‹‹በምሥራቅ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የሌለው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን›› በሚል ተጀምሮ የቆመው የድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ግንባታ ሒሳብና የሥራው ሂደት በመንግሥት ባለሞያዎች እንዲመረመር ታዘዘ

Dire Dawa Saba Debre Hayel St. Gabriel Church

‹‹በምሥራቅ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የሌለው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መገንባት›› በሚል በጥቅምት ወር ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ቢጀመርም ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው በተዘፈቀበት ሙስና የተነሣ ሥራው ቆሞ የሚገኘው የድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን

 • የሥራ ተቋራጩ በ2 ዓመት ጊዜና በ3 ሚልዮን ብር ወጪ ግንባታውን አጠናቅቆ ማስረከብ ነበረበት፤ ይኹንና የሥራው መጠን ከ65 በመቶ በላይ ባልተራመደበትና ከውለታ ጊዜው ውጭ ለ6 ዓመት በዘገየበት ኹኔታ አላግባብ በቀረበ የተቋራጩ የይገባኛል ጥያቄ ከብር 8 ሚልዮን በላይ ወጪ መከፈሉ ተጠቁሟል፡፡
 • ቋሚ ሲኖዶስ መስከረም ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት÷ በ3 ሚልዮን ብር በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው ሕንፃ እስከ አሁን 8 ሚልዮን ብር ፈጀ መባሉ በርግጥም አጠራጣሪ ኾኖ ስለሚታይከጠቅላይ ቤተ ክህነት ታዛቢ ባለበት ከመንግሥት መ/ቤት ከሚገኙ ብቁ የሒሳብ ባለሞያዎች ወጪና ገቢው እንዲመረመርበሕንፃው ጥራት ላይም ባለሞያዎች ጭምር ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዳላቸው የተገለጸ ስለኾነ ገለልተኛ በኾኑ የመንግሥት ሥራና ከተማ ልማት ባለሞያዎች የግንባታው ሂደት እንዲመረመር አዝዟል፡፡
 • ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ ጋራ በጥቅም የተሳሰረው የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ እየጣሰ ለሰበካ ጉባኤው ባለመታዘዝ ከሚፈጽመው ምዝበራ ጋራ ተባብረዋል፤ በግንባታው ወጪና ገቢ፣ በሥራው ሂደትና ጥራት ላይ ጥያቄ የሚያነሡ የደብሩ አገልጋዮችን ደመወዝ በመቀነስ፣ ከደረጃቸው ዝቅ በማድረግና በማዘዋወር ሲበደሉ፣ ምእመናኑ በፖሊቲከኝነትና በአሸባሪነት እየተወነጀሉ ሲሸማቀቁና አቤቱታቸው እንዳይሰማ ሲደረግ ሽፋን በመስጠት ችግሩን አባብሰዋል የተባሉት የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ አባ አረጋዊ ነሞምሳ ከሓላፊነታቸው ተነሥተዋል፡፡
Aba Aregawi Nemomesa

ከድሬዳዋ ሀ/ስብከት የሥራ አስኪያጅነት ሓላፊነታቸው የተነሡት መጋቤ ሐዲስ አባ አረጋዊ ነሞምሳ

 • ለሁለት ዓመት ሀ/ስብከቱን በዋና ሥራ አስኪያጅነት የመሩት አባ አረጋዊ ነሞምሳ ወደ ሓላፊነት የመጡት፣ በታወቁት ሙሰኛ ‹ሊቀ ትጉሃን› ብርሃኔ መሐሪ ከሚመራው የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ተለይተው የወጡ ተቆርቋሪዎች ያቋቋሙት ‹‹የምእመናን ተሟጋች ቡድን›› በሕንፃ ሥራው ሽፋን የሚካሄደውን ምዝበራና የተራቀቁ ወንጀሎች በማጋለጥ የፈጠረውን ንቅናቄ በመደገፍ የግንባታው ወጪና ገቢ በሀ/ስብከቱ ኦዲት እንዲደረግ ትእዛዝ የሰጡት የቀድሞው ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበብ ናሁ ሠናይ በለጠ በቀድሞው ፓትርያርክ ትእዛዝ ከሓላፊነታቸው መነሣታቸውን ተከትሎ ነው፡፡ አባ አረጋዊ ለሙሰኞች ሽፋን ከመስጠት ባሻገር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ከሀ/ስብከቱ በማፈናቀል በኑፋቄ የሚጠረጠሩና ግልጽ የምግባር ችግር ያለባቸውን ግለሰቦች በመሰግሰግ በሀ/ስብከቱ አድባራት አስተዳደሮች ይተቻሉ፡፡
 • በዐሥር አባላት ተቋቁሞ የሀ/ስብከቱን የቀድሞ አስተዳደር ይኹንታ ያገኘው ‹‹የምእመናን ተሟጋች ቡድን›› ሥራ ከተጀመረበት ጥቅምት ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. አንሥቶ ገቢና ወጪውን ኦዲት አድርጎ በ፳፻፬ ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ባቀረበው ሪፖርት ከውጭና ከሀገር ውስጥ የተሰበሰበው አጠቃላይ ገንዘብ ብዛት ብር 11,388,096.23 በላይ መኾኑን አረጋግጧል፡፡ የሒሳብ ምርመራ ሪፖርቱ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአሳማኝም ኾነ አሳማኝ ባልኾነ መንገድ በደረሰኝ የወጣው ወጪ 5 ሚልዮን ብር እንደኾነ ገልጾ ይህ ስሌት ከጠቅላላ ገቢው አንጻር ከ5 ሚልዮን ብር በላይ የገባበት እንደማይታወቅ አመልክቷል፡፡
 • በቋሚ ኮንስትራክሽን መተዳደርያ ደንብ መሠረት የዋጋ ግሽበት ጥያቄ ከሚመለከታቸው ሲሚንቶ፣ ብረትና ነዳጅ ካሉት ዋና ግብአቶች ውጭ አጠቃላይ የነጠላ ዋጋ ይሻሻልኝ ጥያቄ ከውለታ ጊዜው ውጭ ለዓመታት ለዘገየ የግንባታ ፕሮጀክት በማቅረብ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለሥራ ተቋራጭ እንዲከፈል ተደርጓል፡፡ በዋናው ውል መሠረት የቅድሚያ ክፍያ የተከለከለ ቢኾንም የሥራ ተቋራጩ ምንም ዐይነት የቅድሚያ ክፍያ ዋስትና ሳያቀርብ በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ከፍተኛ ገንዘብ በብድር ተሰጥቶታል፡፡ በተለይም ከነሐሴ ፳፻፪ ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ እጃቸውን ባስገቡት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ/አገልግሎት ሓላፊ አቶ ሰሎሞን ካሳዬና ከውድድር ውጭ በተቀጠረ ባለሞያ ሽፋን ሰጭነት ከፍተኛ ገንዘብ በቃል ትእዛዝ ተከፍሏል፡፡
 • ለግንባታው ያለክፍያ ሞያዊ አስተዋፅኦ የማበርከት ዕድል የተነፈጋቸው መሐንዲሶች የተካተቱበት ተሟጋች የምእመናን ቡድን ካካሄደው ምርመራ በመቀጠል በግንባታው ገቢና ወጪ ሁለተኛውን ኦዲት የሠራው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የቁጥጥር አገልግሎት ነበር፡፡ የአገልግሎቱ ባለሞያዎች ኦዲት ደግሞ በውጤቱ ለሥራ ተቋራጩ ከ1.8 ሚልዮን ብር በላይ ከውል ውጭ እንደተከፈላቸው ከማጋለጡም በላይ በጎ አድራጊዎች ለግንባታው በዐይነት የሚሰጣቸውና ማታ ታይተው ለጥዋት የማይገኙት ድንጋይ፣ አሸዋና ሲሚንቶ በገንዘብ ተተምነው እንደማይሰሉ አስረድቷል፡፡ ይኸው ጉድለት ከደንብና መመሪያ አንጻር ተገናዝቦ ማስተካከያ እንዲደረግበት ያሳሰቡትና ‹‹እኛ ያየነውን ችግር አቅርበናል፤ መሸፈን አንችልም›› በሚለው አቋማቸው ተጽዕኖዎችን የተቋቋሙት በወቅቱ የቁጥጥር አገልግሎቱ ሓላፊ በኵረ ትጉሃን ዓለም አታላይ ከሓላፊነታቸው ከመነሣታቸው አልፎ ያለጊዜአቸውም በጡረታ እንዲገለሉ ተደርጓል፡፡
 • ለአሁኑ የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መነሻ የኾነው ሦስተኛ ዙር ማጣራት በቀድሞው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት የተመራና አምስት አባላት ባሉት ልኡክ በኅዳር ወር ፳፻፭ ዓ.ም. የተካሄደ ነው፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ገጾች የቀረቡበት የማጣራት ሪፖርቱ÷ ከውለታ ጊዜው ውጭ አላግባብ በተፈጸሙ ክፍያዎች የተጋነነ ወጪ የወጣበት ግንባታ ሒሳብና የግንባታው ጥራት በገለልተኛ ባለሞያዎች እንዲመረመር፣ ቃለ ዐዋዲውን ከማስከበር ይልቅ ለችግሩ መባባስ ተባብረዋል የተባሉትና በግንባታው ሽፋን ሕገ ወጥ መጠቃቀም እንደነበረ ለአጣሪው አካል ማመናቸው የተዘገበው ዋና ሥራ አስኪያጁ በሓላፊነታቸው መቀጠል እንደሌለባቸው፣ በቃለ ዐዋዲው ጥሰት ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው የተባሉት የደብሩ አስተዳዳሪ በከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ከደረጃቸው ዝቅ እንዲሉ የሚሉ የውሳኔ ሐሳቦች አቅርቧል፡፡
 • በሪፖርቱና የውሳኔ ሐሳቦቹ ላይ በስፋት መነጋገሩ የተገለጸው ቋሚ ሲኖዶስ÷ የግንባታው ወጪና ገቢ ከመንግሥት መ/ቤት ከሚገኙ ብቁ የሒሳብ ባለሞያዎች፣ በመስኩ ዐዋቂዎች ዘንድ ሳይቀር አጠራጣሪ የኾነው የሕንፃው ግንባታ ሂደትና ጥራት ደግሞ በሥራና ከተማ ልማት ባለሞያዎች እንዲመረምሩ፣ በሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና በደብሩ አስተዳዳሪ ላይ ስለቀረበው የውሳኔ ሐሳብ የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አጣርተው አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጡበት፣ የገለልተኛ ባለሞያዎች ምርመራ ተካሂዶ ውጤቱ እስኪታወቅ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው በሀ/ስብከቱ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግበት አሳስቧል፡፡
 • የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ለማስፈጸም በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም በተጠራው የደብሩ ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ፣ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴና የተሟጋች ምእመናን ተወካዮች ምክክር፣ ‹‹ሰላም ፍጠሩ›› ብለው መጠየቃቸው ታውቋል፡፡ ‹‹ውሳኔውን ማንም መሻርና ማስቀረት አይችልም፤›› ሲሉም ውሳኔው በተጨባጭ ርምጃ ሳይደገፍ እንደቀረው የቀደሙት ማጣራቶች እንደማይኾን ስጋታቸውን ላነሡት ተሟጋች ምእመናን አስታውቀዋል፡፡ የቤተ ክህነቱ ታዛቢዎችና የምእመናን ተወካዮች በታዛቢነት የሚገኙበትን የባለሞያዎች ኮሚቴ ለማቋቋምም በዚሁ ሳምንት እንቅስቃሴ እንደሚጀመርና አስፈላጊው ወጪ በደብሩ እንደሚሸፈን ተገልጧል፡፡

  Lique Tiguhan Birhane Mehari00

  እኒህ ሰው ‹ሊቀ ትጉሃን› ብርሃኔ መሐሪ ይባላሉ፡፡ ነበር ታጋይና አካላቸው ‹‹በጥይት ወንፊት እንደኾነ›› በመጥቀስ በሰዎች ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ባላቸው ዝንባሌ ይታወቃሉ፡፡ በፎቶው ላይ፡- ከምሥረታው ጀምሮ በሊቀ መንበርነት በሚመሩት የሳባ ደ/ኃ/ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ባላቸው ሓላፊነት የገንዘብ አስተዋፅኦ ማሰባሰብ ሥራ ላይ እንዳሉ ይታያሉ፡፡ ያለበቂ ምክንያት ከውል ጊዜ ውጭ ከ6 ዓመታት በላይ ለዘገየው የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታና ደብሩ ለተዳረገበት በሚልዮን የሚቆጠር ብር ወጪ ብዙዎች ተጠያቂ ያደርጓቸዋል፡፡

  ግለሰቡ÷ የግንባታ ኮሚቴው ሊቀ መንበር ከኾኑ በኋላ ከሥራ ተቋራጩ ጋራ የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር፣ በደብሩ አስተዳዳሪ፣ በሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና በጠቅ/ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ ሓላፊ ሽፋን ሰጪነት በሚፈጽሙት ሙስና ሽንሌ በተባለ የከተማዋ ክፍል ‹ኢንቨስትመንት› እንደጀመሩ የተሟጋች ምእመናን ቡድን የኦዲት ሪፖርት ያስረዳል፡፡ የሰበካ ጉባኤውን ሥልጣን በመጋፋትና የሰበካ ጉባኤውን ምርጫ በመቆጣጠር ራሳቸውን ለፓትርያርክ ተጠሪ እስከ ማድረግ፣ የኦዲት ሪፖርት እስከ ማስተካከልም ደርሰው ነበር፡፡

  አስተያየትና ጥያቄ የሚያቀርቡ ምእመናንንም ‹‹ገንዘብ አልጎደለም፤ ገንዘብ ጎደለ የሚል አሸባሪና ለቤተ ክርስቲያን የማያስብ ነው፤›› ብለው በዐደባባይ ሕዝቡን ለመዝለፍ የማያፍሩት ‹ሊቀ ትጉሃን› ብርሃኔ፣ በሌላቸው ዕውቀት በዐውደ ምሕረት ነገረ ሃይማኖታዊ ስብከት ለማሰማት የተዳፈሩ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹ሲኖዶሱ ግራና ቀኙን ሳያይ ግብታዊ ውሳኔ ነው የወሰነው?›› እያሉ ናቸው፡፡

 • በምክክሩ ላይ ‹‹ሲኖዶሱ ግራ ቀኙን ሳያይ በግብታዊነት ነው የወሰነው›› በማለት ትችት ለመሰንዘር የሞከሩት ‹ሊቀ ትጉሃን› ብርሃኔ መሐሪ በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበርነታቸው የፈጽሟቸው የምዝበራና ተቆርቋሪዎችን በመሠረተ ቢስ ውንጀላዎች የማሸማቀቅ ተግባራት በግልጽ ተነሥተዋል፤ ተገሥጸዋልም፡፡ የሕግ ተጠያቂነታቸውስ?
 • የመንበረ ፓትርያርኩ የቁጥጥር አገልግሎት በአጣሪነት፣ በአንድ ሰው የሁሉንም የምሕንድስና ዘርፎች ዲዛየንና ቁጥጥር አደርጋለኹ የሚለው የምሕንድስና አገልግሎቱ በተቆጣጣሪነት የተከታተሉትና የተሳተፉበት የድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የግንባታ ሒሳብ ምርመራና የግንባታ ሂደት ክትትል ሪፖርቶች ለቅ/ሲኖዶሱ የተሟላና ተአማኒ አለመኾናቸው መዋቅሮቹ ትክክለኛው አቅምና በቂ ቁጥር ባለው የሰው ኃይል እንዲጠናከ በተደጋጋሚ የሚቀርበውን ዕቅድ ከዓመታዊ ሪፖርቶች ፍጆታ ባለፈ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የሚጠቁም ነው፡፡

Holy Synod decision on D.D St Gabriel bld01Holy Synod decision on D.D St. Gabriel church02

Advertisements

9 thoughts on “‹‹በምሥራቅ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የሌለው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን›› በሚል ተጀምሮ የቆመው የድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ግንባታ ሒሳብና የሥራው ሂደት በመንግሥት ባለሞያዎች እንዲመረመር ታዘዘ

 1. Gishen November 25, 2013 at 6:54 am Reply

  ፍትህ ለቤተክርስቲያናችን!!! ፍትህ ለዕምነታችን!!!
  በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቅድስት ልደታ ማርያም ቤተክርስቲያንን ላለፉት 4 ዓመታት ከቤተክህነት ሹማምንት ጋር በመመሳጠር (በተለይም የቀድሞ የአዲስ አበባ ስራ አስኪያጅ ከነበሩት ‹‹…›› ኢልያስ ጋር የሙስና፣ የዝርያ፣ … ጥምረት በመፍጠር) ከ 20 ሚሊዮን ብር በላይ ሲዘርፉ፣ ሲያዘርፉ፣ በቤ/ክ ሀብትና ንብረት ሲጨፍሩ፣ ዕቁብ ሲጣጣሊ፣ ዶልፊን፥ ተዮታ፥ ቅጥቅት… እያሉ ሲሚዘብሩ በነበሩት የቤተክርስቲያኑ ሹማምነት፣ የሂሳብ ሹም፣ ቁጥጥር፣ …. ሌሎችም ላይ ሰበካ ጉባኤው ክፍተኛ መሰዋትነት በመክፍል በፍትህ ሚኒስቴር ማዘዣ በማውጣት ጉዳዩን አጣርቶ ወደ ፍርድ ቤት በማቅረብ በአሁን ሰዓት በአቃቤ ህግ በአራዳ ምድብ ችሎት ጉዳያቸው እየታየ ይገኛል፤ የፊታችን ህዳር 19 ቀነ ቀጠሮ ተይዟል፡፡
  በሌሎችም የቤ/ክ ሀብትና ንብረት በዘረፉ፣ ባዘረፉ፣ የቤተክህነት ሹማምነት ላይ፣ የቅዱስ ዑራኤል (አ/አ)፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ (አ/አ፥ አራዳ)፣ የቅዱስ ሚካኤል (አዲሱ ሚካኤል፣ አቶቢስ ተራ)፣ የድረደዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ፣ የብስራተ ገብርኤል ቤ/ክ (አ/አ፥ ሳር ቤት)፣ ግቢ ገብርኤል (አ/አ፥ አራት ኪሎ) …. (ተዘርዝሮ የማያልቅ) ሙሰኞችን፣ የተሃድሶ መናፍቃን የእናት ጡት ነካሾች … ላይ ልክ እንደ ልደታ ዓይነት የፍርድ ችሎት ያስፈልጋቸዋል!!! ለቤተክርስቲያናችን፣ ለዕምነታችን ፍትህ ያስፈልጋል !!! … ለዚህ ደግሞ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ የሚል ሁሉ ይመለከተዋል፡፡ በንግስ ቀን ነጠላ ለብሶ ከመምጣት ባለፈ ለቤ/ክ፣ ለዕምነታችን፣… ጠበቃ መቆም አለብን፣ የሂወት መሰዋትነት ቢጠይቅ እንኳን፡፡ የእግዚአብሔር ቤት በጠራራ ጸሐይ ሲዘረፍ እያዩ ዝም ማለት ከተባባሪነት የተለያ አይደለም እና ሁላችንም በየአጥቢያው የሚጠበቅብንን እንድናደርግ የወዴታ ግዴታ አለብን፡፡ የአባቱ ቤት ሲዘረፍ እያየ ዝም የሚል አለ? የእግዚአብሔር ቤትስ ሲዘረፍ ለምን ዝምታን መረጥን፣ ለምን አድር ባይ ሆንን?
  ፍትህ ለቤተክርስቲያናችን!!! ፍትህ ለዕምነታችን!!!

 2. Anonymous November 25, 2013 at 10:59 am Reply

  Hintsaw be2001or 2002 yitenakekel belan begugut sintebik minim liyunet sanay temerekn;ahunim bezaw dereja ley mahonu betam yesezinal
  Ahunim Igziabher mecherashawun yesemiraw.

 3. Anonymous November 26, 2013 at 1:16 am Reply

  የሚገርመው ነገር ቤተክርስቲያን የመናፈቃንንና የላካቸው የወያኔ መፈንጫ መሆኗ ነው ::
  መድኃኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ጠራርጎ ያባራቸው እኛም ባለን አቅም መታገል አለብን ::

 4. Anonymous November 26, 2013 at 5:49 am Reply

  u know such kind of rediculous activites should be stopped immediately.other wise with this kind of coruuption this church will no t survive after 20 years.i dont know who will be deacon after 20 years.

 5. Anonymous November 26, 2013 at 1:18 pm Reply

  “ከምሥረታው ጀምሮ በሊቀ መንበርነት በሚመሩት የሳባ ደ/ኃ/ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ” ከመጀመሪያው ጀምሮ ሊቀመንበር አልነበሩም፣ አቶ ብርሃኔ ሊቀመንበርነቱን በታክቲክ የወሰዱት አቶ ሳሙኤል ከሚባሉና የደብሩ ት/ቤት ዳሪክተር ከነበሩት የዋህ አባት ላይ መሆኑ ይታወቅና እኝህ ሰው ሲመሩት በነበረበት ወቅት ህንጻ ኮሚቴው ለምዝበራ አልተዳረገም ነበር፡፡

 6. yohan November 26, 2013 at 2:57 pm Reply

  ወይ ብርሃኔ ደግሞ ኢሀድግ ነኝ አለ? እኔ በደንብ አውቀዋለሁ የቅርብ ጓድኛው ነኝ ብዙ ነገሮቹን አውቃቸዋለሁ አሁን የምሰማቸው ባጠቃላይ እኔ ከማውቃቸው የተለዩ ናቸው:: ለምሳሌ 2ኛ ዲግሪ አለኝ ታጋይ ነበርኩ የሚሉ እንደውም ከውጭ ዜጋ ልጂ አለኝ የሚላቸው ፍጹም ሀሰት እውነት ከኔ ፊት ሲል ብሰማው መልካም ነው ግን ይህን ሁሉ እየተባለ ስሰማ ብዙ ጊዜ ልቀቅ ብየዋለሁ ግን ፈቃደኛ አይደልም እኔ አሁን የገባኝ ያለው አለመማሩ እንደጎዳው እና የሆነ ጥቅም እንዳለው ነው ለማንኛውም ልብ ይስጠው

 7. Anonymous November 28, 2013 at 9:10 pm Reply

  ወይ ይህች ቤተ ክርስቲያን የፈተናዋ መብዛት። በጣም የሚገርመው ነገር ስንት የተማሩ እና መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው እውነውተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እያሉ እንዴት እንደ እነ ሊቀ ትጉሃን ብርሃኔ መሐሪ እና እንደ እነ አባ አረጋዊ ያሉ ሙሰኞች በእንደዚ አይነት ሐላፊነት ላይ ይቀመጡ ነበር።እነዚ ሰው ሙሰኛ ብቻ ሳይሆኑ መናፍቅም ናቸው።
  እነዚህ አባ አረጋዊ የተባሉ ሰው የቤተ ክህነቱን እና የቤተ ክርስቲያኑን ሀብት ንብረት ሲዘርፉ ሲያዘርፉ ኖረው አሁን ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሁነው ወደ ኦስትርያ ሀገር መላካቸው ለምን ይሆን፡፤ ባልታወቁበት ሀገር ሄደው በውጭ ያለችዉን ቤተክርስቲያችን እንዲዘርፉአት መፍቀድ እኮ ነው።
  አንቺ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር ይሁንሽ

 8. Anonymous November 28, 2013 at 9:15 pm Reply

  ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ ጋራ በጥቅም የተሳሰረው የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ እየጣሰ ለሰበካ ጉባኤው ባለመታዘዝ ከሚፈጽመው ምዝበራ ጋራ ተባብረዋል፤ በግንባታው ወጪና ገቢ፣ በሥራው ሂደትና ጥራት ላይ ጥያቄ የሚያነሡ የደብሩ አገልጋዮችን ደመወዝ በመቀነስ፣ ከደረጃቸው ዝቅ በማድረግና በማዘዋወር ሲበደሉ፣ ምእመናኑ በፖሊቲከኝነትና በአሸባሪነት እየተወነጀሉ ሲሸማቀቁና አቤቱታቸው እንዳይሰማ ሲደረግ ሽፋን በመስጠት ችግሩን አባብሰዋል የተባሉት የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ አባ አረጋዊ ነሞምሳ ከሓላፊነታቸው ተነሥተዋል፡፡

 9. የሸዋሰው ነጋሽ November 28, 2013 at 9:17 pm Reply

  ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምሕንድስና ዘርፍ ጋራ በጥቅም የተሳሰረው የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ እየጣሰ ለሰበካ ጉባኤው ባለመታዘዝ ከሚፈጽመው ምዝበራ ጋራ ተባብረዋል፤ በግንባታው ወጪና ገቢ፣ በሥራው ሂደትና ጥራት ላይ ጥያቄ የሚያነሡ የደብሩ አገልጋዮችን ደመወዝ በመቀነስ፣ ከደረጃቸው ዝቅ በማድረግና በማዘዋወር ሲበደሉ፣ ምእመናኑ በፖሊቲከኝነትና በአሸባሪነት እየተወነጀሉ ሲሸማቀቁና አቤቱታቸው እንዳይሰማ ሲደረግ ሽፋን በመስጠት ችግሩን አባብሰዋል የተባሉት የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ አባ አረጋዊ ነሞምሳ ከሓላፊነታቸው ተነሥተዋል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: