በጋሻው ደሳለኝ በይቅርታ ሚዛን ተመዘነ÷ ቀልሎም ተገኘ – ምእመኑን አስቆጣ አባቶችን አሳዘነ! የ‹ፀጉራሙ በግ› ታሪክ በሐዋሳ ተደገመ

Hawassa St. Gabriel Church

የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም

 • ‹‹በነበረው ሒደት በተለያየ ምክንያት ለበደላችኹን ኹሉ ይቅርታ አድርገንላችኋል፤ እናንተም ይቅርታ አድርጉ፤›› (በጋሻው ደሳለኝ፣ ኅዳር ፳፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.፤ ለሐዋሳ ደ/ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ምእመናን የተናገረው)
 • ‹‹ይኼ ጉልበት ላይ መውደቅ፣ ይቅርታ መጠየቅ በፍጹም እንዳያደርገው፡፡ ጉልበት ላይ መውደቅ፣ ይቅርታ መጠየቅ ማለት ጥፋተኛ ነኝ፤ ተሸማቅቄ እኖራለኹኝ ማለት ነው፤››   (በጋሻው ደሳለኝ፣ ግንቦት ፳፻፬ ዓ.ም. የክብረ መንግሥት ግብረ አበሮቹን ሲመክር)
 • የሐዋሳው የዕርቀ ሰላም መርሐ ግብር ከመጀመሩ አስቀድሞ በጋሻው ደሳለኝ የበደላትን ቤተ ክርስቲያንና ያሳዘነውን ምእመን ይቅርታ እንደሚጠይቅ በቤተ መቅደስ ለብፁዕ አቡነ ገብርኤል አረጋግጦላቸው ነበር፤ ብፁዕነታቸውም ሦስት ጊዜ ‹‹አጥፍቻለኹ÷ይቅርታ›› አሰኝተውት ነበር፡፡
 • ይቅርታ ጠያቂ ሳይኾን ይቅርታ አድራጊ እና ይቅር ባይ መስሎ በቀረበው የበጋሻው ደሳለኝ የእብሪት አነጋገር ያዘኑት አቡነ ገብርኤል እና አቡነ ሉቃስ ምእመኑን ይቅርታ ጠይቀዋል፤ በጋሻው ከእንግዲህ በአህጉረ ስብከታቸው ስፍራ እንደማይኖረው በቁርጥ የተናገሩት አቡነ ገብርኤል፣ ‹‹እርሱ መቼም የሚስተካከልና የሚመለስ ሰው አይደለም›› ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ‹‹አለመማር የሚያመጣው በሽታ ነው፤ ያሳዝናል›› ብለዋል፡፡
 • የሐዋሳው የዕርቀ ሰላም ሥነ ሥርዐት በተፈጸመበት ዕለት በደ/ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በተካሄደው የምሽት ጉባኤ ላይ ከአሜሪካ ተጉዛ የደረሰችውና በበጋሻው አነጋገር ማዘኗ የተነገረው ዘማሪት ወ/ሮ ፋንቱ ወልዴ ግለሰቡን ክፉኛ መገሠጽዋ ተሰምቷል – ‹‹ከአሜሪካ ድረስ ገንዘቤን አውጥቼ የመጣኹትና ያን ኹሉ የደከምነው ይቅርታ እንድትጠይቅ እንጂ እንድታበላሸው አልነበረም፡፡››
 • በ(ተ)ነሳሒነት የማያምነው በጋሻው ደሳለኝ፣ በሐዋሳው የዕርቀ ሰላም ስምምነት አጋጣሚ ቀልሎ የተገኘበት ሚዛን ያለቀኖናዊ ምርመራ በዕርቅ ሰበብ ወደ አገልግሎት እንዲመለስ የተሯሯጡለት እነወ/ሮ ፋንቱ ወልዴም አካሄዳቸውን እንዲያጤኑት አስገዳጅ ኹኔታ የሚፈጥር ነው ተብሏል፡፡
 • የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅ/ገብርኤል ምእመናን የዕርቀ ሰላም ሥነ ሥርዐት የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሠየማቸው ልኡካን ተከናውኗል፤ ለዕርቀ ሰላሙ ዕውቅና እንዲሰጥና ለስምምነቱ መከበር ጥንቃቄ እንዲደረግ ተጠይቋል፡፡

ባለፈው ሳምንት እሑድ፣ ኅዳር ፳፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የዕርቀ ሰላም ሥነ ሥርዐት በተከናወነበት ወቅት ይቅርታ እንዲጠይቅ የአቋራጭ ዕድል የተሰጠው በጋሻው ደሳለኝ÷ ይቅርታ ጠያቂ ሳይኾን ይቅርታ አድራጊና ይቅርታ ተቀባይ መስሎ የቀረበበትን ንግግር በማሰማት ምእመኑን ክፉኛ አስቆጥቷል፤ መድረኩን ያመቻቹለትንም ብፁዕ አቡነ ሉቃስን በእጅጉ አሳዝኗል፤ አበው ካህናቱ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ባሉበት ‹‹እግዚአብሔር ይባርካችኹ›› በማለትም የእብሪቱን ልክ ማሳየቱ ተመልክቷል፡፡

Begashaw roaring in arrogance_2

‹‹በነበረው ሒደት በተለያየ ምክንያት የበደላችኹንን ኹሉ ይቅርታ አድርገንላችኋል፤›› ይቅርታ ወይስ . . .

‹‹በነበረው ሒደት በተለያየ ምክንያት የበደላችኹንን ኹሉ ይቅርታ አድርገንላችኋል፤›› በማለት በከፍተኛ ድምፅ መናገሩ የተዘገበው በጋሻው፣ ቤተ ክርስቲያንን ያሳዘነበትን በደሉን በግልጥ አምኖ (ተ)ነሳሒ፣ ተጸጻች ለመኾን፣ እንደ እግዚአብሔር ሰው መጠን ክሣደ ልቡናውን ለማዋረድና በደሉን ለማፍሰስ ገና ብዙ እንደሚቀረው በዐደባባይ አረጋግጧል፡፡ በበደሉ ተቆጭቶና ከክፋቱ ተመልሶ ራሱን በመክሰስና በመውቀስ በርግጥ ያዘነና የተጸጸተ ኾኖ ባልታየበት ኹኔታም ‹‹እናንተም ይቅርታ አድርጉ›› በማለት ፌዘኛነቱን አሳይቷል፡፡

ለበጋሻው እንደመሰለው÷ በዕለቱ በሐዋሳ ደ/ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የተሰበሰበው ምእመን፣ እርሱ ‹‹ዐውደ ምሕረት ላይ ወጥቶ ቁልቁል የተመለከተው››‹‹ሲጠሩት የሚመጣና የነገሩትን ኹሉ የሚሰማ›› ነው፡፡ እንዲህም ስለሚያምን በሃይማኖት የሚጠየቅበትን ሕጸጹን አድበስብሶ በዋዛ ለማለፍ ያለው ፍላጎት የተጋለጠበትንና ‹‹ዋናው ማለፍ/መሻገር ነው›› ያለበትን ተረት ተናግሯል – ‹‹ሁለት በጎች በአንድ ቀጭን መንገድ ላይ ተገናኙ፤ ለማለፍ ሲሉ ርስ በርሳቸው ተገጣጥመው ሲፋጁ ቆዩ፡፡ አንደኛው በግ ወደ ልቡ ተመለሰና፣ እባክኽ ለዛሬ ሰው አድርገኝ፣ ላሳልፈው ብሎ ሲጸልይ አደረና ያኛው እየተንደረደረ ሲመጣ ይኸኛው አሳለፈው፤ ሁለቱም ተሻገሩ፤ ዋናው መሻገሩ ነው፡፡››

በዕርቀ ሰላም ጉባኤው ላይ የተስተዋለው የብዙኃኑ ምላሽ ግን በጋሻው እንደሚለው÷ ምእመኑ ‹‹ቁልቁል የሚታይና የነገሩትን ብቻ የሚሰማ›› አለመኾኑን በተግባር ያስመሰከረበት ነው፡፡

በጋሻው በተረተው ጠባቡ መንገድ ‹‹ዋናው መሻገሩ/መተላለፉ ብቻ ሳይኾን››፣ እርሱ ብዙኃኑን ያስቆጣበት የዐውደ ምሕረትና የኅትመት ውጤቶቹ ቀኖናዊ ምርመራና ይፋዊ ኑዛዜ እንደሚያስፈልጋቸው በይበልጥ የታመነበት ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊ ትምህርተ ሃይማኖትን በመፃረርና ክርስቲያናዊ ትውፊትን በማቃለል ለጥያቄ ለሚፈለግበት ጉዳይና ይህም ለሚጠይቀው ቀኖናዊ ሒደት የቅድሚያ ትኩረት ባለመስጠት እርሱን ዕርቅ በሚል ብቻ ወደ አገልግሎት ለመመለስ የደከሙለትን እነዘማሪት ወ/ሮ ፋንቱ ወልዴን፣ በመርሐ ግብሩ ዕለትም በእልልታና ጭብጨባ ያጀቡትን ጥቂቶች ሳይቀር ያሳፈረበት አጋጣሚ መኾኑ ነው፡፡

የሐዋሳ ከተማ አብያተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤያት፣ ሰንበት ት/ቤቶችና ምእመናን ከእንግዲህ ለበጋሻው ልብ እንዳልቀራቸውና ይኸው አቋማቸው የተሠመረበት ስለመኾኑ የተረጋገጠበትን በጎ ኹኔታ የተፈጠረበት ነው፡፡

Abune Mathias giving Benediction

‹‹በተለያየ ምክንያት ያስቀየምኋቸው ካላችኹ ይቅርታ እጠይቃለኹ››
የአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል

በእሑዱ የዕርቀ ሰላም መርሐ ግብር ወቅት በጋሻው በግልጽ ይቅርታ እንዲጠይቅ የሚያበረታታው በውዝግብ የተመቻቸለት የይቅርታ ዕድል/መድረክ ብቻ አልነበረም፡፡ በምሳሌነት የሚያስተምሩትና የሚያነሣሡት ንግግሮች በመርሐ ግብሩ ላይ ተሰምተው ነበር፡፡ ከእርሱ ቀደም ብለው የተናገሩት የአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ደጋግመውና ሠልሰው ‹‹በተለያየ ምክንያት ያስቀየምኋቸው ካላችኹ ይቅርታ እጠይቃለኹ›› እያሉ በከፍተኛ ስሜት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

የመርሐ ግብሩ አስተዋዋቂ የነበሩት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ምክትል ሐላፊ መምህር ሳሙኤል እሸቱም በብፁዕ አቡነ ገብርኤል ምጥንታ ላይ በመመሥረት÷ ‹‹የብፁዕ አባታችን ተማኅፅኖ አበጥ አበጥ ያለ ልባችንን ይሉኝታ ሊያስይዝ ይገባል፤›› በማለት በኋላ በጋሻው ያሳየውን እብሪት አስቀድሞ የጠቆመ የሚመስል የምክር ቃል ተናግረው ነበር፡፡

ከዚህ ኹሉ በኋላ ሁለቱም ወገኖች በተስማሙበት መርሐ ግብር ዝርዝር መሠረት ያልተጋበዘ እንግዳ ኾኖ ወደ ዐውደ ምሕረቱ የወጣው በጋሻው ግን በብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ የይቅርታ ጥያቄ ወይም ራሱን በራሱ ከመውቀስና ከመክሰስ፣ በመርሐ ግብር አስተዋዋቂው የምክር ቃል ከመገሠጽ ይልቅ ‹‹አበጥ አበጥ ካሉት ውስጥ አንዱ እኔ ነኝ፤ ድምፄን ለማቅጠን፣ ሰውነቴን ለማክሳት አልችልም›› በማለት መሣለቅን ያስቀደመው፡፡ የመርሐ ግብር አስተዋዋቂው ለበጋሻው ተሣልቆ የሰጡትና ግለሰቡ ክፉኛ የተቃለለበት ምላሻቸው፡- ‹‹አበጥ አበጥ ያለ. . .ያልኹት ልባችንን፣ አስተሳሰባችንን ነበር፤ አበጥ አበጥ ያለው አካላችን/ሥጋችን ከኾነም አስሮጥኻለሁ›› የሚል ነበር፡፡

በጋሻው ተመዝኖና ቀልሎ በተገኘበት የእብሪትና ያላዋቂነት አነጋገሩ የምእመኑ ቁጣ ብቻ አልነበረም የተረጋገጠው፡፡ ከቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተቀበሉትን የዕርቀ ሰላም ተልእኮ ለማስፈጸም በስፍራው የተገኙትን ብፁዓን አባቶች፣ ይልቁንም ከዕርቀ ሰላም ስምምነቱ ውጭ በጋሻው በመጋበዙ ቅሬታ የነበራቸውን ምእመናን ተጭነውና ሓላፊነቱን ወስደው ግለሰቡ ይቅርታ የመጠየቅ ዕድሉን እንዲያገኝ ያመቻቹለት የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ሐዘን በግልጽ ተስተውሏል፡፡

His Grace Abune Lukas

‹‹ልጆቻችን እናንተ አክብራችኹናል፤ ዋናው ዓላማችን ሰላሙና አንድነቱ ነው እንጂ ለእርሱ ቦታ ለመስጠት አልነበረም፤››
ብፁዕ አቡነ ሉቃስ

በጠዋቱ መርሐ ግብር ከበጋሻው ቀደም ብለው የሰላምንና አንድነትን አስፈላጊነት አጽንዖት በመስጠት ያስተማሩት ብፁዕ ዋና ጸሐፊው፣ ሦስቱም ልኡካን በተሳተፉበት በማታው የስብከተ ወንጌል ፕሮግራም ላይ ‹‹ዕንቁላል ሰብሮ ሊወጣ ይችላል፤ ሰብሮ መግባት ግን አይችልም፤›› በሚሉ ኃይለ ቃሎች በአጽንዖት ተናግረዋል – ምሳሌያዊ አነጋገሩ ብፁዕነታቸው ‹‹ሊያበላሽብን ነበር›› በሚል ያፈሩበት በጋሻው፣ በተጠየቀበት ቀኖናዊ አካሄድ እስካላለፈ ድረስ የሚጠብቀውን አስቸጋሪ ጊዜ የጠቆመ ነው እንደኾነ ታምኖበታል፡፡ ከዚህም በላይ ከመርሐ ግብሩ ፍጻሜ በኋላ የምእመናን ተወካዮችን ያነጋገሩት ብፁዕ ዋና ጸሐፊው፣ ምእመኑ የበጋሻውን አነጋገር በመታገሥ ስላሳየው ጨዋነት አመስግነዋል፤ ‹‹ልጆቻችን እናንተ አክብራችኹናል፤ ዋናው ዓላማችን ሰላሙና አንድነቱ ነው እንጂ ለእርሱ ቦታ ለመስጠት አልነበረም፤›› በማለት ማጽናናታቸው ተዘግቧል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ በተወካዮች በኩል ያስተላለፉትን መልእክት የሚጋሩት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ ‹‹እግዚአብሔር ይባርካችኹ›› በሚለው የበጋሻው ንግግር ማጠቃለያ መሠቀቃቸውንና እጃቸውን በማንሣት ጭምር ሲቃወሙት እንደነበር የዐይን ምስክሮች አረጋግጠዋል፡፡

የዕርቀ ሰላም መርሐ ግብሩ ከመጀመሩ አስቀድሞ በጋሻው ደሳለኝ የበደላትን ቤተ ክርስቲያንና ያሳዘነውን ምእመን ይቅርታ እንደሚጠይቅ በቤተ መቅደስ ውስጥ ለብፁዕ አቡነ ገብርኤል አረጋግጦላቸው ነበር፤ ብፁዕነታቸውም እጁን ይዘው ሦስት ጊዜ ‹‹አጥፍቻለኹ÷ይቅርታ›› አሰኝተውት ነበር፡፡

በይቅርታ የማያምነውና ‹‹ቀዝቅዟል›› የሚለውን ‹ዝናውን› ለማሟቅ ግርግርን የሚጠቀመው በጋሻው ግን በዐውደ ምሕረቱ ላይ በቃሉ ባለመገኘቱ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ክፉኛ እንዳዘኑበት ተገልጦአል፡፡ በጋሻው ከእንግዲህ በአህጉረ ስብከታቸው ስፍራ እንደማይኖረው ለምእመናን ተወካዮች በቁርጥ የተናገሩት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ ‹‹እርሱ መቼም የሚስተካከልና የሚመለስ ሰው አይደለም›› ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አበው ካህናት፣ የሁለቱም ወገኖች የዕርቀ ሰላም ኮሚቴ አባላትና የዕርቀ ሰላም አመቻች ግለሰቦችን እንዲሁም የከተማው አስተዳደር ለዕርቀ ሰላሙ መሳካት ላደረጉት አስተዋፅኦ አመስግነዋል፡፡

the three bishops

‹‹አለመማር የሚያመጣው በሽታ ነው፤ ያሳዝናል››
ብፁዕ አቡነ ማትያስ ዘካናዳ

የዕለቱን ጸሎተ ቅዳሴና ጸሎተ ምሕላ የመሩት በዕርቀ ሰላም ሥነ ሥርዐቱ ፍጻሜም ጸሎተ ንስሐ የሰጡት የካናዳው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ናቸው፡፡ በዕርቀ ሰላሙ የተገኘው ሰላምና ስምምነት እንዲጠበቅ አዘውትሮ መጸለይ አስፈላጊ መኾኑን አበክረው የተናገሩት ብፁዕ አቡነ ማትያስ እንደ ሁለቱ ብፁዓን አባቶች ኹሉ የበጋሻውን የእብሪት አነጋገር ታዝበዋል፡፡ በጋሻውን በአካል እንደማያውቁትና ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳዩት ለምእመናን ተወካዮች የተናገሩት ብፁዕነታቸው ‹‹ተርታ ሰው›› ኾኖ እንዳገኙት ገልጸዋል፤ መሠረታዊ ችግሩ አለመማሩ መኾኑን በመጥቀስ ማንንም አስተምራለኹ ብሎ ከመነሣቱ በፊት ለራሱ ማወቅና መማር እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል – ‹‹በአካል አላውቀውም፤ ዛሬ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኹት፤ በጣም ተርታ ሰው ኾኖ ነው ያገኘኹት፤ አለመማር የሚያመጣው በሽታ ነው፤ ያሳዝናል፡፡››

በአጠቃላይ አንድ ምእመን ለሐራዊ ምንጮች እንደተናገረው፣ አጋጣሚው የፀጉራሙን በግ ምሳሌ የሚያስታውስ ነው – ‹‹በአንድ መንደር የሰባ ነው፣ ላታም ነው እየተባለ የሚሞጎስ ፀጉራም በግ ነበር፡፡ አባ ወራውም ከመንደሩ ኹሉ ወፍራሙ በግ የእኔ ነው እያለ ይኩራራበት ነበር፡፡ አንድ ቀን ታላቅ እንግዶች ወደ ቤቱ ሲመጡ አባወራው ወፍራሙ በጌ ካልታረደ ይላል፡፡ ሚስቱ ይቅርብኽ ብላ ብታከላክለውም ባለመስማቱ ፀጉራሙ በግ ይታረዳል፡፡ የሰባ ነው፤ ላታም ነው ከተባለው በግ የተገኘው ግን አጥንትና ቆዳ ብቻ ነበር፡፡ ባለቤቱ አፈረ፡፡ በጉ ሲታረድ ዱለት፣ ላት፣ ጉበት እንበላለን ብሎ ያማረው ኹሉ ‹ካረድኽ አስብተኽ ባረድኽ፤ ካላረድኽም አለኝ እያልኽ በኖርኽ› እያለ በሰውዬው ዘበተ፤ የእርሱ ነገርኮ በቃ. . .ተባለ፡፡››

በሐዋሳው የዕርቀ ሰላም ሥነ ሥርዐት አጋጣሚ ‹‹የበጋሻው ነገር በቃን›› መሰል ሐዘንና ቁጣ ቢታይም ለገዳሙ የስብከተ ወንጌልና የልማት ኮሚቴዎች፣ ለሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ለምእመናኑ አገልግሎታቸውን በተጠናከረ እንቅስቃሴ የሚቀጥሉበት የአንድነትና የመተባበር ምዕራፍ የከፈተላቸው ኾኗል፡፡

በመርሐ ግብሩ ጅማሬ ከቤተ ክርስያቲያኑ አገልግሎት ተለይተው ለነበሩት፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማና የክልሉን ባንዴራ ከቅዱሳት ሥዕላት ጋራ እያሳዩ ወደ ቅጽረ ገዳሙ ለዘለቁ በቁጠር እስከ 500 ለሚኾኑ ምእመናን ‹‹እንኳን ደኅና መጣችኹ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወደ እናታችኹ›› በሚል በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ በሰንበት ት/ቤቱ መዘምራንና መላው ምእመን በእልልታና በመዝሙር አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

አዲሱ የገዳሙ አስተዳዳሪ ‹‹እንኳን ደኅና መጣችኹ፤ ተቀብለናችኋል፤ በቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ውስጥ ሙሉ ተካፋይ መኾን ይገባችኋል›› በማለት አባታዊ ጥሪ አድርገውላቸዋል፡፡ የክልሉንና የከተማውን አስተዳደር በመወከል ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንና ከከተማው የፍትሕና ጸጥታ ቢሮ የተገኙ ሓላፊዎች፣ ለዕርቁ ዕውቅና በመስጠት በሰላም ጉዳዮች ላይ ከቤተ ክርስቲያናችን ጋራ አብረው መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉ በመግለጽ ተገቢውን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በቀጣዩ የአገልግሎት ምዕራፍ በዕርቀ ሰላም ስምምነቱ መሠረት ዘጠኝ አባላት ባሉት የሰንበት ት/ቤቱ ሥራ አመራር ኮሚቴ ላይ ሁለት አባላት ተጨምረዋል፡፡ አምስት፣ አምስት አባላት ባሏቸው የስብከተ ወንጌልና የልማት ኮሚቴዎች ውስጥ ሁለት፣ ሁለት አባላት ተጨምረዋል፡፡ ሦስተኛና የመጨረሻ ዓመቱን በያዘው የገዳሙ ሰበካ ጉባኤ የተደራጁት ሁለቱ ኮሚቴዎች፣ ከሰበካ ጉባኤው አዲስ ምርጫ ጋራ የመዋቀር ዕድል እንዳላቸውን በእኒህም ኹሉ የመምረጥና የመመረጥ መብታቸው ይጠበቅላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በሀ/ስብከቱ የማኅበረ ቅዱሳን የሐዋሳ ማእከል አባላት በሰበካ ጉባኤ እና በሰንበት ት/ቤት ባላቸው አገልግሎት ላይ በሚያዝያ ፳፻፫ ዓ.ም. ጀምሮ የተጣለውና መተዳደርያ ደንቡን የሚፃረረው ማዕቀብ ተሽሮ የአባላቱ የአገልግሎት ተሳትፎ መብት መጠበቁ ተገልጦአል፡፡welcoming banner

Advertisements

67 thoughts on “በጋሻው ደሳለኝ በይቅርታ ሚዛን ተመዘነ÷ ቀልሎም ተገኘ – ምእመኑን አስቆጣ አባቶችን አሳዘነ! የ‹ፀጉራሙ በግ› ታሪክ በሐዋሳ ተደገመ

 1. Anonymous December 15, 2013 at 11:01 am Reply

  atferad yfradbhal.

 2. Anonymous December 25, 2013 at 8:59 am Reply

  ጌታ ኢየሱስ ሰሙ ለዘላለም የተመሰገነና የተባረከ ይሁን እኔም ከዚህ በታች ያለዉን ልጋብዛችሁ

  ወንድሞቼ/ እህቶቼ ይህችን መዝሙር በህብረት እንዘምር
  እሰይ ስለቴ ሰመረ፣ እሰይ ስለቴ ሰመረ፤
  ቅዱስ ሲኖዶሱም እውነት መሰከረ፤
  እሰይ ስለቴ ሰመረ፣ እሰይ ስለቴ ሰመረ፣
  በጋሻው ደሳለኝ ስራውን ጀመረ፤
  እሰይ ስለቴ ሰመረ፣ እሰይ ስለቴ ሰመረ፣
  ከሳሽ ማህበርም በስራው አፈረ፤
  እሰይ ስለቴ ሰመረ፣ እሰይ ስለቴ ሰመረ፣
  ስራ አስኪያጁም ከሐዋሳ ተጫረ ፤
  እሰይ ስለቴ ሰመረ፣ እሰይ ስለቴ ሰመረ፣
  የልዩነት መንፈስ ከእኛ ላይ በረረ፤
  እሰይ ስለቴ ሰመረ፣ እሰይ ስለቴ ሰመረ፣
  የተዋህዶ ልጆች አንድነት በሰረ፤
  እሰይ ስለቴ ሰመረ፣ እሰይ ስለቴ ሰመረ፣
  እልልልልልልልልልልልልልልልልልልል

 3. Anonymous December 25, 2013 at 12:52 pm Reply

  እስቲ ነገር ከምታስተምሩን የእግዚአብሔርን ቃል አስተምሩን ፡፡ ለምንስ ውሽት ታወራላችሁ እናንተ ለመሆኑ ክርስትያኖች ናችሁ? እኛ በዛን ቀን ነበርን እኮ፡፡ እግዚኦ ይህ ሁሉ ውሽት እውነት ለቤተክርስቲያን በመቆርቆር ነው? በወሬ እኮ ጽድቅ የለም መደመጥም፣ መባረክም፣ መመረጥም ከእግዚአብሔር፡፡

 4. Anonymous December 26, 2013 at 9:18 am Reply

  ምናልባት በእርቁ ቦታ ካልነበራችሁ ለምን ውሸት ታወራላችሁ፡፡ ሕዝቡ መቼ ነው ያዘነው? እንዲሁም ካልነበራችሁ እንንገራችሁ ሕዝቡ በደስታና በእልልታ ነው የተቀበላቸው፡፡ ያሳታረቁ አባቶችም በሕዝቡ ተመስግነዋል፡፡ እነርሱን የመረጣቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር ያከበረውን ደግሞ ማንም አያዋርደውም/ማንም አያቀለውም፡፡ በጋሻውንም የመረጠውና እንዲደመጥ ጸጋን የሰጠው እርሱ ልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ እኛን በእርሱ አድሮ ብዙ ነገር እግዚአብሔር ተናግሮናል በዚህም ደስተኞች ነን፡፡ እኛ የዲያቢሎስን ምክር ከቶ አንሰማም፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ግን እንሰማለን፡፡ ኧረ ተውን እኛ ከሆነ ወሬ አንሰማም እርሱን እግዚአብሔር እንዲጠብቀውና ቀሪ የሰብከት ዘመኑን እንዲባርክልን ዕድሜና ጤናን እንዲሰጠው እንጸልያለን፡፡ ለእናንተም እግዚአብሔር ልቦናውን ያድላችሁ፡፡ አሜን

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: