ለሃይማኖት፣ ለሀገርና ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማበርከት የሚገባውን ሁሉ በብቃት ለመሥራት ከምንጊዜውም በላይ መዘጋጀቱን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ

 • የዕርቀ ሰላም ውይይቱ ኹኔታዎች ተመቻችተው እንዲቀጥል መወሰኑን ቅ/ሲኖዶሱ አስታውቋል
 • ለሙስናና ብክነት የተጋለጡ አሠራሮችን ወሳኝ በኾነ መልክ ለመቅረፍ፣ ቤተ ክርስቲያን የምትመራበትን መሪ ዕቅድ ለመቀየስ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንት፣ ካህናትና ምሁራን  ምእመናን ያሉበት ዐቢይ ኮሚቴ እንዲቋቋም ቅ/ሲኖዶስ በአንድ ድምፅ ወስኗል
 • የሕዳሴው ግድብ ተጠናቆ ጥቅም ላይ እስኪውል ድረስ ቤተ ክርስቲያን ድጋፏን አታቋርጥ
 • በመካከለኛው ምሥራቅና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ለሥራ ፍለጋ በሕገ ወጥ መንገድ በሚሄዱ ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም በኹኔታው ጎጂነት ላይ ግንዛቤ የሚፈጥር ትምህርት በስፋት እንዲሰጥ ቅ/ሲኖዶስ ለመምህራን፣ ካህናትና ሰባክያን ሁሉ መመሪያ ሰጥቷል
 • ለቤተ ክርስቲያን ክብርና ሉዓላዊነት መጠበቅ፣ ለህልውናዋ መቀጠልና ለዕድገትዋ መስፋፋት የሚቆረቆሩ የቤተ ክርስቲያናችን አገልጋዮችና ምእመናን በሙሉ ቅ/ሲኖዶስ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች ለመተግበር አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ተጠይቋል
 • ‹‹ዓለም ጥበብ ባፈራው የአሠራር ዕውቀት በየቀኑ በለውጥ ጎዳና በሚራመድበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችንም ከዓለሙ በተሻለና በበለጠ በመንፈሳዊና በአእምሮአዊ ጥበብ ሕዝበ ክርስቲያኑን መምራት፣ ማስተማርና ማገልገል ይጠበቅባታል፡፡›› /ከቅ/ሲኖዶስ መግለጫ/

ከግንቦት 21 ቀን ጀምሮ ለዐሥር ቀናት ሲካሄድ የቆየው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዛሬ፣ ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ተጠናቋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በዐሥራ አንድ ነጥቦችና አቋሞች ያጠቃለለው መግለጫው÷ ‹‹ከሀገር ውጭ ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋራ የተጀመረው የሰላም ውይይት ኹኔታዎች ተመቻችተው እንዲቀጥል›› በምልአተ ጉባኤው መወሰኑን አስታውቋል፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያሉትን ወቅታዊና ነባራዊ ጉዳዮች ለመመርመርና ለመገምገም ሐዋርያዊ ሓላፊነት እንዳለበት ያመለከተው የቅ/ሲኖዶሱ መግለጫ÷ ለቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ተልእኮ አፈጻጸም ዕንቅፋት ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ጉዳዮች በአጀንዳ ቀርጾ በስፋትና በጥልቀት ተወያይቶ ውሳኔ እንደሰጠባቸው ገልጧል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ ብዙ ውይይት ካደረገ በኋላ ካሳለፋቸው ዐበይት ውሳኔዎች መካከል በመግለጫው ላይ በቀዳሚነት የተጠቀሰው÷ በየሥራ ዘርፉ እየተከሠተ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር በተለይም ብልሹ አሠራር፣ ዘመኑን ያልዋጀና ጥራት የጎደለው የፋይናንስ አያያዝ፣ ለሙስናና ብክነት የተጋለጡ አሠራሮች ናቸው፡፡ ምልአተ ጉባኤው እኒህን ተቋማዊና ሥርዐታዊ ችግሮች ወሳኝ በኾነ መልኩ መቀረፍና መድረቅ፣ ከዚህም ጋራ ቤተ ክርስቲያናችን በመሪ ዕቅድ መሥራት የምትችልበትን አሠራር መቀየስ እንዳለበት ሙሉ ስምምነት እንደተደረሰበት አመልክቷል፡፡

ለዚህም ቅ/ሲኖዶሱ÷ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምሁራን ምእመናን የሚገኙበት ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን የማጣራትና የማጥናት ሥራውን እንዲቀጥል በሙሉ ድምፅ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ ይህ ዐቢይ ኮሚቴ ቤተ ክርስቲያን ስትራተጂያዊ ጉዳዮቿን ግልጽ በምታደርግበት መሪ ዕቅድ መሥራት የምትችልበትን አሠራር እንደሚቀይስም በመግለጫው ሰፍሯል፡፡

የስብሰባው ምንጮች እንደገለጹት የዐቢይ ኮሚቴውን ሥራ እንዲያስተባብሩ ቅዱስ ሲኖዶስ በአባልነት ያካተታቸው ሁለት ሊቃነ ጳጳሳትን ሲኾን እነርሱም÷ የምሥራቅ ሐረርጌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም እና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ – ወሊሶ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ናቸው፡፡ የዐቢይ ኮሚቴው ሌሎች አምስት አባላት በምልአተ ጉባኤው ውሳኔ መሠረት በቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ተጠቁመው ይካተታሉ፤ የኮሚቴውም ዝርዝር የሥራ መመሪያ በቋሚ ሲኖዶሱ እንደሚዘጋጅለት ተዘግቧል፡፡

የመግለጫውን ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ይመልከቱ

Press Release of the Rekebe KAhinat Holy Synod Meeting

Advertisements

3 thoughts on “ለሃይማኖት፣ ለሀገርና ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማበርከት የሚገባውን ሁሉ በብቃት ለመሥራት ከምንጊዜውም በላይ መዘጋጀቱን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ

 1. geezonline June 7, 2013 at 4:25 pm Reply

  ኹል ጊዜ እንዲህ ወይም እንዲያ “በምልአተ ጉባኤው መወሰኑን አስታውቋል፡፡” ትላላችኍ፤ የማይሰለቻችኍ ጉዶች! በጽድቅ ከኾነ “ውሳኔ” የምትባለዋ ቃል ላንድ አፍታ “ነባቢ ህላዌ” ብታገኝ ሲኖዶሱን “በውርጃ ወንጀል” ለፍርድ እንደምትገትረው አያጠራጥርም። ስንቴ ተፀነሰች? ስንቴስ ሳትወለድ ሞተች? (ምሳሌውን በቦሌ መድኀኔ ዓለም ከተገተረው ምስለ ጣኦት ተማሩ!)

  ወትቤ ውሳኔ (ውሳኔም አለች)፦ ባካችኍ ላትወልዱኝ አትፅነሱኝ!

 2. Tesfaye June 12, 2013 at 5:48 am Reply

  ቅዱስ ሶኖዶስ የቤተክርስቲያን ሉዓላዊነት ዋልድባን የመሳሰሉትን ገዳማት ደህንነትም የሚጨምር ከሆነ፣ አብነት ትምኽህርትቤቶችን፣ ቅርሥን፣ የክርስቲያን ግለሰብ ክብርን፣ የክርስቲያን ማኅበራት ሕጋዊ መብቶችን በሚያጠቃልል መልኩ ተርጉሞት ከሆነ ቃል ኪዳኑ መልካም ነው፡፡

 3. Anonymous June 13, 2013 at 9:45 am Reply

  ኹል ጊዜ እንዲህ ወይም እንዲያ “በምልአተ ጉባኤው መወሰኑን አስታውቋል፡፡” ትላላችኍ፤ የማይሰለቻችኍ ጉዶች! በጽድቅ ከኾነ “ውሳኔ” የምትባለዋ ቃል ላንድ አፍታ “ነባቢ ህላዌ” ብታገኝ ሲኖዶሱን “በውርጃ ወንጀል” ለፍርድ እንደምትገትረው አያጠራጥርም። ስንቴ ተፀነሰች? ስንቴስ ሳትወለድ ሞተች? (ምሳሌውን በቦሌ መድኀኔ ዓለም ከተገተረው ምስለ ጣኦት ተማሩ!)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: