ዴር ሡልጣን የሃይማኖት ብቻ ሳይኾን የፖሊቲካና የታሪክ ጥያቄም ጭምር ነው

ምንጭ፡- አዲስ ጉዳይ መጽሔት፤ ርእሰ አንቀጽ፤ ቅጽ 7 ቁጥር 162፤ 2005 ዓ.ም.

Addis Guday Top Stories on Dier Sultanኢትዮጵያ ጥንታዊት አገር ናት፡፡ ይህች አገር ከምትታወቅባቸው ነገሮች አንዱና ዋናው ክርስትናንና እስልምናን ከሌሎች አገሮች የተቀበለች መኾኗ ጭምር ነው፡፡ ለረጅም ዘመናት የቆየ የእምነት ታሪኳ የአገሪቱ ታሪክ አንድ አካል ኾኖ ሁሌም ሲጠቀስ ኖሯል፡፡ በዚህ ሳቢያ ይህች ጥንታዊት አገር የክርስትና ቅድስት ሥፍራ ተብላ በምትታወቀው ኢየሩሳሌም ርስት አላት፡፡ ይህ ርስት ለእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይኾን ለመላው ኢትዮጵያዊ ኩራትም ጭምር ነው፡፡ ለምን ቢሉ የኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ በራሱ የአገሪቱን ስምና ክብር፣ ታሪክና ማንነት ከፍ የሚያደርገው በመኾኑ ነው፡፡

እንደሚባለው ፈረንጆቹ ገና ከዋሻ ሳይወጡ ሕንፃ የገነቡት ሕዝቦች፣ ፈረንጆቹ በዛፍና በድንጋይ ሲያመልኩ ሁለቱም ሃይማኖቶች የነበሯቸው ሕዝቦች ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ያም ኾኖ ዛሬ በታሪክ ይኹን በእምነት፣ ታሪካችንም ኾነ እምነታችን ይዞት በመጣው ገናናነት የከበረ ስማችን አሁን የለም፡፡ የዚያ ገናናነት ማስታወሻ ታሪካችን ግን ሞልቶ ተርፏል፡፡ ቁም ነገሩ ይህ ብቻ አይደለም፤ የታላቅነታችንና የክብራችን መገለጫ የኾኑ ቅርሶቻችን በሌሎች አገሮችም ይገኛሉ፡፡ በተለይ በኢየሩሳሌም የሚገኘው የኢትዮጵያ ርስት አገራችን በዚህች ቅድስት ሥፍራ ያላትን ተሰሚነትና የታላቅ ታሪክ ባለቤትነት የወከለ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በታሪክ የነበራት ገናናነት የፈጠረላት ተሰሚነት በዓለም ዋና ዋና የፖሊቲካና እምነት ቦታዎች ላይ መጠርያዋን እንድትተክል አስችሏታል፡፡ የታላቅነታችን ማስታወሻም ኾኗል፡፡

ዛሬ ግን ቢያንስ በዚህ የታላቅነታችን ታሪክ እየተጽናናን እንዳንኖር እንኳ ማስታወሻችን እየጠፋብን አልያም በሌሎች የዘመኑ ኀያላን እየተነጠቅን ነው፡፡ ከእኒህ አንዱ ዴር ሡልጣን ነው፡፡ በኢየሩሳሌም የሚገኘውንና ታሪክ በኢትዮጵያ ንብረትነት የሚያውቀውን ዴር ሡልጣን በግብጾች እየተነጠቅን ነው፡፡ ቀድሞም ብዙውን ክፍል ወስደውብናል፡፡ አሁን ደግሞ ከጠቅላላ ይዞታችን ከዐሥር በመቶ ያልበለጠ ብቻ ነው የቀረን፡፡ ታዲያ፣ ይህ ቅርስና ርስት ባይኖረን ምን ችግር አለው?

ችግር አለው፡፡ ዛሬ የዓለም መንግሥታት ኀያልነታቸውንና የፖሊቲካና የታሪክ የበላይነታቸውን ለማሳየት ከመሣሪያቸው እኩል የሚያዩት ጡንቻቸው ታሪካቸው ነው፡፡ ያለቻቸውን ታሪክ ጠጋግነውና የሌላቸውን ጨማምረው የዓለም አለቆች ነን የሚሉ በበዙበት በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ያሏትን ሐቆች በጉለበተኞች እየተቀማች መቀጠሏ ጥቃት ነው፡፡ ተቆርቋሪ መንግሥት የማጣት ያህል ጥቃት ነው፡፡ የግብጽ መንግሥታዊ ሃይማኖት እስልምና ነው፡፡ የግብጽ መንግሥት ግን ዴር ሡልጣንን በቸልታ አያየውም፡፡ ‹‹ግዛታችን ነው፤ በኢየሩሳሌም ያለንን ተሰሚነትና የበላይነት የምናጠነክርበት መንገዳችን ነው›› በማለት የተረፈችውንም ግዛት ከኢትዮጵያ ላይ ለመንቀል ሲጥር ኖሯል፡፡ በአንጻሩ ግን ኢትዮጵያውያን የሚሟገትላቸው ጠንካራ ተቋምና መንግሥት በማጣታቸው ወይም የጀመሩትም በጊዜ ሂደት እየተሰላቹ ጉዳዩን በመተዋቸው ከክርስቶስ ልደት በፊት የያዝነው ቅርሳችን በመጤዎች እየተቀማና እየተወሰደ አሁን ባዷችንን ልንቀርና ከኢየሩሳሌም ታሪክ ኾነን ልንጠፋ ጥቂት ቀናት ናቸው የቀሩን፡፡

ይህን ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ቤተ ክርስቲያንና ውጭ አገር ባሉ የኢትዮጵያ ተቆርቋሪዎች አነሣሽነት በግፍ የተወሰደው የዴር ሡልጣን ርስታችን እንዲመለስልን በሰላማዊ ሰልፎችና በአቤቱታ ፊርማዎች የታገዘ እንቅስቃሴ ሊደረግ መኾኑ ተሰምቷል፡፡ በርግጥ ይህ ሁሌም አንድን ጉዳይ መንግሥት ብቻ እንዲከታተል የመተው ባህላችን በመጠኑ የሚለውጥና የሕዝቡን የነቃ ተሳትፎ የሚያበረታታ ጉዳይ ነው፡፡ በገዳሙ ያሉ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ሁሌም ሲደበደቡ፣ መብራትና ውኃ ሲቆረጥባቸው፣ እንዳይወጡ ሲከለከሉና መጸዳጃ ቦታ እንኳ እንዳያገኙ ሲታገዱ ይሁ ሁሉ መከራ ሳይበግራቸው ሕይወታቸውን ጭምር እየከፈሉ ያን ርስት ጠብቀው አቆይተውታል፡፡ ይህን ያደረጉት ለሃይማኖታቸው ቀናዒ በመኾናቸው ብቻ ሳይኾን ለታሪካቸውና ለቅርሳቸው ተቆርቋሪና ሟች በመኾናቸው ጭምር ነው፡፡ የእኒህን አባቶች ጥረት ለመደገፍ የአሁኑ ትውልድ ምን ሠርቷል ብሎ ለጠየቀ ግን ችግሩና ብሶቱ ስለመኖሩም የሚያውቀው ጥቂት ነው የሚል ምላሽ እናገኛለን፡፡

ባለፉት ዘመናት ይህን በኢየሩሳሌም የሚገኝ የኢትዮጵያ ርስት ለማስጠበቅ ነገሥታት ብዙ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ከአንዱ ንጉሥ ወደሚቀጥለው በተንከባለለ ቁጥር የሚደረገው ጥረትም እያነሰና ፍሬያማነቱም እየቀነሰ መጥቷል፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን ነገሩ ጭራሽ ተረስቷል ወደሚል ደረጃ ላይ እየደረስን ነው፡፡ የዴር ሡልጣን ርስታችን ልክ እንደ አኵስም ሐውልታችን ቅርሳችን ነውና እንዲመለስልን መጠየቅ ዓለም አቀፍ መብታችን ነው፡፡ በተለይ ይህን ርስት ያጣነው በግብጻውያን የዘመናት ተንኮልና ሤራ እንዲሁም ማን አለብኝነት መኾኑን ስናስበው የሚያንገበግበን ኾኖ እናገኛዋለን፡፡

በዚህ ረገድ ለመንቀሳቀስ አንድ ዕንቅፋት የኾነው ጉዳዩን የሃይማኖት ብቻ አድርጎ መመልከቱ ነው፡፡ ይህ ቢኾን ኖሮ በአገራቸው የሚገኙትን ኮፕት ኦርቶዶክሶች ባገኙት አጋጣሚ ኹሉ የሚጨፈጭፉትና የሚያሠቃዩት የግብጽ እስላማዊ መንግሥት ባለሥልጣናት ዴር ሡልጣን ላይ ያገባናል ብለው እጃቸውን ባላስገቡ ነበር፡፡ ጉዳዩ የታሪክና የፖሊቲካ የበላይነት ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩ የሀገር ሉዓላዊ መብት መከበርና አለመከበር ጉዳይ ነው፡፡ እኛን የሚገባን እዚህ ድረስ ነው፡፡

ያም ኾኖ በጉዳዩ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ቤተ ክርስቲያኒቱም ራሱን የቻለ ችግር ታቅፋ ተቀምጣለች፡፡ አዲሱ ፓትርያሪክ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ኾነው መሥራታቸው ስለጉዳዩ ባላቸው ጥልቅ ግንዛቤ ችግሩን ለመፍታት ያስችላቸዋል ብለን እናምናለን፡፡ ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ሓላፊነት እንደሚሰማው ሚዲያ ተነሣሽነት ወስደን ዘገባ ለመሥራት በተዘጋጀንበት ወቅት ምንም ዐይነት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይኾኑ ቀርተዋል፡፡ ከሰኞ ሚያዝያ 22/2005 ዓ.ም 6፡00 ጀምሮ እስከ ማክሰኞ ምሽት 12፡00 ድረስ አምስት የተለያዩ ቀጠሮዎችን ሰጥተው ቢያመላልሱንም ይህንኑ ታግሠን ስንጠባበቅ በመጨረሻ ላይ ‹‹ሥራ በዝቶባቸዋል›› ተብለን መረጃውን እንደማናገኝ በተዘዋዋሪ ተነግሮናል፡፡ እንግዲህ ጉዳዩ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህን ጉዳይ ካላበረታታችና ዕውቅና ካልፈጠረች ማን ሥራዋን ሊሠራላት ነው?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: