ፓትርያሪኩ የዕርቀ ሰላም ጥረቱ እንደሚቀጥል አሳሰቡ

The 6th Patriarch Enthronmentየብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያሪክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሥርዐተ ሢመት ዛሬ፣ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡ ለበዓለ ሢመቱ አፈጻጸም በወጣው መርሐ ግብር መሠረት በካቴድራሉ ተገኝተው የቅዱስነታቸውን ሥርዐተ ሢመትና ሥርዐተ ጸሎት ያከናወኑት በሹመት ቀደምት የኾኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት÷ ዐቃቤ መንበሩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እና ብፁዕ አቡነ ማትያስ ዘካናዳ ናቸው፤ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩም ቃለ መሐላ ፈጽመዋል፤ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ጋራ ጸሎተ ቅዳሴውን (ቅዳሴ ሐዋርያት) መርተዋል፡፡

‹‹ተኣዝዞ ከመሥዋዕትነት ይበልጣል›› ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ሢመተ ፕትርክናውን እንደሚቀበሉት አስታውቀዋል ፡፡ ቅዱስነታቸው አያይዘውም ‹‹አቅሜ በፈቀደው ለቤተ ክርስቲያኔ እታዘዛለኹ፤ አልችልም ማለት እችል ነበር፤ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥሪ አልቀበልም ማለት መሥዋዕትነትን መሸሽ ነው፤ ሢመቱ ለክብርና ለልዕልና እንዳልኾነ ለእኔም በሚገባ ይገባኛል፤ ሁላችኹም እንደምትረዱልኝም ተስፋ አደርጋለኹ፤›› ብለዋል፡፡

ቅዱስነታቸው የዕርቀ ሰላም ሂደቱን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልአክት÷ ‹‹ለረጅም ጊዜ ሲያወዛግብ የቆየው የዕርቅና ሰላም ሂደት ለጊዜው ባይሳካም በቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ጥረቱ ይቀጥላል፤›› በማለት አመልክተዋል፡፡

ለበዓለ ሢመቱ በተሰራጨው የብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ማትያስ አጭር የሕይወት ታሪክ መጽሔት፤ ዕርቀ ሰላምን መመሥረት በሚል ርእስ በቀረበው ጸሑፍ የሚከተለው ቃል ሰፍሯል፡፡

ብፁዕነታቸው በውጭ ዓለም የሚኖረውንና በተለያዩ ምክንያቶች ከአንድነት የራቀውን ሕዝበ ክርስቲያን ወደ አንድነት ለማምጣት ያደረጉት አስተዋፅኦ ሌላ ተጠቃሽ ተግባቸው ነበር፡፡ ዕርቀ ሰላምን ለማድረግ የትኛውም አካል ባላበበት ዘመን ብፁዕነታቸው ስለ ዕርቀ ሰላም ያስቡም ይደክሙም ነበር፡፡

ለዚህም ተግባር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አትላንታ ጆርጂያ በማምራት የውጭው ሲኖዶስ አባላት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን እንዲሁም ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን አነጋግረዋል፡፡ ከዚህም ንግግር በኋላ ለኢትዮጵያ ሲኖዶስ መልእክት በመላክ ዕርቀ ሰላም እንዲጀመር መሠረት ጥለዋል፡፡ ይ በጵጵስና ዘመናቸው የጀመሩ ሁለቱን ሲኖዶስ አንድ የማድረግ እንቅስቃሴ የሚቀጥል ይኾናል፡፡

የበዓለ ሢመቱ ሙሉ ዘገባው በተከታይ ይቀርባል                               

Advertisements

2 thoughts on “ፓትርያሪኩ የዕርቀ ሰላም ጥረቱ እንደሚቀጥል አሳሰቡ

 1. Gebeyehu March 4, 2013 at 1:53 am Reply

  ተመስገን አምላካችን !!!ተመስገን አምላካችን !!!

 2. Anonymous March 6, 2013 at 6:58 am Reply

  እኔ የሚገርመኝ አቡነ ማትያስ መሾማቸው አይደለም እንዲያውም ካሉት አባቶች በአቋም ሊሻሉ ይችሉ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም አቡነ ጳውሎስን ሁሉም ፈርቶ አባ ገነን ሆነው ቤተክርስቲያኗን ሲመዘብሩና ሲያስመዘብሩ ዝም ጭጪ ሲሉ እርሳቸው በሥርዓተ ቤተክርስቲያን፣ በአምባ ገነንነታቸው፣ በገንዘብ ብክነት፣ በሃይማኖታቸው ወዘተ ይናገሩ ይጣሉ የነበሩት እርሳቸውና እርሳቸው ብቻ ነበሩ፡፡ ይህም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ናቸው በእኔ አመለካከት ጀግና እላቸው ነበር፡፡ አሁን ካሉት ከዓላማቸው ፈሪ የሆኑ፣ ለምን ጳጳስ እንደሆኑ ዓላማቸውን ያልተረዱ፣ ግራና ቀኛቸውን ሳያውቁ የሚወዘወዙ፣ እንደ ቦይ ውሃ በነዷቸው የሚነዱ፣ ለደቂቃ ወጥ አቋም የሌላቸው፣ እንደ ሕጻን ልጅ በየደቂቃው የሚያኮርፉ፣ ሁሉ ጌዜ ብሶት የሚያወሩ ብቻ በተሰበሰቡበት ከእርሳቸው የተሻለ አለ ብየ አላምንም፡፡ ለዚህ ነው ዝም ብለው መርጠው ዝም ብለው የሾሙት፡፡
  እኔ የገረመኝ መሾማቸው ሳይሆን ለቤተክርስቲያን ጠበቃ ነኝ፣ ከእኔ በላይ ለአሳር፣ ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ የሚለው፣ ዘመናዊ አሥተዳደርና ለውጥ በቤተክርስቲያን አመጣለሁ ብሎ ቀን ከሌሊት ደፋ ቀና የሚለው ሥውር የመንግሥት አሥተዳደርን በመደገፍ የመንግሥትን፣ የእነ ንቡረ እድ ኤልያስና የእነ አባ ሠረቀ ባለሟልና ተዋናይ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹በልጅነቱ የመነኮሰ ሰልሞ ይሞታል እንደሚባለው›› ማኅበሩ በትውልድ ተወቃሽ፣ በየዋሃንና በቅንነት ትክክለኛ ዓላማ ያለው መስሎአቸው ለሚከተሉት ኣባላቶቹ አስነዋሪ፣ በየዋኅነት ገንዘባቸውን ለሚሰጡ ምዕመናን አሳፋ ሥራ የፈጸመበት፣ እውነተኛ መሥሎ ሥውር ደባውን በቤተክርስቲያን ያሴረበት፣ የክፋትና የተንኮል እጁን የጫነበት ወቅት መሆኑ ትዝብትና ጥርጣሬ ውስጥ፣ ሃይማኖታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ርምጃ የሚሔድበት መሆኑን ፍንትው አድርጎ አሳይቷል፡፡ ለመንግሥትም ታማኝ አገልጋይ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
  የእውነት አምላክ፣ የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን አባቶቻችን ረድኤትና በረከት፣ በየገዳማቱ፣ በየአድባራቱ፣ በየጫካው፣ በየ ትምህርት ቤቱ ያሉ አባቶቻችን ጸሎት ቤተክርስቲያንን ምዕመናንን ይጠብቅልን አሜን፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን ይፋረድልን፡፡
  ዛሬም ሆነ ወደፊት ቀጥተኛ የሃይማት አባት እግዚአብሔር እንዲሰጠን ገዳማት ውስጥ በዓት አጽንተው ለተቀመጡ አባቶች ማሳሰብ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: