ስለ ሃይማኖት ተቋማት ምዝገባ አንዳንድ ነጥቦች

*ቀለመ ወርቅ ሚደቅሳ

ምንጭ፡- ዕንቁ መጽሔት፣ ቅጽ 6 ቁጥር 90፣ ሚያዝያ 2005 ዓ.ም

መንደርደሪያ

የሃይማኖት እና የእምነት ነጻነት መብት መሠረታዊ የሰብአዊ መብት አካል ነው፡፡ የሃይማኖት ነጻነት መብት የምንለው አንድ ሰው ፈጣሪ መኖሩን በመሰለው መልክ በመበየን ብቻውን ወይም ከሌሎች ጋር የሚኖረውን የማምለክ መብት የሚገልጽ ነው፡፡ የእምነት ነጻነት ደግሞ ፈጣሪ የለም ብሎ ከማመን ጀምሮ አንድ ሰው የእምነት ጉዳይን በሚመለከት ያለውን ነጻነት የሚመለከት ነው፡፡

በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተደረገ የሕዝብ ቆጠራ ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ 97% የሚኾነው ‹‹ሃይማኖተኛ›› መኾኑን ከብሔራዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ ይገልጻል፡፡ ከዚህ ነጥብ በመነሣት በኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ጉዳይ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ማኅበራዊ ጉዳይ መኾኑን መደምደም ይቻላል፡፡ በተጨማሪም የእምነት ነጻነት ጉዳይ ያለው ሽፋን አነስተኛ መኾኑን ማየት ይቻላል፡፡ በመኾኑም የዚህ ጽሑፍ ትኩረት የሃይማኖት ጉዳይ ላይ ይኾናል፡፡

የሃይማኖት ነጻነት መብት በግል የሚያምኑበትን ሃይማኖት መምረጥን ወይም መያዝን፣ ሃይማኖትን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመኾን ማምለክን፣ መተግበርን፣ ማስተማርን ወይም መግለጽን ያጠቃልላል፡፡ በእነዚህ ዝርዝር መብቶች በጋራ ተጠቃሚ ለመኾን አንድ ቡድን የሃይማኖት ተቋሙ የሕግ ዕውቅና እንዲያገኝለት ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ጽሑፍ ከሃይማኖት ተቋማት ምዝገባ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አንዳንድ ነጥቦች ለማንሣት ይሞክራል፡፡

የሃይማኖት ነጻነት መብት የሕግ ማዕቀፍ  

የሃይማኖት እና የእምነት ነጻነት መብት ምንም እንኳ ሰው በመኾን ብቻ የሚገኝ መሠረታዊ መብት ቢኾንም በዓለም አቀፍ፣ በአህጉራዊ እና ብሔራዊ ሕግጋት ዕውቅና የተሰጠው መብት ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መበቶች ቃል ኪዳን ሰነድ (Universal Declaration of Human Rights) ትኩረት ከሰጣቸው የሰው ልጆች መሠረታዊ መብቶች መካከል አንዱ በሰነዱ አንቀጽ 18 የተደነገገው የሃይማኖትና የእምነት ነጻነት መብት ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥትም የሃይማኖትና የእምነት ነጻነት መብትን በአንቀጽ 27 ሥር ዕውቅና ይሰጣል፡፡

ከላይ በመግቢያው እንደተገለጸው፣ የሃይማኖት ነጻነት መብት አንድ ሃይማኖትን መቀበል ወይም በአንድ ሃይማኖት ማመንን፣ በሚያምኑበት ሃይማኖት በግል ወይም በቡድን የአምልኮ ሥርዐት መፈጸምን እንዲሁም የሚያምኑበት ሃይማኖት ሕጋዊ ዕውቅና እንዲያገኝ መጠየቅን የሚያጠቃልል ነው፡፡

የሕግ ሰውነት አንድ አካል (የተፈጥሮ ሰውም ይኹን ተቋም) እኔ ባይ ኾኖ፣ የመብትና የግዴታ ባለቤት ኾኖ የሚኖርበትን ኹኔታ የሚገልጽ ነው፡፡ የተፈጥሮ ሰው የሕግ ሰውነት የሚያገኘው በልደቱ ነው፡፡ አንድ ተቋም የሕግ ሰውነት የሚኖረው በሕግ ሲቋቋም (የመንግሥት ልዩ ልዩ ተቋማትን ይመለከቷል) ወይም ደግሞ በሕግ የተደነገገን መስፈርት አሟልቶ ፈቃድ ከሚሰጥ አካል የምዝገባ ምስክር ወረቀት ሲያገኝ (ልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የንግድ ድርጅቶችን ይመለከቷል) ነው፡፡

የሃይማኖት ተቋማት የሕግ ሰውነት

በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዐት ስለ ሃይማኖት ተቋማት የሕግ ሰውነት ሲነሣ ወደ ውይይት ጠረጴዛ የሚቀርበው በ1952 ዓ.ም የወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አቋቁሟል (አንቀጽ 398ን ይመለከቷል)፡፡ ሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ሕጉን ተከትሎ በሚወጣ ልዩ ደንብ እንደሚመዘገቡ (የፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 407ን ይመለከቷል) ደንግጓል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ታሳቢ የሚያደርገው የሃይማኖት ተቋማት ምዝገባ ደንብ የወጣው በ1959 ዓ.ም ነው፡፡ ንጉሡ ከሥልጣን እስከወረዱበት ጊዜ ድረስ የአገር ግዛት ሚኒስቴር የሃይማኖት ተቋማትን እየመዘገበ ዕውቅና ይሰጥ ነበር፡፡ የደርግ መንግሥት በሕግ ማዕቀፍ ረገድ ከዚህ አሠራር የተለየ ሥርዐት አልዘረጋም፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት ከዚህ ነጥብ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ድንጋጌ የለውም፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 11 መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መኾናቸውን፣ መንግሥታዊ ሃይማኖት እንደማይኖር እና መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ደንግጓል፡፡ የሕገ መንግሥቱ ረቂቅ ማብራሪያ ይህን ነጥብ ሲያብራራ ‹‹መንግሥት የሃይማኖት ነጻነትን ከማክበር በስተቀር የሃይማኖት ተቋማትንና ሃይማኖታዊ ድርጅቶችን አያደራጅም፤ አያግዝም፡፡ መንግሥት የሃይማኖት ስብከት የሚካሄድበትን ትምህርት ቤት አይከፍትም፤ ለሃይማኖት ትምህርት ቤቶችም ዕውቅና አይሰጥም፤›› ይላል፡፡

ሕገ መንግሥቱን ተከትሎ እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ ከሰባት መቶ ሰማንያ በላይ ዐዋጆች እና ከሁለት መቶ ስድሳ አምስት በላይ ደንቦች ወጥተዋል፤ ነገር ግን የሃይማኖት ተቋማት ምዝገባን በሚመለከት የወጣ ዐዋጅም ኾነ ደንብ የለም፡፡

የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመደንገግ የወጣው ዐዋጅ ቁጥር 471/98 የሃይማኖት ድርጅቶች የመመዝገብ ሥልጣን ለፍትሕ ሚኒስቴር ይሰጣል (የዐዋጁን አንቀጽ 23(8) ተመልከት)፡፡ ይኸው ሥልጣን በዐዋጅ ቁጥር 691/2003 ትንሽ ሰፋ ብሎ ‹‹የሃይማኖት ድርጅቶችንና ማኅበራትን ይመዘግባል›› በሚል ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተሰጥቷል (የአዋጁን አንቀጽ 14(1)(ሸ) ተመልከት)፡፡ ሁለቱም ዐዋጆች ለሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ የሃይማኖት ድርጅቶችን የመመዝገብ ሥልጣን ከመስጠት በስተቀር የምዝገባው ዝርዝር አሠራር በተመለከተ የሚያስቀምጡት ድንጋጌ የለም፡፡ በመሠረቱ እነዚህ ዐዋጆች ዓላማቸው የፌዴራል መንግሥቱን አስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር የመደንገግ ስለሆነ ይህን መሰሉን ዝርዝር እንዲያካትቱ አይጠበቅም፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት ዐዋጅ ቁጥር 621/2001 ረቂቅ ላይ በተደረገ ውይይት የሃይማኖት ተቋማት በዐዋጁ እንዲካተቱ የሚል ሐሳብ ተነሥቶ ነበር፤ ነገር ግን ሐሳቡ ተቃውሞ ስለገጠመው ሳይካተት ቀርቷል፡፡ በወቅቱ ሐሳቡን የተቃወሙ አካላት ምክንያታቸውንና የመፍትሔ ሐሳባቸውን በሚከተለው መልኩ አጠቃልለው አቅርበው ነበር፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት ዐዋጅ ድንጋጌዎች በተለይ ከምዝገባ፣ ቁጥጥርና ቅጣት ጋር የተያያዙት ተቋማት ልዩ ጠባይና ከመንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መኾን ሕገ መንግሥታዊ መርሕ አንጻር አግባብነት አይኖራቸውም፡፡ ከዚህ ይልቅ የሃይማኖት ተቋማትን ምዝገባ በሚመለከት ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ ቢዘጋጅ የተሻለ ይኾናል፡፡ የሚዘጋጀውም ሕግ የየሃይማኖት ተቋሙን ልዩ ጠባይ ግምት ውስጥ ያስገባ መኾን ይኖርበታል፡፡  

ከላይ የተነሡትን ዝርዝር ነጥቦች በመመርኮዝ ከሃይማኖት ተቋማት ምዝገባ ጋር ተያይዞ አሁን በሥራ ላይ ያለው የሕግ ማዕቀፍ የፍትሐ ብሔር ሕጉ እና ደንብ ቁጥር 321/1959 ነው ማለት ይቻላል፡፡

ምን ይኹን!!!

በኢትዮጵያ ነባራዊ ኹኔታ የሃይማኖት ተቋማት በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ዓላማቸው የተለያየ የኾኑ ተቋማት የሚመሠረቱበትና ፈቃድ የሚያገኙበት የሕግ ማዕቀፍ ሲዘጋጅ ቢታይም ለሃይማኖት ተቋማት የታየ ነገር የለም፡፡

በተወሰነ ደረጃ ጉዳዩን በሚያስፈጽሙ የመንግሥት ተቋማት አካባቢ መመሪያዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ጉዳይ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩት የሕግ ማዕቀፎች ጉዳዩን ያስተናገዱት በዐዋጅ እና በደንብ ደረጃ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት የሕጎች ተዋረድ (legislation hierarchy) ሕገ መንግሥት፣ ዐዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ እያለ እስከ ዝቅተኛው የሕግ ማዕቀፍ እርከን ድረስ ይወርዳል፡፡ በዐዋጅ የተደነገገን የሕግ ጉዳይ በደንብ ማሻሻል፣ በደንብ የተደነገገውንም በመመሪያ ማሻሻል ከሕግ ማርቀቅ መርሕ አንጻር አግባብነት አይኖረውም፡፡

በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዐት የመመሪያዎች ተፈጻሚነት አከራካሪ ነው፡፡ መመሪያ ላይ የሚነሡ ክርክሮች በርካታ ናቸው፡፡ መመሪያ በአንድ አስፈጻሚ አካል የሚዘጋጅ ስለሆነ ለብልሹ አሠራር የተጋለጠ ነው፣ መመሪያ እንደ ዐዋጅና ደንብ ታትሞ ስለማይሠራጭ ብዙ ሰው የማወቅ ዕድል አይኖረውም የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከላይ ከተነሡት ምክንያቶች አንጻር ሲታይ የሃይማኖት ተቋማት ምዝገባን ጉዳይ በመመሪያ ማስተናገድ የሚደገፍ አይኾንም፡፡ ስለዚህ ቀደም ያሉት የሕግ ማዕቀፎች ጉዳዩን ባስተናገዱበት መጠን በዐዋጅ ወይም በደንብ የሚታይበት አሠራር ቢኖር ለአገር ጠቃሚ ይኾናል፡፡

*አቶ ቀለመ ወርቅ ሚደቅሳ፤ የሕግ ባለሞያና በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የ3ኛ ዓመት ደቀ መዝሙር ናቸው፡፡

Advertisements

3 thoughts on “ስለ ሃይማኖት ተቋማት ምዝገባ አንዳንድ ነጥቦች

  1. Anonymous May 8, 2013 at 8:50 am Reply

    mengest yejemerewen orthodoxen yemadakem tegbar beglest yefa awetaw

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: