የደቀ መዛሙርቱ የምረቃ ቀን ጥያቄዎች እና ጥቅሶች ምን ያመለክታሉ?

 • የኮሌጁ ቦርድና የበላይ ሓላፊ መመስገን የምሩቃኑን ጉርምርምታን አሰምቷል
 • የአስተዳደሩን ሙሰኝነት በቅኔው የነቀፈው ምሩቅ ፓትርያሪኩ የጀመሩትን ርምጃ ከዳር እንዲያደርሱ ጠይቋል
 • ‹‹ጌታ ሆይ፣ ለቤተ ክርስቲያን ቅን መሪ የምትሰጥ መቼ ይኾን?›› /ምሩቃኑ ካሰፈሯቸው ጥቅሶች አንዱ/
 • ‹‹በተመደብንበት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሁሉ ሕግንና ሥርዐትን መሪ አድርገን ለመሥራት፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን በቅንነት ለማገልገል፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርተ ሃይማኖት ለማስፋፋት፣ ልማቷንና ዕድገቷን ለማፋጠን ቀን ከሌሊት የምንሠራ መኾናችንን በእግዚአብሔር ፊት ቃል እንገባለን፡፡›› /ከባዱ የተመራቂዎች ቃለ መሐላ/
Aba Yohannes Worku, Gold Medalist of the Class 2005

አባ ዮሐንስ ወርቁ
በ3.93 እጅግ ከፍተኛ ማዕርግ ልዩ ተሸላሚ

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በቀኑ መደበኛ እና በማታው ተከታታይ መርሐ ግብር ያስተማራቸውን 194 ደቀ መዛሙርት ትላንት ቅዳሜ፣ ሐምሌ ፳፯ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ከስምንት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ በተገኙበት አስመርቋል፡፡

ከ194 ምሩቃን መካከል 54 የቀን መደበኛ ዲግሪ መርሐ ግብር፣ 44 በማታው ተከታታይ ዲግሪ መርሐ ግብር፣ 91 በማታው ተከታታይ የዲፕሎማ መርሐ ግብር እና 5 በግእዝ ቋንቋ የዲፕሎማ ደቀ መዛሙርት ናቸው፡፡

ለተመራቂዎቹ ዲግሪና ዲፕሎማ ለማዕርግተኞች ደግሞ ልዩ ሽልማት የሰጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ እጅግ አድካሚና ከፍተኛ ትጋት የሚጠይቀውን ትምህርተ ሃይማኖት ለሁለት እና አምስት ዓመታት በዲግሪና ዲፕሎማ መርሐ ግብር ተከታትለው ለምረቃው በዓል የደረሱትን ደቀ መዛሙርት እንኳን ደስ አላችኹ ብለዋል፡፡ ‹‹መከሩ ብዙ ሠራተኛው ጥቂት ነው›› የሚለውን ቃለ ወንጌል በመጥቀስ ብዙ የወንጌል ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ ለዚህም የመከሩን ባለቤት መለመን እንደሚገባ ቅዱስነታቸው አመልክተዋል፡፡ ‹‹ልጆቻችን በርቱ፤ እንድትበረቱ እንፈልጋለን›› ለሚለው ምክር አጽንዖት የሰጠው ንግግራቸውም በአጭሩ የተደመደመ ነበር፡፡

በምሩቃኑ መጽሔት ላይ የሰፈረው የቅዱስነታቸው መልእክት፣ ‹‹በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋራ ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀኽ ተከተል፤›› በሚለው የቅዱስ ጢሞቴዎስ ሁለተኛ ክታብ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በአስደናቂ የሰላም ጥበብ የተከናወነው የምድርና የሰማይ ፍጥረታት እንቅስቃሴ ተጠብቆ የሚኖረው አንዱ በሌላው ተግባር፣ ሌላው በሌላው ህልውና ጣልቃ ባለመግባት መኾኑን ያተቱት ቅዱስነታቸው፣ ህልውናው ከሰላም ጋራ በብዙ ድር የተሳሰረው የሰው ልጅም ማኅበራዊ ፍጡር ስለኾነ ከሚመስለውና በአርኣያ እግዚአብሔር ከተፈጠረው ሰው ጋራ በስምምነት መኖር እንደሚገባው፣ ሰላምን አጥብቆ መሻትና መከተል እንዳለበት ሐዋርያት በትምህርታቸው፣ ጠበብት በፍልስፍናቸው መመክራቸውን አትተዋል፡፡

የእግዚአብሔር ሕጉ፣ ትእዛዙ፣ ምክሩና ፈቃዱ ለፍጥረት ሰላምና ደኅንነት ስለኾነ የሰላም ዐዋጅ የኾነውን ወንጌልን ለምእመናን እንድታደርሱ ቤተ ክርስቲያን አስተምራ ለዚህ የምረቃ ቀን አብቃታችኋለችና የተቀበላችኁትን ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ በብቃት እንድትወጡ እግዚአብሔር አምላካችን እንዲረዳችኹ እንጸልያለን በማለት መልእክታቸውን አጠቃለዋል፡፡

ከቅዱስነታቸው አስቀድሞ ሰፋ ያለ ትምህርት የሰጡትና በፈሊጥ የተዋዛ ትምህርታቸው በቅዱስነታቸው የተመሰገነላቸው የምሥራቅ ጎጃም ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ ‹‹ከዚህ ስትወጡ የበለጠ መከራ ይጠብቃችኋል፤ እዚህ ትንሽ ተለማምዳችኋል፤ በትዕግሥታችኹ ነፍሳችኹን ታገኛላችኹ እንደተባለ በትዕግሥታችኹ ዲግሪያችኹን አግኝታችኋል፤›› በማለት የታለፈውን መከራ በማውሳታቸው ምሩቃኑ በጭብጨባ ምስጋናቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡

በአንጻሩ ምሩቃኑ ለደረሱበት ደረጃ የኮሌጁን የሥራ አመራር ቦርድና የበላይ ሓላፊ በማመስገን ሲናገሩ ከምሩቃኑ ተደጋጋሚ ጉርምርምታ ተሰምቷል፡፡ በጉርምርምታው ከንግግራቸው ምልስ ያሉት ብፁዕነታቸው፣ ‹‹እናንተ ያነሣችኁትኮ ጥቃቅኑን ነገር ነው፤ የቆብ ዘረኝነት አታድርጉብኝና ከፍተኛ ውጤት ያመጡት አባ [በ3.93 ከፍተኛ ማዕርግ የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚውን አባ ዮሐንስ ወርቁን] ደጋግመው ሽልማት ሲወስዱ ስመለከት ተመልሰኽ ት/ቤት ግባ ግባ አለኝ፤ እኚህ አባ ነገ ፓትርያሪክ ቢኾኑ ማን ይከፋዋል? ያው መተካካት ነው፤ ዝግባው ጳውሎስ ዓለም አቀፍ ጭንቅላት ይዘው አለፉ፤ ዛሬ ጽዱ ማትያስ ተተክቷል፤ ማትያስም ማለት ምትክ ማለት ነው፤ እኛም ጽዱ ሥር ነው ያለነው፤›› በሚል ማበላለጥ ምሩቃኑ የሚጠብቃቸውን ከፍተኛ አደራና ክብር ጠቁመዋል – የደቀ መዛሙርቱን ለወራት የዘለቁ ጥያቄዎችና በጥያቄዎቻቸው ያገኙትን ውጤት በማመቻመች ቢኾንም!

ከምሩቃኑ ቀጣይ ተልእኮ አንጻርም ‹‹ሑሩ ወመሐሩ ነው የተባላችኁት›› ያሉት ብፁዕነታቸው ‹‹ታዲያ አራት ኪሎ እንድትቀመጡ አይደለም፤ ዓለምን ዞራችኹ እንድታስተምሩ ነው›› በማለት ምሩቃኑ በምደባቸው እንዲሰማሩ አሳስበዋል፤ ለዓመቱ እንስት የምሩቃን ቁጥርም አጽንዖት በመስጠት፣ ‹‹ብዙ ተባዙ ተብሏል – ታዲያ በሌላ አይደለም፣ በዲግሪ ነው፤›› ሲሉ ምሩቃኑንና የምረቃውን ብዙኀን ታዳሚዎች ዘና አድርገዋል፤ እንስት ምሩቃኑ ሌሎች እኅትና እናት ደቀ መዛሙርትን በማብዛትና ተሳትፏቸውን በማጠናከር የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን በመርዳት ረገድ [በብፁዕነታቸው ዘይቤ – ጅግራ ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ እንዳይኾን]  የሚኖራቸውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አመልክተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ከበላይ ሓላፊነት ሥልጣናቸው እንዲገለሉ በቅ/ሲኖዶስ በተላለፈው ውሳኔ ምክንያት በምረቃው መርሐ ግብር የተገኙ ቢኾንም ‹‹የበላይ ጠባቂ›› እየተባሉ ከመጠራትና ቅዱስነታቸውን ከመጋበዝ ያለፈ ሚና አልነበራቸውም፡፡ ቅዱስነታቸውን በሚጋብዙበት ወቅትም የተቃውሞ ምልክት የሚመስሉ ድምፆች ከምሩቃኑ ተሰምተዋል፤ በሪፖርት መልክ የተዘጋጀውን የኮሌጁን መልእክት ያስተላለፉትም ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም መለሰ (ቀድሞ የኮሌጁ ምክትል ዋና ዲን) ናቸው፡፡

የምረቃውን አጠቃላይ መርሐ ግብር የሚመሩት አካዳሚክ ምክትል ዲኑ መ/ር ፍሥሓ ጽዮን ደመወዝ ቢኾኑም ከሓላፊነታቸው ተነሥተው በማስተማር እንዲወሰኑ በመደረጉ በአዳራሹ አልተገኙም፤ የተመራውም በኮሌጁ መምህር ግርማ ባቱ ነው፡፡ የቀኑን የዲግሪ መርሐ ግብር ምሩቃን የሚያቀርበው የክፍሉ ሓላፊ ዘላለም ረድኤት ቢኾንም ከሓላፊነቱ ተነሥቶ ከኮሌጁ እንዲወገድ በመወሰኑ ሥነ ሥርዐቱ የተከናወነው በኮሌጁ ቤተ መጻሕፍት ሓላፊ ቆሞስ አባ ጌድዮን ብርሃነ አማካይነት ነው፡፡ የማታውን ተከታታይ መርሐ ግብር የዲግሪና ዲፕሎማ ምሩቃን የክፍሉ ሓላፊ መ/ር ብርሃኔ ገብረ ጻድቃን፣ የግእዝ ቋንቋ ምሩቃንን መምህሩ ዘርዐ ዳዊት አድሃና አቅርበው አስመርቀዋል፡፡

የኮሌጁ ጊዜያዊ ሓላፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በመርሐ ግብሩ መጀመሪያ ላይ ምሩቃኑን እየመሩ ቃለ መሐላውን አስፈጽመዋል፡፡ ቃለ መሐላው ደቀ መዛሙርቱ÷ ቤተ ክርስቲያናችን በምትቀበላቸው ሦስቱ ዐበይት ጉባኤያት /ጉባኤ ኒቂያ፣ ጉባኤ ቁስጥንጥንያ፣ ጉባኤ ኤፌሶን/ የወሰኑትን አናቅጸ ሃይማኖት ለመጠበቅ፤ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ ቀኖናና ሥርዐት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ፣ በተመደቡበት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሁሉ አስተምህሮዋን ለማስፋፋት፣ ልማቷንና ዕድገቷን ለማፋጠን ቀን ከሌት ተግተው ለመሥራት የተፈጠሙበት ነበር፡፡

ቃለ መሐላው የያዘው አደራ ኤጲስ ቆጶሳት በቅ/ሲኖዶስ ሲሾሙ እንደሚገቡት ቃል ኪዳን ከባድ መኾኑ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ፣ በምሩቃንና በሁሉም የመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች ዘንድ ምስክርነት የተሰጠበት ነበር፡፡

የቃለ መሐላው ሙሉ ይዘት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዲግሪና ዲፕሎማ ተመራቂ ደቀ መዛሙርት ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረተውን፣ ቅዱሳን ሐዋርያት ያስተማሩትን፣ ሊቃውንት አበው በሦስቱ ጉባኤያት ማለትም በጉባኤ ኒቂያ፣ በጉባኤ ቁስጥንጥንያ እና በጉባኤ ኤፌሶን የወሰኑትን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን እምነት፣ ቀኖናና ሥርዐት ጠብቀን እናስጠብቃለን፡፡

እንዲሁም በተመደብንበት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሁሉ ሕግንና ሥርዐትን መሪ አድርገን ለመሥራት፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን በቅንነት ለማገልገል፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርተ ሃይማኖት ለማስፋፋት፣ ልማቷንና ዕድገቷን ለማፋጠን ቀን ከሌሊት የምንሠራ መኾናችንን በእግዚአብሔር ፊት ቃል እንገባለን፡

ያለንበት ዘመን የዓለም ፍጻሜ ምልክቶች ጎልተው እየታዩ ያሉበት፣ የሳምራውያን ከተሞች የተስፋፉበት፣ ከመንፈሳዊ ይልቅ ዓለማዊ ገጽታ ያየለበት፣ ከግራም ከቀኝም በሃይማኖት ተቀናቃኞቻችን የተከበብንበት መኾኑን በምረቃ መጽሔቱ ላይ በሰፈረ መልእክታቸው ያሳሰቡት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ÷ ምሩቃኑ በዚህ ፈታኝ ወቅት የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ መፈጸምና ማስፈጸም የሚችሉት ፈተና በበዛ ቁጥር እንደ ዴማስ ወደ ከተማ ጎራ በማለት ሳይኾን የጢሞቴዎስንና የቲቶን ፈለግ በመከተል፣ የእስጢፋኖስን ዓርማ በማንገብ የተጣለባቸውን ሓላፊነት መወጣት ሲችሉ ነው፡፡

ተልእኮን መፈጸም፣ ሓላፊነት መወጣት ማለትም ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልሞና በጻፈው መልእክቱ፣ ‹‹በመታዘዝኽ ታምኜ ካዘዝሁኽ ይልቅ እንድትጨምር ዐውቄ ጻፍሁልኽ›› /ፌል.፭÷፩/ እንዳለው ቤተ ክርስቲያን ካዘዛቻቸው አስበልጠው ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶ ፍሬ ያፈሩ እንደኾን፣ ‹‹እጃችኹ ከምን›› ተብለው የመክሊታቸውን ትርፍ ሲጠየቁ ምላሹ ከወይራ ዘይት ፍሬ፣ ከስንዴ እሸት ዘለላ እንጂ የሰነፉ አገልጋይ ዐይነት እንዳይኾን ከተጠነቀቁ ነው፡፡

ምሩቃኑ በበኩላቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩን ጨምሮ ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ አደራቸውን የሰጡትና ስሜታቸውን የገለጹት በቅኔ እና በምረቃ መጽሔታቸው ላይ በየሥዕለ ገጻቸው ግርጌ ባሰፈሯቸው ኀይለ ቃሎች ነው፡፡ በምረቃ መርሐ ግብሩ ወቅት ከመ ቅጽበት ተነሥተው ማዕበል ቅኔያቸውን ያዘነቡት ምሩቅ መሪጌታ ዐዲስ መሓ በሰምና ወርቅ፣ በንጽጽር እና ታሪክ/ነገሥት ተጣርቶ በቀርበው ሙሉ ቤት ቅኔያቸው÷ በፈርዖን የመሰሉት ሙስና እንዲወገድ፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ነነዌ ኾናለች፤ እሳት እየነደደባት ነው፤ ጳጳሳት ጹሙ ጸልዩ›› በማለት አሳስበዋል፡፡

አቡነ ጢሞቴዎስን ከፈርዖን ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስን ከሊቀ ነቢያት ሙሴ በማዛመድ በበትረ ሙሴዎ ከፍለው ያሻግሩን ሲሉ አመልክተዋል፡፡ ኮሌጁ እንዲዘጋ የፈረዱበትን የበላይ ሓላፊውንና ሌሎች የኮሌጁን አካላት ‹‹አብያተ ክርስቲያን ይትዐፀዋ›› ካለው ዲዮቅልጥያኖስ ጋራ በማመሳሰል ገሥጸዋል፤ ኮሌጁ እንዳይዘጋ የተሟገቱትን ብፁዕ አቡነ ሉቃስንና ብፁዕ አቡነ ማቴዎስን ‹‹አብያተ ክርስቲያን ይትረኀዋ›› ካለው ራትዕ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በማነጻጸር አወድሰዋል – ‹‹ኮሌጁን መዝጋት ቤተ ክርስቲያንን መዝጋት ነውና!››

በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ላይ የሚገኙት ባለቅኔው ዐዲስ ማዕበል ቅኔያቸውን ለማዝነብ ድንገት ወደ መድረኩ ገብተው ሲያስገመግሙ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ለማከላከል ሲሞክሩ ታይተዋል፤ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ እና ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ደግሞ በአንጻሩ በእጅ ምልክት አበረታተዋቸዋል፤ የቅኔ መምሩ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ጉጉትና ተመሥጦ ግን ከሁሉም ከፍ ያለ ነበር፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ባለቅኔውን አመስግነዋል – ‹‹ቅኔ ያቀረበው ልጅ አመሰግነዋለኹ፤ እኔን ስላመሰገነ ሳይኾን ሙስናን ስለደበደበልኝ፡፡››

ሌሎች ምሩቃን በምረቃ መጽሔታቸው ላይ ከየፎቶግራፋቸው ግርጌ ባሰፈሯቸው ኀይለ ቃሎች የቤተ ክርስቲያናቸውን ወቅታዊ ኹኔታ ከዚያም አንጻር የተሰማቸውን ስሜት አስተጋብተዋል፤ ተምኔታቸውን ገልጸዋል፤ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡-

 • ግን ቤተ ክርስቲያን አታሳዝንም! /አባ ኢያሱ ሰብስቤ/
 • የጳውሎስ ደቀ መዝሙር ጢሞቴዎስ መገረዝ ለአማኞች አስፈላጊ ነው (ግብ. ሐዋ. ፲፮÷፫)
 • ጌታ ሆይ! ለቤተ ክርስቲያን ቅን መሪ የምትሰጥ መቼ ነው?/አባ ሳሙኤል ክብረት/
 • እንግዲህ አትፍሯቸው፤ የማይገለጥ የተከደነ የማይታወቅም የተሰወረ የለምና /መሪጌታ ዐስበ ጻድቅ እሸቱ/
 • እግዚአብሔር ሆይ፣ ለሀገሬ መልካም ሥራ ሳልሠራ እንዳልሞት እለምንሃለኹ /መሪጌታ አዲስ መሓሪ/
 • በዚህ ጊዜ የምለውን አልልም /ዲያቆን ኀይለ ጽዮን መንግሥቱ/
 • ሰው በሀብት፣ በሥልጣን፣ በጉልበት፣ በፆታ ሳይኾን በሰውነት ይለካ!
 • ይህች ዓለም እየዞረች ለምን ታዞረናለች? /አዲስ ኪዳን ተሰማ/
 • ያሉንን ሳይኾን የኾነውን ኾነን ወጣን፤ ኀጢአተኞች ሲከሱን ጻድቁ እያገዘን፡፡
 • አንበሳው በቀበሮዎች ጩኸት እንዳልደነገጠ አያችኹትን? /በኀይሉ በቀለ/
 • ሓላፊነት ለብር ወይስ ለፍቅር? /ብርሃኑ ተስፋዬ/
 • ወንጌልን እንጂ ወንጀልን አልሰብክም /ካሳ ገበየሁ/
 • ሲሞናውያን እጅግ በዙ፣ ሥልጣንን በብር እየገዙ፡፡
 • የሊቅ ሞቱ በደንቆሮ መመራቱ፡፡
 • ሙስናን የሚቃወም ትውልድ መጠላቱ ለምን ይኾን?/ ጴጥሮስ አቧሆይ/
 • ያለሥርዐት የሚሄዱትን ገሥጿቸው(፩ተሰ. ፭÷፲፬) /አባ ሣህለ ማርያም ንጉሤ/
 • በመቅደሱ ውስጥ ርግብ ሻጮች ዛሬም አሉን? /ተስፋዬ ደስታ/
 • የሺሕ ገንዘብ አትብላ፣ ከሺሕ ሕዝብ አትጣላ፡፡
 • ድኃ አደጎችና አባት የሌለን ኾነናል /ተስፋዬ ኀይሉ/
 • ፖሊቲካ በሃይማኖት አይገባም ከማለት የበለጠ ፖሊቲካ የለም /ተስፋዬ ደስታ/
 • ሕዝቡ የሚያለቅሰው ምን ኾኖ ነው? (፩ሳሙ. ፲፩÷፭) /ብርሃኑ ቦጋለ/
 • ታማኝና ልባም መጋቢ ማነው? (ሉቃ. ፲፪÷፵፪) /ዕርገተ ኒኮላ/
 • ሰላም እንዲስፋፋ የዘር መድልዎ ከዓለም ይጥፋ /ገብረ ሚካኤል ገሠሠ/
 • ወዴት እያመራን ነው? /ቀሲስ ይግዛው መኰንን/
 • ለመምህሮቼ ቃለ ሕይወት ያሰማልኝ /ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ/
 • Where is the first century Christianity? /ዲያቆን ዓለማየሁ ዳዊት/
 • የቤተ ክህነት አስተዳደር መጨረሻው ምን ይኾን? /ቀሲስ ጸጋ እምሬ/

በመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ምሩቃኑ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩና ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ የማስታዎሻ ፎቶዎችን ተነሥተዋል፡፡ በኮሌጁ የቀድሞ ምሩቅና አሁንም የድኅረ ምረቃ ትምህርቷን የምትከታተለው ወ/ሮ ዘውዴ ገብረ እግዚአብሔር በሰፊው የተዘጋጀውን የእናትነት ክርስቲያናዊ ማዕድም በደስታ ተቋድሰዋል፤ መርቀዋልም፡፡

በደቀ መዛሙርቱ መብትን የማስከበር ውጤታማ ትግል ታጅቦ የተካሄደው የዘንድሮው መርሐ ግብር፣ በተመራቂዎችና በተከታይ ወንድሞቻቸው እንዲሁም ወደ ሌሎች ኮሌጆች (መምህር ተሾመ ገብረ ሚካኤል፣ መሪጌታ ሐዲስ ትኩነህና ዶ/ር ሐዲስ የሻነህ ወደ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ፣ መ/ር መኰንን ወርቅነህ ወደ መቐለ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ቅዱስ ፍሬምናጦስ) እንዲዘዋወሩ፣ ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሳ በጡረታ እንዲገለሉ በዘላለም ረድኤትና ተባባሪዎቹ ተዶልቶባቸው በነበሩ መምህሮቻቸው ዘንድ ከፈጠረው ከፍተኛ ደስታ አንጻር ልዩ የሐሤት ድባብን የተላበሰ ኾኖ አልፏል፡፡

በቀጣይ ምሩቃኑ የሚጠብቁት ነገር ቢኖር በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ በሚወጣው ዕጣ መሠረት የሚደርሳቸውን የአገልግሎት ምደባ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ እንዳሉት የስብከተ ወንጌል ጉዞ የመስቀል ጉዞ ነውና፣ የስብከተ ወንጌል ተልእኮ ስምሪት ቅዱስ ጳውሎስ ተከሦ ወደ ሮም እንደተጓዘባት መርከብ ጽኑዕ የዓውሎ ነፋስ መናወጥ የበዛበት ነውና የአገልግሎት ዘመናቸው በተመደቡበት ሀ/ስብከት ጸንተው መልካም ፍሬን የሚያፈሩበት እንዲኾን ስንመኝላቸው፣ ቅኔዎቻቸውና የጥቅሶቻቸው ኀይለ ቃላት ያጋቷቸው የመንፈሳዊነት፣ የዕቅበተ ሃይማኖት እና የተቋማዊ ለውጥ ጥያቄዎች ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው መፍትሔ እንዲበጅላቸው በማስታወስ ነው፡፡Holy Trinity Theological College, Regular Graduates, Class 2005

Advertisements

2 thoughts on “የደቀ መዛሙርቱ የምረቃ ቀን ጥያቄዎች እና ጥቅሶች ምን ያመለክታሉ?

 1. Anonymous August 5, 2013 at 4:24 am Reply

  እንግዲህ ምን ይደረጋል ለ አባቶቻችን ልቦና እንዲሰጥልን እግዚአብሔርን ተግተን መለመን እንጂ!!!

 2. Anonymous August 7, 2013 at 1:06 pm Reply

  I wonder the HTTC students.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: