- በአህጉረ ስብከቱ መስፈርት ወጥቶለት ጥናት ተደርጎለት የተደረገ ምደባ የለም
- የወረዳ ቤተ ክህነት መዋቅር በተሰጠው ሥልጣን ሥራውን አለመሥራቱ ችግሩን አግዝፎታል
የአዲስ አበባ አራት አህጉረ ስብከትን የፓትርያሪኩ ረዳት የሚኾን አንድ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በመመደብና ሊቀ ጳጳሱን የሚረዱ አራት ሥራ አስኪያጆች በመሠየም፣ ተጠያቂነትና ሓላፊነት ያለው ግልጽ የኾነ ጠንካራ የአስተዳደር ሥርዐት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አስታወቁ፡፡
ዛሬ ጥዋት የተጀመረውን የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ተተኳሪ ጉዳዮች አስመልክቶ ቅዱስነታቸው በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት÷ በጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት በሁለት ሊቃነ ጳጳሳትና በሁለት ሥራ አስኪያጆች እንዲመራ የተደረገበት አደረጃጀት ችግር ፈቺ ኾኖ አልተገኘም፡፡
በቅዱስነታቸው መልእክት እንደተመለከተው ለአደረጃጀቱ ድክመት በምክንያትነት የተጠቀሱት÷ የሥራ አስኪያጅነት ምደባው ጥናት ተደርጎለትና መስፈርት ወጥቶለት በውድድር የተደረገ አለመኾኑ፣ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ድንጋጌ መሠረት የወረዳ ቤተ ክህነት መዋቅሩ ሥልጣን ተከፍሎ ያልተሰጠውና ሥራውን የማይሠራ መኾኑ የሚሉት ናቸው፡፡ በእኒህ ሁለት አስተዳደራዊ ውስንነቶች ሳቢያ ችግሩ እየገዘፈና እየተመሰቃቀለ ለመልካም አስተዳደር ዕጦት መንሥኤ በመኾኑ አደረጃጀቱን መቀየር አስፈላጊ ኾኖ መገኘቱን ቅዱስነታቸው በስብሰባ መክፈቻ መልእክታቸው ገልጸዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያናችን የሚታዩትን የአሠራር ክፍተቶች በፍጥነት ማስተካከል እንደሚገባ ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው፣ ‹‹ክፍተቶቹን በፍጥነት ማስተካከል ካልቻልን በቅድሚያ እኛ ላይ የሚፈርደው የገዛ ራሳችን ኅሊና ነው፤ በይቀጥላልም እግዚአብሔርም ሌላውም ይፈርድብናል፤›› በማለት ነባሩና ሰሞናዊው የአህጉረ ስብከቱ የሙስናና የጎጠኝነት ችግሮች የፈጠሩትን ጫናና የሚሹትን አስቸኳይ መፍትሔ አስገንዝበዋል፡፡
ለቅዱስ ሲኖዶሱ ተሰብሳቢ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በይፋ ባቀረቡት ተማኅፅኖም፣ ‹‹እኔ ወንድማችኹንም በዚህች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዳገለግልና እንድላላክ መርጣችኹ በዚህ ትልቅ የሓላፊነት ወንበር ላይ ስታስቀምጡኝ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ፣ የምእመናንን የልብ ትርታ እያዳመጥኹ ለእናንተ ለብፁዓን አባቶች ሳቀርብ ይኹንታንና እገዛውን እየለገሳችኹኝ የጋራ ሓላፊነታችንን እንድንወጣ መኾን አለበት፤›› በማለት የምልአተ ጉባኤውን ድጋፍ በይፋ ጠይቀዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ በሙስናና ብልሹ አሠራር ሀብቱ ያለርኅራኄ ሲመዘበር ለኖረው የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት አስተዳደራዊ ችግር አስቸኳይ መፍትሔ ያሳዩት ዝግጁነት የሚመሰገን፣ ሊደገፍና ሊበረታታም የሚገባው ነው፡፡
በቁጥር ከ160 በላይ ለሚደርሱት፣ በርካታ አገልጋይና ምእመን ለሚመሩት፣ ከፍተኛ ሀብት ለሚያንቀሳቅሱት የአህጉረ ስብከቱ አድባራትና ገዳማት ያቀረቡት የመፍትሔ ሐሳብና የጠየቁት ይኹንታም በአጀንዳ ተይዞ፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን፣ የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌና ወቅታዊውን የችግሩን ስበት ባገናዘበ አኳኋን በምልአተ ጉባኤው በስፋትና በጥልቀት ውይይት ተደርጎበት እንደሚጸድቅም ተስፋ ይደረጋል፡፡
እግረ መንገድ፡-
- በአ/አ አህጉረ ስብከት የሚመደበው ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ፓትርያሪኩ ረዳት የተባለው አዲስ አበባ የፓትርያሪኩ ሀ/ስብከት ስለኾነ ነው ተብሏል፡፡ በጉዳዩ ላይ የሚተቹ አስተያየት ሰጭዎች በሕገ ቤተ ክርስቲያን አዲስ አበባ የሁሉም አህጉረ ስብከት ማእከል በመኾኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሠይመው ዐቢይ ኮሚቴና ዐቢይ ኮሚቴውን በሚመራው ሊቀ ጳጳስ እንደሚመራ ከመገለጹ በቀር ከቀድሞ ጀምሮ ሲወራረድ እንደመጣው ሊቀ ጳጳሱ የፓትርያሪኩ ረዳት ይኾናል አለማለቱ እንዲጤንና እንዲገናዘብ ይሻሉ፡፡
- የአራቱ ሥራ አስኪያጆች ምደባ ‹‹በሥራ ችሎታቸው ብቁና ጠንካራ›› መኾናቸው ታይቶ እንደኾነ ተገልጧል፡፡ የአስተያየት ሰጭዎቹ ጥያቄ÷ የሥራ አስኪያጅነት ብቃትና ጥንካሬ በተጨባጭ የሚለካበት የምደባና ቅጥር መስፈርት አለን ወይ? የሚል ነው፡፡
- እንደ ቅዱስነታቸው መልእክት፣ በአጭር ጊዜ የተፈለገውን ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ የለውጡን መሠረት ግን በአስቸኳይ ማስቀመጥና አቅጣጫውን መቀየስ ያስፈልጋል፡፡ እውነት ነው! ትክክል ነው! ጥያቄው ግን የለውጡ መሠረት የሚጣለውና የለውጡ አቅጣጫ የሚቀየሰው ‹‹በአስተዳደር ችሎታው ጠንካራ ረዳት የኾነ ሊቀ ጳጳስ በመመደብ››፣ ‹‹ብቁና ጠንካራ ሥራ አስኪያጅ በመሠየም›› ብቻ ነው ወይ? ከዚህ በላይና ከዚህ በፊት ጠንካራው ሊቀ ጳጳስ፣ ብቁው ሥራ አስኪያጅ የሚሠራበት፣ የቤተ ክርስቲያንን ዘርፈ ብዙ ሀብቶች በሚገባ ለይቶና ዐውቆ የሚያሰማራበት፣ የሚከታተልበትና የሚቆጣጠርበት የሥራ አስተሳሰብ፣ የሥራ መዋቅርና የሥራ ዕቅድስ?
Egezeabehir kezhi kefu ye zeragnenat menifes hulachnenemi yetibeken le abatochachinem melikam ye honewen hulu enemegnalin !!!!!
በአጭር ጊዜ የተፈለገውን ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ የለውጡን መሠረት ግን በአስቸኳይ ማስቀመጥና አቅጣጫውን መቀየስ ያስፈልጋል፡፡ እውነት ነው! ትክክል ነው!
ጅማሬው መልካም ነው እግዚአብሔር ያስበን ፤ቅዱስ አባታችንን እድሜ ይስትልን እዉነተኛ የተዋሕዶ አርበኛ ናቸው፤፤