የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነድ ርክክብ ዛሬ ይካሔዳል

 • የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ደግሞ በነገው ዕለት ለቋሚ ሲኖዶሱ ያስረክባል
A.A Diosces Head Office

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን የተቋማዊ ለውጥ አመራር ሲያጠና የቆየው የባለሞያ ቡድን በዛሬው ዕለት የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነዱን ለሀ/ስብከቱ በይፋ ያስረክባል፡፡

ዛሬ፣ የካቲት ፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ረፋድ ላይ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በሚካሔደው የርክክብ እና ምስጋና መርሐ ግብር፣ 13 አባላት ያሉት የባለሞያ ቡድኑ የእያንዳንዱ ፖሊሲና መመሪያ ማስፈጸሚያ የኾኑ ብዛት ያላቸው ቅጻቅጾችና አባሪዎች ጨምሮ ከአንድ ሺሕ በላይ አጠቃላይ ገጾች ያሏቸውን 12 ሰነዶች በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳትና የጅማ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለኾኑት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ነው የሚያስረክበው፡፡

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በ292 ሚልዮን ብር ወጪ የሚያስገነባውንና የባለሞያ ቡድኑ ከኹሉ አስቀድሞ ሠርቶ የሰጠውን የሥልጠና፣ የአሳዳጊ አልባ ሕፃናትና የአረጋውያን መርጃ ማእከል ግንባታ ፕሮጀክት ሰነድ ሳይጨምር በዛሬው ዕለት ርክክብ የሚፈጽባቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነዶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

 • የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የመዋቅር የአደረጃጀት ጥናትና መመሪያ – 119 ገጽ
 • የአብያተ ክርስቲያናት የደረጃ መስፈርት መመሪያ – 23 ገጽ
 • የአገልግሎት መደቦች የሥራ ዝርዝር መመሪያ – 120 ገጽ
 • የሰው ኃይል ትመናና የተፈላጊ ችሎታ መስፈርት መመሪያ – 53 ገጽ
 • የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የደመወዝ ስኬል ጥናት – 99 ገጽ
 • የአገልጋዮች ማስተዳደርያ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ – 125 ገጽ
 • የሥልጠናና የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ – 30 ገጽ
 • የፋይናንስ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ – 107 ገጽ
 • የግዥ፣ ሽያጭና ንብረት አስተዳደር መመሪያ – 26 ገጽ
 • የልማት ሥራዎች ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ – 16 ገጽ
 • የዕቅድና ሪፖርት ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ መመሪያ – 31 ገጽ

ከረፋዱ 4፡00 – 6፡00 በሚዘልቀው በዚኹ የርክክብና የምስጋና መርሐ ግብር፣ የሀ/ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጨምሮ የዋና ክፍል ሓላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የብዙኃን መገናኛ ዘጋቢዎች እንደሚታደሙ የተመለከተ ሲኾን የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ለመርሐ ግብሩ ክንውን ድጋፍ ማድረጉ ተገልጦአል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አባታዊ መመሪያና በረዳት ሊቀ ጳጳሱ የቅርብ ክትትል የሀ/ስብከቱን የመዋቅር አደረጃጀትና አሠራር ጥናት ያከናወነው የባለሞያ ቡድኑ በዛሬው ዕለት ለሀ/ስብከቱ በይፋ የሚያስረክበው ሰነድ÷ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያዎችና ደርጅቶች ዋና ሓላፊዎች፣ በሀ/ስብከቱ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሥራ ሓላፊዎች፣ በ169 ገዳማትና አድባራት የአስተዳደር ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ የካህናት፣ የአብነት መምህራን፣ የሰንበት ት/ቤቶችና የምእመናን ተወካዮች ውይይት የተደረገበትና ከውይይቱ በተሰበሰቡ ግብዓቶች የዳበረና የተስተካከለ ነው፡፡

ከውይይት መድረኩ የተገኘውን የተሳታፊዎች ትችትና አስተያየት በከፍተኛ ጥንቃቄ መለየቱንና ማደራጀቱን የገለጸው የባለሞያ ቡድኑ፣ በተለይም÷ ከሀ/ስብከት እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ያለው የመዋቅርና አደረጃጀት ጥናት መመሪያን፣ የአገልግሎት መደቦችን የሥራ ዝርዝር መመሪያ፣ የገዳማትና አድባራት የደረጃ መስፈርት መመሪያን፣ የሰው ኃይል ትመናና የተፈላጊ ችሎታ መስፈርት መመሪያን እንዲሁም የፋይናንስ ፖሊሲንና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያን መሠረታዊ ማስተካከያ በማድረግ ጭምር ለማደራጀት ሌት ተቀን ሲሠራ መሰንበቱ ተዘግቧል፡፡

በግንቦት ፳፻፭ ዓ.ም. ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነዱ ወደ ታች ወርዶ በማኅበረ ካህናት፣ ማኅበረ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች ውይይት ዳብሮ በውይይቱ ከተገኘው ግብዓት ጋራ ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ መተግበር ይኖርበታል፡፡

በውሳኔው መሠረት፣ በተለያዩ መመዘኛዎች 96 በመቶ ተቀባይነት ያረጋገጠውን የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነዱን የባለሞያ ቡድኑ ሰብሳቢና አስተባባሪ ከኾኑት አቶ ታደሰ አሰፋ በዛሬው የርክክብና ምስጋና መርሐ ግብር በይፋ የሚረከቡት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ በነገው ዕለት በሚካሔደው ሳምንታዊ የቋሚ ሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አቅራቢነት የመጨረሻ ርክክብ ከቅ/ሲኖዶሱ ጋራ እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: