የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመክፈቻ ሥርዐተ ጸሎት ተካሄደ

 • ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ የአንድነት ምልክት የኾነች ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት፣ ብሔራዊትና ሉዓላዊት ናት፡፡ ትላንት የነበረችው ቅድስት ተዋሕዶ ሃይማኖት ዛሬም አትለወጥም፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፡፡ በመንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷ ሕዝቡን አንድ አድርጋ ትቀጥላለች፡፡››
 • ‹‹ከፍተኛው የቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣን ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ በካህናትና ምእመናን ላይ ሁሉ ሥልጣኑ ይሠራል፡፡ ውሳኔው ይግባኝ የለውም፡፡››
 • ‹‹የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ ለእምነታችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ዋስትና የሚሰጥ ስለኾነ ምእመናን ለሕጉ ተገዥ መኾን አለባቸው፡፡ አባቶች ከቅ/ሲኖዶሱ የሚወጣውን ውሳኔና የሚተላለፈውን መመሪያ በአባትነት ደረጃ መፈጸምና ማስፈጸም፣ ምእመናንም ከአጥቢያ እስከ መንበረ ፓትርያርክ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡›› /ብፁዕ አቡነ ገሪማ/
 • የመክፈቻ ጸሎቱ በአቤቱታ አቅራቢዎች ተጨናንቀ – ኮሌጅ፣ ወሊሶ፣ ዜና ማርቆስ ገዳም
 • የኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ‹‹ማደርያ የለንም፤ የት እንውደቅ›› ሲሉ ተንበርክከው ተማፀኑ

ሐራ ዘተዋሕዶ ፩ ዓመት ፳፻(200) ጡመራ

Opening Prayer of the Synod Annual Meeting'05የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ የመክፈቻ ሥርዐተ ጸሎት ተከናወነ፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ዛሬ፣ ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ሠርክ ላይ ከሠላሳ ያላነሱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት የተካሄደውን የምልአተ ጉባኤውን የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ የመክፈቻ ጸሎት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መርተዋል፤ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤትና የውጭ ግንኙነት መምሪያ የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በጽሑፍ ያዘጋጁትን ትምህርት በንባብ አሰምተዋል፡፡

ብፁዕነታቸው በጽሑፍ የሰጡት ትምህርት ‹‹ሑሩ ወመሀሩ፤ ሒዱና አስተምሩ›› (ማቴ.፳፰ ÷ ፲፱) በሚለው የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዋርያዊ ተልእኮ ትእዛዝ ላይ የተመሠረተ ነበር፤ በይዘቱም በቅ/ሲኖዶስ ምንነትና በጉባኤው ታሪካዊ አመጣጥ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያን አመራርና አስተዳደር ባለው የሕግ አውጭነት ሚናና ሉዓላዊ ሥልጣኑ፣ ውሳኔውን በማስፈጸምና በመፈጸም ከብፁዓን አባቶች ጀምሮ ከካህናትና ከምእመናን በሚጠበቀው ድርሻ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

His Grace Abune Garima

ብፁዕ አቡነ ገሪማ

ብፁዕነታቸው በሰጡት ትምህርት፣ ቤተ ክርስቲያን በምድር ላይ ያለች መንግሥተ እግዚአብሔር ናት፡፡ አስተዳደሯን የምትመራው ቅዱሳን ሐዋርያትና አበው ሊቃውንት በሠሩላትና በወሰኑላት ፍትሕ መንፈሳዊ/ድንጋጌ መሠረት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር በበላይነት የሚመራው ከፍተኛው ባለሥልጣን ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ÷ ሃይማኖት እንዲጸና፣ የአበው ቀኖና እንዳይፋለስ፣ ምእመናን በሥነ ምግባር እንዲታነጹ በፓትርያርኩ ሰብሳቢነት የሚደረግ የኤጲስ ቆጶሳትና ከዚያ በላይ ያሉ ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት ጉባኤ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትና አበው ሊቃውንት ያስተላለፏቸው ውሳኔዎች ዝርዝርም ሲኖዶስ ይባላል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የዕድሜ ልክ አባላት ናቸው፡፡

በኢየሩሳሌሙ የሐዋርያት ጉባኤ ተጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚቀጥለው ቅ/ሲኖዶስ፣ ሕግ በመደንገግና ቀኖና በማውጣት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃል፤ ከፍተኛው የቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣን ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፤ በካህናትና ምእመናን ሁሉ ላይ ሥልጣኑ ይሠራል፤ ውሳኔውም ይግባኝ የለውም፡፡ /ግብ.ሐዋ.፩÷፳፮፤ ምዕ.፮፤ ምዕ.፲፭/

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ የአንድነት ምልክት የኾነች ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት፣ ብሔራዊትና ሉዓላዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ትላንት የነበረችው ቅድስት ተዋሕዶ ሃይማኖት ዛሬም አትለወጥም፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፡፡ በመንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷ ሕዝቡን አንድ አድርጋ ትቀጥላለች፡፡

በፍትሕ መንፈሳዊ በአምስተኛው አንቀጽ ቁጥር 164 በሚያዝዘው መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ፣ በዓመቱ መጀመሪያ ጥቅምት ፲፪ ቀንና በዓለ ትንሣኤ በዋለ በ፳፭ው ቀን /በርክበ ካህናት/ መደበኛ ስብሰባውን ያካሂዳል፡፡ ድንገተኛ ጉዳይ ሲያጋጥም አስቸኳይ ስብሰባ ያደርጋል፡፡ ትምህርተ ወንጌል በስፋት፣ በጥራትና በጥልቀት እንዲሰጥ፣ ቅርስ እንዲጠበቅ ይመክራል፤ ይወስናል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ለእምነታችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ህልውና ዋስትና የሚሰጥ ስለኾነ ምእመናን ለሕጉ ተገዥ መኾን አለባቸው፡፡ አባቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጣውን ውሳኔ፣ የሚተላለፈውን መመሪያ ሁሉ በአባትነት ደረጃ እንዲያስፈጽሙና እንዲፈጽሙ፣ ምእመናንም ከአጥቢያ እስከ መንበረ ፓትርያርክ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ እንዲወጡ ምልአተ ጉባኤው መልእክቱን ያስተላልፋል፤ በማለት ብፁዕነታቸው ትምህርታቸውን አጠቃለዋል፡

የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ነገ በ2፡30 የመነጋገርያ አጀንዳዎችን በማጽደቅ ይቀጥላል፡፡ አጀንዳዎቹ በቋሚ ሲኖዶሱ አማካይነት በቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት የተዘጋጁትንና ከምልአተ ጉባኤው አባላት የሚጠቆሙትን የሚጨምር ይኾናል፡፡ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በ፴፪ው ዓመታዊ ስብሰባው ያወጣው መግለጫና ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በምልአተ ጉባኤው ውይይት ዳብሮ የአህጉረ ስብከት ዓመታዊ የሥራ መመሪያ ለመኾን እንደሚተላለፍ ይጠበቃል፡፡

‹‹ከምዝገባችኹ ቀን ቀድማችኹ መጥታችኋል›› በሚል የኮሌጁን ማደርያ ተከልክለው እየተንገላቱ የሚገኙት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና የኮሌጁን መኖርያ ቤቶች ለቃችኹ ካልወጣችኹ በሚል ደመወዛቸው ታግዶና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ተነፍገው የሚገኙ መምህራን በምልአተ ጉባኤው የመክፈቻ ጸሎት ላይ ተገኝተዋል፡፡ በተለይ ደቀ መዛሙርቱ የመክፈቻ ሥርዐተ ጸሎቱ ተጠናቅቆ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ ሲወጡ በዐውደ ምሕረቱ ላይ ተንበርክከው ‹‹ማደርያ የለንም፤ የት እንውደቅ?›› እያሉ አሰምተው ሲናገሩና አንዳንዶቹም ሲያለቅሱ ተስተውለዋል፡፡

ከደቀ መዛሙርቱ እንደተገለጸው፣ ለምዝገባ ጥቅምት ፭ ቀን እንዲደርሱ ተጽፎላቸው በነበረው ደብዳቤ መሠረት ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ምዝገባው ወደ ጥቅምት ፳፭ ቀን መተላለፉ ተነግሯቸው የኮሌጁን መኝታ ቤት ተከልክለው እየተንገላቱ ይገኛሉ፡፡ እንደ ብዙዎቹ እምነት የምዝገባው ቀን መራዘሙ ተንኰል ያለበት ነው፡፡ ይኸውም እልባት ያላገኘውን የኮሌጁን አስተዳደራዊ ችግር ደቀ መዛሙርቱ በቅ/ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ሰሞን እንዳያሰሙና ምናልባትም ከሥልጣናቸው የተገለሉት የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ የተቃውሞ አስተባባሪዎች ናቸው ባሏቸው የተወሰኑ ደቀ መዛሙርት ላይ ያለሃይ ባይ ለመውሰድ ያሰቡትን የማባረር ርምጃ ለማመቻቸት ነው፤ ተብሏል፡፡

ምልአተ ጉባኤው፣ ከአጠቃላይ ጉባኤው በተሰጠው ዐደራ መሠረት የመንፈሳዊ ኮሌጁን ችግር በአጀንዳነት ይዞ ከዚህ ቀደም ተጣርቶ በቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ መሠረት መቋጫ እንደሚያደርግለት ይጠበቃል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ የትምህርት ተቋማትን በበላይነት ለመከታተልና ለመቆጣጠር በተሰጣቸው ሥልጣንና የኮሌጁን ቦርድ ለፓትርያርኩ ተጠሪ አድርጎ ለኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ በተመቸው መተዳደርያ ደንብ መካከል ያለው መጣረስ ቸል ሊባል አይገባም፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ዓመታዊ ስብሰባ የመዝጊያ ንግግራቸው ‹‹ግልጽነትና መገማገም በሁሉም የቤተ ክርስቲያን አካላት ዘንድ ሊለመድ የሚገባው ባህል ነው›› ብለዋል፡፡

Advertisements

4 thoughts on “የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመክፈቻ ሥርዐተ ጸሎት ተካሄደ

 1. Anonymous October 22, 2013 at 3:40 am Reply

  pls don’t post an information which is irrelevant for z laity. don’t poleticize z church and our bishops. I think one year is enough to repent cuz u don’t bring any change since u start ur insultation.

 2. Anonymous October 22, 2013 at 5:03 am Reply

  melkam lidet le hara zetwahido

 3. Anonymous October 22, 2013 at 7:55 am Reply

  bertu

 4. Gishen October 22, 2013 at 11:20 am Reply

  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ፡፡
  ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም፡- እባካችሁ!!!!
  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በእንግሊዝ ለንደን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን እና ምዕመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ እባካችሁ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲታይ፣ ህዝበ ክርስቲያኑ እንዲያውቀው አድርጉልን፡፡ ቤተክርስቲያን ፈተና ውስጥ ናት እባካችሁ! እባካችሁ! እውነቱን ለህዝበ ክርስቲያኑ፣ ለሚመለከተው ሁሉ አሳውቁልን፡፡
  እውነቱን ብታውጡ፣ ችግሩ የሚፈታበትን መንገድ በሚቻላችሁ ሁሉ ብታደርጉ በእውነት በእግዚአብሔር ዘንድ የዘመኑን መሰዋትነት እንደተቀበላችሁ እመኑ፡፡
  ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ!! እባካችሁ መፍትሄውን አንድ በሉ!!!
  እግዚአብሔር ይስጥልን!!!!
  http://www.ethiotube.net/video/24823/Chaos-at-Ethiopian-Orthodox-Church-in-London-the-youth-stood-up-for-their-religion–February-10-2013

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: