መጋቢት ፲፪ ‹‹የደቀ መዛሙርት ቀን›› ተብሎ በየዓመቱ ይታሰባል

  • ‹‹በድል ኮረብታ ላይ ወጥታችኋል፤ መምህራን ኮርተናል›› /ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ/
  • ‹‹የተቃወምነው ሰውን ሳይኾን ሥርዐቱን ነው›› /የደቀ መዛሙርቱ መማክርት አመራር/
  • የደቀ መዛሙርቱ ምረቃ ሐምሌ ፳፯ ቀን ይካሄዳል
Mmr Degu Alem Kassa

ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ

በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን መምህር በኾኑት ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ አገላለጽ የኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ያሣመሯት የዛሬ ሐምሌ ፳፭ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ምሽት ለሚቀጥለው ትውልድ የተሰጠች መሠረታዊ የትውስታ ዕለት፣ የትውስታ ምሽት፣ የኢያሱ ሐውልት ናት፡፡

ደቀ መዛሙርቱ የኮሌጁ አካዳሚያዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮች እንዲፈቱ ላለፉት ስድስት ወራት ሲያካሂዱ የቆዩት ትግል በውጤት መጠናቀቁን በማስመልከት ከበጎ አድራጊዎች ባገኙት የገንዘብ ድጋፍ በዛሬው ዕለት ምሽት በምግብ ቤት አዳራሻቸው የራት መርሐ ግብር አዘጋጅተዋል፡፡

በራት መርሐ ግብሩ ላይ ‹‹እግዚአብሔርን ግሩም ነኽ በሉት፤ ሥራኽ ድንቅ ነው በሉት›› በሚል ርእስ የተሰብሳቢዎችን ቀልብ የሳበ ትምህርት የሰጡት ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም÷ ‹‹የእናንተ ረኀብ ያላዛለው ክንድ፣ የእናንተ ጥም ያልዘጋው አንደበት አባቶቻችን ሐዋርያትንና አባቶቻችን ሊቃውንትን የሚያስታውሰን ኾኗል፤ ይህ የአባቶቻችን ሥራ ነበር፤ ለብዙ ጊዜ ሻግቶ ነበር፤ በእናንተ ደግሞ ተወልውሎ አበራ፤ በድል ኮረብታ ላይ ወጥታችኋል፤ እውነተኛ የወንጌል ማሕፀን ልጆች በመኾናችኁ መምህራን ሊኮሩባችኁ ይገባል፤ ኮርተናል፤›› በማለት ለውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎች ሳይበገሩ ለወራት በጽናት ዘልቀው ለውጤት የበቁ ደቀ መዛሙርትን አወድሰዋል፡፡

ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ‹‹የግራ የቀኝ ጠላታችን›› ሰው ሳይኾን ክፉ መንፈስ መኾኑን በመግለጽ፣ ‹‹እውነት ነው፣ የላይ ፈሪ የታች ፈሪ እያለ ያጣላን የሁለታችን ጠላት ክፉ መንፈስ ተወግዷል፤ አሁን ድል ያደረገ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ እናንተ ታሪክ ሠርታችኋል፤ ታሪክ ያሠራችኹ እግዚአብሔር ስቡሕ ዉዱስ ነው፤›› ሲሉ ኀያሉን ደካማ፣ ደካማውን ኀያል የሚያደርገውን እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡

ደቀ መዛሙርቱ የቆሙት አባቶቻችን በደማቸው ባረጓት፣ በአጥንታቸው በገነቧት፣ በቆዳቸው ባለሰለሷት ሃይማኖተ ወንጌል ላይ መኾኑን ያዘከሩት መምህሩ÷ ደቀ መዛሙርቱ አፋቸውን በጸሎት፣ እጃቸውን በትዕግሥት፣ ሰውነታቸውን በትሕትና ገዝተው የሃይማኖታቸውን ልዕልና ማስመስከራቸውን በመጥቀስ የተቃውሞ እንቅስቃሴያቸውን ሰላማዊነት አስረድተዋል – ‹‹ማንም ማንንም በጥላቻ የሚያይበት ዘመን አከተመ፤ ልክ እንደ ማንዴላ ኾናችኁ፡፡›› ይህም በኢትዮጵያ እና በውጭ ሀገር ላሉት የቀድሞ ምሩቃን ወንድሞች መኩሪያና መመኪያ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

መምህሩ አያይዘውም ‹‹ነፍሳቸውን የገነት ውኃ ያጠጣልንና›› በማለት የቀድሞውን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ስም ከጠሩ በኋላ የሚከተለውን ቃላቸውን አስታወሱ – ‹‹በዚህ መንገድ የሚያልፈው ሁሉ ይህን ግቢና ተቋም እያየ መንቀጥቀጥ አለበት፡፡ ግቢው እነማን ያላችኁበት መኾኑን ማወቅ አለበት፡፡›› አነጋገራቸውን በማስረገጥም ‹‹ዘንድሮ ተተረጎመ›› ሲሉ ሙሉ አዳራሹ በደማቅ ጭብጨባ አስተጋባ፡፡ በይቀጥላልም ደቀ መዛሙርቱ አባቶቻቸውን አርኣያ አድርገው ሞራላቸውን ጠብቀው ልቡናቸውን በማራቀቅ የኮሌጁን ተመልካቾች ሁሉ እንዲያስገርሙ፣ እንዲያስከብሩ መክረዋል፡፡

በመጨረሻም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍሬ ሽቶባት ሳለ ፍሬ አልባ ኾና ያገኛትን ‹በለስ› በኮሌጁ ተጨባጭ ኹኔታ በማመስጠር መምህሩ ሰፊ ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ዘንድሮ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይኹን፤ ፍቅር ለሲኖዶስ አባላት ይኹን፤ በቋሚ ሲኖዶስ አሳሳቢነት፣ በመምህራን መስካሪነት እና በእናንተ ጩኸት በአንጻረ በለስ ትዝህርት፣ ትዕቢት፣ ስስት፣ ክፋት ደርቀውላችኋል›› በማለት ትምህርታቸውን ቋጭተዋል፡፡

ሙሉ አዳራሹ ቆሞ በሚያሰማው የጋለ ጭብጨባ(standing ovation) መካከል ወደ መቀመጫቸው ሲያመሩም በትምህርታቸው ከተነኩት ደቀ መዛሙርት መካከል ዲያቆን ኀይለ ጽዮን መንግሥት የተባለ ሳተና ደቀ መዝሙር የቆሎ ተማሪነት ጊዜያቸውን የሚያስታውሳቸውና ዐይናቸው የትዝታ እንባ ያቆረዘዘበትን የተማሪ አኩፋዳ  ሸልሟቸዋል፡፡ የአብነት ት/ቤትን መዓዛ የቀመሰው ራሱ ደቀ መዝሙሩ አዘውትሮ ሲናገር እንደሚደመጠው አኩፋዳዋ ‹‹አደራዋን ጠብቆ›› ከራሱ ጋራ ያቆያት ነች፡፡

Performing Woreb

በዚሁ የራት ምሽት የትውስታ መርሐ ግብር ወረብ በኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ቀርቧል፤ ቅኔዎች ተበርክተዋል፤ ከቅኔዎችም መካከል በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ላይ የአርዮስ፣ በእመቤታችን ወላዲተ አምላክነት ላይ የንስጥሮስ ኑፋቄ በአንዱ በዘላለም ረድኤት ላይ ተባብረው የተገኙበትን ኹኔታ የሚያመላክቱ ይገኙበታል፡፡ የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበሩ መ/ር ማንያዘዋል አበበ ‹‹ደቀ መዝሙር መኾን አማረኝ›› በሚል ርእስ የኮሌጁን መዋዕለ ትምህርት ከወቅቱ ፈተናና መከራ ጋራ አሰናኝቶ ያቀናበረውን ግጥም አሰምቷል፡፡ ከስንኝ ቋጠሮዎቹም:-

ብረር ብረር አለው ሸነጠው ልቤን፣

ዳግመኛ ሊመለስ ተማሪ ሊኾን፤

የእውነትን ፋና ከዳር ዳር አድርሶ፣

የእውነትን ፋና ከዳር ዳር ለኩሶ፣

ስለፍትሕ መጮኽ ሁሉንም ታግሦ፣

ስለፍትሕ መጮኽ መልሶ መልሶ፡፡

በማለት የደቀ መዛሙርቱ በጽናት የተሞላና በተዋሕዶ የሠመረ የመብት ማስከበር ትግል በቀደሙት ትውልዶች ከተደረጉት ጥረቶች ልቆ ባስገኘው ውጤት ያሳደረበትን አድናቆት፣ መነሣሣትና የመንፈስ ቅንዐት የገለጠበት ይጠቀሳል፡፡ የቋሚ ሲኖዶስ አባላትና የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተመስግነዋል፤ ምስጋናውስ ለመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ዋና ሓላፊ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤልም የተረፈ ነበር፡፡

የደቀ መዛሙርቱን እንቅስቃሴ በተለይ የምግብ ቤቱን አገልግሎት በተነፈጉበት ወቅት በሚያስፈልገው ሁሉ ሲያግዙ ከነበሩት በጎ አድራጊዎች መካከል የኮሌጁ የቀድሞ የመጀመሪያ ዲግሪ እና የድኅረ ምረቃ ዲፕሎማ መርሐ ግብሮች ምሩቅ የወ/ሮ ዘውዴ ገብረ እግዚአብሔር አለኝታነት ያለተመልካች የቀረ አልነበረም፡፡ ከማንም ሳይኾን በግል ጥሪቷና ጥረቷ ያበረከተችው አስተዋፅኦ ብዙ ምስጋና፣ ብዙ ውዳሴ የተቸረው ነበር፡፡

Mmr Manyazewal reading poem

መምህር ማንያዘዋል አበበ

የኮሌጁን ዕድገት ለማገዝ እና ጥቅሞቹን ለማስጠበቅ እንደ ቤተሰብ የሚደረገው ጥረት ቦታና ጊዜ ሳይገድበው ቀጣይነት እንደሚኖረው ከደቀ መዛሙርቱ መማክርት አመራር በተሰማው መግለጫ ላይ ተመልክቷል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ጥያቄዎቻቸውን ማሰማት ከጀመሩበት ስድስት ወራት በፊት ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ለመጀመሪያ ጊዜ የታዘዙበትና ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉበት መጋቢት ፲፪ ቀን በየዓመቱ ‹‹የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ቀን›› ተብሎ እንዲታሰብ መወሰኑንም አመራሩ አስታውቋል፡፡

ኮሌጁ በቀንና በማታ መርሐ ግብሮች ያሠለጠናቸውን ደቀ መዛሙርት ከነገ በስቲያ ሐምሌ ፳፯ ቀን ያስመረቃል፡፡ ከዘንድሮው ምሩቃን መካከል 54 ያህሉ በቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩና ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሳ በሚገባ እንደገለጹት፣ ባሳለፉት ውጣ ውረድ የተጋድሏቸውን ቋሚ መታወሻ በተተኪዎቻቸው ልቡና ላይ እንደ ኢያሱ ሐውልት በጥረታቸው የተከሉ ውጤታማ ደቀ መዛሙርት ናቸው፡፡

Advertisements

2 thoughts on “መጋቢት ፲፪ ‹‹የደቀ መዛሙርት ቀን›› ተብሎ በየዓመቱ ይታሰባል

  1. Anonymous August 2, 2013 at 8:38 am Reply

    bechigirachin ke gonachin lehonu ye Ethiopia orthodox tewahedo haimanot teketayoch,sirachihun be agbabu yetewetachihu yemegenagna bizuhan. beteley VOA ( addisu), hara zetewahedo. yale LE KINOCH MISGANA YIGEBAL ENA (MEZMUR 22) YEKINOCH WAGA YIDRESACHIHU. KOLEJU ENDAYIZEGA YADEREGACHIHUT MINA TALAK NEW!

  2. Anonymous August 3, 2013 at 5:58 am Reply

    were bicha

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: