የዕጩ ፓትርያሪኮችን የሕይወት ታሪክ የያዘ ኅትመት ታገደ

 • በአስመራጭ ኮሚቴው የተዘጋጀው የዕጩዎች ታሪክ ተቀናንሶ በመታተሙ ታገደ!
 • የአቡነ ማትያስ ታሪክ በሦስት ገጾች፣ የሌሎቹ በአንድ አንድ ገጽ እንዲጠቃለል ተደርጓል

የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ወደ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የላከው የዕጩ ፓትርያሪኮችን አጭር የሕይወት ታሪክ የያዘ ኅትመት (ቡክሌት) ተቀናንሶ በመታተሙ ምክንያት እንዳይሰራጭ ታገደ፡፡ ኅትመቱ ወደ ማተሚያ ቤቱ ከመላኩ በፊት የአምስቱንም ዕጩ ፓትርያሪኮች ልደት፣ ትምህርት፣ ክህነት (አገልግሎት) እና ሹመት ታሪክ በተመጣጠኑ ገጾች ይዞ እንደነበር የኮሚቴው ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

ይኹንና ኅትመቱ ዛሬ ጠዋት ከማተሚያ ቤቱ ወጥቶ ለጋዜጠኞችና ለሚመለከታቸው አካላት መሠራጨት ከጀመረ በኋላ ‹‹የዕጩዎቹ ታሪክ በተመጣጠኑ ገጾች አልተዘጋጀም›› በሚል ምክንያት ተመልሶ እንዲሰበሰብና ዳግመኛ ተስተካክሎ እንዲታተም መታዘዙ ተዘግቧል፡፡ አምልጦ የወጣው ኅትመቱ (ቡክሌቱ) በጠቅላላ ሰባት ገጾች አሉት፡፡

ከሰባቱ ገጾች የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ÷ ስድስተኛው ፓትርያሪክ እንደሚኾኑ ከምርጫው በፊት የሚነገርላቸውን የብፁዕ አቡነ ማትያስን ዕድገት (ትምህርት)፣ ክህነት(አገልግሎት)፣ ሹመት፣ ስደትና ሚጠት በተመለከተ በዝርዝር የያዙ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ አራት ገጾች ደግሞ የቀሪዎቹን አራት ዕጩዎች ታሪክ በአንድ አንድ ገጽ አጠቃሎ የያዘ ነው፡፡

ነገሩ ታስቦበት ይኹን በአጋጣሚ ለማረጋገጥ ባይቻልም የኅትመቱ ኹኔታ አንዳንድ የአስመራጭ ኮሚቴ አባላቱን ማሳዘኑ ተነግሯል፡፡ ውጤቱ አስቀድሞ ለታወቀ ምርጫ ይህ ኅትመት በምንም መልኩ ቢሠራ ከታሪክ ሰነድነቱ በቀር ፋይዳ እንደሌለው የተናገሩ የምርጫው ታዛቢዎች÷ አጋጣሚውን ብፁዕ አቡነ ማትያስን በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ ለማስመረጥ በመላው አህጉረ ስብከት የሚሯሯጡ ቡድኖች (ብፁዕነታቸው እንደማያውቋቸውና እንዳላገኟቸው ቢነገርም) ለሚፈጽሙት ደባ እንደማሳያ ያደርጉታል፡፡

በሌላ በኩል÷ መራጮች ስለ ሁሉም ዕጩዎች የትምህርት ዝግጅት፣ ችሎታና ልምድ ተጨባጭ ግንዛቤ ይዘው ድምፃቸውን ይበጃል ለሚሉት አባት እንዲሰጡ በማስቻል ረገድ መፈጸም የሚገባው ተግባር ቀድሞ እንዳልተፈጸመ ያሳያል፡፡ በምርጫ ሕገ ደንቡ አንቀጽ 6/2/ሸ መሠረት÷ የዕጩዎች የመጨረሻ ዝርዝር ከታወቀ በኋላ የትምህርት ደረጃቸው፣ ችሎታቸውና ልምዳቸው ለሕዝብ መገለጽ እንደሚገባው ያዝዛል፡፡

የምርጫው ዝግጅት በብዙ ተተችቶ ሲያበቃ አሁንም ‹‹ከምርጫው በጎ እናገኛለን›› በሚል ተስፋ ያላቸው ምእመናን ቁጥር የሚናቅ እንዳልኾነ በተለያዩ መንገዶች የሚሰሙ አስተያየቶች ያስረዳሉ፡፡ ከየአህጉረ ስብከቱ ወደ አዲስ አበባ ገብተው ‹‹ማንን እንምረጥ?›› እያሉ ወዳጆቻቸውን የሚያማክሩ መራጮች ቁጥርም ጥቂት ባልኾነበት ኹኔታ ውስጥ÷ ስለ ዕጩዎች የሚሰጠው መረጃ መመጣጠን እንደሚገባው ግልጽ ነው፤ ምርጫው ምርጫ ከተባለ. . .

ለማንኛውም በአስመራጭ ኮሚቴው ተስተካክሎ የሚዘጋጀው የዕጩ ፓትርያሪኮች ታሪክ ታትሞ እስክናነበው ድረስ እስኪ በሚከተለው አጭር ዝግጅት እንቆይ፡፡

ብፁዕ አቡነ ማትያስ

His Grace Abune Matyasበቀድሞው ስማቸው አባ ተክለ ማርያም ዐሥራት የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በ1934 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ቅዳሴ፣ ዜማ፣ ቅኔ፣ ባሕረ ሐሳብ፣ የመጻሕፍተ ሐዲሳት ትርጓሜ ተምረዋል፡፡ በ1948 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ዲቁናን ጮኸ ገዳም ተቀብለዋል፡፡ በ1955 ዓ.ም ከመ/ር ዐሥራተ ጽዮን ኰኲሐ ሃይማኖት ማዕርገ ምንኵስናን አግኝተዋል፡፡ በ1969 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ማዕርገ ቁምስናን ተቀብለዋል፡፡

በጮኸ ገዳም በቄሰ ገበዝነት፣ በመጋቢነትና በልዩ ልዩ ገዳማዊ ሥራ አገልግለዋል፡፡ በገዳሙ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ ሐዲስ ኪዳንን አስተምረዋል፡፡ ከ1964 – 68 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቅዳሴና በልዩ ልዩ አገልግሎቶች ተመድበው አገልግለዋል፡፡ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ዓመታት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አቡነ ቀሲስና ምክትል ልዩ ጸሐፊ በመኾን ሠርተዋል፡፡ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ኤጲስ ቆጶስ ኾነው ተሹመዋል፡፡

ከ1974 ዓ.ም ጀምሮ በስደት ወደ አሜሪካ ሄደው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ በ1984 ዓ.ም ወደ አገር ተጠርተው የአሜሪካ ሊቀ ጳጳስ በመኾን ተመድበዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በቀድሞው ሀ/ስብከታቸው በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ኾነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡

ማስታወሻ፡- በአሁኑ ወቅት የካናዳ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመኾን እያገለገሉ ያሉት ብፁዕ አቡነ ማትያስ የተሾሙት ሐምሌ 17 ቀን 1975 ዓ.ም ነው፡፡ ይኸውም አሁን ለዕጩ ፓትርያሪክነት ይኹንታ ያገኙትና ቀጣዩ ፓትርያሪክ እንደሚኾኑ የሚጠበቁት የኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ የቀድሞውን ሥርዐተ መንግሥት በመቃወም ሀ/ስብከታቸውን ትተው በስደት ወደ አሜሪካ ከገቡ (በገዳሙ አስተዳደር በማኅበረ መነኰሳቱ መካከል ተነሥቶ የቆየውን ጎጥን መነሻ ያደረገ አለመግባባት ቅ/ሲኖዶሱ በወቅቱ ሊፈታው ባለመቻሉ በተባባሰ ችግር መነሾነት እንደኾነ ይነገራል) በኋላ በሦስተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በተላለፈው ውሳኔ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በ1984 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የቅዱስ ሲኖዶስ አባልነታቸውን በመቀጠላቸው ውግዘቱ እንደተነሣ ያህል ተደርጎ በአንዳንዶች ዘንድ ቢቆጠርም በይፋ የተላለፈው ውግዘት በይፋ ስለመነሣቱ አልተረጋገጠም፡፡

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ

His Grace Abune Elsaበፊት ስማቸው አባ ኅሩይ ወልደ ሰንበት (ፈንቴ?)፣ የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በ1930 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ጸዋትወ ዜማ፣ ቅኔ፣ ትርጓሜ መጻሕፍት፣ ፍትሐ ነገሥት፣ ባሕረ ሐሳብ እና ሐዲስ ኪዳንን ተምረዋል፡፡ በ1945 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ዲቁና፣ በ1964 ዓ.ም ምንኵስናን በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተቀብለዋል፡፡ በ1965 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ቅስና፣ በ1969 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ሰላማ ቁምስናን ተቀብለዋል፡፡ በደብረ ጽጌ ገዳም በመዘምርነትና በቅዳሴ አገልግለዋል፡፡ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ የከፋ ሀገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶስ ተብለው ተሹመዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ

His Grace Abune Yosephነሐሴ 16 ቀን 1944 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ክፍለ ሀገር በሸኖ አውራጃ ልዩ ስሙ ጨቴ ጊዮርጊስ በተባለው ቦታ ተወለዱ፡፡ የቀድሞ ስማቸው ቆሞስ አባ ኀይለ ጊዮርጊስ ኀይለ ሚካኤል ይባላል፡፡ ፊደል የቆጠሩት ዜማን የተማሩት ቅኔን የተቀኙት በሀፋፍ ማርያም በኢቲሳ ደብረ ጽላልሽ ገዳም ነው፡፡ ቅዳሴን በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ የቀሳውስት ማሠልጠኛ ት/ቤት ተምረዋል፡፡ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ት/ቤት ለአራት ዓመታት ተምረው በዲፕሎማ ተመርቀው ዘመናዊ ትምህርታቸውን እስከ 12 ክፍል በማጠናቀቅ በምዕራብ ጀርመን እሸት ኬርከሌ መንፈሳዊ ት/ቤት ስለ ገዳማት አስተዳዳር አጥንተዋል፡፡

ሐምሌ 5 ቀን 1991 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ተብለው ተሹመዋል፡፡ በአሁኑ ሰአት የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልHIs Grace Abune Hizkel

የቀድሞ ስማቸው መልአከ ምሕረት አባ ሀብተ ማርያም መኰንን ይባላል፡፡ ግንቦት 7 ቀን 1946 ዓ.ም በደቡብ ወሎ አማራ ሳይንት ልዩ ስሙ ደብረ ብርሃን ለንጓጥ ሥላሴ ተወለዱ፡፡ አባታቸው ግራ ጌታ መኮንን ኀይሉ እናታቸው ወ/ሮ አታላይ ደርሰህ ይባላል፡፡ ዜማ፣ አቋቋም፣ ቅኔ፣ ፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ ተምረዋል፡፡ የቅኔ መንገድ ከነአገባቡ ተምረው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡ በ1956 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል ዲቁና ተቀብለዋል፡፡ ጳጉሜን 3 ቀን 1981 ዓ.ም በደብረ ሊባኖስ ገዳም ሥርዓተ ምንኵስና ፈጽመዋል፡፡ ኅዳር 12 ቀን 1982 ዓ.ም የቅስና ማዕርግ ከብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፤ ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ መዓርገ ቁምስና ተቀብለዋል፡፡

ከ1982 – 87 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ በጽርሐ ጽዮን ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ መምህር ኾነው አገልግለዋል፡፡ ከሰኔ 20 ቀን 1987 – 1990 ዓ.ም በምሥራቅ ሐረርጌ ሐደሬ ጤቆ መካነ ሥላሴ ደብር፣ ከየካቲት 1990-93 ዓ.ም የድሬዳዋ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ከሠኔ 1 ቀን 1993 ዓ.ም – ሐምሌ 1 ቀን 1994 ዓ.ም ጀምሮ ለጵጵስና መአርግ እስከ በቁበት ዘመን በአዲስ አበባ ቦሌ ደብረ ምጽላል እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አገልግለዋል፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን 1994 ዓ.ም የሰሜን ወሎ ደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም አስተዳዳሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ነሐሴ 22 ቀን 1997 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የከፋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ተብለው ተሹመዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የደቡብና ምዕራብ አዲስ አበባ፣ የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ ናቸው፡፡

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስHis Grace Abune Mathewos

በ1955 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ልዩ ስሙ ምንታምር ቀበሌ ከአቶ ጌታነህ የኋላ ሸትና ከወ/ሮ አምሳለ ወርቅ ማሞ ተወለዱ፡፡ አቋቋም፣ ቅኔ ከነአገባቡ፣ ቅዳሴ፣ ኪዳን አንድምታ፣ ዜማ፣ ሠለስት፣ አርያም፣ ጾመ ድጓ፣ ቁም ዜማ ተምረዋል፡፡ በ1969 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ዲቁና ተቀብለው፣ ቅስና ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ተቀብለዋል፡፡ በ1975 ዓ.ም በደብረ ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ሥርዓተ ምንኵስና ፈጽመዋል፡፡ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ለአራት ዓመታት ያህል ተምረው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በሆላንድ ሆህ ስኵል የቴዎሎጂ ትምህርት ቤት ገብተው ለአራት ዓመታት ተምረው በቴዎሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡

በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በሰበካ ጉባኤ አደራጅነት፣ በሰንበት ት/ቤት ሓላፊነት፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሽሮ ሜዳ መንበረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በሰባኪነት፣ በሐረር ደብረ ገነት መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአቃቂ መድኃኔ ዓለም በአስተዳዳሪነት፣ በቃሊቲ ቅዱስ ገብርኤል፣ በሳሎ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ደብር እና በሐረር ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም አብያተ ክርስቲያናት በአስሪተዳዳሪነት አገልግለዋል፡፡ በውጭ ሀገር በአሜሪካ ዳላስ ቅዱስ ሚካኤል፣ በአውሮፓ ስዊዘርላንድ በጀኔቭ፣ በሎዛን፣ በዙሪክና በበርንባዝል ከተሞች ባሉ አድባራት በቀዳሽነትና በሰባኪነት አገልግለዋል፡፡

ነሐሌ 22 ቀን 1997 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የዋግህምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ተሾመዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የወላይታ ዳውሮ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡

Advertisements

9 thoughts on “የዕጩ ፓትርያሪኮችን የሕይወት ታሪክ የያዘ ኅትመት ታገደ

 1. Anonymous February 26, 2013 at 1:26 pm Reply

  Harazetewahido
  yemtsetugn merejawoch tekamiwoch nachewna gefubet.
  Egziabeher yemihonewn yaderg!

 2. ዘይገርም February 26, 2013 at 4:08 pm Reply

  ይሄ ሁሉ ሽር ጉዱ ማንን ለመምረጥ ነው?

 3. Anonymous February 26, 2013 at 5:40 pm Reply

  Mine enantes ye Abune Yoseph ena ye Abune Elsa’e. Trail asaterachihut?

 4. abacoda February 26, 2013 at 8:58 pm Reply

  ጊዜ የሰጠው ቅል ደንጋይ ይሰብራል
  በአቡነ ቄርሎስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የሚመሩና ተቀማጭነታው በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አብያተክርስቲያነት የሆኑት እንደካህናት የሚቀድሱ እንደፈቁራ ሞጅሊስ የሚለብሱ አስተዳዳሪዎችና ተራ ክህናት ፕትርክና በብቃት ሳይሆን በተራ እንደቦኖ ውሃ ወይም እንደማርያም ጸበል በይድረሰኝ ፕትርክናን እኛ እንዋሰው ሲሉ ለመውሰድ መሰለፋቸው ምን ይባላል እኛስ መቸ ይሆን የሸሪአ ኃላፊነት የምናገኘው በውኑ ፓትርክና ይቅርና ሊቀዲቁናስ ለወለየዎች ይገባል; በዚህ ከፍተኛ ኃላፊነት ተቀምጠው ቀርቶ በዋና ስራ አስኪጅነት ዘመናቸው አራቱም የአዲስ አበባ አሁጉረ ስበከቶች በወሎ ተወላጆች ብቻ እንዲሞሉ ማድረጋቸው በአባ ሕዝቅኤል የሚመራው የአባ ፊልጶስ የስልጣን ዘመን ጉልህና እና እየታየ ያለ ግልጽ ዘረኝነት አስተዳደር ምን ላይ ለማድረስ ነው;
  /ስለሆነም የሚገባቸው የክርስቲያን ደሴት ተወላጆች የሆኑት እነ አቡነ ማቴዎስ ዘደብረ ጽላልሽ የመሳሰሉት ቢመረጡ በወጣት ጉልበታቸው የውሻ ገደልን ጠማማ መንገድ ቢያስተካክሉበት እነ ብጸዕ አቡነ ኤልሳዕ የመሳሰሉ ቢመረጡና የአብነት መምህራን ጸሐይ ቢወጣላቸው ከበይ ተመልካችነትም ቢድኑ ወይም አረጋውያን ሊቃነ ጳጳሳቱ እነ ብፁዕ አቡነ ማትያስና አቡነ ዮሴፍ ቢመረጡ በጸሎት ሀገር ከፈጣሪዋ ቢያገናኙበት ይሻላላ ግን ደግሞ ፕትርክና ካልተሰጠን ወደ ቀድሞ ሐይማኖታችን እንመለስ የሚሉም ካሉ ፕትርክናው እነሱን አምኖ መስጠት ችግር ሊያመጣ ስለሚችል ለግሩፕ ቢሰጥ ….

  • Anonymous February 27, 2013 at 8:58 am Reply

   abacoda yemibal beshita neber. Tawqewaleh? Sewinet eyasabete yemigedil!!!

 5. Chiqunu February 27, 2013 at 5:30 am Reply

  Abune Matias seems to be the best.

 6. Anonymous February 27, 2013 at 12:49 pm Reply

  ሰዎችን መተቸት ይቻላል. ነገር ግን ከሰዎች ተነስቶ ስለ አንድ አካባቢ ድምዳሜ መሥጠት ግን አስተዋይነት የጎደለዉ
  የደደብነትና የጨለምተኝነት አስተሳሰብ ነዉ

 7. abacoda February 27, 2013 at 8:41 pm Reply

  tomorrow is a unique date because tomorrow will decide the church for Christ follower or Muslim group those lead bay aba cherlos and aba hizkale If god hate us will transfer the cherch too welo tribe who are the sons of goodit if love us for aba matewos deaz is great than see wolo patriyarch

 8. ጊታ April 3, 2013 at 2:53 pm Reply

  እ/ር በሰዎች አድሮ የወደደውን ይምረጥ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: