ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአ/አ ሀ/ስብከት የፓትርያሪኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ተመደቡ

His Grace Abune Estifanosየርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬ፣ ግንቦት ፳፷ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም የቀትር በፊት ውሎው፣ የጅማ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ የኾኑትን ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስንአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያሪኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው እንዲሠሩ በብዙኀኑ አባላቱ ድምፅ ደግፎ መድቧቸዋል፡፡

ብፁዕነታቸው በሀ/ስብከቱ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እንዲኾኑ የተደረገው ምደባ የቅ/ሲኖዶሱን ይኹንታ ያገኘው በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ አቅራቢነት ነው፡፡ ይኸውም በ1991 ዓ.ም በቅ/ሲኖዶስ ጸድቆ በወጣው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ልዩ መተዳደርያ ደንብ፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የመላው አህጉረ ስብከት ማእከል በመኾኑ ፓትርያሪኩ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን በቋሚ ሲኖዶስ እያስወሰነ በበላይነት እንደሚመራና እንደሚቆጣጠር በተገለጸበት አንቀጽ 7 ንኡስ ቁጥር 1 የተደገፈ እንደኾነ ተገልጧል፡፡

የልዩ መተዳደርያ ደንቡ መውጣት በቃለ ዐዋዲው አንቀጽ 43 ንኡስ አንቀጽ 4 ድንጋጌ የተመለከተ ቢኾንም ሊቀ ጳጳሱን የፓትርያሪኩ ረዳት የሚያደርገው አንቀጽ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 35(2)÷ ‹‹እያንዳንዱ ሀ/ስብከት ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጀምሮ በቅ/ሲኖዶስ በተሾመ ሊቀ ጳጳስ ወይም ጳጳስ ይመራል›› በሚል ከተደነገገው ጋራ የሚቃረን ነው፤ ‹‹ረዳት›› የሚል ቅጽል የለውምና፡፡

በዚያው ልዩ መተዳደርያ ደንብ አንቀጽ 10(3) እና በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 35(3)፣ አንቀጽ 36 (3)፣ (4) እና (5)÷ በቅ/ሲኖዶስ በሚወጣው ልዩ ደንብ አዲስ አበባን የሚመራ የአስተዳደር ዐቢይ ኮሚቴ በቅ/ሲኖዶስ እንደሚቋቋም ከገለጸ በኋላ÷ የአስተዳደር ዐቢይ ኮሚቴውን የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እንደሚመራውና የዐቢይ ኮሚቴውም ተጠሪነት ለቅ/ሲኖዶስ እንደሚኾን ነው የተደነገገው፤ እዚህም ላይ ‹‹ረዳት›› የሚል ዕዝልና ቅጽል የለም፡፡

በአጠቃላይ የሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ድንጋጌዎች፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተጠሪነት ለቅ/ሲኖዶስ ኾኖ እንደማንኛውም ሀ/ስብከት ራሱን የቻለ ሊቀ ጳጳስ ሲኾን ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ጋራ የሚኖረውም ግንኙነት እንደሌሎች አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት እንደሚኾን ነው የሚያረጋግጡት፡፡ ስለዚህም ከጸደቀበት 1991 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ዓመታት ብቻ የተሠራበትና ዕጣ ፈንታው ያልታወቀው ልዩ መተዳደርያ ደንቡ ከሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ጋራ ይቃረናል፡፡

የሕግ አቀራረጹ ተቃርኖ ደግሞ የፓትርያሪኩን ልዩ ሥልጣንና የሊቀ ጳጳሱን ተጠሪነት አሻሚ በማድረግ በ2001 ዓ.ም በሀ/ስብከቱና በመንበረ ፓትርያሪኩ መካከል ተፈጥሮ እንደነበረው ዐይነት ውዝግብ እንዳያስከትል ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በጉዳዩ ላይ የሚተቹ አስተያየት ሰጭዎች÷ የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ታሪካዊ ሚና፣ ወቅታዊ ኹኔታውንና የሌሎች አኀት አብያተ ክርስቲያንን ልምድ ባገናዘበ አኳኋን እንደሚሻሻል በሚጠበቀው ቃለ ዐዋዲና ሕገ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ዐይነቱ የሕጎችና ደንቦች መጣረስ የማያዳግም መፍትሔ እንዲሰጠው ይጠይቃሉ፡፡

በኤጲስ ቆጶስነት ከመሾማቸው በፊት (ቆሞስ አባ ገብረ ሚካኤል በየነ) የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን በዋና ሥራ አስኪያጅነት ያገለገሉት ብፁዕነታቸውበቀጣይ ብቁና ጠንካራ የሥራ አመራር ችሎታ ያላቸውን ዋና ሥራ አስኪያጅ በግልጽ መስፈርትና የውድድር ሥርዐት መርጠው በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ በማሾም ጽ/ቤን (ሥራ አስፈጻሚውን) በሚገባ እንደሚያዋቅሩ ይጠበቃል፡፡

ባለፈው ጥቅምት የተካሄደው የመንበረ ፓትርያሪክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ውሳኔዎች እንደሚያሳዩት፣ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በአንጻራዊነት ከፍተኛ የኾነ የገቢ ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ በአዲስ አበባ ተጨባጭ ኹኔታ ሲታይ ግን በቁጥር ከ160 የማያንሱት ገዳማትና አድባራት ከፍተኛ የሀብት ክምችት ያለባቸው የብዙ ባለሀብትና ንብረት ባለቤቶች ናቸው፡፡ በቃለ ዐዋዲው ሕግና መመሪያ ተደግፎ በታማኝነት ከልብ ከተሠራ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በሁሉም የሥራ ዘርፍ ተኣምር መፍጠር እንደሚቻል ታምኖበታል፡፡

ይኹንና የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው የውሳኔና አቋም መግለጫ እንደሚያስረዳው በሀ/ስብከቱ ሥር የሰደደው፡-

 • የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣
 • በጎሳ ላይ ያተኮረ፣ ካለማስታወቂያና ውድድር የሚፈጸም ቅጥር፣
 • የሠራተኛ ዕድገትና ዝውውር አፈጻጸም ችግር (ለቀቀ ሠራተኛ ስም፣ ቦታና በጀት ጭምር እየተጠየቀ)፣
 • የሰበካ ጉባኤ በቃለ ዐዋዲው መሠረት በየደረጃው አለመደራጀት፣
 • የአባላት በትክክል አስተዋፅኦ አለመክፈል፣
 • የሒሳብ ምርመራን በጊዜውና በትክክል አለማድረግ፣
 • የፐርሰንት ገቢው በየደረጃው በቅጽ ተሞልቶ በጊዜው አለቅረብ፣
 • ምንኩስናቸው እንኳ በሚገባ ላልተረጋገጠ፣ ያለበቂ ዕውቀት መነኰሳት ነን ባዮች በልብስ ብቻ ቅድሚያ ቦታ እየተሰጠ ገዳማት እየተራቆቱ መኾናቸው፣
 • የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የሌላቸው አብያተ ክርስቲያን ጥቂት አለመኾናቸው፣
 • ለገዳማትና አድባራት በዕጣን አዙር የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መሰጠቱ የሚያስደስት ቢኾንም በሰንበቴና ቀብር ቤት ስም ከቤተ ክርስቲያን ልማት ይልቅ የግል መጠቃቀም ተስፋፍቶ መታየቱ፣
 • በሀ/ስብከቱ የዘመኑ ገቢ ላይ የተመዘገበውና የቀድሞው የሀ/ስብከቱ ዋ/ሥ/አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ተጠያቂ የተደረጉበት የ6,753,717.25 ጉድለት

በብፁዕነታቸው አስተዳደር ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ የማያዳግምና ሥር ነቀል ውሳኔ እንደሚሰጠው ይጠበቃል፡፡

ብፁዕነታቸው በጅማ ሀ/ስብከት÷ በስብከተ ወንጌል (የሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያንን ስምሪት ከመቆጣጠር አንጻር ጥንቃቄ የሚወሰድባቸው ጉዳዮች እንደተጠበቁ ኾነው) እና በቤተ ክርስቲያን ልማት ረገድ ያደረጓቸውን አመርቂ እንቅስቃሴዎች በአዲስ አበባ ሀ/ስብከትም እንደሚደግሙት ተስፋ አለን፡፡

ለብፁዕነታቸው መልካም የሥራ ዘመን እንመኝላቸዋለን፡፡

የዜና ማስተካከያ፡- በትላንት ዘገባችን ቅ/ሲኖዶስ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን የ4፡1 አስተዳደራዊ መዋቅር እንዳጸደቀና ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አራት ሥራ አስኪያጆች እንደሚሾሙ መግለጻችን ይታወሳል፡፡ ኾኖም ትክክለኛው የቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔ÷ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ከኅዳር፣ 2005 ዓ.ም በፊት ወደነበረበት አንድነት ተመልሶ በአንድ ረዳት ሊቀ ጳጳስና በአንድ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲመራ መኾኑን እየገለጽን የቀደመው ዜና ስሕተት በዚህ ማስተካከያ እንዲታረም እንጠይቃለን፡፡ ለመረጃው ስሕተት ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

Advertisements
%d bloggers like this: