የኮሌጁን ችግርና የደቀ መዛሙርቱን ጥያቄ የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቋመ

  • በቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው የተለጠፈው ማስታወቂያ ሕገ ወጥ ነው
  • ሁለቱ ሓላፊዎች ከማስተማር እንደተከለከሉ ናቸው
  • የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ‹‹ሁለቱ ሓላፊዎች እንዳይነኩብኝ›› እያሉ ነው

ቤተ ክርስቲያናችን ካሏት ሦስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ቀዳሚ በኾነው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተባብሶ በሚታየው ሙስናና የአሠራር ብልሹነት ሳቢያ ደቀ መዛሙርቱ ያነሧቸውን አካዳሚያዊና አስተዳደራዊ ችግሮች የተመለከቱ ጥያቄዎች የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡

ከመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ፊልጶስ ፊርማ የወጣውና ለመንፈሳዊ ኮሌጁ አስተዳደር የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው÷ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ አራት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች በአመራርነትና በአባልነት፣ ሁለት የኮሌጁ መምህራንና ሁለት የደቀ መዛሙርቱ ተወካዮች በአስረጅነት የሚገኙበት ነው፡፡

በኮሌጁ ምክትል ዋና ዲን ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም መለሰ አማካይነት ለመምህራኑና ለደቀ መዛሙርቱ በተነበበው ደብዳቤ መሠረት አጣሪ ኮሚቴውን በሰብሳቢነት የሚመሩት የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ ዐማኑኤል ሲኾኑ በጸሐፊነት ደግሞ በተከታታይ ትምህርት መርሐ ግብር ከኮሌጁ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁት የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ፍሥሓ ጌታነህ ተመድበዋል፡፡ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊ አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ የአጣሪው ኮሚቴው አባላት ናቸው፡፡

ከአጣሪ ኮሚቴው ጋራ በአስረጅነት የሚሠሩትን ሁለት የመምህራንና ሁለት የደቀ መዛሙርት ተወካዮች መምህራኑና ደቀ መዛሙርቱ በራሳቸው ባካሄዱት ስብሰባ መርጠዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከጠቅላላው የኮሌጁ 16 መምህራን መካከል ዐሥራ ሁለቱ በተገኙበትና በምክትል ዋና ዲኑ በተመራው ስብሰባ÷ የኮሌጁ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መምህር መኰንን ወርቅነህ እና የእንግሊዝኛ መምህሩ ከተማ አሰፋ ተመርጠዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ባካሄዱት ስብሰባ የተማሪዎች መማክርት ሰብሳቢው ዲ/ን ታምርአየሁ አጥናፉ እና አባ ሳሙኤል ለአጣሪ ኮሚቴው በአስረጅነት መመረጣቸው ታውቋል፡፡

አጣሪ ኮሚቴው ሥራውን የሚያከናውነው ደቀ መዛሙርቱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በጽሑፍ በዘረዘሯቸው ችግሮች ላይ ተመርኩዞ ሲኾን እነርሱም፡-

  • በስም የተጠቀሱት ሁለቱ ሓላፊዎች ከቦታቸው እንዲነሡ፣
  • አስተዳደር ጉባኤው አሉበት ስለተባሉት ችግሮች፣
  • ለተማሪዎች መማክርት ጉባኤ ቢሮ እንዲሰጥና በማቴሪያል እንዲሟላ፣
  • በምግብ አገልግሎትና በአገልግሎቱ ዙሪያ የተማሪው ተሳትፎ

በሚሉ አራት ዋና ዋና ነጥቦች ተጠቃለው በደብዳቤው ላይ መቅረባቸው ተገልጧል፡፡ ኮሚቴው ማጣራቱን ጨርሶ ሪፖርቱን የሚያቀርብበት የተወሰነ የጊዜ ገደብ ስለመኖሩ በደብዳቤው የተመለከተ ነገር የለም፡፡

ደቀ መዛሙርቱ ለሁለት ሳምንት ትምህርት በማቋረጥና ከምግብ በመከልከል በአስተዳደሩ ላይ ባሰሙት ተቃውሞ ከቦታቸው እንዲነሡ ጥያቄ ያቀረቡባቸው÷ የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው መ/ር ዘላለም ረድኤትና የአካዳሚክ ምክትል ዲኑ መ/ር ፍሥሓ ጽዮን ደመወዝ ከተቃውሞው በኋላ በክፍል ተገኝተው ከማስተማር ታቅበዋል፤ የአስተዳደር ሥራቸውን ግን እንደቀጠሉ መኾናቸው ተዘግቧል፡፡

ደቀ መዛሙርቱ በመምህራኑ አግባቢነት ትምህርታቸውን ሳያስተጓጉሉ ተቃውሟቸውን ለመቀጠል ወስነው ትምህርት ከጀመሩ በኋላ የቀኑ መርሐ ግብር ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱን በመግለጽ ደቀ መዛሙርቱ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ የሚያሳስበው ማስታወቂያ የተለጠፈው በቀኑ መርሐ ግብር አስተባባሪ ተንኰል መኾኑን ያመለከቱት የኮሌጁ ምንጮች፣ ማስታወቂያው እስከ አሁን ተለጥፎ የሚታይ ቢኾንም የኮሌጁ ሓላፊን ቲተርና ፊርማ፣ ቁጥርና ቀን ሳይዝ በክብ ማኅተምና በነጭ ወረቀት ብቻ የወጣ ሕገ ወጣ ማስታወቂያ እንደኾነ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

ኮሚቴው የደቀ መዛሙርቱን ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ በሚያካሂደው የማጣራት ተግባር ኮሌጁ በሙስናና በአሠራር ብልሹነት ያለበትን ችግር በሚገባ በመፈተሽ የማያዳግም መፍትሔ እንደሚሰጥበት በደቀ መዛሙርቱና በአስተዳደሩ በተገፉት ብዙኀን መምህራን ዘንድ ተስፋ ተጥሎበታል ፡፡ ምንም እንኳ የመማር ማስተማሩ ሂደት በመልካም አያያዝ እየተከናወነ ቢኾንም አካዳሚያዊ መብቶቻችንን በመጠየቃችን፣ ለመልካም አስተዳደር መስፈን በመነሣሣታችን ከዛሬ ነገ የአስተዳደሩ የበቀል በትር ያርፍብናል ለሚሉ የደቀ መዛሙርቱ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም መሪዎችም የአጣሪ ኮሚቴው መቋቋም ዋስትና እንደሚሰጥ ታምኖበታል፡፡

ደቀ መዛሙርቱ ትምህርታቸውን እየተከታተሉና የምግብ አገልግሎት እያገኙ ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ሲያሳስቡ የቆዩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ÷ በቋሚ ቅ/ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት የኮሌጁን አስተዳደር አስመልክቶ የቀረቡት ችግሮች በሚቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ በጥልቀት ተጠንቶ ርምጃ እንደሚወሰድ ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: