ሀገር አቀፉ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የአጠቃላይ ጉባኤ ምሥረታውን ዛሬ ያካሂዳል

 • የማደራጃ መምሪያውን የአምስት ዓመት ስትራተጅክ ዕቅድ ያጸድቃል
 • ‹‹የሰንበት ት/ቤቶች ድምፅ ከ70 በመቶ በላይ የምእመናን ድምፅ ነው፡፡››

ሰንበት ት/ቤቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች አጠቃላይ ጉባኤ ዛሬና ነገ በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በሚካሄድ ሀገር አቀፍ ስብሰባ ይመሠረታል፡፡ የመንበረ ፓትርያሪክ አጠቃላይ የሰንበት ት/ቤቶች ጉባኤ ምሥረታ የሚካሄደው በቁጥር 160 ያህል በሚኾኑ የ49 አህጉረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች በተገኙበት ነው፡፡EOTC Sunday Schoosl Geeneral Assembly

ባለፈው ዓመት ከግንቦት ፳፭ – ፳፮ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ለአጠቃላይ ጉባኤው ምሥረታ ቅድመ ዝግጅት ተጠርቶ በነበረው ሀገር አቀፍ ስብሰባ በውይይት የተተቸው የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የአምስት ዓመት ስትራተጅክ ዕቅድ ረቂቅም በዚሁ መሥራች ጉባኤ ላይ ቀርቦ የጋራ ግንዛቤና አቋም ከተያዘበት በኋላ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል፤ ከስትራቴጂ ዕቅዱ በተመነዘረው የቀጣይ አንድ ዓመት ዝርዝር ሥራዎች ላይም ጉባኤው እንደሚመክር ተመልክቷል፡፡

በአጠቃላይ ጉባኤው የቅድመ ዝግጅት ስብሰባ በተላለፈው ውሳኔ መሠረት፣ ሁለት ሁለት የማደራጃ መምሪያው አደራጅ ልኡካን በተለያዩ ቀጣናዎች በተከፈሉ አህጉረ ስብከት ስምሪት አድርገዋል፡፡ አደራጅ ልኡካኑ በአህጉር አቀፍ ስምሪታቸው የየአህጉረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ በአህጉረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች ጠቅላላ ጉባኤ አማካይነት እንዲመሠረት ማድረጋቸው ተገልጧል፡፡

የሀ/ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ 11 የሥራ አስፈጻሚ አባላት ያሉት ሲኾን ለአምስት ዓመት የሚቆይ የአገልግሎት ዘመን ይኖረዋል፡፡ ዛሬ በሚመሠረተው ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አጠቃላይ ጉባኤ 13 አባላት ያሉትና ለአምስት ዓመት የአገልግሎት ዘመን ያለው የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ምርጫ እንደሚካሄድ ተዘግቧል፡፡

በመንበረ ፓትርያሪክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሰንበት ት/ቤቶች ችግርና ፈተና ላይ ለመምከር በቂ ዕድል የሌለ መኾኑ ለአጠቃላይ ጉባኤው መመሥረት እንደ አንድ መንሥኤ ተወስቷል፡፡ ስለዚህም ዛሬ በመንበረ ፓትርያሪክ ደረጃ በይፋ የሚመሠረተው አጠቃላይ ጉባኤ በቀጣይ÷ በሀገር አቀፍና በውጭ የሚገኙ ሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች ተገናኝተው በራሳቸው ጉዳይ ላይ ተወያይተው ውሳኔ የሚያሳልፉበት፣ በመካከላቸው የሚፈጠረውን የአሠራር ልዩነት የሚያስወግዱበትና ልምድ የሚለዋወጡበት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ የሚኖራቸውን በጎ ሐሳብ ለአባቶች ውሳኔ የሚያቀርቡበት መድረክ የመፈጠሩን አስፈላጊነት አንገብጋቢ እንደሚያደርገው ተብራርቷል፡፡

EOTC Sunday Schools General Assembly00ሰንበት ት/ቤቶች በመዝሙርና በትምህርተ ወንጌል ሰፊ አገልግሎት በመስጠት ሕፃናትና ወጣቶች መሠረተ እምነታቸውንና ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲያውቁ፣ ከስሕተት ትምህርትና ከምግባር ሕጸጽ ተጠብቀው በትሕትናና ፍቅር እንዲያገለግሉ፣ በዐበይት በዓላት ነዳያንን በመመገብና በማልበስ የማይናቅ አገልግሎት በማበርከት ላይ መኾናቸውን ለአጠቃላይ ጉባኤው ዝግጅት የተሰራጨው ኅትመት ያስረዳል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ዘመኑን መዋጀት የሚችሉ፣ የዘመኑን ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ዕውቀት ያካበቱ፣ በሞያ የጎለበቱና በዘመናዊ ጥበብ የመጠቁ በመኾናቸው ከመዝሙር ባሻገር በሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም እንዲሳተፉና ከአባቶች ጋራ ተናብበው አመርቂ ሥራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ኹኔታ ማመቻቸት ለነገ የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ መኾኑ ተጠቁሟል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ከመንበረ ፓትርያሪክ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያቀደቻቸውን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተልእኮዎች ጊዜያቸውን ጠብቀው፣ ዘመኑን ዋጅተው በተሳካ መልኩ ከግብ መድረስ የሚችሉት በወጣቶቻችን ሁለገብ ተሳትፎ እንደኾነ ሁሉም ሊያምንበት እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡

የአጠቃላይ ጉባኤው ዐቢይ ኮሚቴ ጥናት ዝግጅት ክፍል ጽሑፍ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ከ60 ዓመታት ያላነሰ የአገልግሎት ልምድ አላቸው፡፡ ወጣቶች ከቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን ከ70 በመቶ በላይ ያለውን ድምፅ ይወክላሉ፡፡ በመኾኑም በዓመት ሁለት ጊዜ በሚካሄድ ሀገር አቀፍ የአንድነት ጉባኤ አንዳቸው ከሌላቸው የሚማማሩበት መድረክ ቢፈጠር ዕጥፍ ድርብ ጠቀሜታ እንደሚኖረው በማመልከት ቅዱስ ሲኖዶስ፡-

 • ሰንበት ት/ቤቶች እንደጾታቸውና ዕድሜ ክልላቸው የተቀረጸ፣ በማስተማርያ መጻሕፍት የተደገፈ፣ በቂ ሥልጠና ባገኙ መምህራን የሚሰጥ፣ አፈጻጸሙ የቅርብ ክትትል የሚደረግበት ሥርዐተ ትምህርት እንዲዘጋጅ፤
 • የሰንበት ት/ቤቶችን አገልግሎት በተመለከተ ያለው የተዛባ አመለካከት እንዲስተካከል፤
 • ሰንበት ት/ቤቶች ዘመኑን የዋጀ ሥራ መሥራት ይችሉ ዘንድ ከቢሮ ዕቃዎች ጀምሮ የአገልግሎት መሣርያዎች ሁሉ እንዲሟሉላቸው፣ በቂ በጀት እንዲመድብላቸው በማድረግ ቤተ ክርስቲያን የአሳዳጊነት ሓላፊነቷን እንድትወጣ፤
 • የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በበቂ የሰው ኀይልና በጀት እንዲደራጅና እንዲጠናከር፤
 • ቤተ ክርስቲያን የበርካታ ክህሎት ባለቤት የኾኑ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ሞያዊ አቅም ለመጠቀም የሞያ አገልግሎት ማእከል ቢኖራትና ከፍተኛ ወጪዎቿን እንድትቀንስ፣ በምትኩ ሰንበት ት/ቤቶች ላልተቋቁሙባቸው አጥቢያዎች ትኩረት እንድትሰጥ፤
 • ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት አባላት ብዛት በዕድሜ፣ በጾታ፣ በትምህርት ደረጃና በሞያ መስክ ለይታና መዝግባ በመያዝ አካባቢያዊ፣ ሀገር አቀፋዊና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶችን ያገናዘበ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላት ከአጥቢያ እስከ ቅ/ሲኖዶስ መዋቅሩን ጠብቆ የሚደርስ ሥርዐት እንድትዘረጋ፤
 • ቤተ ክርስቲያን በስፋትና ልቀት ሊጠኑ የሚችሉ የዕውቀት፣ ሥልጣኔና ታሪክ ማእከል ናት፤ የወጣቱም ዕውቀትና ሞያ ፈርጀ ብዙ ነው፤ በመኾኑም እንደ ተሰጥኦው በሚሻው የቤተ ክርስቲያን ጥናትና ምርምር ዘርፍ እንዲሰማራ የሚያበረታታ አሠራር እንዲኖር ትኩረት እንዲሰጥበት ጠቁሟል፡፡

የነገውን ምርት ለመሰብሰብ የዛሬው እርሻ ወሳኝ ነው፡፡ የአባቶችን አደራ የሚረከቡት ዉሉደ አበው ወራዙት ናቸው፡፡ የነገዎቹ ጳጳሳት የዛሬ ወጣቶች ናቸው፡፡ የነገዎቹ ካህናትና የሰበካ ጉባኤ መሪዎች ዛሬ ተፍ ተፍ የሚሉት ሰንበት ተማሪዎች ናቸው፡፡ ትኩረት ለወጣቶች! ትኩረት ለሰንበት ተማሪዎች!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች

ትላንት፣ ዛሬና ነገ

ምንጭ፡- በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መ፣ መጽሔተ ወራዙት፤ ግንቦት ፳፭ ቀን ፳፻፬ ዓ.

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በጉዞዋ ሁሉ ወጣቱን ከጎልማሳውና ከአረጋውያን ጋር በማጣመር መልካም የሆነ መንፈሳዊና ሀገራዊ ልማት ስታካሒድ ኖራለች፤ በተለይም ደግሞ በትምህርት ዘርፍ ወጣቱን ከሕፃንነቱ ጀምሮ በማስተማር ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉት የአአምሮና የመንፈስ እድገት የተሟላ እንዲሆኑ ስትሠራ ቆይታለች፤ ወደፊትም ትሠራለች፡፡ ዛሬ ባለው የቤተ ክርስቲያኗ መዋቅር ወጣቱን አሰባስቦ አደራጅቶ የማስተማር እና በአእምሮም ሆነ በመንፈስ የጎለበት ሆኖ እንዲያድግ የማድረግ ኃላፊነት የተጣለው በሰንብት ት/ቤቶች ላይ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች አሠራር መታየት የጀመረው በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህም ዘመን የዘመናዊ ትምህርት ሐሳብ ወደ ሀገሪቷ መግባት የጀመረበት  ከመሆኑ የተነሳ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለወጣቱ የምታስተምርበት መንገድ ወደ አዲስ መንገድ እንደቀየረው ይታያል፡፡ ቀደም ሲል መማር የፈለገ ወጣት ሁሉ በቤተ ክርስቲያን መስመር ውስጥ የሚያልፍበት ዘመን ነበር፤ ለቤተ ክህነትም ሆነ ለቤተ መንግሥት አገልግሎት የሚያፈልገውን የሙያ እውቀት ከቤተ ክርስቲያን የትምህርት ሥርዐት የሚያገኝበት ዘመን ነበር፡፡

ከዚህም የተነሣ ወጣቶች ወላጆቻቸውን ትተው፣ ሙሉ ሕይወታቸውን ሰጥተው ወደ አብነት ት/ቤት በመግባት ተጠልቆ  ከማያልቀው  የእውቀት ማዕድ የቻሉትን ያህል በብዙ ድካም ሸምተው ገሚሱ የመምህራቸውን ወንበር በመተካት  አልያም በተለያዩ ቦታዎች ወንበር ዘርግቶ ቀጣይ ትውልድ የማፍራት ሥራ ላይ ይሰማሩ ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ በተለያዩ የቤተ ክህነትና የቤተ መንግስት የሥራ ዘርፎች በመሰማራት ሀገርና ሕዝብን ያገለግሉ ነበር፡፡

በዋናነት የአባቶች ተተኪ መሆን የወቅቱ ወጣት ዋነኛ ዓላማ ነበር፡፡ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ የተከሠተው የዘመናዊ ትምህርት ሐሳብ ወደ ሀገራችን መምጣቱ ግን ወጣቱን ለሁለት ከፈለው፡፡ ወላጆቹን ትቶ ‹‹በእንተ ስማ ለማርያም ›› እያለ ከምእመናን የዕለት ምግብ እያሰባሰበ በአብነት ት/ቤት የሚማር ወጣትና  መኝታና ምግቡ በሞግዚት እየተዘጋጀለት በዐዳሪ ት/ቤት የሚማሩ በሚል፡፡  በተለይ የዐዳሪ ት/ቤት የወጣቱን ስሜት እየሳበው በመምጣቱ ወደ አብነት ት/ቤት ከሚሄደው ወጣት ይልቅ ወደ ዘመናዊ ት/ቤት የሚገባው ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል፡፡

ከዚህም የተነሣ ቤተ ክርስቲያን ወጣቱን የምታስተምርበት ሁኔታ በመለወጥ በዘመናዊ ትምህርት ከሰኞ እስከ ዐርብ የሚማረውን ትውልድ በመንፈሳዊ ዕድገቱም የተስተካከለ ይሆን ዘንድ ፈቃደኛ በሆኑ ወጣቶችና ካህናት አነሣሽነት የቅዳሜና እሑድ ት/ቤቶችን ማቋቋም ጀመረች፡፡ ይህ ደግሞ ዛሬ ያለውን የሰንበት ት/ቤቶች እንቅስቃሴ መሠረት ጣለ፡፡Temiro Mastemar Sunday School

የቅዳሜና እሑድ ት/ቤት በኢትዮጵያ መቋቋም የጀመረው ከ1939 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ መሠረቱ የተጣለውም በጊዜው “የተፈሪ መኰንን ት/ቤት” በሚባለው በዛሬ ስሙ እንጦጦ ሙያ እና ቴክኒክ ት/ቤት ውስጥ ነው፡፡ መሥራቹም ከተፈሪ መኰንን ት/ቤት እና ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ አንዳንድ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተቆርቋሪ ተማዎች ናቸው፡፡ ምክንያት የሆናቸው በዩኒቨርስቲው ውስጥ በአስተማሪነት ያገለግሉ የነበሩ “ኢየሱሳውያን” የሚባሉ ሚሲዮናውያን ዘመናዊ ትምህርት ለመማር ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚገባውን ወጣት  የኑፋቄ ትምህርታቸውን  ማስተማር ከእናት ቤተ ክርስቲያኑ ያስኮበልሉት በመጀመራቸው ነው፡፡

በተፈሪ መኰንን ት/ቤት የተጀመረው የኦርቶዶክሳዊያን ወጣቶች እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ወደ መስከየ ኅዙናን መድኅኔ ዓለም ገዳም ተዛውሮ ተምሮ ማስተማር የወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበር ተመሥርቶ ሕፃናትና ወጣቶች በተለያዩ የማስተማር ዘዴ ሥራውን ቀጠለ፡፡  በነበረው ምቹ ሁኔታ በመታገዝ  ወደ ቅድስት ሥላሴ፤ ታዕካ ነገሥት፤ መንበረ መንግሥት ቅ/ገብርኤል  እና ወደ ሌሎችም አካባቢዎች ለመስፋፋት ችሏል፡፡

በ1960 ዓ.ም ይህ የሰንበት ት/ቤቶች  እንቅስቃሴ ላማስተባበር ለማጠናከር ይቻል ዘንድ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በስብከተ ወንጌልንና ማስታወቂያ መመሪያ ሥር ማእከላዊ ጽ/ቤት  ተቋቁሞለታል፤ ስያሜውም የሰንበት መምህራን ጽ/ቤት ይባል ነበር፡፡  ይህም ጽ/ቤት  በዋናነት ከመንፈሳዊ ኮሌጅ እና ከሌሎችም ከፍተኛ ት/ቤቶች ያሉ ደቀ መዝሙሮችን “የሰንበት መምህራን” በሚል ስያሜ በአዲስ አበባ ታላላቅ አድባራትና በዘመኑ በነበሩት 14ቱ ክፍለ ግዛቶች አልፎ አልፎ በአውራጃና በወረዳም ጭምር የመመደብ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ በኋላ በ1965 ዓ.ም  ራሱን ችሎ ወደ ወጣቶች ጉዳይ መምሪያነት አደጎ የተለያዩ የወጣቶችንና መንፈሳዊ ማኅበራትን ያስተባበር ጀመር፡፡

ከ1970 – 1982 ዓ.ም

ይህ ምዕራፍ በኢትዮጵያ ሰ/ት/ቤቶች ታሪክ ታላቅ ድርሻ ያለው ክፍለ ጊዜ ነው፡፡ የሰንበት ት/ቤቶች ሕልውና በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ተቀባይነት አግኝቶ “ሰንበት ት/ቤት”  በሚል ስያሜ ይዞ ሕጋዊ ሆኖ  እንዲቀጥልና በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሰንበት ት/ቤቶች እንዲቋቋሙ የተቋቋሙትም እንዲጠናከሩ በ1970 ዓም ተሻሽሎ በተዘጋጀው ቃለ ዐዋዲ ጸድቋል፡፡  ለዚህም ከብፀዕ ወቅዱስ አቡነ ተ/ሃይማኖት ፓትሪያርክ ርእሰ ሊቀነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ሊቃውንት፣ ካህናትና ምእመናን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ በማያያዝም 1976 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀ መተዳደሪያ ሕግ እና ሥርዐተ ትምህርት ተሰጥቶታል፡፡

ነገር ግን ይህ ወቅት ኢትዮጵያን ይመራ የነበረው የደርግ መንግሥት ራሱን ካረጋጋ በኋላ ያዋጣኛል የሚለው መንግሥት የሚመራበት ርእዮተ ዓለም ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የተለየ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያንን ገፍቶ ለመጣል የተለያዩ ርምጃዎች የወሰደበት ጊዜ ስለነበር በሰንብት ት/ቤቶች ዕድገት ላይ ታላቅ ተጽዕኖ ፈጥሯል፡፡ በተለይም ወጣቱ በአንድ ሀገራዊ የወጣት ማኅበር ብቻ ለማሰባስብ በነበረው አቋም ወጣቶች ወደ ሰንበት ት/ቤቶች እንዳይመጡ ገደብ ያደርግባቸው ነበር፡፡ በተጨማሪም በ1970ዎቹ መጨረሻ  የነበረው ጦርነት እየተፋፋመ ሲመጣም ወጣቱ ለጦርነት ይፈለግ ስለነበር በሰንብት ት/ቤት እንደልብ መሰብሰብ  አዳጋች ሆነ፡፡ ከዚህም የተነሳ አባዛኛዎቹ ሰንበት ት/ቤቶች የሕፃናት እና የአዳጊዎች መዋያ ብቻ እንዲሆን  አስገደዳቸው፡፡

ከ1983 ዓ.ም በኋላ

ቀደም ሲል በወጣቶች ላይ የነበረው የመንግሥት ተጽእኖ በመነሳቱ፣ የፕሮቴስታንስ መናፍቃን በወጣቱ ላይ ያደረጉት ወረራ የፈጠረው ቁጭት እና ሌሎቸ በጎ አጋጣሚዎች ተጨምረው ወጣቱ ፊቱን ወደ ቤተ ክርስቲያን የመለሰበትና በወጣቱ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እመርታ የታየበት ነው፡፡ ቀደም ሲል ‹‹ እግዚአብሔር የለም ›› በሚል ርእዮተ ዓለም የተመታውና ፕሮቴስታኒዝምን እንደ ስልጣኔ ይመለከት የነበረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪ ፊቱን ወደ ቤተ ክርስቲያን መመለሱ የሰንበት ት/ቤቶች አገልግሎት ከፍ ወዳለ ምዕራፍ እንዲሸጋገር ምክንያት ሆኗል፡፡

ከዚህም የተነሳ በ1986 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች መተዳደሪያ ደንብ በቅዱስ ሲኖዶስ  ጸድቆ በሥራ ላይ መዋሉ፤ መንፈሳዊ፣ ብሔራዊ በዓላት እና የንግሥ በዓላት በታላቅ ድምቀት እንዲከበሩ ሥርዓት በማስያዝ እና የዝማሬ አገልግሎት በማበርከት፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጥሪ እየደረሳቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚጎርፉትን ወጣቶች መሠረታዊ የክርስትና እምነት ትምህርት መርሐ ግብር ዘርግቶ በማስተማር በኮርስ መልክም በማሰልጠን እና የሰንበት ት/ቤት አባል በማድረግ፤ የስብከተ ወንጌል ፕሮግራም እንዲጠናከርና እንዲስፋፋ በዐውደ ምህረት በሰባኪነት፣ ፕሮግራም በመምራት፣ ያሬዳዊ ዝማሬ በማቅረብ፣ ምዕመናንን በማስተባበርና በማስተናገድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣት አገልጋዮችን በማፍራት፤ የወንጌል ሥርጭትን ለማስፋፋት የሚያግዙ ቋሚ መጽሔትና ጋዜጣ  በማዘጋጀት እንዲሁም በተልዕኮ ትምህርት በመስጠት፤ በማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ደግሞ በዐበይት በዓላት ነዳያንን በመመገብ፣ የተለያዩ አልባሳትን በማደል፣ ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ አዳጊ ሕፃናትንና ወጣቶችን በጎ አድራጊ ምእመናንን በማስተባበር የገንዘብ፣ የትምህርት መርጃ መሳሪያ የምግብ ድጋፍ በማድረግ፣ ዩኒፎርም በማስፋት ትምህርታቸውን ያለችግር ተከታትለው የነገይቱ ኢትዮጵያ ተረካቢ መልካም ዜጋ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠቃሽ ነው፡፡

ሰንበት ት/ቤቶች ምእመናን ጥንታዊና ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ገዳማትን ቅርሳ ቅርሶችን እየጎበኙ መንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያነቃቁ፣ በረከትን እንዲቀበሉ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው የበለጠ እንዲያውቁና በጉዞውም ወቅት በሚፈጠር ቅርርቦሽ መንፈሳዊ ሕብረት፣ አንድነትና ቤተሰባዊ ስሜት እንዲዳብር መንፈሳዊ የጉዞ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት፤ ገቢ በማጣትም ይሁን በልዩ ልዩ ምክንያቶች ለተዘጉ ወይም መቀደሻ ልብሰ ተክህኖ፣ ዘቢብ፣ ዕጣን፣ ጧፍ በማጣት አገልግሎት መስጠት ለሚቸገሩ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎታቸው እንዳይቋረጥ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴና ድጋፍ ሊጠቀሱ የሚችሉ የሰንበት ት/ቤቶች አገልግሎቶች ናችው፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሰንብት ት/ቤቶች ምንም እንኳን የጠቀስናቸውንና መሰል ተግባራት እያከናወኑ ቢሆንም ከሚጠበቅባቸው አንጻር ሲታዩ ገና ያልደረሱባቸው በርካታ አዝመራዎች አሉ፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው ሰ/ት/ቤቶታቻትን ከ65 ዓመታት ያላነሰ ልምድ እና ተሞክሮ ቢኖራቸውም ለቤተ ክርስቲያን ተተኪ አገልጋይ የሚሆን ትውልድ ከማፍራት አኳያ ብዙ አልተጓዙም፡፡

በየጊዜው በተለዋዋጭነት የሚመጡ የወጣቶች ፈተናና ተግዳሮት መቋቋም የሚችል በአእምሮውም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የበለጸገ ወጣት ከማፍራት አንጻር፣ በቃለ ዐዋዲውም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተዘጋጀው የሰ/ት/ቤቶች መተዳዳሪያ ደንብ ላይ የተቀመጠላቸውን ዓላማ እና ግብ ከማሟላት አንጻር ሲታዩ ሰንበት ት/ቤቶቻችን ገና ብዙ የሚቀራቸው መሆኑ ይታያል፡፡SSD GEneral Assembly 03

ለዚህ ክፍተት መፈጠር  በሀገሪቱ ያሉት ሰንበት ት/ቤቶቻችን ወጥነት ያለው አንድ ዓይነት አሰራር የሌላቸው መሆኑ፤ እርስ በርስ ተገናኝተው አሠራርንም ሆነ ልምድን የሚለዋወጡበት መድረክ የሌላቸው በመሆኑ ነው፡፡ እንዲሁም ዘመኑን የዋጀ ወደ ሰንበት ት/ቤት የሚመጣውን ወጣት እንደ ዕድሜውና ዕውቀቱ መጠን ከፋፍሎ ማስተማር የሚያስችል ሥርዓተ ትምህርት ባለመኖሩ፤ ሰንበት ት/ቤቶችን እንዲያቋቁም፣  እንዲያደራጅ  እና እንዲያስተባበር  ኃላፊነት የተሰጠው የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በሰው ኃይል፣ በበጀት፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በበቂ ሁኔታ ያልተደራጀ መሆኑ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው፡፡

ስለዚህ ትላንት የነበረንን ማንነት ተረድተን፣ ዛሬ ያለንበት ጠንካራ እና ደካማ ጎን ገምግመን ስለነገ ማሰብ፣ ዛሬ ያለው ክፍተት ለመቅረፍ መነሳት ወቅቱ የሚጠይቀው አስተዋጽኦ ነው፡፡

ስለሆነም ቤተ ክርስቲያንን ለሰንበት ት/ቤቶች የሚከተሉትን ሁኔታዎች ልታመቻች ያስፈልጋል፡፡

1.  ሀገር አቀፍ የአንድነት ጉባኤ

በዓመት ሁለት ጊዜ የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡ ይነስም ይብዛ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮችም እንዲገኙ ሙከራ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ የሰንበት ት/ቤት ችግር እና ፈተና ላይ ለመምከር ዕድል ተገኝቶ አይታወቅም፡፡ በመሆኑም ከሀገር አቀፍ ሰንበት ት/ቤቶችም ሆነ በውጭ ሀገር ከሚገኙ ሰንበት ት/ቤቶች የተውጣጡ ተወካዮች ተሰባስበው በራሳቸው ጉዳይ ተወያይተው ውሳኔ የሚያስተላልፉበት፤ በመካከላቸው የሚፈጠረውን የአሠራር ልዩነት የሚያስወግዱባት፣ እና ልምድ የሚለዋወጡበት ከዚህም ባሻገር በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ የሚኖራቸውን በጎ ሐሳብ ለአባቶች ለውሳኔ የሚያቀርቡበት ጉባኤ መኖሩ እጅግ በጣም አንገብጋቢ ነው፡፡

የሰንበት ት/ቤቶች ድምጽ ማለት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን ምናልባትም ከ70 በመቶ በላይ ያለው ክርስቲያን ድምጽ ማለት ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ምእመን ድምፅ ሊሰማ የሚችለው በዓመት ቢያንስ ሁለት ጊዜ ሊካሄድ በሚችል የአንድነት ጉባኤ ነው፡፡ አንዱ ከሌላው የሚማርበት መድረክ ከመሆኑም አኳያ ጠቀሜታው እጥፍ ድርብ ነው፡፡ ይህንንም በተመለከተ ቅዱስ ሲኖዶስ ትኩረት ሰጥቶ ሊያየው ይገባል፡፡

2.  ሥርዐተ ትምህርት

በሰንበት ት/ቤቶች ታሪክ ከ60 ዓመታት ያላነሰ ልምድ ያለን ይሁን እንጂ 60 ዓመት ሙሉ በጥንካሬ ሠርተናል ማለት አይቻልም፡፡ ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ወጥ የሆነ ሥርዓተ ትምህርት አለመኖሩ መሠረታዊ የችግሩ ምንጭ ነው፡፡ ሥርዓተ ትምህርት አለ ማለት፤

 • የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች እንደየዕድሜ ክልላቸው እና እንደየጾታቸው መጠን የተጠና የትምህርት ዓይነት እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡
 • ሥርዓተ ትምህርት ካለ በቂ የማስተማሪያ መጻሕፍት ስለሚዘጋጁ በየትኛውም አጥቢያ የሚሰጠው ትምህርት ተመሳሳይነት እና ወጥነት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ይህ በሆነ ጊዜ የሰንበት ት/ቤት ተማሪው በተለያየ ምክንያት ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የሚዘዋወር ቢሆን እንኳ ያለምንም ችግር ካቆመበት እንዲቀጥል ዕድል ያገኛል፡፡
 • የሚሰጠው ትምህርት በመምህሩ ፍላጎት እና ዝንባሌ መመሥረቱ ይቀርና ሥርዓተ ትምህርቱ በሚመራው ስለሚሆን የተማሪዎችን የዕውቀት ደረጃ ለማመጣጠን ከፍተኛ ዕድል ይሰጣል፡፡
 • በተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ለየትምህርቱ ዓይነት የሚመጥኑ መምህራን እንዲመደቡ ያስገድዳል፡፡ ዛሬ ያሉት የሰንበት ት/ቤት መምህራን በበጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የመነጨ አገልግሎት እንጂ መዋቅሩ ወይም ሥርዓተ ትምህርቱ በሚፈቅደው መሠረት የተመደቡ አይደሉም፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን እነዚህን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ መምህራን ዕውቅና የምትሰጥበትን ሥርዓት ዘርግታ በተጠናከረ መንገድ አገልግሎታቸው እንዲቀጥል ልታደርግ ይገባታል

3. የሰንበት ት/ቤቶችን አስፈላጊነት ማስረዳት

ምንም እንኳን ከ60 ዓመታት ያላነሰ ልምድ ቢኖረንም ሰንበት ት/ቤቶችን በተመለከተ ያለው ግንዛቤ አሁንም ድረስ አስደሳች አይደለም፡፡ ከወላጆች እስከ ካህናት /ሁሉም ባይሆኑም/ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ አንዳንዶች እንደ ጊዜ ማሳለፊያ የሚቆጥሩት ሲሆን ሌሎች ደግሞ ከበሮ ከመምታት የዘለቀ ፋይዳ እንደሌላቸው ይመስላችዋል፡፡ የተቀሩት ደግሞ በዓል አድማቂ ብቻ አድርገው ያስቧቸዋል፡፡ ስለሆነም የተዛባ አመለካከት ያላቸው ሁሉ አስተሳሰባቸውን እንዲቀይሩና በተሰናሰለ ሁኔታ የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ የሚሳካበትን መንገድ እንዲቀይሱ ማድረግ ከእንግዲህ ይደር ሊባል አይገባውም፡፡

በዛሬዎቹ ወጣቶች ዓይን ነገን ማየት የምንችለው ይህ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ እስካሁን ወጣቱ የተባለውን ቢባልም ያንን በመቋቋም ጠፍቶ ወይም ተሰድዶ ከማለቅ ይልቅ የተንጋደደውን አመለካከት እየተጋፈጠ በመቆየቱ ምስጋና ይገባዋል፡፡ መጪው ትውልድ እንደዚህ ያለውን ስሑት አስተሳሰብ የሚሸከምበት ትክሻ አይኖረውምና ቀድመን ተመቻችተን ልንቀበለው ያስፈልጋል፡፡

4.  ሙዓለ ንዋይ መመደብ

ሰንበት ት/ቤቶች ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት እንዲችሉ ከጽ/ቤት ዕቃዎች ጀምሮ እንደ ወረቀት፣ እስክርቢቶ፣ ኮምፒዩተር፣ ፕሪንተር፣ የኢንተርኔት አገልግሎት፣ ፕሮጀክተር፣ የመዝሙር ልብስ፣ መቋሚያ፣ ጸናጽል፣ ከበሮ … ወዘተ ሊሟሉላቸው ይገባል፡፡ ከዚህም ባሻገር የመማሪያ አዳራሾች፣ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች፣ ቅዱሳት መጻሕፍት የድራማ ቁሳቁስ … ወዘተ እጅግ በጣም አስፈላጊ እና የሰንበት ት/ቤቶችን እንቅስቃሴ ለማከናወን ወሳኝ እንደመሆናቸው መሟላት እንደሚገባቸው የማያምን አለ ማለት አይቻልም፡፡ በስንት ልፋትና መከራ የሰንበት ት/ቤት አዳራሽ ከሠሩ በኋላ ለገቢ ማስገኛ እየተባለ አዳራሻቸው ለውጭ ተገልጋይ እስከመከራየት እየደረሰ ባለበት ሁኔታ ይህንን ወጣት ነገ አገኘዋለሁ ብሎ ማሰብ ቅዥት ይሆናል፡፡ ይልቁንም በቂ በጀት በመመደብ አስፈላጊ እና መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች እንዲሟሉ ማድረግ ይገባል፡፡ ከሰንበት ት/ቤቶች ባሻገር ለሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥና ተግባሩን መወጣት በሚችልበት መጠንና ደረጃ አስፈላጊውን የሰው ኃይልና በጀት ሊጠናከር ይገባዋል፡፡

5.  የሞያ አገልግሎት

የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የበርካታ ሙያ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሁሉም መስክ የሙያ አገልግሎት ያስፈልጋታል፡፡ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ከሌሎች አገልግሎት ከመጠየቅ ይልቅ በራሷ ልጆች የመሥራት ልምድ ሊኖራት ይገባል፡፡ ወደ ውጭ መሄድ ያለበት ከቤቷ አገልግሎቱን የሚሰጥ ሳይኖር ሲቀር ብቻ መሆን አለበት፡፡ ይልቁኑ ለዚህ አገልግሎት የምታወጣውን ሰንበት ት/ቤት ባልተቋቋመባቸው አጥቢያዎች ለማቋቋም ብታውለው እጅግ በጣም ይጠቅማታል፡፡ ስለሆነም የተጠናከረ የሙያ አገልግሎት ማዕከል በማቋቋም በሁሉም ዘርፍ የሰለጠነና ደረጃውን የጠበቀ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ ወጣቱ ዕውቀቱንና ገንዘቡን እንዲሁም ጉልበቱን ለመስጠት ምንጊዜም ፈቃደኛ ነውና፡፡

6.  ክትትልና ቁጥጥር

ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ወቅት ምን ያህል የሰንበት ት/ቤት አባላት እንዳሏት ከማወቅ ጀምሮ በየትምህርት ደረጃቸው እና በጾታቸው፣ በሙያቸው እና በዘመናዊ መስክም በትምህርት ደረጃቸው ለይታ መዝግባ ቆጥራ እና ሰፍራ መያዝ ይጠበቅባታል፡፡ በተለያዩ ዘመናት ለሰንበት ት/ቤት ተማሪዎ ተግዳሮት የሆኑባቸውን ጉዳዮች በመለየት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት፣ በየአጥቢያው ያሉ አካባቢያዊ፣ ሀገር አቀፋዊ ወይም ዓለማቀፋዊ ኩነቶችን ያገናዘበ ትምህርት ማስተማር ከቤተ ክርስቲያን ይጠበቃል፡፡ በየአጥቢያው ሥርዓተ ትምህርቱን መሠረት ያደረገ ሥርዓት መዘርጋቱንና ተፈጻሚነቱ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መከታተል ያስፈልጋል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤት መዋቅሮች በአግባቡ እየሰሩ መሆናቸውንና አለመሆናቸውን መቃኘት ያስፈልጋል፡፡ ወጣት እና ሕፃናቱ ተገቢውን መንፈሳዊ ስነ ምግባር መላበሳቸውን ማረጋገጥ፣ ክፍተቶች ሲከሠቱም የሚሟሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ወጣቱ ከቤተ ክርስቲያን የሚጠብቀው የአሳዳጊነት ኃላፊነት ነው፡፡ በዚህም ረገድ ከአጥቢያው ሰበካ ጉባኤ ጀምሮ መዋቅሩን ጠብቆ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ የሚደርስ ሥርዓት መዘርጋት ይገባዋል፡፡

7.  የጥናት እና የምርምር ማዕከል ማቋቋም

ወጣቱ ትውልድ ፈርጀ ብዙ የሆነ የዕውቀት ባለቤት እየሆነ መሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ሊጠኑ የሚገባቸው እጅግ በጣም ረቂቅ እና ሰፊ የሆነ ሀብት ያለባት የዕውቀት፣ የሥልጣኔ እና የታሪክ ማዕከል ናት፡፡ እነዚህ መንፈሳዊ እሴቶች እንኳን ተጠንተዋል ሊባል ይቅርና በሥነ ሥርዓት ተቆጥረው እና ተመዝግበው አልተያዙም፤ በጊዜ የማይደረስላቸው ከሆነም ልናጣቸው የምንችልበት ጊዜ ብዙ ሩቅ አይሆንም፡፡

ይህን ስጋት በአጭር ማስቀረት የሚቻለው ባለሙሉ ፍላጎቱን ወጣት እንደየተሰጥኦው በተለያዩ የጥናትና የምርምር ዘርፎች ማሰማራት ከተቻለ ብቻ ነው፡፡ በባዕዳን ወይም በሩቅ ሀገር ሰዎች ጥናትና ምርምር ብቻ የልብን ማድረስ አይቻልም፡፡ የዳበረ ልምድ እና አቅም ያላቸውን ወጣቶች በሚገባ በማደራጀት በጥቂት ወጪ ብዙ መሥራት ይቻላል፡፡ ከብራና መጻሕፍት እስከ ኪነ ጥበብ ከአድማስ እስከ አድማስ የተዘረጉት የቤተ ክርስቲያን ሀብቶች ሊተረጉሙ፣ ሊታወቁ፣ በአግባቡ ለቀጣዩ ትውልድ ከነሙሉ ክብራቸው ሊተላለፉ የሚችሉት በዚህኛው መንገድ በሩ የተከፈተ እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ሰንበት ት/ቤቶቻችን ሊደረጁ የሚችሉበትን መንገድ ከወዲሁ ማሰብ እና ማጥናት ተገቢ ነው፡፡

ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ከብዙ በጥቂቱ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች በኩል ለወጣቱን ልታደረገው የሚገባትን ለማመላከት የቀረቡ ናቸው እንጂ ሊሠሩ የሚገባቸው እነዚህ ብቻ ናቸው ብሎ ለመደምደም አይደለም፡፡ ያለምንም ተጨማሪ ቀጠሮ እነዚህን ተግባራዊ ማድረግ እጅጉን ያተርፋል፡፡ የነገ ተረካቢዎች ስንቅ ሳይዘጋጅላቸው፣ መንገዱ ሳይቀየስላቸው መሽቶ መንጋት የለበትም፡፡

የነገውን ምርት ለመሰብሰብ የዛሬው እርሻ ወሳኝ ነው፡፡ የአባቶችን አደራ የሚረከቡት አባቶች አይደሉም፤ ወጣቶች ናቸው፡፡ ነገ እነርሱ ናቸው፡፡ የነገዎቹ ጳጳሳት ዛሬ ወጣቶች ናቸው፣ የነገዎቹ ካህናት ዛሬ ሰንበት ተማሪዎች ናቸው፣ የነገዎቹ የሰበካ ጉባኤ መሪዎች ዛሬ ተፍ ተፍ የሚሉት ሰንበት ተማሪዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ወጣቶች በማፍራትና በመከባከብ ላይ አተኩራ ልትንቀሳቀስ ይገባታል፡፡

 

                                                               ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                       ከዐቢይ ኮሚቴ ጥናት ዝግጅት ክፍል

Advertisements

3 thoughts on “ሀገር አቀፉ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የአጠቃላይ ጉባኤ ምሥረታውን ዛሬ ያካሂዳል

 1. Anonymous June 26, 2013 at 2:32 pm Reply

  ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሪዎች በሙሉ
  ጥንትም ጌታን ሲቃወሙ የነበሩ እንነማን እነደሆኑ ማስተዋሉን ቢሰጣችሁ እናውቃለን የሚሉ ካህናትና የካህናት አለቆች ነበሩ፡፡ ዛሬ እናንተ የጥንቶቹን የጌታን ተቃዋሚዎች በብዙ መልክ ብዙዎቻችሁ እየመሰላችኋቸው እንደመጣችሁ ብታስተውሉ መልካም ነበር፡፡ ግን እየሆነ ያለ አይመስልም፡፡ በአስተዳደሩ የሄው ቤተክርስቲያኒቱን ለሁለት ከፍላችሁ ሕዝቡን ውዥምብር ውስጥ መክተታችሁ ሳይሆን የእናንተ ጭንቀት የራሳችሁን የበላይ መሆንን ነው፡፡ በሥጋዊ እንኳን ስለሕዝብ እኔ የቅርብኝ የሚል ብዙ ሰው አለ፡፡ እናነተ ጋር ግን አልተቻለም፡፡ መፍትሔው ለብዙዎቻችን ቀላልና የግለሰቦች ፍቃድ ብቻ የሚጠይቅ እንደሆነ ብናውቅም ይሄው በአልሸነፍነት ዘልቃችሁበታል፡፡ መፍትሄ እናመጣለን የሚሉትም ግራ አጋቢ ስልት ሲጠቀሙ ይታያል፡፡ እናንተ ይቅር ለማለት እንዲ የከበዳችሁ እውን የቤተክርስቲያን ቅንዐት እንዳልሆነ ውስጣችሁ ያውቀዋል፡፡ እሱን እንደ ሕዝብነታችን ምንም ማድረግ ስላልቻልን ተውናችሁ፡፡ አሁን ደግሞ እኛን ወደሕይወትና ደህንነት የሚያመጣ ትምህርትና ስነምግባር ላይ ማውደሙን ተያይዛችሁታል፡፡ ዛሬ ቤተክርስቲያኗ እንደሰው የሚያስብ መሪ አጥታ በገንዘብ በሚገዛ ማሽኖች እየተመራች ነች፡፡ ትክክለኛዎቹ ሁሌም አደጋ ተደቅኖባቸዋል፡፡ እንደምሳሌ መምህር ግርማን የመሰሉ የሕዝብ መድሐኒት ሆነው ከአምላክ የተላኩልንን ሰው በብዙ ሺ የሚቆጠር ሕዝብን ከሚያስተምሩበትና ከሚፈውሱበት ለማገድ ብዙዎች ተባባሪዎች ናችሁ፡፡ የቤተክርስቲያን ነን የሚሉ ዜናዎችና ድረ-ገጾችንም ለመታዘብ የበቃንው በዚሁ አጋጣሚ ነበር፡፡ ሁሉም ይህ የሰው ልጆች ከብዙ ሰቆቃዎች የሚድኑበት ጉባዔ በመቋረጡ እንዴ ጮቤ እንደረገጣችሁ፡፡ ጥሩ ነው እኛም እንኳን አወቅናችሁ! አሁን ግን ስጋታችን ከነጭርሱም ቤተክርስቲያኗ እየተመራች ያለችው እውን በራሷ አማኞች ነው ወይ የሚል ጥያቄ ሁሉ በብዙዎቻችን እያጫረ መጥቷል፡፡ ግን እውን ታምናላችሁ ወይ? አብሮ ብዙ ጥያቄዎች አሉት????????????????? መልስ እንፈልጋለን!!!!!!!!

 2. Anonymous June 28, 2013 at 5:02 am Reply

  Time is for the Sunday Schools. Wonderful, we will be there with you.

 3. mkindaya February 17, 2016 at 2:18 pm Reply

  በናታችሁ የሰ/ት/ቤት ታሪክን ከብሉይ ኪዳን እስከ ሐዲስ ኪዳን በተለይም በአምስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት ያለውን አስረዱኝ ለሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች ለማስረዳት መረጃ ስላጣን ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: