የአ/አ ሀ/ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ጥናታዊ ውይይት የመጨረሻ ዙር ተሳታፊዎች የሚኾኑት የቦሌ፣ ልደታ፣ አዲስ ከተማና ቂርቆስ ክፍላተ ከተማ አብያተ ክርስቲያን ለተቋማዊ ለውጡ ያላቸውን ድጋፍ እየገለጹ ነው፤ ለውጡ ‹‹ተረፈ ደርግና አሸባሪ የኾነው ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመቆጣጠር የዘረጋው አሠራር ነው›› የሚሉ ‹ተቃዋሚዎች› ጥናቱ ጸድቆ የሚተገበር ከኾነ ‹‹ፐርሰንት አንከፍልም፤ ተገንጥለን በቦርድ እንተዳደራለን›› በማለት በረዳት ሊቀ ጳጳሱ ቀጣይነት ላይ እያደሙ ነው

A.A.D Parish churches discussion on change mgt.

የየካ ክፍለ ከተማ ገዳማትና አድባራት ጥናታዊ ውይይት (ፎቶ: የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ድረ ገጽ)

 • ዛሬ ዐርብ ታኅሣሥ ፲፩ – ፲፪ የሚካሄደውን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እና የልደታ፣ አዲስ ከተማና ቂርቆስ ክፍላተ ከተማ አብያተ ክርስቲያን ልኡካን የሚሳተፉበትን ጥናታዊ ውይይት መስተንግዶ የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ካቴድራል እና የመርካቶ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን፤ ከታኅሣሥ ፲፫ – ፲፬ የሚካሄደውንና የቦሌ ክፍለ ከተማ አብያተ ክርስቲያን የሚሳተፉበትን ጥናታዊ ውይይት ደግሞ የቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ስፖንሰር ለማድረግ በየሰበካ ጉባኤያቸው ማስወሰናቸውንና የሀ/ስብከቱን ወጪ መጋራታቸውን ገልጸዋል፡፡
 • ታኅሣሥ ፮ እና ፯ በኮልፌ ቀራንዮ፤ ታኅሣሥ ፬ እና ፭ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍላተ ከተማ አብያተ ክርስቲያን እንደ ቅደም ተከተላቸው የተካሄደው ጥናታዊ ውይይት÷ ከአሉባልታዎች ይልቅ ከቀረበው የጥናት ረቂቅ ይዘት ጋራ ቀጥተኛ ተያያዥነት ያለው፣ ለሰነዱ መዳበር ብቻ ሳይኾን የይዘት መስተካከልም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ ገንቢና ሞያዊ እንደነበር ባለሞያዎቹ፣ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ እና አዘጋጅ ኮሚቴው ጥናታዊ ውይይቶቹ በተካሄዱባቸው ዕለታት በመደበኛነት ያደረጓቸው የውሎ ምዘናዎች/ግምገማዎች በጉልሕ ያመለክታሉ፡፡
 • በክፍላተ ከተማው ልኡካን ከተነሡት ነጥቦች መካከል በሀ/ስብከቱ አድባራት፣ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት የደረጃ መስፈርት ጥናት÷ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች ጋራ የተመጣጠነ የሰው ኃይል /በቁጥር፣ በክህሎት፣ በሞያና ልምድ/ እንዲያገኙ የሚጠቁመው ሐሳብ ይገኝበታል፡፡ ሐሳቡ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ያላቸውን ሀብት፣ ታሪክ፣ ንብረት፣ ገንዘብ በተሻለ ደረጃ ለመጠቀም የሚችሉበትን ኹኔታ ለማመላከትና መንፈሳዊ ቅናትን በመፍጠር የአገልግሎት አሰጣጥ ተነሣሽነትን በአገልጋዮች መካከል ማስፈን መኾኑ ተገልጧል፡፡
 • በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ ገዳማትና አድባራት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ክምችት እንደያዙ የታመነበት በመኾኑ በጥናቱ መሠረት ገዳማቱና አድባራቱ ካሉበት ደረጃ ጋራ ተመጣጣኝ የኾነ የአገልጋይ ቁጥር በመደበኛነት ከያዙ በኋላ ቀሪዎቹን ሳያፈናቀሉ ለማስተዳደር የሚችሉባቸው አግባቦች/አማራጮች በጥናቱ ተቀምጠዋል፡፡ ከአግባቦቹ አንዱ፣ ከመደበኛው (ስታንዳርድ) የአገልጋይ ቁጥር የቀረውን አገልጋይ ጊዜያዊ ምደባ ሰጥቶ ደመወዛቸውና ጥቅማጥቅማቸው ሳይነካ የሰው ኃይል ወደሚፈልግባቸው አጥቢያዎች የሚንሸራሽበት ሥርዐት ነው፡፡
 • ሌላው አማራጭ፣ አጥቢያዎች በራሳቸው አልያም ከሌሎች አጥቢያዎች፣ ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት፣ ከሌሎች አህጉረ ስብከትና አብያተ ክርስቲያናት ጋራ በልማት ተቋማት ማስፋፊያ ፖሊሲው መሠረት እየተቀናጁ በሚከፍቷቸው የልማት ተቋማት አንጻር ተገቢውን የክህሎት/ሞያዊ ሥልጠና በመስጠት ማሰማራት ነው፡፡ ከመደበኛ ቁጥር ውጭ የኾነው አገልጋይ በትርፍነት የሚቆየው ለረጅም ጊዜ ከኾነ ደግሞ ሲያገኘው የቆየው ደመወዝና ጥቅማጥቅም እንደተጠበቀለት በአዲስ አበባ ዙሪያ ይኹን በአህጉረ ስብከት የካህናት እጥረት ባለባቸው አብያተ ክርስቲያን አበል እየታሰበለት ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥበት መንገድ ነው፡፡ የገጠሪቱን ቤተ ክርስቲያን ከማገልገልና የቅጥር ወጭን ከመቀነስ አንጻር ከፍተኛ ትርጉም ያለውን ይህን ሐሳብ የጥናታዊ ውይይቱ ተሳታፊዎች በሙሉ ልብ የደገፉ ሲኾን አፈጻጸሙ በአገልጋዩ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ እንዲኾን በአጽንዖት አሳስበዋል፡፡
 • ‹ቅሬታ› አቅራቢ ነን ባይ ተቃዋሚዎቹ ግን አሁን በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ከፍተኛ የሰው ኃይል ክምችት መኖሩ ችግር መኾኑን እያወቁ፣ ከዚህ አንጻር የቀረበው የመፍትሔ ሐሳብም በገጠርም በከተማም ያለችውን አንዲት ቤተ ክርስቲያን ለማገልግል የሚያስችል እንደኾነ ሳይሰወራቸው መረጃው አይኖረውም ብለው የሚያስቡትን ብዙኃኑን ካህን ‹‹በየአጥቢያው ኻያ ኻያ ካህን ብቻ ነው የሚያስፈልገው ተብሏል፤ መፈናቀላችኹ ነው፤ ወደ ጋምቤላ መበተናችኹ ነው፤›› እያሉ ሰፊ ውዥንብር መፍጠራቸው የ‹ቅሬታቸውን› አግባብነትና ቅንነት አጠያያቂ የሚያደርገው ነው፡፡
 • የለውጡ ተቃዋሚዎች ኅቡእ ስብሰባ እንደተካሄደበት የተዘገበው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት አባ ኪሮስ ጸጋዬ÷ የኅቡእ ስብሰባውን መካሔድ በማስተባበልና የኅቡእ ስብሰባውን ዓላማ በጽኑ በመቃወም ለለውጡ ተግባራዊነት ያላቸውን ድጋፍ የሚገልጽ ደብዳቤ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ለረዳት ሊቀ ጳጳሱ እና ለሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ጽፈዋል፡፡

*                                 *                                *

 • በቀንደኛ የሀገረ ስብከቱ ሙሰኛ የአድባራት አለቆች፡- መልአከ ገነት ኃይሌ ኣብርሃ (ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ሊቀ ትጉሃን ዘካርያስ ሐዲስ (ኮተቤ ደብረ ጽባሕ ቅዱስ ሚካኤል)፣ መልአከ ብሥራት መልአክ አበባው (አፍሪቃ ኅብረት ቅዱስ ሚካኤል) እና ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ተክለ ጊዮርጊስ (የካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል) የሚመሩ ‹ተቃዋሚዎች›÷ ፓትርያርኩ ጥያቄዎቻቸውን የማይቀበሏቸው ከኾነ ‹‹የ[አቡነ] መርቆሬዎስ ደጋፊዎች ነን ብለን ሰልፍ እንወጣለን፤ መግለጫ እንሰጣለን›› እያሉ በፓትርያርኩ ላይ ሲዝቱ ውለዋል፤ ‹‹በቅዱስነትዎ ዘመን ደም እንዲፈስ ይፈልጋሉ ወይ? ይህ ጥናት የማይቆም ከኾነ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እናሳውቃለን፤ ፐርሰንት አንከፍልም፤ ለሳዑዲ ዓረቢያ ተመላሾች አስተዋፅኦ አናወጣም፤ የአባ እስጢፋኖስን ስም አንጠራም፤ ተገንጥለን በቦርድ እንተዳደራለን፤›› በማለትም የለውጥ ትግበራ ሂደቱን ለእነርሱ ብቻ በሚታያቸው ብጥብጥ የማወክና የማምመከን ዝንባሌና ውጥን እንዳላቸው ገልጠዋል፡፡
 • በፓትርያርኩ ጽ/ቤት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መምሪያዎች፣ በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ከሚገኙ ግለሰቦች ጋራ የጥቅምና ዓላማ ግንኙነት መፍጠራቸው የሚነገርላቸው ‹ቅሬታ› አቅራቢዎቹ÷ የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለጥናቱ አጸዳደቅ የሰጠው የአፈጻጸም አቅጣጫ እንዲፈጸም መስማማታቸውን በፊርማቸው ያረጋገጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ‹‹ጥናቱን ይቃወማሉ›› በሚል ከፓትርያርኩና ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ ጋራ ለማጋጨት፣ በዚህም የተቋማዊ ለውጥ ሒደቱ ርስ በርሱ ተጠላልፎ የሚወድቅበትን ውጥን መዘርጋታቸው ተጠቁሟል፡፡ የመካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ዋና ጸሐፊ የኾነው ሊቀ ትጉሃን ደነቀ ተሾመ በዋናነት የሚያስፈጽመው ነው የተባለው ይኸው ሊቃነ ጳጳሳቱን የመከፋፈል ውጥናቸውም፣ የውሳኔውን አፈጻጸም በመረጃ ደረጃ እየተከታተሉ የማያቋርጥ ምክር በመለገሥ ላይ የሚገኙትን እንደ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ያሉ የተቋማዊ ለውጥ ጠበቆችን ማስቆጣቱ ነው የተሰማው፡፡
 • ‹ቅሬታ› አቅራቢ የተቋማዊ ለውጥ ተቃዋሚዎቹ ከትላንት በስቲያው ምክራቸው በኋላ ለፓትርያርኩ አቀረቡት በተባለው አቤቱታ ‹‹ሙሉ የጥናት ሰነዱ›› እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ይህን እነርሱ ባይሉትም በየደረጃውና በየሞያ ዘርፉ በተለየ ኹኔታ በሚዘረጋው የሥልጠና መርሐ ግብር መሠረት ለየአብያተ ክርስቲያናቱ የሥራ ክፍሎች 13ቱም ጥራዞች እንደሚደርሱ በጥናታዊ ውይይቱ ላይ በተደጋጋሚ በመገለጽ ላይ ያለ ነው፡፡ ሊተኮርበት የሚገባው ግን፣ የጥናት ረቂቅ ሰነዱን በጋራ ውይይትና ግንዛቤ ለማዳበር የተዘረጋላቸውን መድረክ በአካል እየተገኙና አግባቡ እየተሳተፉ አስተዋፅኦ ባላደረጉበት፣ አንዳንዶቹም በወጣው መርሐ ግብር መሠረት ተራቸው ደርሶ ባልተወያዩበትና ባልተሳተፉበት ኹኔታ ይህን ጥያቄ የማቅረባቸው መግፍኤ ነው፡፡
 • ከዚህ አኳያ በተወካዮቻቸው በእነ መልአከ ገነት ኃይሌና ሊቀ ትጉሃን ዘካርያስ አማካይነት በፓትርያርኩ፣ በረዳት ሊቀ ጳጳሳቸው፣ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ እና በቋሚ ሲኖዶስ አባላት ፊት ያቀረቡትን ‹ቅሬታ› በጥሞና ያዳመጡት የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ‹‹ከዚህ የሚያደርሳችኹ ነገር አልነበረም፤ እዚህ ከመምጣታችኹ በፊት ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ ጋራ መነጋገር ነበረባችኹ›› ሲሉ የሰጧቸው ምላሽ አግባብነት ይኖረዋል፡፡ ውሏቸውን በቅርበት የተከታተሉ ምንጮች እንደተናገሩት ‹ቅሬታ› አቅራቢዎቹ፣ ‹‹ሙሉ ሰነዱን እንመረምራለን›› በሚል ዐቢይ ኮሚቴና ንኡሳን ኮሚቴዎችንም አዋቅረዋል፡፡

*              *             *

 • ‹‹በየሬስቶራንቱና በየሆቴሉ ከምትሰበሰቡ›› በሚል በተፈቀደላቸው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ከትላንት በስቲያ፣ ታኅሣሥ ፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ከቀትር ጀምሮ ሲመክሩ የዋሉት ከ60 የማይበልጡ ‹ቅሬታ› አቅራቢዎቹ÷ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን በጦር ሜዳ የተሸነፈው የደርግ ርዝራዥ ነው፤ በጦር ሜዳ ገጥሞ ያልቻለውን ሥርዐት በሃይማኖት ገብቶ ሊጥለው ነው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን አሠራር በጥናት ስም እየዘረጋ ነው፤ አሸባሪ ነው፤ ማኅበረ ቅዱሳን ባወጣው ደንብ አንመራም፤›› በማለት ከመሠረተ ቢስ ውንጀላ፣ ከጭፍን ጥላቻ እና ሕገ ወጥ ጥቅምን አስጠብቆ ለመኖር ከመፈለግ በቀር ለውጡን በግልጽ መድረክ በምክንያት ተደግፎ በሚቀርብ የአማራጭ ሐሳቦች ግብግብ የሚሟገቱበት መሬት የረገጠ መከራከርያ እንደሌላቸው አረጋግጠዋል፡፡
 • ረዳት ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ እና የባለሞያ ቡድኑ አስተባባሪ አቶ ታደሰ አሰፋ÷ በጥናት ሰነድ ረቂቅ ዝግጅቱ ማኅበረ ቅዱሳን እንደተቋም ያደረገው ተሳትፎ እንደሌለ በየጥናታዊ ውይይቶች ላይ ከባለሞያዎቹ ዝርዝር ማንነትና ስብጥር ጋራ ተደጋጋሚ መረጃዎች በመስጠት ሲያስረዱ ቆይተዋል፡፡
 • ከባለሞያ ቡድኑ መካከል የማኅበረ ቅዱሳን አባላት መኖራቸው ርግጥ ቢኾንም ሀ/ስብከቱ የተጠቀመው ግለሰባዊ ዕውቀታቸውን/ሞያቸውን እንጂ የማኅበራቸውን መዋቅር እንዳልኾነ ለተወያዮች በተደጋጋሚ ሲገልጹ የቆዩት ብፁዕነታቸው፣ ‹‹ሰነዱን ማን አዘጋጀው ትታችኹ መሬት ወድቆ ብታገኙት አትጠቀሙበትም ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋቸዋል፡፡ ባለሞያዎቹ በመደበኛ ሥራቸው በከፍተኛ ደረጃ የሚከፈላቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች መኾናቸውን የጠቀሱት ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ፣ ጥናቱ የቤተ ክህነታችንን ችግር በቅርበትና በጥልቀት በማወቅ ላይ ተመሥርቶ በአጭር ጊዜ መከናወኑ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ከመኾኑም በላይ ከባለሞያ ክፍያ አንጻር ብቻ ከ2 ሚልዮን ብር በላይ ወጭ የዳነበት መኾኑን አስረድተዋቸውም ነበር!!
 • በዚህ ረገድ የባለሞያ ቡድኑ አስተባባሪ አቶ ታደሰ አሰፋ ከሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ተክለ ጊዮርጊስ ተቃውሞ አይሉት ጥያቄ ጋራ ያደረጉት ምልልስ በተሳታፊዎች ዘንድ የጥቅስ ያህል የተያዘ ነው፡፡ የቤት እና የንግድ መኪኖች፣ ከአንድ በላይ መኖርያ ቤቶች ባለቤትነታቸው ብቻ ሳይኾን ከሽጉጥ ታጣቂነታቸው ጋራ በቁጣቸውና ለመነኮስ ከሚገባ አኗኗር መራቃቸው የሚታወቅላቸው የየካ ደብረ ሣህል ቅ/ሚካኤል አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ በውይይቱ ወቅት ርስ በርሱ በሚምታታው አነጋገራቸው እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሙስና ሙስና ትላላችኹ፤ ሙስና የለም! በልጆቻችን እንድንሠለጥን ያደርጉናል ወይ? ሕግ አያስፈልግም! ማንነታችኹ አይታወቅም፤ የቤተ ክርስቲያን ልጆች አይደላችኹም፤ ልጅና ጎረቤት እኮ ልዩነት አለው፡፡››
 • አቶ ታደሰ ለሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ በሰጡት አስተያየት፡- ‹‹የቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን በ፵ እና በ፹ ቀን በተፈጸመልን ጥምቀተ ክርስትና ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ልጅነት እኩል ነን እንጂ ልጅና ጎረቤት የለም፡፡ በዘመናችን የእግዚአብሔር የለሽ ፍልስፍና ስንቶች ፀረ ቤተ ክርስቲያን ኾነው ወጥተዋል፡፡ እኛ የሥላሴ ልጅነት ካገኘንባት ቤተ ክርስቲያን ሳንወጣ እዚህ በመገኘታችን መሰደብ አለብን?
 • እግዚአብሔር በሰጠን ዕውቀትና ሞያ ለቤተ ክርስቲያናችን መታዘዝ እንዳለብን እናምናለን፡፡ በቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን ተጠርተንና ሞያችንን ዐሥራት አድርገን የሠራነው ጥናት የልጅነት ድርሻችንን የተወጣንበት የመታዘዝ ፍሬ ነው፡፡ እነ ሊቀ ሊቃውንት ደግሞ የጠመመውን ማቅናት፣ የጎደለውን መሙላት ይጠበቅባችኋል፡፡ ካልፈለጋችኹት ጋርቤጅ ውስጥ ጣሉት፤ ይጠቅማል ካላችኹ አሻሽሉት፡፡
 • ሊቀ ሊቃውንት እንደተናገሩት፣ በቤት ልጅና ጎረቤት ዘይቤ ከቀጠልን ግን ወደ 43.7% የወረደውና በዐሥር ሚልዮኖች ያጣነው የምእመናን ቁጥር ከ20% ወርዶም እናገኛዋለን፡፡ ሊዘነጉት የማይገባው ቁም ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን የካህናትም የሊቃውንትም የምእመናንም መኾኗን ነው!!››

Holy Synod direction on A.A.D Change mgt000Holy Synod direction on A.A.D Change mgt0002Holy Synod direction on the A.A Change mgt.01

Holy Synod direction on the A.A Change mgt.02

Advertisements

12 thoughts on “የአ/አ ሀ/ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ጥናታዊ ውይይት የመጨረሻ ዙር ተሳታፊዎች የሚኾኑት የቦሌ፣ ልደታ፣ አዲስ ከተማና ቂርቆስ ክፍላተ ከተማ አብያተ ክርስቲያን ለተቋማዊ ለውጡ ያላቸውን ድጋፍ እየገለጹ ነው፤ ለውጡ ‹‹ተረፈ ደርግና አሸባሪ የኾነው ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመቆጣጠር የዘረጋው አሠራር ነው›› የሚሉ ‹ተቃዋሚዎች› ጥናቱ ጸድቆ የሚተገበር ከኾነ ‹‹ፐርሰንት አንከፍልም፤ ተገንጥለን በቦርድ እንተዳደራለን›› በማለት በረዳት ሊቀ ጳጳሱ ቀጣይነት ላይ እያደሙ ነው

 1. Anonymous December 20, 2013 at 6:10 am Reply

  አቤቱ የሰላም ባለቤት ሰላምን ስጠን::
  ለነገሩ ይሄ ሁሉ አለመግባባት መኖሩ የግድ ነው ምክንያቱም ቤተክርስቲያናችን ለረጅም አመታት ባስተናገደችው የአስተዳደር ችግር :: ወጥ የሆነ እና ግልጽ እና ማእከላዊ በሆነ መንገድ አድባራት እና ገዳማት እንዲሁም የተለያዩ የቤተክርስቲያኑአ ተቁዋማት የሚተዳደሩበት ቁጥጥር የሚደረግበት መንገድ ጠንካራ አልነበረም:: በዚህም የተነሳ አንዳንድ ሃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች የቤተክርስቲያኑን ንብረት እንደራሳቸው የግል ንብረት ሲቆጥሩ ኖረዋል:: ሰዎች በትምህርት እና ስልጠና ሃላፊነት እና ግዴታቸውን ማወቃቸው አይቀርም ሁሉም መስተካከሉም አይቀርም ዘመኑም እንዳለፉት ዘመናት እንድንሆን አይፈቅድልንም :ትልቁ ነገር ሰላም እና ትእግስት ነው አሁን እምቢ ያሉ ሰዎችም ባለማወቃቸው ነው:: ምእመኑም በዚህ ትልቅ ሃላፊነት አለበት የቤተክርስቲያን ነገር ሊያገባው ትክክለኛውን ነገር ጠይቆ ሊረዳ ይገባል::
  እግዚሃብሔር አምላክ አስተዋይ አገልጋይ ይስጠን ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን

 2. Anonymous December 20, 2013 at 8:09 am Reply

  መናፈቃንን ሁሉ ከበትክርስቲያን ጠራርጎ ማስወጣት ነው

 3. mezgebu December 20, 2013 at 9:05 am Reply

  1. እባካችሁ ምእመኑን ማስፈራሪያ አታድርጉት!!!መጀመሪያ ነገር እናንተ የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች እንጅ ምእመኑ መርጦ የላካችሁ የምእመናን ተወካዮች አይደላችሁም!!!ምእመኑ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያደርግበትና ተወካዮቹን የሚመርጥበት ፍትሀዊ የምርጫ ስርዐት (በሰበካ ጉባኤ፣በልማት ኮሚቴ፣በሰ/ት/ቤት) ቤ/ክ የዘረጋችው ገና እናንተ ሳትወለዱና ህገ-መንግስቱም ከመጽደቁ በፊት ነው፡፡ስለዚህ በምእመኑ ጀርባ ለመንጠላጠል አትሞክሩ!!ደግሞም እኮ ጥናቱ ‘ለክህነታዊ ስራዎች’ ተብሎ እንጅ ‘የምእመናን ተሳትፎ ለማረጋገጥ’ በሚል የተሰራ አልመሰለኝም፡፡የውዝግቡ ነጥብም ካህናቱ በጥናቱ ውሰጥ የተካተተውን(ከተካተተ!!)የምእመናን ድርሻ ስለተቃወሙ አይደለም!!!
  2. ሲቀጥል እናንተ ከሌላችሁ ኦርቶዶክስ ወደ 20% እንደምትወርድ ለማርዳት መሞከር ለራሳችሁ የሰጣችሁትን የተጋነነ ግምት ያሳያል፡፡ቢያንስ አብዛኛው ኦርቶዶክሳዊ በሚኖርበት የገጠሩ ክፍል ያለው የእናንተ ተሳትፎ ሲለካ ያን ያህል ‘እነሱ ባይኖሩ ኖሮ’ የሚያሰኝ እንዳልሆነ እናውቃለን!!!አትቸኩሉ!!! ገና በ20 አመት እድሜያችሁ ‘እኛ ከሌለን ኦርቶዶክስ አለቀላት’ ብሎ መታበይ ‘የሲኦል ደጆች አይችሉአትም’ የምንላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከዚህ የከፉ ጊዜያትንም ተሻግራ እዚህ መድረሱዋን የዘነጋ ነው፡፡እውነት አሁን የኦርቶዶክሳውያን ቁጥር ከ43% እንዳይወርድ የረዳው የእኛ መኖር ብቻ ነው ልትሉን ነው!!ተው!!! ለቤ/ክ እየሰጣችሁት ያለውን አገልግሎት ስማችሁ በየሚዲያው ስለተጠራ ብቻ ተወዳዳሪ አልባ አድርጋችሁ በመገመት በአጉል ከንቱ ውዳሴ አትውደቁ!!!ትሩፋታችሁን አታበላሹት!!!
  3. ይሄውላችሁ!!! ድርቅ ብላችሁ ‘ይሄን ጥናት የሚቃወመው ሌባና ሙሰኛ ብቻ ነው’ ብላችሁ አትደምድሙ፡፡ስለትርፍ የሰው ሀይል እያወራችሁ፣ወደ ገጠር ስለመላክ እየተነጋገርን መነኩሴና ዲያቆኑ ይቅር ትዳር ይዘው ልጆች የሚያስተምሩ ቀሳውስት የስራ ዋስትና የማጣት ስሜትና የልጆቻቸው ጉዳይ ቢያሳስባቸው ምን ይገርማል???እንዴ!!!እስኪ በራሳችሁ አስቡት!!!ቄሶችም እኮ ከቤ/ክ መልስ የሚመሩት ቤተሰብ አላቸው፡፡ስለዚህ ጉዳዩ የነፍስ ብቻ ሳይሆን የስጋም ጥያቄ አለበት፡፡የሚያበራየውን በሬ አፉን እንዳናስረው እንጠንቀቅ!!!ስንት የተማረ የሰው ሀይልና ፋይናንስ አለው የሚባለው መንግስት እንኩዋ በቢ.ፒ.አር(BPR) እና ቢ.ኤስ.ሲ(BSC) ትግበራ ወቅት ያየውን ፈተና ተመልከቱ፡፡እንደኔ እንደኔ ካህናቱ ጥናቱን ባያዩትም እንኩዋ የመቃወም መብት አላቸው!!!ጥናቱ ለምን ካህናትን ሳያካትት እንደተሰራና ባይካተቱ እንኩዋ ለቤ/ክ ያለውን ጠቀሜታ በትእግስት ማሰረዳት ደግሞ የአጥኚው ግዴታ ነው!!!
  4. መንግስት እንኩዋ አንድ ወቅት ያወጣው የሊዝ አዋጅ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲቀርብበት አዋጁን ኮፒ አድርጎ ለተወያዮች በማደል መጠነ ሰፊ የማወያየት ስራና የአዋጁን የተፈጻሚነት ጊዜ የማራዘም ስራ ሰርቱዋል፡፡እናንተም “ብትፈልጉ ተጠቀሙበት ባትፈልጉ ጋርቤጅ ጣሉት” እያላችሁ የግብር ይውጣ ስራ መስራት ሳይሆን በትእግስት ለማስረዳት ሞክሩ፡፡አሁን ጥያቄ እየተነሳ ያለው ገና እናንተ ከመድረክ ባቀረባችሁት ብቻ ነው፡፡ወደፊት ጥናቱ ተባዝቶ በዝርዝር ሲታይ ደግሞ ከዚህም በላይ ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል ጠብቁ፡፡
  5. በነገራችን ላይ የአባ ዕዝራን “ልጅና ጎረቤት” አገላለጽም ሆነ ከመድረክ የተሰጣቸው እልህ የተቀላቀለበትና ለምን ተነካሁ የሚመስል እሰጥ አገባ አልተመቸኝም ፡፡የአባ ዕዝራ ስሜት የብዙ አባቶችን የማህበሩን አባላት እንደ ልጅ ሳይሆን እንደ ክፉ ጎረቤት የማየት የስጋት አስተያየት የሚወክል ይመስለኛል፡፡ያው ልጅ አድጌያለሁ ብሎ ብቅ…ብቅ ሲል፣አባቴ አንተ አታውቀም, ዝም ብለህ እኔ የምልህን ብቻ እየሰማህ አድርግ ሲል አባት ልጁን ‘ጎጆ ስራና ወጥተህ እንጎራበት እንጅ በአንድ ቤት ሁለት የቤት ራስ አይኖርም’ ማለቱ የሚጠበቅ ነው፡፡
  6. እንደኔ ምልከታ(ግለሰባዊ እይታ እንጅ ጥናት አለመሆኑ ይታወቅልኝ) በአሁኑ ሰዐት ጥናቱ በቀጥታ በሚመለከታቸው ካህናትና የቢሮ ሰራተኞች አካባቢ ያለው ተቀባይነት ቀጥታ ስራ ላይ ለማዋል የሚያስችል አይደለም፡፡ስለዚህ የተሻለ ዘለቄታ፣ተቀባይነትና ተፈጻሚነት እንዲኖረው ከተፈለገ፡
  -ጥናቱ በብዙ ኮፒ ይባዛና ለብዙሀኑ ቀድሞ ይድረስ፣
  -ጥናቱ ካህናትንና ሊቃውንትን ባለማሳተፉ የተሰራውን ስህተት ለማረም በ16 ሰዎች ብቻ ሳይሆን በመላው የአ.አ አገልጋይ ነጥብ በነጥብ ተነስቶ ውይይት ይደረግበት፣
  -ከካህናቱ የተሰበሰበው ቅሬታ እንደ ግብዐት ተወስዶ ጥናቱ እንደአስፈላጊነቱ ይከለስ፣
  -ሲኖዶሱም በግራቀኝ የሚነፍሰውን ነፋስ ለማርገብና ጥናቱ ዘመን ተሸጋሪ እንዲሆን መመሪያ አድርጎ ከማጽደቁ በፊት ጥናቱን የሚገመግም ተዋጽኦውን የጠበቀ የባለሙያ ቡድን ቢያቁዋቁም፣
  – ከቃለ-ዐዋዲውም ሆነ ከአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ(አዋጅ ቁ.377/1996) ጋር ያለው ስምምነት በጥልቀት ይፈተሽ፣በተለይ ከሰራተኞች መብት አንጻር
  -በትንሹ ከአንድ አመት ያላነሰ የሽግግር ጊዜ እንዲኖረው ይደረግ፣አሁን የተያዘው ትንፋሽ የሚያቆም ሩጫና ጥናቱ ካልተተገበረ/ከተተገበረ ሞቼ እገኛለሁ የሚል እልህ ይስከን!!!!

  • maty December 20, 2013 at 11:44 am Reply

   3gnaw asteyaet sech balew esmamalew yegudayu balebet menfesawyi agelgayu kedash awedashu new asatfunnnn

 4. ms December 20, 2013 at 12:16 pm Reply

  ኣዬዬዬዬ! ማኅበሩ በትምህርተ ሃይማኖት ኣይታማም! ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ነው! ነገር ግን ይሄ የትምክህተኝነት ኣካሄድ ለቤተ ክርስትያኒቱ ኣደጋ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል! ጥሩ ክርስትያን መሆን መልካም ነው:: ነገር በክርሰትና ስም ፖሎቲካዊ ኣስተሳሰብ ማራመድ መንጀል ነው! ማኅበረ ቀዱሳን እኔ እስከማውቀው ከሃይማኖተኝነቱ ይልቅ ፖሎቲከኝነቱ ያመዝናል! እንደ ክርሰትያን መጠን ለቤተ ክርስትያኒቱ የሚያበረክተው ኣስተወጽኦ የምደግፍ ብሆንም የትምክህተኞች መሸሸግያ መሆኑን ግን ኣልደግፍም! የኣገሪቱ ሕገ መንግስት ኣክብሮ የማይነቀሳቀስ ከሆነ ግን ኣደገኛ ነው! በተለይ ለቤተ ክርስትያኒቱ ካህናትና ዲያቆናት የሚያሳየው የማሳነስ ባህርይ ሊስተካከል ይገባል! እውነት ነው ኣባቶች ካህናት ዘመናዊ ትምህርት ብዙም የተማሩ ኣይደሉም ነገር ግን ሊከበሩ እንጂ ሊናቁ አይገባም!

 5. Melaku December 20, 2013 at 4:20 pm Reply

  I think it is better to recognize existence of resistance whenever there is change!!!!
  change with out resistance is impossible!!!. So, we should accept it as a constructive idea!!!.

 6. Eskedar December 20, 2013 at 10:28 pm Reply

  In our Church management is necessary; waiting 1 year to accept is wrong, because it give time to theft the Church wealth.

 7. denberu sete December 22, 2013 at 11:29 am Reply

  በየወረዳው ሞደል 30 እያቃጠለ የመጣ ሁሉ አሁን ሲነቃበት ለውጡን ቢቃወም አይደንቀንም ዜና የሚሆነው ቢደግፍ ነበር እንጂ …. የሚገርመው ሌባ መናፍቅ እና የሰው ሚስት የሚያባልግ ሁልጊዜ ጠላቱ ማኅበረ ቅዱሳን መሆኑ ነው … ይህም አዲስ አይደለም … ችግሩ እነሱ ከደገፍን ነው፡፡ ….. ለማንኛውም እነዚህ ሰዎች ቢበቃቸው ነው የሚሻለው … እያወቅናቸው እንድህ ሊቀልዱብን አይገባም … ካሁን በኋላ ግን ሞደል 30 አቃጥሎ ቤት መስራት መኪና መግዛት መቆም አለበት …

 8. Melkamu December 24, 2013 at 10:10 am Reply

  Tequwamawi lewut balebet hulem yetelemede firacha, tekawumo, chinket balemum ale enkuan Bebetekrsian. Yihe min yigermal.

 9. Anonymous December 26, 2013 at 2:13 pm Reply

  አወቀ ከበባ/ዳር
  yehe gudagne yetekem inji geter ewotalehu bilo yemefrat ayedelem bewunet selzihe tinatu betlowu wodetegebare melewote yenorebtal

 10. Anonymous December 26, 2013 at 4:12 pm Reply

  eleleleleleleleleleleleleleleleleeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeee telate hoye bewodeke dese ayebelehi alech kidiset tewahido zare bakerebechiwu lemena meseret enibewa litabese new .eleeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeeelelelelelele betekiresetiyan mechegeruan yemitawuku hulu elele belu.

 11. birhanu April 3, 2014 at 5:28 pm Reply

  abetu ante kezih fetena awutan

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: