የአ/አ ሀ/ስብከት በደብረ ጽጌ ቅ/ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል የተባለውን የከፋ ሙስናና ብልሹ አሠራር ሊያጣራ ነው

 • ደብሩ በተጭበረበረ የሕንጻ ኪራይ ውል ከ2 ሚልዮን ብር በላይ ገቢ ማጣቱ ተነግሯ

 •  የደብሩ ገንዘብ ቤትና ቁጥጥር ቢሮዎች በአጣሪ ኮሚቴው ታሽገዋል

St Urael Church YeHulegeb Agelgelot Hintsaበቋሚ ሲኖዶስ አሻሽሎ ባጸደቀው ውስጠ ደንብ አስተዳደራዊ መዋቅሩን እያደራጀ የሚገኘው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ‹‹ከፋይናንስ እንቀስቃሴና አሠራር›› ጋራ በተያያዘ በደብሩ ጽ/ቤት ተፈጽሟል የተባለውን ሙስናና ብልሹ አሠራር ሊያጣራ ነው፡፡

ከሀ/ስብከቱ ዐበይት አድባራት አንዱ በኾነው የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል የተባለውን የከፋ ሙስናና ብልሹ አስተዳደር የመመርመሩ ሥራ የሚካሄደው፣ በደብሩ ከፋይናንስ እንቅስቃሴና አሠራር ጋራ በተያያዘ ሥር የሰደደ ችግር በመኖሩ የሒሳብ ምርመራ እንዲደረግ የሰበካ ጉባኤ አባላትና ምእመናን ለሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲያሳስቡ በቆዩት መሠረት እንደኾነ ተዘግቧል፡፡

ይህንኑ የሒሳብ ምርመራ ሥራ የሚያከናውን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት ዋና ሓላፊና ሁለት የሀ/ስብከቱ ልኡካን የሚገኙበት ልኡክ በሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መሠየሙ ተሰምቷል፡፡

በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ሲፈጸም የቆየው የአስተዳደር በደልና የገንዘብ ምዝበራ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የአጥቢያው ምእመናንና የደብሩ ካህናት ለሐራዊ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

በሀ/ስብከቱ በርካታ የገቢ ምንጮችና ከፍተኛ ገቢ ካላቸው ገዳማትና አድባራት በቀዳሚነት በሚጠቀሰው በቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ምዝበራው የተባባሰው፣ ደብሩ ለሁለገብ አገልግሎት ባሠራው የሕንጻ ኪራይና ከሙዳየ ምጽዋት ሚሰበሰቡት የገቢ ምንጮች ላይ መኾኑ ተገልጧል፡፡

‹‹በሕንጻው የኪራይ አገልግሎት የሚፈጸመው ዐይን ያወጣ ምዝበራ ሕንጻው ባለቤት የለውም ወይ የሚያሰኝ ነው?›› የሚሉት ካህናቱና ምእመናኑ፡-

 • የሕንጻው ክፍሎች ከአካባቢው ሕንጻዎች የኪራይ ተመን ዝቅተኛ በኾነ ዋጋ እንደሚከራዩ፣
 • ከተከራዮች ጋራ የጊዜ ገደብ የሌላቸው ውሎች እንደሚፈጸሙ፣
 • በተጭበረበረ ማኅተምና ቲተር የተደረጉ ሕገ ወጥ ውሎች መኖራቸውን፣
 • ባለፈ የኪራይ ተመን በተፈጸሙ የውል ማራዘሞች ደብሩ ከፍተኛ ገቢ ማጣቱን፣
 • ከአንድ ሚልዮን ብር በላይ ውዝፍ ክፍያ ያለባቸው ተከራዮች መኖራቸውን፣
 • ያለወቅታዊ የዋጋ ማስተካከያ በዝቅተኛ ክፍያ ለረጅም ጊዜ ውል የፈጸሙ ተከራዮች እንዳሉ፣
 • ፈጽሞ ውል የሌላቸው ተከራዮች መኖራቸውን፣

በመዘርዘር ያስረዳሉ፡፡

የሕንጻውን የኪራይ ውል አሰጣጥ ለመመርመርና የኪራይ ተመኑን ከአካባቢው ዋጋ ጋራ ለማጣጣም በደብሩ ጽ/ቤት እና ሰበካ ጉባኤ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ለአስተዳደሩ ያቀረበውን ሪፖርት በመጥቀስ አቤቱታ አቅራቢዎቹ እንደሚያስረዱት÷ የውል ጊዜያቸው ካለቀ ሁለት ተከራዮች ጋራ ብቻ በተጭበረበረ መንገድ በተፈጸሙ የውል ማራዘሞች ደብሩ ከሚያዝያ ወር ፳፻፬ ዓ.ም ጀምሮ ማግኘት የሚገባውን 2,637,603.30 /ሁለት ሚልዮን ስድስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺሕ ስድስት መቶ ሦስት ከሠላሳ ሳንቲም/ እንዲያጣ ተደርጓል፡፡

ኮሚቴው አሻሽሎ ካቀረበው ወቅታዊ የኪራይ ዋጋ ተመን ይልቅ ባለፈ የክፍያ ተመን ላይ በመመሥረትና ከተከራዮች ጋራ የጥቅም ተካፋይ በመኾን አላግባብ እንዲራዘም የተደረገው ሕገ ወጥ ውል፣ ‹‹የደብዳቤ ውል ቁጥር በሌለውና ከሓላፊነት በተነሡት የደብሩ አስተዳዳሪ ፊርማ›› የተሰጠ እንደኾነ ተመልክቷል፡፡ የደብሩን ንብረት የመጠበቅ፣ የኪራይ ውሎችን በመከታተል የደብሩን ጥቅሞች መከላከል የሚገባቸው ጸሐፊውና ቁጥጥሩ የሕገ ወጥ ውሉ ‹‹አዘጋጆችና ምስክሮች›› መኾናቸው ምዝበራውና ሙስናው በምን ደረጃና በእነማን እንደተፈጸመና እየተፈጸመ እንዳለ አረጋጋጭ ነው ተብሏል፡፡

St Urael Church Building Complexበሕንጻ ኪራይ ውል አሰጣጥ ለሚፈጸሙ ምዝበራዎች የማያዳግም መፍትሔ ለመስጠት÷ ሀ/ስብከቱ በዋና ጸሐፊውና ተቆጣጣሪው ላይ የእርምት ርምጃ እንዲወስድ፣ አግባብነት የሌላቸውን ውሎች የፈጸሙ ሓላፊዎች በሕግ እንዲጠየቁና ደብሩ ያጣቸውን ገቢዎች እንዲያገኝ፣ ተከራዮች በኪራይ ውል ውስጠ ደንቡ መሠረት እንዲስተናገዱና ደንቡን ከማያከብሩ ተከራዮች ጋራ ውል እንዲቋረጥ ኮሚቴው የመፍትሔ ሐሳብ አቅርቦ የነበረ ቢኾንም አንዱም ተግባራዊ ሳይደረግ ‹‹ጸሐፊው በይቅርታ፣ ቁጥጥሩ በዝውውር መታለፋቸውን›› ነው ምእመናኑ የሚናገሩት፡፡

የደብሩ ጽ/ቤት በበኩሉ ከኪራይ ውሎች ጋራ በተያያዘ ከተጠቀሱት ስሕተቶች አብዛኞቹ በቀድሞው የደብሩ አስተዳደር የተፈጸሙ መኾናቸውን ገልጾ፣ ደብሩ ከሚያከራያቸው 47 ሱቆች መካከል የ35 ሱቆችን ውል እንደ አዲስ የማስተካከል ሥራ መሥራቱን፣ በሕገ ወጥ መንገድ ከሁለት ተከራዮች ጋራ የተፈጸሙት ውሎችም ከስድስት ወራት በፊት እንዲቋረጡ ተደርጎ ጉዳዩ በፍርድ ቤት መያዙን አስረድቷል፡፡

በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ በወር ሁለት ጊዜ የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ የሚካሄድ ሲኾን በእያንዳንዱ ወር በአማካይ ከግማሽ ሚልዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚደረግ ተመልክቷል፡፡ በ2003 ዓ.ም ሐምሌ ወር የተመረጠው የደብሩ ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ በሥራ ላይ በቆየባቸው ባለፉት 22 ወራት ለ44 ጊዜያት በተካሄደው የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ ከ12 ሚልዮን ብር በላይ እንደሚሰበሰብ ቢታመንም በደብሩ የባንክ ሒሳብ ያለው ተቀማጭ ግን ከአምስት ሚልዮን ብር እንደማይበልጥ የደረሱን ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከአምስት ሚልዮን ብሩ ውስጥ 3.5 ሚልዮን ብሩ ካለፈው ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ የዞረ ሒሳብ እንደኾነ የሚያሰሉት ካህናቱና ምእመናኑ፣ በ2003 ዓ.ም የተመረጠው ሰበካ ጉባኤ ወደ ደብሩ ካዝና ያስገባው ገቢ ከ1.5 ሚልዮን ብር የማይበልጥ መኾኑ የምዝበራውን መጠን በጉልሕ እንደሚያሳይና አሳሳቢ እንደሚያደርገው በምሬት ይናገራሉ፡፡

በሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ ወቅት የቆጠራውን ሂደትና የገባውን የገንዘብ መጠን በዝርዝር የሚያሳዩት የ22 ወራት 44 የቆጠራ ቃለ ጉባኤዎች፣ በቀድሞው የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት አስተዳደራዊ መዋቅር ደብሩ ከተካለለበት የምሥራቅ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት በተላኩ ልኡካን ለሒሳብ ምርመራ በተፈለጉበት ወቅት የደብሩ ጸሐፊ፣ ‹‹የቆጠራው ቃለ ጉባኤዎች የጠፉ ስለኾነ አናስመረምርም›› በማለታቸው ማጣራቱ ሳይካሄድ መቅረቱን ካህናቱና ምእመናኑ አስታውሰዋል፡፡

የቀድሞው የምሥራቅ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት በድጋሚ ለሒሳብ ምርመራ የላካቸው መርማሪዎች ‹‹የቆጠራ ቃለ ጉባኤዎች ስለጠፉ አናስመረምርም፤ ከዚህ ቀደም ስላስመረመርን በድጋሚ አናስመረምርም፤ የሰበካ ጉባኤ አባላት ባሉበት አናስመረምርም›› በሚ በቃለ ዐዋዲው ለደብሩ ዋና ጸሐፊ የተሰጡ ተግባራትን የዘነጉ የደብሩ ጽ/ቤት የተለያዩ ሰበቦች ሥራቸውን ሳይፈጽሙ እንዲመለሱ መደረጋቸው በአቤቱታው ተመልክቷል፡፡ ይህም የደብሩ አስተዳደር ጽ/ቤት፣ ደንብና አሠራርን በመጣስ የፈጸመው ምዝበራ ከሚያስከትልበት የሕግ ተጠያቂነት ለማምለጥ የሚያደርገውን ሙከራ በግልጽ እንደሚያሳይ ካህናቱና ምእመናኑ አብራርተዋል፡፡

የሙዳይ ምጽዋት ገንዘብ ቆጠራ ቬርቫል /ቃለ ጉባኤ/ በተጠያቂነት ደረጃ የሚቀመጥበት አካል ያለመኖሩን በመግለጽ ክሡን የሚቃወመው የደብሩ ጽ/ቤት÷ ለሒሳብ ምርመራው አግባብነት ያላቸው ሕጋዊ የሰነድ ማስረጃዎች ሞዴላሞዴሎቹ መኾናቸውን በመጥቀስ ይከራከራል፡፡ ይህም ኾኖ ይፈለጋሉ ከተባሉት የሙዳይ ምጽዋት ገንዘብ ቆጠራ ቃለ ጉባኤዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚኾኑትን ለማጣራቱ ሥራ ማዘጋጀቱን ገልጧል፡፡ ይህን ምክንያት በማድረግ የደብሩን ጽ/ቤት ከሚከሡ አካላት መካከልም ግለሰባዊና ቡድናዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚያልሙ እንዳሉ አመልክቷል፡፡

የሕንጻውን ኪራይና ሙዳየ ምጽዋቱን ጨምሮ በሌሎች የደብሩ ዘጠኝ የገቢ ምንጮች ላይ በአስተዳደር ጽ/ቤቱ አባላት የሚፈጸመውና ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋ መምጣቱ የተገለጸው ምዝበራ፣ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎቷን ለመፈጸም ያላትን መንፈሳዊ ሥልጣንና ፋይናንሳዊ አቅም እየተፈታተነው እንዳለ የሰበካ ጉባኤ አባላቱ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የአስተሳሰብና የምግባር ብልሽቱን›› በእነርሱ ደረጃ ለማስተካከል ከሚቻለው በላይ ስለኾነባቸውም ጉዳዩ ተጣርቶ አስቸኳይ የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ ለአዲሱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስና ለዋና ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት በአካል ቀርበው ማስረዳታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከሳምንታት በፊት በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የአጥቢያው ምእመናንና የደብሩ አገልጋዮች በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ሁለት ጊዜ ከሊቀ ጳጳሱና የሀ/ስብከቱ የሥራ ሓላፊዎች ጋራ ተገናኝተው በችግሩ ላይ ግልጽ ውይይት አካሂደዋል፡፡ ሊቀ ጳጳሱና ዋና ሥራ አስኪያጁ በአካል በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር በተገኙበት ተመሳሳይ ውይይት የተደረገ ሲኾን ካህናቱና ምእመናኑ የአሠራር ብልሽቱንና ምዝበራውን ባጋለጡባቸው በእኒህ መድረኮች፣ በደብሩ ጸሐፊ ‹‹ጠፍተዋል›› የተባሉት ቃለ ጉባኤዎችና ለምርመራው የሚያስፈልጉ ሌሎች ሰነዶች በአስቸኳይ ቀርበው የማጣራቱ ሥራ እንዲካሄድ ሊቀ ጳጳሱ ጠንካራ የቃል ትእዛዝና ቀነ ገደብ ለአስተዳደር አባላቱ መስጠታቸው ተዘግቧል፡፡

ሀ/ስብከቱ ለሒሳብ ምርመራ በሠየመው ኮሚቴ÷ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የቁጥጥር አገልግሎት መምሪያ ዋና ሓላፊ መልአከ ብርሃን ኤርሚያስ ተድላ፣ የቀድሞው የምሥራቅ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ሠርጸ አበበ እና የቁጥጥር ክፍሉ ሓላፊ ገብረ መስቀል ድራር እንደሚገኙበት የተዘገበ ሲኾን በከፋ ሙስና የሚታሙ ግለሰቦች በአባልነት መካተታቸው ሂደቱን በከፍተኛ ጥንቃቄ ለመከታተል እንደሚያስገደድዳቸው የዜናው ምንጮች አልሸሸጉም፡፡Letter by the former East Addis Ababa Diosces to St Urael Parish

Advertisements

One thought on “የአ/አ ሀ/ስብከት በደብረ ጽጌ ቅ/ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል የተባለውን የከፋ ሙስናና ብልሹ አሠራር ሊያጣራ ነው

 1. Haymanot December 24, 2013 at 10:44 am Reply

  telam leboch! hodam merchants! enaneten neber kewoyane kedemo kager matefat! ethiopian yekeberachu enanete nachu!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: