የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ በ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ላይ የተላለፈውን እግድ አጸኑ

 • ‹‹እግዱ ለምን እንደተፈጸመ ሲጣራ÷ በቅዱስ ፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት፣ በጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ቢሮ፣ በም/ሥራ አስኪያጁ ቢሮና በአስተዳደር መምሪያ ቢሮ እየገቡ ሁከት መፍጠራቸው›› ተገልጧል፡፡
 • የጨለማው ቡድን በቀጣዩ የዋና ጸሐፊና ዋና ሥራ አስኪያጅ ምርጫ ላይ አነጣጥሯል

‹‹የሚያውኩአችኹ ይቆረጡ›› ይላል ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ /ገላ.5÷14/፡፡ በዚህ አገባብ ‹‹ይቆረጡ›› የሚለው ቃል አቻ ትርጉም ‹‹ይለዩ›› ማለት እንደኾነ ግልጥ ነው፡፡ ሐዋርያው በሌላ መልእክቱ፣ ‹‹ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችኹ ይወገድ›› በማለት አዝዟል /1ቆሮ.5÷2/፡፡ በክሕደታቸውና ኑፋቄያቸው የሚያውኩን ኢአማንያንና መናፍቃን ከምእመናን ተለይተው የሚወገዱበት መንፈሳዊ ሰይፍ ሥልጣነ ክህነትን መሠረት ያደረገው ውግዘት ነው፡፡ እምነታቸውን በሙስና ምግባር የካዱ፣ ሙሰኛ ምግባራቸው እንዳይጋለጥ የጎጥ ማንነታቸውን ጨምሮ የተለያዩ ሽፋኖችን በመከላከያነት የሚጠቀሙ አዋኪዎች የሚገሠጹበት፣ በተግሣጹ የማይታገሡ ከኾነ ደግሞ ለቀሪው ጤንነት ሲባል ተመትረው – ተቆርጠው የሚለዩበት ጠንካራ ተቋማዊ ሥርዐት ብቻ ሳይኾን ሥርዐቱ ተፈጻሚ የሚኾንበት መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ቁርጠኝነት ያሻናል፡፡

ሙስናን በሁለንተናዊ መልኩ ለማስወገድ የሚያስችል መንፈሳዊ እሴት አለን፡፡ ይህን እሴት ወደ ተቋማዊነት መመንዘር፣ በእያንዳንዱ አገልጋይና ሠራተኛ ውስጥ በተግባር ማበልጸግ ባለመቻላችን ግን በቤተ ክህነታችን ሙስና ሥርዐታዊ ኾኗል፡፡ መዋቅሩን ተቆጣጥሮ ቢሮአዊ ቋንቋ እስከ መኾን በደረሰው ሥርዐታዊ ሙስና ውስጥ ሁሉም ዐይነት ችግሮች አሉ – ጎጠኝነትና የዘመድ አዝማድ አሠራር መግነን፤ የመንፈሳዊነት፣ ቀኖናዊነትና ሞያዊነት ዋጋ ማጣት፤ የአድርባይነት፣ ብኩንነትና አቅመ ቢስነት መንሰራፋት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ለውጭ ተጽዕኖ መጋለጥ በተለይም ድሉል የሥራ ሓላፊዎች በሚፈጥሩት ክፍተት የተነሣ የመናፍቃንና አስመሳዮች ቦታ መያዝና የኦርቶዶክሳዊ ማንነታችንን መሠረቶች የሚሸረሽሩበትን የጥፋት ተግባር ለማስፋፋት ዕድል ማግኘት!!

ሙስና ሥርዐታዊ በኾነበት ተቋም ከአስተሳሰብ ለውጥ የሚነሣ መዋቅራዊ ማሻሻያ ማካሄድ ግድ ነው፡፡ ነገር ግን ተቋማዊ ሥርዐቱ በዚህ ደረጃ ንቁ ምላሽ መስጠት ባልቻለበት ኹኔታ በተለይም በከፍተኛ አመራሩ ዘንድ የምትወሰደው እያንዳንዷ ፀረ – ሙስና አቋምና እያንዳንዷ ፀረ – ሙስና ርምጃ አቅምና ተስፋ ናትና እርሷን እንደ አብነት ለማስተጋባት /ለመጦመር/ እንገደዳለን፡፡

በዚህ ረገድ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ለዘገባው ይኹን ለአዘጋገቡ ያላቸውን ስሱነት/ስጋት/ ብንረዳም መራራው እውነታ ግን÷ ‹‹አድጎ አነስ፣ ዐይቶ ዐጣ›› በኾነው ቤተ ክህነታችን ሙስናና ብልሹ አሠራር የደረሰበት ደረጃ ነው፡፡ ይኸውም ነገሩ በተከናወነለትና በበረታ ጊዜ ለጥፋት በታበየው ልቡ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የማይገባውን ሠርቶ እግዚአብሔርን በበደለው የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን ግምባር ላይ እንደወጣውና ታላቁን ካህን ጨምሮ ሁሉም ካህናት እንደተመለከቱት ለምጽ ሊሸፍኑት የማይችሉት ምናልባትም ሊሸፍኑት የማይገባ ገመና መኾኑ ነው፡፡

በለምጽ የተቀሠፈው ንጉሡ ዖዝያን እንኳ ከቤተ መቅደሱ ለመውጣት ቸኩሏል፤ ካህናቱም ፈጥነው አባረውታል፡፡ /2ዜና. 26÷1-23/ ዛሬ ግን ከበርካታ ችግሮቻችን መካከል ስመ መነኰሳት የሚፈጥሩትን ሁከት እንኳ ብናይ፣ አባቶቻችን ንጽሐ መላእክትን ገንዘብ ባደረጉበት ምንኵስና ስም እኛን መስለው ወደ ውስጣችን ከገቡ በኋላ የመናፍቃን ቅጥረኛ የኾኑ፣ ወሳኝ አስተዳደራዊ ቦታዎችን በ‹‹ኔትወርኪንግ›› በመቆጣጠር ግላዊ ጥቅም የሚያካብቱና ነውሩን በዐደባባይ አብነት አድርገው የሚሠሩ መነኰሳት ነን ባዮች ከዕለት ዕለት እየበዙ፣ ከቁጥጥር ውጭ ለመኾንም መድረሳቸው ግልጽ ነው፡፡

በአንጻሩ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ አህጉረ ስብከቱም ይኹኑ አብዛኞቻችን ዐደባባይ የወጣውን ችግር በገመና ከታችነት እንከላከላለን እንጂ በተጨባጭ ያበጀነው መፍትሔ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ እንዲያውም ‹‹ቅድሚያ ለመነኰሳት›› በሚል በተለይ በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት በይፋ ያልታወጀና ከጥቅመኝነት በቀር አግባብነት የሌለው የአህጉረ ስብከት የሹመት፣ ቅጥርና ዝውውር አሠራር ስለመኖሩ ለችግሩ መስፋፋት በምክንያትነት የተጠቀሰበት አጋጣሚ ታይቷል፡፡ የምሕረት ዘመን እንደ መኾኑ በደለኞች ከበደላቸው እንዲመለሱ ወዶ መታገሥና ማስታመም ክርስቶሳዊነት ነው፡፡ በክፋታቸው ጋንግሪን ኾነው የተገኙትን ደግሞ በቀኖናዊ ይኹን አስተዳደራዊ ርምጃ ለይቶ ማስወገድ ተገቢ ነው – ‹‹የሚያውኩአችኹ ይቆረጡ›› ይላልና!!

በዓዲ ግራት ሀ/ስብከት የደብረ ዐላማ አሲራ መቲራ ገዳም አበምኔት መኾናቸውን ሽፋን በማድረግ ራሳቸውን በሕገ ወጥ መንገድ ሲያበለጽጉ የቆዩት ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ገብረ ጊዮርጊስ ወደ መ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት እንዳይገቡ የተላለፈባቸው እግድ ከዚህ አጠቃላይ ኹኔታ ተለይቶ የማይታይ የርምጃው አንድ ምዕራፍ ነው፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሥራ አስፈጻሚ ማኔጅመንት ኮሚቴ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት የሥራ ድርሻ የላቸውም፡፡ ነገር ግን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ዋና ክፍል በቅርቡ ለፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት ሓላፊ ኾነው በቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ለተመደቡት አቶ ታምሩ አበራ ቢሮ በሚያዘጋጅበት ወቅት ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን በፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት ገብተው ሁከት ፈጥረዋል፡፡ በአስተዳደር መምሪያ ዋና ሓላፊው ቢሮ ገብተው እነ እገሌን ካልቀጠርኽ ብለው ለመደባደብ ተጋብዘዋል፤ ዝተዋል፡፡Eotc letter

‹‹አባ›› ገብረ መድኅን የቢሮ ዝግጅቱን በመቃወም ሁከት የፈጠሩት ‹‹ቅዱስነታቸው የማያውቁት የቢሮ ዝውውር ስለኾነ ቢሮ እንዳትለቁ›› በሚል ነበር፡፡ እግዚአብሔር ያሳያችኹ! በመንበረ ፓትርያሪኩ አንዳችም የሥራ ድርሻ የሌላቸው ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን፣ በፓትርያሪኩ ሰብሳቢነት የሚመራው ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ያሳለፈውን ውሳኔ በፓትርያሪኩ ስም ተፈጻሚ እንዳይኾን ሲያውኩ!

‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ስለፈጠሩት ሁከት በሠራተኞች አስተዳደርና በጠቅላላ አገልግሎት ዋና ክፍል ሓላፊ በኩል ሪፖርት የተደረገለትና ‹‹መታገሥ ከሚችለው በላይ›› የኾነበት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሥራ አስፈጻሚ ማኔጅመንት ኮሚቴም ሚያዝያ 9 ቀን 2005 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን በማያገባቸው ገብተው የቋሚ ቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ እንዳይፈጸም ዕንቅፋት በመኾን ሁከት መፍጠራቸውን አረጋግጧል፡፡ በዚህም መሠረት ሰባት አባላት ያሉት የማኔጅመንት ኮሚቴው ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ከሚያዝያ 11 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ መ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት ግቢ እንዳይገቡ በአንድ ድምፅ ወስኗል፡፡

እግዱ ተግባራዊ ከኾነበት ዕለት አንሥቶ ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን÷ ‹‹ለገዳሙ ጉዳይ ወደ መ/ፓ/ጠ//ጽ/ቤት እንዳልገባ ታገድኹ፤ የገዳሙን ሥራ እንዳላከናውን አጉላሉኝ›› በማለት የአስተዳደር መመሪያ ሓላፊውን በፖሊስ ጣቢያ ክሥ ለማስፈራራት፣ ከጥበቃ ክፍል ሓላፊውና ከጥበቃ አባላት ጋራ ግብግብ ለመግጠም ሞክረዋል፡፡ በዚህ እንዳልተሳካላቸው ሲረዱ ደግሞ የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልን በማሳሳት ግንቦት 1 ቀን 2005 ዓ.ም ለመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት በተጻፈ ደብዳቤ እግዱን ለማስነሣት ሞክረዋል፡፡

ኾኖም የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት ሓላፊዎች ስለርምጃው አግባብነት ለማስረዳት ባደረጉት ጥረት ከምስጉን አቋማቸው የመንሸራተት ስጋት የታየባቸው ብፁዕ ዋና ጸሐፊው፣ በተሳሳተ መረጃ እግዱ እንዲነሣ የጻፉትን ደብዳቤ በተለዋጭ ትእዛዝ በመሻር አስተካክለውታል፡፡ ‹‹እግዱ ለምን እንደተፈጸመ ሲጣራ በቅዱስ ፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት፣ በጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ቢሮ፣ በም/ሥራ አስኪያጁ ቢሮና በአስተዳደር መምሪያ ቢሮ እየገቡ ሁከት መፍጠራቸው›› ስለተገለጸላቸው የቀደመው ትእዛዝ መሻሩን አመልክተዋል፡፡1

በዚህም መሠረት የጠ/ቤ/ክ ሥራ አስፈጻሚ ማኔጅመንት ኮሚቴ ቀደም ሲል በሁከተኛው ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ያሳለፈው እግድ ‹‹ወደፊት [የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሚካሄድበትን ወቅት ይጨምራል] ኹኔታው ተጣርቶና ታይቶ የውሳኔ ሐሳብ ለበላይ ሓላፊዎች እስኪቀርብና አመራር እስከሚሰጥበት ድረስ›› እንዲጸና የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ግንቦት 5 ቀን 2005 ዓ.ም ለመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡

‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ እንዳይገቡ ለታገዱበት ውሳኔ መነሻ በኾነው ጉዳይ ውስጥ የምንረዳው ትልቁ ቁም ነገር÷ ቀንደኛው ፅልመታዊና ሙሰኛ ‹‹አባ›› ገ/መድኅን ገ/ጊዮርጊስ ከእነ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ እና አባ ሠረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል ጋራ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩን ልዩ ጽ/ቤት እና የውጭ ግንኙነት ለመቆጣጠር የነበራቸውን የጥቅመኝነት ፍላጎት ነው፡፡

ቀደም ሲል ባስነበብነው ዘገባ÷ የጠ/ቤተ ክህነቱ ፅልመታዊ ቡድን የፓትርያሪኩን ልዩ ጽ/ቤትና የውጭ ግንኙነት በንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ የበላይ ሓላፊነት፣ ፕሮቶኮሉንና የግቢ ጥበቃውን የንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ቤተ ዘመድ እንደኾኑ በሚነገርላቸውና ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ካልተቀጠሩ በሚል ለድብድብ በተጋበዙባቸው ሌሎች ግለሰቦች ሓላፊነት ይዞ በፓትርያሪኩ ዙሪያ ተጽዕኖውን ለማጠናከር ማቀዱን ጠቁመን ነበር፡፡ ይህንንም ካሳካ በኋላ ደግሞ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን በጀትና ሒሳብ መምሪያ በሌላው ሙሰኛ ገብረ መስቀል ድራር በኩል ለመቆጣጠር ዕቅድ እንደነበረውና ‹‹አባ›› ገብረ መድኅንም በገዳማት አስተዳደር መምሪያ ዋና ሓላፊነት ለመሾምና ለመቀጠር እየተፍጨረጨሩ መኾኑን በዘገባችን አመልክተን ነበር፡፡

ፊት በኢትዮ – ኤርትራ ጦርነት አገራቸውን በወታደርነት ያገለገሉት የዛሬው ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን፣ ውትድርና የሚያላብሰው ጥንቃቄና ዲስፕሊን እንኳ የተሣለባቸው አይመስሉም፡፡ ያደረጉትን ለሌሎች ሲናገሩ÷ ለዐቃቤ መንበሩ የ60,000 ብር የእጅ መስቀል እንደሰጧቸው፣ ምግባቸውን የቻሉት እርሳቸው እንደነበሩም አይቀራቸውም፡፡ በዚህ መደለያቸው ከዐቃቤ መንበሩ ጋራ መቀራረባቸው የሚነገርላቸው ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን፣ ‹‹ጉዳይ አስፈጽማለኹ›› በሚል ቲተራቸውን ለመቆጣጠር ችለው ነበር፡፡ ይህን ዐይን ያወጣ ድርጊት የተቃወሙት የዐቃቤ መንበሩ አቡነ ቀሲስ የሚሰማቸው በማጣታቸው ሥራቸውን እስከመተው ደርሰው ነበር፡፡

‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ደግሞ አጋጣሚውን በመጠቀም ከዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ አካላት ሳይቀር ከአንድ ሚልዮን ሚልዮን ብር በላይ ‹‹የፕሮጀክት ድጋፍ›› የጠየቁባቸውን ደብዳቤዎች አውጥተዋል፡፡ በሀ/ስብከቱና በገዳሙ የልማት ኮሚቴ ጥረት ከሸፈ እንጂ በኢሉባቦርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት በባሮ ወንዝ ተፋሰስ የሚገኝ የገዳም መሬት በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው ለመጠቀምም ሞክረው ነበር፡፡ እንግዲህ የገዳማት አስተዳደር መምሪያው ዋና ሓላፊነት የተፈለገው ይህንና የመሳሰሉትን ጥገኛ ፍላጎታቸውን የበለጠ ለማሳለጥ በማሰብ ነበር፡፡

ይኹንና ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን የኢትዮጵያ ገዳማትን በማእከል ደረጃ በበላይነት ለመምራት ቀርቶ አበምኔት ነኝ የሚሉበትን የደብረ ዓላማ አሲራ መቲራ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳምን እንኳ ገደብ በሌለው ብኩንነታቸው እንዳራቆቱትና እንዳዳከሙት ነው የሚነገረው፡፡ ሐራውያን አስተያየት ሰጭዎች በተቹት መሠረት፣ ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ለግል መፍቀዳቸው ገንዘብ የሚረጩበትን አሳፋሪ ጉዳይ እንተወውና በአዲስ አበባ አውራ ጎዳናዎች በድርጅት ኮድ (05) የሚያሽከረክሯቸው ላንድክሩዘርና ዶልፊን መኪኖች እንዲሁም በአምባሳደርና በሲ.ኤም.ሲ በባለቤትነት የያዟቸው ሁለት ቤቶች÷ አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት፣ በእንስሳት ርባታ ለሚደክሙት ገዳማውያን የሚያተርፉት ነገር ስለመኖሩ አልተረጋገጠም፡፡

የምንኵስናውን ነገር እንተወውና በትምህርት ረገድ ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ዘመናዊው ይቅርና ጽሕፈቱ፣ አቡነ ዘበሰማያቱ እንኳ የሚያዳግታቸውና በሰው ርዳታ ያሉ ናቸው፡፡ እንዲህም ስለኾነ የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ዋና ሓላፊ ለመኾን በሕገ ወጥ መንገድ ያጻፉትን ደብዳቤ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሥራ አስፈጻሚ ማኔጅመንት ኮሚቴ አልተቀበለውም፡፡ ፍላጎታቸውን በጉልበት ከማስፈጸም ወደ ኋላ የማይሉት ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ግን በማኔጅመንት ኮሚቴው ደብዳቤ ላይ እንደተገለጸው÷ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ቢሮ ድረስ ገብተው አስፈራርተዋል፤ በምክትል ሥራ አስኪያጅ ቢሮ ገብተው ትርምስ ፈጥረዋል፡፡

‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ሲያስፈራሩ፣ ትርምስ ሲፈጥሩ፣ ለግብግብ ሲጋበዙና ሲዝቱ የሚያስፈራሩባቸውና ትምክህታቸውን የሚያሳዩባቸው ከፍተኛ የፖለቲካና የደኅንነት ባለሥልጣናት ስም የሚጠሩ ሲኾን እኒህም÷ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ አቶ ሥዩም መስፍን፣ አቶ ኣባይ ፀሃዬ፣ አቶ ኢሳይያስ ወልደ ጊዮርጊስና እና ወ/ሮ ነጻነት አስፋው ናቸው፡፡ ከእኒህም መካከል ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን በስማቸው እንደሚነግዱ የተረዱት አንዳንዶቹ ግለሰቡን ከአጠገባቸው ማራቃቸውና ማስጠንቀቃቸው ተነግሯል፡፡ ማራቁና ማስጠንቀቁ ‹‹ሁሉንም ለእነርሱ ነግሬ አስፈጽማለኹ፤ የምፈልገውን አሳካለኹ›› በማለት የሚታወቁትን ‹‹አባ›› ገብረ መድኅንን ከሕገ ወጥ ድርጊታቸው ይገታቸው እንደኾን ቆይተን የምናየው ይኾናል፡፡

በቅድመ ፓትርያሪክ ምርጫው የሽግግር ወቅት የዐቃቤ መንበሩን ቲተር በመቆጣጠር ያሻቸውን ደብዳቤ ሲያበሩ የነበሩት ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን፣ በዚያ ሁሉ አሠራርን የጣሰ ሕገ ወጥ ተግባራቸው ክቡን ማኅተም የሚያሳርፉላቸው ተባባሪዎች አላጡም፤ በገንዘብ የሚደልሏቸው የመዝገብ ቤት ሠራተኞች ነበሩም፤ አሉም!! በፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤትና በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት /ቀድሞ/ መዝገብ ቤቶች የነበሩትና ያሉት እኒህ ድሉል ሠራተኞች /አንዲቷ በአዲስ አበባ ሰሜን ማዘጋጃ በሚገኘው ‹‹ሙሉ ወንጌል›› ሳምንታዊ ተከታታይ እንደኾኑ ይታመናል/ ለ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ሕገ ወጥ ደብዳቤዎች ማኅተም ማድረግ ብቻ ሳይኾን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ብሎጎች መረጃ በማሾለክ ጭምር የሚረዱ የጨለማው ቡድን ገባሮች እንደኾኑና እንደነበሩ ተመልክቷል፡፡

Mahebere Selama revealed‹‹አባ›› ገብረ መድኅን በእምነታቸው ሕጸጽ ካለባቸው አካላት ጋራ ያላቸው ግንኙነት የሰነበተ እንደኾነ ነው መረጃዎች የሚያረጋግጡት፡፡ ከእኒህ መረጃዎች አንዱ የዛሬውን ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ዋነኛ ዓላማ በማያሻማ ኹኔታ ያሳያል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በቁጥር 27/58/2000 በቀን 22/2/2000 በአድራሻ ለክልል ትግራይ መስተዳድር ጽ/ቤት በግልባጭ ደግሞ ለስድስቱ የትግራይ አህጉረ ስብከት የጻፈው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው÷ በወቅቱ በትግራይ ምሥራቃዊ ዞን ዓዲ ግራት ሀ/ስብከት ሥር በሚገኘው የደብረ ዓላማ አሲራ መቲራ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ‹አገልጋይ› የነበሩት ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን፣ ‹‹ማሕበረ ሰላማ ምትሕግጋዝ ማኅበር›› ከተባለ የዓላማና የተግባር ቅንጅት ፈጥረው ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡

ማኅበሩ በ‹‹ባሕታዊ ነኝ›› ባዩ ‹‹አባ›› ወልደ ሥላሴ አስገዶም ቅስቀሳ በ1997 ዓ.ም የተመሠረተው ሲኾን የሚመራውም መ/ር ተስፋ ዓለም በርሀ የተባለ ግለሰብ ነው፡፡ ያለቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ከክልሉ ፍትሕ ቢሮ ፈቃድ በማውጣት ለመንግሥት ‹‹ቀጥተኛ የልማት ማኅበር ነኝ›› ለቤተ ክርስቲያን ደግሞ ‹‹ገዳማትን ለመርዳት›› በሚሉ ሁለት ባርኔጣዎች ይንቀሳቀሳል፡፡

በ‹‹በሰላማ›› ሽፋን /አንዱ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎግ እንደሚያደርገው/ መንግሥትንም ቤተ ክህነትንም የሚያጭበረብረው ማኅበር መሪዎች፣ በ26/10/99 ዓ.ም እና በ26/2/98 ዓ.ም በተጻጻፉት ደብዳቤ ዋነኛ መሪ ነኝ ባዩ ተስፋ ዓለም በርሀ እንደሚከተለው ጽፏል፡-

‹‹የቤተ ክርስቲያን ታዋቂ አባቶችን በመመሳሰል እንዲሁም በመቐለ ከሚገኙ ተመሳሳይ የማኅበራት መሪዎች ጋራ በመኾን ማኅበሩ እየመራኹኝ እገኛለኹ፤ የመቐለ 26ቱ የግሩፕ መሪዎች በሴል በመከፋፈል እንዲጠናከሩ እየተደረገ ከአጽቢና ከስንቃጣ ቅርንጫፍ ግንኙነት አጠናክረናል፡፡ እንዲሁም ወደተለያዩ ቀደምት ገዳማትና አድባራት በመሄድ ቀደምት ቅርሶችን እየጎበኘንና የተለያዩ ስጦታዎችን ለገዳማት አባቶችና አገልጋዮች በመስጠት ጥንታውያን ብርቅዬ የኾኑ ውድ ቅርሶች ኹኔታ እያጠናን ነው፤ ይህን የምንሠራውም የአሲራ መቲራ ገዳም አገልጋይ ከኾኑት ከአባ ገብረ መድኅን ጋራ ነው፡፡ ሥራውም በቅንጅት እየሠራን እንገኛለን፡፡ ጠቃሚ የኾኑ መረጃዎች እያገኘን ነን፡፡››

ለክልሉ መስተዳድር የተጻፈው የቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ደብዳቤ እንደሚገልጸው፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ Mahibere Selama revealedበጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ቡድኑ እምነታችንን በማፋለስ፣ እርስ በርሳችንም በማጣረስ ብቻ የሚመለስ ሳይኾን የቤተ ክርስቲያናችንና የሀገራችን ኢትዮጵያ ኩራትና አለኝታ የኾኑ ብርቅና ድንቅ ቅርሶቻችንንም እየጠቀሰ ለባዕድ አገር አሳልፎ የመስጠት ዕቅድ ያለው ‹‹አደገኛ ግሩፕ›› መኾኑን ተረድቷል፡፡ በመኾኑም የክልሉ መንግሥት አንዴ ‹‹ቀጥተኛ የልማት ማኅበር ነኝ›› ሌላ ጊዜ ‹‹ገዳማትን እረዳለኹ›› በሚሉ ሽፋኖች ውስጥ ውስጡን መርዙን የሚረጨውን የጥፋት ቡድን ፈቃድ እንዲሰርዝ የቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ጠይቆ ነበር፡፡

የመቐለ ሀ/ስብከት በ1997 ዓ.ም ማኅበሩ በማንኛውም የሀ/ስብከቱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መሰብሰብ እንደማይችል በመግለጽ የማገጃ ደብዳቤ ጽፎበታል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ደግሞ ባለፈው ዓመት ግንቦት፣ 2004 ዓ.ም የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ማኅበሩ ከቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ውጭ የቤተ ክርስቲያንን አሠራር በሚቃወም ኹኔታ እንደሚንቀሳቀስ በማረጋገጥ በሕገ ወጥነት ፈርጆታል፡፡

እንግዲህ ከዚህ የጥፋት ቡድን ጋራ በቅንጅት የሚሠሩት ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን፣ ዛሬ አበምኔት ነኝ በሚል የሚመሩትን ገዳም ከሀ/ስብከቱ መዋቅርና ቁጥጥር ውጭ ማድረጋቸው የዚህ እንቀስቃሴያቸው አንድ ፍጻሜ በመኾኑ ነው ብሎ ለመደምደም ይቻላል፡፡ የገዳማት አስተዳደር መምሪያው ዋና ሓላፊ ለመኾን የሚቃተሉትም ጥንታዊና በኢኮኖሚያ አቅማቸውም ጠንካራ የኾኑትን ገዳማት ቅርስ አልባ በማድረግ የባዕዳንን ተልእኮ ለማሳካት፣ የግል ጥቅማቸውንም ለማደለብ ነው ቢባል ስሕተት አይኾንም፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን የበዓላት አስተምህሮና ቀኖና ‹‹ኋላ ቀርነት›› እና ‹‹የልማት ዕንቅፋት›› እንደኾነ ጊዜውን መስለው ለማደር የማይገዳቸው ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ለኢ.ቢ.ኤሱ ‹‹ኤፍራታ ሾው›› ከቤተ ክርስቲያኗ ሳይወከሉ በድፍረት ተናግረዋል፡፡ ከጥፋት ቡድኖች ጋራ ከማበር ወደ ኋላ የማይሉት ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ለቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊ አገልግሎት መስፋፋትና መጠናከር ለመሥራት የተነሣሣውን የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር አዘጋለኹ በሚል በብዙ ጥረው ነበር፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ለማኅበሩ አገልግሎት መቃናት የሰጡት ቡራኬና መመሪያ አሳፍሮ መለሳቸው እንጂ!!

‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ለፓትርያሪኩ በዓለ ሢመት በደብረ ዓላማ አሲራ መቲራ ገዳም ስም 50,000 ወጪ በማድረግ የፓትርያሪኩ የቁም ፎቶግራፍ የሚታይበት ፖስተር አሠርተው አሰራጭተው ነበር፡፡ ከግሪክ ሙሉ ልብስና አይከን ሊያስመጡላቸውም አስበው ነበር፡፡ ያለአስመራጭ ኮሚቴው ዕውቅናና ያለፓትርያሪኩ ፈቃድ የተሰራጨው ፖስተር በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ መመሪያ እንዲወገድ ተደርጓል፡፡ ሌላውን የስጦታ ሐሳብ ይኸው የፓትርያሪኩ ፀረ ጥቅመኛ አቋም ዘግቶታል፡፡

ሐራዊ ምንጮች እንደተረዱት፣ የእነ ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ፅልመታዊ ቡድን በቀጣይ ያነጣጠረው÷ በመጪው የርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሚካሄደው የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ምርጫ ላይ ነው፡፡ ይመቹናል በሚል አስበውና መርጠው የመለመሏቸው፣ ‹‹ፕትርክናውን ብናጣ. . .›› ያሉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንዳሉም ከወዲሁ ማስወራት ጀምረዋል፡፡ በምን መንገድ? በምን ዘዴ እንደሚያደርጉት የምንከታተለው ይኾናል፡፡

የሚባሉት ዐይነት ሊቃነ ጳጳሳት ቢኖሩም ባይኖሩም ከእንግዲህ ለፅልመታዊው ቡድን የሚመች የሙስና ጫካ መመንጠር ይኖርበታል፡፡ የሙስናን ጫካ ለመመንጠር፣ መረቡን ለመበጣጠስ መንፈሳዊው ሰይፍ ሊሳል፣ አስተዳደራዊው ቁርጠኝነት ሊጠናከር ከሁሉም በላይ ተቋማዊው ሥርዐት ሊዘረጋ ይገባል፡፡

Advertisements

One thought on “የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ በ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ላይ የተላለፈውን እግድ አጸኑ

 1. ARAYA May 16, 2013 at 1:01 pm Reply

  ያሁኑ ዘገባችሁ ይሻላል. ቢያንስ የለዘበ ክርስቲያናዊ ቁዋንቁዋና የተወሰነ ማስረጃ ተጠቅማችሁዋል. ስለሙስና ያላችሁት ሁሉም እውነት ነው.እ/ር ይስጣችሁ.
  አሁንም ግን ጥያቄ አለኝ
  1.ፅልመታዊ የምትሉኣቸው ሁሉም የአንድ ብሄር ሰዎች መሆናቸው እናንተን ዘረኛ አያስብላችሁም ወይ?(እነወታደር ጥላሁን ዘአየርጤናን ስለመሳሰሉ ኢሰፓ የሸዋ ቀሳውስት አንደም ቀን ስትናገሩ አናይማ!!)
  2.የአባን መሀይምነት የነገረን አንደበታችሁ ስለ ን/ዕድ ምሁርነት(ሰይፍ ዘክልኤነት) ትንፍሽ አላለም.ለምን ሁለት መመዘኛ(የሙስና ሀሜቱ እንዳለ ሁኖ)
  3.የሆነውን ብቻ ሳይሆን መሆን ያለበትንም ተናገሩ ያለበለዚያ ትርፉ አማኙን ተስፋ ማስቆረጥ ነው
  4.በሰ/ት/ቤቶች ስለሚታዩ የአሰራርና የስ/ምግባር ጉድለቶች ምንም ማለት አትፈልጉም.ለምን?
  5.አስተዳደሩን ሁሌ ከማማረር ምናለ ስልጠና ብትሰጡ.
  6.ዘገባዎችን ዘላችሁ ከማውጣታችሁ በፊት ዘገባዎቹ ለቤ/ክ፣ለካህናት፣ለምእመናን/ት እና ለሀገር ያላቸውን ጥቅምና ጉዳት ለምን አትመዝኑም?
  7.በተረፈ ራሳችሁን ሃራ(ወታደር) እያላችሁ የአባን ውትድርና አታቃሉ(ጉዋዳዊ መከባበር ይኑር)!!!ለኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ያላችሁን ቀናኢነት(ስሜታዊነት አላልኩም) እወደዋለሁ!!!.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: