በአ/አ ሀ/ስብከት የተቋማዊ ለውጥ አመራር ጥናታዊ ውይይት ካህናት፣ መምህራን፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮችና ምእመናን ሱታፌያቸውን እንዲያረጋግጡ ተጠየቀ

 • ለጥናታዊ ውይይቱ÷ ካህናት፣ የአብነት መምህራን፣ መዘምራን፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ የሰንበት ት/ቤት ተጠሪዎች እና ምእመናን የሚወከሉበት ቁጥር ተወስኗል፡፡
 • የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች÷ ተሳታፊዎቹ በአገልግሎት ድርሻቸው እና በተወሰነላቸው ቁጥር መሠረት መወከላቸውን የማረጋገጥ ሓላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡
 • ሀ/ስብከቱ የተሳትፎ ጥሪ ያስተላለፈበትን ደብዳቤ በማፈንና የተለያዩ ሰበቦችን በመደርደር ጥናታዊ ውይይቱን ለማኮላሸት አሻጥር የሚሠሩ የለውጡ አደናቃፊዎች (አንዳንድ አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች) በጥንቃቄ ተለይተዋል፤ በጸጥታ አካሉ የታገዘ ጥብቅ ክትትል እየተደረገባቸው ስለ መኾኑም ተጠቁሟል፡፡
 • ከእነርሱም መካከል፣ የባለሞያ ቡድኑን እንዲያግዙ ሳይገባቸው የተመደቡትና ስለ ጥናቱ ሐሰተኛና የተሳሳተ መረጃ (lies and misinformation) በመንዛት ገዳማትና አድባራትን ለተቃውሞ እየቀሰቀሱ በአፍራሽ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ተጠምደው የቆዩት የቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ጸሐፊ መ/ር ሰሎሞን በቀለ ይገኙበታል፡፡
 • የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች በግንባር ቀደምነት የማስተባበር ሚና የሚጫወቱበት የገዳማትና አድባራት የተቋማዊ ለውጥ አመራር ጥናታዊ ውይይት በውጤታማው የአራዳ ጉለሌ ክፍለ ከተማ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ተሳትፎ ነገ ይጀመራል፡፡
 • ለክህነታዊ አገልግሎት ልዩ ትኩረት የተሰጠባቸው የአብያተ ክርስቲያን አምስቱ ደረጃዎችና ተነጻጻሪ መዋቅራቸው፤ የሒሳብ አያያዝ፣ ኦዲትና የልማት ተቋማት ማቋቋሚያና ማስፋፊያ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ተሳታፊዎችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያወያዩ ይጠበቃል፡፡
 • ‹‹የለውጡ ተቃራኒዎች ጉዳይ አስፈጻሚ ኾነው አሉባልታ የሚነዙና አሻጥር የሚሠሩ አሉ፡፡ አሉባልታውና አሻጥሩ ለውጡን ወደ ኋላ አያስቀረውም፡፡ ችግር የሚፈታው በውይይት ነው፡፡ መመካከር፣ ሙስናን ማጥፋትና መልካም አስተዳደርን ማስፈን አለብን፡፡ ስለዚህ ጥናቱ ከየአብያተ ክርስቲያኑ የሚወከሉ 16፣ 16 ተሳታፊዎች በሚሰጡት ግብአት ከዳበረ በኋላ ትግበራው ይቀጥላል፡፡›› (ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ)
A.A Diosces Head Office

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት

በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተቋማዊ ለውጥ አመራር መዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር ጥናት ረቂቅ ላይ የተጀመረው የሥርጸትና ግብአት ማሰባሰቢያ መድረክ ከነገ፣ ኅዳር ፳፯ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. አንሥቶ በሦስት ተከታታይ ዙሮች በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ተወካዮች ደረጃ በሚካሄደው ጥናታዊ ውይይት ይቀጥላል፡፡ የተቋማዊ ለውጡ ዋና መሠረት እንደኾኑ የሚታመንባቸው የሀ/ስብከቱ ገዳማትና አድባራትም ተወካዮቻቸውን በአግባቡ በመላክ ለመዋቅራዊ የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ረቂቁ መዳበርና ተግባራዊነት የድርሻቸውን እንዲወጡ የሱታፌ (አንድነትና መተባበር) ጥሪ ተላልፎላቸዋል፡፡

ሀ/ስብከቱ በክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች አማካይነት ባስተላለፈው የሱታፌ ጥሪ፣ ከሀ/ስብከቱ 166/169 ገዳማትና አድባራት ተውጣጥተው በግንዛቤ ማስጨበጫና የግብአት ማሰባሰቢያ ጥናታዊ ውይይቱ ላይ ስለሚሳተፉ አገልጋዮች ውክልናና ብዛት ያስታወቀ ሲኾን የተሳታፊዎች አላላክም በዚኹ አኳኋን እንዲከናወን አሳስቧል፡፡

በሀ/ስብከቱ የጥሪ ደብዳቤ መሠረት ከእያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚወከሉት ተሳታፊዎች ጠቅላላ ብዛት 16፣ 16 ሲኾን የውክልናቸው ኹኔታም፡-

 • ከቀሳውስት – 1
 • ከዲያቆናት – 1
 • ከመዘምራን – 1
 • ከአብነት መምህራን – 2
 • ከስብከተ ወንጌል – 1
 • ከሰንበት ት/ቤት – 2 (ሰብሳቢና በሰበካ ጉባኤው የሰንበት ት/ቤቱ ተወካይ)
 • ከምእመናን – 4 (የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢን ጨምሮ)
 • አስተዳዳሪ፣ ጸሐፊ፣ ሒሳብ ሹም፣ ቁጥጥር – 4

እንደኾነ ተገልጦአል፡፡

አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ከላይ በተመለከተው አኳኋን ተወካዮቻቸውን በአግባቡ ለይተውና መርጠው ዝርዝራቸውን በሰበካ ጉባኤ ስብሰባ በቃለ ጉባኤ ይዘው ከወሰኑ በኋላ ይህንኑ ለጥናታዊ ውይይቱ ከወጣላቸው መርሐ ግብር ሦስት ቀናት በፊት ለየክፍላተ ከተማቸው ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች እንዲያሳውቁ መታዘዛቸው ተዘግቧል፡፡

ከነገ ኅዳር ፳፯ – ታኅሣሥ ፲፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በሦስት ተከታታይ ዙሮች በሚካሄደው ጥናታዊ ውይይት ገዳማቱና አድባራቱ በየክፍለ ከተማቸው በወጣላቸው መርሐ ግብር ቅደም ተከተል እንደሚሳተፉ ተዘግቧል፡፡ በሽግግር መዋቅሩ ሦስት ወራት በጽ/ቤት አደረጃጀት፣ በሰው ኃይል አስተዳደር፣ በፐርሰንት አሰባሰብና የልማት ሥራዎችን በማስተባበር የሥራ አፈጻጸም ውጤታማ እንደነበር የተገለጸው የአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ገዳማትና አድባራት ቅድሚያውን እንደሚወስዱም ታውቋል፡፡

 • የአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ አብያተ ክርስቲያን – ኅዳር ፳፯ – ፳፰ ዓ.ም.
 • የካ ክፍለ ከተማ አብያተ ክርስቲያን – ኅዳር ፳፱ – ፴ ዓ.ም.
 • ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አብያተ ክርስቲያን – ታኅሣሥ ፬ – ፭ ዓ.ም.
 • ኮልፌ ቀራንዮ እና አዲስ ከተማ ቂርቆስና ልደታ ክፍላተ ከተማ – ታኅሣሥ ፮ – ፯ ዓ.ም
 • አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ – ታኅሣሥ ፲፩ – ፲፪ ዓ.ም.
 • ቦሌ ክፍለ ከተማ አብያተ ክርስቲያን – ታኅሣሥ ፲፫ – ፲፬ ዓ.ም.

የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ የሚልኩላቸውን በቃለ ጉባኤ የተደገፈ ዝርዝር በጥንቃቄ በመመርመር የተሳታፊዎች ውክልና በአግባቡ መከናወኑን የማረጋገጥ ሓላፊነት እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡ ጥናታዊ ውይይቱ የሚካሄደው በሀ/ስብከቱ አዳራሽ ሲኾን ለዚህም የተቋቋመው ሦስት ንኡሳን ክፍሎች ያሉት ኮሚቴ ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ተነግሯል፡፡

Advertisements

One thought on “በአ/አ ሀ/ስብከት የተቋማዊ ለውጥ አመራር ጥናታዊ ውይይት ካህናት፣ መምህራን፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮችና ምእመናን ሱታፌያቸውን እንዲያረጋግጡ ተጠየቀ

 1. TEGEHAS December 6, 2013 at 10:30 am Reply

  በቤ/ክ ያልተማከለ አስተዳደር(decentralization) እንዲሰፍን መደረጉን እመኝ ነበር፡፡ የምመኘውም ካህናት መብትና ግዴታቸውን አውቀው ለምእመኑ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል በሚል ነበር፡፡ አሁን ሳስተውል ግን ቀረበ በተባለው ጥናት ጥያቄ እንዳነሳ የሚገፋፋ ጉዳይ ገጠመኝ፡፡ ልጠይቅ!!!!

  1. በጥናቱ ወቅት የካህናት ተሳትፎ፡
  ጥናቱ “ለክህነታዊ አገልግሎት ልዩ ትኩረት የሰጠ ነው” ተብሉዋል፡፡ግን በጥናቱ ሂደት የካህናት ተሳትፎ ምን እንደነበር አልተገለጸልንም.ስለሆነም እጠረጥራለሁ፡፡ የክህነት አገልግሎት እስከሚገባኝ የውስጥ ማለት: የቅዳሴ፣ የማህሌት፣ የሰዓታት፣ የኪዳን፣ የፍትሀት፣ የክርስትና፣ የስብከተ-ወንጌልና የመሳሰሉትን የሚመለከት ነው፡፡ ስለዚህ መጠናት ቢኖርበት እንኩዋ ቢቻል በዘርፉ ባለፉ ሊቃውን ካልተቻለም እነሱ ለአጥኚው አማካሪ ሆነው በተሰየሙበት መካሄድ ነበረበት እንጅ ለ’አቶ’ዎች በነጻነት መተው አልነበረበትም፡፡

  ጥናቱ ስንት ጊዜ እንደወሰዳና በምን ዘዴ እንደተሰራ እንኩዋ ሳይገለጽ ዘሎ 3 ሚሊዮን ይፈጃል መባሉም “ለራስ ሲቆርሱ…” የሚያሰኝ ነው፡፡

  አሁን የተያዘው ከተቀበላችሁ ጥናቱ በገዳማውያን ጸሎት ስለታገዘ ዝም ብላችሁ ተቀበሉ ካልሆነ ደግሞ የጸጥታ አካሉ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ ነው(ለተቃራኒ ሀይሎች ሲሆን የሚዘለፈው ጸጥታ ሀይል ለራስ ግሩፕ ሲሆን ይወደሳል!!)፡፡ አርምሙ!!!!

  2. የሽግግሩ ጊዜ እንከኖች፡
  በሽግግሩ ወቅትም ያልተቀረፉ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ልግለጻቸው!!

  (1) የክ/ከ/ቤ/ክህነት ሀላፊዎች በፍጥነት በጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ቁጥጥር ስር መሆንና የአንድ ግለሰብ(ስ/አስኪያጅ)ፈላጭ ቆራጭነት፣
  (2) በሙስና የሚፈጸሙ ቅጥሮችና ዝውውሮችን ሀይ-ባይ መጥፋቱ፣
  (3)የደሞዝ ጭማሪ ለማጸደቅ ለስ/አስኪያጅ ጉቦ መክፈል ያልተጻፈ ህግ ሆኖ መቀጠሉ፣ ለምሳሌ፡ በን/ስ/ላፍቶ ክ/ከ/ቤ/ክህነት እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡ ካህናት ሌት-በቁር ቀን-በሀሩር በሙታን መካከል እየተመላለሱ ተንገላተው ባመጡት ገንዘብ የደሞዝ ጭማሪ ለማግኘት ጉቦ ክፈሉ ሲባሉና እነሱም ያለዚህ እንደማይፈጸም አምነው በተስፋ መቁረጥ ስም ዝርዝራቸውን ጽፈው በይፋ የጉቦ መዋጮ ሲሰበስቡ እያየን ለውጡ ውጠየታማ ነበር ለማለት ይከብደናል፡፡ ገና ነው….ገና…!! በነገራችን ላይ ለዚህ ማስረጃ ከፈለጋችሁ አዲስ አምባ ኪ.ምህረት፣ ብ/ጽጌ ማርያም፣ ላፍቶ ሚካኤል ወዘተርፈ ካሉ ካህናት ውስጥ አንዱን ጠይቁት፡፡ “ይሄ እኮ የተለመደ ነው” ካላላችሁ ሀሳዊ በሉኝ!!
  (4)ተውማ!!! የስራ ስንብትና የእግድ ደብዳቤዎች ላይ የቀረበ አቤቱታን እልባት ለመስጠት ከ6 እስከ 1 አመት የሚፈጅበት መዋቅር ዘርግተንና አቤታ ባዩ የሚያቀርበው ማመልከቻ በቅጡ ተመዝግቦ የሚቀመጥበት መዝገብ ቤት ባለመቁዋቁዋሙ ማመልከቻዎች እንኩዋን ሊነበቡ ደብዛቸውም እንዲጠፋ ሲደረግ እያየን ለውጡ አመርቂ ነበር ለማለት ገና…ገና….ነው፡፡ ብዙ ይቀረናል!!! ተገሀስ!!!!!!!!!!

  3. ጥናቱ በገለልተኛ አካል አለመሰራቱ፡ ማህበረ-ቅዱሳን የልማቱን ያህል የቤ/ክ የችግር አካልም ሆኖ ሳለ ካባውን ቀይሮ መፍትሄ ሰጭ እንዲሆን መደረጉ አግባብ አይደለም፡፡ ምንድን ነው ችግሩ ቢሉ??

  እንዲህ እላለሁ – ፐርሰንት አይከፍልም፡
  የማይከፍለውም “የበጎ ፈቃድ አገልጋይ ስለሆንኩ እና ከቤ/ክ በጀት ስለማይመደብልኝ” በሚል ነው፡፡ ጥሩ!! ቃለ-ዓዋዲውን እንየው፡፡

  ቃለ-ዐዋዲያችን በአንቀጽ 56(2)(ሰ) ከቤ/ክ የገቢ ምንጮች አንዱ “ከሰ/ት/ቤት መንፈሳዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች” የሚገኝ ገቢ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ማህበሩ በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ስር ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ድንጋጌ ተፈጻሚ ይሆንበታል፡፡ ሰ/ት/ቤትም ቢሆን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንጅ የሙሉ ሰዓት ስራ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ከቤ/ክህነት የሚለቀቅልን በጀት የለም የሚለውም መከራከሪያ ውሃ የሚቁዋጥር አይደለም፡፡ ቤ/ክህነት ከመንፈሳዊ ት/ቤቶች ውጭ እንኩዋን ለማህበር ለአጥቢያ ቤ/ክርስቲያንም በጀት እንደማይበጅት ይታወቃል፡፡ ከሁሉም በላይ ለቤ/ክ የበላይ አስተዳደር በቤ/ክ ስም የሚሰበሰብ ገቢን አሳውቆ ፐርሰንት መክፈል አስተዳደሩ በመንፈሳዊ ጉዳዮች ያለውን ሉአላዊነት ማሳያ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን አለማድረግ የሚያሳየው አንድም የአስተዳደሩን የበላይነት አለመቀበል ነው እንዲያም ሲል በአስተዳደሩ በኩል ስልጣንን አሳልፎ መስጠት መኖሩን ነው፡፡ የሚያሳዝነው ይህ ህገ-ወጥነት ወደ ሰ/ት/ቤቶችም በፍጥነት ተዛምቶ ዛሬ የቤ/ክ ሞዴላሞዴሎችን የሚጠቀምና ገቢና ወጭውን በትክክል ለአጥቢያው ሰ/ጉባኤ ሪፖርት የሚያቀርብ ሰ/ት/ቤት ብርቅ ሆኖዋል፡፡ እናም እንዲህ አይነት ለቃለ-አዋዲው የማይገዛና ለቤ/ክ ሲሆን የበጎ ፈቃድ አገልጋይ ነኝ ለታክስ ሲሆን የቤ/ክ ነኝ እያለ ስለ ገቢና ወጭው በገሀድ ለመናገር የማይደፍር ማህበር የቤ/ክርስቲያንን አስተዳደርና የፋይናንስ ስርዐት አስተካክላለሁ ሲል “ኦ በዐለስራይ አድህን ርእሰከ” እንለዋለን!!!

  -የማህበሩ የተደበቀ ዘረኝነት፡
  በተራ አባላት ደረጃ ከሆነ ማህበሩ በብሄር ተዋጽኦ አይታማም፡፡ በአመራር ደረጃ ግን ‘ስልጣን ለሸዋ ብቻ’ የሚሉ ትምክህተኞች አሉበት፡፡የአቡነ ጳውሎስን ሞት ተከትሎ ማህበሩ አውራ ፓርቲ(dominant party) ሆኖ እየወጣ ነው፡፡ አቡነ ማትያስ ከእርግናቸው አንጻር ያን ያህል በመንበሩ ይቆያሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ስለዚህ ሲወርዱ የግድ ትክክለኛው ‘እጨጌ ዘደብረ-ሊባኖስ’ መተካት አለበት፡፡ ሸዋ በአሁን ሰዓት በቤ/ክ መዋቅር ዙሪያ ያለው ሀይል ደግሞ ይህን ለመፈጸም የሚያስችል አይደለም፡፡ ያለው አማራጭ አ/አ ባሉ ጉምቱ የሸዋ ልሂቃንና ከበርቴዎች እየታገዙ ከግል ሚዲያው ጋር በመናበብ ማህበሩን ሽፋን በማድረግ የታችኛውንና የፓትርያርክ ምርጫ ድምጽ ሰጭውን ክፍል በጥናታዊ መዋቅር ለውጥ ስም ተቆጣጥሮ የሲመቱን እለት መጠበቅ ነው፡፡ እስከዚያው ግን ራስን አጋልጦ ስልጣን ለሸዋ ማለት ሳይሆን የመፎካከር አቅም ያላቸውን (ትግራይ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ)ልዩ ልዩ ስም እየሰጡ ማጥላላት ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ተጥላልቶ ሲያልቅ አንድ ቅዱስ ከሸዋ መጋረጃ ይወጣል፡፡

  ይህ በማህበረ-ቅዱሳን በኩል በተሰራ ስሌት የተካሄደ የሸዋን መራሄ-ሃይማኖትነት ዘውድ የማስመለስ ከአለማዊ ህግም ሆነ ከህገ እ/ር ያልሆነ እንቅስቃሴ (ከሀግ በተጣጣመ መንገድ ከማንም ቢመረጥ ችግር የለብኝም) በ6ኛው ፓ/ክ ተሞክሮ የከሸፈ ሲሆን አሁን በጥናታዊ ለውጥ ስም የአንድን ብሄር አባላት ባማከለ መልኩ የሚደረገው እንቅስቃሴም ለ7ኛው ፓ/ክ ምርጫ ዝግጅት ስላለመሆኑ ዋስትና የለም፡፡ ይቺ አካሄድ የሸዋ መኩዋንንት ልጅ ኢያሱን ካስወገዱበት መንገድና ራሳቸውን መሀል-ሰፋሪ ብለው ቀ/ኃ/ስ’ን ወደ መንበሩ ካወጡዋቸው ሴረኞች ጋርም ትመሳሰላለች፡፡ ስለሆነም ይሄን ያህል በዘረኝነት የምጠረጥረው ማህበር ከቤ/ክ ዘረኝነትን ለማጥፋት ጥናት አቀረብኩ ሲለኝ እጠረጥራለሁ….እጠራጠራለሁ…ምንታዊ ይይዘኛል!!!!

  ግን….ግን….በዚህ ሁሉ መሀል የአሰራር እንጅ የሃይማኖት ልዩነት ስለሌለ ከላይ የጠቀስኩዋቸው እንከኖች ሁሉ ተቀርፈው የቤ/ክ የአስተዳደር መዋቅርም ሆነ የማህበሩ ጉድለቶች ተስተካክለው ቤ/ክ ዳግመኛ በጎደፈ ስም የማትጠራበትንና የራሳቸውን የአንድ ፓስተር መራሽ አዳራሽ ጉድ ሳይፈትሹ ቅ/ኦ/ተ/ቤ/ክ’ንን ለማስተሀቅር የስድብ አፍ የተሰጣቸውን ስሁት መናፍቃን የምናሳፍርበት ጊዜ እንዲመጣ እጸልያለሁ!!! ፀልዩ!!!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: