የአዲሱ ፓትርያሪክ ፈተና እና ተስፋ

ምንጭ፡- አዲስ ጉዳይ መጽሔት፤ ቅጽ ሰባት ቁጥር 153፤ የካቲት 2005 ዓ.ም

 • የቅ/ሲኖዶሱን የመወሰን አቅም ማጠንከር፤
 • የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ከግለሰቦች ይኹን ከመንግሥት ተጽዕኖ ማጥራት፤
 • ለምእመናን ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት፤
 • የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት ከሙስናና ከግል ጥቅመኞች መጠበቅ፤
 • ቁርሾዎችንና ጠቦችን በማስታረቅ መፍታት፤
 • አንድነት መፍጠርንዲሁም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ውስጥና በውጭ ያላትን ክብርና ተሰሚነት ጠብቃ እንድትቀጥል ማድረግ፡፡

  Untitled-3

  ተመራጩ – ፮ኛ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ
  (ፎቶ አዲስ ጉዳይ)

ባለፉት ኻያ ዓመታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች በብዙ ፈተና ውስጥ ያለፉበት ወቅት መኾኑን ለጉዳዩ ቅርብ የኾኑ ወገኖች ይመሰክራሉ፡፡ በአስተዳደር ሽኩቻዎች የተፈጠረው ጭቅጭቅ በብዙዎች ዘንድ ቂም ከመያያዝ እስከ መጋደል አድርሷል፡፡

የአዲሱ ፓትርያሪክ ፈተና

ከሁሉም በላይ አዲሱ ፓትርያሪክ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት ቅድሚያ በመስጠት በሀገር ውስጥና በውጭ የተፈጠረውን የአባቶች ችግር መፍታት አፍጥጦ የሚጠብቃቸው ፈተና ነው ይላሉ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት እንድትከፈል፣ በብሔር ላይ የተመሠረተ ልዩነት እስከ ማድረግ ያደረሰው ዋነኛ ጉዳይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ራስ የኾኑ አባቶች አለማስማማት መኾኑን የሚገልጹት እኒህ ወገኖች÷ የብፁዓን አባቶች ግለሰብን ሳይኾን እምነትን ማእከል ወዳደረገ አንድ የጋራ አስተሳሰብና ራእይ መምጣት የምእመናኑን መቀራረብ ለመፍጠር ጊዜ አይወስድበትም፡፡ ‹‹አዲሱ ፓትርያሪክ ይህን ዘመናት የተሻገረ ቁርሾ በመፍታት አንድነትን ማምጣት የሚያስፈልግበት ወሳኝ ወቅት ላይ ወደ መንበሩ መጥተዋል፤›› የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች ከዚህ አንጻር የሚጠብቃቸው ሥራ ቀላል ባይኾንም በጥረት ከሄዱበት ግን የማይሳካ አይደለም ይላሉ፡፡

ሃይማኖት ዋነኛ ማጠንጠኛው እምነት እንጂ አስተዳደር ባለመኾኑ በዚህ ገዥ የጋራ ጉዳይ ላይ ተወያይቶ ስምምነት ላይ በመድረስ ‹‹ሁለተኛ የኾነውን የአስተዳደር ችግር መፍታት አይከብድም›› የሚሉ ምእመናን በበኩላቸው አዲሱ ፓትርያሪክ በዚህ በኩል ጠንክረው ከተጓዙ የብዙኀኑን አማኝ ድጋፍ ማግኘት አያዳግታቸውም ይላሉ፡፡

ሌላው የአዲሱ ፓትርያሪክ ፈተና÷ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ከፖሊቲካው ነጻ ማድረግ ነው፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመን ሕዝበ ክርስቲያኑ በጳጳሱ ላይ የመረረ ተቃውሞ ማሰማት ጀምሮ ነበር፡፡ አንድ የሃይማኖት አባት ከቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አልፎ በመንግሥት የዕለት ከዕለት ሥራዎች ሁሉ ውስጥ እየገባ ለመንግሥት የሚወግን ንግግርና ተሳትፎ ማድረግ የሃይማኖትና መንግሥት መለያየት ድንጋጌን የሚፃረር ነው ይላሉ ታዛቢዎች፡፡

ይህ አካሄድ መንግሥት በእምነቱ ላይ ፈትፋችና ወሳኝ እንዲኾን በር ይከፍትለታል የሚሉ ወገኖች በተግባር የታየውም ይኸው ነበር ይላሉ፡፡ አቡነ ጳውሎስ በሃይማኖታዊ በዓላት ላይ ሳይቀር ንግግር ሲያደርጉ ሕዝብ እየጮኸ አላዳምጥም ያለበት ወቅት ተስተውሏል፡፡ ይህ የምእመናኑና የብፁዓን አባቶች መለያየት ሃይማኖቱን የሚጥልና ለአንድነቱም ስጋት ነው የሚሉ ምእመናን አዲሱ ፓትርያሪክ ከዚህ ብዙ መማር ይጠበቅባቸዋል በማለት ይመክራሉ፡፡

ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉት እንደኾነ የተናገሩትና ለአዲስ ጉዳይ አስተያየታቸውን የሰጡ የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድ አባት እንደሚሉት÷ ዘመን የተሻገረን ችግር በአንድ ጀንበር መፍታት ባይቻልም አዲሱ ፓትርያሪክ ሁለቱን ወገኖች ለማቀራረብ ከአሁኑ ጥረት ቢጀምሩ የተሻለ ውጤት ማግኘት የማይችሉበት ምክንያት የለም፡፡

የአዲሱ ፓትርያሪክ ፈተና ናቸው ከሚባሉ ሌሎች ጉዳዮች ውስጥ በዘረኝነትና ጎሰኝነት ያለውን መከፋፈል አስወግዶ ሕዝበ ክርስቲያኑን ማቀራረብ ነው፡፡ ፓትርያሪኩ ራሳቸውን ከቀድሞዎቹ ፓትርያሪኮች አሉታዊ ዳና አሸሽተው በንጹሕ ልብ ሁሉንም ለማገልገል የተነሡ አባት ከኾኑ ያለምንም ችግር የተከፋፈለውን ምእመን በአንድ ጎጆ ለመሰብሰብ አይቸገሩም ይላሉ አስተያየት ሰጭዎች፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያኒቱ የቅርብ ሰዎች ምልከታ ሥር የሰደደውና ዘመናትን የተሻገረው በሀገር ውስጥና በውጭ ያለው የዘረኝነትና የብሔርተኝነት አስተሳሰብ እንዲቀየርና ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን በአንድ ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር እንዲጠለል ለማድረግ ያላሰለሰለ ሥራ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡

የአዲሱ ፓትርያሪክ ተስፋዎች

እኒህ ፈተናዎች እንዳሉ ኾነው አዲሱ ፓትርያሪክ ተስፋዎችም አሏቸው፡፡ በዘረኝነትና ብሔርተኝነት ላይ የተመሠረተው ክፍፍል በአቡነ ጳውሎስ ጊዜ የተንሰራፋ እንደመኾኑ አሁን ያንን ለማከም መልካም ጊዜ ነው ይላሉ የቀድሞዎቹ አስተያየት ሰጭዎች፤ ምክንያቱ ደግሞ አዲሱ ፓትርያሪክ ከጉዳዩ ጋራ ያላቸው ንኪኪ ይህ ነው ተብሎ የሚወራለት ባለመኾኑ ነው፡፡ ‹‹በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ አንድ ለማምጣትና መከፋፈሉን በሰላምና አንድነት ለመተካት የተሻለ ዕድል አላቸው፡፡ በርሳቸው ላይ ይህን አድርገዋል፤ ያን አድርገዋል ብሎ ቂም የያዘባቸው ባለመኖሩ በአውራሻቸው የተፈጠሩ ነገሮችን ለመፍታት ኹነኛ ሰው መኾን ይችላሉ፤ እንደገለልተኝታቸውም የሚሰማቸው ያገኛሉ፤›› ይላሉ አስተያየት ሰጭዎች፡፡

አዲስ ጉዳይ ያነጋገራቸው የቤተ ክርስቲያን አመራሮችና ምእመናን እንዳሉት ሕዝበ ክርስቲያኑና ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአዲሱ ፓትርያሪክ የሚጠብቁት ተቀዳሚ ተግባር፡-

 • የሲኖዶሱን የመወሰን አቅም ማጠንከር፤
 • ከግለሰቦች ይኹን ከመንግሥት ተጽዕኖ ማጥራት፤
 • ለምእመናን ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት፤
 • የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት ከሙስናና ከግል ጥቅመኞች መጠበቅ፤
 • ቁርሾዎችንና ጠቦችን በማስታረቅ መፍታት፤
 • አንድነት መፍጠር እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ውስጥና በውጭ ያላትን ክብርና ተሰሚነት ጠብቃ እንድትቀጥል ማድረግ ናቸው፡፡

ለዚህ ስኬት ደግሞ ይላሉ አስተያየት ሰጭዎቹ÷ ‹‹አዲሱ ፓትርያሪክ ራሳቸውን ለኅሊናቸውና ለሾማቸው እግዚአብሔር ማስገዛት ብቻ በቂያቸው ነው፡፡››Untitled-5

Advertisements

One thought on “የአዲሱ ፓትርያሪክ ፈተና እና ተስፋ

 1. Anonymous March 2, 2013 at 8:14 pm Reply

  egzeabhair yalfekedew alemawy mercha .egzeabhair yefrede.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: