ማኅበረ ቅዱሳን – የሃይማኖት አጥባቂነት ወይስ የአክራሪነት ትእምርት?

Semea_Tsidq_Logo

(ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፤ 19 ዓመት ቁጥር 255፤ ነሐሴ 16 – ጳጉሜ 5 2004 ዓ.ም)

ዲ/ን ታደሰ ወርቁ*

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ መንግሥታዊ አካላት በወጡ ሰነዶችና በሚሰሙ ንግግሮች ማኅበረ ቅዱሳንን ‹‹የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት አክራሪዎች›› ማንጸርያ አድርጎ የመውሰድ አዝማሚያዎች እየታዩ ነው፡፡ ይህን የተሳሳተ አቻ ፈጠራ በመጠቀም አፅራረ ቤተ ክርስቲያን የራሳቸውን ፍላጎት ሲያራግቡበት ይታያል፡፡ ተከታዩ ጽሑፍ መንግሥት አቋሞቹን የገለጸባቸውን ሰነዶችና የማኅበረ ቅዱሳንን የኅትመት ውጤቶች በመፈተሽ ማኅበረ ቅዱሳን የሃይማኖት አጥባቂነት እንጂ የሃይማኖት አክራሪነት ትእምርት እንዳልኾነና ሊኾንም እንደማይችል ያስረዳል፡፡

*                         *                       *

Mmr. Tadesse Worku

ዲ/ን ታደሰ ወርቁ

አክራሪነት አሉታዊ ትርጉም ሲኖረው የራስን እምነትና አመለካከት በሌሎች ላይ ለመጫን መሞከር ነው፡፡ ሃይማኖት መንግሥታዊ ቅርጽ ይዞ እንዲወጣ ለማድረግ መሞከር ራሱ አክራሪነት እንደኾነ የዘርፉ ዐዋቆች ይሞግታሉ፡፡ አክራሪነት በአሉታዊ መልኩ የፖሊቲካ ገጽታ ያለው ነው፡፡ ኾኖም ግን ሃይማኖትን ማጥበቅ አክራሪነት አይደለም፡፡ ሃይማኖት ፍጹም እውነታን በፍጹም እምነት ስለሚቀበል ከሌሎች ግላዊ አስተሳሰቦች የተለየ ነው፡፡ የሃይማኖት መገለጫዎችን መጠቀም የዚያን ሃይማኖት ጥልቀት የሚያሳይ እንጂ እንደ ችግርም የሚወሰድ ወይም አክራሪነት ሊኾን አይችልም፡፡ «መጾም፣ መጸለይ፣ ሥርዓተ አምልኮን መፈጸም ለሃይማኖቱ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንጂ አክራሪነት ሊባል አይችልም፤» ይላሉ የዘርፉ ምሁራን፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም የሃይማኖት አክራሪነትን ለመቃወም ባዘጋጃቸው ሰነዶች የአክራሪነትና የአጥባቂነት ፅንሰ ሐሶቦች በጥሩ ኹኔታ ተለይተው ተገልጸዋል፡፡ ሰነዶቹ አክራሪነትንና አጥባቂነትን በአግባቡ ለይተውና ተንትነው ያስቀምጣሉ፡፡ በዚሁ መሠረት አጥባቂነትን፣ ‹‹የግል ሃይማኖትን ሃይማኖቱ በሚያዘው መሠረት ሳይንጠባጠብ ሁሉንም ትእዛዛት መፈጸም ነው፤» በማለት ሲፈታው አክራሪነትን ደግሞ፣ «ከራስ እምነት ወጥቶ ሌላውን መተንኮስና የሌሎችን ሃይማኖት መኖር አለማመንና አለመፍቀድ ወይም ሌሎቹን አስገድዶ የራስ እምነት ተከታዮች ለማድረግ መጣር ነው፤» ይላል፡፡

ከዚህ ብያኔ ስንነሣ ሙስሊምም ኾነ ክርስቲያን ከርሱ ውጭ የኾኑትን የሌሎቹን መኖር የማይቀበልና ከግለሰቦቹ ፈቃድ ውጭ አስገዳጅ እስከኾነ ድረስ እርሱን አክራሪ ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ መልኩ አክራሪው ይህንኑ ድርጊት ሊፈጽም የተነሣውን ቡድን ብቻ እንጂ «አክራሪው ቡድን» የወጣበትን/የተገኘበትን ቤተ እምነት ሊወክል አይችልም፡፡ ስለዚህ የአክራሪ እስልምና ቡድን መኖር የእስልምና ተከታዮችን በሙሉ «አክራሪ» አስብሎ ሊያስፈርጃቸው አይችልም፤ ለሌላው ቤተ እምነትም እንዲሁ፡፡

የሃይማኖት አክራሪነትንና አጥባቂነትን በዚህ መልኩ ከተረዳን ማኅበረ ቅዱሳን የሃይማኖት አክራሪነት ወይስ አጥባቂነት ትእምርት የሚለውን ወቅታዊ ጥያቄ መመለስ ግድ ይለናል፡፡ ይኸውም መንግሥት የተለያዩ መግለጫዎችን ከማውጣት አንሥቶ ውይይቶችን እያካሔደና ሌሎች ርምጃዎችንም እየወሰደ ይገኛል፡፡ ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ማኅበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት ለማስፈረጅና ከመንግሥት ጋራ ለማጋጨት ቆርጠው የተነሡ አካላት እንዳሉ ከአንዳንድ የውይይት መድረኮች፣ ሰነዶች፣ [የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ] ብሎጎችና የደብዳቤ መጻጻፎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

በተለይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሚያዝያ 9 ቀን 2004 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወር ሪፖርት በሚያቀርቡበት ወቅት የሃይማኖት አክራሪነትንና የመንግሥታቸውን የፀረ አክራሪነት እንቅስቃሴ በተመለከተ ለምክር ቤቱ አባላት ሰፊ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ «. . . አንዳንድ የሰለፊ እምነት ተከታዮች . . . በተለያየ መንገድ አንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የሚያራምዱትን ግልባጭ ሲያራምዱ ታይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሙስሊም ነው፡፡ስታቲስቲክስ መሥሪያ ቤት ያቀረበው መረጃ ውሸት ነው፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ሙስሊም ስለኾነ የእስላም መንግሥት ነው መቋቋም ያለበት የሚል ቅስቀሳ በሰፊው ነው የሚካሔደው፡፡ በእነዚህ አክራሪዎች፡፡. . .» ብለው መጥቀሳቸውን ተከትሎ የስም ማጥፋት ዘመቻው ከወትሮው ተባብሷል፡፡

ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪነትን ከመቃወም አንጻር ምን እንደ ሠራ ከዚህም ጋራ በማኅበሩ ላይ ያሉ ብዥታዎችን በማጥራት የማኅበሩን አጠቃላይ ኹኔታ ለመግለጽ ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ኾኗል፡፡ ይህ ጽሑፍም ማኅበሩ በሃይማኖት አክራሪነት ጉዳይ ያለውን አቋም፣ የማኅበሩን እውነተኛ ማንነትና ትክክለኛ ገጽታ ከድርጊቱና ከወሰዳቸው አቋሞች አንጻር ለማስረዳት የተዘጋጀ ነው፡፡ ሦስት መሠረታዊ መነሻዎችን እናቅርብ፡፡

የፍረጃው አዝማሚያና የቅርብ መነሻ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት መኾኑ፤

በምክር ቤቱ ማብራሪያ ውስጥ አቶ መለስ ማኅበረ ቅዱሳንን የሰለፊ ማንጸርያ አድርገው ያቀረቡት ከሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት አንጻር ብቻ ነው፡፡ ይህም ቢኾን በራሱ ማኅበረ ቅዱሳንን እንደ ተቋም አክራሪ አያሰኘውም፤ ስለ ሁለት ነገር፤ የመጀመሪያው፣ አቶ መለስ «አንዳንድ የማኅበረ ቅዱስን አባላት» አሉ እንጂ ማኅበረ ቅዱሳን አላሉም፡፡ ይህም ግለሰባዊ ሓላፊነትን እንጂ ተቋማዊ ሓላፊነትን አይገልጽም፡፡ ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ማኅበር የሃይማኖት አክራሪነት ትእምርት ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡

ሁለተኛው፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራውን ውጤት ከአለመቀበል ጋራ ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ተቋም «አክራሪ» ተብሏል በሚለው ብንሔድ እንኳን የመረጃና የማስረጃ ዳጥን ከማሳበቅ ውጭ ማኅበረ ቅዱሳንን የሃይማኖት አክራሪ አያሰኘውም፡፡ ምክንያቱም የሕዝብና ቤት ቆጠራው ውጤት ላይ «ጥርጣሬ አለኝ» ያለችው /ይህም ቢኾን አክራሪ አያስብልም/ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንጂ ማኅበረ ቅዱሳን ወይም አንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት አይደሉም፡፡

በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክለው መግለጫ የሰጡት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ መጋቤ ሥርዐት ዳንኤል ወልደ ገሪማ ቤተ ክርስቲያኒቱ በውጤቱ ላይ ያላትን ጥርጣሬ ሲገልጹ፣ «መንግሥት የሕዝብና ቤት ቆጠራ በሚያካሒድበት ወቅት ከቦታ ርቀት የተነሣ በገዳም የሚገኙ መነኮሳትና መነኮሳዪያትን፣ የቆሎ ተማሪዎች ቁጥር ካለማካተቱም ባሻገር በተለያዩ ምክንያቶች ያልተቆጠሩ ምእመናን ተካተዋል ለማለት ስለሚያጠራጥር ቤተ ክርስ ቲያኗ መንግሥት ይፋ ያደረገውን ውጤት ሙሉ ለሙሉ ለመቀበል ይቸግራታል፤» በማለት ነው፡፡ የማኅበሩ ልሳን የኾነችው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በወቅቱ «የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሕዝብ ቆጠራ ውጤት ጥርጣሬ እንዳላት አስታወቀች» በሚል ርእስ ዘግባለች፡፡ /16 ዓመት ቁጥር 71 ቅጽ 16 ቁጥር 168 ከታኅሣሥ 16 – 30 ቀን 2001 ./፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ መግለጫው የተሰጠው በቤተ ክርስቲያኒቱ ነው፡፡ ይህም መግለጫ በራሱ አክራሪ አያሰኝም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ይህን ከመግለጽ/ከማስታወቅ አልፎ የሰጠው መግለጫ የለም፡፡ በምንም መስፈርት የማኅበረ ቅዱሳንን ተቋማዊ ሰውነት ወይም የማኅበሩን አባላት የሃይማኖት አክራሪነት ትእምርት አድርጎ አያስወስድም፡፡

 

የመንግሥት የሃይማኖት አክራሪነት ብያኔ ማኅበረ ቅዱሳንን አይገልጽም

የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱ በየሰነዶቹ እንደገለጸው፣ የሃይማኖት አክራሪነትን የሚመለከተው ከሃይማኖት ሳይኾን ከልማት፣ ዴሞክራሲና ሰላም አንጻር ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነቱ ኀልዮት አከራካሪ ቢኾንም መንግሥት፣ «እኔ አንድን ተቋም ወይም ግለሰብ የሃይማኖት አክራሪ ነው የምልበት የራሴ የብያኔ መስፈርት አለኝ» ካለ መብቱ ነው፡፡ የትኛውም ሀገር ከራሱ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ኹኔታዎች አንጻር መበየን ስለሚችል፡፡ መስፈርቱንም «የሃይማኖት አክራሪነትና የፀረ አክራሪነት ትግላችን» በሚል ርእስ ለመንግሥት አመራሮች ሥልጠና በቀረበው ሰነድ እና «ልማት፣ ዴሞክራሲና የሃይማኖት አክራሪነት» በሚል ርእስ በፌዴራል ጉዳዮች የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀው ጽሑፍ እንዲሁም በአዲስ ራእይ የንድፈ መጽሔትም ሲያትተው እንደሚከተለው ይላል፡-

 • በዜጎች የእምነት ነጻነት አለማመን፤ በማስገደድ የራስን እምነት ለማስያዝ መንቀሳቀስ፤ እምነት ለመያዝ ያለውን ነጻነት በኀይል በማስገደድ መገደብ ወይም መከላከል፤
 • በሃይማኖት እኩልነት አለማመን፤ የእኔ ይበልጣል የሌላኛው ያንሳል በሚል መንቀሳቀስ፤ ሁሉም እኩል መኾኑ የእኔን ሃይማኖት ክብርና ሞገስ ይቀንሳል በሚል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማካሔድ፤
 • መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለውን መንግሥታዊ መርሕ በመጣስ መንግሥታዊ ሃይማኖት ካልሆንኩ ወይም ሃይማኖታዊ መንግሥት ከሌላ በሚል ይህንኑ ለማሳካት በተግባር መንቀሳቀስ፤ 

በእነዚህ የመንግሥት የሃይማኖት አክራሪነት መስፈርትነት ማኅበረ ቅዱሳን ሲመዘን ማኅበሩ አንዱንም አሟልቶ አይገኝም፤ ወይም ሦስቱም የብያኔ መስፈርቶች ማኅበረ ቅዱሳንን አይመለከቱም፡፡ እስኪ አንድ በአንድ እንመልከታቸው፡፡

በዜጎችእምነት ነጻነት አለማመን፤ ከዚህ አንጻር ማኅበረ ቅዱሳን ሲታይ እምነቱን ከመግለጽ አልፎ ለዜጎች እምነት ነጻነት መከበር የድርሻውን ተወጥቷል፡፡ ይኸውም ሌሎችን በማስገደድ የራሱን እምነት ለማስያዝ መንቀሳቀስ ወይም የሌሎችን የእምነት ነጻነት በኀይል መገደብ ፀረ ሕገ መንግሥታዊ ብቻ ሳይኾኑ ኢ-ሃይማኖታዊ ድርጊት መኾኑን በይፋ የገለጸ ማኅበር ነው፡፡ ያለአንዳች ማጋነን በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ የሕገ መንግሥት ትምህርት ከመጀመሩ በፊት፣ ማኅበረ ቅዱሳን የእምነት ነጻነት በሕገ መንግሥቱ ብቻ ሳይኾን በሌሎቹም የሀገሪቱ ሕጎች ያለውን ቦታ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በመጽሔቱና በጋዜጣው አስተምሯል፡፡ ይህን ያደረገው ደግሞ በመንግሥት ወይም በሌላ ኀይል ትእዛዝ አይደለም፡፡ የዜጎችን የእምነት ነጻነት በመሠረቱ ከማመን ነው፡፡

ማኅበሩ ይህን እምነቱን «ሐመረ ጽድቅ» በሚል ርእስ በ1996 ዓ.ም ባሳተመው የሐመር መጽሔትና የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ልዩ የጋራ ዕትም፣ «የእምነት ነጻነት በኢትዮጵያ ሕግ» በሚል በተዘጋጀው መጣጥፍ ላይ፣ «የእምነት ነጻነት ሰፋ ባለ መልኩ ሲታይ የኅሊና ነጻነት ማለትም ማንም ሰው ያለፍላጎቱ ማንኛውንም ዐይነት ሃይማኖት ወይም እምነት እንዲቀበል አይገደድም ማለት ነው፡፡ ማንም ሰው በማንኛውም መንገድ አንድን ሃይማኖት ከሌላው በመምረጡ ወይም ምንም ዐይነት ሃይማኖት እንዳይኖረው በመፈለጉ ምክንያት በምንም መንገድ አይቀጣም፡፡ የአንድ ሰው የሃይማኖት እምነት የግል ጉዳይ እንጂ በመንግሥት ባለሥልጣናት ወይም በሌሎች ሰዎች አስገዳጅነት የሚመረጥ ወይም የሚተውና የሚለውጥ ጉዳይ አይደለም፤» ሲል ገልጿል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ማኅበሩ በዚሁ መጣጥፍ ላይ የእምነት ነጻነት በሀገራችን ያለውን ሕጋዊ ይዞታና ጥበቃ ሲያትት እንዲህ ብሏል፡-

የእምነት ነጻነት በሕገ መንግሥቱ ልዩ ቦታ ከተሰጣቸው መሠረታዊ የሰው ልጆች መብቶችና ነጻነቶች አንዱ ነው፤. . . በሀገራችን ማንም ሰው የመረጠውን እምነት የመከተል፣ የማስተማርና የማስፋፋት መብት አለው፡፡ መንግሥትን ጨምሮ ማንኛውም ሰው ጣልቃ በመግባት በሌላው ሰው የእምነት ነጻነት ላይ ተጽዕኖ እንዳይደረግበት የሕግ ጥበቃ አለ፡፡ ስለዚህ በሕጉ መሠረት የሌሎችን ሰዎች ነጻነትና መብት ለመጠበቅ ከተቀመጠው ገደብ ውጭ ማንም ሰው በማንኛውም ቦታና ጊዜ ሥርዐተ አምልኮቱን እንዳይፈጽም ሊከለከል ወይም ማንኛውም ተጽዕኖ ሊደረግበት አይገባም፡፡ /ሐመረ ጸድቅ፣ 1996፣55/፡፡

ከዚህ ሁሉ መረዳት የሚቻለው ማኅበረ ቅዱሳን በሃይማኖት አክራሪነት ስሜት የሌሎችን የእምነት ነጻነት መብት አለመቀበል ወይም መገደብ ይቅርና የራስን እምነት አጽንቶ ከመያዝ ጋራ ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ የሌሎችን የእምነት ነጻነት እንዲያከብሩ ብርቱ ጥረት ማድረጉን ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ መንግሥታዊ ያልኾኑ አካላት እንዲህ ዐይነቱን ሕገ መንግሥታዊ መብት መጣሳቸውንም በዚህ ጽሑፍ እንዲህ ሲል አጋልጧል፡፡

አንዳንድ መንግሥታዊ ያልኾኑ ገባሬ ሠናይ ድርጅቶች በሚሰጡቸው ማኅበራዊ አገልግሎቶች ዜጎችን በድርጅቶቹ የሚደገፈውን እምነት ካልተቀበሉ አድልዎ ይፈጽሙባቸዋል፡፡ በተለይ ትምህርት፣ በማናቸውም ረገድ ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካ አመለካከትና ከባህላዊ ተጽዕኖ ነጻ በኾነ መንገድ መካሔድ እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 90/2/ በግልጽ ተደንግጎ እያለ በአሁኑ ሰዓት በአንዳንድ መንግሥታዊ ባልኾኑ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና የእምነት ተቋማት በተቋቋሙ /ቤቶች የሚማሩ ሕፃናትና ወጣቶች ከወላጆቻቸው የወረሱትን ሃይማኖት እንዲለውጡ ይገደዳሉ፡፡ ፈቃደኛ ካልኾኑ ደግሞ ሌሎች ምክንያቶች እየተፈለጉ ከትምህርት ገበታቸው እንዲወገዱ የሚደረግበት አጋጣሚ እየታየ ነው፡፡ በአንዳንድ የመንግሥት የትምህርት ተቋማትም ሓላፊዎች በተማሪዎቻቸው የእምነት ነጻነት ላይ የሀገሪቱ ሕግ ከሚፈቅደው ውጭ ገደብ የሚጥሉበት ኹኔታ አለ፡፡

እነዚህ ድርጊቶች የሀገሪቱ የበላይ ሕግ የኾነው የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የሚጥሱ በመኾናቸው የድርጊቱን ፈጻሚዎች ተጠያቂነት የሚያስከትል ነው፡፡ እዚህ ላይ መብቱን የማስከብር ሓላፊነትና ግዴታ የተጣለባቸው በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተጠያቂነት ስላለባቸው ተገቢውን የእርምት ርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የራሱን እምነት በሌሎች ላይ ለመጫን እንዲያመቸው የሌሎችን የእምነት ነጻነት በኀይል ወይም በጉልበት ሊገድብ ይቅርና በአመለካከት እንኳን እንዲህ ዐይነቱ ኢ-ሃይማኖታዊ ድርጊት የሚታይበት ማኅበር አለመኾኑን በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ አኳያ ማኅበረ ቅዱሳን የሃይማኖት መከባበር ትእምርት እንጂ የሃይማኖት አክራሪነት ትእምርት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ማኅበር አለመኾኑን ብያኔው ይገልጣል፡፡

ሌላው የመንግሥት የሃይማኖት አክራሪነት ብያኔ በሃይማኖት እኩልነት አለማመን ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ጥንቱንም ቢኾን በዚህ ረገድ የአመለካከትም ኾነ የተግባር ችግር የለበትም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በሃይማኖት ልዩነት መከባበር ላይ ያለውን እምነት በተለያዩ ጊዜ ገልጿል፡፡ በሃይማኖት ልዩነት መከባበርን የሚተነትኑ ጽሑፎችን በልሳኖቹ አስተናግዷል፡፡ በሐመር መጽሔት መስከረም/ጥቅምት፣ 1999 ዓ.ም. ዕትሙ «ሽብር ሃይማኖት የለውም» በሚል ርእስ ስለ ሽብርተኝነትና የሽብር መሣሪያ ስለኾኑት አክራሪነትና ጽንፈኝነት የሚተነትነውን ጽሑፍ ማስታወስ ብቻ በቂ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ስለ ሃይማኖት እኩልነት የሰፈረውን ሐሳብ እንመልከት፡፡

. . .ስለዚህ ማንኛውምና የየትኛውም እምነት ተከታይ የእምነቱን አስተምህሮ በመከተል በራሱ የተስተካከለ ሕይወት ሊኖርና የተቻለውን ሊያደርግ ይገባል፡፡ የራሱን ሃይማኖት አጥብቆ ሊከተልና የሌሎችንም ሃይማኖት ሊያከብር ይገባል፡፡ ከመወያየት ይልቅ ከአንተ የኔ ይሻላል ወይም ይበልጣል እያሉ ሳይፎካከሩና ሳይወራረዱ እርስ በርስ ተከባብረው ሊኖሩ ይገባል፡፡ ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው የሚነሡ ጽንፈኛ ቡድኖችና ግለሰቦች ለመከላከል ዋናው መንገድ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ በልዩነት መቻቻልንና አንድነትን መስበክ፣ ማስተማርና በተለያዩ እምነት መሪዎች መካከል መከባበርንና መዋደድን ማስፈን ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን እንዲህ ዓይነቱን የሃይማኖት እኩልነት መርሕን ያከበረና የሚተነትን ጽሑፍ ብቻ አይደለም ያስተናገደው፡፡ ከሀገሪቱ ሕግ አንጻር የሃይማኖት እኩልነት ሲባል ምን ማለት እንደኾነ ለሁሉም በሚኾን መልኩ ያስተማረ ማኅበር ነው፡፡ ይህንንም በ2001 ዓ.ም በታተመው «ሐመረ ተዋሕዶ የሐመር መጽሔት ልዩ ዕትም» ላይ «ሃይማኖት በመድበለ ሃይማኖት ማኅብረሰብ» በሚል ርእስ የተዘጋጀውን መጣጥፍ መመልከት ከበቂ በላይ ማረጋገጫ ነው፡፡ ጽሑፉም የሚያጠነጥነው ሀገራችን ኢትዮጵያ የመድበለ ሃይማኖት ማኅበረሰብ ሀገር እንደ መኾኗ መጠን ሁሉም ቤተ እምነት ከእነርሱ ውጪ ካሉ ቤተ እምነቶች ጋራ እንዴትና በምን ኹኔታ ተከባብረው መኖር እንዳለባቸውና በመድበለ ሃይማኖት ማኅበረሰብ ውስጥ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያ የሃይማኖት እኩልነትና ነጻነት ከሕግ አንጻር በምን አግባብ መፈታት እንዳለበት የሚያመለክት ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በመርሑ ከማመን በላይ በተግባር ብዙ ርቀት መጓዙን ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ ጽሑፎቹ «የእኔ ይበልጣል፣ የሌላው ያንሣል» በሚል ትምክህት ሌላውን ለመድፈቅ አለመነሣቱንም በሚገባ የሚገልጹ ሐቆች ናቸው፡፡ «ሁሉም እኩል መኾኑ የእኔን ሃይማኖት ክብርና ሞገስ ይቀንሳል» በሚል ተግባራዊ እንቅስቃሴ አለማካሔዱን ብቻ ሳይኾን የሃይማኖት እኩልነት መርሕን በአግባቡ ተንትኖ እየተገበረው ያለ ማኅበር መኾኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ከዚሁ መርሕ በመነሣት «ክርስትናና እስልምናን ጨምሮ ማንኛውም ሃይማኖት በመሠረቱ የሚሰ ብከው በሰላም አብሮ ተቻችሎ መኖር ነው፤» በማለት የሌሎችንም ቤተ እምነታት ሰላም ወዳድነት ዕውቅና የሰጠ የአብሮነትና የመከባበር ትእምርት ነው ማኅበረ ቅዱሳን፡፡ /ሐመር፣ መስከረም/ጥቅምት 1999 ዓ.ም.፣ 22/

የመጨረሻው የመንግሥት የሃይማኖት አክራሪነት ብያኔ፣ «መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ መርሕ በመጣስ መንግሥታዊ ሃይማኖት ካልኾነ ማለት ወይም ሃይማኖታዊ መንግሥት ከሌለ በሚል ይህንኑ ለማሳካት በተግባር መንቀሳቀስ» የሚል ነው፡፡ ከዚህ የሃይማኖት አክራሪነት ብያኔያዊ መስፈርት አንጻር ማኅበረ ቅዱሳን ሲፈተሽ ፍርጃው ተገቢ አይደለም፡፡

የፍርጃውን አስገራሚ ገጽታ ጉልሕ የሚያደርገው ደግሞ «የሃይማኖት አክራሪነትና የፀረ አክራሪነት ትግላችን» በሚል ርእስ ለአመራር ሥልጠና በተዘጋጀው ሰነድ ላይ የሰፈረው አቋም ነው፡፡ የሥልጠና ሰነዱም ማኅበረ ቅዱሳንን ሲገልጸው፣ «ማኅበረ ቅዱሳን የእምነት ነጻነትን፣ የሃይማኖት እኩልነትንና መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ መርሕ ይቃወማል» በማለት ነው፡፡

ዳሩ ግን ማኅበረ ቅዱሳን በሰነዱ ላይ እንደተቀመጠው የእምነት ነጻነትን፣ የሃይማኖት እኩልነትንና መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ መርሕ ሊቃወም ይቅርና እንዲያውም ሐመር መጽሔትና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አለኝታነቱን አረጋግጠው በርእሰ አንቀጾቻቸው በተደጋጋሚ አስፍረዋል፡፡ ለዚህም የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣን 14 ዓመት ቁጥር 21፣ ቅጽ 14 ቁጥር 121 ኅዳር 1999 ዓ.ም ዕትም ብቻ መመልከት በቂ ነው፡፡ አይደለም ማኅበረ ቅዱሳን ለመኾኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን «ክርስቲያናዊ መንግሥት» ብቻ የሚል አስተሳሰብ ያለው የት ነው? በሀገሪቱ ሕግም ኾነ በሃይማኖታቸው መሪ ተቋም ውስጥ ከማይተዳደሩትና በሌላ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ ዓለም ዓቀፍ የእስልምና አክራሪ ቡድኖች ጋራ ማኅበረ ቅዱሳን ተደምሮ የሚፈረጅበት መስፈርትም ግልጽ አይደለም፡፡

ማኅበረ ቅዱሳንና አባላቱ የተገነቡበት ሥነ ልቡና ለአክራሪነት የተመቸ አይደለም

በርግጥ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም ከመስከረም 1 – 15 ቀን 2002 ዓ. ም. ለኅትመት በዋለችው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ላይ እንዳመለከቱት፣ «አክራሪ» ማለት የሃይማኖቱን ሕግ አክብሮ የሚኖር፣ ተግቶ የሚጾም፣ የሚጸልይ፣ በሃይማኖቱ ላይ ለሚነሡ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥና ታሪኩንና ቤተ ክርስቲያኑን የሚወድ፣ ለሃይማኖቱ የሚቀና፣ የማይዋሽ ወይም ወደ ከፍተኛ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት ራሱንም የሃይማኖት ወገኑን ሁሉ ለማድረስ የሚተጋ ከኾነ የማኅበራችንን አባላት ሊገልጽ ይችላል፡፡ ሰዎች ምናልባት በልማድ በዚህ ብያኔ ለመጥራት ፈልገው ከኾነ ችግር ላይኖረው ይችላል፤ ነገር ግን በዚህ ኹኔታ የሚመላለሱት ክርስቲያኖች «አክራሪ» እያሉ ከማጥላላት ይልቅ አጥባቂ፣ ዐቃቤ ሃይማኖት፣ ቀናዒ ቢባሉ የተሻለ እንደኾነ እሙን ነው፡፡

በሌላ በኩል ግን «አክራሪ» የሚለው ቃል በሰነዱ ላይ እንደተቀመጠው፣ «አብያተ ክርስቲ ያናትንና ገዳማትን ለፖሊቲካ ዓላማ ጥቅም ላይ ማዋል፣ ከተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶች ጋር በመተሳሰር ፀረ መንግሥት ቅስቀሳና አድማ ማስተባበር፣ በሃይማኖቶች መካከል የከረረ ጥላቻን በመዝራትና በማስተጋባት በሕዝብ ውስጥ የመተማመን፣ የመከባበርና የመቻቻል ዕሴት እንዲሸረሸር ሌት ተቀን መረባረብ» ከኾነ ግን ከማኅበራችን አቋምና ከአባሎቻችን ሥነ ልቡና እጅግ የራቀ አሉባልታ ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ፀረ መንግሥት ቅስቀሳና አድማ ሊያደርግ ይቅርና በጅማና ኢሉ አባቦራ አክራሪዎች በክርስቲያኖች ላይ ግድያ በፈጸሙበት ወቅት በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 14 ዓመት ቁጥር 21፣ ቅጽ 14 ቁጥር 121 ኅዳር ዕትም ላይ የወቅቱ መልእክት ያለው ዜናና ርእሰ አንቀጽ ጽፏል፡፡ ርእሰ አንቀጹ የመንግሥትንም ጥረት የሚያሳይና ለወደፊቱ መንግሥት፣ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ማድረግ ያለባቸውን የሚጠቁም ነበር፡፡

በዜናውም የመንግሥትን ጥረት «የሕዝቡን ሰላም በሚያደፈርሱ ኀይሎች ላይ መንግሥትና ኅብረተሰቡ የተጠናከረ ርምጃ እየወሰዱ ነው፡፡ . . . በጅማና ኢሉ አባቦራ አህጉረ ስብከት አንዳንድ ወረዳዎች በተከሰተው ግጭት ለችግሩ መንሥኤ ናቸው የተባሉትም ሕግ ፊት እየቀረቡ ነው» በማለት ነበር የገለጸው፡፡ እንዲህ የዘገበው ማኅበር ነው እንግዲህ ፀረ – ሕገ መንግሥት የተባለው፡፡ እንዲህ አድርጎ ከፈረጀ ማኅበረ ቅዱሳን በኀይል እስላሞችን ወይም ፕሮቴስታንቶችን ኦርቶዶክስ አድርጓል? መስጊድ አቃጥሎ እስላሞችን ወይም የማምለኪያ ቦታዎችን አቃጥሉ ፕሮቴስታንቶችን ገድሏል? ለሚሉ ጥያቄዎችም መልስ መስጠት ይገባ ነበር፡፡ አለበለዚያ የመንግሥት አካሂደዋለኹ የሚለው የፀረ አክራሪነት እንቅስቃሴ በመንግሥት መርሐ ግብር ተጠቅመው ስውር ዓላማቸውንና ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የተዛባ ፍረጃና የተሳሳተ አቻ ፈጠራ ላይ ለተሰማሩ አካላት መሣርያነት አለመጋለጡን በምን ማረጋገጥ ይቻላል?

ይኹንና ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀ ሕግና መተዳደሪያ ደንብ ያለው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል እንጂ ሌላ የእምነት ጽንፍ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታውቃቸው ጋዜጣ፣ መጽሔትና መካናተ ድሮች አሉት፤ ምን እንደሠራም በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን እንደተፈረጀው ሳይኾን መቻቻልን በተመለከተ ከማኅበሩ ሚዲያዎች ቀድሞ የዘገበ ነበር ለማለትም የሚቻል አይመስለንም፡፡

በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ጥቅምት ወር 1999 ዓ.ም ዕትም በጅማና በኢሉ አባቦራ የደረሰውን ጥቃት በዜናው ዘግቦ ነበር፡፡ ማኅበሩ ይህን ያደረገው ጥቃቱ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመ በደል ስለኾነ ብቻ አይደለም፡፡ አንድን ነገር እየሰሙ እንዳልሰሙና እንደሌለ ከመቁጠር ይልቅ ችግሩን በትክክል አሳውቆ ለመፍትሔው መሥራት ይገባል ብሎ ስለሚያምን ብቻ ነው፡፡

በተጠቀሰው የጋዜጣው ዕትም ባወጣው ርእሰ አንቀጽም የቆየው የመቻቻል ባህል ዳብሮ እንዲቀጥል የሚጠይቅ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው የመንግሥት አካላት ሊፈጽሙት ይገባል የሚላቸውን ተግባራት በማመልከት የማኅበሩን አቋም አንጸባርቋል፡፡ በቀጣዩ ወር ኅዳር 1999 ዓ.ም ዕትም ግን በመቻቻል እንዴት መኖር እንደሚገባ የሚያሳይ ሰፊ ሽፋን ያለው ሥራ ተሠርቷል፡፡ የመቻቻልን ምንነት፣ በኢትዮጵያ የነበረውን ታሪካዊ ቦታና አስፈላጊነት በመተንተን የሁሉም ቤተ እምነት ተከታዮች በዚሁ ሀገራዊና መንፈሳዊ ባህላችን ጸንተው እንዲኖሩ የሚያግባባ ነበር፡፡ ርእሰ አንቀጹ ደግሞ ከላይ የተገለጹትን አሳቦች በማጽናት ተግባብቶና ተከባብሮ መኖር የሚያስገኘውን ጥቅም ካካተተ በኊላ ለዚህ ባለድርሻ የኾኑ አካላት ሁሉ ድርሻቸውን እንዲወጡ የሚጋብዝ ነበር፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን «በሃይማኖቶች መካከል የከረረ ጥላቻን ሊዘራና ሊያስተጋባ» ይቅርና ሁሉም የእስልምና ተከታዮች አንድ ዓይነትና አክራሪዎች አለመኾናቸውን የሚያሳዩ ሥራዎችን የሠራ ማኅበረ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በስምዐ ጸድቅ ጋዜጣ ጥር 15 – 30 ቀን 2000 ዓ.ም በአርሲ የእስልምና ተከታዮች ለቤተ ክርስቲያን ግንባታ ያደረጉትን አስተዋፅኦ ከዘገበ በኋላ በርእሰ አንቀጹ ደግሞ የሁለቱን የእምነት ተከታዮች መረዳዳት አብነት በማድረግ ድርጊቱን አወድሷል፡፡

ከየካቲት 15 – 30 ቀን 2000 ዓ.ም ዕትም ደግሞ በወልቂጤ አካባቢ በቤተ ክርስቲያን ምረቃ ላይ ድንጋይ የወረወሩ አክራሪዎች ልጆቻቸውን ለሕግ አካላት አሳልፈው በመስጠት ለመቻቻሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉትን ሙስሊም ሽማግሌዎችን ድርጊት በአዎንታዊ ዘግቧል፤ ሥራቸውም ተወድሷል፡፡ ይህም መቻቻልን በተግባር ያሳየ ዘገባ ብቻ ሳይኾን የማኅበረ ቅዱሳን ትእምርተ መከባበር መኾኑንም ያሳየ ነበር፡፡

 

የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ቅዠት?

በርግጥ ማኅበሩ ወጣቱን በሃይማኖት አክራሪነት ይቀርጻልን የሚለውን ለመረዳት ሌላውን የማኅበሩን ሥራዎች ማየት የሚገባ ይመስለናል፡፡ ለአብነትም ማኅበረ ቅዱሳን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን የሚያስተምርባቸው ኻያ ያህል የመማርያ መጻሕፍት ታትመው አገልግሎት ላይ ከዋሉ ቆይተዋል፡፡ ትምህርቱ የሚሰጠው በይፋ በቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ሰው የኾነ ፍጡር ሁሉ ሊከታተለው የሚችለው ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ይፋዊ በኾነ መንገድ በሚሰጡበትና መጻሕፍቱን ሁሉ መመርመር በሚቻልበት ኹኔታ ያለምንም ማስረጃ «ወጣቶችን በሃይማኖት አክራሪነት ይቀርጻል» ማለት ስሕተት ነው፡፡

ይህን አገላለጽ የሚያይና የማኅበሩን ሥራ በርግጥ የሚያውቅ የዚህ አሳብ አፍላቂዎች በመንግሥት የፀረ አክራሪነት አጀንዳ አስታከው ማኅበረ ቅዱሳንና ቤተ ክርስቲያንን ለማሳጣት ወይም ለማጋጨት የተነሡና ሃይማኖታዊ መግፍኤ ያላቸው ኀይሎች ሊኾኑ አይችለምን? በርግጥ የማይኾኑበትስ ምክንያት ሊኖር ይችል ይኾን?

ቀደም ብለን እንደገለጽነው ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያን ትውልዱን በትምህርቷ ትዋጅ ዘንድ ሥርዐተ ትምህርት ቀርጾ ንጹሕ ቃለ እግዚአብሔር ብቻ የሚያስተምር ማኅበር ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን ይጠብቃል ተብሎ ይታማ ካልኾነ በቀር በአክራሪነት ሊወነጀል አይችልም፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን መዋቅራዊ ቁመና ለአክራሪነት ብቻ ሳይኾን ለፖሊቲካም የሚመች አይደለም፡፡ በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ መስከረም 1 – 15 ቀን 2002 ዓ.ም ዕትም ላይ የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም እንዳመለከቱት፣ ማኅበሩ ሃይማኖታዊ አገልግሎት ለመስጠት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር የተቋቋመ የአገልግሎት ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩም እንደ ተቋም የሚሰጠው አገልግሎት ሃይማኖታዊ ነው፡፡ መቼም ቢኾን ለየትኛውም ዐይነት የፖለቲካ አደረጃጀት ለማገዝ/ለመሥራት ተቋማዊ ፍላጎት የለውም፡፡

በዚህ አጋጣሚ ማኅበሩ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የገለጸውን አቋሙንም አስታውሶ ማለፍ የሚገባ ይመስላል፡፡ በአንቀጽ 5 ላይ «ማኅበሩ በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት አይኖረውም» በማለት ማኅበሩ ፖለቲካ ላይ ጣልቃ የማይገባ መኾኑን ይገልጻል፡፡ የዚህን አንቀጽ ይዘት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል በማኅበሩ ያሉ የተወሰኑ አባላት በሓላፊነት ላይ እያሉ የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ በ1998 ዓ.ም የሥራ አመራር ጉባኤው ወስኗል፡፡

በውሳኔውም መሠረት፡- የሥራ አመራር ጉባኤ አባላት፣ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት፣ የኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ክፍል አባላት፣ የኤዲቶሪያል ቦርድ አባላት፣ መደበኛ መምህራን፣ የማኅበሩ ጋዜጠኞች፣ የማእከላት ሰብሳቢዎች በሓላፊነት እያሉ የማንኛውም የፖለቲካ ­ርቲ አባል መኾን አይችሉም፡፡ ስለኾነም ማኅበሩ እንደ ተቋም የትኛውንም የፖለቲካ አስተሳሰብ በመደገፍ ወይም በመቃወም ከ­ርቲዎች ጋር ግንኙነት ስለማይኖረው ለማንም ስጋት ወይም ዕድል ሊሆን የሚችል ተቋማዊ ምቹነት የለውም፡፡mahibere-kidusan-statement

ይህ ባይኾን ኖሮ ከመላዋ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና የተለያዩ ማኅበራዊ ዳራዎች የተሰበሰቡ አባላቱ በየትኛው የፖለቲካ አቋም ሊስማሙና ቤተ ክርስቲያንን ሊያገለግሉ ይችላሉ? የማኅበሩ አቋም ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖረው የተወሰነው ግን ለዚህ ሲባል ብቻ አይደለም፡፡ በአንድ የፖለቲካ ፓ­ርቲ ውስጥ በርእዮተ ዓለም የተሰባሰቡ የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች ይኖራሉ/ፓ­ርቲው አክራሪ ሃይማኖታዊ ፓ­ርቲ እስካልኾነ ድረስ/፤ እንደዚሁ ሁሉ የተለያየ የፖሊቲካ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የአንድ ቤተ እምነት ተከታዮች ይኾናሉ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ሃይማ ኖታዊ ዕሴታቸውንና ለቤተ ክርስቲያናችን ማበርከት አለብን የሚሏቸው ዓላማዎች የሚያገናኟቸው ሰዎች የተሰበሰቡበት ማኅበር ነው፡፡ ስለዚህ ዓላማው አንድና አንድ ነው – ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ብቻ፡፡ ስለኾነም እንደ ማኅበር በየትኛውም የፖሊቲካ ርእዮተ ዓለም ላይ ጣልቃ ገብነት የለውም፤ ወደፊትም አይኖረውም፡፡

የብዥታው ምንጭ ምንነት

እውነታው ከላይ የተመለከትነው ከኾነ ማኅበረ ቅዱሳን «አክራሪ» ያሰኘው የብዥታው ምንጭና ምንነት ምን ይመስላል? የሚለው ሌላው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ የመጀመሪያው፣ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን የተሳሳተ መረጃ ነው፡፡ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ንጽሕት ርትዕት የኾነችውን እምነትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ህልውና ለማጥፋት በመፈታተን ለዘመናት ሌት ተቀን ሳያቋርጡ እንደሚጥሩት ሁሉ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጅ የኾነው የማኅበረ ቅዱሳንን ቅን መንፈሳዊ አገልግሎትም እንዲኖር አይፈልጉም፡፡ በተለይም በክርስትና ስም እንቀሳቀሳለን የሚሉ የተለያዩ የእምነት ድርጅቶችና የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ አራማጆች ሁሉ፣ ከውጭም ኾነ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉያ ውስጥ ኾነው የሚያደርሱትን ጥቃትና ቡርቦራ በመከላከል፣ ለቤተ ክርስቲያን አባቶችና ለምእምናን በማሳወቅ የሚያደርገውን ቀና ጥረት በሚገባ ያውቁታል፡፡

በጌታችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሠረት ላይ ጸንታ በእርሱ ጥበቃ የምትኖረውን ቤተ ክርስቲያን በመፈታተን እኩይ ዓላማቸውን በፈለጉት መጠን እንደልባቸው ለማሳካት አለመቻላቸውን ተረድተውታል፡፡ ለእኵይ ተግባራቸው እንቅፋት የኾነውን ማኅበር ንጹሕ መንፈሳዊ አገልግሎት ለማስቆም ባገኙት አጋጣሚና መድረክ ሁሉ የተሳሳቱና የተፈበረኩ መረጃዎችን ይሰጣሉ፡፡ የፍረጃው ምንጭ ይኸው የተሳሳተና የተፈበረከ መረጃ ነው፡፡

የማኅበረ ቅዱሳንን አገልግሎት ለማስተጓጎል የሚጣደፉት እነዚህ የኑፋቄና የጥፋት ኀይሎች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅሮች ውስጥ ሓላፊነት ይዘው ቤተ ክርስቲያንን ለሚያጠፉ አካላት የማይታይ ስውር እጅ ኾነው ለመሥራት እየሞከሩ ያሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ማኅበረ ቅዱሳን የተለየ አጀንዳ ያለው ይመስል ስጋት ኾኖ እንዲታይ ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልወጡት ዳገትና ያልወረዱት ቁልቁለት የለም፡፡

የራሳቸው ጥቅምና ክብር እንጂ የቤተ ክርስቲያን ንጹሕ ዓላማ የማይታያቸው እነዚህ በእሳት የሚጫወቱ ግለሰቦችና ቡድኖች ሲፈልጉ በጥርጣሬ፣ በመመሪያና ደንብ፣ ሲያሻቸው ደግሞ ስም በማጥፋትና በአባላቱ መካከል መለያየት ለመፍጠር በመሞከር. . . ወዘተ ማኅበረ ቅዱሳንን መቅበር፣ በመቃብሩም ላይ መቆም፤ ከዚያም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ያደረጉት እንቅስቃሴ ሁሉ በእነርሱው ቋንቋ «በማኅበሯ» ሲከሽፍባቸው መንግሥት ታላቅ ሓላፊነት ያለበት አካል እንደ መኾኑ መጠን የሚመች ቦታ ይዘው የራሳቸውን ውስጣዊ ፍላጎት በመንግሥት መርሐ ግብር አሳዝለው ማኅበሩን ያስመታልናል የሚሉትን የሐሰት መረጃ መፈብረክ ተያይዘውታል፡፡

በጥቅሉ የመናፍቃኑንና ቤተ ክርስቲያንን እናድሳለን ብለው የተነሡት የመናፍቃኑ ተላላኪ ቡድኖች ሤራና የአክራሪ እስልምናን እንቅስቃሴ በመረጃ አስደግፎ በማጋለጡ፣ ከክፉ ትምህርታቸው መመለስ ያልፈለጉ የተሐድሶ ኑፋቄ ቡድን አባላት ከቤተ ክርስቲያን ተወግዘው እንዲወጡ ስለተወሰነባቸውና ሌሎችንም የቤተ ክርስቲያን ችግሮች እየተከታተለ ለዕድገቷና ብልጽግናዋ በመሥራቱ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ወዳጆች ማፍራት መቻሉ የእግር እሳት የኾነባቸው አካላት የፍረጃ ውጤት ነው የማኅበሩ «አክራሪ» መባል፡፡

ሁለተኛው፣ የተሳሳተ አቻ ፈጠራ የወለደው ብዥታ ነው፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማትና ሓላፊዎች አንድን ችግር ለመፍታት ሲሉ ሚዛን የጠበቁና የማያደሉ የሚባሉ እየመሰላቸው ማኅበረ ቅዱሳንን ለወሃቢያ የተሳሳተ አቻ ፈጠራ አክራሪ ማለታቸው ሌላው የብዥታው ምንጭ  ነው፤ ነገር ግን ይህ ፈጽሞ አግባብ አይደለም፡፡ ከዚህም ውጭ የተሰጣቸውን መንግሥታዊ ሓላፊነት ዘንግተው በራሳቸው የሃይማኖት አመለካከት ምክንያት የማኅበሩን መኖር የማይፈልጉ አካላት የሰጡት መረጃ ሊኾን እንደሚችል መጠርጠር፣ የመረጃውን ፍሰት/አካሔድ/ መመርመርና ተገቢውን እርምት መውሰድ አለመቻልም ለብዥታው መነሻ ነው፡፡

ሦስተኛውና የመጨረሻው የብዥታው ምንጭ፣ ማኅበረ ቅዱሳን «እውነት ነጻ ያወጣችኊል» በሚለው የወንጌል ቃል መሠረት አሉባልታውን ሁሉ እየተከተለ በወቅቱ ምላሽና አጸፋ አለመስጠቱ ነው፡፡ በጊዜ ሒደት ግን የመረጃውን ስሕተት ከማኅበሩ እውነተኛ ማንነት ጋራ አለመግለጻችን ራሳችንን ለከሳሾቻችን የፈጠራና የተሳሳተ መረጃ ረዳት አድርጎ ሊያስቆጥረን ይችል ይኾናል፡፡ የኾነው ኾኖ ማኅበሩ እንደ እምነት የአገልግሎት ተቋምነቱ ላልሠራው ሥራ አይጨነቅም፤ ጊዜ ይወስዳል እንጂ እውነቱን ደግሞ ማንም አይደብቀውም፡፡

ጌታ በወንጌል እንደተናገረው «የማይገለጥ የተከደነ፣ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለምና» /ማቴ. 10፥26/ የሁሉንም ስውር ተንኮል እግዚአብሔር በጊዜው ጊዜ ይገልጠዋል፡፡ ያን ጊዜ ማኅበሩ ማን እንደኾነም በእውነት ይታያል፡፡ በዚያን ጊዜ ሁሉም የዘራውን ያጭዳል፡፡ ጠብ እየዘራ ያለ አካል ቢኖር እርሱ የጠብ ውጤት የኾነውን መከራ ከዘራው ዘር ማጨዱ አይቀርም፡፡

ከዚህ በኋላስ... 

መንግሥት በየትኛውም የእምነት ተቋማት አሉ የሚላቸውን ችግሮች ማንሣቱ ወይም ተቋማቱ ራሳቸው እንዲፈቱ እገዛ መስጠቱ የሚያስመሰግነው ተግባር ነው፤ ነገር ግን የሚያሰራጫቸው መረጃዎች ይህን ተግባሩን ጥያቄ ውስጥ እንዳይከቱት መጠንቀቅ ብቻ ሳይኾን ማስተካከያ ሊሰጥበትም ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ መፍትሔው መፍትሔ መኾኑ ቀርቶ ለችግር ፈጣሪዎቹ ከለላ ሰጭ እንዳይኾን ያሰጋል፡፡

ሃይማኖታዊ ጉዳይ በተፈጥሮው ውስብስብና በእጅጉ ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው፡፡ በኻያኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛው አጋማሽ ላይ በሕንድና ቀደም ብሎም በግሪክ የመንግሥትን ኃይል ተጠቅመው በእውነኞቹ አማኞች ላይ ታላቅ ጥፋት ካደረሱት ውስጥ የአንዳንዶቹን አካላት ታሪክ ማየትም ለእኛ ምሳሌ ሊኾነን ይችላል፡፡ የተሰጣቸውን ሓላፊነት በመጠቀምና የተሳሳተ መረጃ በማቀበል የመንግሥትን አግባብነት ያለው የፀረ አክራሪነት እንቅስቃሴ ከትክክለኛው አቅጣጫ ሊያስቱ የሚችሉ አካላት መሣሪያ እንዳያደርጉት ስጋታችን ታላቅ ነው፡፡ ሐሰት ተደጋግሞ በመነገሩ እውነት ቢመስልም በፍጹምና መቼም እውነት ሊኾን አይችልም፡፡

በሌላ በኩል፣ ሚዛን ለመጠበቅ በሚል ስሜት ሁሉንም አንድ ዓይነት ጥፋት እንዳጠፉ አድርጎ መመልከትና መግለጽም መቆም ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ለተለያየ ዓላማ ከሚያወጣቸው ይፋዊ ሰነዶች ጥናትን መሠረት ያደረጉ መረጃዎች ብቻ ይጠበቃሉ፡፡ ለምሳሌ፣ በሃይማኖታዊ ጉዳይ ላይ የተጻፉ ጸሑፎችን በሙሉ ሰብስቦ አጥንቶና ገምግሞ ማውጣት ቢቻል ሕዝቡንም በአግባቡ ለማስረዳት ይጠቅማል፡፡ ማን መጀመሪያ ምን ብሎ በሌላው እምነት ላይ ጻፈ? የትኞቹ ምላሾች ናቸው? የትኞቹስ የትንኮሳ ጽሑፎች ናቸው? ሌላው ቀርቶ ሃይማኖትን ለማሳመን፣ ሌላውን ለማስረዳት አልያም ለማጣጣል ብቻ የተደረጉት ላይ ቢጠና እንደ ዘይትና ውኃ ተለይተው ከሩቅ የሚታዩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሁሉንም በአንድነት በመፈረጅና በሕግ የተቋቋመውን ካልተቋቋመው እየደባለቁ በመናገር የተፈጸመን ድርጊት ሁሉ በአንድ ለይ በመጫንና በመለጠፍ ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ይታወቃል፡፡

ስለዚህ በቂ ማስተካከያዎችና እውነተኛ ገጽታን የሚገልጹ ሥራዎች ለዛሬ ባይደርሱ ለነገ ይጠበቃሉ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም የሃይማኖት አክራሪነትን መቃወም ብቻ ሳይኾን በጽኑ ያወግዛል፤ ማኅበረ ቅዱሳን  የሃይማኖት አክራሪነት ሳይኾን የሃይማኖት አጥባቂነት ትእምርት ነውና!!

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር

*ዲ/ን ታደሰ ወርቁ፣ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የቀድሞው ምክትል ዋና አዘጋጅ ኾኖ ሠርቷል፡፡

Advertisements

35 thoughts on “ማኅበረ ቅዱሳን – የሃይማኖት አጥባቂነት ወይስ የአክራሪነት ትእምርት?

 1. Fikru Sinshaw October 9, 2013 at 2:47 pm Reply

  ለመቸም መልስ ነዉ

 2. bint halid October 9, 2013 at 3:37 pm Reply

  ..ስለዚህ የአክራሪ እስልምና ቡድን መኖር የእስልምና ተከታዮችን በሙሉ «አክራሪ» አስብሎ ሊያስፈርጃቸው አይችልም፤ ለሌላው ቤተ እምነትም እንዲሁ፡፡ betam yasazenal xnde lemnete ekorekoralhu kemil sew endih begedemdame yelelawn emnet menkat aytebekm

 3. Asmelash Gebrehiwot October 9, 2013 at 5:37 pm Reply

  እናመግናለን! ማኅበረ ቅዱሳን የተለያዩ ስሞች ቢሰጡትም ዓላማው ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ነውና እውነቱን እግዚአብሔር እስኪገልጠው ምንም ሳይሸበር አገልግሎቱን ይቀጥላል፡፡

 4. Anonymous October 9, 2013 at 5:49 pm Reply

  ቃለ ህይወት ያሰማልን፡፡ እውነቱን እንዲህ አብራርቶ ማስቀመጥ ተገቢ ነው፡፡

 5. Anonymous October 9, 2013 at 8:38 pm Reply

  በርግጥ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም ከመስከረም 1 – 15 ቀን 2002 ዓ. ም. ለኅትመት በዋለችው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ላይ እንዳመለከቱት፣ «አክራሪ» ማለት የሃይማኖቱን ሕግ አክብሮ የሚኖር፣ ተግቶ የሚጾም፣ የሚጸልይ፣ በሃይማኖቱ ላይ ለሚነሡ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥና ታሪኩንና ቤተ ክርስቲያኑን የሚወድ፣ ለሃይማኖቱ የሚቀና፣ የማይዋሽ ወይም ወደ ከፍተኛ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት ራሱንም የሃይማኖት ወገኑን ሁሉ ለማድረስ የሚተጋ ከኾነ የማኅበራችንን አባላት ሊገልጽ ይችላል፡፡ ሰዎች ምናልባት በልማድ በዚህ ብያኔ ለመጥራት ፈልገው ከኾነ ችግር ላይኖረው ይችላል፤ ነገር ግን በዚህ ኹኔታ የሚመላለሱት ክርስቲያኖች «አክራሪ» እያሉ ከማጥላላት ይልቅ አጥባቂ፣ ዐቃቤ ሃይማኖት፣ ቀናዒ ቢባሉ የተሻለ እንደኾነ እሙን ነው፡፡

 6. Anonymous October 9, 2013 at 11:50 pm Reply

  mengst erasu betekrstiyanua endtnor ayfelgm slezih yetnkarewa meseret yehonutn menad alamaw now.bedenb gebtonal.

 7. Anonymous October 10, 2013 at 1:55 am Reply

  Well done Deacon Tadesse Worku!!!! Keep up with the good job. Tewahedo will shine forever!!!!

 8. daniel October 10, 2013 at 4:08 am Reply

  Great response!

  All the government accusation came from T-protestant website. These websites have been falsely accusing MK years ago, now they are using the government media for their hidden mission.

  Watch a YouTube video ” false attack on Ethiopian Orthodox Church by Protestants +

 9. ermyas sweet October 10, 2013 at 7:36 am Reply

  ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ እውነቱን እውነት ሓሰቱን ደግሞ ሓሰት፡በሉ፡ብሏል ማህበረ፡ቅዱሳን፡አዎ፡አክራሪ፡ነው፡አዎ፡ጽንፈኛ፡ነው፡እስቲ፡ሚዛናዊ፡በሆነ፡አስተሳሰብ፡ እንዳኝ በስራው፡ እንከን፡ የሌለበት፡ ልኡል፡ እግዚአብሔር፡ ብቻ፡ ነው፡ የማህበሩንም፡ የክፋት፡ ሴራ፡ ተመልከቱት፡ ሁልጊዜ፡ በጎ፡ጎኑን፡ ብቻ፡ መናገር፡ የበለጠ፡ ማህበሩ፡፡ እንዲጠላ፡አድርጎታል፡፡

  አክራሪነት እንደተገለጸው፡ ብቻ፡ ትክክል፡ ብሎ፡ የሚያስባ፡የሌላውን፡ነጻነት፡ የሚረግጥ የሚል፡ ትርጉም፡ እንዳለው፡ በመረጃ፡ ቀርቧል፡፡ ታዲያ፡ ማህበረ፡ ቅዱሳን፡ ስንቱን፡ የቤተ፡ክርስቲያን፡ አገልጋይ፡ ነው፡ ያለስሙ፡ ስም፡ እየሰጠ፡ ከቤተ ክርስቲያን፡ ያሳደደው፤ ያንገላታው፤ ደሙንስ፡ ያፈሰሰው፡ እግዚአብሔር፡ እኮ፡ያያል፡ ሰው፡ ሰውን፡ ሊዋሽ፡ ይችላል፡ እግዚአብሔር፡ ግን፡እግዚአብሔር፡ ነው፡ አሁን፡ ያንን፡ ሁሉ፡ አተታ፡ የሰጠው፡ ታደሰ፡ ወርቁ፡ ራሱ፡ ማን፡ ነው፡፡ ከአራት፡ ኪሎ፡የቱሪስት፡ግሩፕ፡ ጋርና፡ የጥምቀት፡ ተመላሽ፡ ወጣቶች፡ በሚል፡ የተሰበሰቡትን፡ ልጆች፡ ለአመጻ፡ እያሰባሰበ፡ የቤተ ክርስቲያንን፡ አገልጋዮች፡ የሚያሳድድና፡ ስም፡ የሚያጠፋ አይደለም፡እንዴ፡ ዛሬ፡ጻድቅ፡መስሎ፡ ለመታየት፡ ቢሞክርም፡፡
  የእግዚአብሔር፡የ፡ፍርድ፡ጽዋ፡ስለሞላ፡ጌታ፡ፍርዱን፡ይቀጥላል፡ምክንያቱም፡በማህበረ፡ቅዱሳን፡የተገፉ፡የተሰደዱ፡ስማቸው፡የጠፋ፡የተደበደቡ ሁሉ፡ እንደ፡ ራሔል፡ እንባቸውን፡ ወደ ሰማይ፡ ረጭተውባቹሃልና ነው።

  ማህበረ፡ቅዱሳን እኮ፡ እንደ፡ እኔ፡ ያልዘመሩ፡ ዘማርያን፡ ዘማርያን፡ አይደሉም፡ እንደ፡ እኔ፡ አስተሳሰብ፡ ያልሔዱ፡ ሰባክያነ፡ ወንጌል፡ መናፍቃን፡ ተሃድሶ፡ ናቸው፡ እያለ፡ ቤተ ክርስቲያን፡ያሳደገቻቸውንና አስተምራ ፡ለአገልግሎት፡ ያበቃቻቸውን፡ ደግሞ፡ በተገለጠ፡ ጸጋ እግዚአብሔር የቀባቸውን፡አገልጋዮች፡ስም፡የሚያጠፋ የንግድ፡ድርጅት፡ነው፡፡ ምክንያቱም፡ የኣገልግሎት፡ መድረኮችን፡ በእርሱ፡ አጫፋሪዋች፡ ሞኖፖላይዝ፡ አድርጎ ህዝበ፡ ክርስቲያኑን፡ መፍቀሬ፡ ክርስቶስ፡ ሳይሆን፡ መፍቀሬ፡ ማህበር፡ አድርጎ፡ የኣባልነት፡ፎርም፡ በማስሞላት፡ በወርሃዊ፡ክፍያ፡ ካዝናውን፡ ማጨናነቅ፡ የሚፈልግ፡ አስመሳይ፡ ማህበር፡ነው፡ ይህ፡ ካልሆነ፡ ደግሞ፡ የገጠሪቱን፡ ቤተ ክርሲያን፡ እንርዳ፡ የአብነት፡ ትምህርት፡ ቤቶችን፡ እናስፋፋ፡ በሚል፡ ማግባቢያ፡ ፕሮጀክት፡ እየነደፈ፡ በአካፋ፡ እየሰበሰበ፡ እንዳይነቃበት፡ በማንኪያ፡ እየሰጠ ህልውናውን፡ ዘለአለማዊ፡ ለማድረግ፡ የተነሳ፡የቢዝነስ፡ሴንተር፡ነው፡፡

  የሚያሳዝነው፡ በየዋህነትና፡ በቅንነት፡ የማህበረ፡ ቅዱሳን፡አባል፡ ወይም፡ደጋፊ፡በመሆናቸው፡ቤተክርስቲያንን፡እንደመርዳት፡ቆጥረው፡ገንዘባቸውን፤ጉልበታቸውን፤እውቀታቸውን፤ጊዜያቸውን፡የሚገፈገፉ፡የዋህ፡ ክርስቲያኖች፡ እንዳሉ፡ይታወቃል፡ አሁን፡ ግን፡ በእውነት፡ እግዚአብሔር፡ ለየዋሆቹም፡ አይናቸውን፡ የሚገልጥበት፡ በመሰሪዎችም፡ ላይ፡ ፍርዱን፡ የሚገልጽበት፡ ለተገፉትም፡ እንባቸውን ፡የሚያብስበት፡ የፍርድ፡ ፡ላይ፡ ደርሰናልና፡ መድሓኔ፡ ዓለም፡ ክብር፡ ይግባው።

  • Dawit October 10, 2013 at 1:53 pm Reply

   When you open your big mouth put references. Its such talk we sick of it!

  • Kachissa October 11, 2013 at 2:51 pm Reply

   Aya ERMIYAS,

   Yebeg lemd yelebese tekula honubensa! Degmo beyekalatu mekakel neteb bemaskemet yeabatochen atsatsaf bemasmesel betezewawari rasewon keabew endeandu lemasmesel felegu.

   Maheberu erso endemilut ene becha lesbek, lelochacheu ewnetegna yebetekrstiyan lijoch bethonum kemedrek lay zor belu belo kehone betechebach magalet new. Ewnetegna masreja kakerebu kuter 1 (number one) tebabariwo ehonalehu. “Manafekan , tehadeso nachew eyale” alu? Wanaw gudayo yehe yemeslegnal. Yetehadesoawyan megalet yangebegebot yemeslal. Ewnet yebetekrstiyan lej newot weynes keneziyaw yediyablos melektegnoch ekuyan menafikan? Selfewo kewedet new? Lenegeru kewedet endehonu megemet aykebdem. Mefcherchero enesun lemekelakel mehonun lemegenzeb bezu memeramer ayteyekem.

   Come to your senses man! Your gods (the missionaries) in the Western world fed into your poor soul the poison of hatred towards your own history and values including religion and culture in the name of Christianity. The funny thing is those same people who pretended to have preached to you our Lord Christ have long changed their churches into night clubs, museums, art galleries…. Remember they sent their satanic spies as missionaries to Ethiopia to “evangelize” the already EVANGELIZED. Their main MISSION however was to sow seeds of division and hatred among us the sons and daughters of Ethiopia so that we will fall prey to their long term agenda of breaking our pride and make us ready for them to use us as they wish. Please use your intellect, come to your heart and rejoin with the original, apostolic, absolutely true church, that is the ETHIOPIAN ORTHODOX CHURCH. This church belonged to your fathers and mothers and yourself although you betray it now. Don’t ever continue collaborating with the enemies of Ethiopia who always work hard to destroy her history, including her ancient true church.

  • Anonymous October 11, 2013 at 4:38 pm Reply

   totally wrong !!!

  • Anonymous October 11, 2013 at 5:51 pm Reply

   Yeqena bizu yaweral

 10. Anonymous October 10, 2013 at 8:30 am Reply

  ጌታ በወንጌል እንደተናገረው «የማይገለጥ የተከደነ፣ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለምና» /ማቴ. 10፥26/ የሁሉንም ስውር ተንኮል እግዚአብሔር በጊዜው ጊዜ ይገልጠዋል፡፡ ያን ጊዜ ማኅበሩ ማን እንደኾነም በእውነት ይታያል፡፡ በዚያን ጊዜ ሁሉም የዘራውን ያጭዳል፡፡ ጠብ እየዘራ ያለ አካል ቢኖር እርሱ የጠብ ውጤት የኾነውን መከራ ከዘራው ዘር ማጨዱ አይቀርም፡፡
  የማኅበረ ቅዱሳንን አገልግሎት ለማስተጓጎል የሚጣደፉት እነዚህ የኑፋቄና የጥፋት ኀይሎች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅሮች ውስጥ ሓላፊነት ይዘው ቤተ ክርስቲያንን ለሚያጠፉ አካላት የማይታይ ስውር እጅ ኾነው ለመሥራት እየሞከሩ ያሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ማኅበረ ቅዱሳን የተለየ አጀንዳ ያለው ይመስል ስጋት ኾኖ እንዲታይ ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልወጡት ዳገትና ያልወረዱት ቁልቁለት የለም፡፡

 11. Yeshiwondim Girmay October 10, 2013 at 8:42 am Reply

  ይህ መንግስት በተለያዩ መድረኮች ቤተ ክርስቲያንን መንካቱ የተለመደ ነው፡፡አሁንም ሌላ…… የሚገርም ነው፡እውነቱን ነው፤ስንት ክርስቲያኖች እየሞቱ፤ቤተ ክርስቲያን እየተቃጠለች መቻቻልን ለመስበክ ሁሉንም ችለን ዝም ስላልን? በእውነቱ ይህ በስልጣን ላይ ያሉ የሌላ እምነት ተከታዮች የሚሰሩት ሴራ ስለሆነ ችግሩን ነቅተን ልንጠብቀው ይገባል፡፡ማህበረ ቅዱሳን ማለት የቤተ ክርስቲያናችን ልጅ፤ጠበቃ መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል፡፡

 12. annonymus October 10, 2013 at 9:35 am Reply

  ማህበሩ ለአለፉት በርካታ ዓመታት ቤተክርስቲያኗን በተለያየ መልኩ ሲያግዝና በተለይም ቁልፍ የመረጃ ምንጭ በመሆን ሲያገለግል መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ግድፈቶች እየተነበቡበት በሕዝብም ዘንድ ጥራጣሬን እያሳደረ መጥቷል፡፡ ማህበሩ ከአለው የአለውን ተቀባይነት ወደ ትምክህት እነዳለወጠውም ስጋት አለ፡፡ ማህበሩ አጠፋህ የሚለውን የመቀበል አቅሙ እየደከመ ማንም አያርመኝም አይነት አዝማሚያም ይታይበታል፡፡ በአንጻሩ ግን ብዙ ግድፈቶችን ሲሰራ ይታያል፡፡ ቤተክርስቲያኗን ከጎደፈ እምነት አራማጆች ለመጠበቅ በሚያደርገው ጥረትም የተሳሳቱ ግለሰቦችን ለማረም ከሚጋብዙ ይልቅ የሚገፉ አሰራሮችን እንደሚሰራ ማህበሩ ይወቀሳል፡፡ አንዳንዴም ራሱ ተሳስቶ ምንም ስህተት የሌለባቸውን እንደገፋ ጭምር፡፡ በዚህም የተነሳ ከዚህስ ቢቀር ሲሉ እምነታቸውን ሳይቀር ያጡ ወገኖች እነዳሉ ይነገራል፡፡ ይህ ደግሞ ከስህተቶች ሁሉ ስህተት ነው፡፡ የባስ በእምነቱ ባለቸው ጥንካሬ ከልዑል አምላክ የተሰጣቸውን አባቶች ፀጋ ሲያቃልልና በተቃራኒው ማህበሩ ይደግፉኛል የሚላቸውን እምነትን ሳይሆን ዘመናውነትን ለሚኖሩ አባት ተብዬዎች ሲያካብድ ይታያል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በዘመናችን የልዑል አማላክን ኃይልና የክፉ መናፍስትን ሴራ ገሃድ ያወጡትን መ/ር ግርማ ወንድሙ በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አግባብ ባልሆነ መልኩ ሲታገዱ ማህበሩ ቀዳሚ ደጋፊ ሆኖ የምስራች ያህል ነበር ክስተቱን የዘገበው፡፡ በዚህ ምክነያት ብዙ የእምነቱ ተከታይ ደጋፊዎቹን እንዳጣ ይገባኛል፡፡ ለማህበሩ መንፈሳዊነት ሆያ ሆዬ ባህልን ከእምነት ያለየ አይነት አምልኮ እንጂ እውነተኛው አምልኮ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው አጠያያቂ ሆኗል፡፡
  ሌላው ማህበሩ ራሱ የሚደገፋቸውን የሀይማኖት አባቶች ይክባል ሌሎችን ደግሞ በተለያዩ የመረጃ ምንጮች ብዙም ጊዜ በአልታረሙ ቃላት ጭምር እየኮነነ በቤተክርስቲያኗ ሰላም እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ በኋላ በአንዳንድ የማህበሩ ናቸው ተብለው በሚታሙ ደህረገጾች የሚወጡ ጉዳዮች ፍጹም የቤተክርስቲያኗን ስነምግባር ያልተከተሉ መሆናቸው በግልጽ ይታያል፡፡ ሲጀምር የቤተክርስቲያኗን የውስጥ ጉዳይ (ችግር ቢኖር እንኳን) ሚዲያ ስላመቸ ብቻ ለሕዝብ ማውጣት ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ ሲቀጥል ግን አብዛኛዎቹ የማህበሩ ናቸው ተብሎ በሚገመቱት ድረ-ገጾች የሚወጡ መረጃዎች በጣም የወረዱና ገለልተኛ ያልሆኑ ናቸው፡፡ እንዲህ ያለው አዘጋገብ በአለማውያኑ ዘጋቢዎች አይታይም፡፡ አባቶችን በዝለፍ፣ ጉዳዮችን ወደ ራስ ብቻ ጽንፍ እንዲታዩ መሞከር፣ ሌሎችም ችግሮች በግልጽ ይነበባሉ፡፡ ከዚህ አንጻር በሌሎች የፖለቲካ ጉዳዮች ሳይቀር ላለመተላለፉ ዋስትና ሊኖር አይችልም፡፡
  በአጠቃላይ ብዙ አስተያየት ሰጭዎች እንደገለጻችሁት የማህበሩ መነካት እናንተ እንደምታስቡት የቤተክርስቲያኗ ወይም የአማኞቿ መነካት ሳይሆን አሁን የራሱና የደጋፊዎቹ መነካት ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ ሕዝብ ማህበሩን ድሮ እንደሚያምነው አሁን እያመነው ለመሆኑ እጠራጠራለሁ፡፡ ጥንቃቄ ያለበት አካሂድ ሊጓዝ ይገባዋል እላለሁ፡፡ ማህበሩ በቤተክርስቲያኗ በሚፈጠሩ ችግሮች መፍትህ እንጂ የችግር አባባሽ ሆኖ አለመግባባቶች እንዲጎሉ ማድረግ የለበትም፡፡ ራሱንም ከሲኖዶስ ሳይቀር አስቀድሞ መገኘት የለበትም፡፡ የቤትክርስቲያን የተባሉ ሚዲያዎችም ስነምግባርን የተላበሱ ዘገባዎችን እንዲያቀርቡ፣ በሚስጢር መያዝ የሚገባቸውን ጉዳየዮች በሚስጢር እንዲይዙ አስፈላጊ ሲሆን አግባብ ባለው ሁኔታ በብልህ አቀራረብ እንዲያቀርቡ ማድረግ ቢችል ጥሩ ነው፡

 13. mulushewa October 10, 2013 at 10:12 am Reply

  መልካም!!መልካም!!ይበል!!ይበል!!
  አሁንም ከማህበሩ መልስ የሚሹ በጥብቀቱ ውስጥ ያሉ ጥያቄዎች
  1. ዋናው ማእከል በኢት.ሲኖዶስ ስር እያለ የአሜሪካ ቅርንጫፉ ገለልተኛ በሚል ተቀጽላ እስከመቼ???
  2. ዋናው ማእከል በውጭ ማእከላቱ እንቅስቃሴ ያለው ሀላፊነት እስከምን ድረስ???
  3. በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የየእለት አስተዳደር ውሰጥ (የሚስጥር አገልግሎት ሳይቀር) በአባላት እየታዩ ያሉ ጣልቃ ገብነቶችስ???
  4. ማህበረ ካህናት በማህበሩ ላይ ያላቸው አመኔታስ ???
  5. ማህበሩ የአስተዳደር ችግር አለ እያለ በአፍና በመጣፍ እንደሩቅ ተመልካች ከማማት ባለፈ ችግሩን ለመቅረፍና ካህናቱን ለመተካት በሚመስል መልኩ ሳይሆን በቅንነት ድጋፍ ለመስጠት በሚመስል መልኩ ተንቀሳቅሱዋለን???
  6. ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ማህበሩ ከሲኖዶስ ቀድሞ የሚያሳልፈው ቡድን ጠቀስ ገፊ ውግዘትስ ???(በገሀድ አዳራሽ ውለው ለ11 ሰዓት ጉባኤ ካልመጣን የሚሉትን እንደነ ፅጌ አይነቶቹ ደረቆችን እናንተም ባትሉ ሰፊው ምእመን ይታገላቸዋል.እነሱ በሃይማኖት ወደሚመስሉዋቸው ሂደው ባይሆን መቻቻል በሚለው ቁዋንቁዋ ብንግባባ ይሻላል. አረጀች የሚሉዋትን ቅድስት የኢኦተቤክ እናድሳለን ብለው ከመድከም እሱዋን ሁሌም ሙሽራ ናት ለምንለው ትተውልን ለምን አዲስ እንደማይሰሩ አይገባኝም)
  7. ለቡድን መጫወት የሚመስል አካሄድስ???
  8. አግዚአብሄር ይመስገን አባላት እየበዙ ነው ግን የአባላት የስነምግባር ደንብ አያስፈልግም???
  9. ከጊዜ ወዲህ እየተስፋፉ ስለመጡት ቤ/ክህነት ተኮር ብሎጎች የማህበሩ አቁዋም ምንድን ነው???

  የግቢ ጉባኤን ይጠብቅልን!!!!

 14. ms October 10, 2013 at 11:30 am Reply

  ባለ ስልጣናትን ከሃይማኖታዊ ዳራቸው ተነስቶ መክሰስ ኣሁንም የስህተት ስህተት ነው!
  ኣንድ ነገር መታወቅ ያለበት ማኅበሩ ቤተ ክርስትያኒቱ የፖሎቲካ መድረክ እንድትሆን እያደረጋት መሆኑ ነው! ንጹ የእግዚኣብሔር ቃል ፈልገው የተጠጉት ወጣቶች ኣሁን ኣሁን ቅሬታ እያሰሙ ነው
  ስለዚህ ማህበሩ ስህተቱን ኣስተካክሎ የቤተ ክርስትያኒቱ ትምህርት ብቻ እንዲያስተምር እመክራለሁ
  የማኅበሩ ዓላማ በግልፅ የተጻፈ ቢሆንም በተግባር ግን ሌላ ነው! ዓላማው በጽንፈኛ ፖሎቲከኞች ተጠልፈዋል! ንፁ ትምህርተ ሃይማኖት ፈልገው የተጠጉት ወጣቶች የፈለጉትን ኣላገኙም !
  ስለዚህ ማኅበሩ ስህተቱን ኣስተካክሎ ቢንቀሳቀስ ለቤተ ክርስትያኒቱ የሚሰጠው ኣገልግሎት ከፍተኛ ይሆን ነበር የሚል አምነት ኣለኝ!

 15. geezonline October 10, 2013 at 2:32 pm Reply

  ሐራዎች፦ ታዘብዃችኍ! “መጋብያነ ልማታ” ማታ የተነፈሱትን ለጧት ለማድረስ ዕንቍ ፍለጋ በሌሊት ስትሯሯጡ እንቅፋቱን አትሰቀቁትም። እንዲኽ ያሉ ጥቡዐነ ሃይማኖት ግን ዐምና የተናገሩትን እነሆ ዘንድሮ አስነበባችኹን። ይኹን፤ ይኸውም አንድ ነገር ነው። ነገር ግን፤ በዚኽ ዐይነት ዘንድሮ ያሉበትን ኹናቴ ለመረዳት መረጃ የምንጠብቀው ለከርሞ መኾኑ ነው? ዐስቡበት!

 16. Anonymous October 10, 2013 at 4:35 pm Reply

  እውነትን የሚናገር እውነትን የሚሰራ ካልተከሰሰ/ካልተወነጀለ ሠይጣን ሥራውን አቁሟል ማለት ነው፡፡
  ምክንያቱም የሰይጣን ትልቁ በሽታ እውነት ነውና፡፡

  …ከአንድ አባት…

 17. daniel elias October 10, 2013 at 4:43 pm Reply

  ማህበረ ቅዱሳን ገፋን አስወጣን የሚሉ ወገኖች እምነቶውስጥ ሆነው ለሌሎች ሲሰሩ ደርሶባቸው በበቂ መረጃ ነው ከቤተክርስቲያን አካሄዳቸውን አስተካክለው ካልሆነ እንዲወጡ የተደረጉት እራሳቸውም ምስክር ናቸው እዛው እያለን ነው ጌታን የተቀበልነው ማህበሩ ደረሰብን እንደጂ ብዙ ሰው ይዘን እንወጣ ነበር ያሉት ስለዚህ ዛሬም ሆነ ነገ ማህበሩ ብቻ አይደለም ሰ/ት/ቤት ።ስለእምነቶ የሚቆረቆሩ ሁሉ ለቤተክርስቲናችን ስርዓት ይተጋሉ ። ጥቅም ፈላጊዎች ብዙ ቢሰሩም እነርሱ ይደክማሉ እንጂ ቤተክርስቲያን ምንም አትሆነም ፡፡ ወደድንም ጠላን ለእምነታችን የምንቆረቆር ከሆነ ለማህበረ ቅዱሳን ስራ ተቆርቆሪ አጋዥ መሆን አለብን፡፡ ሁሌም ብዙ ድክመት ቢኖርበትም ለቤተክርስቲያናችን ሁለንተናዊ እድገት የሚሰራ ማህበር ነው ፡፡

  • Zekarias October 11, 2013 at 11:43 am Reply

   sew wod kirstos enji made yalebet denegay yekeberu geta yemotlet hezeb berehab eyalek yenanet ablat american hager eyetenesherasru new edeget? yegetan wenet yeterabu yemisebekuten new edeget? ye’Egeziabheren hezeb eres beres maleyayet new edeget? hezeben endayetsenana kalun edayesema teret mawerat new edeget? Gebetal wondemu ene pawelos eko lebeterkrestan edege kenanem safelegu denakan esyesu yegetan wonegle le’alem eyenegeru eyetenekefu new yemotut lemehonu awo aleferedebehem edeget le’enanet bealemawi neger mashenerek new edeget nurachu hulu ede jovawetenesh bemeder slemimeslachu yesematun neger atasebum. gen geta ahun edekedmo ye’bareyan belek yezo lesekele ayametam be’meyasefera kerema lefered yemetal. keza yasadedachuten hezeb je’egachu yeteyekachula betasetewelu yeshlala. enesu letekemachew yerotalu anet gen wondime lemedan asetewl .geta ke’anet gar yehun

 18. Birhan Asfaw October 10, 2013 at 5:22 pm Reply

  Bewnet egziabher yesrachuhn ystachuh egziabher yetekelewn manm endemayneqlew enawqalen

 19. freedom October 11, 2013 at 8:31 am Reply

  girum neew

 20. Alem October 11, 2013 at 11:33 am Reply

  Aye mahbere kidusanena enesu teketayoch ebakachu neseha gebu ene alem sew kesew ga atedebadebu get neseha edetegebu belo new yeh yemanekeya dewel new. eset ahun enekan asetewelu yetegnawen melekam neger legeta aderegacheu new ewneten yeminager ayewodedem eyemetelut geta yemotleten hezeb be’alem hasab tebetebachu ebakachu neseha genu geta memechaw deresal.” yemewegeyawen beret lemikawem lesu yebesebetal” yegetan neger kemeseru ga atetagelu selefu yegeta new ye’tnebet mefesemya kemehon danu yegetan sera kebeserut ga heberet feteru esu new yemeyawatachu poltica tew

 21. Girum October 12, 2013 at 7:29 am Reply

  ሃራዎች እናንተ ግን ሁሌም አስመሳዮች ናችሁ:: ፈጣሪም ህዝብም ሀገርም ታሪክም እንዳይፋረዳችሁ የያዛችሁትን ጠማማ አስተሳሰብ አቃኑ ማህበረ ቅዱሳንን ለማዳከም የምታደርጉትን ሁሉ ውጭ ሀገር እንኩዋን በጥልቀት እናውቃለን እምላክ መልካሙን ያሳስባችሁ!!!

 22. Anonymous October 12, 2013 at 9:19 am Reply

  እኔ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በማህበራችን ማህበረ ቅዱሳን በሥራ አስፈጻሚም ሆነ አመራር እንዲሁም በተለያዬ ክፍሎች ለአለፎት 13 አመታት አገልግያለሁ፡፡ሁለት ሰዎች ይገርሞኛል፡፡ከሩቁቹ ዲ.ን አባይነ፤ከቅርቦቹ ዲ.ን ታደሰ፡፡ምንም እንኳን አንዳንዶች አቋመ ግትር አድርገው ቢውስድዋቸውም እንደ ሁኔታው የማይገለባበጡ ለመርሕ የሚኖሩ ውን ድሞች መሆናቸውን አይክዱም፡፡ለእኔ ደግሞ ዝናና ጥቅም ያመኑበትን ጉዳይ በአደባባ ይ ለመግለጽ የማያሳሳችው ወንደሞች ናቸው፡፡ይህም ጹሁፍ ያረጋገጠልኝ ይህንኑ ነው፡፡ይህ ለማህበራችን አቅም ነውና ኖሩልን፡፡ለማህበራችን ውስጣዊ አንድነት ተግተን እንስራ፡፡

 23. Anonymous October 12, 2013 at 1:06 pm Reply

  If the government doesn’t stop accusing the Mahiber Kidusan, It amounts to waging war against all its members and EOTC. therefore, we will take the struggle to its doors and offices!

  sooner or later this party may try to take measures to halt MK. I demand all political scientists to prepare a document to struggle the enemy and let us all know about it!

 24. ዘመኑ ተሻለ October 12, 2013 at 1:33 pm Reply

  ሐሰት ተደጋግሞ በመነገሩ እውነት ቢመስልም በፍጹምና መቼም እውነት ሊኾን አይችልም፡፡

 25. s October 19, 2013 at 3:35 am Reply

  ከማያምኑት ስለማኅበረ ቅዱሳን መልካም ነገር ይጠበቃልን ከአንደበታቸውስ መልካም ነገር ይወጣልን?

 26. Dawit October 22, 2013 at 4:06 pm Reply

  መንግስት በክርስቲያን university ተማሪውች ያውጣውን ህግ እና ስለ ግቢ ጉባጴ ማህበሩ ያለውን አቆም ያሳውቀን።

 27. Anonymous October 23, 2013 at 12:24 pm Reply

  ሐራዎች፦ ታዘብዃችኍ! “መጋብያነ ልማታ” ማታ የተነፈሱትን ለጧት ለማድረስ ዕንቍ ፍለጋ በሌሊት ስትሯሯጡ እንቅፋቱን አትሰቀቁትም። እንዲኽ ያሉ ጥቡዐነ ሃይማኖት ግን ዐምና የተናገሩትን እነሆ ዘንድሮ አስነበባችኹን። ይኹን፤ ይኸውም አንድ ነገር ነው። ነገር ግን፤ በዚኽ ዐይነት ዘንድሮ ያሉበትን ኹናቴ ለመረዳት መረጃ የምንጠብቀው ለከርሞ መኾኑ ነው? ዐስቡበት!

 28. Anonymous October 24, 2013 at 7:46 am Reply

  ሐሰት ተደጋግሞ በመነገሩ እውነት ቢመስልም በፍጹምና መቼም እውነት ሊኾን አይችልም፡፡ከማያምኑት ስለማኅበረ ቅዱሳን መልካም ነገር ይጠበቃልን ከአንደበታቸውስ መልካም ነገር ይወጣልን?

 29. enie November 7, 2013 at 7:03 am Reply

  ሐሰት ተደጋግሞ በመነገሩ እውነት ቢመስልም በፍጹምና መቼም እውነት ሊኾን አይችልም፡፡ከማያምኑት ስለማኅበረ ቅዱሳን መልካም ነገር ይጠበቃልን ከአንደበታቸውስ መልካም ነገር ይወጣልን?

 30. amare November 25, 2013 at 9:43 am Reply

  መንፈሳዊ ኣገልግሎት ምንድን ነው

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: