የቅ/ሲኖዶስ የሲዳማና ጉጂ ቦረና አህጉረ ስብከት ልኡክ ነገ በሐዋሳ የዕርቀ ሰላም መግለጫ ያወጣል፤ ዕርቀ ሰላሙና መግለጫው የሐዋሳውን ውዝግብ ብቻ እንጂ በሊቃውንት ጉባኤው ፊት ቀርቦ እንዲጠየቅ የታዘዘውን በጋሻው ደሳለኝንና ሌሎች ሕገ ወጦችን አይመለከትም

 • ዕርቀ ሰላሙን በሚያወርደው የሁለቱም ወገኖች ስምምነት መሠረት ከኅዳር ወር ፳፻፫ ዓ.ም. ጀምሮ ከሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተለይተው ‹‹ወንዲታ›› በተባለው የግለሰብ ስቱዲዮ ውስጥ ሲሰበሰቡ የነበሩ ምእመናን÷ በሰንበት ት/ቤት፣ በስብከተ ወንጌል እና በልማት ኮሚቴዎች ውስጥ የመሳተፍና የማገልገል መብታቸው ይጠበቅላቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት በሰንበት ት/ቤቱ አመራርና በስብከተ ወንጌል ኮሚቴ ሁለት፣ ሁለት፤ በልማት ኮሚቴ ውስጥ ደግሞ በሰበካ ሳይወሰኑ እስከ አምስት አባላትን በማሳተፍ የማገልገል መብት ይኖራቸዋል፡፡
 • የ‹‹ወንዲታ›› ተሰብሳቢዎች ጥያቄ ያነሡበት የደብረ ምሕረት ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ በቃለ ዐዋዲው ደንብ መሠረት የተመረጠ በመኾኑ የሥራ ጊዜውን ሲጨርስ በሚያካሂደው አዲስ ምርጫ ብቻ ይተካል፡፡ በሌሎች የከተማው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ያለ ሰበካቸው በሰበካ ጉባኤያት የተመረጡ ምእመናን ካሉ በአህጉረ ስብከቱ ተጣርቶ እርምት እንዲደረግበት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
 • ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው ባወጣቸው መመሪያዎች መሠረት በቤተ ክርስቲያናችን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሚሰጡ ሰባክያንና መምህራን ሕጋዊነት የሚኖራቸው፡- 1) የቤተ ክህነቱ ሠራተኛ ሲኾኑ፣ 2) የጠቅላይ ቤተ ክህነት ማስረጃ ሲኖራቸው፣ 3) በአህጉረ ስብከት የመምህራን ይላክልን ጥያቄ ሲቀርብ ነው፡፡
 • ስለኾነም ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት ለመስጠትና ለአገልግሎቱ መሳካት ይረዳ ዘንድ ሰባክያንና መምህራነ ወንጌል÷ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ወይም ከአህጉረ ስብከት ጽ/ቤት ወይም ከአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት ዕውቅናና ፈቃድ ሊያገኙ ይገባል፡፡
 • በዚህ መሠረት ያለ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ ያለሀ/ስብከቱና ያለብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ማዘጋጀት ይኹን ሰባክያንና መምህራንን መጋበዝ እንደማይቻል፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱም ከቡድናዊ ተጽዕኖዎች ነጻ ኾኖ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት መጠናከርና መስፋፋት ማዕከል አድርጎ መፈጸም እንደሚገባው በሐዋሳው የዕርቀ ሰላም ስምምነት ላይ ተገልጦአል፡፡

*                      *                        *

 • ሁለቱ ወገኖች (የሐዋሳ ደ/ምሕ/ቅ/ገብርኤል ገዳም ልማት ኮሚቴ አባላት የኾኑ የምእመናን ተወካዮች እና በወንዲታ ስቱዲዮ ተሰብሳቢዎች) በቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት በዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ሰብሳቢነት ባካሄዱት የሁለት ቀን የፊት ለፊት የዕርቀ ሰላም ውይይት÷ ‹‹ግለሰባዊ››፣ ‹‹ሀገረ ስብከታዊ›› እና ‹‹ሲኖዶሳዊ›› በሚል የተከፈሉ ችግሮች በዝርዝር መቅረባቸው ተገልጦአል፡፡
 • በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ኅዳር ፭ እና ፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በተካሄደው የሁለቱ ወገኖች የዕርቀ ሰላም ውይይት፣ ‹‹ሀገረ ስብከታዊ›› በሚል ከ‹‹ወንዲታ ስቱዲዮ ተሰብሳቢዎች›› ከቀረቡት ነጥቦች ውስጥ የሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸት ገብረ ጻድቅ ከሓላፊነታቸው መነሣት እንዳለባቸው የቀረበው ጥያቄ አንዱ እንደነበር ተመልክቷል፡፡
 • ይኸው ጥያቄ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ገብርኤልም ከሀ/ስብከቱ እንዲነሡ ከሚጠይቀው የሐዋሳ፣ ክብረ መንግሥት፣ ነገሌ ቦረና ሠላሳ ጠርዘኛ ግለሰቦች ከባለሥልጣናት እንደተሰጣቸው በተነገረ ድጋፍ በቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ፊት ካቀረቡት የተለየ እንደኾነ የገለጸው የዜና ምንጩ÷ ሥራ አስኪያጁ በአስተዳደርና በሥነ ምግባር ባለባቸው ግልጽ ችግር ሳቢያ ከሓላፊነት መነሣታቸው ሁለቱም ወገኖች የተስማሙበት መኾኑንና በዚህም መሠረት በሚመለከተው አካል ርምጃ መወሰዱን ገልጦአል፡፡
 • ‹‹ሲኖዶሳዊ›› በሚል እንደ ችግር የቀረበው፣ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ሐዋሳ ማዕከል አባላት በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ጉዳይ ጣልቃ አይግባ›› በሚል መነሻ በቀድሞው ፓትርያርክ ርእሰ መንበርነት የተመራው ቋሚ ሲኖዶስ በቁጥር 3378/56/2003 በቀን ፲፫/፰/፳፻፫ ዓ.ም. ለሀ/ስብከቱ ያስተላለፈውን በምልአተ ጉባኤው የጸደቀውን የማኅበሩን መተዳደርያ ደንብ በእጅጉ የሚፃረር ውሳኔ ተፈጻሚነት የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ውሳኔ ሽፋን የሐዋሳ ምእመናን አንገብጋቢ ጥያቄዎች ሲደፈቁ መኖራቸውን ያስታወሰው የመረጃ ምንጩ÷ የማኅበሩ አባላት በየአጥቢያቸው በሰበካ ጉባኤ፣ በሰንበት ት/ቤት፣ በስብከተ ወንጌልና በልማት ኮሚቴዎች የመምረጥና የመመረጥ መብታቸው የተጠበቀ እንደኾነ በዕርቀ ሰላም ስምምነቱ ላይ መስፈሩን ጠቅሷል፡፡

*                      *                        *

 • የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥቅምት ፳፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ እንደጠቀሰው፣ ከ፳፻፫ ዓ.ም. ጀምሮ የተፈጠረው ‹‹ሁከት›› ‹‹በዕርቅ›› እንዲፈጸም ጥያቄ ያቀረቡት ሁለቱም ወገኖች ናቸው፡፡ ይኹንና ጉዳዩ ከዕርቅ መንገድ ይልቅ ከቤተ ክርስቲያን የወጡ ወገኖች ጥፋታቸው እንደ ግለሰብ መጠን በዝርዝር እየተለየ ስሕተታቸውን አምነው ንስሐ በመግባት ቀኖናዊ መንገድ እንዲመለሱ በማድረግ መፈጸም ይገባው እንደነበር በመጥቀስ የተደረሰውን የዕርቀ ሰላም ስምምነት የሚተቹ ወገኖች ተደምጠዋል፡፡   
 • በሌላ በኩል ዕርቀ ሰላሙና ስምምነቱ÷ ‹‹ሊቀ ጳጳሱ ይነሡ››፣ ‹‹ዐውደ ምሕረቱን መቆጣጠር ሀ/ስብከቱን መቆጣጠር ነው›› በሚል የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴውን፣ በተለይም በደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤና ሰንበት ት/ቤት ላይ ያለከልካይ ለመንሰራፋት ለሚያልሙቱ፤ ከእነርሱም መካከል የፕሮቴስታንት ባለሥልጣናት አስተዳደራዊ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው የሚነገርላቸውን ግለሰቦች ጥፋት ለመከላከል እንደሚያስችል የሚያምኑ አስተያየት ሰጭዎች በበኩላቸው፣ ከ፳፻፫ ዓ.ም. ጀምሮ ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆች ጋራ የዓላማና ጥቅም ግንኙነት ፈጥረው ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ሲደረግላቸው ለቆዩ አካላት የጅምላ ፈቃድ ና ሾልኮ መግቢያ እንዳይኾን አፈጻጸሙን በከፍተኛ ጥንቃቄና ያለማቋረጥ መከታተል እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ፡፡
 • የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እዚያው ሐዋሳ ተገኝተው ዕርቀ ሰላሙን እንዲያወርዱ የሠየማቸው ብፁዓን አባቶች÷ ብፁዕ አቡነ ማትያስ የካናዳ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የጅማ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና በክልል ትግራይ የምዕራብ ሰቲት ሑመራ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነገ፣ ኅዳር ፳፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅ/ገብርኤል ገዳም ዐውደ ምሕረት ላይ ተገኝተው ሁለቱ ወገኖች የደረሱበትን የዕርቀ ሰላም ስምምነት በመግለጫ መልክ ለመላው የሐዋሳ ኦርቶዶክሳዊ ምእመን ይፋ ያደርጋሉ፡፡
 • ይኸው ዕርቀ ሰላም ስምምነት መግለጫ ሥነ ሥርዐት ስምምነቱን የሚፃረር አላስፈላጊ ትዕይንት ለማሳየት ሊጠቀሙበት ከሚያስቡ አካላት አደፍራሽ ድርጊት ሊጠበቅ እንደሚገባ በርካታ ወገኖች እያሳሰቡ ነው – ‹‹ጥቁር ጨርቅ አውለብልበን እንደወጣን ነጭ ጨርቅ እያውለበልብን እንገባለን፤ በጋሻውን በመካከል አድርገን እየዘመርን እንገባለን›› የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡

*                      *                        *

 • ኦርቶዶክሳዊ ትምህርተ ሃይማኖትንና ትውፊትን የሚፃረሩ ንግግሮችን ከመናገር አልፎ ‹‹እርስዎ ፈቃድ ሊሰጡኝም ሊነሱኝም አይችሉም›› እያለ መመሪያቸውን እየጣሰ ሕገ ወጥ ጉባኤያትን ሲያካሂድ የቆየው በጋሻው ደሳለኝ፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እግር ላይ ወድቆ ይቅርታ ጠይቋል፤ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ የይቅርታ ጥያቄውን ሲቀበሉ ስለ ሃይማኖት ሕጸጽ የቀረበበት ጥያቄ በተጀመረበት ቀኖናዊ መንገድ ማለቅ ያለበት በመኾኑ የይቅርታ ጥያቄውን የሚቀበሉትና ይቅርታ የሚያደርጉለት በግላቸው እንደ መንፈሳዊ አባት መጠን መኾኑን ግልጽ አድርገውለታል – ‹‹በግሌ የተጣላኹት ሰው የለኝም፤ ብትሰድበኝም ድንጋይ ብትወረውርብኝም መጥተኽ ጉልበቴ ላይ ስትወድቅ አባት ነኝና ይቅርታ አደርግልሃለኹ፡፡››
YeBitsuan Liqane Papasat ena Likawunet Timir Gubae on Begashaw

የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጥምር ጉባኤ ሚያዝያ ፴ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. ለጥያቄ ተፈልጎ ስላልቀረበው በጋሻው ደሳለኝ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ያቀረበው ሪፖርት

Holy Synod on Begashaw

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ የኾኑ 7 ድርጅቶችንና 16 ግለሰቦችን ባወገዘበት ውሳኔው በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና በሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጥምር ጉባኤ ለጥያቄ ተጠርቶ ስላልቀረበው በጋሻው ደሳለኝ የሰጠው ትእዛዝ

 • እንደ በጋሻው ለይቅርታ ጥያቄ ወደ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ የቀረበው ዲ/ን ያሬድ አደመም ‹‹የሐዋሳ ችግር የምእመናኑ፣ የሰበካ ጉባኤውና የሀ/ስብከቱ ጉዳይ ስላለበት በእኔ ብቻ የሚያልቅ አይደለም፤›› የሚለው የሊቀ ጳጳሱ አቋም ከተገለጸለት በኋላ ነበር የዕርቀ ሰላሙ ሂደት ለደረሰበት ፍጻሜ ግንባር ቀደም ኾኖ የተንቀሳቀሰው፡፡ በዚህም የ‹‹ወንዲታ›› ስቱዲዮ ተሰብሳቢ ከኾኑና ለዕርቀ ሰላም ውይይቱ ተወክለው ከመጡ ዘጠኝ ግለሰቦች መካከል ከሦስቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር ተዘግቧል፡፡
 • ‹‹ሊቀ ጳጳሱና ሥራ አስኪያጁ ከሀ/ስብከቱ ይነሡ፤ የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅ/ገብርኤል ገዳም ሰበካ ጉባኤ፣ ሰንበት ት/ቤትና ልማት ኮሚቴ ፈርሶ ዳግመኛ ይዋቀር›› ለሚሉት ‹ጥያቄዎቻቸው› የሽምግልናን/የዕርቅን መንገድ ሳይኾን የቅ/ሲኖዶሱን ቀጥተኛ ውሳኔ እንደሚሹ መስከረም ፳፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት በተካሄደ ውይይት ላይ ገልጸው የነበሩት ሦስቱ የዲ/ን ያሬድ አደመ ተቃዋሚዎች፣ ሕዝቡ ከእነርሱ ጋራ መሰለፉን በመናገር ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሚመሩትን ውይይት አቋርጠው መውጣታቸው ተሰምቷል፡፡

*                      *                        *

 • አሁን ለተደረሰው የሐዋሳ ዕርቀ ሰላምና ስምምነት ከጥቅምት ወር ፳፻፫ ዓ.ም. ወዲህ የተጀመረውና የተቀጣጠለው የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ንቅናቄ ለመላው አገልጋይና ምእመን የፈጠረው ግንዛቤ ኹነኛ አስተዋፅኦ እንዳለው እየተጠቀሰ ነው፡፡ ንቅናቄውን ተከትሎ የሕገ ወጥ ሰባክያንና  ዘማርያን የእንቅስቃሴ አድማስና ዕድል ተገድቧል፤ ሲዲዎቻቸውንና ቪሲዲዎቻቸውን የሚያትሙና የሚያሰራጩ ‹መዝሙር› ቤቶችም ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርገው እስከ መዘጋት ደርሰዋል፡፡ ዲ/ን ያሬድ አደመና በጋሻው ደሳለኝ የዕርቀ ሰላሙን ጅምር ለወሰዱ አመቻቾች እንደመሰከሩት፣ ይህ የእንቅስቃሴ ገደብ በተለይ በሐዋሳና በአዲስ አበባ በስብስቡ ውስጥ በሚገኙ ግለሰቦች ላይ ከፍተኛ ሥነ ልቡናዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና አሳድሯል፡፡
 • በተለይ የኑሮ ጫናው ‹‹እነበጋሻው በመድረክ ያስተዋውቁናል፤ ግጥምና ዜማ ይሰጡናል፤ እንደ ምርትነሽና ዘርፌ እንኾናለን›› በሚል በተቀላቀሏቸውና ከድምፃቸው በቀር ትምህርት ይኹን ሌላ ሞያ የላቸውም በሚባሉት ሴቶች ላይ መበርታቱንከእኒህም መካከል የኑሮ ጫናውን መቋቋም ባለመቻላቸው ወደ ዐረብ አገር የተሰደዱ መኖራቸውን የቡድኑ መሪዎች ይናገራሉ፡ከዚህ በላይ አሳሳቢ የተባለው ግን ጫናው በቆይታ በመካከላቸው የፈጠረው የአቋም/የጎራ መከፋፈል ነው፡፡
 • ይኸውም በአቋም ክፍፍሉ በይፋ ይቅርታ ጠይቆ የመመለስ ሐሳብ ያነሡ እንዳሉ ኹሉ ‹‹እኔ የኢየሱስ ነኝ›› እያሉ በግላጭ የወጡ፣  በሚያባብሏቸው መናፍቃንና አንዳንድ ባለሥልጣናት ፈንድ ለመደገፍ የተስማሙና ፈንዱን የተቀበሉ፣  ‹‹የራሳችንን ቸርች እናቋቁማለን›› በሚል ከከተማ አስተዳደር መሬት የጠየቁና በዚህ ረገድ ከአንዳንድ የፕሮቴስታንት ባለሥልጣናት ማበረታቻ የሚደረግላቸው፣ ወደ ፕሮቴስታንቶች ቤተ ጸሎት በግላጭ መሔድ የጀመሩ፣ ከፍተኛ ክፍያ በሚከፈልባቸው የኪራይ ቤቶች ፓስተሮችንና የተወገዙ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ግለሰቦችን እየጋበዙ እስከ መማር የደረሱ ድሉል አፍቃሬ ፕሮቴስታንት ዘማርያንና ሰባክያን ነን ባዮች መታየታቸው ነው፡፡  
 • ኹኔታው ‹‹ከባድ ስጋት፣ ጸጸትና የተጠያቂነት ስሜት›› እንደፈጠረበት ለዕርቀ ሰላሙ አመቻቾች መናገሩ የተገለጸው ዲ/ን ያሬድ አደመ፣ በሐዋሳም በአዲስ አበባ ለሚገኙት ለእኒህ ‹‹ጥራዝ ነጠቆች›› ለሁለት ወራት ያህል ኮርስ ለመስጠት መገደዱን አልሸሸገም፡፡ በጋሻው ደሳለኝ ስለዚህ ኹኔታ ሲያስረዳ፡- ‹‹4 ኪሎዎች(?) እኛ የማርያም ነን ይላሉ በሚል እኛ የኢየሱስ ነን ብለው እንደዋዛ ነው ጀመሩት፡፡ በነገሩ እያመረሩ መጡና አነጋገራቸው፣ ኹለመናቸው ፕሮቴስታንታዊ ኾነ፤ ልጆቹ በአንዳንድ ምእመናንና በዐውደ ምሕረት ሳይቀር ይታይባቸው በጀመረው አኳኋን ቀጥለው ካመለጡን ይቅርታ ጠየቅን አልጠየቅን፣ ሲኖዶሱ ተመለሱ አለን አላለን ዋጋ የለንም፡፡ ያሬድ አደመ የኹላችን ታላቅ ስለኾነ፣ በአገልግሎትም ስለሚቀድመን ሰብስቦ ኮርስ መስጠት ከጀመረ ሁለት ወር ኾኖታል፡፡››
 • በወቅቱ በዚህ ኹኔታ ውስጥ እንዳሉ ስማቸው ተለይቶ የተጠቀሰው ሀብታሙ ሽብሩ፣ ዘርፌ ከበደ፣ ዕዝራ ኃይለ ሚካኤል፣ ሐዋዝ ተገኝ እና ጋሻዬ መላኩ(ማሜ) ናቸው፡፡ ዘርፌ ከበደ ሰሞኑን ባወጣችው ቪሲዲ ቀረጻ ወቅት ‹‹ለማርያም አንድ መዝሙር ሲበዛባት ነው፤ ከእንግዲህ የኢየሱስን ክብር መግለጥ ነው የምፈልገው›› በማለት ቅራኔ መፍጠሯ ተሰምቷል፡፡ ሐዋዝ ተገኝ ለቀረጻ በተዘጋጀበት ስቱዲዮ ውስጥ ለቅ/ሚካኤል የተዘመረ ነው የተባለውን መዝሙር ‹‹ለኢየሱስ ቢኾን ጥሩ ነበር፤ ሚካኤልን እኔ እበልጠዋለኹ›› ብሎ በድፍረት በመናገሩ ዘውዱ ጌታቸው በተባለው የክራር ተጫዋች ከመፈንከት በገላጋይ ተርፏል፡፡
 • ከእኒህም ጥቂት የማይባሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እየተንቀሳቀሰ ምእመኑን ግራ በሚያጋባው ‹‹ታዖሎጎስ.›› በተሰኘው የኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘውትረው የሚታዩ ሲኾን ይህም ፕሮግራሙ ከፕሮቴስታንቶች ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚደረግለት ሲገለጽ የቆየውን የሚያረጋግጥ ኾኖ ተወስዷል – ‹‹ታዖሎጎስ ፕሮግራም በማኅበር የሚመራ ነው፤ ከ፳፻፬ ዓ.ም. ጀምሮ የአምስት ዓመት ሳምንታዊ ወጭው በፕሮቴስታንቶች ተከፍሏል›› ይላል የዕርቀ ሰላሙን ሂደት በመደገፍ ከሕገ ወጥ ቡድኑ መለየቱን የሚገልጽ አንድ ምስክር፡፡
 • አሁን ባለው ኹኔታ በቡድኑ ውስጥ ሦስት ዓይነት ስብስቦች እንዳሉ የሚናገረው ምስክሩ÷ ‹‹በጎጠኝነትና በጭፍን ቡድናዊነት ነገሩን ሳይመረምሩ የወጡና ይቅርታ ጠይቀን እንመለስ/አንመለስ በሚል የሚወዛገቡ፣ ተመሳስሎ በመግባት ወይም ለይቶ በመክፈል የመናፍቃንን ፍላጎት ለማስፈጸም በዓላማ የገቡ፣ አገልግሎቱን እንደ ቢዝነስ ቆጥረው የመጡና ሁለቱ ወገኖች የሚነጣጠቋቸው›› በሚል በሦስት ወገን ይከፍላቸዋል፡፡
 • ለምሳሌ፡- እንደ ናትናኤል ታምራት (ቴቬዝ) ያሉት ‹‹ድንጋይ ተሸክሜ እበላለኹ እንጂ በፍጹም ይቅርታ አልጠይቅም›› ዮች ናቸው፡፡ ጥፋተኞች መኾናቸውንና ይቅርታ ጠይቀን እንመለስ ማለታቸው የተዘገበው ያሬድ አደመ፣ በጋሻው ደሳለኝ፣ ተረፈ አበራ፣ በሪሁን ወንደወሰን እና አሸናፊ ገብረ ማርያም፡- ‹‹ችግር ስላለ ወጣን እንጂ ወደ ሌላ ቸርች የመሔድ ወይም ልዩ ቸርች የመመሥረት ዓላማ የለንም፤›› ባዮች እንደኾኑ ተገልጦአል፡፡ በባር ዱባይ በብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ባልተባረከና ለሀ/ስብከቱ በማይታዘዝ ሕንፃ የቆዩት እነቀሲስ ተስፉ እንዳለ ከነዚህ እንደሚደመሩ ተጠቁሟል፡፡ እነቀሲስ ተስፉ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነው››፤ ‹‹አሁን መነጠቅ እንችላለን›› በሚል በቅርቡ እነአሰግድ ሣህሉና ጋሻዬ መላኩ(ማሜ) ያስተማሩትን ግልጽ ኑፋቄ ተቃውመው ለሀ/ስብከቱ አስተዳደር ከማይታዘዘው ሕንፃ ጌቶች ጋራ ቅራኔ መፍጠራቸው ነው የተሰማው፡፡
 • በአንጻሩ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄያቸው የመሰንበትና ይህንኑ ኑፋቄአቸውን የማስፋፋት ዓላማ ያላቸው እነአሰግድ ሣህሉ በለመዱት ፈንድ እየተረዱ በቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በተወገዘውና በሚሽነሪ ቸርች ምሥረታ ሂደት ላይ ባለው በአሸናፊ መኰንን ቤት ራሳቸው እየተገኙና ሌሎችንም እያባበሉ በመውሰድ ‹በመጠነካከር› ላይ መኾናቸው ነው የተገለጸው፡፡ አሳሳቢና አፋጣኝ ርምጃ የሚሻው ግን በየአህጉረ ስብከቱ በመዞር ማዕከላዊ አሠራርንና የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴን ለማወክ ከሕገ ወጦችና እንደ አሰግድ ሣህሉ ካሉ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ተላላኪዎች ጋራ የሚተባበሩ ግለሰቦች አሁንም በመዋቅራችን ውስጥ መኖራቸው ነው፡፡

List of associations and individuals excommunicated by the Holy Synod

 • የምሥራቅ ሐረርጌ ሀ/ስብከት በቁጥር 1650/3/2005 በቀን 13/10/2005 ዓ.ም. ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የጻፈው ደብዳቤ እንደሚገልጸው፣ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የሒሳብና በጀት ክፍል ሓላፊ የነበረውና ሀ/ስብከቱ ባካሄደው የሦስት ወራት የሽግግር ወቅት ግምገማ ወደ ቅርስና ቱሪዝም ክፍል ሓላፊነት የተዛወረው ኢዮብ ይመር ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ እየተመላለሰ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱም ይኹን ሀ/ስብከቱ የማያውቀው ‹‹ጉባኤ መሰል የዐመፅ መቀስቀሻ›› ከሕገ ወጦች ጋራ አዘጋጅቷል፤ የሀ/ስብከቱን የስብከተ ወንጌል መዋቅራዊ እንቅስቃሴ ተፈታትኗል፡፡ ‹‹ስለ ጌታ ነው እንጂ ስለ መላእክት መናገር አይመጣልኝም›› በማለት የሚታወቀው ኢዮብ ይመር ከእነአሰግድ ሣህሉ ጋራ ቅርበት እንዳለው የሚነገር ሲኾን በዚህ አቋሙና አመለካከቱ የሀ/ስብከቱ ቅርስና ቱሪዝም ክፍል ሓላፊ ኾኖ መቀመጡ ዳግመኛ በጥንቃቄ ሊጤን የሚገባው ነው፡፡

East Harrghe Diosces on Eyob Yimer

Advertisements

2 thoughts on “የቅ/ሲኖዶስ የሲዳማና ጉጂ ቦረና አህጉረ ስብከት ልኡክ ነገ በሐዋሳ የዕርቀ ሰላም መግለጫ ያወጣል፤ ዕርቀ ሰላሙና መግለጫው የሐዋሳውን ውዝግብ ብቻ እንጂ በሊቃውንት ጉባኤው ፊት ቀርቦ እንዲጠየቅ የታዘዘውን በጋሻው ደሳለኝንና ሌሎች ሕገ ወጦችን አይመለከትም

 1. Anonymous December 7, 2013 at 7:35 pm Reply

  qalehywetyasemaln.

 2. Fetsum December 10, 2013 at 4:36 pm Reply

  Pls ere yebkachehu; geta lemeta nw; erefu

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: