የስድስተኛው ፓትርያሪክ በዓለ ሢመት ዝግጅት

 • ፓትርያሪኩ ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ
 • የኮፕቱ ፖፕ የማይገኙት በደብዳቤ አጻጻፍ ስሕተት ምክንያት ነው
 • ዐራተኛውን ፓትርያሪክና አብረዋቸው የሚገኙ አባቶችን የተመለከቱ ዝርዝር ሰነዶች የያዘ ኅትመት በበዓለ ሢመቱ ላይ ይሰራጫል

የስድስተኛው ፓትርያሪክ ሥርዐተ ሢመትና ሥርዐተ ጸሎት ነገ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም ይፈጸማል፡፡ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በሚፈጸመው የ፮ው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ በዓለ ሢመት አከባበር÷ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ለመላው ካህናትና ምእመናን ርእሰ አበው መኾናቸውን (የአባትነት ሓላፊነታቸውን)፣ መሠረተ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ያለባቸውን ሓላፊነት የተመለከተ ቃለ መሐላ እንደሚፈጽሙ ይጠበቃል፡፡Patriarch - Elect - Abune Matyas

በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ አንቀጽ 11/ለ/1 – 3 እንደተመለከተው÷ ፓትርያሪኩ ቃለ መሐላውን የሚፈጽመው በተሾመበት ዕለት በመንበረ ሐዋርያት ቆሞ በግራ እጁ አርዌ ብርት በቀኝ እጁ መስቀልና ወንጌል በመያዝ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ በካህናትና ምእመናን ፊት ድምፁን አሰምቶ በመናገር ነው፡፡ ቃለ መሐላውን የሚያስፈጽሙት ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩና በሹመት ቅድምና ያላቸው ሌሎች ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት መስቀል ይዘው ከፊት ለፊቱ በመቆም በአንድ ላይ ኾነው ነው፡፡

ፓትርያሪኩ የሚፈጽመው ቃለ መሐላ የሚከተለው ይዘት ይኖረዋል፡-

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላ

1.  እኔ አባ . . . . የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ኾኔ በመሾሜ የተጣለብኝ ሓላፊነት ያለምንም አድልዎና ተጽዕኖ ሁሉንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ ምእመናንና ምእመናት በእኩል አባትነት በቅንነትና በታማኝነት በፍቅርና በትሕትና አገለግላለኹ፡

2.  በምስጢረ ሥላሴና በምስጢረ ሥጋዌ ትምህርትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት፡-

ሀ) በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ልዩ ሦስትነት/በቅድስት ሥላሴ/ አንድ አምላክ መኾን/አሐዱ አምላክ/

ለ) የወልድ እግዚአብሔርን ከእመቤታችን መወለድና ሰው መኾን፤

ሐ) የመለኰትንና የትስብእትን ፍጹም ተዋሕዶና በዚህ የተገኘውን የድኅነተ ዓለም ትምህርተ ክርስትና በተኣምኖ በማስተማር የሚጠበቅብኝን ሁሉ እፈጽማለኹ፤ አስፈጽማለኹ፡፡

መ) በኒቂያ፣ 325 ዓ.ም በ318 ሊቃውንት የተወሰነውን፤ በቁስጥንጥንያ በ381 ዓ.ም በ150 ሊቃውንት የተወሰነውን፤ በኤፌሶን በ431 በ200 ሊቃውንት የተወሰነውን ትምህርተ ሃይማኖትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን አከብራለኹ፤ አስከብራለኹ፡፡ ለዚህም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ቃል እገባለኹ የሚል ይኾናል

3.  በመጨረሻም ጸሎተ ሃይማኖት ይደርሳል፡፡

ለበዓለ ሢመቱ አከባበር በወጣው መርሐ ግብር መሠረት ቅዳሜ፣ የካቲት 23 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ለእሑድ አጥቢያ ከሌሊቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ ሊቃውንቱና ካህናቱ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በመገኘት ለበዓሉ የሚገባውን ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ያድራሉ፡፡ ከሌሊቱ ፲ ሰዓት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ከብፁዕ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ጋራ በመኾን በካቴድራሉ እንደደረሱ ለሦስት ደቂቃ ያህል የካቴድራሉ የደወል ድምፅ ይሰማል፡፡ የካቴድራሉ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ጥንግ ድርብ የለበሱ ሊቃውንት ግራና ቀኝ ተሰልፈው ‹‹ብሩክ ዘይመጽእ›› የሚለውን መዝሙር እየዘመሩ ቅዱስነታቸውን ይቀበላሉ፡፡ የ፮ኛው ፓትርያሪክ ሥርዐተ ሢመትና ሥርዐተ ጸሎት ተከናውኖ ጸሎተ ኪዳን ይደርሳል፡፡ የቅዳሴው ሥነ ሥርዐት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ መሪነት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተራዳኢነት ከጠዋቱ ፲፪ ተጀምሮ ፪፡፴ ይፈጸማል፡፡

የዐውደ ምሕረቱ መርሐ ግብር ከጠዋቱ ፫ ላይ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ጸሎተ ቡራኬ ሲከፈት የደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ኃረይከ ወሤመከ የሚለውን አርያምና ብፁዕ ወቅዱስ አንተ የሚለውን አቡን ከቃኙ በኋላ ወአንተሰ ብፁዕ ወቅዱስ የሚለውን ግስ ለ፳ ደቂቃ ያህል ያሸበሽባሉ፡፡ የቆሜ አጫብር ሊቃውንት አንተ ውእቱ ዘላዕለ ኵሉ ሢመት የሚለውን ግስ ያቀርባሉ፡፡ ከአራቱም የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት የተውጣጡ የሰንበት ት/ቤት አባላት ያሬዳዊ መዝሙር ያቀርባሉ፡፡ ሦስት ሊቃውንት እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት መወድስ ቅኔ ያበረክታሉ፡፡

በበዓሉ ላይ የአኀት አብያተ ክርስቲያን መሪዎች መልእክት ያስተላልፋሉ፤ ለዚህም የግብጽ  ኮፕት ኦርቶዶክስ  ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ቢሾይ፣ የሕንድ ኦርቶዶክስ  መንበረ ቶማስ ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ የአርመንና  የሶርያ  ሊቃነ  ጳጳሳት በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን 118 ፖፕ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ በበዓለ ሢመቱ ላይ ሊገኙ ይችሉ እንደነበር የተናገሩት የቤተ ክርስቲያኒቱ ምንጮች÷ ይኹንና ከበዓል አከባበር ኮሚቴው የተጻፈው ደብዳቤ ‹‹ተወካይ ላኩ›› ከሚል በቀር ፕሮቶኮሉ በሚያዝዘው መሠረት በፖፑ አድራሻ ባለመጻፉ በምርጫው ለመሳተፍ የመጡት ልኡካን በበዓለ ሢመቱ ላይ እንዲገኙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ፣ የኢፌዴሪ መንግሥት ተወካይ፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያን ም/ቤት እና የአፍሪቃ አብያተ ክርስቲያን ም/ቤት ተወካዮች በበዓለ ሢመቱ ላይ መልእክት እንዲያስተላልፉ መርሐ ግብር ተይዞላቸዋል፡፡ የፓርላማውን አፈ ጉባኤና የፕሬዝዳንቱን ተወካይ ጨምሮ በርካታ ሚኒስትሮች፣ አምባሰደሮች፣ የክብር እንግዶችና ብዙኀን መገናኛ ዘጋቢዎች በበዓሉ ላይ እንደሚገኙ ተገልጧል፡፡

የዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክነት ሓላፊነታቸውን በ፮ው ፓትርያሪክ በዓለ ሢመት በማጠናቀቅ የሚያስረክቡት የአርሲ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ በመጪው ግንቦት ወር የዋና ሥራ አስኪያጅነት ሥልጣናቸው የሚያበቃው የኢሉባቦርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በዓሉን በሚመለከት መልእክት እንደሚያስተላልፉ ይጠበቃል፡፡ በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ በሚሰጡት ትምህርተ ወንጌል፣ ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ የበዓለ ሢመቱ መርሐ ግብር ፍጻሜ እንደሚኾን ከወጣው ፕሮግራም ለመረዳት ተችሏል፡፡

የፓትርያሪክ ምርጫውን ለማስፈጸም የተቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ አንድ ንኡስ ክፍል የነበረው የሎጅስትክ ንኡስ ክፍል የበዓለ ሢመቱን ዝግጅት በዋናነት እያስተባበረ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡ የንኡስ ክፍሉ አባላት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት እና በዋናነት ከማኅበረ ቅዱሳን አባላት የተውጣጣ የቴክኒክ ቡድን በጋራ የሚገኙበት ነው፡፡ ዛሬ ከቀትር በኋላ በጽርሐ መንበረ ፓትርያሪኩ የሚገኘውንና የቀድሞው ፓትርያሪክ ሲገለገሉበት የነበሩበትን መኖሪያና የሥራ ቦታ ለተሿሚው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ የማሰናዳት ሥራ ሲከናወን አምሽቷል፡፡ የደኅንነት ጥበቃውና የፕሮቶኮል ጓዙም ለፓትርያሪክ በሚተካከል ወግና ሥርዐት እንዲጀምር ኾኗል፡፡

በሌላ በኩል ዐራተኛውን ፓትርያሪክና አብረዋቸው በስደት (በውጭ) የሚገኙ አባቶችን የተመለከቱ ዝርዝር ሰነዶች (ደብዳቤዎችና ቃለ ጉባኤዎች) የያዘ ኅትመት በበዓለ ሢመቱ ላይ እንደሚሰራጭ ተመልክቷል፡፡ የዐራተኛውን ፓትርያሪክ አሿሿም፣ ከደርግ/ኢሕዴሪ መንግሥት ጋራ ነበራቸው ስለሚለው የ‹‹ኢሠፓ አባልነት›› ግንኙነት፣ ከመንበረ ፕትርክናው ለመውረድ አቅርበውት ነበር የተባለውን ጥያቄ፣ ጥያቄውን ተከትሎ በወቅቱ የነበረው ቅዱስ ሲኖዶስ አካሂዶታል የተባለውን ማጣራትና የጥንቃቄ ርምጃ፣ ከሀገር ከወጡት ሊቃነ ጳጳሳት መካከል እርሳቸውን ከመንበረ ፓትርያሪኩ ለማስወጣት ጥረት ስላደረጉ አባቶች፣ በመጨረሻም ዐራተኛው ፓትርያሪክ ከአገር ስለወጡበት ኹኔታና አምስተኛውን ፓትርያሪክ ለመሾም ስ ለ ተደረሰበት ውሳኔ (በፓትርያሪክ ላይ ፓትርያሪክ እንዳልተሾመ) ፣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ስለ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የኤርትራ ጉብኝት (በራሳቸው ፈቃድ እንጂ ሲኖዶሱን ወክለው እንዳልኾነ) በጻፉት ደብዳቤ ‹‹፪ቱ አብያተ ክርስቲያናት›› ስለማለታቸው በሰነድ አስደግፎ ያስረዳል – ነገ በበዓለ ሢመቱ ላይ የሚሰራጨው ባለ 52 ገጽ ኅትመት!!

የኅትመቱ ሥርጭት ለሰላም የተደረጉትን ጥረቶች በማስረጃና ትንተና አስደግፎ በመላው ዓለም ለሚገኘው ምእመን በሁሉም የመገናኛ አውታሮች ለማስረዳት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት የተፈጸመ እንደኾነ ተገልጧል፡፡ የውሳኔው አፈጻጸም የስደት ሲኖዶስ ያቋቋሙ አባቶች በቤተ ክርስቲያኒቱ ስምና ዓርማ እንዳይጠቀሙ ክትትል ማድረግንና በሕግ አገባብ መፍትሔ ማስገኘትን እንደሚያካትት በሰነዱ ላይ ተመልክቷል፡፡ በሦስት ዙር የተሞከረውን የዕርቅና ሰላም ጉባኤ በማስቀጠል የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት ማረጋገጥ ከአዲሱ ፓትርያሪክ ዋነኛ ተግዳሮቶች መካከል ቀዳሚው መኾኑ እየተገለጸ ባለበት ኹኔታ እንዲህ ዐይነቱ ኅትመት እንዲሰራጭ መደረጉ በዕውኑ አነጋጋሪ ነው፡፡

በተያያዘ ዜና በትላንትናው ዕለት ምሽት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልንና ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ከተመራጩ ፮ው ፓትርያሪክ ጋራ የማግባባቱ ጥረት ያለብዙ ችግር ለማከናወን መቻሉ ተነግሯል፡፡ በዋናነት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ያስተባበሩትና 12 ያህል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የተገኙበት የማግባባቱ ውይይት በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ቤት÷ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልንና ብፁዕ አቡነ አብርሃምን በማነጋገር ተጀምሮ ከብፁዕ አቡነ ማትያስ ጋራ በማገናኘት በመልካም የተፈጸመ መኾኑ ነው የተገለጸው፡፡

Advertisements

2 thoughts on “የስድስተኛው ፓትርያሪክ በዓለ ሢመት ዝግጅት

 1. teka March 3, 2013 at 6:26 am Reply

  wursi betemelekete bemircha denbu yalewus kere malet new

 2. Debasu March 3, 2013 at 6:43 am Reply

  ሐራዎች አንድ ግልጽ ልታደርጉት ይገባችሁ የነበረ ነገር ነበር፡፡ አቡነ ሳሙኤልንና አቡነ አብርሃምን ከአዲሱ ፓትርያርክ ጋ የማገናኘቱ ጉዳይ፤ አባ ሰላማ እንዳለው ሁለቱ ለቃነ ጳጳሳት አልቅሰው፣ እግር ሥርም ወድቀው፣ የምናደርገውን አናውቅም ያሉበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ክርክሩና ውይይቱ ሦስት ቀናትን የፈጀ፣ አባቶችን ብቻ ሳይሆን ምእመናንንም የጨመረ ነበር፡፡ እኔ ከምእመናኑ አንዱ ነኝ፡፡ ሁለቱም ያነሡት የወጣውን ሕግና የሕግ አፈጻጸሙን ነበር፡፡ በዚህ ላይ ችግር እንደነበር፣ አንዳንዱ ነገር ግን ከራሳቸው ከአዲሱ ፓትርያረትክም ዕውቅና ውጭ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ ውይይቱ የተጠናቀቀው ላለፈው ይቅር በመባባል፣ ለወደፊቱ ግን ችግሮቹን በጋራ ለማየት በመስማማት ነበር፡፡ እንዲያውም ሌሎች አባቶች አስቀሩት እንጂ ችግሩ እንደገና በሲኖዶስ ይታይ የሚል ሃሳብ ከአዲሱ ፓትርያርክም ተነሥቶ ነበር፡፡
  እናንተ ትክክለኛ መረጃ እያላችሁ ባለመስጠታችሁ ምእመናን የተሳሳተ መረጃ እንዲደርሳቸው አድርጋችኋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን አቡነ አብርሃምንና አቡነ ሳሙኤልን በተመለከተ ታስተላልፉት የነበረው አሉታዊ መረጃ ዛሬ ለደረስንበት አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ እናንተም ‹ባያዝድ› ስለሆናችሁ የሲኖዶሱን የመጨረሻ ስብሰባ ስትዘግቡ እንኳን የእነዚህን የሁለት አባቶች ብርታትና ቃል ለመግለጥ ተሥኗችኋል፡፡ አሁንም ትክክለኛውን መረጃ እንጂ የምትፈልጉትን መረጃ ብቻ አትስጡን፡፡
  ደባሱ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: