ከዕለቱ ቃለ ምልልሶች – የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ቀጣይ አንድነት በአብነት ትምህርት ቤት: የፕሮፌሰር ተከሥተ ነጋሽ አስተያየት

tegestemedia

ፕሮፌሰር ተከሥተ ነጋሽ

እ.አ.አ በ፲፱፻፵፯ ዓ.ም. በአሥመራ ከተማ ተወልደው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሥመራ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጅማ ተከታትለዋል፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአሥመራ ዩኒቨርሲቲ በሕግ አግኝተዋል፡፡ ከ፲፱፻፸፪ – ፲፱፻፸፬ ዓ.ም በአሥመራ ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩት ፕሮፌሰር ተከሥተ በሎንዶን ዩኒቨርሲቲ ከ‹‹ስኩል ኦቭ ኦሪየንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ›› ሁለተኛ ዲግሪ ያገኙ ሲኾን የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከስዊድን ኡፕሳላ ዩኒቨርስቲ በታሪክ ትምህርት ሠርተዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ ዛሬ ታትሞ ከወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል÷ የኤርትራ ሕዝብ ዛሬ ያለበትን የነጻነት ኹኔታ ከቀድሞው ጋራ ማስተያየትንና “Ancient Eritreans” በሚል ርእስ የኤርትራ ቴሌቪዥን በቅርቡ ስላሳየው ዶኩመንታሪ የሚመለከት ነበር፡፡

የታሪክ ምሁሩ በተለይ ለሁለተኛው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ፣ በኢትዮ – ኤርትራ መካከል ያለው ወቅታዊ ችግርና የሕዝቡ ቀጣይ አንድነት (በፕሮፌሰሩ አነጋገር÷ በኤርትራ በኩል እየተጠየቀ ያለውን ድንበር በማሥመር ሳይኾን ከደርግ ሽንፈት በኋላ የተሠመረውን ድንበር በማፍረስ ፍጽምና እንደሚያገኝ) አመልክተዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ በምላሻቸው ውስጥ፣ የሁለቱ መንግሥታት ግንኙነት በቆመበት ኹኔታ ውስጥ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን (ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ኤርትራ) ወጣት ኦርቶዶክሳውያንን በድብቅ ወደ ጎንደር ለአብነት ትምህርት ይልኩ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ለምሳሌ ያህል÷ ጠብቃ ባቆየችው የአብነት ትምህርቷ እና ቤተ ጉባኤዋ በኩል በይበልጥም ለኦርቶዶክሳውያን ካህናትና ምእመናን ቀጣይ አንድነት ምክንያትና ለሁለቱ መንግሥታት ችግር የመፍትሔ አካል (cohesive institution) መኾን እንደምትችል አጠይቀዋል፡፡ ጥያቄውን በማስቀደምና ምላሹን በማስከተል በጡመራ መድረኩ አስተናግደነዋል፡፡

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ 18 ቁጥር 721 ቅዳሜ፣ ጥቅምት ቀን ፳፻፮ ..)

ኤልሳቤጥ ዕቊባይ

አዲስ አድማስ፡- የኤርትራ ሕዝብ አሁን ያለበትን የነጻነት ኹኔታ ከቀድሞው ጋራ ሲያስተያዩት ምን ትርጉም ይሰጥዎታል?

ፕ/ር ተከሥተ ነጋሽ፡- እኔኮ በመጀመሪያም ኤርትራውያን ከማን ነው የሚገነጠሉት የሚል አቋም ነው ያለኝ? ማነው ከማን የሚገነጠለው? የደቡብ ወይም የኦሮሞ ሕዝቦች እንገነጠላለን ቢሉ ኖሮ ምክንያት ነበራቸው፡፡ የኤርትራ የነጻነት ጥያቄ በተነሣበት ወቅት ኤርትራውያኑና ከላይ የጠቀስኋቸው ሕዝቦች በኢትዮጵያ ውስጥ ያገኙትን ዕድል (comparative advantage) ስናይ፣ ኤርትራውያኑ በጣም ተጠቃሚ ነበሩ፡፡ በጣሊያን፣ በእንግሊዝ እና በፌዴሬሽኑ ዘመን፤ በ፲፱፻፷ዎቹ የዐዲስ አበባ ሀብታሞቹ እነርሱ ነበሩ፡፡ በትምህርት መስክ 25 በመቶ የዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች ኤርትራውያን ነበሩ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችንም ካየሽ 25 በመቶ የሚኾኑት ኤርትራውያን ነበሩ፡፡ ይህን ዕድል ያገኙ ሰዎች ከኢትዮጵያ እንገነጠላለን ሲሉ ምክንያቱን ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ምንም ምክንያት አልነበራቸውም፡፡

ለናፅነት የተደረገው እንቅሰቃሴ ሠላሳ ዓመት ቢፈጅም ስድሳ ሺሕ ሕዝብ ቢሞትም በቂ ምክንያት አልነበረውም፡፡ የኔ ጥናት ‹‹የጣልያን ቅኝ አገዛዝ በኤርትራ›› የሚል ነው፡፡ እንዲገባኝ ሞክሬአለኹ፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል እንዳለባት የሚያሳይ ምንም ነጥብ አላገኙኹም፡፡ ነጻ ወጣን አሉ፡፡ ሁለት ዓመት ሳይቆዩ፣ ‹‹እኛ የታገልነው ለናፅነት ብቻ አይደለም፤ የኛ ዕድል ከኢትዮጵያ ጋራ ነው›› ማለት ጀመሩ፡፡ ይህን የሚሉት ተገደው ነው፤ ምክንያቱም የኤርትራ ኢኮኖሚ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ በራሱ ሊቆም የሚችል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ልዩ አገር ነች፤ ነጻነቷን ጠብቃ የቆየች አገር ነች፡፡

አዲስ አድማስ፡- የኤርትራ ቴሌቪዥን በቅርቡ “Ancient Eritreans” (የጥንት ኤርትራውያን) የሚል ዶክመንታሪ አቅርቦ ነበር፡፡ አይተውታል?

ፕ/ር ተከሥተ ነጋሽ፡- (ረጅም ሣቅ) አላየኹትም፡፡ ግን ምንም ዐዲስ ነገር አይፈጥርም፡፡ ወጣቶቹ ኢትዮጵያን አያውቋትም፤ ነገር ግን መንግሥት የሚያደርገው አንድ ነገር ነው፤ ሕዝቡ የሚያስበው ሌላ ነገር ነው፡፡ መንግሥት በቴሌቪዥን የሚያሳየውና ሕዝቡ የሚያስበውና የሚመኘው ሌላ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ብትለያይም ወጣቶቻቸውን በድብቅ ለትምህርት ወደ ቤጌምድር(ጎንደር) ይልኩ ነበር፡፡

የ[ፕሬዝዳንት]ኢሳይያስን መረጃ በማየት ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ ኤርትራዊውን ማን አገኘው? የተለየን ነን የሚል አቋም የት ነው ያለው? በኤርትራ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ምን ያህል አለ ለሚለው መልስ ለማግኘት ድንበሩ መፍረስ አለበት፡፡ ለሁለቱ ሕዝቦች መፍትሔ የሚኾነው በኤርትራ በኩል እየተጠየቀ ያለው ድንበር ሲሠመር ሳይኾን ከደርግ ሽንፈት በኋላ የተሠመረው መሥመር ሲፈርስ ነው፡፡

*                          *                           *

መጨመ፡-

ዘማርያን ነን ባዮቹ ዕዝራ ኃይለ ሚካኤል፣ ሐዋዝ ተገኝ እና ሀብታሙ ሽብሩ በሕገ ወጥ ሰባክያን ዙርያ ተሰባስበው ሲያበቁ እንደዋዛ ጀምረውታል በሚባለው ‹‹እኔ የየሱስ ነኝ›› ፕሮቴስታንታዊ ዘይቤ ወደ ፕሮቴስታንታዊነት እየነጎዱ መኾናቸው እየተነገረ ነው፡፡ ሐዋዝ ተገኝ የተባለው ግለሰብ ለቀረፃ በተዘጋጀበት ስቱዲዮ ውስጥ፣ ለቅዱስ ሚካኤል የተዘመረውን መዝሙር ‹‹ለኢየሱስ ቢኾን ጥሩ ነበር፤ ሚካኤልን እኔ እበልጠዋለኹ›› ማለቱ ለምሳሌ ያህል ይጠቀሳል፡፡

ከዚህ ቡድን ጋራ ስትንቀሳቀስ የቆየችው ወይዘሮ ዘርፌ ከበደ አዲስ አድማስ በዛሬው ዕትሙ በቃለ ምልልስ ካስተናገዳቸው እንግዶች መካከል ሌላዋ ናት፡፡ በአሁኑ ወቅት መኖርያዋን በአሜሪካ – ኒውዮርክ ያደረገችው ወ/ሮ ዘርፌ በጆን ኤፍ ኬኔዲ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ጋራ ባደረገችው ቃለ ምልልስ÷ ‹‹በአሜሪካ አማርኛ መስማት ለማይችሉና ቤተ ክርስቲያን እየመጡ ለማምለክ ለሚቸገሩ የሐበሻ ልጆች›› መፍትሔ ለመስጠትዕቅድ እንዳላት ተናግራለች፡፡

በእንግሊዝኛ የተዘመረ መዝሙር አለመኖሩን የጠቀሰችው ወ/ሮ ዘርፌ፣ አማርኛ መስማት የማይችሉት የሐበሻ ልጆች ‹‹በኢትዮጵያ ያለውን ነው እየዘመሩ ያሉት›› በሚል የመዝሙር እጥረት እንዳለ አስረድታለች፡፡ በመኾኑም ‹‹ለእነርሱ በእንግሊዝኛ መዝሙር የመሥራት ሐሳብ አለኝ›› በማለት ‹በእንግሊዝኛ በመዘመር መፍትሔ ለመስጠት› ያላትን ፍላጎት አስታውቃለች፡፡

በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ‹‹አዲሱን መዝሙሯን›› በተቀረጸችበት ወቅት÷ ‹‹ስለ እመቤታችን መዝሙር መዘመር አልችልም፤ አንድ መዝሙርም ሲበዛባት ነው፡፡ እኔ የኢየሱስን ክብር መግለጥ ነው የምፈልገው›› ማለቷ የተዘገበው ወ/ሮ ዘርፌ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአገራቸውንና የቤተ ክርስቲያናቸውን ሁለንተና ባገራቸው ግዕዝ (አኳዃን፤ ዐመልና ልማድ) መማር ለሚገባቸው የሐበሻ ልጆች እንደምን ያለ ‹‹የእንግሊዝኛ መዝሙር›› ታሰማን ይኾን!?

‹‹በእግዚአብሔር ቃል ስለማደጓ›› ስለራሷ ምስክርነት የምትሰጠውና ቀድሞ ታዋቂ ዘፋኝ የመኾን ሕልም እንደነበራት የምትናገረው ወ/ሮ ዘርፌ፣ ‹መዝሙሯን› የሚሰሙ የውጭ ሰዎች ‹ዜማዋንና የድምፅዋን ቅላፄ› ሲሰሙ የሚያደንቁት ‹‹ሙዚቃ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ስለኾነ›› እንደሚመስላትም ገልጻለች፡፡ በቤትዋ ውስጥ ባህላዊም ዘመናዊም የሙዚቃ መሣርያዎች እንዳሏት የተናገረችው ወ/ሮ ዘርፌ፣ ወደፊት የሙዚቃ ት/ቤት ገብታ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያላትን ተሰጥኦና ችሎታ ‹‹ለማሳደግ›› እየተዘጋጀች መኾኑንም አልሸሸገችም፡፡ እስኪ ለማንኛውም ከተነሡት ነጥቦች ጋራ በተያያዘ ከቃለ ምልልሱ የተወሰደውን የተወሰነ ክፍል በጥሞና በመከታተል ወ/ሮ ዘርፌ ‹‹ነጻነት አለው›› ባለችው አሜሪካ ያሳየችውን ‹‹የአመለካከትና የሥራ ዕድገት›› እንከታተል፡-

አዲስ አድማስ፡- የአሜሪካን ኑሮ ለመድሽው?

ወ/ሮ ዘርፌ፡- በጣም ቆንጆ ነው፡፡ እዚህ አገር መኖር ነጻነት አለው፡፡ መጀመርያ ወደ አሜሪካ የመጣኹት ለአገልግሎት ነበር፡፡ ዳላስ ያለው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ጥሪ አድርጎልኝ ማለት ነው፡፡ በአሜሪካ ስቴቶች እየተዟዟርኹ ሳገለግል በአጋጣሚ የትዳር አጋሬን አገኘኹና እዚሁ ቀረኹ፡፡

አዲስ አድማስ፡- በአንድ ወቅት በጋብቻ ላይ ጋብቻ እንደደረብሽ ሲወራ ነበር?

Woizero Zerfe Kebede

ወ/ሮ ዘርፌ ከባለቤቷ ቀሲስ ዘገብርኤል ጋራ

ወ/ሮ ዘርፌ፡- ይህ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ያን ጊዜ እዚህ አገልግሎት ላይ ነበርኹ፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ጓደኛ ነበረኝ፡፡ ያለመስማማት ተፈጥሮ ተለያየን፤ ግን ማግባቴ በመገናኛ ብዙኃን ይናፈስ ነበር፡፡ እኔ አላገባኹም፤ መግባባት ስላልቻልንና ከአገልግሎቴ ጋራ በተገናኘ ብዙ ችግር ስለገጠመኝ ግንኙነታችንን ገትቸዋለኹ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ነገሩን ሳያውቁና ሳይረዱ ‹‹አገባችና ፈታች›› እያሉ ወሬ ተናፍሶ ነበር፡፡ እውነት ስላልኾነ ግን ምንም አልመሰለኝ፡፡

አዲስ አድማስ፡- ወደ መንፈሳዊ መዝሙሮች ከመግባትሽ በፊት ዓለማዊ መዝሙሮችን ታቀንቅኝ ነበር፤

ወ/ሮ ዘርፌ፡ያኔ እንደውም ፍቅርአዲስ ነቅዐ ጥበብን ትመስያለሽ ይሉኝ ነበር፡፡ ዘፈኖቼን ለማሳተም ሁሉ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ስጀምረው ታዋቂ ዘፋኝ ኾኜ ትልቅ ሰው የመኾን ሕልም ነበረኝ፤ ማንኛውም ሰው እንደሚያስበው ማለት ነው፡፡ በኋላ ነው ነገሮች የተቀየሩት፡፡ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች፣ እንግሊዝኛ፣ ዐረብኛና ሱዳንኛ ዘፈኖችንም እዘፍን ነበር፡፡

አዲስ አድማስ፡- መንፈሳዊ አገልግሎት ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ዘርፌ፡- በጣም ጥሩ ነው፡፡ ‹‹እኛን አገልግይ›› የሚሉ በርካታ ጥሪዎች ከተለያዩ ቦታዎች ይመጣሉ፡፡ አሜሪካ እንደመጣኹ ያወቁ በሙሉ በየስቴቱ ስለሚጠሩኝ እየሔድኹ አገልግላለኹ፡፡ ከአሜሪካ ውጭ ደቡብ አፍሪካና አውስትራልያ ሔጃለኹ፡፡ በቅርቡ ደግሞ አውሮፓ እሔዳለኹ፡፡ ወደፊትም ብዙ ጥሪዎች ስላሉ በፕሮግራም እየሔድኹ አገልግላለኹ፡፡ ቅዳሜና እሑድ ሳይቀር ከአገር አገር እዞራለኹ፡፡

አዲስ አድማስ፡- ግጥምና ዜማ ትደርሻለሽ?

ወ/ሮ ዘርፌ፡- አዎ፤ የመዝሙርና ዜማ ግጥም እሠራለኹ፡፡ ‹‹መንፈስ ቅዱስ›› የሚለው አዲሱ መዝሙር ካሴቴ ላይ ዐሥራ አንድ ዜማዎች አሉ፡፡ ሦስቱን ግጥምና ዜማ ራሴ ነኝ የሠራኹት፡፡ ምንም አልል. . .እኅቴ፡

አዲስ አድማስ፡- ከቀድሞ ሥራሽ አንጻር በአዲሱ ካሴትሽ አድጌአለኹ፤ ተሻሽዬአለኹ ብለሽ ታስቢያለሽ?

ወ/ሮ ዘርፌ፡- አዎ!! አድጌአለኹ፡፡ ዕድገቴን ራሴ ነኝ የማየው፡፡ ምናልባት ብዙ ሰው ዕድገቴ አይታየው ይኾናል፡፡ ትላንትናና ዛሬ ግን ብዙ ልዩነት እንዳለኝ ዐውቃለኹ፡፡ በእግዚአብሔር ቃል አድጌአለኹ፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ካደግኹ ደግሞ የተሻለ ሥራ እሠራለኹ፡፡ የአሁኑ ሥራዬ የተሻለ ነው፡፡

አዲስ አድማስ፡- አዲሱ ሥራሽ በአማርኛ ብቻ ነው ወይስ. . .

ወ/ሮ ዘርፌ፡- ሌላ ቋንቋ አልተጠቀምኹም፡፡ ወደፊት ግን ብዙ ዕቅድ አለኝ፡፡ ጌታ ቢፈቅድ ብዙ ልሠራቸው ያቀድኋቸው ነገሮች አሉ፡፡ በእኛ አገር በተለያዩ ቋንቋዎች መዝሙሮች መሠራት አለባቸው፡፡ እዚህ አሜሪካ ብዙ የሐበሻ ልጆች አማርኛ መስማት አይችሉም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይመጣሉ፤ ግን ለማምለክ ብዙ ይቸገራሉ፡፡ በእንግሊዝኛ የተዘመረ መዝሙር የለም፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን ነው እየዘመሩ ያሉት፡፡ ለእነርሱ በእንግሊዝኛ መዝሙር የመሥራት ሐሳብ አለኝ፡፡ ከዚህ በተረፈ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብቼ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያለኝን ተሰጥኦና ችሎታ ለማሳደግ እየተዘጋጀኹ ነው፡፡ በቤቴ ውስጥ የሙዚቃ መሣርያዎች አሉኝ፤ ባህላዊም ዘመናዊም፡፡ እነርሱንም እያጠናኹ ነው፡፡

አዲስ አድማስ፡- መዝሙሮችሽን የሚያደንቁ የውጭ ሰዎች አልገጠሙሽም?

ወ/ሮ ዘርፌ፡- ኢትዮጵያውያኖች ነጮችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ይዘዋቸው ይመጣሉ፡፡ አማርኛ አይሰሙም፤ ነገር ግን ዜማውንና የድምፄን ቅላፄ ሲሰሙ ይደነቃሉ፡፡ ለራሴም መጥተው ይነግሩኛል. . .፤ ‹‹የሚያምር ድምፅ ነው ያለሽ›› ይሉኛል፡፡ አይሰሙትም፣ ግን እንዴት ነው የሚያደንቁት እላለኹ፡፡ ሙዚቃ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ስለኾነ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ በማይገባን ቋንቋ ሙዚቃውን ብቻ ሰምተን ‹‹ቅላፄው ደስ ሲል. . . ሙዚቃው ደስ ሲል›› የምንልበት ኹኔታ አለ አይደል፡፡ ወደነው የምንቃትትበት ጊዜ አለ፡፡ ምን ማለት እንደፈለጉ ይገባናል እኮ፡፡

Advertisements

17 thoughts on “ከዕለቱ ቃለ ምልልሶች – የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ቀጣይ አንድነት በአብነት ትምህርት ቤት: የፕሮፌሰር ተከሥተ ነጋሽ አስተያየት

 1. ሚሚ November 10, 2013 at 5:38 am Reply

  ብራቮ ዘርፌ……….መዝሙር ፣ ክብርና ምስጋና ሁሉ ለአምላካችን ብቻ ነው መሆን ያለበት፡፡

 2. Anonymous November 10, 2013 at 12:35 pm Reply

  ‹‹ስለ እመቤታችን መዝሙር መዘመር አልችልም፤ አንድ መዝሙርም ሲበዛባት ነው፡፡ እኔ የኢየሱስን ክብር መግለጥ ነው የምፈልገው›› ማለቷ የተዘገበው ወ/ሮ ዘርፌ፣ min lemalet endefelegech Aligebagnem???? dear Zerfe aqitachashin meqeyer kefelegish ***ye-BEG LEMIDISHIN AWLIQI***** ORTODOX TEWAHIDO ene liqe-mezmiran YILMAN yemsaselu zemariyan aluwat!!!!

  • Anonymous April 27, 2015 at 8:21 am Reply

   መቼ ነው እንዲህ ብላ የተናገረችው

 3. Anonymous November 11, 2013 at 6:19 am Reply

  እግዝኣብሔር ይቅር ይበልሽ

 4. Anonymous November 11, 2013 at 7:41 am Reply

  እናትን ከልጅ ነጥሎ ማየት ይቻላል እንዴት;

 5. Bante November 11, 2013 at 7:50 am Reply

  የመዘመር አቅሟን ማሳደግ ከፍለገች አብነት ትመህርት ቤት ገብታ ውዳሴ ማርያም ዜማ አትማርም መዝሙር ለመዘመር አለማዊ ሙዚቃ ቤት አይ…….አለማዊ የሙዚቃ መሳሪያ ለመንፈሳዊ ዘማሪ ምን የሆን ጠቀሜታው..እረ ተይ የደንበር ምልክት አታፍርሽ ፡፡
  ለካ እኔነኝ የተሳሳትኩት ለዘፈን ከሆነ ትክከል ነሽ

 6. KAHN November 11, 2013 at 11:31 am Reply

  እነዚህ ልጆች ከዘማሪት ዘርፌ ውጭ(እሱዋ ከአለማዊነት የመጣች ናትና አልፈርድባትም) ሁሉም ትናንት ተራ ሰ/ተማሪ ነበሩ. በኛው ጉያ ስር አድገዋል. የልጅነት ድምጻቸው መስጦን በዝማሬያቸው ቆመን ታድመናል. አጨብጭበናል. “ሙዳየ-መና ግሩም” ሲሉ አጅበናቸዋል. በዝማሬያቸው የራቁትን አቅርበዋል.
  1. ሆኖም አሁን አሁን የዝማሬያቸው ቃና ከኛ ይልቅ ለሌሎች የሚቀርብ ሆኖ ይሰማኛል. ችግሩ አብዝተው ስለ ጌታ መዘመራቸው አይደለም፣በገእዝ አለመዘመራቸውም አይደለም(ሰብህዎ በክሂሎቱ ብሉዋልና)ጌታን የሚያነሱበት መንገድ እንጅ. የኔ…ውዴ…ወዳጄ…..ጌትየ….ሰባሪው….ከፍ በል….ከፍታ….ጠላቴ….መሞላት….ወዘተርፈ የሚሉ ጌታን ከንጉስነት ወደ ጥሬ ጉዋደኛነት(ሎቱ ስብሀት) የሚያወርዱ የሚመስሉ ቃላት ምንም እንኩዋ ቃላቱ ኢ-መንፈሳዊ ናቸው ባይባሉም ከኛ ይልቅ በሌሎቹ እነስም-አይጠሬ ቸርቾች ስለተለመዱ ለነፍሳችን አይቀርቡም፣
  2. ምናልባት በኢኦተቤክ ስለ ክርስቶስ አይሰበክም የሚለው አደንቁዋሪ አሉባልታ ወስዱዋቸው ከሆነ ስለ ክርስቶስ ዘወትር በነግህ (ጠዋት) የሚደረሰውን ጸሎተ-ኪዳን ከነእግዚኦታው መታደም ፣
  3. እነ እንትናን ለማናደድ ብለው ከሆነም እልህ በሃይማኖት ስለማይሰራ ሰውን ከእ/ር በመለየት ስመ-ክርስትና ሰጥታ ገና በእቅፍ ሳሉ በስላሴ ስም የተቀበለቻቸውን ርእትእት ቤ/ክ ቅ/ያሬድን አርአያ አድርገው እንዳልሰሙ አልፈው በተአግሶ ማገልገል፣
  4. ሊቀ-መዘምራን ዳዊት እኮ ስንት ጊዜ ስለ ኢየሩሳሌም፣ስለ ጽዮን ዘምሩዋል. “ተዘከር ኪዳነ አግብርቲከ ቅዱሳን” ይል ነበር. እነዚህ ዝማሬዎች የጌታን ክብር ይከልላሉ አልተባሉም. ከዛ ይልቅ በጌታ የታመኑ ቅዱሳንን መዘከር እኛም እንደነሱ ተስፋ-መንግስተ ሰማያት እንዳለን ያዘክረናል. ስለዚህ ስመ-ቅዱሳንን ጠርቶ መዘመርን ችላ አትበሉ. ያለበለዚያ መንጋው የእረኛውን ድምጽ እየለየ መስማቱን ይቀጥላል፣
  5. እኛ ካህናቱም እነዚህን ልጆች ከመንገድ ሲወጡ መክሮ ገስጾ መመለስ. ወጣቶችም ብትሆኑ ልጆቹን እንደ መንፈሳዊ ወንድም ቀርቦ መምከር እንጂ ‘ጠርገን እናስወጣለን’ እያሉ ከሲኖዶስ ቀድሞ እያወገዙ ስም ለማውጣት አለመቸኮል. ወንድም ሲሳሳት ለመመለስ የተቻለን ያህል መጣር እንጅ መገፋፋት ዋጋ አያስገኝም. እና የመሳደድ ስመመየት እንዲሰማቸው አናድርግ. ሌሎች እኛን ለማናደድ ቢሰሙዋቸውም አይግረመን፣
  6. ለመሆኑ የየትኛው ዘማሪ መዝሙር ነው በድጉዋ ምልክት የተጮኸ መዝሙር. በፊት እነ መ/ታ ጸሀይ፣እነ ሊ/መ/ኪነጥበብ፣እነቀሲስ አበበ፣እነ ዲ/መገርሳ፣እነ መ/ር እስመለዓለም….. ለያሬዳዊ ዜማ የቀረቡ መዝሙሮችን ያቀርቡልን ነበር አሁን ሁሉም ድምጹን በሰ/ት/ቤት መዝሙር ክፍል ይፈትሽና ድንገት ተነስቶ “ዘምር-ዘምር አለኝ” ይላል…ባለቤት የሌለው ቤት!!
  7. በማህበረ-ቅዱሳን የሚታተሙ የህብረት መዝሙራት ከላይ ከተጠቀሱት እንከኖች የጸዱ ቢሆኑም ያን ያህል ማስተዋወቂያ ስለማይደረግላቸውና አቀራረጻቸውም ከድሮው የትምህርት በሬዲዮ መዝሙሮች የተሻሉ ባለመሆናቸው ለአድማጩ ምእመን ሰፊ አማራጭ ሆነው መቅረብ አልቻሉም.
  ስለዚህ መፍትሄው ቢያችል በቃለ-ዓዋዲው ላይ ካልሆነም በሊቃውንት ጉባኤ በሚወጣ መመሪያ አንድ መዘሙር የኢኦተቤክ መዝሙር ለመባል ማሙዋለት ያለበት ቅድመ-ሁኔታ ቢዘረዘር፣ቤ/ክ ልክ እንደ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ሁሉ የራሱዋ ሰቱዲዮ ቢኖራት፣በቤ/ክ መድረክ ለመዘመር ከሀ/ስብከቶች ፈቃድ ግድ ቢሆን….. ከዛ በሁዋላ ሳንሳቀቅ የምንሰማቸው መዝሙሮች ቢቀርቡልን!!
  “ወነዓምን በአሀቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት!!”

  • ታታ November 12, 2013 at 9:46 am Reply

   KAHN እናመሰግናለን
   የማህበረ ቅዱሳን የህብረት ዝማሬ ጣፋጭ ምግብ ናቸው፤ አይጠገቡም፡፡
   የማህበረ ቅዱሳን መናፍቃንን ማሳደድ ግን ተቀባይነት የለውም፤ ምክንያቱም እንክርዳዱን እንነቅላለን ብለው ስንዴውንም አብረው እየነቀሉት ስለሆነ ነው፡፡
   ማ/ቅዱሳን ከመናፍቃን ጋር ለምታደርጉት ውጊያ ስልታችሁን ብትቀይሩት ጥሩ ነው፡፡

 7. Anonymous November 11, 2013 at 12:03 pm Reply

  ayeee mimi emneet smeet aydeleem, qaal sgaaa koneee, betaam kebaad neew beman bekuuuul????

 8. Anonymous November 11, 2013 at 12:34 pm Reply

  tiru new egziabher yabertash zeriyeeee!

 9. Anonymous November 12, 2013 at 11:04 am Reply

  ere yemigerm zemen lay deresin !!! ewnet yebetekrstian lahy alat?

 10. Anonymous November 12, 2013 at 6:48 pm Reply

  Min aynet zemen new yederesn leyaried geez yegelexelet amlak english languege ayakm malet newn?neger gn geta yegesexew rkus menfes behawaryat egr asketlo gena be zar beshta betenedefu sewoch yezefen muzika be yariedawi kebero simeta yasaznal. Zerfe mamesgensh tru new aganintm yamesegnalu abatochsh satiteyki betibit menagershm enka mekseft new neger gn emebetachn banchi sayhon dmxachew kef adrgew bebetkrstias endiamesegnwat betemeretu tmesegenalech engi. anchins hawariat sinodos betebale mexafachewsnkua yaswegezut new yeserash (32a) bente anst.slezih yh hulu chihotsh msgana sayhon medefafer yhonal. lib ystish menfesawian abatoch neteyek xega new.

 11. Anonymous November 13, 2013 at 4:41 am Reply

  ለእናቱ ለቅደስት ድንግል ማረያም መዘመር ካልቻልሽና አንድ መዝሙር ከበዛባት
  እነዴት ለልዑል ልጇ ልትዘምሪ ቻለሽ እናትን ትቶ ልጅን መውደድ ይከብዳል ለማንኛውም
  ይሄ በፊት የነበርሽበትን ህይወት የሚያሳይና የምንፍቅና ህይወትሽ ምንኛ እንደከፋ የሚያሳይ ነ

 12. Anonymous November 19, 2013 at 9:02 am Reply

  በእዉነት ከዚህ በላየ ያለዉ አስደነጋጭ ነዉ እመቤታችን እኮ ጌታዪና መደሃኒቴ ያለችዉን ታላቅ ጌታ ከእናቱ ጋር ማወዳደር አምላክነቱን መካድ አሊያም እሱዋም አምላክ ናትና መበላለጥ የለባቸዉም ማለት ነዉ ይህ ጭልጥ ያለ ምንፍቅና ነዉ እረ እባካችሁ መተዳደሪያችንን ቅዱሱን መጽሃፍ አንብቡና የእናትና ልጁን ልዩነት አጥኑ ተሸፍኖ የምንሳለመዉ መጽሐፍ የሚነበብ ነዉ እንድንስመዉ እንጂ እንድናነበዉ የማይመክሩን ካህናቶቻችን የሚጠየቁበት ጊዜ አለ ያም ሩቅ አይሆንም እናንተም በዚህ ምንፍቅና እመቤታችንን እያስለቀሳችሁ ተቆርቁዋሪ መመስላችሁ እርስ በርሱ የሚቃረን ነዉ በከበደና የከበደ ምድራዊ እናት መካከል እንኩዋን ልዩነት አለ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ እናቱንም የፈጠረዉ ጌታ መካከልማ ያለዉ ልዩነት እንዴት ትልቅ ይሆን ለኛ ሲል ከእርሱዋ መወለዱ እንዲህ ሊያስደፍረዉ አይገባም የእዉቀት ማነስ ወደ ስድብ ስለሚወስዳችሁ character assassination ይቀናችሁዋል ይቅር ባይ ጌታ ይቅር ይበላችሁ ዛሬዉኑ ንሰሐ ግቡ በጌታ መምጫ አታስጨንቁን

  • sirak November 19, 2013 at 1:35 pm Reply

   1. ተፈስሂ ኦ ማርያም እም ወአመት- እናትና አገልጋይን የሆንሽ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ!! we know z difference!! that is why we say እናትና አገልጋይ!!እናትነቱዋና አገልጋይነቱዋ ለጌታ መሆኑን ማወቃችን አውቀን እንደምንመስክር የሚያሳይ ይመስለኛል!!እሱዋን ብጽእት የምንላት ከሴቶች መካከል የተመረጥሽ ብለን እንጅ “የፈጠርሽን” ብለን ስላልሆነ ፍጡር የፈጣሪን ምስጋና እንደወሰደው አታስመስል/ይ!!የእሱ የባህሪ የእሱዋ የጸጋ ምን አገናኘው!!at least don’t misquote, at most try 2 perceive z difference b4 spitting out!!!
   2. ያስተበጽኡኒ ኩሉ ትውልድ- ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑኛል(ብጽእት ይሉኛል)!!!ገና ገና ገና……..ገና….ገና…እንልሻለን…..ሰዐሊ ለነ ቅድስት…ቅድስት ሆይ ለምኝልን!!!
   3. የጌታ መምጣት ደግሞ ለክርስቲያኖች ብስራት እንጅ ጭንቅ የለውም አይዞህ/ሽ!!እንዲህ ካንተ/ቺ የተለየ ሃሳብ በሰማህ/ሽ ቁጥር የምትጨነቅ/ቂ ከሆነ ደግሞ እሱ ሳይመጣ አንተ/ቺ እንዳትሄድ/ጅ ተጠንቀቅ/ቂ!!

 13. Anonymous November 23, 2013 at 7:08 am Reply

  anchi batamesegengat eko feteret hulu betseet yelushal tebelaleche anchi tegodashe enge eshua mene kerebate anchi gene tasazengiyalshe!

 14. Beyn Tesfamariam May 24, 2014 at 6:24 pm Reply

  enante amarawoch min abatachu agbtachu new sle eritrea yemtaweru. ato tekeste negash ante derg yerasnh ager mejemerya mra keza sle eritrea taweraleh. enante amarawoch mindnew chgrachu. aseb atagegntum.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: