አዲስ አበባ በለውጥ አመራር ያብባል ገና

 • በምደባ ቅር የተሰኙ ሓላፊዎች በየሆቴሉና ሬስቶራንቱ የዐመፅ ምክክር ይዘዋል
 • ‹‹የቋሚ ሲኖዶሱ ምደባ በአተገባበር በደላሎች ተጠልፏል›› የሚል ቅሬታ አላቸው
 • የረዳት ሊቀ ጳጳሱና ጽ/ቤታቸው ድርሻ የቋሚ ሲኖዶሱን ምደባ ማስፈጸም ብቻ ነው
 • በዘላቂው የሀ/ስብከ መዋቅር ስፍራ የሚኖራቸው በጊዜያዊ ምደባቸው ብቃት ያሳዩ ሓላፊዎችና ሠራተኞች መኾናቸው ተገልጧል

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ በሚያደርገው ቅድመ ዝግጅት ለዘረጋው የሽግግር ጊዜ መዋቅር የሓላፊዎችና ሠራተኞች ምደባ አካሂዷል፡፡ እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ፳፻፮ ዓ.ም ድረስ ለሦስት ወራት በሚቆየው የሽግግር መዋቅር 133 የሀ/ስብከቱ ሐላፊዎችና ሠራተኞች በምደባው ታቅፈዋል፡፡ ከእኒህም ውስጥ 57 በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት፣ 76 ያህሉ ደግሞ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ቅርበት ባላቸው ሰባት የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የተመደቡ ናቸው፡፡

ምደባውን ያካሄደው በቋሚ ሲኖዶስ የተሠየመውና በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም መለሰ የሚመራ መዳቢ ኀይለ ግብር ነው፡፡ ኀይለ ግብሩ ሰብሳቢውን ጨምሮ አምስት አባላት ያሉት ሲኾን እነርሱም የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ አስተዳደር መምሪያ፣ የሒሳብና በጀት መምሪያ፣ ጠቅላላ አገልግሎት ሓላፊዎችንና የቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተወካይን በአባልነት የያዘ ነው፡፡ መረጣና ምደባው (selection and placement) የተሠራበት መነሻ በቋሚ ሲኖዶሱ የጸደቀው የሀ/ስብከቱ አስተዳደራዊ መዋቅርና ከእያንዳንዱ የሥራ መደብ ጋራ ተነጻጽሮ የቀረበው ዝርዝር የመመዘኛ መስፈርት ነው፡፡ በመስፈርቱ መሠረት የትምህርት ዝግጅት እና የሥራ ልምድ ዋነኛ መመዘኛ መደረጉ የተገለጸ ሲኾን ‹‹የብሔር ተዋፅኦ››ም ከግንዛቤ ገብቷል ተብሏል፡፡

ምደባውን/ድልደላውን የሠራው ኀይለ ግብር በቋሚ ሲኖዶስ የተሠየመ እንደመኾኑ መጠን የፓትርያሪኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስም ይኹኑ የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት መጨረሻ ላይ በሪፖርት ከተገለጸላቸው ውጭ በሂደቱ ላይ ቀጥተኛ ይኹን ተዘዋዋሪ ተጽዕኖ ያደረጉበት ኹኔታ እንዳልነበር ተጠቅሷል፡፡ ይኸውም ሊቀ ጳጳሱና የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት በቋሚ ሲኖዶስ ጸድቆ በወረደው ምደባ ቀጥተኛ ተጠያቂ እንዳይኾኑና ምደባውን በማስፈጸም ላይ እንዲያተኩሩ አስችሏቸዋል – በቅ/ሲኖዶስ የጸደቀ ውሳኔ ይግባኝ እንደሌለው ታስቦ፡፡

ኾኖም እንደተሰጋው ምደባውን ተከትሎ በርካታ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች እየተሰሙ ነው፡፡ ምደባው ‹‹የሲኖዶስ ድልደላ ሳይኾን የደላሎች ድልደላ ነው›› የሚሉት ቅሬታ አሰሚዎቹ፣ መዳቢ ኀይለ ግብሩ ለቋሚ ሲኖዶሱ አቅርቦ ያጸደቀውና ተፈጻሚ እንዲኾን ያዘዘው ድልደላ ትክክለኛና ተገቢ ነበር፤ ችግሩ ግን ቅሬታ አሰሚዎቹ በረዳት ሊቀ ጳጳሱ ዙሪያ ተሰልፈዋል ያሏቸው ‹ደላሎች› ዐይነተኛውን ምደባ ‹‹በጥቅምጥቅምና ቡድንተኝነት ቀሽበውታል ወይም በውዘውታል፡፡›› በስም ተለይተው ከሚጠቀሱትና ‹ደላሎች› ተብለው ከተገለጹት ሦስቱ በምደባው የዋና ክፍል ሓላፊነት ያገኙ፣ አንዱም በሀ/ስብከቱ ጨርሶ በጀት ያልነበረው፣ ሌላውም በጀቱ ከአጥቢያ ኾኖ በሀ/ስብከቱ የሚታወቅ ሥራ የሌለው ነው፡፡

ዐይነተኛው ምደባ በትግበራው ወቅት በደላሎቹ ለመጠለፉ በተቺዎቹ የሚቀርቡት ማብራሪያዎች÷ ሰሞኑን መልካም አስተዳደርን ስለማረጋገጥ በተከታታይ የተሰጠው ሥልጠናና ሥልጠናው ያሳደረውን የመሻሻል ተስፋ ተከትሎ በድልደላው ለአንዳንድ ሓላፊዎች የተሰጠው ምደባ ከትምህርት ዝግጅታቸው፣ ከሥራ ልምዳቸውና ከሥነ ምግባራቸው ጋራ አይጣጣምም፤ ‹‹የብሔር ተዋፅኦ›› ለማካተት በሚል አድልዎ ተፈጽሟል፤ ‹‹ሥራ ያለው ክፍለ ከተማ ላይ ነው›› በሚል ከትምህርታቸው ዝግጅት፣ ከሞያቸው አግባብነትና ከሥራ ልምዳቸው አንጻር በሀ/ስብከት ለመመደብ የሚበቁ ሓላፊዎችና ሠራተኞች ወደ ክፍለ ከተማ ‹ወርደው› በማይጎዳኛቸው ቦታ ተመድበዋል፤ ለእነእገሌ ቋሚ ሲኖዶስ የወሰነላቸው ምደባ ተለውጦ በደብዳቤ የተሰጣቸው የተለየ ነው የሚሉና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

በአስረጅነትም፣ በሀ/ስብከቱ የሰው ኀይል አስተዳደርና ፋይናንስ ክፍል ላይ የተመደቡት ሓላፊ ከሓላፊነቱ ጋራ የሚጣጣም የትምህርት ዝግጅት እና አግባብነት ያለው የሥራ ልምድ የላቸውም፤ የሰንበት ት/ቤት ጉዳዮች ሓላፊው ከመመዘኛው አኳያ ልምዳቸው በቂ አይደለም፤ በዶክመንቴሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል የተመደቡት ሓላፊ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋራ ጨርሶ አይተዋወቁም፤ በሀ/ስብከት ደረጃ በስብከተ ወንጌል ሲሠሩ የቆዩትና ለሓላፊነቱም ብቁ የነበሩቱ የክፍለ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ተደርገዋል፤ የቁጥጥር አገልግሎት ሓላፊው በትምህርት ዝግጅትና ልምድ መመዘኛውን ቢያሟሉም ቦታው ለሚጠይቀው የምግባር አርአያነት አይበቁም፤ ይህም በክፍለ ከተማ ደረጃ በተመሳሳይ ሓላፊነት በተመደቡቱ ላይ ጎልቶ ይታያል በሚል ተጠቅሷል፡፡

ምደባ ካገኙ ከ130 በላይ ሠራተኞችና ሓላፊዎች ‹‹የ29ኙ ተበውዟል/ተቀሽቧል›› የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ በምደባው ‹‹የሲኖዶሱ የበላይነት ሳይኾን የደላሎች የበላይነት ነው የታየው›› በማለት ያማርራሉ፤ ችግሩ ቋሚ ሲኖዶስ አጽድቆታል ብለው በሚያምኑት ዐይነተኛው ምደባ በአስቸኳይ እንዲስተካከል ይጠይቃሉ፤ ካልተስተካከለ ‹‹በየሆቴሉ ከፍተኛ አድማና የዐመፅ ምክክር ተይዟል፤ ከገነፈለም ከባድ ይኾናል፤›› ሲሉም ይዝታሉ፤ ‹‹የአድማና የዐመፅ ምክክሩ›› ሰሞኑንና በቀጣዮቹ ጊዜያት በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አስተዳደር ላይ ከሚካሄዱት ማስተካከያዎች ጋራ ተደማምሮ ሊጠናከር እንደሚችልም ያሳስባሉ፡፡

ስለቅሬታዎቹ አስተያየታቸውን የሰጡ የጉዳዩ ተከታታዮች በበኩላቸው፣ ሥልጡን ተቋማዊ ሥርዐት ባልዳሠሠው ቤተ ክህነት ይቅርና ሥርዐቱ በዳበረባቸው ታላላቅ ተቋማት ለውጥ በሚካሄድበት ወቅት እንዲህ ዐይነቱ አቤቱታ የሚጠበቅ ነው፡፡ ቁም ነገሩ ሥርዐቱና አሠራሩ ለሒስ ክፍትና ትችትን የሚያስተናግድ ኾኖ ራሱን በራሱ እያረመ የአካሄዱን ጤናማነት የሚያረጋግጥበት መፈተሻና ሚዛን (check and balance) ያለው መኾኑ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ የለውጡን አጠቃላይ ሂደት ለመገምገም በተዘጋጁ መጠይቆች ክንውኑ መፈተሹን ያስረዱት የጉዳዩ ተከታታዮች÷ የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ብቻ የማይመልሳቸው ጥያቄዎች በበቂ አለመታየታቸውን አልሸሸጉም፤ በምደባው በሀ/ስብከቱ የተከማቸውን የሠራተኛ ብዛት ቦታ ከማስያዝ አንጻር ቅድሚያ ተሰጥቷል፤ የሽግግር መዋቅሩ እስከ መጪው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ የሚቆይ የሦስት ወራት የለውጥ ቅድመ ዝግጅት መኾኑ ላይ ተተኩሯል፤ ይህም በመኾኑ ያለውን ሠራተኛ በለውጥ መዋቅሩ አስገብቶ በሽግግር ወቅቱ በመፈተን ለውጡን ሊያራምድ የሚችልና በተመሳሳይ የግንዛቤ ደረጃ ላይ የሚገኝ የሰው ኀይል በቀጣይነት ማጠናከር እንደተመረጠ አብራርተዋል፡፡

ምደባው በየትኛውም ቦታ በሓላፊነት ለተቀመጡት ሁሉ ‹‹የዛፍ ላይ ዕንቅልፍ ነው›› ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ፣ ራሳቸውን ለለውጥ ያዘጋጁ ሠራተኞችና ሓላፊዎች በሥልጠና የሚታገዙበት፣ በዕድገት የሚበረታቱበት በተቃራኒው ለተገኙት ደግሞ ግምገማን ጨምሮ በዝርዝር የብቃት መመዘኛዎች ማጥራት የሚካሄድበት እንደሚኾን አመልክተዋል፡፡ ድልደላው ‹በደላሎች› እንደተጠለፈ የተነገረውም ከእውነት የራቀ ነው ያሉት ምንጮች፣ በቋሚ ሲኖዶስ በጸደቀውና ተግባራዊ በተደረገው መካከል ልዩነት እንደሌለ፣ ካለም በክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች በሥራ አስኪያጅነት ተመድበው የነበሩትን ሦስት የቀድሞው አ/አ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጆች ወደ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት መልሶ ካለፈው ጊዜ አፈጻጸማቸው አንጻር ከገንዘብ ጋራ በማይገናኙበት ዋና ክፍል በሓላፊነት ደረጃ የተመደቡበት ብቻ ነበር ብለዋል – ከሙስና ምንጮች ለማራቅ፡፡

*          *          *

ሀ/ስብከቱ በቋሚ ሲኖዶስ ባጸደቀው የለውጥ ሽግግር አስተዳደራዊ መዋቅሩ መሠረት በዘጠኝ ዋና የሥራ ክፍሎች ተዋቅሯል፡፡ መሠረታዊው የቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ የሚፈጸምባቸው የሰበካ ጉባኤ፣ ስብከተ ወንጌል፣ ክህነት፣ ሰንበት ት/ቤት፣ ቅርስ ጥበቃ እና ልማት ጉዳዮች ቅድምና ያገኙበት የሽግግር መዋቅሩ÷ መሠረታዊውን ተልእኮ ለመፈጸም ድጋፍ የሚሰጡት የአስተዳደር፣ ፋይናንስ፣ ዕቅድ ዝግጅት እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተግባራት አግባብነት ባላቸው ባለሞያዎች የሚመሩበት፣ የቁጥጥር አገልግሎቱ ሥልጣን ከአስፈጻሚው የተለየበት ብቻ ሳይኾን የጎለበተበት እንደኾነ ተገልጧል፡፡

ከዘጠኙ የሀ/ስብከቱ ዋና ክፍሎች መካከል አምስቱ መሠረታዊው የቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ (main functions) የሚፈጸምባቸው ናቸው፡፡ የዋና ክፍሎቹ ስያሜና ሓላፊዎቹ የሚከተሉት ናቸው፤

 • የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮና ማኅበራት ማደራጃ ዋና ክፍል – ሊቀ ኅሩያን ሠርጸ አበበ
 • የክህነት ጉዳይና ፍትሕ ዋና ክፍል – ንቡረ እድ አባ ዮሐንስ ገብረ ሕይወት
 • የሰበካ ጉባኤ ልማትና ምግባረ ሠናይ ዋና ክፍል – መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ
 • የሰንበት ት/ቤቶች ጉዳይ ዋና ክፍል – መ/ር ደምስ
 • ቅርስና ቱሪዝም ዋና ክፍል – ሊቀ ጉባኤ መሐሪ ጥበቡ

ናቸው፡፡ በፍትሕ መንፈሳዊ ክፍሉ የሚመራውን መንፈሳዊ ፍ/ቤት በነገረ መለኰት ዲፕሎማና በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው መ/ር ባሕሩ ተፈራ ያስችሉታል፡፡

Organizational Structure of the A.A Diosces

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አስተዳደራዊ መዋቅር

የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ማኅበራት ማደራጃ ዋና ክፍሉ÷ የኅትመት ዝግጅትና ሥርጭት፣ የስብከተ ወንጌልና ማኅበራት ማደራጃ የተሰኙ ሁለት ክፍሎች አሉት፡፡ ኆኅተ ጥበብ የተሰኘውን የሀ/ስብከቱን መጽሔት በማዘጋጀትና በማሠራጨት፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን በበላይነት ከማስተባበር ባሻገር ስለተለያዩ ዓላማዎች ተቋቁመው በሀ/ስብከቱ ክልል ለሚንቀሳቀሱ መንፈሳውያን ማኅበራት ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋራ በመቀናጀት ፈቃድ የመስጠት፣ የማደራጀትና የመቆጣጠር ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት መንፈሳዊ የጉዞ መርሐ ግብሮችን በማዘጋጀት፣ በበጎ አድራጎትና መሰል መንፈሳዊ አገልግሎት ዙሪያ የተደራጁ 36,000 ያህል ማኅበራት በሀ/ስብከቱ እንደሚንቀሳቀሱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የክህነት ጉዳዮች፣ ፍትሕ መንፈሳዊ እና የሕግ አገልግሎት የተሰኙ ሦስት ክፍሎች አሉት – የክህነት ጉዳይና ፍትሕ ዋና ክፍል፡፡ በተለይ የክህነት ጉዳይ ክፍሉ በሀ/ስብከቱ ክልል በማንኛውም ደረጃ የሚሰጥ ሥልጣነ ክህነት ከክፍሉ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ዕውቅና ውጭ እንዳይፈጸምና ማዕከላዊነቱ እንዲጠበቅ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ ተግባሩን ለማከናወን ከክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች በእነርሱም በኩል ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ጋራ በቅርበት የሚሠራ ሲኾን ለሥልጣነ ክህነት የቀረቡ አገልጋዮች በሞያው ተፈትነው፣ ብቃታቸውና አግባብነታቸው ተረጋግጦ በረዳት ሊቀ ጳጳሱ እንዲሾሙ ያደርጋል፡፡ የክፍሉ የፍትሕ ዘርፍ የሕግ አገልግሎት እና ፍትሕ መንፈሳዊ (መንፈሳዊ ፍ/ቤት) ሥራዎችን ያቅፋል፡፡ በሕግ አገልግሎቱ በኩል አስተዳደሩን በሕግ ጉዳዮች ያማክራል፤ በመንፈሳዊ ፍ/ቤት በኩል በመስኩ በሠለጠነ ዳኛ የዲስፕሊን ጉዳዮችን ይመለከታል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ ተልእኮዋን የምትፈጽምበት ፋይናንሳዊ አቅም በዋናነት ከሰበካ ጉባኤ አስተዋፅኦና ከሙዳይ ምጽዋት ገቢ የሚሰበሰብ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ኾኖ በምርት ውጤቶቻቸውና ማኅበራዊ አገልግሎታቸው ከፍተኛ ገቢ የሚያመነጩ፣ አሳዳጊ አልባ ሕፃናት ክብካቤ ለሚያገኙበትና አረጋውያን ለሚጦሩበት የምግባረ ሠናይ ረድኤታችን ሰፊ አቅም የሚፈጥሩ የልማት ተቋማትን ለማስፋፋት ሰፊ ዕቅድ ተይዟል፡፡ በክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች እና በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን (በጋራ ወይም በተናጠል) ደረጃ በስፋት የሚከናወኑትን እኒህ ተግባራት የፖሊሲ ሐሳቦች እያመነጨና አቅጣጫ እየሰጠ የሚመራው የሀ/ስብከቱ ሰበካ ጉባኤ ልማትና ምግባረ ሠናይ ዋና ክፍል ነው፡፡ ዋና ክፍሉ የልማት ተቋማት፣ ምግባረ ሠናይ እና ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ የተሰኙ ሦስት ክፍሎች ይኖሩታል፡፡

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ክብካቤ እና ልማት ማኅበር በቅርቡ ባካሄደው የምክክር ጉባኤ በልማት ስም በርካታ ቅርሶች ለጥፋት እየተዳረጉ እንደኾነ ተገልጧል፡፡ ለዚህም የአዲስ አበባ የጥንት ቤቶች መሠረተ ህልውናቸውን ከማጣት በላይ ሚናቸው ተለውጦ ሌላ አገልግሎት እየሰጡ ያሉበት ኹኔታ በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡

በጥገናና ክብካቤ ስም ሕንጻዎቻችንና ቅዱሳት ሥዕሎቻችን ከገጽታቸው ጀምሮ ጥንተ መልካቸው ጨርሶ የተለወጠበት ኹኔታ በቅዱስ ላሊበላ፣ በቆማ ፋሲለደስ፣ በወይዛዝርት ኪዳነ ምሕረትና በደብረ ወርቅ ኪነ ሕንጻ፤ በይምርሐነ ክርስቶስ፣ ጎርጎራ፣ ናርጋ ሥላሴ፣ ሞጣ ጊዮርጊስና ሽሬ እንዳሥላሴ አብያተ ክርስቲያን ቅዱሳት ሥዕላት አብነት ተብራርቷል፡፡

የመስቀሎቻችንና የብራና ጽሑፍ ሀብቶቻችን ቤተ ክህነቱ እንደ ተቋም በማይቆጣጠረው በዲጅታይዜሽን መሰነድ፣ በጥናትና ምርምር ሰበብ በጥቅመኛ ቀራፂዎችና ጸሐፊዎች እየተመዘበሩና በተቀሰጡ ሥራዎች (forgery) እየተተኩ መሰወራቸውንና እየተሰወሩ ስለመኾናቸው በ1970ዎቹ እና 1980ዎቹ በዩኔስኮ ተመዝግበው ዛሬ ለምስክርነት በማይገኙት የጎንደርና ጎጃም አብያተ ክርስቲያን በጽሕፈታቸውና ድጒሰታቸው መተኪያ የሌላቸው ብራናዎችና መስቀሎች ደብዛ መጥፋት ተረጋግጧል፡፡ ይህም በታወቁትና በተመዘገቡት ቅርሶች ደረጃ ለመናገር ያህል እንጂ ምንነታቸው ሳይታወቅና ማንነታቸው ሳይመዘገብ እየተሰወሩ ያሉት ቅርሶች ቁጥር የላቸውም፡፡

ለዚህ ሁሉ ጥፋት÷ መንግሥት ለታሪክና ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዋፅኦ ያለው አመለካከት ተተችቷል፤ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ቅርስን ከመመዝገብ ባለፈ ሚናውን በበቂ አለመወጣቱ አሳዝኗል፤ በቁጥር እየተበራከቱ ናቸው የተባሉ የቅርስ ቀሳጮች፣ ቅርስን መከባከብ ከዘመድ መቃብር ዕድሳት የማይለዩና በገንዘባቸው እያዘዙ ያሻቸውን (ለምሳሌ፡- ካቴድራልን ማስፋፋት፣ የሣር ክዳንን በቆርቆሮ መለወጥ) ከመሥራት በቀር የቅርስ ባለሞያዎችን የማያማክሩ ባለሀብቶች ተወቅሰዋል፤ ከሁሉም በላይ ተጠያቂ የተደረገው ግን የቅርስ ጥናትና ጥበቃን የሚመለከተው የቤተ ክህነቱ መምሪያ ነው፡፡

ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከታቸው ምሁራን ዝግ ነው የተባለው መምሪያው ክፍት የኾነው ቅርሱን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ተጠቃሚነትና ባለቤትነት አውጥተው ለራሳቸው ለሚያደርጉ ጥቅመኞች ነው፤ መንፈሳዊና ቁሳዊ ቅርሱን መሠረት ላደረገው ቱሪዝምም ቸልተኛ ነው፡፡ አስጎብኚዎች ለቱሪስቶች በሚያደርጓቸው ገለጻዎች የሚታዩ ስሕተቶችን ለማረም እንኳ ይህ ነው የሚባል እርምትና ሥልጠና ሲሰጥ አይታይም፤ ሲከፋም ቱሪዝሙ የቤተ ክርስቲያን ቅርስ ለሚነገድበት የተመራማሪ ነን ባይ ጥቅመኞች ሽፋን የሚኾንበት አጋጣሚም እንዳለ ተመልክቷል፡፡

የምክክሩ ተሳታፊ የነበሩ ምሁራን እንደገለጹት፣ አገራችን በሚገባ ካልተጠቀመችባቸው ሀብቶች አንደኛው የውኃ ሀብቷ ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ የቱሪስት መስሕቦቿ ናቸው፡፡ የቅርሶች ሙዝየም በኾነችው አገራችን የመንፈሳዊ ማንነታችን መሠረቶች የኾኑት የቤተ ክርስቲያናችን ሀብቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ፤ ነገር ግን እንደ ጨው ገደል እየተናዱ ናቸው፡፡

በመኾኑም ቤተ ክህነቱ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ነድፎ፣ የሰው ኀይልና ፋይናንሳዊ አቅሙን አጎልብቶ፣ ባለድርሻ አካላትን ለይቶ÷ በሕግ፣ በትምህርትና ጉትጎታ፣ በጥበቃና ክብካቤ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በቱሪዝም ረገድ በተለይ የተማረው የዘመኑ ትውልድ የቅርሶቹን መንፈሳዊ እሴት፣ ሳይንሳዊ ፋይዳና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በጥልቀትና በስፋት ያውቃቸው ዘንድ ብልሆች ልጆቿ ተባብረው መሥራት እንደሚገባቸው በአጽንዖት ተገልጧል፡፡

ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት መሠረታዊ መዋቅሮች አንዱ ቅርስና ቱሪዝም ዋና ክፍል ነው፡፡ በተለይ የቅርስ ክፍሉ በመዲናዪቱ ታዋቂ ቤተ መዘክሮች ከሚገኙት ቅርሶች በተጨማሪ መታወቅ፣ መመዝገብና መጠናት የሚገባቸው ሌሎች በርካቶች እንዲታሠሡ፣ እንዲታወቁ፣ ተመዝገበው እንዲጠበቁና እንዲጠኑ ከማድረግ አንጻር አብነታዊ ሥራ እንደሚሠራ ተገልጧል፡፡ በሌላ በኩል የቱሪዝም ክፍሉ እንደ መስቀል ደመራ እና ጥምቀተ ክርስቶስ ያሉ ዐበይት እና ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት የሚታይባቸው በዓላት የሚያስገኙትን የብዙኀን መድረክ በአግባቡ ከመጠቀም ጋራ በደማቅ ኹኔታ እንዲከበሩ የማድረግ ተግባርም ይኖረዋል፡፡

ከ156 – 174 በሚቆጠሩት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አድባራትና ገዳማት ከ131 በላይ ሰንበት ት/ቤቶች ይገኛሉ፡፡ በሰንበት ት/ቤቶቹ ታቅፈው የሚማሩና የሚያገለግሉ ሕፃናትን፣ ወጣቶችንና ጎልማሶችን አገልግሎት፣ ትምህርትና ሥልጠና በበላይነት የሚያስተባብረው የሀ/ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች ጉዳይ ዋና ክፍል ነው፡፡ ዋና ክፍሉ በአሠራሩ የሕፃናት፣ ወጣቶች እና ጎልማሶች ተብለው የሚከፋፈሉ ሦስት ክፍሎች ይኖሩታል፡፡ ይህም የወጣቶችና ጎልማሶች ዕድሜ ክልልን አስመልክቶ ከሚነሡ ጥያቄዎች አኳያ በቃለ ዐዋዲው የሰንበት ት/ቤት አባላት ዕድሜ ከ4 – 30 መኾን እንዳለበት የተቀመጠው ገደብ በማሻሻያው የመታየቱን አስፈላጊነት የግድ ያደርገዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን ቀጥተኛ ተልእኮ የሚተገበሩባቸውን እኒህ ዋና ዋና ተግባራት (core functions) የሚፈጽሙት መሥመራዊ ክፍሎች (Line Positions) ክህነታዊ ሥልጣንና ሞያ ባለው በሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የበላይነት ይመራሉ፤ በፓትርያሪኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ርእሰ መንበርነት በየጊዜው/እንዳስፈላጊነቱ የሚሰበሰበውን የሀ/ስብከቱን መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ (ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ) ያቋቁማሉ፡፡ የወቅቱ የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት ናቸው፡፡ ሹመታቸው ከምደባው የቀደመ ቢኾንም ለቦታው ከተዘረዘረው መስፈርት መካከል ሥልጣነ ክህነት፣ ዲፕሎማ እና 10 ዓመት የሥራ ልምድ፣ 4 ዓመት በተመሳሳይ ሓላፊነት ደረጃ የሠራ የሚለውን መመዘኛ እንደሚያሟሉ ተገልጧል፡፡

የሀ/ስብከቱ ቁጥጥር አገልግሎት ተጠሪነቱ በዓመት አንዴ ለሚሰበሰበው ለሀ/ስብከቱ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እና ጉባኤውን በርእሰ መንበርነት ለሚመሩት ለሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ተደርጓል፡፡ ይህም በተለመደው የአህጉረ ስብከት አሠራር ተጠሪነቱ ለሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የኾነውን የቁጥጥር አገልግሎት ሓላፊውን ከአስፈጻሚው አካል ተጽዕኖ በመጠበቅና በመለየት፣ የቁጥጥርና ሚዛን ሥርዐቱን ጠንካራ በማድረግ ሀ/ስብከቱ ድክመቱን በወቅቱ እያረመና አቋሙን ጤናማ እያደረገ ለመሄድ እንደሚረዳው ይታመናል፡፡

ለቁጥጥር አገልግሎት ሓላፊነት የተቀመጠው መስፈርት÷ ከመሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ዕውቀት ጋራ በአካውንቲንግ ዲፕሎማና 8 ዓመት የሥራ ልምድ ወይም ዲግሪና 6 ዓመት የሥራ ልምድ ከዚህም ውስጥ 2 ዓመት በተመሳሳይ ሓላፊነት የሠራ የሚል ነው፡፡ በአሁኑ ምደባ የቁጥጥር አገልግሎት ሓላፊ የኾኑት መ/ር ገብረ መስቀል ድራር በአካውንቲንግ ዲፕሎማ ያላቸው፣ በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሒሳብና በጀት መምሪያ ብቻ ከ6 ዓመት በላይ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ተዘግቧል፡፡ በዘገባዎቻችን እንዳስነበብነው እኚኽ ሓላፊ ከከፋ ምዝበራና ብልሹ አሠራር ጋራ ስማቸው ተያይዞ የሚነሣ ከመኾኑ አኳያ ይህን ከፍተኛ ሓላፊነት ላይ መቀዳጀታቸው ሌሎች ምደባዎችም በጥንቃቄ መጤን እንዳለባቸው የሚጠቁም ይኾናል፡፡

በሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ የሚሳተፈው የሀ/ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተጠሪነቱ ለሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡ በአገልግሎት መልክ የተቋቋሙትን የጽ/ቤቱን አስተዳደራዊና ሞያዊ (managerial and technocratic) ድጋፍ ሰጭ ክፍሎች በበላይነት የሚያስተባብር ቀጥ ያለ ባለሞያ ነው፡፡ እስከ አሁን በሓላፊነቱ ላይ የሚቀመጠው ሰው ተለይቶ ባይታወቅም ለቦታው የወጣው መስፈርት ምክትል ሥራ አስኪያጁ÷ በማኔጅመንት ዲፕሎማና 10 ዓመት ልምድ ወይም በማኔጅመንት ዲግሪና 8 ዓመት የሥራ ልምድ ያለውን፣ ከዚህም ውስጥ 4 ዓመት በተመሳሳይ ሓላፊነት ደረጃ የሠራውን የሚጠይቅ ነው፡፡ ሥልጣነ ክህነት በመስፈርቱ ባይካተትም መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ዕውቀት ያለው መኾን እንዳለበት ተመልክቷል፡፡

ምክትል ሥራ አስኪያጁ በአስተዳደር ጉባኤው ስብሰባዎች ተሳትፎው ያለድምፅ ነው፤ ከእርሱም ጋራ የሰው ኀይል አስተዳደርና ፋይናንስ ክፍል ሓላፊው በስብሰባዎቹ የሚገኝ ሲኾን በአስረጅነት የሚሳተፍ ነው፡፡ የድጋፍ ሰጪ ክፍሎቹ (Support positions) በቁጥር ሦስት ሲኾኑ ከሓላፊዎቻቸው ጋራ የሚከተሉት ናቸው፤

 • የሰው ኀይል አስተዳደርና ፋይናንስ ክፍል – መ/ር ዮናስ ፍቅረ
 • የዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ክፍል – ሊቀ ብርሃናት ኀይሉ የማነ
 • የዶክመንቴሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል – ወ/ሮ የትናየት አሰፋ

ናቸው፡፡ የሰው ኀይል አስተዳደርና ፋይናንስ ክፍሉ ከሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ጀምሮ መላው የሀ/ስብከቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በሚወጣላቸው ደረጃ መሠረት÷ የአገልጋዮች ቁጥር ምጣኔው/ትመናው፣ የደመወዝና ጥቅማጥቅሙ፣ ቅጥር፣ ዝውውርና ዕድገት ሥርዐቱ ወጥነት እንዲኖረው ይሠራል፡፡ ባለፉት ጊዜያት ለሥራ ሲባል ሳይኾን ለሰው ሲባል ሲፈጸሙ በቆዩ ቅጥሮች ሳቢያ በየደረጃው አለቅጥ በተከማቸው የሠራተኛ ቁጥር ሳቢያ በአጭር ጊዜ የሚፈጸም አዳዲስ ቅጥር እንደማይኖር ተመልክቷል፡፡ በምትኩ፣ በአዲስ መልክ የሚተከሉ አብያተ ክርስቲያንንና አብያተ ክርስቲያኑ በጋራና በተናጠል የሚያቋቁሟቸውን የልማት ተቋማት ማእከል አድርጎ፣ በተለይ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ከልክ በላይ የተከማቸውን የሰው ኀይል ብዛት በተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እያበቁ በዝውውርና ዕድገት የማሸራሸትና የማተካከል ሥራ እንደሚሠራ ይጠበቃል፡፡

ሌላው የሀ/ስብከቱ ድጋፍ ሰጭ መዋቅር የዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ክፍል ነው፡፡ በዚህ ክፍል ከአጭር ጊዜ እስከ ስትራተጅያዊ ዕቅድ ያሉት የሀ/ስብከቱ ቁልፍ ተግባራት እና ዝርዝር ሥራዎች ታህታይ መዋቅሩን ባሳተፈ፣ በጀቱም ከፋይናንስ ክፍሉ ጋራ በተቀናጀና በሚለካ አኳኋን እንዲዘጋጅና እንዲጸድቅ ይደረጋል፡፡ በበጀት የተደገፉት ዕቅዶች ከጸደቁ በኋላ የአፈጻጸም ሂደታቸውን ለመከታተልና አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል የክትትል፣ ድጋፍና ግብረ መልስ ሥርዐት ይዘረጋል፡፡ በዚህ ረገድ የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የዕቅድና ልማት መምሪያ ቤተ ክርስቲያናችን የምትገኝበትን ተጨባጭ ኹኔታ የተነተነበትና ይህን በተገነዘበ አኳኋን በመምሪያዎችና በአህጉረ ስብከት ደረጃ መከናወን ስለሚገባቸው ሥራዎች ዐቢይ ተግባርና የአፈጻጸም አቅጣጫ የለየበት የ፳፻፮ ዓ.ም. በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ እንደመነሻ ሊያገልግል ይችላል፡፡

እንደ ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ሁሉ ለሀ/ስብከቱ በአዲስ መልክ የተቋቋመው የዶክመንቴሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል የሽግግር መዋቅሩ ክሥተት ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ክፍሉ ቤተ ክህነታችን ከላይ እስከ ታች ክፉኛ የሚተችበትን የመሠረታዊ መረጃዎች አያያዝ ድክመት በማስቀረት÷ ከሀ/ስብከት እስከ አጥቢያ ትይይዙ የተጠናከረና ማዕከላዊነቱ የጠበቀ፣ ወቅታዊነቱና አግባብነቱ የተረጋገጠ፣ ተደራሽነቱ የተቀላጠፈና ዘመኑን የዋጀ ምሳሌያዊ ሥራ እንደሚሠራ ተስፋ ተደርጓል፡፡

በዚህም የሀ/ስብከቱ አገልጋዮች፣ ምእመናን፣ አብያተ ክርስቲያንና መሰል ስታቲስቲካዊ መረጃዎች በዘመናዊ መንገድ ይደራጃል፡፡ ዋና ዋና ክፍሎችና ድጋፍ ሰጭ መዋቅሮች እንደየሚናቸው ክፍሉ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሚሰጠው አገልግሎትና እገዛ ተጠቃሚ ይኾናሉ፡፡ የሀ/ስብከቱን መሠረታዊ መረጃዎችና ወቅታዊ እንቅስቃሴዎች በሚዲያዊ ሥራዎች ከማሳወቅ አንጻርም የራሱ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፡፡

ከዚሁ የዶክመንቴሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል መደራጀትና መጠናከር ጋራ በተያያዘ÷ ጠቅላላ የጽሕፈት፣ መዛግብትና ማኅደረ ጉዳዮችን የመሥራትና የመጠበቅ፣ የአስተዳደር ጉባኤ ስብሰባዎችን ቃለ ጉባኤ የመያዝ፣ የክፍሎችን የሥራ ክንውን በመከታተልና ስታቲስቲካዊ መረጃዎችን በማጠቃለል ለአስተዳደር ጉባኤው ወቅታዊ ሪፖርት የማቅረብና መሰል የጽ/ቤት ሥራዎች ይሠራበት የነበረው የጸሐፊ ሥራ መደብ በሀ/ስብከት ይኹን በክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ደረጃ እንዲቀር መደረጉ/አለመካተቱ ነው የተጠቆመው፤ ቃለ ጉባኤ መያዝና ደብዳቤዎችን ማርቀቅ ጨምሮ ያሉት የጸሐፊው የሥራ ዝርዝሮችም በየክፍሎቹ ይፈጸማሉ ማለት ነው፡፡ ከሀ/ስብከት እስከ አጥቢያ የሙስናውና ብልሹ አሠራሩ መሽከርከሪት የኾነው ይህ የሥራ መደብ በሽግግር መዋቅሩ መቅረቱ በለውጡ ተከታታዮች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ ተችሮታል፤ ለዘላቂውም በዚያው እንዲያስቀረው!!

*          *          *

በቀደሙት ዘገባዎች እንደተጠቆመው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በሰባት የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ተደራጅቷል፡፡ ከሚናው አኳያ በቃለ ዐዋዲው የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ከሚለው ጋራ ሊነጻጸር የሚችለው ይኸው የክፍለ ከተማ አደረጃጀት፣ በክፍለ ከተማው ክልል ውስጥ ለሚገኙት ገዳማትና አድባራት እንዲሁም በየደረጃው ለተቋቋሙት ሰበካ መንፈሳውያን ጉባኤያት የሥራ አመራርና ከፍተኛ የአስተዳደር ሓላፊነት ያለው መሥሪያ ቤት ነው፡፡ በሥሩ የተካተቱት ገዳማትና አድባራት÷ በቃለ ዐዋዲው መሠረት በሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ የማደራጀትና የማጠናከር፣ መርሐ ግብር እያዘጋጀ ወንጌልን በመስበክና በማሰበክ ምእመናንን የማንቃትና የማትጋት፣ የአብያተ ክርስቲያናቱን ስታቲስቲካዊ መረጃዎች፣ የበጀት ዓመቱን የሥራ ክንውንና የፋይናንስ ሪፖርት ለሀ/ስብከቱ በወቅቱ ማቅረብ ያለበት ነበር፡፡

ይኹንና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ የርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ መክፈቻ ንግግር ላይ እንደተመለከተው፣ ይኸው ሥልጣኑና ተግባሩ ስላልተጠበቀለት ችግሩ እየገዘፈ ለከፋ የመልካም አስተዳደር ዕጦት መንሥኤ ኾኗል፡፡ በአሁኑ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሽግግር አደረጃጀት መዋቅሩ ሥልጣኑ ተጠብቆለት ተግባሩን ተጠያቂነት፣ ግልጽነትና ሓላፊነት ባለበት አኳኋን ለመወጣት የሚያስችለው ጠንካራ የአስተዳደር ሥርዐት ለመዘረጋት ጥረት እየተደረገ መኾኑ ተመልክቷል፡፡ በዚህም መሠረት ሰባቱ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች÷ አራት የመሠረታዊ ተልእኮ ማስተባበርያዎችንና ሦስት የድጋፍ ሰጭ ክፍሎችን ይዘው ተደራጅተዋል፡፡

አራቱ የዋና/መሠረታዊ ተልእኮ ማስፈጸሚያ መዋቅሮች÷ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ማስተባበርያ፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃና ማስተባበርያ፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃና ማስተባበርያ እና የቅርስና ንብረት ክፍል ሲኾኑ ድጋፍ ሰጪዎቹ ደግሞ ሒሳብ በጀትና ዕቅድ ክፍል፣ የሰው ሀብት አስተዳደር ክፍል እንዲሁም ልማትና ምግባረ ሠናይ ክፍል ናቸው፡፡ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ተጠሪነቱ ለሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የኾነ የክፍለ ከተማ ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባኤ ይኖራቸዋል፤ በክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች አስተዳደራዊ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው የቁጥጥር ሓላፊውም ተጠሪነቱ ለሀ/ስብከቱ ቁጥጥር አገልግሎት ነው፡፡ አንድ የክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ከ13 – 15 አጠቃላይ የሰው ኀይል አለው፡፡ እንደ ሀ/ስብከቱ ሁሉ እዚህም የጸሐፊ ሥራ መደብ ቀርቷል፡፡

ሀ/ስብከቱ በሰባት ክፍለ ከተሞች እንዲደራጅ ሲደረግ ለአከፋፈሉ ዋነኛ መነሻ የተደረገው የከተማ አስተዳደሩ ክፍለ ከተሞች አወቃቀርና በውስጣቸው የያዟቸው አብያተ ክርስቲያን ብዛት ናቸው፡፡ በታወቀ መነሻ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የሚገኙት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ከ156 በላይ ናቸው፡፡ ክፍለ ከተሞቹ ከያዟቸው የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ብዛት አንጻር በሰባት የተጠቃለሉት የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶችና የተመደቡላቸው ዋና ሥራ አስኪያጆች የሚከተሉት ናቸው፡-

 • አራዳ ጉለሌ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት – ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ
 • የካ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት – ሊቀ መኳንንት ብርሃኑ ጌጡ
 • ቦሌ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት – ላእከ ወንጌል በዕደ ማርያም ይትባረክ
 • ኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት – ሊቀ ሥልጣናት ወልደ ሰንበት አለነ
 • ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት – መጋቤ አዕላፍ ማሙዬ ሸዋ አፈራ
 • ልደታ ቂርቆስ አዲስ ከ/ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት – መ/ሰላም አባ አእምሮ ታከለ
 • አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት – መልአከ ምሕረት አምኃ መኳንንት

በዘላቂው የሀ/ስብከቱ መዋቅር የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት እስከ አሁን በተለምዶ ከሚሠራበት የገቢ ደረጃ ባሻገር በዝርዝር በሚዘጋጀው መመዘኛ መሠረት ደረጃ ይወጣላቸዋል፡፡ በዚህም ላይ ተመሥርቶ የተመጣጠነ የሰው ኀይል እና የፋይናንስ አቅም ባላቸው አብያተ ክርስቲያን ጥንቅር የሚደራጁት የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች በውድድር መንፈስ እንዲሠሩ ለማድረግ መታቀዱ ተመልክቷል፡፡ በውድድሩ አጥጋቢ ውጤት የሚያስመዘግቡ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶችና ሓላፊዎቻቸውም ደረጃ ወጥቶላቸው ዕድገትና ማበረታቻ እንደሚሰጣቸው ተገልጧል፡፡

*          *          *

በአጠቃላይ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በወሰነው መሠረት በቋሚ ሲኖዶስና በመንበረ ፓትርያሪኩ ጥብቅ ክትትል እየተደረገበት ያለው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በመልካም አስተዳደር፣ በፋይናንስ አያያዝና በሰው ኀይል አመዳደብ ሞዴል መኾን የሚችልበትን አቅጣጫ እየያዘ ነው፡፡ የሀ/ስብከቱ የሽግግር ወቅት አስተዳደራዊ መዋቅር ትኩረታቸውን የሳባቸው እንደ ባሕር ዳርና አዊ ዞን አህጉረ ስብከት ያሉት እንኳ ገና ከወዲሁ ከሞዴሉ አዲስ አበባ ልምድ ለመቅሰም እያሰቡበት መኾኑ ተሰምቷል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ የመዋቅር ዝርጋታውን የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቅ አስመልክቶ በሥራው የተሳተፉ ኤክስፐርቶችን ባመሰገኑበት አጋጣሚ እንደተናገሩት፣ የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ መዋቅሩ በተጀመረበት አኳኋን ቀጥሎ ጠዋት ማታ ከተሠራበት ወደ ሌሎች አህጉረ ስብከት የማይስፋፋበት ምክንያት አይኖርም፡፡

ከዚህ በኋላ በአንድ በኩል በአስተዳደራዊ መዋቅሩ በምደባ የገባው የሰው ኀይል ወደ ሥራ ተሠማርቶ አቅሙን እየፈተሸ ተሞክሮ ይቀስማል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተቋማዊ ለውጡን ቀጣይነት የሚያረጋግጥ የአምስት ዓመት ስትራተጅያዊ ዕቅድ ከፖሊሲ እና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያዎች (የሰው ኀይል፣ የፋይናንስ፣ የኦዲትና ኢንስፔክሽን፣ የክትትልና ድጋፍ፣ የዕቃ ግዥ ማኑዋሎች. . .ወዘተ) ጋራ መዘጋጀቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል – አዲስ አበባ ያብባል ገና. . . 

ነገር ግን፣ ነገር ግን ዋናው ሀብትና የለውጥ ኀይል ያለው በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ነውና የላዩን መዋቅር የምናሳምረው የቆመበትን መሠረት ዘንግተን መኾን የለበትም፡፡ ሰሞኑን በስፋት የተካሄደው ሙሰኛና ዐምባገነን አስተዳዳሪዎችን ያለአንዳች ተጠያቂነት ከአንዱ ወደ ሌላው የማዘዋወር ኹኔታ ሀ/ስብከቱን ለትችት እንዳጋለጠው ሳይጠቅስ የሚታለፍ አይደለም፡፡

 • ከደብረ ጽጌ ቅ/ዑራኤል ወደ ቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል በቅዳሴ ጸሎት አሳራጊነት የተቀየሩትን አስተዳዳሪ የተኩት የቀድሞው የደብረ ነጎድጓድ ቅ/ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ÷ ሀ/ስብከቱ ለክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የቢሮ ዕቃዎች ማሟያ በፈጸመው የሚልዮን ብር ዕቃ ግዥ ኮሚቴ ውስጥ የተካተቱት፣ በገቢ አቅሙ ቀዳሚ ወደ ኾነው ታላቅ ደብር የተዘዋወሩት በየትኛው መታመናቸው ነው?
 • ርምጃው ካልነካቸው የሙስና ጌቶች መካከል የደብረ ብሥራት ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ÷ ባለሁለት ሚኒባስ፣ ሁለት ሃይገር/በቅርቡ ሸጠውት ኮንዶሚኒየም ገዝተውበታል/ ባለቤት የኾኑት፣ በሰንዳፋ ‹‹ቄሶች ሰፈር›› ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ከሲ.ኤም.ሲ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ እና ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ጎን ለጎን ያን የመሰለ ቤት የሠሩት በግል ገንዘባቸው ይኾን???

አዲስ አበባ በለውጥ አደረጃጀት በሥልጡን አመራር ያብባል ገና!

Advertisements

7 thoughts on “አዲስ አበባ በለውጥ አመራር ያብባል ገና

 1. Anonymous August 11, 2013 at 6:21 pm Reply

  good news!!!

 2. Anonymous August 12, 2013 at 1:12 am Reply

  cher were yaseman endih enji yibel yasegnal ye ewnet yadirgew

 3. Anonymous August 12, 2013 at 2:17 pm Reply

  leboch !! enate !!

 4. Anonymous August 12, 2013 at 2:22 pm Reply

  እንዲህ ያለውን ቸር ዜና ያሰማን ::እግዚአብሔር ቤተክርስትያናችንን ከጠላት ዲያብሎስ ኃይሎች ይጠብቅልን ::በውስጣችን የተደበቁ ተኩላ ይንቀንልን ::

  ለጦማሪዎቹም እግዚአብሔር እድሜ ይስጣችሁ ::

 5. Anonymous August 13, 2013 at 2:29 am Reply

  melkam jmr now. des blognal.EGZIABHER yrdachhu.

 6. Anonymous August 13, 2013 at 12:06 pm Reply

  ዜናው መልካም ነው ነገር ግን ስጋቴ እንዲህ ያለውን ለውጥ የማይፈልጉና ሀ/ስብከቱ እንደ ቀድሞ ጫካ ሆኖ ሙስናቸውን በዚያ ለመደበቅ የሚፈልጉ አንዳንድ የደብር አለቆች እዲሁም አንዳንድ ቀደምት የሀ/ስብከቱ “ሰራተኞች” ይህን ለውጥ ለመጣል የሚያደርጉት ደባ ለሊቀ ጳጳሱ ትልቅ ፈተና ይሆንባቸዋል ባይ ነኝ፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነቱ ሰዎች አሁንም በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ጉዳዩን በማንሳት መዋቅሩን ለማፈራረስ /አንዳንድ ወሬ ሰሚ ጳጳሳትን በማነሳሳት/ትልቅ አድማ ላይ መሆናቸው አሳዛኙ ዜና ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንን ሰላም ያድርግልን

 7. Asnake Feleke August 14, 2013 at 10:26 am Reply

  Egziaber Amlak yekeberyemesgenina ketayeseraw betam kebadeselhon selotmihila behulum betekeristiyanatena gedamat liyaz yesfeligal endihum meemenanen betlot enditegu mabertata yesefelgal. Abetu yetadikan, yesemaeitate, yekidusan melaeket, beatekaley yekidusan amlak selemberihan ena selwedajochu sill hagerachen, betecrtinyanachen ena hizibochwan yetbikilen amen.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: