ቋሚ ሲኖዶስ: አቡነ ጢሞቴዎስ በኮሌጁ መምህራንና ሠራተኞች ላይ ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች ውድቅ አደረገ

  • የአካዳሚክ እና አስተዳደር ዲኖችን መድበዋል
  • ቋሚ ሲኖዶሱን ያጠያየቀው ምደባ አጽድቆቱን ይጠብቃል
  • ዘላለም ረድኤት ባቀረበው የመልቀቂያ ደብዳቤ ይሰናበታል
  • መምህራኑ ደመወዛቸው ታግያለውኃና መብራት ሁለት ሳምንት አስቆጥረው ነበር

ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት ባካሄደው ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው÷ ከሥልጣናቸው ተገልለው እንዲቆዩ የተወሰነባቸው ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህራንና ሠራተኞችን ከኮሌጁ መኖርያ ቤቶች የማስለቀቅ፣ ደመወዝ የማገድ፣ አዲስ ቅጥር የማካሄድ፣ ከሓላፊነት የማዘዋወርና የማሰናበት ውሳኔዎችንና መመሪያዎችን ውድቅ በማድረግ የዓመቱ የትምህርት መርሐ ግብር ቅድመ ዝግጅት ተጠናክሮ እንዲካሄድ አዘዘ፡፡Teachers of the Holy Trinity Theological College

ቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔውን ያስተላለፈው 11 የኮሌጁ መምህራንና ሠራተኞች ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጨረሻ የሊቀ ጳጳሱ ዐምባገነናዊና የግፍ አስተዳደር አስመልክቶ ባቀረቧቸው ባለሰባት ነጥብ ጥያቄዎች ላይ ከተወያየ በኋላ ነው፡፡ በውይይቱ የብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ አስተዳደር ‹‹አጠቃላይ የሕንጻ ጥገና ለማካሄድ›› በሚል በኮሌጁ የሚኖሩ መምህራንና ሠራተኞች ከነሐሴ ፱ – ፴ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ድረስ የቤቶችን ቁልፍ እንዲያስረክቡ ያስተላለፉት ውሳኔና እስከተጠቀሰው ቀን የማያስረክቡ ደግሞ ደመወዛቸው እንዳይከፈላቸው ለኮሌጁ ፋይናንስ ክፍል የሰጡት ትእዛዝ አግባብነት የሌለው በሚል ውድቅ ተደርጓል፡፡

የአቡነ ጢሞቴዎስን ውሳኔና ትእዛዝ በመቃወም በኮሌጁ ቅጽር በሚገኘው መኖርያ ቤታቸው የሚገኙት መምህራንና ሠራተኞች የነሐሴ ወር ደመወዛቸው የታገደ ከመኾኑም በላይ ከነሐሴ ፴/፳፻፭ ዓ.ም ወዲህ የመብራትና ውኃ አገልግሎት ተቆርጦባቸው ቆይቷል፡፡ እስከ 18 ዓመት ድረስ በመኖርያ ቤቶቹ ለቆዩ መምህራንና ሠራተኞች በሁለት ሳምንት ውስጥ ቁልፍ አስረክበው እንዲለቁ የተላለፈውን ውሳኔ ውድቅ ያደረገው ቋሚ ሲኖዶሱ፣ መምህራኑና ሠራተኞቹ የተቆረጠባቸው የመብራትና ውኃ አገልግሎት እንዲቀጥል፣ የታገደባቸው ደመወዝ እንዲለቀቅላቸውና በቀጣይም በአግባቡ እንዲከፈላቸው፣ የዓመቱ የትምህርት መርሐ ግብር ቅድመ ዝግጅትም ተጠናክሮ እንዲካሄድ አዝዟል፡፡

ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ውድቅ ያደረጋቸው የአቡነ ጢሞቴዎስ አስተዳደር ሌሎች ውሳኔዎች ውስጥ ሊቀ ጳጳሱ ከሥልጣን እንዲገለሉ ከተወሰነበት ሰኔ/፳፻፭ ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ለኮሌጁ ቤተ መጻሕፍት ያካሄዷቸውን ቅጥሮች፣ የቤተ መጻሕፍቱን ሓላፊ መ/ር አባ ጌዴዎን ብርሃነ ከሓላፊነት በማግለልና በማሰናበት የወሰዷቸውን ርምጃዎችም እንደሚጨምር ተመልክቷል፡፡ አላደረሳቸውም እንጂ ከመምህራኑም መካከል በጡረታ እንዲገለሉ፣ ወደ ሌሎች ኮሌጆች እንዲዘዋወሩ ያሰቡባቸውም እንደነበሩ ተዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት ለሰባት ወራት የኮሌጁ ደቀ መዛሙርትና መምህራን በአቡነ ጢሞቴዎስ አስተዳደር ላይ ባነሡት ጥያቄ ላይ በተካሄደው ማጣራት፣ ከቀን መደበኛ መርሐ ግብር ሓላፊነቱ ተነሥቶ ከኮሌጁ እንዲወገድና ስለ ሃይማኖቱ ሕጸጽ እንዲጠየቅ የተወሰነበት ዘላለም ረድኤት÷ ከውሳኔው በተፃራሪ በሊቀ ጳጳሱ ድጋፍ ሲወጣና ሲገባ ከቆየ በኋላ በዚህ ሳምንት ሰኞ ለኮሌጁ አስተዳደር አቅርቦታል በተባለው የመልቀቂያ ደብዳቤ መሠረት ከሓላፊነቱ ተነሥቶ ከኮሌጁ እንደሚሰናበት ተገልጧል፡፡

የኮሌጁ አካዳሚክ ምክትል ዲን የኾኑት መ/ር ፍሥሓ ጽዮን ደመወዝ ከሓላፊነታቸው ተነሥተው በመምህርነት ተወስነው የሚቀጥሉ ሲኾን በእርሳቸው ቦታ ኮሌጁን በመምህርነትና በሬጅስትራርነት ለረጅም ጊዜ ያገለገሉት መ/ር ግርማ ባቱ መመደባቸው ታውቋል፡፡ በትምህርት ደረጃቸውና በማስተማር ብቃታቸው ምስጉን እንደኾኑ የሚነገርላቸው መ/ር ግርማ ባቱ÷ ከዚያው ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በቴዎሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ጥናት ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው፡፡ የዜና/ነገረ አበው (Patrology)፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን (Canon Law) እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ኮርሶችን በመንፈሳዊ ኮሌጁ የሚያስተምሩት መ/ር ግርማ፣ መንፈሳዊ ኮሌጁ ባለፈው ዓመት በድኅረ ምረቃ  ፕሮግራም የጀመረውንሲስተማቲክ ቴዎሎጂ መርሐ ግብር በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡

የአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ቅዱስ ፍሬምናጦስ ኮሌጅ ምሩቁና የቀድሞው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ልዩ ጸሐፊ የነበሩት መ/ር ያሬድ ክብረት የኮሌጁ አስተዳደር ምክትል ዲን ኾነው እንዲሠሩ በፓትርያርኩና በዋና ሥራ አስኪያጁ ውሳኔ ተመድበዋል፡፡ መ/ር ግርማ ባቱ በትላንትናው ዕለት ከመ/ር ፍሥሓ ጽዮን ጋራ ርክክብ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲኾን ምደባው ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ጢሞቴዎስ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባቀረቡት መነሻና ፓትርያርኩ ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በሰጡት መመሪያ የተካሄደ መኾኑ ተጠቅሷል፡፡ በዛሬው የቋሚ ሲኖዶሱ ስብሰባ የሁለቱም ሓላፊዎች ምደባ አጠያይቋል፡፡

ይኸውም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ባለፈው ዓመት በቋሚ ሲኖዶስ በተወሰነውና ከቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት በተሰጠው መመሪያ መሠረት ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ በማቋቋም ለመንፈሳዊ ኮሌጁ ዋና ዲን፣ አስተዳደር ምክትል ዲንና አካዳሚክ ምክትል ዲን ለመኾን የሚበቁ ሓላፊዎችን እንዲያቀርብ አዝዞ ሳለ ትእዛዙ ባልተፈጸመበትና ሊቀ ጳጳሱም ከሥልጣን ተገልለው እንዲቆዩ በተወሰነበት ኹኔታ የተካሄደ በመኾኑ ነው፡፡ ስለዚህም የአዲሱ አካዳሚክ ዲንና አስተዳደር ዲን ምደባዎች የቋሚ ሲኖዶሱ ቀጣይ እይታና አጽድቆት እንደሚያስፈልጋቸው ተመልክቷል፡፡

ይኸው ምደባ በቀረቡት ሓላፊዎች የቋሚ ሲኖዶሱን አጽድቆት የሚያገኝ ከኾነ÷ መ/ር ግርማ በአካዳሚክ ምክትል ዲን ሓላፊነታቸው የቀን መደበኛ፣ የማታ ተከታታይና የርቀት ትምህርት መርሐ ግብሮችን፣ የጥናትና ምርምር ማእከሉን እንዲሁም የቤተ መጻሕፍቱን አገልግሎት ከኮሌጁ ራእይና ተልእኮ አንጻር አቀናጅቶ መምራት፣ ማሻሻል፣ ማስፋፋትና ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ አስተዳደር ምክትል ዲኑ የሚነሡባቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ያሉ ቢኾንም የኮሌጁን የሰው ኃይል፣ ፋይናንስና ንብረት እንዲሁም የደቀ መዛሙርቱን የምግብ ቤት አገልግሎት አቀናጅቶ መምራት፣ መጠበቅና ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

Advertisements

3 thoughts on “ቋሚ ሲኖዶስ: አቡነ ጢሞቴዎስ በኮሌጁ መምህራንና ሠራተኞች ላይ ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች ውድቅ አደረገ

  1. Anonymous September 19, 2013 at 3:46 am Reply

    አቡነ ጢሞቴዎስ ምን የሚሉት ሰይጣን ነው የሰፈረባቸው?ሙሰኛ

  2. Hailemariam September 26, 2013 at 1:18 am Reply

    Abune Thimostiwous, the man who is there for the destruction of Ethiopian Canona and Tiwifit and the ambassader of Devil

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: