራው ዓይነት ምን እንደሆነ/ከመንፈሳዊ አገልግሎት ጋር የማይጋጭ መሆን ይኖርበታል፣
  እነማንን በምርቱ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ፣
  የገበያውን ሁኔታ/ምርቱ የት እንደሚሸጥ
  ለምርት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በቀላሉ መገኘት መቻላቸው
  በቅርበት ከኛ በተሻለ ሁኔታ ያሰብነውን ሥራ ማቅረብ የሚችል ሰው ወይም ድርጅት መኖሩን
  ምርትን ወደ ገበያ ለማቅረብ አመች ሁኔታ መኖሩን፣
  ያሰብነው ሥራ ማን ያስተዳድረዋል እራሳቸውን ችለው የሚወከሉ ሠራተኞችን መመደብ መቻሉን፣
  ወደፊት ተጨማሪ ማስፋፊያ ብናደርግ ገቢ ይረዳናል ወይ የሚሉትን፣
  ሥራውን ለመጀመር የሚያስፈልገው ገንዘብ፣ ቁሳቁስ ወይም ቦታ በዝርዝር ይይዛል፡፡
  የገቢ ማስገኛ ዘዴ ዕቅድ ከወጭ ቀሪ ተቀንሶ የተሻለ ገቢ ማስገኘቱን እንዲሁም በአጠቃላይ የወጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንድናመዛዝን የሚያግዘን ሂደት ነው፡፡
  የገቢ ማስገኛ ዕቅድ ማዘጋጀት ለምን ይጠቅማል
  ሥራውን በሥራ ላይ ስናውለው በቀላሉ ሥራ ላይ መተርጎም እንድንችል ያግዘናል፤
  ለሥራው የሚያስፈልገውን ወጭ አስቀድመን እንድናውቀውና እንድንገመግም ያግዘናል፤
  የገበያ ሁኔታ ለመለየት፣
  የገቢ ማስገኛ ዘዴ ተግባራዊ ከመደረጉም በፊት ለታለመው ምርት ወይም አገልግሎት በቂ ጠቀሜታ መኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ያለውን ጠቃሚ/ገዥ/ ተገልጋይ የመግዛት አቅም በማስተዋል የትኛው ተጠቃሚ ላይ ማተኮር እንዳለብን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

  የትኛው ምርት ወይም አገልግሎት በብዛት ማምረት/መስጠት/ አለብን የዋጋ መጠኑስ ምን ሊሆን ይችላል? ሌሎች በገበያ ጥናት ወቅት ሁል ጊዜም አምራቾች መኖራቸውን ተመሳሳይ ምርት በሌሎች የተመረተ በገበያ በስንት እንደሚሸጥ ማወቅ ይኖርብናል፤ በተቻለ መጠን ከሌሎች አቅራቢዎች በተለየ ሁኔታ ማቅረባችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡

  የሰው ኃይል ስለማዘጋጀት
  በቤተ ክርስቲያን /በገዳማት/ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን ለመሥራት ብቁ ሰው መመደብ፤ የተመደበውም ሰው አስፈላጊውን ሥልጠና እንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልጋል በመጨረሻም የገቢ ማስገኛ ዘዴዎችን ውጤታማ ለማድረግ የተመደቡት ሰዎች የፈጠራ ክህሎት፣ ለሥራው የሰጡት ትኩረትና ጊዜ ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡

  ምርት ለማምረት /ግዢና ሽያጭ ለመፈጸም/ የሒሳብ አያያዝ ለመሥራት፣ የማስተዋወቅ ሥራ ለመሥራት የሰው ኃይል ያስፈልጋል፡፡
  ሥራውን ለመሥራት እውቀቱ፣ አቅም/ ተነሳሽነትና ፍላጎት/ ያለው፣
  ችግርን መቋቋም የሚችል፣ ተስፋ የማይቆርጥ ሰው አለ ወይ?
  ሓላፊነትን ከጠቃሚነት ጋር መቀበል የሚችል፣
  የገንዘብ ምንጭና የመነሻ ወጭ
  የገቢ ማስግኛ ዘዴዎች አነስተኛ ወጭ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የብድር አቅርቦት ሊኖር ይችላል፡፡ አነስተኛ የብድር ተቋማት ለዚሁ ተብለው የተቋቋሙ አሉ፡፡ /መደበኛ ባንኮች መያዥያ ስለሚጠይቁ ገንዘብ መበደር አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል/
  ቤተ ክርስቲያን በምን መልኩ ማቋቋም እንደምትችል ማሰብ ይኖርባታል፡፡
  1- አብያተ ክርስቲያናት ከሚያገኙት ከልዩ ልዩ ገቢ ለዚህ ሥራ መመደብ መቻል ነው፤
  2- አብያተ ክርስቲያናት በቅንጅት በመሥራት ያላቸውን ሀብት በማጣመር፤
  3- ምእመናን ለድሆች የሚያደርጉትን ድጋፍ ሥራን ከመፍጠር ጋር ማድረግ፣
  በገቢ ማስገኛ ዘዴ ለማቋቋም በገቢው የሚሰሉ ልዩ ልዩ ወጭዎች ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህም ወጭዎች ቋሚ ወጭ ወይንም የኢንቨስትመንት ወጭ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ቋሚ ወጭውም እንደ ገቢ ማስግኛ ዘዴ ዓይነት የሚወሰን ይሆናል፡፡

  ከላይ የተጠቀሱትን ሀብቶች በማቀናጀትና በማስተባበር በአጥቢያ ደረጃ፣ በወረዳ ቤተ ክህነት ደረጃ፣ በሀገረ ስብከት ደረጃ እንዲሁም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ የተለያዩ ማስግኛና አገልግሎት ሰጭ የልማት ሥራዎችን መሥራት ይቻላል፡፡

  ለምሳሌ የሚከተሉት የገቢ ማስገኛ ዘዴዎች በአማራጭነት ሊካተቱ ይችላሉ፡፡
  1. የንዋያተ ቅድሳት ምርት
  ንዋያተ ቅድሳት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቅዳሴና በልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች የምትጠቀምባቸው ግብዓቶችን ያጠቃልላል፡፡ እነዚህ ግብዓቶች ቤተ ክርስቲያን ካላት መንፈሳዊ አገልግሎት ስፋት ቅዳሴ፣ ክርስትና፣ ተክሊልና ፍትሐት ማለትም ሌሎች እንዲሁም የምእመናኑን የአብያተ ክርስቲያናቱ ቁጥር ከግምት ሲያስግባ ከፍተኛ ምርትንና ሽያጭን ይጠይቃል፡፡
  ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የገቢ ምንጭ ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን፣
  ትውፊትና ሥርዓቱን ለማስጠበቅ፣
  ከከተማው ውጭ ያሉትን አድባራት የንዋያተ ቅድሳት እጥረት ለመቀነስ በከፍተኛ ሁኔታ ያግዛል፣
  በአሁኑ ሰዓት ለዚሁ ገለጻ በተሰበሰበው መረጃ መሠረት ንዋያተ ቅዱሳቱ በገበያ ላይ ለሽያጭ የሚቀርቡት 95 በመቶ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው ለትርፍ በተቋቋሙ ወይም በሚሠሩ የግል አቅራቢዎች ወይም አምራቾች ነው፡፡
  ሀ. የጧፍ ምርት፡- /95 በመቶ በግል አቅራቢ በአብዛኛው ከመርካቶ የሚቀርብ ነው/
  ምእመናን በአነስተኛ ግምት በዓመት ወደ 93 ሚሊዮን ብር ለጧፍ ግዥ ያወጣሉ፡፡ ከ93 ሚሊዮን ብር ሽያጭ 20 ሚሊዮን ብር ትርፍ ይገኛል ተብሎ ሊሰላ ይችላል፡፡ ይህ ትውፊቱን ጠብቆ በቤተ ክርስቲያኒቱ ካህናት ተመርቶ ቢሆን ኖሮ የካህናቱን ገቢ በዚሁ መጠን ያድግ ነበር፡፡

  የጧፍ ምርት፡- “የሰው ኃይል፣ የፈትል ክር፣ ሰም ወይም ዋክስ በአካባቢው በሚሠራው ቴክኖሎጂ በመጠነኛ ቦታ ማዘጋጀት ነገር ግን ሁሌም ገበያ ያለው ምርት ነው፡፡ የተለየም ሙያ የማይጠይቅ ሥራ ነው፡፡ በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ካህናት የካህናት ሚስቶች በቀላሉ ሥልጠና ቢሰጣቸው ኑሮአቸውን ሊያሻሽሉ ይችላሉ፡፡

  ጧፍ በቤተ ክርስቲያን ካለመመረቱ የተነሳ በአሁኑ ሰዓት አምራቾች የሚጠቀሙት የሰም ዋጋ ውድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ትውፊቱንም ለመጠበቅ የሚያስችል ምክንያት ስለሌላቸው በአብዛኛው ልዩ ልዩ ኬሚካሎች በመጠቀም ምርቱን በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ካህናትን ከጢሱ ጋር በተያያዘ በሽታ ለጤና ችግር እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡

  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋም የጧፍ ማምረቻ ማሽን ሠርቶ በየዓመቱም 250.000 ጧፍ ከሰም ያመርታል፡፡ ምርቱን ለማምረት ለሚፈልጉ አብያተ ክርስቲያናት የማሽን ሥራና ሥልጠና ይሰጣል፡፡

  ለ. ዘቢብም፡- ሙሉ በሙሉ ከውጭ ሀገር በአብዛኛው ከአረብ ሀገር ይገባል፡፡
  ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን ዘቢብ የሚያቀርቡት ሙሉ በሙሉ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት ውጭ በሆኑ ለትርፍ ከተቋቋሙ የንግድ ድርጅቶች ነው፡፡ ዘቢብ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ እስከ 25.00 ብር /1.4 ዶላር/ የሚፈጅ ቢሆንም በገበያ ላይ ግን በኪሎ እስከ 100.00 ይሸጣል፡፡ በየጊዜውም አስመጪዎች አቅርቦቱና ዋጋውን የመወሰን መብት ስላላቸው በየጊዜው ዋጋ መናርና በገበያ ላይ ያለመገኘት ይታይበታል፡፡ ከዋጋው ከፍተኛነት ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን እስከ 120-150 ሚሊዮን ብር በዓመት ለዘቢብ ወጪ እንደሚያደርጉ ይገመታል፡፡ ዘቢብ በርካታ የገጠር አብያ ክርስቲያናት ሲቸገሩ ይታያል፡፡ ኢትዮጵያ ወይን ለመምረት የሚያስችል የአየር ንብረት ያላት ሀገር ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ ለወደፊት ወይን /ዘቢብ/ በሀገር ውስጥ ለማምረት ወይንም ቀጥታ ከውጭ ማስመጣት የምትችልበትን መንገድ አጥንታ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የዕጣን አቅርቦት ምንም እንኳን በሀገር ውስጥ ምርት ያተኮረ ቢሆንም በርካታ ገዳማት የዕጣን ዛፍ ቢኖራቸውም በጥቅም ላይ ሲውል ግን አይስተዋልም፡፡ በዚህም የዕጣንን አቅርቦት አንዱ የገቢ ማስግኛ ዘርፍ ሊሆን ይገባዋል፡፡

  ሐ. የቤተ ክርስቲያን መገልገያ አልባሳት፡-
  የዚህ ምርት አቅርቦት /ስፌትና ማዘጋጀት/ 85-90 በመቶ በግል አቅራቢ ነጋዴዎች የተያዘ ነው፡፡ ለግብዓት የሚሆነውን ጨርቅ አስመጪዎቹ ደግሞ መቶ በመቶ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ የሆኑ አካላት ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ዋጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መጥቷል፡፡ ዛሬ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በጋቢ ይቀድሳሉ ሲባል እንሰማለን፡፡ ለምን ብንል ከአልባሳት ውድነት የተነሳ በተለይ የገጠሩ ምእመን መግዛት ባለመቻሉ ነው፡፡

  ይህ እንዳለ ሆኖ የዓመቱ በትንሹ ከ13-15 ሺህ የካህናት አልባሳት እንዲሁም 10 ሺህ የሚጠጋ መጎናጸፊያ በገበያ ላይ ይውላሉ፡፡ ይህም በቀጥታ ቢሰላ 55 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ይኖረዋል፡፡ ከዚህም 14 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ሊገኝ ይችላል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች ምእመናን በቤተ ክርስቲያን አልባሳት ስፌት እንዲሠለጥኑ ምቹ ሁኔታ ብትፈጥር ካህናትን በግልም ሆነ በመደራጀት በሥራው ቢሠማሩ ገቢያቸውን ሊያሳድጉ ይችላሉ፡፡

  መ. ሌሎች መገልገያዎች፡-
  ጽንሐ፣ ጽዋ፣ የመጾር መስቀል፣ መንበርና የመሳሳሉትን 97 በመቶ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ የሚመረት ነው፡፡ በተለይም በአገር ውስጥ የአመራረቱ ሂደት ባህላዊና አድካሚ በመሆኑ ምርት እየቀነሰ ይገኛል፡፡ በዚህም ብዙዎቹ አምራቾች ወደ ሌላ ሥራ ዘርፍ ሲቀይሩ ይስተዋላል፡፡

  ሠ. ቅዱሳት ሥዕላትና ቅርጻቅርጽ፡-
  የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ጠብቀው የሚሳሉ ሥዕሎች ባለመኖራቸው በውጭ ሀገር የሚሳሉ ሥዕሎችን ምእመኑ ሳይወድ እንዲገዛ ሆኗል፡፡ ይህ በቤተ ክርስቲያን የነበረ ጥንታዊ ጥበብ ቢዳብር ዛሬም ለካህናት የገቢ ማስገኛ ይሆን ነበር፡፡

  አክሱምና ላሊበላን ያነጹ፡- ዛሬም በጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት የሚገኙትን ድንቅና ብርቅ ንዋያተ ቅድሳት የቀረፁ እጆች የት ሄዱ ያስብላል፡፡ ይህ የሙያ ዘርፍ ተጠናክሮ በተለይም ከቱሪዝም ገቢ ጋር ተያይዞና ተጠንቶ ቢቀጥል ብዙ አካላትን በሥራ ማሳተፍ ያስችላል፡፡

  2. የእንስሳት እርባታ ዘመናዊ አሠራርን
  በመከተል የወተትና የወተት ተዋጽኦ /የእንስሳት ማድለብ/ ዶሮና የእንቁላል ምርት የመሳሰሉትን ማቅረብ በተለይም በገዳማት ተሞክሮ ያለው አዋጭ የሥራ ዘርፍ ነው፡፡ ሀገራችን በዚህ በኩል ሰፊ ገበያ ያላት ስትሆን በአቅርቦቱ ግን በተለይም በከተሞች አካባቢ ዝቅተኛ ነው፡፡ ኢትዮትጵያ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር የቤት እንስሳት ባለቤት ብትሆንም ተጠቃሚነቷ ግን ዝቅተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የወተት አቅርቦት ብንመለከት እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ሰው በዓመት በአማካኝ የነፍስ ወከፍ የወተት ፍጆታው 100 ሊትር ወተት ሲሆን ይህን ወደ ሀገራችን ስናመጣው ግን 20 ሊትር ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያት የወተት አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ያለመኖሩ ነው፡፡ ለዚህም የዱቄት ወተት በውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገራችን እንዲገባ ሆኗል፡፡

  ዘመናዊ ወተት ርባታ/የእንስሳት ማድለብ/ ሥራዎች በርካታ አብያተ ክርስቲያናት እንደየአቅማቸው ሊተገበር የሚችል የሥራ ማስገኛ ዘዴ ነው፡፡ መጠነኛ ቦታ፣ በቂ የሰው ኃይል ከመጠነኛ ሥልጠና ጋር መሥራት መቻሉ በቀላሉ ተግባራዊ እንዲሆን ያስችላል፡፡

  3. ዘመናዊ የንብ ፕሮጀክት
  ድህነትን ከመቀነስ ረገድ ሌላው ሥራ መስክ የንብ ርባታ ነው፡፡ አብዛኞቹ ገዳማት /አብያተ ክርስቲያናት/ በደን በተከበበ ቦታ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ደን ለንብ ርባታ ተቀዳሚ ግብዓት ነው፡፡ በአገራችን 95 በመቶ የሚሆነው ምርትም በተነጣጠለና በግል የማመረት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሚኘው የማር ምርት በአካባቢ ብክለት ነጻ ሆኖ ሥራውም ብዙ የው ኃይል ጉልበትም የማይጠይቅ በመሆኑ በተለይም ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ምቹ ሲሆን በቀላል ቁሳቁስ አቅርቦች ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል፡፡ የንብ ርባታ በቂ ክትትል የሚፈልግ ሲሆን በአግባቡ ከተሠራ ለምሳሌ፡- ከአራት ዘመናዊ የንብ ቀፎ የሚገኘው ምርት ከግማሽ ሄክታር ከሚገኘው የበቆሎ ምርት ጋር ይወዳደራል፡፡

  4. አትክልት፣ ፍራፍሬና የሰብል ልማት
  በተፈጥሮ ሀብት በታደሉ አብያተ ክርስቲያናት ያላቸው ቦታ የሰው ኃይል ተጠቅመው የአትክልት፣ ፍራፍሬና የሰብል ልማት በገበያ የሚቀርቡ ማምረት ይችላሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉ ሥፍራዎች ሳር በቅሎባቸው ወይንም የቆሻሻ መጠራቀሚያ ሆነው ይታያሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ቦታዎች ከአካባቢው ግብርና መረጃ በማግኘት ብዙ ጥረት ሳይጠይቅ ልዩ ልዩ ፍራፍሬዎች ለምሳሌ፡- ሸንኮራ አገዳ፣ ፓፓያ፣ አፕል ከአትክልትም እንደ ሽንኩርትና ቃሪያ የመሳሰሉት ሊለሙበትና ወደ ገበያ ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡

  /በዝናብ ወይም መስኖ ውኃን በመጠቀም/ ለአካባቡው ተስማሚ የሆኑ የሰብል ዓይነቶችን በተገቢው የአመራረት ዘዴ በመጠቀም ማምረት ይቻላል፡፡ ሰብል ሲባል ለገበያ ለምሳሌ ሰሊጥ፣ ለምግብነት /በቆሎ ማሽላ/ ወይም ለማቀነባበሪያ ፋብሪካ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ምሳሌ የብቅል እህሎች ያጠቃልላል፡፡ እነዚህን ምርቶች በገበያ ላይ በከፍተኛ ዋጋ ስለሚሸጡ ጥሩ ገቢ ማግኘት ይቻላል፡፡

  5. የአትክልት ዘር የዘር ማብዣና መሸጫ
  አስከ አሁን ድረስ የተለያዩ የአትክልት ዘሮች ልማት በመንግሥት፣ በግል ኢንቨስተሮች እና በአነስተኛ ደረጃ በግለሰቦች እየተመረተ ያለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ሥራ መሠራቱ በቤተ ክርስቲያናት የሥራ ዕድል ከመፍጠርም በላይ የሀገር ኢኮኖሚ ማሳደግ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ጤናን መጠበቅ፣ የአካባቢ የአየር ንብረት መቆጣጠር እና የመሳሰሉትን ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን ይህ ተግባር በቤተ ክርስቲያናት ቢተገበር ለውጤታማነቱ የሚያግዙ በቂ የሰው ኃይል፣ መሬት፣ ውኃ፣ ገበያ መኖራቸው ሥራው አዋጭ መሆኑን ያሳያል፡፡

  6. የዓሣ ምርት በገዳማት
  ለዓሣ ርባታ የሚሆን ምቹ ቦታና የውኃ ሀብት ያላቸው ገዳማት በገዳሙ ተግባር ቤት የሚጠቀሙትን የተለያዩ የምግብ፣ የአትክልት ተረፈ ምርቶችን ለርባታው ወደሚዘጋጀው ገንዳ /ኩሬ/ በመጨመር በአንስተኛ ዋጋ የተለያዩ የዓሣ ዓይነቶችን ማምረት ለገዳሙ የሚጠቅም ገቢ ያስገኛል፡፡

  7. የሐር ትል ልማት በገዳማት
  ሐርን ለማምረት የሐር ትልን የማርባት ሥራ ነው፤ የሐር ትልን ለማርባት የምንጠቀምበት የጉሎ ቅጠል ሲሆን ይህንንም የቅጠል ዓይነት በቀላሉ በቅዱሳት መካናት ማምረት የሚቻል ሲሆን ትሉ የሚሠራው ሐር ደግሞ ውድ የሆኑ የልብስ ዓይነቶች ለማምረትና ከፍተኛ የሆነ የገቢ ምንጭ ለማስገኘት ይረዳል፡፡

  8. ወፍጮ ቤት /ዳቦ ቤት/ አገልግሎት
  ቤተ ክርስቲያን ካላት ማኅበራዊ ሀብት ከምእመናን ጋር ባላት የጠበቀ ትስስር የቤተ ክርስቲያን የሆነውን አገልግሎት ከማግኘት አንጻር ቤተ ክርስቲያን ልትሳተፍባቸው የሚገቡ ሥራዎች ናቸው፡፡ /በተለይም ገዳማት/

  9. ቤተ መዘክሮችን ማቋቋም
  የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የበርካታ ቅርሶች ባለቤት ብትሆንም በተለይም ከቱሪዝም ከሚገኘው ገቢ ቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ ካህናቱ ተጠቃሚ እየሆኑ አይደለም፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ያለውን ቅርስና ታሪክ ለጎብኝዎች በሚስብ መልኩ ማደራጀት ባለመቻሉ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ተጠቃሚ የሚሆኑትን አብያተ ክርስቲያናት በመለየት ቤተ መዘክሮችንና ሌሎች ለጎብኝዎች መስህብ የሆኑ ሥራዎችን በቀላል በመሥራት የካህናት ገቢ ከፍ ማድረግ ይቻላል፡፡

  10. የግንባታ ቁሳቁስ አቅርቦት
  በተራራማ አካባቢ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት በአካባቢያቸው ብዙ ድንጋይ ሊገኝ ይችላል፡፡ በተለይም ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚያወጣ መንገድ ለመሥራት ሲባል ብዙ ተራራማ ይፈርሳል ድንጋይ ግን ጥቅም ላይ አይውልም፡፡ በአሁኑ ሰዓት የግንባታ ግብዓት እጥረት አንጻር አብያተ ክርስቲያናት የድንጋይ አቅርቦትና በብሎኬት ምርት ላይ ቢሳተፉ አዋጭ ይሆናል፡፡

  11. የኪራይ አገልግሎት መስጠት
  ሰፊ የመሬት ይዞታ ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት በተለይም ለሱቅ ወይም ለመኖሪያነት የሚሆኑ ግንባታዎች በማካሄድ ከቤት ኪራይ በሚገኝ ገቢ ሊደጎሙ ይችላሉ፡፡

  የገቢ ማስገኛ ዘዴን ውጤታማ ስለማድረግና ተጠቃሚ ስለመሆን

  ማጠቃለያ
  በለሱን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል፡፡ ምሳሌ. 27፡118 ተስፋው ፍሬ በለሱን ለተንከባከበ/ በአነስተኛ የሥራ ዘርፎች ተግባራዊ በማድረግ ለዜጎች ሥራ መፍጠርና ገቢያቸውን ማሳደግ ከድህነት የመውጫ አንዱና ዋነኛ ዘዴ ነው፡፡ ይህ ዘዴ አገራችንን ጨምሮ በብዙ ሀገሮች ተፈትኖ ውጤቱም ያረጋገጠ ሆኗል፡፡ ሥራውም፡-
  ተነሳሽነት ፍላጎትና ትጋትን
  ታታሪነትን ትዕግሥትን አቅዶ መሥራትን ይጠይቃል፡፡
  ይህንኑ ቤተ ክርስቲያን በይበልጥ ተግባራዊ ለማድረግና ተጠቃሚም ለመሆን ቤተ ክርስቲያን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ በተለይ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በአነስተኛ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች እንዲሠማሩ የሚያግዙ እቅድ አውጥታ መንቀሳቀስ ይኖርባታል፡፡ ለምሳሌም ያህል ለልዩ ልዩ እደ ጥበብና መብዓ ሥራዎች በቤተ ክርስቲያን ተግባራዊ እንዲሆን የሥልጠና ማእከል በማቋቋም፤ የመነሻ ገንዘብ አቅርቦትን ችግር ለመፍታት የብድር ተቋማትን በማቋቋም፣ ምእመናንን በዚህ ሥራ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስተማር የሥራን ክቡርነት መግለጽ ይኖርበታል፡፡ ከዚህም አንጻር ልጆች የሥራን ክቡርነት፣ ፈጠራን፣ እራስን ማስተዳደር አብሮአቸው እንዲያድግ በሰንበት ትምህርት ቤት ይህ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት በሥርዓተ ትምህርት ቢካተት መልካም ነው፡፡
  ወስብሐት ለእግዚአብሔር
  በወ/ሮ ዓለምፀሐይ መሠረት
  የማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት
  ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ሓላፊ
  ከቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ የተወሰደ፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: