አንድ የኮሌጁ ደቀ መዝሙር ከዐርብ ጀምሮ በእስር ላይ ነው

 •  ልኡኩ ከኮሌጁ አስተዳደር ወግኗል በሚል እየተተቸ ነው
 • አምስት ደቀ መዛሙርት በረኀብ አድማው ተጎድተዋል
 • የደቀ መዛሙርቱ ዕለታዊ ምግብ ዳቦና ሙዝ ኾኗል

በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተጀመረው የደቀ መዛሙርት ተቃውሞ እንደቀጠለ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት÷ አምስት ደቀ መዛሙርት በረኀብ አድማው መጎዳታቸውንና አንድ ደቀ መዝሙር ደግሞ በእስር ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት ትምህርት በማቋረጥ የተጀመረውና ዘግይቶ በረኀብ አድማ በተጠናከረው የቀኑ መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርት ተቃውሞ÷ ሦስት የሁለተኛ ዓመት (ዲ/ን ገብረ እግዚአብሔር፣ ዲ/ን በኀይሉ እና ዲ/ን ጥላሁን)፣ አንድ የአራተኛ ዓመት (ዲ/ን ኤልያስ)፣ አንድ የአምስተኛ ዓመት (አባ ኢያሱ ሰብስቤ) ደቀ መዛሙርት ተጎድተው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጧል፡፡ ከአምስቱ ደቀ መዛሙርት አራቱ የሕክምና ርዳታ አግኝተው ወደ ኮሌጁ የተመለሱ ሲኾን አምስተኛው ደግሞ በጣም በመጎዳታቸው ከሕክምና ርዳታው በኋላ ወደ ቤተሰብ መመለሳቸው ተዘግቧል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በቀን አንዴ የሚቀምሱት ከውጭ የሚገዙትን ዳቦና ሙዝ ሲኾን ከምግብ ተከልክለው በመቆየታቸው ሳቢያ ብዙዎች ከፍተኛ ድካም እንደሚታይባቸው ተገልጧል፡፡

በኮሌጁ ተባብሰው ለሚታዩት አካዳሚያዊና አስተዳደራዊ ችግሮች የኮሌጁን ሁለት ሓላፊዎች ቀዳሚ ተጠያቂ በማድረግ ከሥልጣን እንዲነሡ የሚጠይቁት ደቀ መዛሙርቱ÷ ዲ/ን ኀይለ ጽዮን መንግሥት የተባለ የአምስተኛ ዓመት ደቀ መዝሙር ካለፈው ሳምንት ዓርብ ተሲዓት ጀምሮ በፖሊስ ከተወሰደ በኋላ በእስር ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፤ ወደ  አራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 04 ፖሊስ ጣቢያ የተወሰደውና በሰሞኑ የተቃውሞ መድረኮች ርቱዕና ብርቱ ተናጋሪ ነበር የተባለው ዲ/ን ኀይለ ጽዮን፣ ከሌሎች ተለይቶ ለእስር የተዳረገው ‹‹ተማሪዎቹን ለተቃውሞ አነሣሥተሃል›› በሚል መኾኑን ደቀ መዛሙርቱ ገልጸው፣ በዛሬው ዕለት ከቀትር በኋላ ፍ/ቤት ቀርቦ በዋስ ይፈታል ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱና ከኮሌጁ አስተዳደር ሓላፊዎች ተውጣጥቶ ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋራ ለሦስት ጊዜ ያህል መወያየታቸውን የገለጹት ደቀ መዛሙርቱ፣ ኮሚቴው ችግራቸውን በትክክለኛ ገጽታው ተመልክቶ ከመፍታት ይልቅ ‹‹ሽምግልና›› መምረጡን በመጥቀስ ይነቅፉታል፡፡ የችግሩ ሥር መሠረት ለኮሌጁ ሓላፊዎች ሽፋን የሚሰጠውና ከሓላፊዎቹ ጋራ የሚመቻቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ማኔጅመንት ኮሚቴ ነው የሚሉት እኒህ ደቀ መዛሙርት÷ ከዚህ ቀደም ያለጥያቄ ከቦታቸው የተነሡና የተዘዋወሩ ሓላፊዎችን በማስታወስ፣ አሁን ከቦታቸው ገለል እንዲሉ የጠቀሷቸው ሓላፊዎች ከሚፈጥሩት ከፍተኛ ችግር አንጻር ከሓላፊነታቸው ማንሣት ወይ ማዘዋወር አስተዳደሩ ሊቸገርበት የሚገባ እንዳልነበር ያስረዳሉ፡፡

ሌሎችም ኮሚቴው ‹‹ግቡና ተማሩ፤ ችግሩ እየተማራችኹ ይፈታል›› እያለ ከቢሮው (አስተዳደሩ) ጋራ ከመወገን በቀር ችግሮቹን መዳኘትና መፍትሔ ማምጣት እንዳልቻለ ጠንከር አድርገው ይተቹታል፡፡

‹‹ወንድማችን ይፈታ፤ ሁለቱ ሓላፊዎች ገለል ይደረጉ፤ ኮሚቴ ተቋቁሞ ችግራችን ይጠና፣ ይጣራ፤ ይህ ሲሆን ነው ትምህርታችንን የምንቀጥለው›› የሚሉት ደቀ መዛሙርቱ ዛሬ፣ ለተከታታይ ዐሥራ አምስተኛ ቀን ተቃውሟቸው እንደቀጠሉ መኾኑ ታውቋል፡፡

*ይህ ዜና ከተዘገበ በኋላ ዘግይቶ የደረሰን መረጃ እንደሚጠቁመው ለአምስት ቀናት በእስር ላይ የቆየው ዲ/ን ኀይለ ጽዮን መንግሥ  ዛሬ ከቀትር በኋላ ከእስር ተፈቷል፡፡

Advertisements

4 thoughts on “አንድ የኮሌጁ ደቀ መዝሙር ከዐርብ ጀምሮ በእስር ላይ ነው

 1. Anonymous March 27, 2013 at 12:16 pm Reply

  እነዚህ ናቸው ነገ ተመርቀው ስለ ፆም የሚያስተምሩን እግዚኦ መሀረነ

 2. Anonymous March 28, 2013 at 1:04 am Reply

  ቱልቱላ ምን ለማለት ፈልገህ ነው?ሰው መብቱ ሲደፈር መጠየቅ የለበትም ?

 3. Mebrat March 28, 2013 at 10:37 am Reply

  እንደ ፌስ ቡክ እዚህም ‘like’ ቢኖር ኖሮ ሁለተኛ ላይ አስተያየት ለሰጠው ሰው like አደርግለት ነበር:: የተማሪዎቹ ጥያቄ ምግብ አይደለም:: በቤተክርስቲያን ስም የአስተዳድሩን ቦታ ይዘው ግን የቤተክርስቲያኒቱን ሃብት ንብረት በህገ ወጥ መንገድ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ ሰዎችን ነው እንዲወገዱ የጠየቁት:: ጥያቄያቸው በየትኛውም መስፈርት ስህተት ሊሆን አይችልም ለሃገር ቀና አመለካከት ላለው ሰው:: ሐይማኖታችን ደግሞ ከየትኛውም ተቋም ይልቅ እንዲህ አይነት ወንጀሎችን አጥብቃ ትቃውማለች:: ስለዚህ ተማሪዎች እንደዚህ አይነት ወንጀሎችን እያዩ ዝም ቢሉ ነበር የሚያስወቅሳቸው:: አሁን ግን ህዝበ ክርስቲያኑ በሙሉ እንዲሁም ቅዱስ ሲኖዶስ ከነሱ ጋ ሊሆን ይገባል::

 4. Anonymous April 13, 2013 at 9:41 am Reply

  tikikl bilehal antes mejemeria lay letsafkew gin tifatin eyayu zim bilu eko endante beselam menor yichilu neber! serko tasere meseleh ende !

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: