‹‹አቡነ ሺኖዳ ተብዬ ጵጵስና እሾማለኹ›› በሚል ተስፋ የኖሩት የቅ/ላሊበላ ደብር አስተዳዳሪ በ‹‹ሕክምና ፈቃድ›› ሰበብ ከአገር ሊወጡ ነው፤ የሕክምና ፈቃዱ ከባድ ቅጣት ከሚያስከትልባቸው የሕግ ተጠያቂነት ለመሸሽም የዘየዱት ነው ተብሏል

Komos Aba Gebre Eyesus Mekonen

ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ መኰንን
የቅዱስ ላሊበላ ደብር አስተዳዳሪ

 • ከ15 – 20 ዓመት በሚያስቀጡ ቅርስን የማፍረስ፣ ከባድ የእምነት ማጉደል እና ሐሰተኛ ሰነድ የመፍጠር የወንጀል ተግባራት ይፈለጋሉ፡፡
 • የደብሩን ካህናትና ሊቃውንት ‹‹ሐሳቤን ተቃውማችኋል›› በሚል አላግባብ ከሥራ በማባረር፣ በሽጉጥና በአካላዊ ጥቃት በማስፈራራት፣ በጉልበታቸው በማንበርከክና በደመወዝ በመቅጣት፣ እንዳሰኛቸው በማዘዋወር እርስ በርስ በመከፋፈል፣ ከንስሐ ልጆቻቸው በመለየት ዐምባገነናዊ አስተዳደራቸው በክልልና በከተማው አስተዳደር ሓላፊዎች ፊት ክፉኛ ተተችተዋል፡
 • አስተዳዳሪው በግፍ ከሥራና ከደመወዝ ያገዷቸው አንድ አገልጋይ የአቋቋም መምህር፣ የሐረግ ሥዕላት፣ የቅርጻ ቅርጽ እና የቁም ጽሕፈት ባለሞያ ናቸው፡፡ ከቤተ ጊዮርጊስ አቅራቢያ የሚገኘውንና በደብሩ አስተዳደር ፈቃድ የተረከቡትን 16‚000 ሄክታር መሬት ተማሪዎቻቸውን አስተባብረው ከቆሻሻ በማጽዳትና በአገር በቀል ዛፎች በማልማት በጥር ፳፻፬ ዓ.ም በአካባቢ ጥበቃ ‹‹የአረንጓዴ ልማት›› /Green Award/ አገር አቀፍ አሸናፊ በመኾን ከፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ እጅ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ ልማቱን የስማቸው መጠሪያ በማድረግ ለመንግሥት ባለሥልጣናት ለማስጎብኘት ሽተው ያልተሳካላቸው ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ  በአንጻሩ ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱን ሽልማት ግለሰቦች ወሰዱት›› በሚል አገልጋዩን በተለያዩ ሰበቦች ወንጅለው ከሥራና ከደመወዝ እስከ ማገድ ደርሰዋል፡፡ እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በይግባኝ የተንገላቱት አገልጋዩ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ከመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት የተሰጠላቸውን ትእዛዝ የደብሩ አስተዳደርም የሰሜን ወሎ ሀ/ስብከትም ተቀብለው ለመፈጸም ፈቃደኛ አልኾኑም
 • ሐሰተኛ የፊርማ ማሰባሰቢያ ሰነድ በመፍጠር ከሥራ ያፈናቀሏቸውን እኚህን አገልጋይ በተመለከተ የተጠርጣሪነት ቃላቸውን እንዲሰጡ በላሊበላ ከተማ ፖሊስ መጥሪያ ተልኮላቸው እያለ በ‹‹ሕክምናና ጠበል›› ፈቃድ ሰበብ የውጭ ጉዟቸውን ለመቀጠል ከትላንት ጀምሮ በአዲስ አበባ ይገኛሉ፤ በመጥሪያው መሠረ ቀርበው ቃላቸውን ካልሰጡ የማደኛ ትእዛዝ ሊወጣባቸው እንደሚችል የከተማው ፖሊስ በዛሬው ዕለት ለደብሩ ጽ/ቤት ባደረሰው ደብዳቤ አስጠንቅቋል፡፡
 • ‹‹ተራማጁ እና ልማታዊው›› በሚል የሚሞካሹት ቆሞሱ በመንበረ ጵጵስና ብፁዕ አቡነ ቄርሎስን የመተካት ምኞት ነበራቸው፤ ይህን ምኞታቸው ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ለከፍተኛ ሕክምና በጀርመን በነበሩበት ፳፻፩ ዓ.ም በማኅበረ ካህናት ስብሰባ ላይ ‹‹አቡነ ሺኖዳ ተብዬ ጵጵስና ተሹሜ እመጣለኹ›› በሚል ገሃድ አድርገውታል ምኞታቸውን ለማሳካትም በቀድሞው ዘመነ ፕትርክና ሁለት ጊዜ (በግንቦት ፳፻፫ ዓ.ም እና በጥቅምት ፳፻፬ ዓ.ም) በሲሞናዊ መንገድ ለኤጲስ ቆጶስነት ለመታጨት ሞክረዋል
 • ከብር 250‚ 000 – 350‚ 000 የቅዱስ ላሊበላን ደብር ገንዘብ መድበው ንቀሳቅሰውበታል የተባለው ሲሞናዊ ሢመተ ኤጲስ ቆጶስነት ምኞት እንዳሰቡት ባለመሳካቱ የደብሩን ሰበካ ጉባኤና ‹‹ጀርመን ልኬ አሳክሜያቸዋለኹ፤ ምን ያደርጉኛል!›› በሚል መመሪያቸውን ባለመቀበል ጭምር የሚዳፈሯቸውን የሰሜን ወሎ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሳያሳውቁ በሕመም ፈቃድ ሰበብ ወደ አሜሪካ አቅንተው ለሁለት ወራት ተኩል (ከጥቅምት ፳፻፬ –  ታኅሣሥ ፳፻፬ ዓ.ም) ዕረፍት አድርገው ተመልሰዋል፡፡ በወቅቱ በቦታው ሌላ አስተዳዳሪ እንዲመደብ በቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ተወስኖ የነበረ ቢኾንም የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ውሳኔውን ተፈጻሚ ሳያደርጉት ቀርተዋል፡፡ በ‹‹ሕክምና እና ጠበል›› ስም ፈቃድ የጠየቁበት የአሁኑ ጉዟቸው ደግሞ ከሐምሌ ፳፯ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም – መስከረም ፲ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም የሚዘልቅ እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡ በውጭ ጉዟቸው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሚመራውን ሲኖዶ ማኩረፊያ አድርገውት ይኾን?
 • ሙሰኝነታቸውንና የአስተዳደር በደላቸውን የሚቃወሙ ካህናትንና የመንግሥት ሓላፊዎችን በዞን፣ ክልልና ፌዴራል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስሞች በማሸማቀቅ ይታወቃሉ፤ የማስፈራሪያ ስሞቹ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር አማካሪ ሚኒስትር አቶ በረኸት ስምዖንን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን አቶ ደመቀ መኰንን፣ የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንትና የግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ሓላፊ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውንና የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳዳሪን አቶ ጸጋ አራጌን ይጨምራል፡፡
 • በተለያዩ የደመወዝ መክፈያ ቅጾች በወር ከብር 13,000 በላይ ይከፈላቸዋል፤ ለግል ጉዳያቸው በሚሄዱባቸው ቦታዎች ሁሉ ብር 200 ዕለታዊ አበል ይታሰብላቸዋል፡፡
 • ደብሩ በ1.4 ሚልዮን ብር የገዛው የመካነ ልዕልት ካፌና ሬስቶራንት በ4.5 ሚልዮን ብር እንደተገዛ ተደርጎ ለጠቅ/ቤተ ክህነት ሪፖርት ቀርቧል፤ መካነ ልዕልት በሚባለው ቦታ ለሚሠራው የእንግዳ መቀበያ/ገስት ሃውስ/ በ8 ሚልዮን ብር የቀረበ ተጫራች እያለ 10 ሚልዮን ብር ያቀረበው ሥራ ተቋራጭ አሸናፊ ተደርጓል፤ ለደብሩ በስጦታ የተበረከተው የመቶ ሺሕ ብር ትርፋማው ሰባት ወይራ ሆቴል በአስተዳዳሪው ደብዳቤ ለጠቅ/ቤተ ክህነቱ ተላልፎ መሰጠቱ እየተነገረ ነው፡፡
 • ከቤተ ደናግል ቤተ መቅደስ ጋራ አብሮ የተሠራው የደንጊያ መንበር ተነቅሎ ወደ ቤተ አብርሃም ሆቴል ተወስዶ ‹‹ሲጃራ መተርኰሻ እና መጠጥ ማቅረቢያ›› ኾኗል፤ በቤተ መድኃኔዓለም እና ቤተ ዐማኑኤል አቅራቢያ የነበሩና ከአብያተ መቅደሱ ጋራ አብረው ታንፀው በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ አራት የሣር መክደኛ ያላቸው ቤቶች ‹‹ተቃጥለው›› የተወሰደ ርምጃ የለም የምርመራ ሂደቱ ‹‹ማን እንዳቃጠለው መረጃ ስላላገኘን ቆሟል›› በሚል ተዳፍኖ ቀርቷል፤ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የፌዴራሉ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለጉዳዩ የሰጡት ትኩረት አጥጋቢ አይደለም በሚል እየተተቸ ነው፡ የሣር መክደኛ ያላቸው አራቱ ጥንታውያን ቤቶች (Tukuls) ለዘመነ ላሊበላ የቤቶች አሠራር ሕያው ምስክሮች ነበሩ

  Bete Medhanialem

  ቤተ መድኃኔዓለም

 • ለላሊበላ ከተማ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማ ዕድገት ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ የሚያደርገው ደብሩ ከቱሪዝም፣ ከሆቴሎች መስተንግዶ እና ሌሎች የልማት ተቋማት ከ28 ሚልዮን ብር በላይ ዓመታዊ ገቢ ያገኛል የሚል ሪፖርት በአስተዳዳሪው የሐምሌ ፳፩ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም እሑድ ሰንበት ንግግር እየቀረበ ባለበት ኹኔታ÷ ቤተ ገብርኤል፣ ቤተ ጊዮርጊስ፣ ቤተ ጎልጎታ እና ቤተ መርቆሬዎስ በከፋ የመፈራረስ አደጋ ላይ ናቸው፤ ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ ደናግል፣ ቤተ መስቀል፣ ቤተ ዐማኑኤል እና ቤተ አባ ሊባኖስ በዩኔስኮ ላስቲክ ‹እንደተጠለሉ› ነው!

  Bete Mariam

  ቤተ ማርያም

 • በቃለ ዐዋዲው ከታዘዘው የሦስት ዓመት ገደብ በተፃራሪ አምስተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ተጨማሪ ስድስት ወራት እንዲሰጠው በአስተዳዳሪው የስንብት ንግግር ተጠይቆለታል፤ በሕዝብ ያልተመረጡ አባላት የሚበዙበት ሰበካ ጉባኤው ከአስተዳደር ሠራተኞች የተሻለ ሥልጣን የሌለው የአስተዳዳሪው ፈቃድ ፈጻሚ ነው፤ የደብሩ ሒሳብ በውጭ ኦዲተር እንዲመረመር ሲቀርብ የቆየውን ጥያቄ እንኳ በቅጡ የሚያስፈጽመው አልተገኘም፡፡
 • የደብሩን ችግር አጣራኹ ያለው የመንበረ ፓትርያሪኩ አጣሪ ልኡክ የስምሪት ሪፖርቱን ማቅረብ ተስኖታል፤ የልኡኩ አባል የኾኑት የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ፣ የቅ/ላሊበላ ደብር አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ መኰንን ‹‹ወደ ከፍተኛው ማዕርግ ቢደርሱማ ኑሮ የሰማይ መና ሳያወርዱ አይቀሩም ነበር›› በማለት የኤጲስ ቆጶስነት ተስፋቸውን በጋዜጣው አጯጩኸውላቸዋል፡፡ 

 

Advertisements

14 thoughts on “‹‹አቡነ ሺኖዳ ተብዬ ጵጵስና እሾማለኹ›› በሚል ተስፋ የኖሩት የቅ/ላሊበላ ደብር አስተዳዳሪ በ‹‹ሕክምና ፈቃድ›› ሰበብ ከአገር ሊወጡ ነው፤ የሕክምና ፈቃዱ ከባድ ቅጣት ከሚያስከትልባቸው የሕግ ተጠያቂነት ለመሸሽም የዘየዱት ነው ተብሏል

 1. Anonymous July 30, 2013 at 1:52 pm Reply

  እኔ የቅዱስ ላሊበላ ደብር አገልጋይ ዲያቆን ነኝ ሐራዎች እግዚአብሔር ይባርካችሁ እነደዚህ አይነቱ ስመ መነኩሴ ናቸው እንግዲህ በቅዱስ ላሊበላ መንበር ላይ ተቀምጠው በእንጦስና በመቃርስ ቆብ የሚነግዱት! ለነገሩ እናንተ መረጃ አጥታችሁ ነው ብዬ ባልገምትም በቅርብ እኔ መነኩሴ ነኝ ባዩ አስመሳይ ሙሰኛ ግለሰብ እናንተ ከገለጻችሁኋቸው በተጨማሪም፡-
  1. ወታደር የነበረ የአስር አለቃ ጌተው ውቤ መኮንን በመባል እነደሚታወቅ አንዳንድ የውስጥ አዋቂ ምንጮች ይናገራሉ፡፡
  2. በዘማዊ ሕይወታቸው የቅርብ ጓደኞቻቸው ሳይቀር መክረዋቸው ማቆም ያልቻሉና የሦስት ልጆቾ አባት መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ይህንን ጉድ አቡነ ቄርሎስ እያወቁ በቸልታ ማለፋቸው ብቻ ሳይሆን ጵጵስና አሾማለሁ በሚል ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ መሆናቸው እናውቃለን፡፡
  3. ብዙ ጊዜ ግንኙነታቸው የሽናሻ እና የዋድላ ደብተራዎች ጋር መሆኑን የቅዱስ ላሊበላ ነዋሪዎች አብዛኞቻችን እናውቃለን በአባ ዱላው መኪና ጋቤና ተቀምጠው ጥርሳቸው በመፋቂያ እየፋቁ ከተማውን በተደጋጋሚ ጊዜ እንደሚዞሩ ይታወቃል፡፡ በከተማው ነዋሪዎች ላይ አዚም ለማድረግ መሆኑን አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ፡፡
  4. ኮተቤና ሲኤሚሲ ያሉት ቤቶች በምን ገንዘባቸው ሠሩት? ቤተ ክርስቲያን በምትከፍላቸው ደመወዝ? አሄሄሄሄሄ……

 2. Anonymous July 30, 2013 at 2:19 pm Reply

  እግዚኦ እረ እግዚአብሔር በቃ ይበለን ::

 3. Anonymous July 31, 2013 at 12:10 pm Reply

  I know the Abott very well. Do not tell extended lies. As any of the current members of the clergy he might have wrongs, but not that far. How about the developmental works he is engaged and proved to be prominent. I know that there are few people who are making conspiracy theory against him. The article seems the by product of that sect.

 4. Anonymous July 31, 2013 at 5:36 pm Reply

  “ወታደር የነበረ የአስር አለቃ ጌተው ውቤ መኮንን በመባል እነደሚታወቅ አንዳንድ የውስጥ አዋቂ ምንጮች ይናገራሉ፡፡”
  Completely false

 5. Anonymous July 31, 2013 at 9:20 pm Reply

  አንዱ ጥቅመኛ ሳትሆን አትቀርም ወይንም ሴት አጣባሹ አሂሂ…

 6. Anonymous August 1, 2013 at 6:44 pm Reply

  ቂመኛና ዘረኘውን ጳጳስ አባ ቄርሎስን በተመለከተ ብዙ እያወቃችሁ በአባ ገ/ኢየሱስ ላይ ብቻ ማተኮራችሁ ግምት ላይ ይጥላችሁአል የጠሉትን አሳደው የሚያሲያስለቅሱ የትውልድ ሀገራቸውን ሰዎች ያለችሎታ እና እውቀት ሲሾሙ ቅንጣት ታክል ፈሪሀ እግዚአብሄር ስሌለላቸው ለ26 ዓመታት ቅንጣት ታክል የቅድስና ቀርቶ የአዲስ አማኝን ያክል ፈሪሃ እግዚአብሄር ምልክት የማየማይታይባቸውንና በፊውዳለዊ አምባገንን አገዛዛቸው የሚታዎቁትን ጳጳስ ጉዳይ ተጨባጭ መረጃ በዚሁ አምድ ስለምናቀርብ ያን ጊዜ የአባ ገ/ኢየሱስ ጉዳይ ሚዘን የማይደፋ ሆኖ ይገኛል ጥፋት የለባቸውም ለማለት አይደለም ከመህምሩ ደቀመዝሙሩ ለማት እንጅ

 7. astu August 2, 2013 at 4:11 am Reply

  why all this lies about abune kerlos? he is very known by his strong commitment for evangelizing the remote area even using horses and mules.he was one of the true bishops who stood against the unfair leadership of abune paulos, that is why he was attacked. please, there is God above us. lets be truth full and lets comment being under the fear of God. this is only for those who are trying to be honest not for those with the mission of destructing the name of our fathers so that our church.

 8. Anonymous August 2, 2013 at 3:12 pm Reply

  አልሰሜን መጣ ና ግባ በሉት ቂቂቂቂቂቂ በፈረስ እና በበቅሎ ተጉዘው አስተምረዋል ትክክል በቃል ወንጌሉን ሰብከዋል በግብር ግን በቃሉ ሽፋን እንደንጉስ ገዝተዋል ጎጣቸውን አስከብረዉበታል ዘመዶቻቸውን ቀጥረው ጎጆ አውጥተውበታል ድረውበታል የሚጠሉትን በቂም በቀል አፈር አስግጠውበታል አቡነ ጳውሎስን መቃዎም ብቻ የጽድቅ አክሊል አያስደፋም

 9. Anonymous August 3, 2013 at 5:41 pm Reply

  deer haratewahido the above which you expressed not expressed abba G/eyesus he is the little brother of devil he mastered all devil’s technique.

 10. Anonymous August 8, 2013 at 7:05 pm Reply

  አባ ገ/ኢየሱስ በቅዱስ ላሊበላ ደብር እንዲህ ያለ ተው ባይ ሲናኝበት የሀገረስብከቱ ሊቀጳጳስ ታወቂ በሆኑበት የሙስና አባዜ የደብሩን ገንዘብ እየቆነጠረ አፋቸውን ዘጋው እንበል የደብሩ ካህናት እና የላሊበላ ከተማ ህዝብስ ለምን የሩቅ ተመልካች ሆኖ ቆመ እጅግ ያሳዝናል

 11. beti August 11, 2013 at 11:06 am Reply

  ብጹዕ አቡነ ቄርሎስን እኛ እምናቃቸው፡-
  1. በሰሜን ወሎ፣በዋግሕምራና በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌልን በጥራትና በብቃት ሲያስፋፉ፤
  2. ብዙ ሰባክያነ ወንጌል፣ካህናትና የአብነት ተማሪዎችን ሲያፈሩ፤
  3. ቤተክርስቲያን በራስ አገዝ ልማት ራስዋን እንድትችል ሲያደርጉ፤
  4. ብዙ ሃይማኖታዊ መጻሕፍትን ሲጽፉ፤
  5. መንበረ ጵጵስና በራሳቸው ገንዘብ አስገንብተው ለቤተክርስቲያን ሲያስረክቡ፤
  6. በእግራቸው ዞረው ወንጌለ መንግስቱን ሲሰብኩ፤
  7. አጽራረ ቤተክርስቲያንን ሲቃወሙ ነው፡፡
  ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ ሰሜን ኢትዮጵያን በወንጌል ያቀኑ ታልቅ አባት ናቸው፡፡ በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት 3000 ሺህ ብር የፈጀ የካህናት ማሰልጠኛ በመክፈት ክህነትና ካህናት ሥራና ሠራተኛ እንዲገናኙ አድርገዋል፡፡ እስከ 4ኛ ክፍል የሚያስተምር ትምህርት ቤት ከፍተዋል፡፡ ሁለ ገብ ሕናጻ በመገንባት የሀገረ ስብከቱን ገቢ አሳድገዋል፡፡ 200 የሚሆኑ የድጓ ተማሪዎችን በጎንደር እንዲሰለጥኑ በማድረግ በሀገረ ስብከቱ ስር ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ቀጥረዋል፡፡ 6 አዳሪ ት/ቤቶችን በመክፈት አብነቱን አስፋፍተዋል፡፡
  አስተያየት ሰጪው የዚህን ታላቅ አባት ስም ለማጥፋት ከእውነት የራቀ ወሬ አውርተዋል፡፡ እግዚአብሔርን የማይፈሩ ፀሐፊ ናቸው፡፡ ምን አልባት የግል ጥላቻ እንዳላቸው ያሳያል፡፡ የእውነተኛ አባቶችን ስም ማጥፋት ተገቢ አይደለም፡፡ ልብ ይስጣችሁ፡፡

 12. bet August 15, 2013 at 11:53 am Reply

  ስም ከማጥፋት ልማት ማልማት
  ቆሞስ አባ ገ/ኢየሱስ መኮነን የቅ/ላልይበላ ደብር አስተዳዳሪ ላይ ስለተጻፈው የሀሰት ቅራቅንቦ የተሰጠ ማስገንዘቢያ ቆሞስ አባ ገ/ኢየሱስ መኮነን ዘመን ያስነሳቸው የዘመኑ የልማት አርበኛ ሃሳባቸውን የተቃወሙትን ሳይሆን ከመሥራት ይልቅ ወሬ በማናፈስ የግል ጥቅም ለማሰባሰብ የሚሞክሩት ላይ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ የማይሉ ናቸው፡፡

  ቆሞስ አባ ገ/ኢየሱስ መኮነን ግን ከሰሯቸው እና እየሰሯቸው ካሉት ሥራዎች ጥቂቱን እናካፍላችሁ፡፡ ብር 150.00 የነበረው የቱሪስት ገቢ ወደ ብር 900.00 ከፍ እንዲል አደረጉ፡፡ ከብር 200.00 – ብር600.00 የነበረ ያገልጋይ ደመወዝ ከብር 1500.00 – ብር 5000.00 ከፍ አደረጉ፡፡ ቤተ አብርሃምን ሆቴል በማሠራት ፤ይምርሃ ሆቴልን በመግዛት የ3 አለም አቀፍ ሆቴሎች ባለቤት ያደረጉ ፤የ7 ወይራ ሆቴልን ያስመለሱ ፤ መካነልዕልት የተባለውን ቦታ በመግዛት ዘመናዊ ሆቴል እና ገበያ ማዕከል በማሠራት ላይ ያሉ የልማት ጀግና ናቸው፡፡ ቱሪስቶችን በማዋከብ ለሀገራችን ጥላሸት የነበረውን የልመና ተግባር ለማስቀረት ከ80 በላይ የሚሆኑ ድኩማንን በማሠባሰብ በአንድ ማዕከል እንዲረዱ በማድረግ ልመናና ወከባን በከተማዋ ያስቀሩ ፡፡
  3 የተለያየ ደረጃ ያላቸው መኪኖችን በመግዛት ለደብሩ ጽ/ቤት እና ለሆቴሎቹ አገልግሎት አውለዋል ፡፡
  የደብሩን አመታዊ ገቢ ከ3ሚሊዮን ብር ወደ 20 ሚሊዮን ብር ከፍ ያደረጉ፡፡
  የደብሩን ሠራተኞች በቤተክርስቲያን ትምህርት እና በዘመናዊ ትምህርት በድግሪና በሁለተኛ ድግሪ የተመረቁትን የአካባቢው ልጆች አወዳድሮ በመመደብ ደብሩ የዘመናዊ ቴክኖሎጅ ተጠቃሚ አድርገዋል ፡፡

  አባ ገ/ኢየሱስ መኮነን በዕርግጥም ለአጭበርባሪዎች እና ለአታላዮች አይመቹም ፡፡ የጵጵስና ሹመቱም ቢሆን እግዚአብሔር ከፈቀደው አይቀርም በፋይናንስ እንቅስቃሴም ቢሆን ሥራውን የሚሠሩት የቦታው ተወላጅ በሆኑ እጅግ ታማኝነት ባላቸው ገቢው በህጋዊ ደረሠኝ እየተሰበሰበ ወጭውም በዚህ መልኩ የሚሠራ የሀገረ ስብከት ኦድተሮች በየጊዜው የሚመረምሩት አልፎም የጠቅላይ ቤተክህነት ኦድተር ድንገት እየመጣ ሂሳቡን በማየት በተለያየ ጊዜ ምስጋና የሰጠበት መሆኑ እየታወቀ ለማስመሠል መሞከሩ ተገቢ አይደለም፡፡ ለህክምና አሜሪካ ሂደው በፈቃዳቸው መሠረት መመለሳቸው እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ታማኝ የቤተክርስቲያኗ ልጅ መሆናቸውን ያስመሰከሩ በመሆናቸው አሁንም በፈቃድ ቢሄዱ ተመልሰው ወደ ተመደቡበት ቦታ እንደሚመጡ ጥርጥር የለንም ለወሬ የማይበገሩ የልማት አርበኛ በመሆናቸው ፡፡

  አንድ ድያቆን ተብየ የተናገረው ክብር ባለው ወታደር ሰይሟቸዋል ለመሆኑ የሰማዕታትን ገድል አንብበሃል ለመሆኑ ሳትማር የደቆንክ ነህ እንጅ ወታደር ክብር ያለው አገሩን የሚጠብቅ ለሃገሩ ሟች ታማኝ ዜጋ እንዳንተ ባንዳ ያልሆነ በመሆኑ ይህን መናገርህ የወታደርነትን ክብር ዝቅ እንደማድረግ ይቆጠራል ስለዚህ የሚመለከታቸው ከዩት ወነጀል ነው ተጠንቀቅ ፡፡

  ይህንን የልማት ጀግና በቅ/ላልይበላ ደብር በአስተዳዳሪነት መድበው በማሠራታቸው በብጹዕ አቡነ ቄርሎስ ላይም የድፍረት ጽሁፍ ለመጻፍ ተሞክሯል ፡፡ የእርሳቸውን ማንነት እኳን ሀገራዊ ቀርቶ የአለም ህዝብ የሚያውቃቸው በመሆኑ ጸሀፊውን ከመርገም በቀር የሚሠጠው ትርጉም እንደሌለ ለመግለጽ እወዳለሁ ፡፡

  ስለ ብፁዕነታቸው አንድ መልስ ሰጭ የገለጹት ስለሆነ ብዙ ባልልም የልማት ጀግና ፤የወንጌል ገበሬ ፤ ሙስናና የገንዘብ ብክነትን የሚጸየፉ ፤ለቤተክርስቲያን እድገት የቆሙ ፤ ከአጥቢያ እስከ ሀገረ ስብከት ሥራና ሠራተኛን በተገቢው መንገድ የሚያገናኙ ፤ ለወገን ለዘመድ የማይሉ ፤የግል ገንዘባቸውን በማውጣት እራሳቸውን ችለው ዘመናዊ ቤተክርስቲያን አሠርተው በጥሩ ሁኔታ ያስመረቁ ፤ በእርግጥም ከቤተክርስቲያኗ ይልቅ የግል ጥቅማቸውን ለሚያሳድዱ ለአጭበርባሪዎችና ለሌቦች የማይመቹ በመሆናቸው የቀበሮ ባህታዊ ፤ጫት ቃሚ ፤የሺሻና መጠጥ የሲጋራ ጥማት ያሠከራቸው ኦርቶዶክሳዊ ነኝ ባዮች ብዙ ቢሉ አይገርምም ምክንያቱም ትክክለኛ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን የሆነ በአንድ እውነተኛ እና ታላቅ የቤተክርስቲያን መሪ ላይ እንዲህ ያለ ፅሁፍ ሊጽፍ አይችልምና ነው ፡፡

  የግል ፍላጎታቸው ያልተሟላላቸው የቤተክርስቲያኗን ንብረቶች እንደ ግል ሃብታቸው በማድረግ ሲጠቀሙ የኖሩ ያያቸው ሁሉ ይህ ነገር ምንድን ነው እያለ አስተያየት ሲሰጥባቸው የነበሩ በራሳቸው ችግር ጥቅማቸው ሲቋረት ይህን መጻፋቸው የፊተኛው መልስ ሠጭ እንዳለው የቀበሮ ባህታዊነታቸውን የሚያሳይ ፤አስመሳይ በመሆናቸው እግዚአብሔር ያስታግሳቸው እንላለን ፡፡

 13. Anonymous August 21, 2013 at 8:11 pm Reply

  ከመጨረሻው መልስ ሰጭ በፊት በታረመ አንደበት መልስ የሰጡት እና ብጹእነታቸው የሰሮአቸውን ተግባሮች ከ 1-7 ተራ ቁጥር በመዘርዘር እኛም የምናውቀዉን ተግበር በሚገባ አስቀምጠዋል ተገቢም ነው እንላለን
  የመጨረሻው አሰተያየት ሰጭው ግን በባዶ ሜዳ ነው የሚጨፍሩት አቀራረባቸው ተራ ተወዳጅነት ለማግኘት ብቻ ይመስላል ምንአልባትም ለጻፉት አሉባልታ መልስ ሲሰጥ እራሳቸው በቀጥታ ለማንሳት የሸሾአቸውን ጉዳዮች በሌሎች እንዲጻፉላቸው የፈለጉም ይመስላሉ ወዳጅ መሳይ ድብቅ ጠላት ይላሉ እንዲህ ነው ፡፡ ለሁሉም የፍርዱ ባልተቤት እግዚአብሄር ስላለ ለባልተቤቱ ሁሉም ነገር ቢተው መልካም ነው ፡፡ በድብቅ በኢንተርኔት ላይ መጻጻፉም ቢቆም ድንቅ ነው ክርስትና ወደው ፈቅደው የሚያመልኩት እንጅ የጦርነት አውድማ አይደለም ፡፡

 14. Anonymous August 30, 2013 at 6:26 pm Reply

  የቆሞሱ የአባ ገ/ኢየሱስ ጠበቃ የጥብቅና አሙን አልቻልክበትም ውትደርና የተከበረ ተግባር ስለመሆኑ ከአንተ መማር አያስፈልገንም እያልን ያለነው ግን ተገቢ ያልሆነ ሰው ጭምብል ለበሶ በታለቁ ደብር የቅድስና መንበር ላይ ተቀምጦአል ነው ጠመንጀውን ይዞ በውትድርናው ቢቀጥል ተቃውሞ የለንም የእርሱ እጅ ለምን መስቀል ጨበጠ ነው ጥያቄው ተገቢ ስላልሆነም ተገቢ ያልሆነ ስራ እየፈጸመ ነው፡፡
  ዲያቆን ተብየው በለህ ለመዘርጠጥ አስበሃል እኔ እንዳንተ ውዳሴ ማርያም ዜማ ሳልዘቅ በባዶው መላከ እንትና ተብየ የምጠራ አይደለሁም ጥርት አድርጌ የቤተክርስቲያን ትምህርቴን የቀጸልኩ ከቤተክርስቲያ ሙህራን አብራክ የተገኘሁ ፍሬ ነኝ ወታደሩ ና የሶስት ልጅ አባቱ አባ ገ/ኢየሱስ ልጅህን ላሊበላ ልከህ ያስተማረልህ በእኛ ደብር ገንዘብ ነው ይህንን ታውቃለህ ለመሆኑ አንተና ቢጤዎቸህ ከየትኛው ተም ተመርቃቸሁ ነው ኦዲተር የምትሆኑት ገና ወደፊት ሁሉም ነገር ሲስተካከል ለኦዲት እያልክ ስትመላለስበት የከረምክበትን ጉዳይ ተገቢውን ክህሎት በትምህርት አገኝተው በእውቀታቸው የተመሰከረላቸው ኦዲተሮች ይመረምሩታል ጫት ቃሚ ሲጋራ አጫሾችም አይደለንም እንዳንተ ባልተጠመቁም በተጠመቁሙ እቁባቶች የተከበብንም አይደለንም
  ጳጳሱ እግራቸው ተቆርጦአል ከሄዱበት አይመለሱም ከዚህ በኋላ ተወደደም ተጠላም ሊቀጳጳሱ አባ ገ/ኢየሱስ ናቸው እያልክ ላሊበላ በመጣህ ቤተ አብርሃም ሆቴል ተቀምጠህ ስትነግረን ነበር አባ ገ/እየሱስን ጮቤ ስታስረግጥ ነበር አሁን ደግሞ የጳጳሱ ጠቃ ሆነህ ተገኘህ ጉደኛ ነህ ፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: