አስመራጭ ኮሚቴው አጠቃላይ የሥራ ሪፖርቱን ለቅ/ሲኖዶሱ አቀረበ

 • የምርጫው ሂደት በይፋ ተዘጋ
 • ‹‹ቅ/ሲኖዶሱ ያወጣውን ሕገ ደንብ መፈጸምና ማስፈጸም የማይችል ከኾነ ቤተ ክርስቲያን ለከፋ ፈተና ትጋለጣለች›› /የምእመን ተወካይ/
 • ‹‹ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት መሠረት የተደረገው ሁሉ ትክክለኛ ነው›› /ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ/

ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ በመኾን በትላንትናው ዕለት ሥርዐተ ሢመት የተፈጸመላቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ÷ ቅዱስ ሲኖዶሱን በርእሰ መንበርነት የመሩበትን የመጀመሪያ ስብሰባ በዛሬው ዕለት በማካሄድ አገልግሎታቸውን ጀምረዋል፡፡

በአዲሱ ፓትርያሪክ ርእሰ መንበርነት ዛሬ፣ የካቲት 25 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀትር በኋላ የመጀመሪያ ስብሰባውን ያካሄደው ቅዱስ ሲኖዶሱ÷ የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ አጠቃላይ የሥራ ሂደቱን በሚመለከት ያቀረበውን የጽሑፍ ዘገባ አዳምጧል፤ ኮሚቴው የምርጫውን ሂደት ከዘገበበት የጽሑፍ ሪፖርቱ በተጨማሪ ምርጫውን ያከናወነባቸውን ሰነዶች ለቅዱስ ሲኖዶሱ ማስረከቡ ተገልጧል፡፡ የጽሑፍ ዘገባው በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ አንቀጽ 12/1 መሠረት÷ የኮሚቴው ሥራ መጠናቀቁንና የምርጫው ሂደት በይፋ መዘጋቱን የሚያስታውቅ እንደኾነ ተገልጧል፡፡

አብዛኞቹ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት በዚህ ስብሰባ የቀረበው የአስመራጭ ኮሚቴው ሪፖርት÷ የምርጫውን ሂደት፣ የመራጮችን ተሳትፎና ለምርጫው የወጣውን ወጪ እንዲሁም የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ ተፈጻሚ መኾን አለመኾኑን መነሻ ባደረጉ የተለያዩ ጥያቄዎች መፈተኑን የዜናው ምንጮች አስረድተዋል፡፡ ከ13 የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት መካከል ሦስቱ ከምእመናን የተወከሉ ሲኾኑ በዛሬው ስብሰባ የተገኙት አንዱ ብቻ ናቸው፡፡

እርሳቸውም በሰጡት የቃል ማብራሪያ÷ ቅ/ሲኖዶሱ ያወጣውን ሕገ ደንብ መፈጸምና ማስፈጸም የማይችል ከኾነ ቤተ ክርስቲያን ለከፋ ፈተና እንደምትጋለጥ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው በብዙ የደከመው ድካም ውጤት አስገኝቷል ብለው እንደማያምኑ የተናገሩት ምእመኑ÷ ከመራጮች እንግልትና ከገንዘብ ወጭ ይልቅ ቅዱስ ሲኖዶሱ በዝግ ስብሰባ የሚሻለውንና ወቅቱን የዋጀውን አባት መርጦ ቢሠይም ደግና የዋህ የኾነውን ሕዝብ ተቀባይነት ያገኛል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ስለመናገራቸው ተዘግቧል፡፡Asmerach Com Meetings

የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል፤ የምርጫው ሂደት ቀጥተኛና በሕገ ደንቡ መሠረት የተፈጸመ መኾኑንም አስረድተዋል፡፡ በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ÷ ‹‹ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት መሠረት የተደረገው ሁሉ ትክክለኛ ነው፤›› ነው ብለዋል፡፡ ይኹንና እንደ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ሁሉ ሪፖርቱን በመደገፍ አስተያየት ከሰጡ ጥቂት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በቀር ብዙዎቹ ዝምታን መርጠዋል ተብሏል፡፡

ከሁሉም በተለየ መልኩ የኮሚቴውን ሪፖርት ለመስማት እንኳ ያልታገሡት የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ስብሰባውን አቋርጠው እንደወጡ ተመልክቷል፡፡ ብፁዕነታቸው ስብሰባውን አቋርጠው ከመውጣታቸው በፊት ባሰሙት ቃል÷ ‹‹ሲኖዶሱንና ሲኖዶሱን፤ ሲኖዶሱንና ቤተ ክርስቲያንን ማእከል አድርጎ ከግለሰብ እና ከሌሎች አካላት ጫና ነጻ ኾኖ መሥራት ካልተቻለ ችግሩ ይቀጥላል፤ የከፋም እንዳይኾን ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት ማድረግና እንደ አባትም መጸለይ አለብን፤›› ብለዋል፡፡

በመጪው ግንቦት የዋና ጸሐፊነት ሓላፊነታቸው የሚያበቃው የብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል አስተያየትና ስብሰባውን አቋርጦ መውጣት÷ በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ አንቀጽ 10/1-3÷ ስለምርጫ የሚነሡ ቅሬታዎችን በተመለከተ በምርጫው ላይ ቅሬታ እንዳላቸው የገለጹበት መንገድ እንደኾነ የዜናው ምንጮች ቢያምኑም፣ በሕገ ደንቡ በተጠቀሰው ቀነ ገደብና የአቀራረብ ደረጃ ባለመቅረቡ አንዳች ፋይዳ/ውጤት ይኖረዋል ተብሎ እንደማይገመት ያላቸውን ጥርጣሬ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ይኸውም ቅዱስ ሲኖዶሱ የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ያቀረበውን ሪፖርትና ያስረከባቸውን የምርጫ ሰነዶች ተቀብሎ በቅዱስ ሲኖዶስ መዝገብ ቤት እንዲቀመጡ መወሰኑ ነው፤ ውሳኔውን እንዲያስፈጽሙም ስብሰባውን አቋርጠው በወጡት በዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ምትክ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ በምርጫ ሕገ ደንቡ አንቀጽ 12/1 መሠረት ቅዱስ ሲኖዶሱ የኮሚቴውን ሪፖርት እንደተቀበለው ሲረጋገጥ የምርጫው ሂደት በይፋ እንደሚዘጋ ተደንግጓል፡

በበዓለ ሢመቱ ቀን በኅትመት የተሠራጨውን የአስመራጭ ኮሚቴ ሪፖርት ከዚህ በታች ይመልከቱ፡፡Report 001Report 0002Report 003Report 004Report 005Report 006Report 007Report 008

Advertisements

One thought on “አስመራጭ ኮሚቴው አጠቃላይ የሥራ ሪፖርቱን ለቅ/ሲኖዶሱ አቀረበ

 1. Anonymous March 6, 2013 at 6:54 am Reply

  እኔ የሚገርመኝ አቡነ ማትያስ መሾማቸው አይደለም እንዲያውም ካሉት አባቶች በአቋም ሊሻሉ ይችሉ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም አቡነ ጳውሎስን ሁሉም ፈርቶ አባ ገነን ሆነው ቤተክርስቲያኗን ሲመዘብሩና ሲያስመዘብሩ ዝም ጭጪ ሲሉ እርሳቸው በሥርዓተ ቤተክርስቲያን፣ በአምባ ገነንነታቸው፣ በገንዘብ ብክነት፣ በሃይማኖታቸው ወዘተ ይናገሩ ይጣሉ የነበሩት እርሳቸውና እርሳቸው ብቻ ነበሩ፡፡ ይህም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ናቸው በእኔ አመለካከት ጀግና እላቸው ነበር፡፡ አሁን ካሉት ከዓላማቸው ፈሪ የሆኑ፣ ለምን ጳጳስ እንደሆኑ ዓላማቸውን ያልተረዱ፣ ግራና ቀኛቸውን ሳያውቁ የሚወዘወዙ፣ እንደ ቦይ ውሃ በነዷቸው የሚነዱ፣ ለደቂቃ ወጥ አቋም የሌላቸው፣ እንደ ሕጻን ልጅ በየደቂቃው የሚያኮርፉ፣ ሁሉ ጌዜ ብሶት የሚያወሩ ብቻ በተሰበሰቡበት ከእርሳቸው የተሻለ አለ ብየ አላምንም፡፡ ለዚህ ነው ዝም ብለው መርጠው ዝም ብለው የሾሙት፡፡
  እኔ የገረመኝ መሾማቸው ሳይሆን ለቤተክርስቲያን ጠበቃ ነኝ፣ ከእኔ በላይ ለአሳር፣ ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ የሚለው፣ ዘመናዊ አሥተዳደርና ለውጥ በቤተክርስቲያን አመጣለሁ ብሎ ቀን ከሌሊት ደፋ ቀና የሚለው ሥውር የመንግሥት አሥተዳደርን በመደገፍ የመንግሥትን፣ የእነ ንቡረ እድ ኤልያስና የእነ አባ ሠረቀ ባለሟልና ተዋናይ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹በልጅነቱ የመነኮሰ ሰልሞ ይሞታል እንደሚባለው›› ማኅበሩ በትውልድ ተወቃሽ፣ በየዋሃንና በቅንነት ትክክለኛ ዓላማ ያለው መስሎአቸው ለሚከተሉት ኣባላቶቹ አስነዋሪ፣ በየዋኅነት ገንዘባቸውን ለሚሰጡ ምዕመናን አሳፋ ሥራ የፈጸመበት፣ እውነተኛ መሥሎ ሥውር ደባውን በቤተክርስቲያን ያሴረበት፣ የክፋትና የተንኮል እጁን የጫነበት ወቅት መሆኑ ትዝብትና ጥርጣሬ ውስጥ፣ ሃይማኖታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ርምጃ የሚሔድበት መሆኑን ፍንትው አድርጎ አሳይቷል፡፡ ለመንግሥትም ታማኝ አገልጋይ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
  የእውነት አምላክ፣ የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን አባቶቻችን ረድኤትና በረከት፣ በየገዳማቱ፣ በየአድባራቱ፣ በየጫካው፣ በየ ትምህርት ቤቱ ያሉ አባቶቻችን ጸሎት ቤተክርስቲያንን ምዕመናንን ይጠብቅልን አሜን፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን ይፋረድልን፡፡
  ዛሬም ሆነ ወደፊት ቀጥተኛ የሃይማት አባት እግዚአብሔር እንዲሰጠን ገዳማት ውስጥ በዓት አጽንተው ለተቀመጡ አባቶች ማሳሰብ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: