‹‹መሪዎች ጥቅመኞች ከኾኑ የውስጥ ሰላም አይኖርም›› (ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ)

ሰኔ ፮ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በተከናወነው መርሐ ግብር÷ በርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያሪኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው የተመደቡትን ብፁዓን አባቶች ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመምሪያና የድርጅት ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የክፍል ሓላፊዎችና ሠራተኞች ጋራ የማስተዋወቅ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡

ለወትሮው ከተለመደው በመወዳደስ የተሞላ የተመረጡ ሰዎች ንግግር በተለየ መልኩ ለሓላፊዎችና ሠራተኞች በተሰጠው የተሳትፎ ዕድል በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ስላለው ችግርና ስለሚያስፈልገው ለውጥ በርካታ አስተያየቶች ተደምጠዋል፤ በእንባ ታጅበው የቀረቡ፣ የቤተ ክህነታችንን መንፈሳዊነት አጠያያቂ የሚያደርጉና ፍትሕን የሚማፀኑ የአስተዳደር በደሎችም ተሰምተዋል፡፡

በቀደመው ዘገባችን ጠቅለል አድርገን ለማሳየት እንደሞከርነው አጋጣሚው የአድርባዮቹንም የእውነተኞቹንም ሐሳብ ለመታዘብ ዕድል የሰጠ ነበር፡፡ መርሐ ግብሩ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ‹‹እንኳን ደኅና መጣችኹ፣ አብረን እንሠራለን›› የሚባባሉበት ቢኾንም በቀጣይ ሠራተኛው ከሥራ ሓላፊዎች ጋራ ሐሳብ የሚለዋወጥበት መድረክ እንዲመቻችለት የጠየቀበት፣ ጥቅመኛና አስመሳይ ተናጋሪዎችን ያጋለጠበትና በግልጽ የገሠጸበት ነበር፡፡

‹‹በዚህ መድረክ ያልተነገረ ቃል፣ ያልተዘመረ መዝሙር፣ ያልቀረበ ጽሑፍ የለም፤›› ያሉት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ÷ መሰባሰቡ፣ መገናኘቱ ተጠናክሮ ሥራን ለመሥራት፣ ራስን ለመመልከትና ዘመኑን ለመዋጀት ልንጠቀምበት እንደሚገባ በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልእክት መነሻነት መክረዋል፡፡ በብፁዕነታቸው ንግግር÷ የመልካም እምነት መልካም ምግባር አስፈላጊነት፣ ከራስ በፊት ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ቅድሚያ ሰጥቶ ግዴታን የመወጣት፣ እንደ እግዚአብሔር ሠራዊት መጠን የእግዚአብሔር ዓላማ ግቡን እንዲመታ የማድረግ ጉዳይ አጽንዖት ተሰጥቶታል፡፡ ዘመኑን በመገምገም ዘመኑን መዋጀት እንደሚያስፈልግ ያሳሰቡት ብፁዕነታቸው፣ ‹‹እዚህ አሠሪና ሠራተኛ የለም፤ ሁሉም ሠራተኛ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በትውውቅ መርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ባስተላለፉት መልእክት÷ ቤተ ክርስቲያናችን በእምነቷ እንከን እንደሌለባት አረጋግጠው በመልካም አስተዳደር ረገድ ግን ሙስናውና ጎጠኝነቱ ወደ ኋላ እንዳስቀራት፣ አስተዳደሯን እንዳነቀዘው ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የመሠረታዊ ለውጥ ርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡ ለዚህም ሠራተኛው ከሓላፊዎች ጋራ በመገናዘብ በአንድነት መሥራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ከዚህ በታች የቀረበው ደግሞ ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በትውውቅ መርሐ ግብሩ ላይ በጽሑፍ ያስተላለፉት መልእክት ሙሉ ቃል ነው፡፡ እንድከታተሉት እንጋብዛለን፡፡

 

His Grace Abune Mathewos

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖ

ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የጅማ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የሰቲት ሑመራ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት

የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያና ድርጅቶች ሓላፊዎች፣ ሠራተኞችና የጉባኤው እድምተኞች፤

 

ለቸርነቱ ወሰን ለአባትነቱ መጠን የሌለው እግዚአብሔር አምላካችን ለዚህ ሰዓት ለዚህ ዕለት ስላደረሰን ለታላቅነቱ ለአባትነቱ ክብር ምስጋና ይግባው፡፡

ወዘሰ በውኁድ ምእመን ወበብዙኅኒ ምእመን ውእቱ ወዘሰ በኅዳጥ ዐማፂ ወበብዙኅኒ ዐማፂ ውእቱ፤ ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፤ ከሁሉ በሚያንስ የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዐመፀኛ ነው፡፡ (ሉቃ.፲፮÷፲)

የተከበራችኹ የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኞች እንደዚሁም የየድርጅቱ ሓላፊዎች÷ ዛሬ ብዙ ንግግር ላልናገር እችላለኹ፡፡ ወደፊት አብረን ስለምንጓዝ ዋናው ከመንፈስ ርዳታ ጀምሮ የምንጠይቅበት ቀን ስለኾነ እግዚአብሔር እንዲረዳን፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን አሳድገን እኛም ተረድተን ሌሎችንም እንድንረዳ ለማሳሰብ ያህል ነው፡፡

ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ከተመረጥን በቤተ ክርስቲያን ሥርዐት መኖር አለብን፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሥርዐት እንድናገለግል ከተጠራን አገልግሎታችን በመጠኑም ቢኾን የተሻለ መኾን አለበት፡፡ የሚያዝዘን ሥርዐታችንና ሕጋችን እንጂ ሥልጣናችን አይደለም፡፡ ሥልጣናችን የሚያዝዘን ከኾነ ሥራችን ሕይወት ሊኾን አይችልም፤ ምክንያቱም የምንሠራው እገሌ ያዝዘናል ብለን እንጂ እንጠቀምበታለን፣ እንሠራበታለን፣ እንታመንበታለን ብለን ስለማይኾን፡፡ እኛ ከሠራን ሁሉም ሊሠራ ይችላል፤ እኛ ከቆምን ሁሉም ይቆም ይችላል፡፡

በዓለም ያሉ ፈላስፎች እንዲህ ይላሉ÷ ማንም ማንንም ስለ መልካም ሥራው የሚቀጣ መሪ የለም፤ የድርጅቶችና የተቋማት መሪዎች የሚጠሉት፣ ተመሪዎች የሚጠሏቸው÷ ታታሪ አሠሪ ነው የሥራ ጫና ያበዛብናል፤ ሥራ ወዳድ ነው ያለዕረፍት ያሠራናል፤ ሥራ ዐዋቂ ነው ሥራ ስናበላሽ ይቆጣናል ብለው አይደለም፡፡ ሠራተኞች ቢያንስ ቢያንስ ሥራው ለሀገርና ለወገን እንደሚጠቅም ያውቃሉና፡፡ ትክክለኛ መሪ መቼም አይጠላም፡፡ ተመሪዎች መሪዎችን የሚጠሏቸው÷ ከቆሙበት ዓላማና ተግባር ውጭ ራሳቸውን ሲያስቀድሙ ነው፡፡ በዐምባገነንት፣ በጉቦኝነት፣ በዘረኝነት፣ በአድርባይነት ሲጠመዱ ተመሪዎች ያኮርፋሉ፤ ይጨነቃሉ፤ አስቀድመው ለመበቀል ስለሚዘጋጁ ተመሪዎች ይጨነቃሉ፡፡

መሪዎች ጥቅመኞች ከኾኑ የውስጥ ሰላም አይኖርም፤ በተመሪዎች ውስጥ መጠን የሌለው መረበሽ ይፈጠራል፤ የኅሊና ሰላም ስለሌላቸው ርካታ በማጣት ስሜታቸው ይታወካል፤ ሕዋሳቸው ይጨነቃል፤ ማንንም ማን አያምኑም፤ እንደ ቃየን በገዛ ጥላቸው ይደነግጣሉ፤ የአንድ መሪ ልብ ሰላማዊና የተዝናና ካልኾነ አመራሩና ሥራው እንዲሁ ሰላማዊ ሊኾን አይችልም፡፡ ለምን፤ ማንም ሥልጣን ፈላጊ መፈለግ ያለበት ሥልጣኑን ሳይኾን ሥራውን ነው፡፡ ሥልጣኑ በሥራው ውስጥ ሥራው በሥልጣኑ ውስጥ ይተያያሉ፡፡

በሥራው የተሾመ ሰው መሾሙም አለመሾሙም ለእርሱ ምኑም አይደለም፡፡ ተሠራ ተሾፈ ውጤቶቹን ሥራው ይመሰክርለታል፡፡ በዚያን ሰዓት እንደተሾመ ሁሉም ያውቃል፡፡ መሾም ብቻ እንደኾን የፈለገው ቦታውን ጥሎ ሲሄድ ብቻ ሰዎች ያዩታል፡፡ መሪዎች ብዙዎቹ ዐምባገነንኖች ሲኾኑ ከተመሪዎቹ ውስጥ ግን ካሠሯቸው ለሥራው የማይመቹ ሠራተኞች ጥቂቶች ሊኾኑ ይችላሉ፡፡

 

ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣

ክቡራን እድምተኞች፤

ሓላፊነታችንን በሥልጣን ላይ አንጫነው፡፡ ወደፊት ገና ብልህ አስተዋይ ሰው ተሾሞ ሥርዐት ያወጣልናል፤ እንደ ሙሴ ባሕር ከፍሎ እንደ ኤልያስ ዝናም ሰቅሎ የሚታገል ይመጣልናል ብለን አንጠብቅ፡፡ ራሳችን ባለንበት ዘመን የሥራ ነቢያት፣ የሰላም ሐዋርያት መኾን አለብን፡፡ አለበለዚያ አንዱ አንዱን እየጠለፈ ቀራንዮ መስክ ላይ የሚያውለው ከኾነ ቀራንዮ ከዚህ በኋላ የበረከት ሳይኾን የጥፋት፣ የውድመት፣ የመጠፋፋት ይኾናል፡፡ ማንም ለማንም ሳይኾን ለራሱ ያስብ፤ ለራሱ ያሰበ ለወንድሙ ያስባል፤ ራሱን የወደደ ወንድሙን እኅቱን ይወዳል፤ ራሱን የሚወድ ሰው በመጠኑም ቢኾን የማይነቀፍ ሥራ ሊሠራ ይችላል፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎችና ድርጅት ሠራተኞች፣ የዛሬው መተዋወቅ ሆሳዕና ኾኖ በቀጣዩ ዕለተ ዐርብ እንዳይኾን ለሁላችኁም አደራ እላችኋለኹ፡፡

መሪ እንደ ንቧ አውራ ነው፤ እናንተ እንደ ንቦቹ ናችኹ፡፡ የንብ አውራ የሚጠብቀው ከንቦቹ ነው፡፡ ከንቦቹ አውራ የሚጠበቀው ሓላፊነት ድምፁን ማሰማት ብቻ ነው፡፡ ንቦቹ የአውራውን ድምፅ ካልሰሙ እንኳ ማር ሊሠሩ በቀፏቸው ውስጥ ለአፍታም መኖር አይችሉም፡፡ ስለዚህ መሪ እንደ ንብ አውራ ተገኝቶ ድምፁን ማሰማት፣ ተመሪዎች በቀፏቸው ውስጥ ተገኝተው ማር መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ክቡራን እድምተኞች፤

ስለዚህ እናንተም ሰላማዊ ድምፅ እያሰማችኹ እንደ ንቦቹ ታታሪ ሠራተኞች፣ ሐሰት የምትጸየፉ፣ አሉባልታ የምትንቁ፣ ሥራ የምትወዱ፣ ሰላም የምትናፍቁ እና በፍቅር የምትመላለሱ እንድትኾኑ አደራ እላችኋለኹ፡፡

 

እግዚአብሔር ሥራችንን ያቃናልን፤

የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በረከት አይለየን፤

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን፣ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን፣ በይበልጥ የምንወዳት አገራችንን እግዚአብሔር ይጠብቅል

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

Advertisements

3 thoughts on “‹‹መሪዎች ጥቅመኞች ከኾኑ የውስጥ ሰላም አይኖርም›› (ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ)

 1. Anonymous June 24, 2013 at 10:32 am Reply

  Melkam yesira zemen endihonilachew emegnalehu!

 2. Anonymous June 26, 2013 at 2:29 pm Reply

  ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሪዎች በሙሉ
  ጥንትም ጌታን ሲቃወሙ የነበሩ እንነማን እነደሆኑ ማስተዋሉን ቢሰጣችሁ እናውቃለን የሚሉ ካህናትና የካህናት አለቆች ነበሩ፡፡ ዛሬ እናንተ የጥንቶቹን የጌታን ተቃዋሚዎች በብዙ መልክ ብዙዎቻችሁ እየመሰላችኋቸው እንደመጣችሁ ብታስተውሉ መልካም ነበር፡፡ ግን እየሆነ ያለ አይመስልም፡፡ በአስተዳደሩ የሄው ቤተክርስቲያኒቱን ለሁለት ከፍላችሁ ሕዝቡን ውዥምብር ውስጥ መክተታችሁ ሳይሆን የእናንተ ጭንቀት የራሳችሁን የበላይ መሆንን ነው፡፡ በሥጋዊ እንኳን ስለሕዝብ እኔ የቅርብኝ የሚል ብዙ ሰው አለ፡፡ እናነተ ጋር ግን አልተቻለም፡፡ መፍትሔው ለብዙዎቻችን ቀላልና የግለሰቦች ፍቃድ ብቻ የሚጠይቅ እንደሆነ ብናውቅም ይሄው በአልሸነፍነት ዘልቃችሁበታል፡፡ መፍትሄ እናመጣለን የሚሉትም ግራ አጋቢ ስልት ሲጠቀሙ ይታያል፡፡ እናንተ ይቅር ለማለት እንዲ የከበዳችሁ እውን የቤተክርስቲያን ቅንዐት እንዳልሆነ ውስጣችሁ ያውቀዋል፡፡ እሱን እንደ ሕዝብነታችን ምንም ማድረግ ስላልቻልን ተውናችሁ፡፡ አሁን ደግሞ እኛን ወደሕይወትና ደህንነት የሚያመጣ ትምህርትና ስነምግባር ላይ ማውደሙን ተያይዛችሁታል፡፡ ዛሬ ቤተክርስቲያኗ እንደሰው የሚያስብ መሪ አጥታ በገንዘብ በሚገዛ ማሽኖች እየተመራች ነች፡፡ ትክክለኛዎቹ ሁሌም አደጋ ተደቅኖባቸዋል፡፡ እንደምሳሌ መምህር ግርማን የመሰሉ የሕዝብ መድሐኒት ሆነው ከአምላክ የተላኩልንን ሰው በብዙ ሺ የሚቆጠር ሕዝብን ከሚያስተምሩበትና ከሚፈውሱበት ለማገድ ብዙዎች ተባባሪዎች ናችሁ፡፡ የቤተክርስቲያን ነን የሚሉ ዜናዎችና ድረ-ገጾችንም ለመታዘብ የበቃንው በዚሁ አጋጣሚ ነበር፡፡ ሁሉም ይህ የሰው ልጆች ከብዙ ሰቆቃዎች የሚድኑበት ጉባዔ በመቋረጡ እንዴ ጮቤ እንደረገጣችሁ፡፡ ጥሩ ነው እኛም እንኳን አወቅናችሁ! አሁን ግን ስጋታችን ከነጭርሱም ቤተክርስቲያኗ እየተመራች ያለችው እውን በራሷ አማኞች ነው ወይ የሚል ጥያቄ ሁሉ በብዙዎቻችን እያጫረ መጥቷል፡፡ ግን እውን ታምናላችሁ ወይ? አብሮ ብዙ ጥያቄዎች አሉት????????????????? መልስ እንፈልጋለን!!!!!!!!

 3. Anonymous June 24, 2016 at 3:54 pm Reply

  Amen, kalehiwot yasemaln

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: