ተረፈ ምርጫ. . .

 • ‹‹ከቤተ ክርስቲን አፍራሾች ጋራ አልቆምም›› /ብፁዕ አቡነ ማትያስ/
 • አቡነ ማቴዎስ÷ አቡነ ሳሙኤልንና አቡነ አብርሃምን ከተመራጩ ፓትርያሪክ ጋራ እያግባቡ ነው
sss

ተመራጩ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ

በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ እንዲኾኑ ተመርጠዋል፡፡ በትላንቱ የቀጥታ ዘገባችን እንዳስነበብነው÷ በመራጮች፣ በታዛቢዎች፣ በጋዜጠኞች፣ በዕጩ ፓትርያሪኮች እና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፊት የተከናወነው ምርጫ መራጮችን ሥነ ሥርዐት ለማስያዝ በተወሰነ መልኩ ከታየው ማዋከብ በቀር ይህ ነው የሚባል ተጠቃሽ ችግር የታየበት አልነበረም፡፡ የድምፅ አሰጣጡ፤ የመዝገብ – የምርጫ ካርድ – የድምፅ መስጫ ወረቀቱን ማመሳከሩ፤ የቆጠራውና የውጤት ማሳወቁ ግልጽና ቀልጣፋ ነበር፡፡

የምርጫውን ሂደት ለትችት የዳረገውና በፍጻሜው/በውጤቱ/ ብቻ እንዳይለካ ያደረገው እንከን የታየው በቅድመ ምርጫው ወቅት ከአዳራሹ ውጭ የተፈጸሙ ተግባራት ናቸው፡፡ የምርጫው ተከታታዮች መንግሥትን ወይም በመንግሥት ስም የሚነግዱ ጥገኛ ኀይሎችን የሚኰንኑባቸው፣ አስመራጭ ኮሚቴውን የሚነቅፉባቸው እኒህ ተግባራት በሁለት ነጥቦች ተጠቃለው የሚታዩ ናቸው – በዕጩዎች ምርጫ እና በመራጮች ውሳኔ ላይ፡፡

የመጀመሪያው÷ የፓትርያሪክነት መመዘኛ መስፈርቱን የሚያሟሉ፣ በተቀራራቢ ብቃት ሊወዳደሩ የሚችሉ ሊቃነ ጳጳሳት በዕጩነት እንዳይካተቱ መደረጋቸው ምርጫው ከቀኑ አስቀድሞ ያከተመለት እንዲኾን፣ ብዙዎች ዕጩዎች ተመራጩን ያጀቡበት እንዲኾን አድርጎታል፡፡ ሁለተኛው÷ የመራጮችን የምርጫ ውሳኔ በሚያዛባ መልኩ በአካልና በተለያዩ መገናኛ መንገዶች ማጨናነቅ፣ ‹‹ከሰላም አባት፣ ከልማት አባት አቡነ እገሌ ውጭ ትመርጡና›› በሚል በመሐላ እስከማሰር የተደረሰበት ነበር፡፡

ምርጫው ተካሄደ ፡፡ ቆጠራው ተጠናቀቀ፡፡ በአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ አማካይነት ተወዳዳሪዎች ያገኙት ውጤት ሲገለጽ በመጀመሪያ ረድፍ የተቀመጡት ብፁዕ አቡነ ማትያስ ከ806 መራጮች 500 ማግኘታቸው ተነገረ፡፡ ብፁዕነታቸውን ለማስመረጥ ቀደም ሲል የተጠቀሱትን የቅድመ ምርጫ ተግባራት ሲመሩ የከረሙት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃን ጨምሮ በአዳራሹ የነበሩት መራጮች አጨበጨቡ፤ የምንኩስና ቆቡን ቢያደርጉም የዘለሉም ነበሩ፡፡ ጭብጨባውና ዝላዩ የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሚሰጡት ማሳሰቢያ እንኳ ሊያስቆመው አልቻለም ነበር፡፡

ከምርጫው ክንውን በኋላ ማምሻውን፣ በጽርሐ መንበረ ፓትርያሪኩ የሚገኘው የብፁዕ አቡነ ማትያስ ቤት ደስታቸውን በሚገልጹ የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ሌሎች እንግዶች ተጨናንቆ አምሽቷል፡፡ እንግዶቹን ሲቀበሉ ያመሹት ብፁዕነታቸው÷ መልካም ምኞታቸውን ለሚገልጹላቸው እንግዶች፣ ‹‹በዚህ ወቅትና በዚህ ሰዓት የዚህች ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ መኾን መስቀል ነው፤ መከራ ነው፤ ነገር ግን እናንተን ይዤ እሠራለኹ፤›› በማለት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

ከእንግዶቹ አንዳንዶችም ብፁዕነታቸውን ለማስመረጥ የድጋፍ እንቅስቃሴ አስተባብረዋል፤ በቀጣይም እንደ ቀድሞው ፓትርያሪክ÷ ‹‹በብፁዕነታቸው ዙሪያ ተሰልፈው የግልና የቡድን ጥቅማቸውን ለማራመድ ተዘጋጅተዋል፤›› ስለሚባሉት ግለሰቦች በማንሣት ሊያሳስቧቸው ሞክረዋል፡፡ የብፁዕነታቸው ምላሽ ‹‹ከቤተ ክርስቲያን አፍራሾች ጋራ አልቆምም›› የሚል ነው፡፡

ከምርጫው ራሳቸውን ስለማግለላቸው የተዘገበላቸው ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ከምርጫው የቀትር በኋላ ውሎ ላይ ተገኝተዋል፡፡ በቅ/ሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ የተናገሩትን ቃል ‹‹እኔ የለኹም፤ ብመረጥም አልቀጥልም›› በማለት እስከ ምርጫው ቀን ድረስ  ማጽናታቸው የተነገረላቸው ብፁዕነታቸው በአባቶች ምክርና ልመና የምርጫው ውጤት ከመገለጹ በፊት በአዳራሹ ተገኝተው ነበር፡፡ ለዕጩነት አልበቃም ያሉበት ትሕትናቸው በአርኣያነት የሚጠቀስ፣ ውጤቱ አስቀድሞ ከታወቀ ምርጫ ራሳቸውን ከእንቅስቃሴ ማቀባቸው በአርቆ አስተዋይነት (ብልህነት) እንዲታዩ አድርጓቸዋል፡፡

በምርጫው ለብፁዕ አቡነ ማትያስ በማድላት ታይቷል ያሉትን የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በመኰነን፣ ስለብፁዕ አቡነ ማትያስ ዜግነትና ሌሎች የግል መረጃዎች የጠየቋቸው ጥያቄዎች ምላሽ መድበስበስ እንዲሁም አስመራጭ ኮሚቴው በዕጩዎች አመራረጥ ለካህናትና ምእመናን ጥቆማ የሰጠውን ዋጋና የተጠቀማቸውን ሌሎች መመዘኛዎች በመንቀፍ፣ በምርጫው እንደማይሳተፉ የካቲት 16 ቀን በተደረገው የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ ያስታወቁት ብፁዕ አቡነ አብርሃም እና ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በምርጫው ቀን በድምፅ አሰጣጡ አልተሳተፉም፤ በምርጫው ስፍራም አልታዩም፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከመካሄዱ አንድ ቀን በፊት ሁለቱ ብፁዓን አባቶች ተቃውሟቸውን እንዲያረግቡና አቋማቸውን እንዲያለሰልሱ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን ጨምሮ አምስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ቤት ተገኝተው ያደረጉት ጥረት መቋጫ ሳያገኝ ነበር የተለያዩት፡፡ ምርጫው ከተከናወነ አንድ ቀን በኋላ ዛሬ እንደተሰማው ደግሞ÷ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በቤታቸው ብፁዕ አቡነ አብርሃምንና ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ከተመራጩ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ጋራ በማገናኘት በተፈጠረው ልዩነት ዙሪያ እያነጋገሯቸው መኾኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከምርጫው ባሻገር

ምርጫው በተከታተልነው መንገድ ተጠናቋል፡፡ የምርጫው ሂደትና ውጤት ያስከተላቸውን ያልተፈለጉ ኹኔታዎች የማከም ሥራ ይጠብቀናል፡፡ ከዚህ በላይና በፊት ደግሞ በምርጫው ሳቢያ ወደ ጎን የተውናቸው የቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ጉዳይ፤ በሐሳብና በንግግር እንጂ በተግባር የማይታወቀው የተቋማዊ ለውጥ አጀንዳ – የሕገ ቤተ ክርስቲያንና የቃለ ዐዋዲ ማሻሻያ ቀጣዩን ፓትርያሪክ የሚጠብቋቸው አንኳር የቤት ሥራዎች ናቸው፡፡ በቀጣይነት እንወያይባቸው፤ እንምከርባቸው!!

Advertisements

5 thoughts on “ተረፈ ምርጫ. . .

 1. Girum March 2, 2013 at 2:19 am Reply

  .”..የሕገ ቤተ ክርስቲያንና የቃለ ዐዋዲ ማሻሻያ ቀጣዩን ፓትርያሪክ የሚጠብቋቸው አንኳር የቤት ሥራዎች ናቸው፡፡”……አይ ተሃድሶ ስንት ጉዳይ ሞለቶ ሁሌም ስለ ማሻሻልና ተሀደሶ ነው ጭንቀታችሁ ! የተሀድሶ ነገር ዘይገረም ነው !

 2. Abera March 2, 2013 at 8:54 am Reply

  10q

 3. Mengistu March 2, 2013 at 10:16 am Reply

  ስንት ቋንቋ ይችላሉ ነው ያላችሁት? ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም ነው የሚባለው። ዘንድሮ ደግሞ ጉድ ሳይሰማ ጾመ ዓርባዕ አይያዝም ብንልስ? አምስት ነው ስምንት ያላችሁት? ጆሮዬ የሰማውን ማመን አቃተው። የአስተዳደር ችሎታው ጉዳይ እንዲያው ዝም ይሻላል። የቋንቋውን ግን ዝም አልልም። አዲሱ ፓትርያርክ እያቃሰቱ በስንት ጣር ጥቂት እንግሊዝኛ ይወረውራሉ። ከዚያ ውጪ ግን ዐረብኛ፤ጽርዕ እና እብራይስጥ ጆሮአቸውን ቢቆርጧቸውም እንደማይሰሙ አሳምሬ አውቃለሁ። መቼም መቀባባት የቤተ ክህነት ልምድ ስለሆነ ለማስመረጥ ማሳበቂያ ጥበብ መሆኑ ነው። አባ ጳውሎስም ሲሾሙ 7 ቋንቋ ይችላሉ የሚል ዲስኩር መሰማቱ ትዝ ይለኛል። እሳቸው ግን አንዱንም ቢሆን በደንብ ሰልቀው ይናገሩት ነበር። ከእነ ሳሙኤል መቼም ሳይሻሉ አይቀሩም። ቢያንስ ብዙ የጎደፈ ስም የላቸውም። በዚያ ላይ ጥሩ ጺምና የገጽ ቅብ አላቸው። ከዚያ ውጪ ግን እዚህ አሜሪካ በአንድ ቦታ ተቀብረው 28 ዓመት ሲኖሩ እንኳን ድኩትርና ቀርቶ ፕሮፌሰርና መድረስ በቻሉ ነበር። የሆኖ ሆኖ አህአዴግ ሾሟቸዋል። ጽናቱን ይስጣችሁ።

 4. ሃይማኖት ርትእት March 2, 2013 at 1:48 pm Reply

  ወየሐውሩ እም ትግረ ወትግረ

  ጳውሎስ…….ናትናኤል………ማትያስ……..ሌላው ሁሉ አጃቢ……….

 5. Anonymous March 11, 2013 at 5:18 pm Reply

  መንግስቱ ስልታናቸው ቢቀር አባቶች ናቸውና ክብር መስጠት እወቅ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: