ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወስድስቱ ዓመተ ምሕረት

His Holiness Abune Mathias

ፎቶ: ማኅበረ ቅዱሳን

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን

 • በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
 • ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፣
 • የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችኹ፣
 • በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችኹ፤
 • እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ኾናችኁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

የዘመናት ፈጣሪ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከ፳፻፭ ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ ወደ ፳፻፮ ዓ.ም ዘመነ ማርቆስ በሰላም አደረሳችኹ!!!

‹‹ወሠርዐ ዕድሜኹ ወዓመታቲኹ መጠነ ይነብሩ በዘየኃሥሥዎ ለእግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር እርሱን ፈልገው ያገኙት ዘንድ፣ ሰዎች የሚኖሩባቸውን የዕድሜና የዘመናት መጠን ሠራ›› /የሐዋ. ሥራ ፲፯÷ ፳፭ – ፳፯/

አምላካችን እግዚአብሔር፣ ለፍጡራን ከሰጣቸው መልካም ስጦታዎች መካከል የዘመን ስጦታ የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን፣ እግዚአብሔር በጥንተ ፍጥረት ፍጥረታትን ውብ አድርጎ ሲፈጥር፣ ዘመናትንና ዕለታትን ለመለየት ያስችሉ ዘንድ ብርሃናትን በሰማይ ጠፈር ፈጥሯል፡፡ /ዘፍጥ.፩ ÷፲፬ – ፲፱/

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጅ በብርሃን ዑደት እየታገዘ ዘመናትን፣ ወቅቶችን፣ ወራትንና ዕለታትን ለይቶ በማወቁ መርሐ ግብር እያወጣ ለሥራ አፈጻጸም ይጠቀምባቸዋል፡፡ በመኾኑም ዘመናት ለሥራችን የሚሰጡት ግብአት ከፍ ያለ ኹኖ ይታያል፡፡

እግዚአብሔር ዘመናትን በሰዓታት፣ በቀናት፣ በወራት፣ በወቅቶችና በዓመታት ከፋፍሎ የፈጠረበት ዋና ምክንያት፣ በእነርሱ መለኪያነት ዐቅደን፣ አልመንና ጠንክረን በመሥራት፣ ራሳችንን፣ ቤተ ሰባችንን፣ አገራችንንና በአጠቃላይ ዓለማችንን ለኑሮ የተመቸች፣ ውብና ለም አድርገን እንድንጠብቅ ነው፡፡ /ዘፍጥ.፪፥፲፭/

የዘመን ጸጋ በሥጋዊ ሕይወታችን ብቻ ሳይኾን በመንፈሳዊ ሕይወታችንም ከፍተኛ ትርጉም አለው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ከፍ ብሎ እንደነገረን፣ ዘመናት እግዚአብሔርን ፈልገን የምናገኝባቸው መሣርያዎች ናቸው፡፡

ይህም ማለት እያንዳንዱ ዓመት በሰው አእምሮ ጥሎት የሚያልፍ ተግባራዊ ዕውቀትና ትምህርት አለ፤ ከዚህ አኳያ ሰው በየዓመቱ ከሚቀስመው ሰፊ ግንዛቤ ዕውቀቱን እያሰፋ ወደ ተሻለ ማስተዋል ይሸጋገራል፡፡ ጤናማ ማስተዋልን ሲያገኝ ፈጣሪውን ወደ መፈለግና ወደ መከተል፣ ፍጹም ሰው ወደ መኾንም ይደርሳል፤ በዚህ ምክንያት ዘመን፣ ሰው ፈጣሪውን እንዲያውቅ የሚያስችል የማብቃት ጸጋ አለው ማለት ነው፡፡ /የሐዋ. ሥራ ፲፯÷ ፳፮ – ፳፯/

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት

እግዚአብሔር እኛን ሲፈጥር ዓላማ አለው፤ ተቀዳሚ ዓላማውም በተፈጥሮ የተሰጠንን ዕውቀት ተጠቅመን፣ እርሱን እንድናውቅ፣ እርሱን እንድናምን፣ እርሱን እንድናመልክና ለእርሱ እንድንታዘዝ፣ በእርሱም የዘላለም ሕይወትና ክብር እንድናገኝ ነው፡፡ /ሮሜ ፩÷ ፲፱ – ፳፩፤  ዮሐ. ፳÷፴፩/

በምድራዊ ኑሮአችንም እንዳንቸገር ልዩ ልዩ ሀብት ያላትን ምድር ፈጥሮ ሰጥቶናል፤ ይኹንና ምድራችን በማሕፀንዋ የያዘችውን ልዩ ልዩ ጥሬ ሀብት፣ መልክና ጣዕም እንዲኖረው አድርጎ ወደ ጥቅም የመለወጡ ሓላፊነት ለእኛ አስረክቦአል፡፡ ይህም እግዚአብሔር እኛን የሥራው ተሳታፊዎች የማድረግ ዓላማ ያለው መኾኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

እግዚአብሔር፣ የሥራ ሁሉ ጀማሪ ከመኾኑም ሌላ ሁሌም ሲሠራ የሚኖር ሥራ ወዳድ አምላክ ነው፡፡ /ዮሐ. ፭÷፲፯/ የእኛንም አካል ለሥራ የተመቸ አድርጎ መፍጠሩ፣ የሥራው ተሳታፊዎች እንድንኾን ብሎ እንደኾነ ልናስተውል ይገባል፡፡

ስለኾነም እኛ ታታሪ ሠራተኞች በኾን ቁጥር፣ የእግዚአብሔር ተባባሪዎች እንኾናለን፤ ከሥራ በራቅን ቁጥር ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋራ ላለመተባበር እየከጀልን እንደኾነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ አንጻር እያንዳንዱ ሰው፣ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ በኅሊናው ማቃጨል ያለበት ዐቢይ ነገር፣ በሥጋዊውም ኾነ በመንፈሳዊው ሓላፊነቱ ምን ሠራኹ፣ ምንስ ቀረኝ፣ በአዲሱ ዓመትስ ምን ሠርቼ ከእግዚአብሔር ጋራ ተባባሪ ልኹን የሚለውን ነው፡፡

ሥራ መሥራት ማለት ከእግዚአብሔር ጋራ መተባበር ማለት ነውና፣ እያንዳንዱ ሰው ይህን አስተሳሰብ አንግቦ አዲሱን ዘመን በአዲስ መንፈስ ከተቀበለው፣ እውነትም ዘመኑን በአዲስ ሥራ ይለውጣል፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት

ዓይነተ ብዙ በኾነ የተፈጥሮ ጸጋ የታደለችው አገራችን ኢትዮጵያ፣ በተፈጥሮ ጸጋ የጎደላት የሌለ ብቻ ሳይኾን፣ ከሁሉም የበለጠና የተሻለ ሀብት ያላት አገር ናት፤ ነገር ግን በአገራችን ከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ተከማችቶ የሚገኘውን ሀብት ጠንክረን በመሥራት ወደ ጥቅም መለወጥ እየቻልን የሌላውን ትርፍራፊ ለመለቃቀም በሚል በተሳሳተ ግንዛቤ መተኪያ የማናገኝላቸው ልጆቻችን በየአቅጣጫው እየተጎዱብን ነው፡፡

ወጣት ልጆቻችን ለአደጋ በተጋለጠ ኹኔታ በሕገ ወጥ መንገድ ከውድ አገራቸው እየወጡ በየአካባቢው ወድቀው እየቀሩ ናቸው፤ ይህን አሳዛኝ ኹኔታ ለማስቆም ሕዝቡ በርትቶ በማስተማርና በመሥራት ልጆቹን ከአሠቃቂ ኅልፈተ ሕይወት ማዳን አለበት፡፡

ሃይማኖታችንና አገራችንን የምንወድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ በሀገራችን ሥር ሰዶ የቆየውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር በመቅረፍ፣ በማኅበራዊ ኑሮው የተስተካከለና በኢኮኖሚው የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ርብርቦሽ፣ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በመቻቻል፣ በመከባበር፣ በመፈቃቀር፣ በስምምነትና በመመካከር መሥራት፣ ተቀዳሚ ዓላማችን ማድረግ አለብን፡፡

ከሁሉም በላይ የተጀመሩም ኾኑ ለወደፊት የሚጀመሩ የልማት ሥራዎች ፍጻሜ አግኝተው ሀገራችንን በልማት የመለወጥ ሕልማችንን እውን ሊያደርግ የሚችል ሰላማችንን በአስተማማኝ ኹኔታ የተጠበቀ እስከኾነ ድረስ ብቻ መኾኑን፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለአፍታ እንኳ ሊዘነጋው አይገባም፡፡

በመኾኑም ሁላችንም ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በአካባቢ ሳንለያይ የዕድገታችን ዋስትና የኾነውን ሰላማችንን በንቃት መጠበቅ አለብን፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት

የሀገር ደኅንነትና ልማት ከሚረጋገጥባቸው መንገዶች አንዱ፣ በአካል፣ በአእምሮና በአስተሳሰብ ጭምር ሙሉ ጤናማ የኾነ ማኅበረሰብ ሲኖረን ጭምር ነው፡፡

ስለኾነም በአገራችን በእርግዝናም ኾነ በወሊድ ጊዜ የጤና ባለሞያ ተገቢ ክብካቤና እገዛ ባለማግኘት ለሞት አደጋ የሚጋለጡ እናቶችና ሕፃናት በርከት ያሉ እንደኾነ ይታወቃል፡፡ ይህን ለመቀነስና ለመከላከል ታስቦ በአገራችን እየተካሄደ ያለው የእናቶችና ሕፃናት የጤና ክብካቤ የተሳካ ይኾን ዘንድ ሁሉም ሕዝባችን ሊደግፈውና በመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ሊኾን ይገባል፡፡

ሕክምና ማለት ጥበብ ማለት ነው፤ ጥበብን ደግሞ አጽንተን እንድንከተላትና እንድንጠቀምባት፣ እግዚአብሔር ያዘዘን በመኾኑ በባለሞያና በሕክምና ጥበብ እየተረዱ በጤና ተቋም መውለድ እግዚአብሔር የሚወደውና የሚፈቅደው ነው፡፡

በተለይ እናቶቻችን የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝበው፣ በየአካባቢያቸው በሚገኙ የጤና ተቋማት እየተገኙ በጤና ባለሞያ ድጋፍና ርዳታ በመውሰድ ጤንነታቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡

በመጨረሻም፣ በአዲሱ ዓመት ሕዝባችን ሁሉ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ኑሮው የበለጸገ፣ በዕውቀትና በማስተዋል የተካነ፣ ጤንነቱና ሰላሙ የተጠበቀ ይኾን ዘንድ በተሠማራበት የሥራ መስክ ጠንክሮ በመሥራት አገሩን ያለማ ዘንድ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር አዲሱን ዘመን ይባርክልን፤ ይቀድስልን፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

መስከረም ፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም

Advertisements

3 thoughts on “ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወስድስቱ ዓመተ ምሕረት

 1. Anonymous September 10, 2013 at 5:58 pm Reply

  amen!!!

  • yetayali ewunetu September 11, 2013 at 8:00 am Reply

   እግዚአብሔር በአሁኑ ወቅት ቤተክርስቲያንን ይመሩ ዘንድ አደራ ያስጠበቃቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የቤተክርስቲያንን ፕሮስትሮይካ በማካሄድ የተሻለ ለውጥ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ለማምጣት እየጣሩ ይመስላል፡፡ ነገር ግን እየተደረገ ያለው ለውጥ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ከጅማሬው እየታየ ነው፡፡180 የኮሌጅ ተማሪዎችን በምክትል ዲንነት መምራት ተስኖት ፍጹም በተዝረከረከ አሰራር ኮሌጁን ለዉድቀት ዳርጎ የለቀቀን፡ የጵጵስናን ሹመት ለማግኘት በመመኘት ጥፋትን በድፍረት ከመቃወም ይልቅ ከራስ በላይ ነፋስ ብሎ ከየሊቃነ ጳጳሳቱ ፊት የሚጎናበስ ሰውን በጠቅላይ ቤ/ክህነት ምክትል ስራ አስኪያጅ ማድረግ ከእንደዚህ ያለም ለውጥን መጠበቅ አምለክ ወስኖ በሰጠ ጊዜ መቀለድ ነው፡፡ በጣም አሳሳቢው ጉዳይ የነገዋ ቤተክርስቲያን ዕጣ በእነዚህ ከእውነት ጋር ለመኖር በሚሰጉ አደርባይ አካላት እጅ ላይ ለመውደቅ መቃረቡ ነው፡
   አብዛኛዎቹ ብጹዓን አባቶች ማንን ማማከር ከማን ጋር መጓዝ አንዳለባቸው መለየት ተሳናቸው፡፡ በንጽህናቸው; መማለጃን በመቀበል; በምንፍቅና ከሚታሙ ብቻ ሳይሆን በገሃድም ከተከሰሱ; የመሸታ ቤት ቋሚ ደንበኞች መነኮሳትና ዲያቆናት ጋር በየአደባባዩ ሲታዩ ሁሉን እየተመለከተ ልቡ የቆሰለው ምዕመን ለአባቶች ያለው ቦታ ግብዓተ-መሬት እየገባ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ቀንደኛ መናፍቅ ሆኖ በተማሪዎች ሙሉ ተቃዉሞ ከማስተማር የታገደው በወር ከሚከፈለው ደሞዝ በላይ የኮሌጁን ዘመናዊ አፓርትማ ተከራይቶ የሚኖረውን፡ ያስታማሩትን ዕንቁ መምህራንን ከመኖርያቸው ለማስወገድ እየኳተነ ባላቅን ያሳተ በለዓም በመሆን ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ጢሞቴዎስን በማሳሳት እስከዛሬ ለሆነው ምስቅልቅል ሁሉ ተጠያቂው የደም ሰው አቶ ዘላለም ረድኤት/መርገም/ የምዕራብ ሸዋ ሀ/ስብከትን በመወከል ከሀ/ስብከቱ ሊቀ-ጳጳስ ጋር በበጎ አደራጎት ስም ቀዳዳ ቀልቀሎውን ይዞ በየሄዱበት በመሯሯጥ ላይ ነው፡፡
   ከምዕራብ ሸዋ ሀ/ስብከት በእውቀት ሳይሆን በምንፍቅና የተካኑ ደቀ-መዛሙርትን ወደየኮሌጆቹ በመላክ ከሀ/ስብከቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ጋር በጋራ በጣምራ የሰሩት ስራ ወደፊት ጊዜ የሚገልጠው ይሆናል፡፡ ታዲያ ስለግለሰቡ ከመምህራን እስከ ሊቀ-ጳጳስ እውነቱን ጠይቀው የተረዱት አባት የዚህ ሰው ሚስጠረኛ መሆናቸው ምንይባል ይሆን?
   አለቃን ከቤተክርስቲያን ቤተክርስቲያን ማቀያየር ሳይሆን መልካም አለቃን ማዘጋጀት ከየስፍራው ለሚሰማው የህዝብ ሮሮ ቀላል መልስ መሆኑን መሪዎቻችን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡

 2. Anonymous September 11, 2013 at 7:55 am Reply

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: