የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የሽግግር ዘመኑን አፈጻጸም ይገመግማል

Addis Abeba diosces facebook profile pic

 • ግምገማውን ተከትሎ የዋና ሥራ አስኪያጅ ሹመትና የለውጥ አመራሩን ሂደት ለማደናቀፍ በተለያዩ የመቀስቀሻ አጀንዳዎች አሉባልታ ሲነዙ፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያንን ለአድማ ሲቀስቀሱ በቆዩ ሓላፊዎች ላይ የሚወሰዱ ርምጃዎች ይጠበቃሉ፡፡
 • ለዋ/ሥ/አስኪያጅ ሹመት÷ በጎጠኝነትና ጥቅመኝነት ላይ የተመሠረተ የማግባባት እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው፤ ወደ ረዳት ሊቀ ጳጳሱ እና ወደ ፓትርያርኩ የጳጳስና የባለሥልጣን አማላጅ የላኩ፣ የድጋፍ ፊርማ በማሰባሰብ የተጠመዱም አሉ፤ ከብር 6.7 ሚልዮን በላይ በኾነ የገቢ ጉድለት ከሓላፊነታቸው የተወገዱትና በዘረጉት አስከፊ የሙሰኞች ሰንሰለት መዋቅራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚጥሩት የቀድሞው የሀ/ስብከቱ ዋ/ሥ/አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ አንዱ መኾናቸው እየተነገረ ነው፡፡
 • ሀ/ስብከቱ በሽግግር ዘመን ግምገማው÷ ከአሉባልተኞች ተጽዕኖና በባለጉዳዮች ከመጨናነቅ እፎይታ አግኝቶ በዕቅድና ጥናት ላይ የተመሠረቱና በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ትብብር የሚከናወኑ የልማት ዕቅዶች ትግበራን ስለማስተባበር፣ ቅ/ሲኖዶስ የአፈጻጸም አቅጣጫ የሰጠበት የለውጥ አመራር መዋቅር ፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር ጥናት የብዙኀኑን ግንዛቤ አግኝቶና ዳብሮ በሥራ ላይ እንዲውል የውይይት መድረኰች ስለማመቻቸት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚነጋገር ተመልክቷል፡፡
 • የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ይዞታ በማስደፈር በዙሪያው ከተማ/ከተሜነት እንዲስፋፋ በማድረጋቸውና ሥርዐተ ማኅበሩን በመጣሳቸው በማኅበረ መነኰሳቱ የተባረሩት ጸባቴ አባ ኃይለ መስቀል ውቤ የታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም ሊቀ ሊቃውንት ሊኾኑ ነው፡፡ በከፋ ሙሰኝነታቸው ከሚታወቁት የአ/አ ደብረ ምሕረት ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጸሐፊና ሒሳብ ሹም ጋራ የምእመኑ የማያባራ ተቃውሞ የሚሰማባቸው የደብሩ አስተዳዳሪ፣ አባ ኃይለ መስቀል ውቤን ተክተው የገዳሙ ጸባቴ ይኾናሉ – ተጠያቂነት የሌለበት፣ ዘራፊዎችን የሚያበረታታ ዝውውር!!

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የሦስት ወራት የሽግግር ዘመን የአገልግሎት አፈጻጸሙን ለመገምገም ስብሰባ ሊቀመጥ ነው፡፡ ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ፳፻፭ ዓ.ም. ጀምሮ በጊዜያዊ መዋቅርና አደረጃጀት ሲሠራ የቆየው ሀገረ ስብከቱ፣ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ የሚያካሂደው የሽግግር ዘመኑ ሊፈጸም ጥቂት ቀናት በቀሩበት ኹኔታ ውስጥ ነው፡፡

ዛሬ፣ ጥቅምት ፳፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ይጀመራል በተባለውና በሀ/ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በሚመሩት ግምገማዊ ውይይት÷ የሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ አባላት(ዋና ክፍሎች ሓላፊዎች)፣ የሰባቱ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ሥራ አስኪያጆችና የሰው ኃይልና አስተዳደር ክፍል ሓላፊዎች ተሳታፊዎች እንደሚኾኑ ተገልጧል፡፡

በግንቦት ፳፻፭ ዓ.ም. የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ ከአራት አህጉረ ስብከት ወደ አንድ ተመልሶ በአንድ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና በአንድ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲመራ የተደረገው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት፣ በሦስት ወራት የሽግግር ዘመኑ ልዩ መተዳደርያ ደንቡን /መዋቅሩንና አደረጃጀቱን/ በቋሚ ሲኖዶስ በጊዜያዊነት በማጸደቅ ሀ/ስብከቱ በሰባት የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች አደራጅቷል፤ በዚሁ ላይ የተመሠረተ የሰው ኃይል ድልድል ቋሚ ሲኖዶሱ በመደበው መዳቢ ግብረ ኃይል አማካይነት አከናውኗል፡፡

In-service training for the A.A Diosces

የለውጥ ግንዛቤ ማስጨበጫ ዐውደ ትምህርት
ፎቶ: አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት

በሽግግር መዋቅሩ በሁለት ተከታታይ ዙሮች የለውጥን ምንነት የሚያስገነዝቡና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ በመጀመሪያው ዙር ‹‹መልካም አስተዳደር ለዘላቂና ሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን ዕድገት›› በሚል ርእስ ለአምስት ቀናት ያህል የአ/አ ሀገረ ሰብከት ሠራተኞች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች፣ የገዳማትና አድባራት የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ የገዳማትና አድባራት የክፍል ሓላፊዎች፣ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች ሠልጥነዋል፡፡ የሀገረ ስብከቱን ረዳት ሊቀ ጳጳስ ጨምሮ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የየክፍላተ ከተሞቹ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ሥራ አስኪያጆች፣ የክፍል ሓላፊዎችና ሠራተኞች በሁለተኛው ዙር የተካፈሉበት ሥልጠና፡-  ‹‹የለውጥ ሥራ አመራር››፣ ‹‹የኦዲትና ኢንስፔክሽን /ክትትልና ቁጥጥር/ ሥርዐት›› እንዲሁም ‹‹የሒሳብ አያያዝ›› የሚሉ ርእሰ ጉዳዮችን ያካተተ ነበር፡፡

የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን ጥቅምት ፳፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው፣ ሀ/ስብከቱ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ድረስ አዲስ የሥራ መዋቅር በባለሞያ አስጠንቷል፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ፴፪ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የተደመጠው የሀ/ስብከቱ ሪፖርት እንደጠቆመው ለአምስት ዓመታት የሚያገልግል ነው የተባለው አዲሱ የለውጥ አመራር መዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር ጥናት በባለሞያዎች ገለጻ ታግዞ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ከቀረበና ምልአተ ጉባኤው ከመከረበት በኋላ፡- ‹‹ወደ ታች ወርዶ በካህናት፣ በምእመናንና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በውይይት ዳብሮ በሚገባ ተጠንቶና ተስተካክሎ ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲቀርብና ቋሚ ሲኖዶሱም ዓይቶና ተመልክቶ በሥራ ላይ እንዲያውል›› በምልአተ ጉባኤው ተወስኗል፡፡

ሀ/ስብከቱ ዛሬ ከቀትር በኋላ በሚያካሂደው ግምገማዊ ውይይት ይኸው ጥናት የመላውን ፈጻሚ/ባለድርሻ አካላት ግንዛቤና የጋራ ባለቤትነት አግኝቶ ሰፊ መሠረት የሚይዝበትን የብዙኀን መድረክ ስለማመቻቸት በሰፊው እንደሚመክር ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም ጋራ የለውጥ አመራር ጥናቱ ገና ሲጀመር አንሥቶ የተለያዩ የመቀስቀሻ መንገዶችን በመጠቀም ለጥናቱ ምቹ ኹኔታ የፈጠሩትን ረዳት ሊቀ ጳጳሱንና ባለሞያዎችን ለማሸማቀቅ፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳደሮችን ለዐመፅ ለማነሣሣት ሲንቀሳቀሱ የቆዩ የሀ/ስብከቱ፣ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነትና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሓላፊዎች ጎታች ድርጊት ትኩረት እንደሚደረግበት፣ በአንዳንዶቹ ላይም የማሸጋሸግ ርምጃ(?) ሊወሰድ እንደሚችል ተነግሯል፡፡

የ‹ብሉይ ቡድን› እየተባሉ የሚጠሩት እኒህ የለውጥ ተቃዋሚ ጥቅመኞች የዐመፅ ቅሰቀሳቸውን ለማጠናከር ሲያናፍሷቸው ከቆዩዋቸው አሉባልታዎች መካከል፡-

 • የሙዳይ ምጽዋት ቆጠራ ወደ ሰንበት ት/ቤቶችና ምእመናን ሊዘዋወር ነው፤ አንተ [የአድባራት የቢሮ ሠራተኞችንና ካህናትን] ባይተዋር/ተመልካች ብቻ ልትኾን ነው!
 • ማኅበረ ቅዱሳን ካህናትንና የጉባኤ ሊቃውንትን ከየአድባራቱ ጠራርጎ አስወጥቶ ባለዲግሪና ባለዲፕሎማ ሊተካበት ነው፤ ዘመናዊ ትምህርት ያልተማረ ዋጋ የለውም ተብሏል፤ ተነሥ!
 • አባ እስጢፋኖስ፣ በአድባራት ምእመናንን [የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርትን] የበላይ ሊያደርጉ ነው፡፡
 • የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ምክትል ሥራ አስኪያጅነት ማኅበረ ቅዱሳን ለራሱ የሰፋት ናት፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ለራሱ ‹የሰፋትን› የም/ሥ/አስኪያጅነት ሥልጣን ይዞ ሀ/ስብከቱን በአባላቱ ሊያጥለቀልቀው ነው፤ ብጥብጥ ሊያሥነሳ ነው፡፡
 • እነ[እገሌ ተወላጆች] ተዘምቶብናል፤ ከሀ/ስብከቱ ተጠራርገን እንድንወጣ ተደርገናል፤ መብታችን የሚያስጠብቅ ምደባ ሊደረግልን ይገባል፡፡
 • አረጋውያን አለቆች ጡረታ ሊወጡ ነው፡፡
 • ከጥቅምት [ከቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ] በኋላ አባ እስጢፋኖስን ወደ ጅማ እንመልሳቸዋለን፤ ክፍለ ከተማ የሚባል መዋቅር አፈር ድሜ ይበላል!

የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡

የዐመፅ አስተባባሪዎቹ ይኹነኝ ብለው በዚህና በመሳሰለው መልኩ የሚያቀነባበሯቸው መሠረተ ቢስ መቀስቀሻዎች÷ አጥኚ ባለሞያዎቹን እንዲረዱ የተመደቡ ግለሰቦች፣ የትምህርት ዝግጅትና ሞያዊ ብቃት ማነስ የሚታይባቸው አንዳንድ የሀ/ስብከቱ ዋና ክፍሎች ሓላፊዎች የሥራ ሥነ ምግባርን በመጣስ ከአድኃሪ ፍላጎታቸው አንጻር እየቃኙ የሚያናፍሷቸው መረጃዎች እገዛም ያለበት መኾኑ፣ ከግምገማዊ ውይይቱ ጋራ ተያይዞ የሚጠበቀው ማስተካከያና እርምት በምን ያህል ጥልቀትና ስፋት መወሰድ እንደሚገባው የሚጠቁም ይኾናል፡፡

በሌላ በኩል፣ ሀ/ስብከቱ የሥራ መዋቅርና አደረጃጀት ሳይኖረው ለአራት አህጉረ ስብከት ተከፍሎ በነበረበት ወቅት ‹‹ከፍተኛ ሁከትና የገንዘብ ብክነት ከነበረባቸው ገዳማትና አድባራት›› ለዞሩ ችግሮች ግብረ ኃይል በማቋቋም ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠትና ለመቀነስ የተደረገውን ጥረት፣ የሥራ ዕድገትና ዝውውር የሚጠይቁ ባለጉዳዮች መብዛትና የሚስተናገዱበት ጥራትና አግባብነት፣ በየምክንያቱ ሀ/ስብከቱ በሠራተኞቹ የሚከሠሥበትና የቤተ ክርስቲያኒቱ ክብር የሚነካበት ኹኔታ ሌሎች የግምገማዊ ውይይቱ ተጨማሪ ነጥቦች እንደሚኾኑ ተጠቁሟል፡፡

የሀ/ስብከቱን የመዋቅርና አሠራር ለውጥ በመቃወም ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በብርቱ የሚንቀሳቀሱ ሙሰኞችና እነርሱን መተላለፊያ ያደረጉ የተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኞች የሚነዙት አሉባልታ የሚፈጥረውን ማንኛውንም ተጽዕኖ በጽናት መቋቋም፣ የባለጉዳዮች አቤቱታ በለውጥ አመራር መዋቅሩና አሠራሩ መሠረት የሚቀንስበትና በየደረጃው በፍትሐዊነት የሚስተናገድበትን አግባብ በመልካም አስተዳደር መርሖዎች (ግልጽነትና ተጠያቂነት) መሠረት መፈጸምና ማጠናከር ይገባል፡፡

በርግጥም፣ ሀ/ስብከቱ እንደ ከፍተኛ (ውሳኔ ሰጪ) አካል መጠን÷ ለዐበይት መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ልማታዊ ጉዳዮች ቁልፍ አመራር በሚሰጥበት፣ ሀ/ስብከቱ ከአብያተ ክርስቲያን ጋራና አብያተ ክርስቲያን እርስ በርሳቸው በመተባበር የሚያወጧቸውን የልማት ዕቅዶች በበላይነት በሚያስተባብርበት ደረጃ ላይ ለመገኘት የዛሬው ግምገማዊ ውይይት ሂደትና ውጤት ዐይነተኛ መልእክት ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: