ፓትርያሪኩ ሙስናን በጋራ መቃወም እንደሚገባ አሳሰቡ

 • ‹‹ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ እንደተነሣ እኛም ሙስናን ከቤታችን ማጥፋት አለብን፤ የካህን ሙሰኛ፣ የካህን ሌባ፣ የካህን ጉቦኛ መኖር የለበትም፡፡›› /ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በበዓለ ትንሣኤ የ‹‹እንኳን አደረስዎ›› መርሐ ግብር ላይ ከተናገሩት/
 • በ‹‹እንኳን አደረስዎ›› መርሐ ግብር በኬክ፣ ቼክ እና ሌሎችም ውድ ገጸ በረከቶች ስም የሚፈጸመው ዝርፊያና ብኩንነት እንዲቀር ተደርጓል!
 • የፓትርያሪኩ ጽኑ የፀረ – ሙስና አቋም ፅልመታዊውን ቡድን አሳስቧል፡፡

Resurrection of Jesus Christከክርስቶስ ሞት ጋራ አንድ እንኾን ዘንድ በምስጢረ ጥምቀት እንደተባበርን ሁሉ ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋራ እንተባበራለን፡፡ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት መንፈሳዊና የማይበስበስ አካል ይዘን የምንነሣበት ትንሣኤ፣ ክርስቶስን የምንመስልበት የሕይወት ትንሣኤ ነው፡፡ ለሕይወት ትንሣኤ እንበቃ ዘንድ በምድር ሳለን በሚሞተው ሥጋችን ኀጢአት እንዳይገዛን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስጠነቅቁናል፡፡

ለትንሣኤ ዘለሕይወት የሚታደሉት በዚህ ዓለም ሳሉ በክርስቶስ አምነው፣ የትንሣኤው ተካፋይ ኾነው በየጊዜው በንስሐ ሕይወት እየታደሱ የሚኖሩ፣ ለኀጢአት የሞቱና መልካም የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለቈላስይስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ እንደገለጸው ለኀጢአት መሞት፣ መልካሙን ማድረግ÷ ‹‹በላይ ያለውን መሻት፣ በላይ ያለውን ማሰብ›› ነው፡፡ /ቈላ.3÷1፤ ሮም 6÷4-11/

በላይ ያለውን ለመሻት፣ በላይ ያለውን ለማሰብ የመንፈስ ልዕልና ያስፈልገናል፡፡ የኅሊና ትንሣኤ፣ የልቡና ትንሣኤ መነሣት ይገባናል፡፡ ትንሣኤ ኅሊና፣ ትንሣኤ ልቡና÷ ለትንሣኤ ዘለክብር፣ ለትንሣኤ ዘለሕይወት የሚያበቃን፣ ከትንሣኤ ዘለኀሳር፣ ከትንሣኤ ዘለሞት የሚጠብቀን ‹‹የፊተኛው ትንሣኤ›› ነው፡፡ የሞት መውጊያው፣ የመቃብር ኀይሉ የተሻረበትን፤ ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገርንበትን የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ ማክበር በጀመርንበት የፋሲካ ሰኞ /ማዕዶት/÷ ትንሣኤ ኅሊና፣ ትንሣኤ ልቡና ጥሪ ተደርጓል፡፡ ትንሣኤ ኅሊና፣ ትንሣኤ ልቡና በፀረ – ሙስና አቋም!

ሚያዝያ 28 ቀን 2005 ዓ.ም በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከፋሲካ ሰኞ /ማዕዶት/ ጋራ በተከበረው የፓትርያሪኩ የእንኳን አደረስዎ በዓል ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ድረስ ያሉ አገልጋዮችና ሠራተኞች ሙስናን በጋራ እንዲቃወሙ ጥሪ አድርገዋል፡፡ ‹‹ሙስና ቤተ መቅደስም ገብቷል›› በማለት የወቅቱን የቤተ ክርስቲያናችንን ቀንደኛ ችግር በሐቅና በግልጽ የተቀበሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ፣ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ነን የሚሉ ሁሉ ሙስናን ሊጸየፉት፣ ቤተ ክርስቲያንን ከሙሰኞችና ከሌቦች ለማጽዳት ሊነሣሱ፣ ሊተባበሩ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ቅዱስነታቸው÷ በዓለ ትንሣኤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ የተነሣበት መኾኑን ጠቅሰው፣ ‹‹እኛም ሙስናን ከቤታችን ማጥፋት አለብን›› ብለዋል፡፡ ‹‹ሙስና ቤተ መቅደስም ገብቷል›› በማለት የችግሩን አስከፊነት የገለጹት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ‹‹የካህን ሙሰኛ፣ የካህን ሌባ፣ የካህን ጉቦኛ መኖር የለበትም!›› በማለት ፀረ – ሙስና እና ፀረ – ሙሰኛ አቋማቸውን በግልጽ አስታውቀዋል፡፡

ሙስና በሁሉም ዐይነት ትርጉሙና ገጽታው በተንሰራፋበት፣ አስተሳሰቡን ይኹን ተግባሩን ከመጸየፍና ከማውገዝ ይልቅ በሙሰኝነት ለመክበር የሚጎመጀው ቁጥር በየጊዜው እየበዛና እየበረከተ በመጣበት ወቅት በተከበረው በዚሁ መርሐ ግብር ቀርበው የተሰሙት ቅኔዎችም ፀረ – ሙስና አቋሞችና መልእክቶች በግልጽ የተስተጋቡበትና የተላለፉት ጭምር እንደነበር ተዘግቧል፡፡

His Holiness Abune Matyas Qedamawi

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በስድስተኛ ፓትርያሪክነት ሥርዐተ ሢመት ከፈጸሙ ወዲህ የመጀመሪያቸው በኾነው የበዓለ ትንሣኤ የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር ላይ÷ በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደርን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ አራቱ አህጉረ ስብከት አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎችና የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤያት ሊቃነ መናብርት ተገኝተዋል፤ ሙስናንና ሙሰኞችን በመቃወም ለተላለፉ መልእክቶችም አጨብጭበዋል – ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን በመወከል የእንኳን አደረስዎ መልእክት ያስተላለፉትና መርሐ ግብሩን የመሩት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃን ጨምሮ ሲያጨበጨቡ ካረፈዱት ጥቂት የማይባሉት የሙስና ጌቶች መኾናቸው ሳይዘነጋ!

በሙስናና የአሠራር ብልሽት የአገርና የሕዝብ ሀብት እየባከነ፣ ክትትልና ቁጥጥር እየጠፋ፣ ሓላፊነት የሚሰጠው ሹመኛ፣ እምነት የሚጣልበት ተቋምና ሥርዐት እያጸጸ ለመኾኑ የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ግልጽ ባደረገበት ሳምንት÷ ሙስናንና ሙሰኞችን በመቃወም በተለይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የተላለፉት መልእክቶች ችግሩን በተመለከተ በተቋማዊ ድብታ (Institutional apathy) ውስጥ ለቆየው ቤተ ክህነታችን ታላቅ መነቃቃት፣ ታላቅ የትንሣኤ ተስፋ ነው፤ የኑፋቄ ሤረኞችን ጨምሮ ለተቋማዊ ለውጡ ዕንቅፋት የኾኑ ግለሰቦችና ቡድኖች የተጠለሉበትን የቤተ ክህነታችንን ሙስናና ሙሰኝነት እንደ ዋነኛ ችግር በሐቅ ተመልክቶ አስከፊነቱን ማወቅና መቀበል ትክክለኛውን መፍትሔ ለማግኘት ያስችላልና፡፡

ሙስናና ኑፋቄ ተሳስረውና ተመጋግበው ያቋቋሙት የቤተ ክህነቱ ፅልመታዊ ቡድን ቅዱስነታቸው በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት ጽኑ የፀረ ሙሰኝነት አቋም እንደተደናገጠ በዕለቱ በግልጽ ታይቷል፡፡ ባለፉት ኻያ ዓመታት በተለያዩ መምሪያዎችና ድርጅቶች በሓላፊነት እየተፈራረቁ ባካሄዱት ዘረፋ ቤተ ክርስቲያኒቱን ‹‹በዐፅሟ ያስቀሯት›› የጨለማው ቡድን ግለሰቦች፣ ከመርሐ ግብሩ ፍጻሜ በኋላ በግቢው በተለያየ ቁጥር ተነጣጥለው በመሰብሰብ በመቆም ሲመክሩ ታይተዋል፡፡ የቅዱስነታቸው መልእክት የሙስና አስከፊነት በመጪው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከአንገብጋቢ የተቋማዊ ለውጥ አጀንዳዎች መካከል በቀዳሚነት ሊነሣ እንደሚችል ጠቋሚ መኾኑን የተናገሩ አስተያየት ሰጪዎች÷ ኹኔታው በአንድ በኩል ጥቅማቸውን አስጠብቀው ለመቀጠል በሚፍጨረጨሩት ፅልመታውያኑ ዘንድ ከፍተኛ ስጋት ማሳደሩን እንደሚያመለክት ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በፀረ ሙስና አቋም ለተቋማዊ ለውጥ በመታገላቸውና በመጻፋቸው የተገፉና የተበደሉ የለውጥ ኀይሎች በበለጠ ጽናትና ተስፋ እንዲነሣሡ ብርታት ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡

ለ፮ው ፓትርያሪክ የመጀመሪያ በኾነው በዘንድሮው በዓለ ትንሣኤ የእንኳን አደረስዎ በዓል በፀረ – ሙስና አቋም የታየው የልቡናና የኅሊና መነሣሣት በቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳንና በቅኔዎች ብቻ አልነበረም የተገለጸው፡፡

ባለፉት ዓመታት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ እንኳን አደረስዎ በዓላት ኬክና ቼክን ጨምሮ በውድ ዋጋ የሚገዙ ስጦታዎች በገጸ በረከት ስም የሚቀርብባቸው፣ በዚህም ሰበብ በሙስና ያገኙትን ሹመት ማስጠበቅ የሚፈልጉ የአንዳንድ አድባራትና ገዳማት ሓላፊዎች ከፅልመታዊ ቡድኑ አባላት ጋራ በመመሳጠር የሚዘርፉባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ በዘንድሮው የበዓለ ትንሣኤ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ እንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር በዚህ ደረጃ የታየ የስጦታና ገጸ በረከት ጋጋታ የለም፡፡

ባለፉት ዓመታት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ እንኳን አደረስዎ በዓላት በጾምና በመንፈሳዊ አገልግሎት ሲደክሙ የሰነበቱት ካህናት እንዲሁም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች፣ በቅዳሴ አድረው በበዓላቱ ዕለት ጠዋት በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ እንዲገኙ ከካህናት አስተዳደር መምሪያው በሚተላለፈው ትእዛዝ ይገደዱ ነበር፡፡ በዘንድሮው የበዓለ ትንሣኤ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ እንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር፣ ካህናትና ሠራተኞች በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋራ እንዲውሉ ተደርጓል፤ በፋሲካ ሰኞ /ማዕዶት/ ደግሞ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ጋራ በዓሉን በጋራ አክብረዋል፡፡ ‹‹መርሐ ግብሩ እኔን ብቻ ሳይሆን እርስ በርሳችንም እንኳን አደረሳችኹ የምንባባልበት ነው፤›› ብለዋል ቅዱስነታቸው፡፡

በበዓሉ አከባበር ወቅት በገጸ በረከት ስም መዝረፉ፣ ከዋዜማው ድካም ጋራ በግዳጅ መገኘቱ የቀረው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ከበዓሉ ሳምንታት አስቀድሞ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አማካይነት ለሚመለከታቸው ሁሉ ያስተላለፉትን አባታዊ መመሪያ ተከትሎ ነው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ከሥርዐተ ሢመታቸው በኋላ በአባታዊ መመሪያ የሸኟቸው እንዲህ ያሉ ረብ የለሽ የቀደሙ ልምዶች በርካታ ናቸው – የአጃቢዎች ትርምሱን፣ የጥበቃ ጋጋታውን፣ ከንቱ ውዳሴውንና ጩኸቱን፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚፃረሩ ሌሎች አሠራሮችንም ይጨምራል፡፡ የፅልመታዊ ቡድኑን የጥቅመኝነት ተስፋ ከንቱ ያደረጉት እኒህ አባታዊ መመሪያዎች፣ በቅርቡ በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ታይተውና ተመርጠው በልዩ ጽ/ቤታቸው በጸሐፊነት የተመደቡት ልዩ ጸሐፊያቸው በሚያሳዩት የአሠራር ለውጥም እየተገለጸ ነው፡፡ ይበል፤ ይቀጥል ያሰኘ የተግባር ጅምር ነው፡፡

ነገር ግን÷ ለውጡ በጅምር ነውና የቤተ ክርስቲያናችን ነባራዊና ወቅታዊ ተግዳሮቶች በሚጠይቁት ልክ እንዲሰፋ፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ታሪካዊ ክብርና ተቋማዊ ሉዓላዊነት መጠበቅ ዋስትና በሚሰጥ አኳኋን እንዲጠናከር፣ አስተማማኝና ዘላቂ እንዲኾን እንመኛለን፡፡ አስተማማኝና ዘላቂ ለውጥ ያለተቋምና ሥርዐት ግንባታ እውን አይኾንምና ለውጡ÷ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዕድገት ባገናዘበ አኳኋን በሚሻሻለው ቃለ ዐዋዲና ሕገ ቤተ ክርስቲያን ሊደገፍ፤ በመንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የቤተ ክርስቲያኒቱን ርእይና ተልእኮ በግልጽ በሚያሳይ ስትራተጂያዊ ዕቅድ ሊመራ ይገባል፡፡

ለውጡ÷ ሙስናውና የአሠራር ብልሽቱ አስመርሮ የገፋቸውንና ከባለቤትነት ስሜት አርቆ ባይተዋር ያደረጋቸውን ሥልጡንና ቀናዒ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ሊያሳትፍ ይገባል፡፡ ለውጡ÷ ጠቅላይ ቤተ ክህነታችን በተሐድሶ ኑፋቄ ርዝራዦች፣ ሙሰኞች፣ ጎጠኞችና አድርባይ ፖለቲከኞች ሤራ የታጀለበትን ‹‹አሮጌ ሰውነት›› ከሥራዎቹ ጋራ ገፍፎ ለመንፈሳዊነትና ሞያዊነት ተገቢው ዋጋ የሚሰጥበትን፣ ሠራተኞችና አገልጋዮች በመንፈሳዊነታቸው፣ ቀናዒነታቸውና ሞያዊ ብቃታቸው ብቻ ተመዝነው የድርሻቸውን ለመወጣት ዕድል የሚያገኙበትን ‹‹አዲስ ሰውነት›› እንዲላበስ ያስፈልጋል፡፡

ጠቅላይ ቤተ ክህነታችን በሙስናና ሙሰኝነት ሚካበተው ሥልጣንና ጥቅም ከሚጎመጅ ነውርና ርኲሰት ተጠብቆ ‹‹አዲስ ሰውነት›› /ቈላ3÷11/ የሚላበሰው÷ ከመንበረ ፓትርያሪክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ያለው አመራርና አስፈጻሚ፣ ካህንና ምእመን ትንሣኤ ኅሊናን፣ ትንሣኤ ልቡናን ገንዘብ ሲያደርግ፣ ቅዱስነታቸው በትንሣኤ በዓል ቃለ በረከታቸው እንዳሳሰቡን ለሥራ ሲተጋና በፍጹም ፍቅር ሲኖር ነው፡፡

ቤተ ክህነታችን ሆይ÷ ትንሣኤን ያሳየን!!

Advertisements

8 thoughts on “ፓትርያሪኩ ሙስናን በጋራ መቃወም እንደሚገባ አሳሰቡ

 1. Anonymous May 10, 2013 at 8:32 am Reply

  ነገር ግን÷ ለውጡ በጅምር ነውና የቤተ ክርስቲያናችን ነባራዊና ወቅታዊ ተግዳሮቶች በሚጠይቁት ልክ እንዲሰፋ፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ታሪካዊ ክብርና ተቋማዊ ሉዓላዊነት መጠበቅ ዋስትና በሚሰጥ አኳኋን እንዲጠናከር፣ አስተማማኝና ዘላቂ እንዲኾን እንመኛለን፡፡ አስተማማኝና ዘላቂ ለውጥ ያለተቋምና ሥርዐት ግንባታ እውን አይኾንምና ለውጡ÷ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዕድገት ባገናዘበ አኳኋን በሚሻሻለው ቃለ ዐዋዲና ሕገ ቤተ ክርስቲያን ሊደገፍ፤ በመንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የቤተ ክርስቲያኒቱን ርእይና ተልእኮ በግልጽ በሚያሳይ ስትራተጂያዊ ዕቅድ ሊመራ ይገባል፡

 2. Anonymous May 10, 2013 at 11:37 am Reply

  Amen!!! EGZIABHER Ye BETEKIRISTIYANACHININ ena Ye ETHIOPIAN tinsae yasayen

 3. mesfin May 10, 2013 at 12:59 pm Reply

  temesgen ,temesgen, temesge cheru medhanialem yedingil mariam lij yasiben yewetenutin yasfetsimachew torinetu ke erkusan menafisit gar newna tselotun hulachinim beyalenibet endaniresa…tesfa yekoretu yetehadiso blogoch mesadebina sim matifat jemirewal…harawoch bertulin

 4. Anonymous May 10, 2013 at 11:56 pm Reply

  በጄ የሚያስብል ነው:: እግዚአብሔር ይርዳቸው

 5. Adamu May 11, 2013 at 10:58 am Reply

  that is very interesting News

 6. geezonline May 12, 2013 at 2:02 pm Reply

  Short circuit this piece with this one: http://ecadforum.com/Amharic/archives/7716 and you will get the real sense and purpose of all the fuss about corruption. It is no coincidence, my friends. My question to Hara is this: is it unbeknownst to you that you have lately been engaged in a quasi-campaign to help the completely rotten system survive, mainly through building an image of a wolf in sheep’s clothing?

 7. Anonymous May 14, 2013 at 2:03 pm Reply

  ጅማሬው ይበል የሚያሰኝ ለፍፃሜው ግን የሁላችንም ሃላፍነት አለብን

 8. Anonymous May 14, 2013 at 2:45 pm Reply

  it is good start!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: